Tuesday, February 2, 2016

ነገረ ማርያም፡- ክፍል ፳፫፤ብሥራተ ቅዱስ ገብርኤል፤

ብሥራት፡- በቁሙ ሲተረጐም የምሥራች፥ አዲስ ነገር፥ ደስ የሚያሰኝ ወሬ፥ ስብከት፥ ትንቢት፥ ወንጌል ማለት ነው። አብሣሪው፡- “ደስ ይበልህ፥ ደስ ይበልሽ፥ ደስ ይበላችሁ፤” እያለ የተላከበትን እና የመጣበትን የሚናገርበት ነው። ደስ የሚያሰኝ ዜና የተነገረውም አካል፡- “ይሁንልኝ፥ ይደረግልኝ፤” እያለ ብሥራቱን በሃይማኖት ይቀበለዋል። ጥርጥር ከገባው ግን፥ ነገሩ ከእግዚአብሔር በመሆኑ ተግሣጽ ይወድቅበታል። “አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻል።” ጻድቁ ካህን ዘካርያስ፡- የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፡- መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን እንደሚወልድ ባበሠረው ጊዜ፥” እኔ ሽማግሌ ነኝ፥ ምስቴም አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” በማለቱ፥ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤” ብሎታል። ሕፃኑ እስከሚወለድም ድረስ ዲዳ ሆኖአል። ሉቃ፡፩፥፲፰።                                                    
     
ቅዱስ ገብርኤል፡- ጥንት በዓለመ መላእክት በሳጥናኤል ምክንያት የተነሣውን ማዕበል ጸጥ ያደረገ መልአክ ነው። ሳጥናኤል፡- ሲፈጠር የመላእክት አለቃ ሆኖ ነው፥ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ከፈጠረ በኋላ፥ “በሰጠኋቸው አእምሮ ተመራምረው ይወቁኝ፤” ብሎ ተሰወረባቸው። እነርሱም፡- “ከየት መጣን? ማን ፈጠረን?” ማለት ጀመሩ። ይኽንን የሰማ ሳጥናኤል፡- ከበላዩ ማንም አለመኖሩን አይቶ፥ “እኔ ፈጠርኳችሁ፤” በማለቱ ሁከት ሆነ። በዚህን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፡- “ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአማላክነ፥ የፈጠረንን አምላክ እስከምናገኘው ድረስ በየህልውናችን ጸንተን እንቁም፤” በሚል ዐዋጅ አረጋግቶአቸዋል። እግዚአብሔርም በብርሃን ጐርፍ ተገልጦላቸዋል። ቅዱስ ገብርኤል፡- አምላክ ሰው የሚሆን በትን ምሥጢር እንዲያበሥር የተመረጠው በዚህ ምክንያት ነው። በመጀመሪያ ለቅዱሳን መላእክት የተገለጠበት ምሥጢር፥ በኋላ በተዋህዶ ሰው ሁኖ ለሰው ለሚገለጥበት ምሥጢር ምሳሌ ነውና።                                                                                            

“ስድስተኛው ወር፤”

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን የተላከው በስድስተኛው ወር ነው፥ ይላል። ሉቃ፡፩፥፳፮። “ስድ ስተኛ ወር፤” የሚለው የሚተረጐመው በሁለት ወገን ነው። የመጀመሪያው ትርጉም በስድስተኛው ሺህ ዘመን ማለት ነው። ይህም አዳም ከተፈረደበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ዘመን ቆጥሮ ነው። አዳም በበደሉ ምክንያት በተፈረደበት ፍርድ ከማልቀስ በቀር ሌላ ኅሊና አልነበረውም። እግዚአብሔርም፡- መጸጸቱን አይቶ “አምስት ቀን ተኵል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ) ሲፈጸም፥ ከሰማየ ሰማያት ወርጄ፥ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።” የሚል ተስፋ ሰጥቶታል። በእግዚአብሔር ዘንድ ሺው ዘመን እንደ አንድ ቀን ወይም እንደ አንድ ወር እንደሚቆጠር በቅዱሳት መጽሕፍት ተገልጧል። ነቢዩ ዳዊት፡- “ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና፤” ያለው ለዚህ ነው። መዝ፡፹፱፥፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ! በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ፤” ብሎአል። ፪ኛ፡ጴጥ፡፫፥፰። በመሆኑም፡- “በስድስተኛው ወር፤” ሲል አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተፈጽሞ ስድስተኛው ሺህ ሲጀመር ማለት ነው። ሁለተኛው ትርጉም ደግሞ፡- መጥምቀ መለኰት በተፀነሰ በስድስተኛው ወር ማለት ነው።                                                                                                                                                   

ናዝሬት ዘገሊላ፤

ገሊላ፡- በሰሜን የምትገኝ ከሦስቱ የእስራኤል ክፍለ ሀገሮች አንዷ ናት፤ በምሥራቅ፡- ከዮርዳኖስና ከገሊላ ባሕር፥ በሰሜን፡- ከሶርያ፥ በምዕራብ፡- ከፊንቄ ሀገር፥ በስተ ደቡብ፡- ከሰማርያ ጋር ትዋሰናለች። ከእስራኤል ምርኮ በኋላ አሕዛብ ወደ ዚህች ሀገር በመግባታቸው የአሕዛብ ገሊላ ተብላለች። ፪ኛ፡ነገ፡፲፭፥፳፱፤ ፲፯፥፳፬፣ ማቴ፡፬፥፲፬። አሕዛብ ስለ ገቡባትም በገሊላ የሚኖሩ አይሁድ ቋንቋቸውና ሃይማኖታቸው ትንሽ ለየት ያለ ሆነ፥ በዚህ ምክንያት ሌሎቹ አይሁድ ይንቋቸው ነበር። ማቴ፡ ፳፮፥፶፯፣ ዮሐ፡፩፥፵፯፤ ፯፥፶፪።        
                                                                                              
ናዝሬት፡- በገሊላ ውስጥ የምትገኝ በተራራ ላይ የተመሠረተች ከተማ ናት፤ ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ ፳፭ ኪ.ሜ. ርቃ ትገኛለች። እስራኤል ርስት በተካፈሉበት ወቅት የነገደ ዛብሎን ድርሻ ነበረች። እመቤታችን፡- ከጠባቂዋና ከዘመዷ  ከጻድቁ ከዮሴፍ ጋር በዚያ ትኖር ነበር። ቅዱስ ሉቃስ በገሊላ ውስጥ የምትገኘውን ናዝሬትን የጠቀሰው ለዚህ ነው። የናዝሬት ከተማ ወደ ጠረፍ የተጠጋች በመሆኗ በአይሁድ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣት ከተማ አልነበረችም።እግዚአብሔር ሁል ጊዜ የሚፈልገው ከሰውም ከቦታም የተናቀውን ነው። የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐና፡- እግዚአብሔር መናቋን አይቶ የልቧን መሻት በፈጸመላት ጊዜ፡- “አትታበዩ በኵራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ፤” ያለችው ለዚህ ነው። ፩ኛ፡ሳሙ፡፪፥፫።                                                                     

ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ፤

“በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤” ይላል። (የእጮኛን ትርጉም፡- ነገረ ማርያም ክፍል ፲፪ን ተመልከት፤) ቅዱስ ገብርኤል ወደ ድንግል ማርያም የመጣው፥ ስሟን ጠርቶ በፊቷ የተንበረከከው፥ በፍጹም ትህ ትና አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ያበሠረው፥ ከእግዚአብሔር ተልኮ ነው። እግዚአብሔር ያልላ ከው፥ ወደ እመቤታችን አይመጣም፤ ስሟንም ጠርቶ አያመሰግናትም። ወላዲተ ቃል፥ ወላዲተ አምላክ፥ እመ እግዚአብሔር ጸባዖት አይላትም። ስለዚህ ወደ እመቤታችን የመጣን፥ በቅዳሴ፣ በማኅሌትና በመዝሙር ስሟን የምንጠራ፥ ውዳሴዋን የምንደግም ሁሉ የእግዚአብሔር መልክተኞች እንደሆንን እናምናለን።    


2 comments: