Friday, January 15, 2016

ነገረ ማርያም፡- ክፍል-፳፩
       እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡-ገና በሦስት ዓመቷ ለእግዚአብሔር ተስጥታ፥ ያደገችው በቤተ መቅደስ ውስጥ ነው። ቅዱሳን መላእክት እየመገቧት፥እየዘመሩለት እና እየሰገዱላት ዓሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ኖራለች።ቅዱስ አባ ሕርያቆስ፡- በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፥ መንፈስ ቅዱስ ቢገልጥለት፥ አስተዳደጓ እንዴት እንደነበረ ከሌሎቹ እያነጻጸረ ተናግሮአል። “ድንግል ሆይ! አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ (አታሞ እየመቱ፥ እስክስታ እየወረዱ እንደሚያድጉ) እንደ ዕብራውያን ልጆች በቧልት (በቀልድ፥በፌዝ) በጨዋታ ያደግሽ አይደለም፤ በቅድስና፥ በንጽሕና በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ እንጂ። ድንግል ሆይ! ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለሽም፥ ከሰማይ የተገኘ (በጥበብ አምላካዊ የተሠራ) ኅብስትን ተመገብሽ እንጂ።ድንግል ሆይ! ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለሽም፥ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ (ከሰማይ የተገኘ) ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤” በማለት አድንቆአል። ይኸውም ወደ ቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት፥ ቅዱስ ፋኑኤል ሲመግባት በገሀድ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ እሰከ መጨረሻው የዘለቀ ነው።                                                                                                                 

የቅዱሳት መጽሐፍትን ትርጓሜ የሚያውቅ፥ ምሥጢራቸውንም የሚያራቅቅ ቅዱስ ያሬድም፡- በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ፡- “ከንጹሓን ሁሉ ይልቅ ንጽሕት የሆንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ እንጨት እንደ ተሠራ በወርቅ እንደ ተጌጠ፥ ዋጋውም እጅግ ውድ በሆነ በሚያበራ ዕንቍ እንደ ተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ፥ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ። እንዲህ ሆነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር ምግብሽን ያመጡልሽ ነበር፤ ቅዱሳን መላእክት እንዲህ እየጐበኙሽ ዓሥራ ሁለት ዓመት ኖርሽ፤ መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፥ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር። አባትሽ ዳዊት በመሰንቆ አመሰገነ፤ በትንቢት መንፈስም፥ በመንፈስ ቅዱስም በገና እየደረደረ እንዲህ ብሎ ዘመረ። ልጄ ሆይ! ስሚ፥ እዪም፥ ጆሮሽንም አዘንብዪ፥ ሕዝብሽንና የአባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና፥ ስገጂ፥ ትሰግጂማለሽ፤” በማለት አመስግኖአታል። በማኅፀኗ ላለ፥ ጌታዋ ለሆነ፥ ለማኅፀኗ ፍሬ መስገዷ፥ ከመነገር በላይ ነው፥ ዕፁብ ድንቅ ነው። በቤተ መቅደስ የኖረች ታቦተ እግዚአብሔር በውስጥም በውጪም በንጹሕ ወርቅ እንደ ተለበጠች፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም፡- በውስጥ በነፍሷ፥ በውጭ ደግሞ በሥጋዋ ንጽሕት ናት። ወርቅ የንጽሕናዋ ምሳሌ ነው። እግዚአብሔር ታቦቷን በረድኤት እንደ ተገለጠባት፥ እመቤታችንንም፡- በተለየ አካሉ ከሰማይ በመውረድ፥ በማኅፀን ከእርሷ የነሳውን ሥጋና ነፍስ ተዋህዶ ሰው ኹኖ በመወለድ ተገልጦባታል።                                                                                        
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሰማይ የሆነ ኅብስትን የተመገበች ብቻ አይደለችም፤ ሰማይ ሆና ሰማያዊ ኅብስትን ለዓለሙ የመገበች ናት። ምክንያቱም፡- የማኅፀኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደ፥ ከዳግሚት ሰማይ ከእርሷም የተወለደ ኅብስት ነው። “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” ይላል። ይህን፡- መለኰቱን አዋህዶ የሕይወት እንጀራ አድርጐ የሰጠንን ሥጋውን የነሳው ከእመቤታችን ነው። ዮሐ፡፮፥፶፩። በመጽሐፈ ዚቅ ላይ፡- “ናሁ ተግህደ ልዕልናሃ ለወለተ ሐና፤ ኅብስተ ሕይወት ተፀውረ በማኅፀና፤ ጽዋዓ መድኃኒት ዘአልቦ ነውር ወኢሙስና። የሐና ልጅ የድንግል ማርያም፡- ክብሯ፥ ልዕልናዋ እነሆ ተገለጠ፤ ጥፋትና ነውር የሌለበት፡- መድኃኒት የሆነ መጠጥ እና የሕይወት እንጀራ በማኅፀኗ አድሮአልና።” የሚል አለ። ዳግመኛም፡- “ንጽሕተ ንጹሐን ከዊና ከመ ታቦት ዘዶር ዘሲና፥ ውስተ ቤተ መቅደስ ነበረት በቅድስና፤ ሲሳያ ኅብስተ መና ወስቴሃ ስቴ ጽሙና፤ የመለኰት እሳት እንደ ሆነች የሲና ታቦት፡- ንጽሕተ ንጹሐን ሆና፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ ነበረች፤ ምግቧ የሰማይ እንጀራ፥ መጠጧም የእርጋታ መጠጥ ነበር፤” በማለት ነገረ ማርያምን ያደንቃል። በኦሪቱ፡- እስራኤል ዘሥጋ፡- መና ከሰማይ እየወረደላቸው ተመግበው ነበር፥ዳሩ ግን ከመቅሰፍት ሞት አላዳናቸውም። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፥ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።” ያለው ለዚህ ነው። ዘጸ፡ ፲፮፥፲፬፣ ዮሐ፡፮፥፵፱።                                                                                               
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- በቤተ መቅደስ ስትኖር፥ ቅዱሳን መላእክት ያረጋጉአት እንደነበር፥ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ ተናግሮላታል።“ድንግል ሆይ! ተድላ ዓለም፣ ብዕለ ዓለም የሸፈጣቸው፥ አጋንንት በውዳሴ ከንቱ የሚያታልሏቸው (ፈቃደ ሥጋ ያታለላቸው) ወራዙት(ወጣቶች) ያረጋጉሽ አይደለሽም፤ የሰማይ መላእክት ጐበኙሽ እንጂ፤ በነገረ ማርያም እንደ ተነገረ፡- ካህናት፥ ሊቃነ ካህናት ጎበኙሽ እንጂ፤” ብሎአል። እመቤታችን፡- ከቤተ መቅደስ ሳለች፥ አይሁድ “እንጣላታለን፤” ብለው፡ -ጦር ሠርተው ቢሄዱ፥ አጥሩ፣ ቅጥሩ እሳት ሆኖ መልሶአቸዋል። ይህንንም፡- እንደ ተአምራት ሳይሆን እንደ ምትሐት ቆጠሩት። በዚህን ጊዜ፡- “ምትሐትን በምትሐት ነው፤” ብለው፥ “መጥቁል” የተባለ ጠንቋይ ፈልገው አገኙ። ተጨንቀው የመጡበትን ጉዳይም ካስረዱት በኋላ፡- “እርሷን የምታጠፋልን ከሆነ ወርቅና ብር፥ በግና ላም በብዛት እንሰጥሃለን፤” ብለው ቃል ገቡለት። ለጊዜውም እንደ እጅ መንሻ ብዙ ወርቅና ብር ሰጡት። እርሱም፡- “የዛሬን እደሩና ነገ የምትፈልጉትን ሁሉ አደርግላችኋቸሁ፤” አላቸው። በማግሥቱም የሰጡትን ወርቅና ብር ቢመለከት ወደ ድንጋይነት ተለውጦ አገኘው፤ እንስሳቱንም ሞተው አገኛቸው። በልቡም፡- “አይሁድ እንደ ነገሩኝ፥ ለካስ፡- የማትቻል ምትሐተኛ ናት፤” አለ።                                                                                                                           
የተደረገውን ተአምር እንደ ምትሐት የቆጠረው መጥቁል በሆነው ነገር እጅግ ተበሳጨ። ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑ የአየር ላይ አጋንንትም ወደ እርሱ መጥተው፡- “ምነው አዝነሃል? ሰማይን እንኳ ጠቅልሉት ብትለን እንጠቀልለዋለን፤” አሉት። በዚህን ጊዜ እንደ አስለመዳቸው ሰው ቢያርድላቸው፡- ሥጋውን በልተው፥ ደሙን ጠጥተው፥ እመቤታችንን ሊያጠፉለት ቃል ገቡለት። ይህ ሁሉ ሲሆን፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- “ስድክኤል” የሚባል የእግዚአብሔር ኅቡዕ (ስውር) ስሙ ተገልጦላት እየጸለየች ነበር፤ ቅዱሳን መላእክትም የእሳት አጥር ሆነው ይጠብቋት ነበር። በመጥቁል መሪነት የሄዱ ሰዎችም አጋንንትም ከቤተ መቅደሱ ሳይደርሱ በአንድነት ጠፍተዋል፥ መሬትም አፏን ከፍታ ውጣቸዋለች። በዚህን ጊዜ ከአዳም ጀምሮ እስከ እርሷ ድረስ ያሉ አበው፡- “በአማን ስብሕት፥ በአማን ውድስት አንቲ፤ በእውነት አንቺ የተመሰገንሽ ነሽ፤” እያሉ አመስግነዋታል።    
  
ጥንቈላ ከጥንት ጀምሮ እንደ ነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ይታወቃል። እግዚአብሔር ባልፈቀደው መንገድ (በሰይጣን መንገድ) መንፈሳዊ ኃይልን መፈለግ ጠንቋይነት ነው። ጠንቋዮች የእግዚአብሔርን ሥራ ለመገዳደር የሞከሩበት ጊዜ ነበረ። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር የላከው ሙሴ፥ እግዚአብሔር እንደ አሳየው፥ የእግዚአብሔር በትር የተባለች በትሩን፡- በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊት እባብ ቢያደርግ፥ የግብፅ ጠንቋዮችም በትራቸውን እባብ አድርገው ነበር። ነገር ግን፡- እባብ የሆነች የሙሴ በትር ሁሉንም እባቦች ውጣቸዋለች። ይህም የሚያሳየን፥ የእግዚአብሔር ሥራ፡- የሰይጣንን ሥራ እንዴት እንዳጠፋው ነው። ዘጸ፡፯፥፰፣ ኢሳ፡፲፱፥፫። የአሕዛብ ነገሥታት ጠንቋዮችን በአማካሪነት በቤተ መንግሥት ያስቀምጧቸው ነበር። ዳን፡፪፥፪። እስራኤላውያንም በዚህ መንፈስ እየተመሩ በማስቸገራቸው፡- በጠንቋዮች መንገድ እንዳይሄዱ ተከልክለው፥ጠንቋዮችንም እንዲያጠፉ ታዝዘው ነበር።ዘጸ፡፳፪፥፲፰፣ዘሌ፡፳፥፳፯። በሐዋርያት ዘመን ሲሞን የተባለ ጠንቋይ ሕዝቡን በምትሐቱ ያስቸግራቸው ነበር፥ እንዲያውም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በቅዱሳን ሐዋርያት እጅ ሲሰጥ ባየ ጊዜ በገንዘብ ለመግዛት ፈልጐ ነበር። ቅዱስ ጴጥሮስ ግን፡- “የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና፥ ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።” አለው። ሲሞንም ይህን በሰማ ጊዜ፡- በአንደበቱ፡- “ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ፤” እያለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እያዩት በምትሐት ወደ ሰማይ ለማረግ ሞከረ። በዚህን ጊዜ፡- ቅዱስ ጴጥሮስ ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢያማትብበት ከሰማይ ወድቆ ተሰባብሮ ሞቶአል። የሐዋ፡፰፥፲፱-፳፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- በርያሱስ የተባለ ጠንቋይ፥ ሀገረ ገዢውን ከማመን እያጣመመ ስለ አስቸገረው፡- “አንተ ተንኰል ሁሉ፣ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ(ወንጌልን) ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ፥ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም።” በማለት ገሥጾታል። “ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ፤” ይላል። የሐዋ፡፲፫፥፯-፲፪። እየጠነቈለች ለጌቶቿ ብዙ ትርፍ ታመጣላቸው የነበረችውን፥ የሟርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት፥ መንፈሱን በመገሠጽ ከእርሷ እንዲወጣ አድሮጐአል። የሐዋ፡ ፲፮፥፲፮።                                                                                                             

          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- በቤተ መቅደስ የኖረችው፥ ስራ ፈት ሆና አይደለም፤ በአጭር ታጥቃ፣ ማድጋ ነጥቃ ውኃ እየቀዳች፥ ሐርና ወርቅ አስማማታ እየፈተለች፥ መጋረጃ እየሠራች፥ የተቀደደውንም እየሰፋች ነው። በመጽሐፈ ዚቅ ላይ፡- “ገብርኤል መልአክ መጽአ፥ ወዜነዋ ጥዩቀ፤ በዕንቈ ባሕርይ እንዘ ትፈትል ወርቀ፤ በዕንቈ ባሕርይ ወርቅ ስትፈትል መልአኩ ገብርኤል መጣ፥ አስረግጦ (የተረጋገጠ ነገር) አበሠራት፤” ይላል። ከዚህም ጋር የኦሪትን እና የነቢያትን መጻሕፍት ትመረምር ነበር። ከዕለታትም አንድ ቀን፥ የታላቁን ነቢይ የኢሳይያስን የትንቢት መጽሐፍ ስታነብ፡- “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወልድንም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤” ከሚለው አንቀጽ ደረሰች። በዚህን ጊዜ፡- “እግዚአብሔር ዕድሜ ከጤና ሰጥቶኝ፥ አምላክን በድንግልና ፀንሳ፣ በድንግልና ከምትወልደው እመቤት ቢያደርሰኝ፥ ገረድ ኹኜ አገለግላት ነበር፤” በማለት ተመኝታ ነበር።

3 comments:

 1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማይ ያውርስልን ጸጋውን ያብዛልን፡፡

  ReplyDelete
 2. Abatachin Yageleglot Zemenewon Yarzimilin KALE HIYWOT YSEMALIN

  ReplyDelete
  Replies
  1. The Truth Ethiopian OTC Faith. St Mary Bless U. Tewahdo lezelalem Timur!!!!

   Delete