Tuesday, February 16, 2016

ነገረ ማርያም፡- ክፍል ፳፬፤


የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድንግልና፡-በሦስት ወገን ነው። በሥጋዋ፥ በነፍሷ እና በልቡናዋ ድንግል ናት፤ ይህ ድንግልና፡- የዘለዓለም ድንግልና ነው። ይህም በምሳሌ ኦሪት፥ በነቢያት ትንቢት የተረጋገጠ ነው። ከአዳም ብቻ በቀር ከድንግል መሬት የተፈጠረ የለም፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሰው ሆነ፤ይላል። ዘፍ፡፪፥፯። ከአንድ ከሔዋን ብቻ በቀር ከአዳም ጎን የተፈጠረ የለም፤ እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት፤ይላል። ዘፍ፡፪፥፳፩

አበ ብዙኃን አብርሃም፡- ከአንድ በግ ብቻ በቀር ከዕፀ ጳጦስ አላገኘም። አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ፥ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፈንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው፤ይላል። ዘፍ፡፳፪፥፲፫። አብርሃም የእግዚአብሔር አብ፥ ዕፀ ሳቤቅ የድንግል ማርያም፥ በግ የኢየሱስ ክርስቶስ፥ ይስሐቅ ደግሞ የአዳም ምሳሌዎች ናቸው። አብርሃም፡- ከዕፀ ሳቤቅ የተገኘውን አንድ ብቻ በግ በይስሐቅ ፈንታ እንደሠዋው፥ እግዚአብሔር አብም፡- ከድንግል ማርያም የተወለደውን፥ ለእርሱም ለእናቱም አንድ ብቻ የሆነውን፥ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን፥ ስለ አዳም ልጆች ፈንታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶታል። እግዚአብሔር አንድ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወድዶአልና። . . . ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም፤ይላል። ዮሐ፡፫፥፲፯፣ ፩ኛ፡ዮሐ፡፬፥፲።በዚህ ምሳሌ መሠረት፡- ከድንግል መሬት አንድ አዳም ብቻ እንደተፈጠረ፥ ከአዳም  ጎንም አንዲት ሔዋን ብቻ እንደተፈጠረች፥ ከዕፀ ጳጦስ ደግሞ አንድ በግ ብቻ እንደተገኘ፥ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም የተወለደው አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። -ከቅዱሳን ነቢያት፥ ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ፡- “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወልድንም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤ብሎአል። ኢሳ፡፯፥፲፬።ነቢዩ ሕዝቅኤልም፡- እግዚአብሔር የነገረውን ቃል በቃል በትንቢት መጽሐፉ ላይ አስቀምጦአል።ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም፡-ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፤ብሎአል። ሕዝ፡፵፬፥፩። የተዘጋ የመቅደስ በር የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፤የሚለው በድንግልና ጸንታ መኖሯን የሚያመለክት ነው።ሰው አይገባበትም፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፤የሚለው ኃይለ ቃል ደግሞ የሚያመለክተው፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ፀንሳ፥ በድንግልና የወለደችው ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ በመሆኑ፥ ከርሷ ሰው አይወለድም፥ በድንግልና እንደጸናች ትኖራለች፥ ማለት ነው። በመሆኑም፡- ቅድመ ፀኒስ፥ ጊዜ ፀኒስ፥ ድኅረ ፀኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፥ጊዜ ወሊድ፥ድኅረ ወሊድ ኅትምት በድንግልና ናት።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- ለእግዚአብሔር የተሰጠች የብፅዓት ልጅ ስለሆነች፥ እንደ እናቶቿ፡- በዘር በሩካቤ መፅነስ፥ በሰው እጅ መዳሰስ የለባትም። አንድም ለአብ ምሳሌው በመሆኗ ከሥግው ቃል ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለዕሩቅ ብእሲ እናት መሆን፥ በባህርይዋ ሁለተኛ መውለድ አትችልም። እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድን፡-ቅድመ ዓለም ያለ እናት ለመውለዱ፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- ምሳሌም ምስክርም ለመሆን የበቃችው ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነውን ወልድን(አካላዊ ቃልን) ያለ አባት በመውለዷ ነው። ወልድ ለአብ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ ልጅ እን ደሆነ ሁሉ፥ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ ልጅ ነው። በጳጳስ ወንበር ቄስ፥በንጉሥ ዙፋን ራስ ደፍሮ እንደማይቀመጥ ሁሉ፡- በአምላክ ዙፋን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ማን ያድራል? ሠዓሌ ሕፃናት(የሕፃናት ፈጣሪ) በተሣለበት ሰሌዳ፥ በተቀረፀበት ሰፋድል፥ ማን ይሣላል? ማን ይቀረፃል? ይህ እንኳን ሊደረግ ፈጽሞ የማይታሰብ መሆኑን ነው፥ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለሕዝቅኤል አስቀድሞ የነገረው። በመሆኑም ዐውደ ማኅፀንዋ ለመለኰት ማደሪያነት ብቻ በትንቢት አጥር መታጠሩን በሃይማኖት ማስተዋል ይገባል። ጠቢቡ ሰሎሞንም፡-“እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ፥ የታተመ ፈሳሽ ናት፤ብሎአል። መኃ፡፬፥፲፪። መቼም እንደተቆለፈ የኖረ የአትክልት ሥፍራ፥ ተዘግቶ የሚመነጭ፥ ታትሞም የሚፈስ ውኃ የለም። እንደተቆለፈች አምላክ ብቻ አድሮባት የወጣባት ገነት፥ እንደተዘጋች የዘለዓለምን ሕይወት ክርስቶስን ያመነጨች፥ እንደታተመች የሕይወትን ውኃ ክርስቶስን በአራቱም ማዕዝን አፍስሳ የተጠሙ ነፍሳትን ያረካች፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። ጠቢቡ ሰሎሞን፡-“ የተቈለፈ፥ የተዘጋ፥የታተመ፤በማለት ምሥጢሩ አንድ በሆነ በሦስት ኃይለ ቃል በምሳሌ የተናገረው የዘለዓለም ድንግልናዋን ነው።

5 comments:

  1. Kale hywet yasemaln

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማይ ያውርስልን፡፡

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመኖትን ይባርክ፡፡ እንደናንተ አይነቶችን የቤተክርስቲያን አባቶችን ከቤተመቅደሱ አያሳጣን፡፡ ያብዛችሁ፡፡

    ReplyDelete