Monday, January 25, 2016

ነገረ ማርያም፡-ክፍል ፳፪

           የተጠማ ውሻ፤


ውሻ፡- ለበጎም ለክፉም ምሳሌ ይሆናል።በጎ ምሳሌነቱ፡- ለጌታው ታማኝ መሆኑ ነው፥ አስተማማኝ የቤት ጠባቂ ነው። ዘጸ፡፲፩፥፯፣ ኢሳ፡፶፮፥፲። እንደሚታወቀው የሚኖረው በቤት ውስጥ ከሰው ጋር ነው። ከነዓናዊቱ ሴት፡- “የልጆችን እንጀራ ይዞ ለውሾች (የሴምን በረከት ለከነዓን) መስጠት አይገባም፤” በተባለች ጊዜ፡- “አዎን ጌታ ሆይ፥ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤ (የጻድቅ በረከት ለኃጥእ ይተርፋል፤ እንዲል፡- የሴም ልጆች በረከት፥ እርግማን ለወደቀባቸው ለከነዓን ልጆችም ተርፎ ጾም አያድሩም)፤” ያለችው ለዚህ ነው። ማቴ: ፲፭፥፳፮። ምክንያቱም፡- ውሻ ከጌታው ጋር በቤት እንደሚኖር፥ ጻድቁ ኖኅ የረገመው ከነዓንም እንደ ልጅ ሳይሆን፥ ለወንድሞቹ የባሪያ ባሪያ ሆኖ በቤት እንዲኖር ተፈቅዶለታልና ነው። ዘፍ፡፱፥፳፰። ይልቁንም አሁን ባለንበት ዘመናዊ ዓለም፡- ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከታተል፥ ከቴክኖሎጂው ይልቅ ውሻ አስተማማኝ ረዳት ሆኖ ተገኝቶአል። በክፉ ምሳሌነቱ ደግሞ፡- እንደ ርኵስ ስለ ተቆጠረ በቅድስናው ስፍራ እንዲቆም አልተፈቀደለትም። በዚህም ለመናፍቃን እና ለአሕዛብ ምሳሌ ሆኖአል። “በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ የተቀደሰ ውን ለውሾች አትስጡ፤” ይላል። ማቴ፡፯፥፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- “ከውሾች ተጠበቁ፤” ብሎአል። ፊል፡፫፥፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ፡- ፈጥነው የሚክዱትን ሰዎች በውሾች መስሎ፡- “በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፡- የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለ ሳለች እንደሚል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋለ።”በማለት ተናግሮአል።፪ኛ፡ጴጥ፡፪፥፳።ባለ ራእዩ ቅዱስ ዮሐንስም፡- ወደ መንግሥተ ሰማያት የማይገቡትን ሰዎች በአምስት ውሾች መስሎአቸዋል።“ አምስቱ ውሾች ግን ከዚያች አገር ወጥተው ይሄዳሉ። እሊህም ሥራይን የሚያደርጉ፥ ሴሰኞች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖትን የሚያመልኩና የሐሰትን  ሥራ የሚወዱ ሁሉ ናቸው፤” ይላል። ራእ፡፳፪፥፲፭። እንግዲህ ጌታችን በወንጌል፡- የእባብን መርዙን ትተን ልባምነቱን እንድንማር በነገረን መሠረት ከውሻም ታማኝነቱን ወስደን በነገር ሁሉ ታማሽ ልንሆን ይገባል። ማቴ፡፲፥፲፮። እመቤታችን ጽዮን ድንግል ማርያም፡- ጸወነ ሥጋ ጸወነ ነፍስ (የሥጋም የነፍስም መጠጊያ) በመሆኗ ለሁሉም ትራራላቸዋለች።   እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡-በቤተ መቅደስ ስትኖር፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተመለከተች፥ ቤተ መቅደስንም እያገለገለች እንደ ነበረ ባለፈው ተመልክተናል። በአጭር ታጥቃ፥ ማድጋ ነጥቃ፥ ተራዋን ጠብቃ የጉድጓድ ውኃ ትቀዳ ነበር። ብዙ ሴቶችም ውኃ ለመቅዳት ወደዚያ ይመጡ ነበር። እነዚያ ሴቶች በየተራቸው ውኃ በሚቀዱበት ጊዜ ውኃ ጥም የጠናበት አንድ ውሻ እየተቅበዘበዘ ወደ እነርሱ መጣ። እነርሱም ለተጠማው ውሻ ከሰው የሚጠበቅ ርኅራኄ ሳያደርጉለት ያባርሩታል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ውሻው፡-በጽኑ ውኃ ጥም ተይዞ ከወዲያ ወዲህ፥ ከወዲህ ወዲያ ሲመላለስ ባየች ጊዜ፡- ስለ መጠማቱ አዘነችለት። እጅግ ማዘኗን ያዩ እነዚያ ሴቶች፡- “አንቺ ለውሻው ትራሪለታለሽን? ምናልባት ክርስቶስ የሚባለው መሲሕ የሚወለደው ካንቺ ይሆንን?” ብለው ተሣለቁባት። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም፡-ይኸንን ነገራቸውን በሰማች ጊዜ በልብዋ ታደ ንቅ ነበር።የእግዚአብሔር ታማኝ የምሥጢር መዝገብ እንደሆነች መጽሐፍ ቅዱስም ይመሰክራል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ፡- “እናቱም (በመንፈስ ቅዱስ ግብር በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችው እናቱ ድንግል ማርያም) ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር፤”ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ፡፪፥፶፩።                                                      

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- ማድጋዋን አንሥታ ከሚሣለቁባት ሴቶች ራቅ ካለች በኋላ፥ በወርቅ ጫማዋ የተጠማውን ውሻ በፍጹም ርኅራኄ ውኃ አጠጣችው። ከሴቶቹም መክከል አንዷ፡- “ሳይቸግርሽ ማድጋሽን አጕድለሽ በምን ልትሞዪው ነው? የጉድጓድ ውኃ መቅጃው ተቋርጧል፤”አለቻት።እመቤታችን ግን፡-“ውኃ የሚገኘው ከላይ ከሰማይ (ከእግዚአብሔር) እንጂ ከታች ከጕድጓድ አይደለም፥ ይህንን የተጠማ ውሻ ያጠጣ አምላክ ለእኔም ይሰጠኛል፤” ስትል በትህትና መለሰችላት። ይኽንን የእምነት ቃል ተናግራ ስትጨርስ ማድጋዋ በውኃ ተሞላ፤ከቤተ መቅደስ ስትደርስ ደግሞ፡- ብሥራተ ቅዱስ ገብርኤልን ሰምታ፡- “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ፤” ባለች ጊዜ፥ የሕይወት ውኃ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅፀኗ አደረ። መንፈስ ቅዱስ የሴቶቹን ሳቅና ስላቅ ለውጦ እውነተኛ ትንቢት አደረገው፤ አንድም አፋቸውን ከፍቶ፥ ፊታቸውን ጸፍቶ እውነት አናገራቸው። እመቤታችን እንደተናገረችው በረከት ሁሉ ከላይ ከሰማይ ነው።“ረዳቴ፥ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ነው፤” ይላል። መዝ፡፻፳፥፪።
                
ርኅራኄ፡- ምሕረትን እና ቸርነትን ማድረግ ነው፥ በተቻለ መጠንም ለተቸገረ ማዘንና መርዳት ነው። ርኅራኄ ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤” ይላል። መዝ፡፻፪፥፲፫። ነቢዩ ኢሳይያስም፡- “መድኃኒትም ሆነላቸው። በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም  መልአክ አዳና ቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው።” ብሎአል። ኢሳ፡፷፫፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ደግሞ፡- የኢዮብን ትዕግሥትና የእግዚአብሔርን ቸርነት ከተናገረ በኋላ “ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና፤” ብሎአል። ያዕ፡፭፥፲፩። በትንቢተ ዮናስ ላይ፥ እግዚአብሔርን፡- “እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉበት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” ሲል እናገኘዋለን። ዮና፡፬፥፲፩። እመቤታችንም ማዘንዋና መራራቷ ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም ጭምር ነው። ይኽንን በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ደራሲ፡- “ሴስይኒ ማርያም ለጸማድኪ ዐሳብ፥ ኅብስተ አእምሮ ሰናይ ወወ ይነ ጥበብ፥ እመኒ ፈድፈደ ኃጢአትየ እምሕዝብ፥ ተዘከሪ እግዝእትየ በርኅራኄኪ ዕፁብ፥ ከመ አስተይኪዮ ማየ ለጽ ሙዕ ከልብ፤ ማርያም ሆይ! ምንደኛ አገልጋይሽን፥ መልካም እውቀት ኅብስትንና ጥበብ ወይንም መግቢኝ፤ ኃጢአቴ ከሕዝብ ኃጢአት ቢበዛም፥ እመቤቴ ሆይ! በአስደናቂ ርኅራኄሽ፥ ለተጠማው ውሻ ውኃ ማጠጣትሽን አስቢ፤” ብሏል። መንፈሳዊው ደራሲ፡- በጸሎቱ የገለጠው፥ የራሱን የኃጢአት ብዛትና የእመቤታችንን አስደናቂ ርኅራኄ ነው። ምንም  ኃጢአቱ የበዛ ቢሆን፥ ለውሻው እንኳ ርኅራኄ ያደረገች ድንግል ለርሱም የምሕረት ጥላዋን እንድትጥልበት ነው፤ ከፈጣሪውም ጋር የሚታረቅበትን መንገድ እንድታሳየው ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን፡-እንዲህ አይነቱን ርኅራኄ፡- “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤” በማለት ገልጦታል። ምሳ፡፲፪፥፲። ክርስቲያኖችም፡- አባታችንን እግዚአብሔርን እና እናታችንን ድንግል ማርያምን አብነት አድርገን ርኅሩኃን ልንሆን ይገባል። ኢሳ፡፩፥፲፯፣ ማቴ፡፲፰፥፳፫፣ ኤፌ፡፬፥፴፪፣ ፩ኛ፡ጴጥ፡፫፥፰፣፩ኛ፡ዮሐ፡፫፥፲፯።  

1 comment:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!! እግዚአብሔር አምላክ የአገልግሎት ዘመንዎትን ይባርክልን፡፡ እንደናንተ አይነት አባቶችን ያብዛልን፡፡

    ReplyDelete