Friday, December 11, 2015

ተሀድሶ                            ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ቅዱሳን፡-        
                                              
“ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፥የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፤”

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ሞትን ድል ነስቶ፥ ሙስና መቃብርንም አጥፍቶ ከተነሣ በኋላ፥ የሄደው ወደ ደቀመዛሙርቱ ነው። እነርሱ አይሁድን ፈርተው፥ (በእርሱ ላይ ይህን ያህል የጨከኑ እኛንም አይምሩንም ብለው)፥ የቤቱን ደጆች እና መስኰቶች ዘጋግተው ተቀምጠው ነበር። ጌታችንም በሩ ሳይከፈት ገብቶ በመካከላቸው ቆመና፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” አላቸው። ይኸውም፡- ሰውና እግዚአብሔር፥ ሰውና መላእክት፥ ነፍስና ሥጋም ታርቀው ሰላም ወረደ ሲላቸው ነው። ሰላም የወረደውም፡- ስለ እኛ ብሎ በመስቀል ላይ በቆሰለው ቍስል ስለሆነ፥ በችንካር የቆሰሉትን እጆቹንና በጦር የተወጋውን ጐኑን አሳያቸው። አንድም ምትሐት ያዩ መስሎአቸው ደንግጠው ነበርና፥ ለምትሐት ሥጋና አጥንት የለውም ሲል ተዳሰሰላቸው። እነርሱም፡- እርሱ መሆኑን ስለ አረጋገጡ እጅግ ደስ አላቸው። ጌታም ፍርሃትን አርቆ ደስ ካሰኛቸው በኋላ፥ ዳግመኛ፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ ”አላቸው። ከዚህም አያይዞ፡- “አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ፤ (አብ የባህርይ ልጁን እኔን፡- መከራ ተቀበል፣ ተሰቀል፣ ሙት ብሎ እንደላከኝ፥ እኔም፡- እናንተን የጸጋ ልጆቼን፥ መከራ ወደሚያጸናባችሁና ወደሚገድላችሁ ዓለም እልካችኋለሁ፤) ብሎ በንፍሐት (እፍ በማለት) ጸጋ መንፈስ ቅዱስን አሳድሮባቸዋል። (ማዕረገ ቅስናን ሰጥቶአቸዋል)። በሰጣቸው በዚህ ሥልጣን ምን እንደሚሠሩ ሲነግራቸው ደግሞ፡- “ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፥ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፤” ብሎአቸዋል። ዮሐ፡፳፥፲፱ -፳፫። ከዚህ በፊት፡- “እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” ብሎ ንባቡን ብቻ ነግሮአቸው ነበር። ከትንሣኤው በኋላ ደግሞ የሚያስሩትና የሚፈቱት ኃጢአትን እንደሆነ ትርጓሜውን ነግሯቸዋል። በመሆኑም ኃጢአትን ይቅር የሚሉበትና የሚይዙበት ይህ ሥልጣን፡- በምድር በተከታዮቻቸው ላይ የሚያድር፥ ከእነርሱም ጋር እስከ አጸደ ነፍስ ድረስ ተከትሎአቸው የሚሄድ ጸጋ ነው።

                                
በብሉይ ኪዳን ዘመን አሮን እና ማርያም ወንድማቸውን ሙሴን በማማታቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶባቸው ነበር። ይኽንን የተመለከተ አሮን ወደ ልቡናው ተመልሶ ሙሴን፡- “ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ ኃጢአት አታድርግብን።” ሲል እናገኛለን። ዘኁ፡፲ ፪፥፲፩። እንዲህ ያሰኘው እኅቱን በለምጽ የቀጣ፥ እርሱንም የተቆጣ እግዚአብሔር ነው። ምክንያቱም፡- እግዚአብሔር በመረጣቸው፣ በወደዳቸውና ባከበራቸው ቅዱሳን ላይ ማጉረምረም፥ የእግዚአብሔርን ቍጣ ማነሣሣት ነው። ታላቅ ስንፍና፥ በደል እና ኃጢአትም ነው። የእግዚአብሔር ደስታው፡- እርሱ የወደዳቸውን ስንወድለት፥ ያከበራቸውንም ስናከብርለት ነው። የሚገርመው ነገር፥ እነዚህ የኦርቶዶክስን መለያ ለብሰው፥ በኦርቶዶክስ ሜዳ ላይ ለፕሮቴስታንት የሚጫወቱ ተሀድሶዎች፥ ቅዱሳንን እያስጠሉ እነርሱ ግን ከመወደድም አልፈው መመለክ ይፈልጋሉ።                                                           
የቅዱሳን ክብር በምድር ባሉ ምእመናን ዘንድ ብቻ ሳይሆን፥ በሰማይም፡- በእግዚአብሔር እና በቅዱሳን መላእክትም ዘንድ ነው። “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤” ይላል። ማቴ፡፲፥፴፪። ታዲያ እነዚህ በኢየሱስ ስም የሚነግዱ ተሀድሶዎች (አዲስ ጴንጤዎች)፥ በምድር ላይ፡- “የቅዱሳን ገድላቸው ለምን ተነገረ?” ብለው ይኽንን ያህል ከታገሉ፥ ወደ ሰማይም ወጥተው ኢየሱስን፡- “ለምን ትመሰክርላቸዋለህ፤” ሊሉት ይሆን? ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ሙሴ በአጸደ ሥጋ በነበረበት፥ በብሉይ ኪዳን ዘመን፡- “ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ለምን አላፈራችሁም?” ብሎ እንደመሰከረለት፥ ሙሴ በአጸደ ሥጋ ባልነበረበት በአዲስ ኪዳን ዘመንም፡- “እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤የሚከሳችሁ አለ፥ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው።” በማለት መስክሮለታል። እንግዲህ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ቅዱሳን በአጸደ ነፍስ ሆነው፥ ተስጥቶአቸው በነበረ ጸጋ ከቀድሞው በበለጠ ሥራ እንደሚሠሩ እንዲህ እየመሰከረላቸው፥ “የቅዱሳንን ስም አታንሡ፤” ማለት የጤና አይደለም። ባለፈው በሰፊው እንደተመለከትነው፥ ነገረ ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያሳይ የጠራ መስተዋት እንጂ መሸፈኛ መጋረጃ አይደለም። ቅዱሳንን በመጀመሪያ የወደደ እግዚአብሔር ነው፥ ከእግዚአብሔር የሆኑ ሁሉ እርሱን ተከትለው ቅዱሳንን ይወዳሉ። ቅዱሳንን በመጀመሪያ የጠላ፥ መናፍቃንን እና አሕዛብን አስነሥቶ፥ በእሳት ያቃጠላቸው፥ በሰይፍ ያሳረዳቸው፥ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ያሳደዳቸው ሰይጣን ነው። የእርሱ ወገኖች የሆኑ ሁሉ ቅዱሳንን ይጠላሉ። ደግሞም እንኳን ቅዱሳንን ጠልተው፥ እኔን ኃጢአተኛውን እንኳ ጠልቶ የሚጸድቅ የለም። ወንጌል ፍቅር ናት፥ የሠራት ክርስቶስም ፍቅር ነው፥ ያዘጋጃት መንግሥተ ሰማያትም በፍቅር የምትወረስ ናት።       
                                                    
“እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፥ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፤”

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በእርሱ ማመን ያለውን ዋጋ፥ (ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ከባህርይ አባቱ ከአብ እና ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኰት፣ በሥልጣን፣ በባህርይ፣ በፈቃድ፣ በፈጣሪነት፣በእግዚአብሔርነት፣ በአምላክነት አንድ ነው ብሎ ማመን የሚያሰጠውን ጸጋ) ሲናገር፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፥ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፤” ብሎአል። ዮሐ፡፲፬፥፲፪። እንዲህም ማለቱ ለቅዱሳን የሰጣቸውን ጸጋ ታላቅነት ሲናገር እንጂ፥ ፍጡር ከፈጣሪ በላይ ይሠራል ለማለት አይደለም። ለምሳሌ እርሱ በዚህች ምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን፥ ጉባኤ ሠርቶ ያስተማረውና በአደባባይ ተአምራትን ያደረገው ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ነው። እነርሱ ደግሞ ከዚያ የበለጠ ሃያ ሠላሳ ዓመት ስለሚያስተምሩና አያሌ ተአምራትን ስለሚያደርጉ ነው። አንድም፡- በባሪያው በቅዱስ ዮሐንስ ፊት ራሱን ዝቅ አድርጐ በመጠመቅ፥ እርሱን ከፍ ከፍ እንደ አደረገው፥ አሁንም ራሱን በትህትና ዝቅ አድርጐ፥ ወዳጆቹን ቅዱሳንን ከፍ ከፍ ሲያደርጋቸው ነው። እንግዲህ የክርስቶስ የሆንን ሁሉ እርሱን አብነት በማድረግ፥ ራሳችንን ዝቅ፥ ቅዱሳንን ደግሞ፡- በመዝሙርም በትምህርትም ከፍ ከፍ ልናደርጋቸው ይገባናል። ከዚህም ጋር ልናስተውለው የሚገባን ነገር አለ፥ ይኸውም፡- ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሠራው በምድርም በሰማይም ነው። በመሆኑም፡- “እኔ የምሠራውን ሥራ ያደርጋሉ፤” የተባሉ ቅዱሳን በተሰጣቸው ጸጋና ሥልጣን ሥራ የሚሠሩት፥ በአጸደ ሥጋ በምድር ብቻ ሳይሆን፥ በአጸደ ነፍስ በሰማይም ነው። ነቢየ ኤልሳዕ በመቃብር በረገፈ አፅሙ ሙት ማስነሣቱ፥ ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ በአጸደ ነፍስም እንደሚያማልዱና ተአምራትን እንደሚያደርጉ ያስተምረናል። ኤልሳዕም ሞተ፥ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ።” ይላል። ፪ኛ፡ነገ፡ ፲፫፥፳። ከዚህም ጋር እያንዳንዳችን በሕይወታችን እናውቀዋለን፥ ምክንያቱም፡- በአጸደ ነፍስ ባሉ ቅዱሳን አማላጅነት እና ቃልኪዳን ያልተደረገልን ነገር የለም። 

No comments:

Post a Comment