Friday, January 8, 2016

ነገረ ማርያም፡- ክፍል ፳

  በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን፥ ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን 
                      ለአንተ እፈጽማለሁ፤መዝ፡፷፭፥፲፬                                 
       በአምላክ ኅሊና ተቀርፃ የኖረች ጽላት፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- የብጽዓት ልጅ ናት። ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፡- ወንድ ልጅ ብንወልድ፡- ወጥቶ ወርዶ፥ አርሶ ቆፍሮ ይርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር እንሰጠዋለን። ሴት ልጅም ብንወልድ፡- እንጨት ሰብራ ውኃ ቀድታ፥ ፈጭታ ጋግራ ታገልግለን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር እንሰጣታለን። ብለው ተስለው ነበር። በመሆኑም፡- ገና በሦስት ዓመቷ ለቤተ እግዚአብሔር ሊሰጧት ተስማሙ። ይህም፡- ሕልቃና እና ሐና፥ ነቢዩ ሳሙኤልን፡- ለቤተ እግዚአብሔር ለመስጠት እንደተስማሙት  አይነት ነው። ሐና ሕልቃናን፡- ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘለዓለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ። እንደ አለችው፥ ቅድስት ሐናም ቅዱስ ኢያቄምን፡- ይህች ብላቴና ሆዷ ዘመድ ሳይወድ፥ አፏ እህል ሳይለምድ ወስደን አንሰጥምን? «የሰጠ ቢነሳ የለበትም አበሳ፤» እንደሚባለው፥ አንድ ነገር ብትሆንብን ከልጃችንም ከእግዚአብሔርም ሳንሆን እንቀራለን፤ ብለዋለች። በኦሪቱ ዘመን ሕልቃና ለሐና፡- በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና፤እንደ አላት፥ ቅዱስ ኢያቄምም ቅድስት ሐናን፡- ፍቅርሽ ያልቅልሽ እንደሆነ ብዬ ነው እንጂ፥ እኔማ ፈቃደኛ ነኝ፤ ብሎአታል። ምክንያቱም ከፍቅሯ ጽናት የተነሣ አንድም ቀን ከእቅፏ አውጥታት፥ ከጭኗ አውርዳት አታው ቅም። እንዲህም ማድረግዋ፡- አንድ ቀን ለብቻዋ ትታት ከደጅ ወጥታ ስትመለስ፥ መልአከ እግዚአብሔር ሰውሮባት በመከራ አግኝታት ስለነበረ ነው፤ ሁሌም እንደዚያ እየመሰላት ከላይዋ አታወርዳትም ነበር።   
                           
የነቢዩ የሳሙኤል እናት በእግዚአብሔር ቤት ቆማ፡- ስለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፤ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ ዕድሜውን  ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል፤ ብላ ለሊቀ ካህናቱ ለዔሊ እንደ አስረከበችው፥ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐናም ወደ ቤተ መቅደስ ሄደው እመቤታችንን ለሊቀ ካህናቱ ለዘካርያስ አስረክበዋታል። በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን፥ ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን ለአንተ እፈጽማለሁ፤ ማለት እንዲህ ነው። ባያደርጉት ዕዳ እንደሚሆንባቸው ያውቃሉ። ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኃጢአትም ይሆን ብሃልና መክፈሉን አታዘግይ። . . . ሰው በችኰላ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ (የተለየ) ነው ብሎ ቢሳል፥ ከተሳለም በኋላ ቢጸጸት ወጥመድ ነው። . . . ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘ ግይ፤ የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል፤ ይላል። ዘዳ፡፳፫፥፳፩፣ ምሳ፡፳፥፳፭፣ መክ፡፭፥፬።  
ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ለእናትዋ አንዲት ናት፥ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት።መኃ፡ ፮፥፱፤ እንዲል፡- ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፡- በሐዘንና በዕንባ፥ በጾምና በጸሎት ያገኟትን አንድ ልጃቸውን፥ ለሰጣቸው ለእግዚአብሔር መልሰው ለመስጠት መወሰናቸው፥ ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል መጠበቃቸው፥ የሚደነቅ ሃይማኖት ነው። በመሆኑም ሃይማኖታቸውን ማድነቅ ይገባል፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ጽኑዕ የሆነ ሃይማኖትን እንድናደንቅ የሰጠን አብነት አለ። ይኸውም፡- የቅፍርናሆሙን መቶ አለቃ ሃይማኖት በማድነቁ ታውቆአል፤ ለተከተሉት ሕዝብ፡- እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው፤ ይላል። ሉቃ፡፯፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- የአቤልን፥ የሄኖክን፥ የኖኅን፥ የአብርሃምን እና የሣራን፥ የይስ ሐቅን፥ የያዕቆብን፥ የሙሴን እና የወላጆቹን፥ ሃይማኖት አድንቆአል። ገድላቸውንም የሃይማኖት እና የምግባር ማስተማሪያ መጽሐፍ አድርጐአል። ዕብ፡፲፩፥፩-፳፰።                                                                                              
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፡- ሕፃኗን ማርያምን ይዘው ከቤተ እግዚአብሔር ሲደርሱ፥ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ፡- ሕዝቡን ሰብስቦ እያስተማረ ነበር። እነርሱምእነሆ ስእለት ተቀበሉን፤ አሉአቸው። እንቀበላለን፤ብለው ቢቀርቡ፥ ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርታ፥ ከመብረቅ ሰባት እጅ አስፈርታ፥ የምታበራ ዕንቈ ባሕርይ መስላ ታየቻቸው። እንዲህ አይነቱ ድንቅ ተአምራት፥ እግዚአብሔር ለመረጣቸው እንደሚደረግ መጽሐፍ ቅዱስ ቋሚ ምስክር ነው። ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቍርበት አንጸባረቀ፤ (እንደ ፀሐይ አበራ) . . . ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። . . . ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ።. . .  እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።. . . በሸንጎም የተቀመጡት ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ አዩት። ይላል፤ ዘጸ፡፴፬፥፳፱፣ ዳን፡፲፪፥፫፣ ማቴ፡፲፫፥፵፫፣ የሐዋ፡፮፥፯፤፲፭። የመልአክ ፊቱ ምን እንደሚመስል መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን፡- አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል (እንደ ብርሃን ያብለጨ ልጭ) ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና (መብራት) ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ። . . .  የጌታ መልአክ ከሰ ማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤ ብሎናል። ዳን፡፲፥፮፣ ማቴ፡፳፰፥፪።                                                                                              
ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ እና ካህናቱ፡- የተሰጣትን ጸጋ አይተው፥ ይህችን የመሰለች ልጅ ተቀብለን ምን እናደርጋታለን? ምን እናበላታለን? ምን እናጠጣታለን? ምን እናለብሳታለን? ምን እናነጥፍላታለን? ምን እንጋርድላታለን?” በማለት እንደ ሰው ተጨነቁ። በዚህ መካከል ሕፃኗ ማርያም ረኀብ ተሰምቷት አለቀሰች። በዚህን ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል፡- ሰማያዊ እንጀራን በመሶበ ወርቅ፥ ሰማያዊ መጠጥን ደግሞ በብርሃን ጽዋ ይዞ፥ ወደ ታች ሳይወርድ ረቦ ታያቸው። ሕዝቡም ለአባታቸው ለካህኑ ለዘካርያስ የመጣ ጸጋ በረከት መስሎአቸው፡- እጅ ነስተህ፥ ሰግደህ ተቀበል፤ ብለውት፥ እጅ ነስቼ ሰግጄ እቀበላለሁ ብሎ ቢቀርብ፡- ወደ ሰማይ ራቀው። ከሕዝቡም እያንዳንዳቸው እጅ ነስተን፥ ሰግደን እንቀበላለን ብለው ቢቀርቡ፡- እነርሱንም ወደ ሰማይ ራቃቸው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ዘካርያስ ሐናን ጠርቶ፡- ለእናንተ ለእንግዶቹ የወረደ ጸጋ በረከት ሊሆን ስለሚችል ሕፃኒቱን ይዘሽ ወደዚያ ፈቀቅ ብለሽ ተቀመጪ፤ አላት። ቅድስት ሐናም ካህኑ እንደ ነገራት ብታደርግ፥ ቀረብ ብሎ ከራሳቸው ላይ ረቦ አልወርድም አለ። ሁለተኛም ዘካርያስ ሐናን ጠርቶ፡- አምላከ እስራኤል የሚያደርገው ነገር ስለማይታወቅ (ስለማይመረመር) ሕፃኒቱን እዚያው ትተሽ አንቺ ወዲህ ነዪ፤ አላት። ቅድስት ሐና ገና ዘወር ከማለቷ፥ ቅዱስ ፋኑኤል ወርዶ፥ አንደኛውን ክንፉን አንጥፎላት፥ ሁለተኛውን ክንፉን ደግሞ ጋርዶላት እመቤታችንን መገቦአታል፥ ሰግዶላታልም። በእግዚአብሔር የታዘዙ ቅዱሳን መላእክት፡- የእግዚአብሔርን ቅዱሳን እንዲህ እንደሚመግቡ በመጽሐፍ ቅዱስ የታወቀ ነው። እመቤታችን ደግሞ ቅድስት ቅዱሳን በመሆኗ ከእነዚህ ሁሉ ትበልጣለች። ነቢዩ ኤልያስ ከኤልዛቤል ፊት ሸሽቶ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና፡- ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ (ከአብርሃም ከሙሴ) አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ። በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋ ደመ፥ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም መልአክ ዳሰሰውና፡-ተነሥተህ ብላ አለው።ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጐቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ።በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ። የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፡- የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነ ሥተህ ብላ አለው። ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ፤ ይላል። ፩ኛ፡ነገ፡፲፱፥፩-፰።    
                                                                                                   ካህናቱና ሕዝቡም፡- የምግቧ ነገር በቅዱሳን መላእክት እጅ ከተያዘማ ከተርታው ሰው ጋር ምን ያጋፋታል፤ ብለው፥ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አስገብተው፥ መኖሪያዋን በቤተ መቅደስ አደረጉላት። ይኸውም ነቢዩ ሳሙኤል ገና በሦስት ዓመቱ ለቤተ መቅደስ ተሰጥቶ በዚያ እንደኖረው ማለት ነው። ፩ኛ፡ሳሙ፡፩፥፳፪-፳፱። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሕንፃው ብቻ አይደለም፥ የሰው ሰውነቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው። የእግዚአ ብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?. . . ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። ይላል። ፩ኛ፡ቆሮ፡፫፥፲፮፤፮፥፲፱። ከዚህ የምንማረው ትልቅ ትምህርት አለ፤ ይኸውም፡- ሰውነታችን በእውነት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከሆነ፥ እመቤታችን በልባችን ውስጥ እንድትኖር፡- የተሰጠችን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሆነች እናምናለን። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆኖ ካልተገኘ ደግሞ ፈጽሞ በውስጣችን ልትኖር አትችልም።                                                           እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ታኅሣሥ ሦስት ቀን ነው። በዚህም፡- አባቷ ቅዱስ ዳዊት ተናግሮት የነበረው ቃለ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶአል። ከእናት ከአባቷ ቤት ወጥታ፥ ለቤተ መቅደስ ተሰጥታ፥ በዚያው እንደምትኖር አስቀድሞ ስለ ተገለጠለት፡- ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ፥ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽንም የአባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ (ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔር) ውበትሽን (የአዳም ኃጢአት ያልወደቀበትን ንጽሕናሽን) ወድዶአልና፤ ብሎአል። መዝ፡፵፬፥፲። ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፡- ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች በተቀመመ ምስጋናቸው፡- አንቲ ውእቱ ንጽሕተ ንጹሐን፥ ዘነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ ከመ ታቦት፥ ወመላእክት ያመጽኡ ወትረ ሲሳየኪ፥ ስቴኪኒ ስቴ ሕይወት ውእቱ፥ ወመብልዕኪኒ ኅብስት ሰማያዊ። እንደ ታቦተ እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖ ርሽ አንቺ፥ ከንጹሐን ይልቅ ንጽሕት ነሽ፤ ቅዱሳን መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡልሽ ነበር፥ ትጠጪው የነበረውም መጠጥ የሕይወት መጠጥ ነው፥ መብልሽም በሰው እጅ ያልተሠራ ሰማያዊ እንጀራ ነው፤ ብለዋታል።

2 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን፡፡ እናንተን እግዚአብሔር አምላክ ይጠብቅልን፡፡ የተዋህዶ ፍሬዎች የአባቶቻችን ሊቃውንት በረከታቸው አይለያችሁ፡፡ በርቱ፤

    ReplyDelete
  2. betana yitebkiln , kalehiywit yasemaln

    ReplyDelete