Friday, November 13, 2015

ተሀድሶበክፍል ፱ ላይ በመጠኑ እንደገለጥነው፥ የብሉይ ኪዳንም ሆነ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፥ እግዚአብሔር ወድዶ ፈቅዶ በጠራቸው፥ ቅዱሳን ገድል እና ተአምር የተሞላ ነው። እርሱ፡- ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የሰጣቸው፥ መልካሙን ገድል እንዲጋደሉ እና በስሙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዲያደርጉ ነውና። ጌታ በወንጌል፡- “ሄዳችሁም፡- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። ድውዮችን ፈውሱ፥ ሙታንን አስነሡ፥ ለምጻሞችን አንጹ፥ አጋንንትን አውጡ፤ያላቸው ለዚህ ነው። ማቴ፡፲፥፯። ይኸንን ድንቅ ሥራ መሥራት የሚችሉት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመሆኑም፡- “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ (በነቢዩ በኢዩኤል የተነገረውን ቃለ ትንቢት እፈጽምላችኋለሁ) እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ (ኃይል የሚሆናችሁ፥ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እስኪሰጣችሁ) ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።ብሎአቸዋል። ሉቃ፡፳፬፥፵፱። የማዳን ሥራውንም ፈጽሞ ወደ ሰማይ ባረገ በአሥረኛው ቀን የተነገረውን ተስፋ ፈጽሞላቸዋል። የሐዋ፡፪፥፩-፳፩፣ኢዩ፡፪፥፳፰። (ከትንሣኤ እስከ ዕርገት አርባ ቀን፥ ከዕርገት እስከ ጰራቅሊጦስ ደግሞ አሥር ቀን፥ በጠቅላላው ፶ ቀን ነው)                                
                            
የቅዱሳን ሐዋርያትን ገድልና ተአምር በመጠኑ የመዘገበ ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ፥ነገር ግን በሰው ሁሉ ላይ ፍርሃት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ።ብሎ እንደነገረን፥ ቤተ ክርስቲያን፡- የእያንዳንዱን ቅዱስ ገድልና ተአምር በጥንቃቄ መዝግባ ትገለገልበታለች። የሐዋ፡፪፥፵፫። ምክንያቱም፡- የቅዱሳን ሕይወት የተተረጐመ ወንጌል ነውና። እንዲህ ባይሆን ኖሮ፥ ወንጌል ሊፈጽሙት የማይችሉት ንባብ ብቻ ይመስለን ነበር። ነገር ግን የእነርሱን ገድል እያነበብን፥ በሕገ ወንጌል ጸንተን ለመኖር እንበረታለን፥ ቅን የሆነ መንገዳቸውንም እንከተላለን።የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአችሁን ፍሬ (ምግባር ትሩፋታቸውን፥ ገድል ተአምራቸውን፥ ጌታ የሰጣቸውንም ቃል ኪዳን) እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።ይላል። ዕብ፡፲፫፥ ፯። ስለዚህ፡- ገድላቸው ካልተነገረ፥ በምን አውቀናቸው ነው፥ የምንመስላቸው? ማለት ይገባል።                                                                                                                          
የቅዱሳን ገድል የሚያመለክተን፡- ጌታ በወንጌል የነገረንን እና ፈጽሞ ሊፈጸም የማይቻል መስሎ የሚመስለንን ነገር ሁሉ እንዴት መፈጸም እንደሚቻል ነው። ለአብነትም ያህል፥ የሚከተለውን የወንጌል ቃል እናያለን። እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህ ብታሰናክልህ አው ጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።ይላል። ማቴ፡፲፰፥፰፣ ፭፥፳፱። ንን የጌታችንን ቃል ከቅዱሳን በቀር ማን ፈጸመው? ማንስ ይፈጽመዋል? በመሆኑም ቅዱሳን ሊደነቁ እንጂ፥ የበግ ለምድ በለበሱ ተኵላዎች(በመናፍቃን፣በከሀድያን) ሊነቀፉ አይገባም። እግዚአብሔር ኖኅን፡- “በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።በማለት አድንቆታል። ዘፍ፡፯፥፩። ሊቀ ነቢያት ሙሴንም፡- “ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ (እንደ ሌሎቹ አይደለም) እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፥ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል።ብሎለታል። ዘኁ፡፲፪፥፯። በአዲስ ኪዳንም፡-መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን፡- “ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ። ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም ፤በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው (የመንግሥተ ሰማያት ጌታ ሲሆን በትህትና ራሱን  ዝቅ አድርጐ ፥ ከድንግል ማርያም በተዋህዶ ሰው  ሆኖ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ) ይበልጠዋል። በማለት አድንቆታል። ማቴ፡፲፩፥፱። ይኸንን የመሰለም ብዙ አለ።                                                                                                                 
እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ ቈረጠህ ከአንተ ጣላት፤
አባ መርትያኖስ የተባለ መናኝ መነኵሴ ነበር። በዓቱ (ዋሻም ነው ቢሉ፥ ደሳሳ ጎጆም ነው ቢሉ) ከመንደር አጠገብ ነበር። ከበረሀ ውሎ ወደ ማታ ሲመለስ ዘማት(አመንዝሮች) ተሰብስበው ያዩታል፥ እርስ በርሳቸውም፡-“ይህ መነኰስ ኃያል ጽኑዕ ነው፥ ማንም ቢሆን ሊያስተው አይችልም፤ተባባሉ። በዚህን ጊዜ፡- ከመካከላቸው አንዷ፡-“እኔ ላሳስተው እችላለሁ፤ብላ ተወራረዱ። እርሷም፡- እንዴት እንደምታሳስተው ማሰላሰል ጀመረች። ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ አፍዋም ከቅቤ የለሰለሰ ነውና፥ ፍጻሜዋ ግን እንደ ሬት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም የተሳለ ነው። እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው።. . .አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች።ይላል። ምሳ፡፭፥፫፣፮፥፳፮። ያች በዝሙት የረከሰች ሴት፥ አውጥታ አውርዳ፥ አሁን በጊዜ የሄድኩ እንደሆነ አይቀበለኝም፤ብላ፥ በሌሊት ሂዳ፥ እጇን ጸፋች፥ ደጁን አንኳኳች። ከበዓቱ ወጥቶ ማነሽ?” ቢላት፥ ከሩቅ አገር የመጣሁ የእግዚአብሔር እንግዳ ነኝ፤ የምጠጋበት አጥቼ፥ አውሬ ይጣላኛል፥ ወንበዴ ይቀጠቅጠኛል ብዬ ፈርቼ፥ ከደጅ ቁሜ አለሁ። አለችው። እርሱም በጽናቱ ሳይመጻደቅ፥ ባስገባት ፆር ይነሣብኛል፥ (ፈተና ውስጥ እገባለሁ) አይሆንም ብላት፥ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ፥ እንግዳ ሆኜ ብመጣ አልተቀበልከኝም ብሎ በገሃነመ እሳት ይፈርድብኛል፤እያለ ያወጣ ያወርድ ጀመር። በዚህ ዓይነት ከኅሊናው ጋር ከተሟገተ በኋላ፥ ጌታዬስ ከሚፈርድብኝ፥ ፆሩን(ፈተናውን) በእግዚአብሔር ቸርነት እታገሠዋለሁብሎ፥ አስገባት። የሌሊቱ ውርጭ ወርዶባት ብርድ መትቷታል ብሎም እንድትሞቅ እሳት አነደደላትና ጸሎት ያዘ። እርሷ ግን እርሱን ለማጥመድ የተለያየ ዓይነት ሽቱ ትቀባ፥ የምታጤሰውንም ታጤስ ጀመረች። ምክንያቱም፡- በአማረ ሽቱ እና ጢስ አየሩን በማወድ፥ ለዝሙት መንፈስ መቀስቀሻ ይጠቀሙበት ስለነበረ ነው። የሽቱ ዓላማው ግን ይህ አልነበረም። ዘጸ፡፴፥፳፪፣ መዝ፡፻፴፫፥፩፣ ሉቃ፡፯፥፴፯፣ ማቴ፡፳፮፥፯፣ ዮሐ፡፲፱፥፴፱። አባ መርትያኖስ፡- የሽቱውና የጢሱ መዓዛ አስቸገረው፥ በዚህም ብቻ ሳይሆን፥ ሳታፍር ሳትፈራ፥ አብረን እንተኛ፤ብላዋለች። እርሱም፡-“ከተኛን ላይቀር ከእሳቱ ላይ እንተኛ፤ቢላት፥ እሳቱ ያቃጥለናል፤አለችው። በዚህን ጊዜ፥ የዚህን ዓለም እሳት ካልቻልነው ገሃነመ እሳትን እንዴት እንችለዋለን?” አላት። በኅሊናውም፡- “መሰናክል የሆነብኝ ይህ እግሬ ነው፥ ወደዚህ መንደር ባልመጣ ኖሮ ይህ ሁሉ ፈተና አይኖርም ነበር፤ብሎ አሰበ። አስቦም አልቀረ የሽቱውን መዓዛ እስኪያጠፋው ድረስ እግሩን ከእሳቱ ውስጥ ማግዶ አንጨረጨረው። እርሷም፡- “አባቴ አላበጀሁም፥ ማረኝ፤ብላ ንስሐ ገብታለች። አባ መርትያኖስም፡- አስተምሮና አመንኵሶ በዓቱን ለቅቆላት ሂዷል።                                                                                                 
ሌለኛው ገድል ደግሞ የሊቀ ጳጳሱ የአትናቴዎስ ነው። የአንፆኪያው ሊቀ ጳጳስ አባ አትናቴዎስ፥ ወደ ክርስትና ሕይወት ከመጠራቱ በፊት፥ ሃይማኖት የሌለው አረማዊ ነበር። በኋላ ግን ተምሮ፥ አምኖ፥ ተጠምቆም ክርስቲያን በመሆን፥ ለሊቀ ጵጵስና በቅቶአል። (በአረማዊነት የኖረ ሰው ከተጠመቀ በኋላ ንጽሕ ጠብቆ ከኖረ፥ እንደ ድንግል  ስለሚቆጠር፥ ጵጵስና ይሾማል።) በሀገራቸው አዲስ የተሾመ ሊቀ ጳጳስ፥ ሰባት ቀን በተከታታይ ቀድሶ ያቆርባል። በዚያ ልማድ ቀድሶ፥ አቍርቦ እየዞረ በሚባርክበት ጊዜ፥ ጥንት በአረማዊነት ሳለ በግብር የምታውቀው ሴት፥ እርሷ መሆኗን እንዲለያት ብላ እንደ ተሸፋፈነች እጁን ነክሳ አቆሰለችው። ወዲያው የዝሙት ፆር ተነሣበትና ተቸገረ። በኅሊናውም፡- “ከዚህ ያደረሰችኝ ይህች እጄ አይደለችምን? እጄን ባልነከስ ኖሮ፥ እንዲህ ያለ ከባድ ፈተና ውስጥ አልገባም ነበር።ብሎ አሰበ። አስቦም አልቀረ ወደ ግምጃ ቤት ገብቶ፥ እጁን ቆርጦ ጣላትና ከትራሱ ስር አስቀመጣት። ከዚህ በኋላ መቀደስ ስላልቻለ፥ ቍስሉን እያስታመመ ከበዓቱ ተከተተ። ካህናቱም እየተመላለሱ፥ እንደ ሥርዓቱ ቀድስልን፤ቢሉት፥ አይቻለኝም፤እያለ መለሳቸው። በዚህን ጊዜ፡- “ወደ ቀደመ ግብሩ ወደ አረማዊነቱ ተመልሶ ቢሆ ን ነው፤ብለው በሐሜት የሚጐዱ ሆኑ። ሐሜት ታላቅ ኃጢአት ነው፤ አፍህ ክፋትን አበዛ፥ አንደበትህም ሽንገላን ተበተበ። ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፥ ለእናትህም ልጅ ዕንቅፋት አኖርህ። . . .ባልንጀራውን በቀስታ የሚያማን እርሱን አሳደድሁ፤. . .ሐሜትንም የሚገልጥ ሰነፍ ነው።. . .ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና፤ እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁ አትታመኑ። ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል፥ በእውነትም አይናገርም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ። ማደሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፥ ከሽንገላም የተነሣ እኔን ያውቁኝ ዘንድ እንቢ ብለዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።የሚል አለ። መዝ፡ ፵፱፥፳፤ ፻፩፥፭፣ ምሳ፡፲፥፲፰፣ኤር፡፱፥፬። ሊቀ ጳጳሱ አቡነ አትናቴዎስ፡- ካህናቱ በሐሜት እንደተጐዱ ባወቀ ጊዜ፥ ከሥዕለ ማርያም ስር ተደፍቶ ወደ እመቤታችን ቢያመለክት ብርህት እጅ ቀጠለችለት። በማግስቱም ገብቶ ሲቀ ድስ፥ የእጁ ብርሃን ዓይናቸውን እየበዘበዘ (እያጥበረበረ) የማያሳያቸው ሆነ። ከቅዳሴ ውጭ ሲሆን፥ ካህናቱ ተሰብስበው፥ አባታችን ንገረን፥ ምሥጢሩ ምንድነው?” ቢሉት፥ የትራሴን ምንጣፍ ግለጡት፤አላቸው። ቢገልጡት የተቆረጠች እጁን ወድቃ አገኟት። በዚህን ጊዜ፡- “ይህች የተቆረጠች እጅ የኔ ናት፥ ይህች የምታበራው ደግሞ እመቤታችን የሰጠችኝ ነው፤ብሎአቸዋል።                                                                                    ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤                                
ይኸንን ያደረጉ ብዙዎች ናቸው፥ ከእነዚህም መካከል ስምዖን ጫማ ሰፊው አንዱ ነው። ይህ ሰው ከፍጹምነት የደረሰ ጻድቅ ነው። ነገር ግን እንደ ተርታ ሰው ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ጫማ ይሰፋ ነበር። የሚያገኘውንም ገንዘብ በስውር ለጦም አዳሪዎች ይሰጥ ነበር። ቀን ቀን ጫማ ሲሰፋ ይውላል፥ ሌሊት ሌሊት ደግሞ ሲመጸውት ሲሰግድ ያድራል። የቅዱሳን ባላጋራቸው (ጠላታቸው)የሆነ ሰይጣንም ፈተና አመጣበት። አንዲት ሴተ ወይዘሮ ጫማ ስፋልኝ ብላ ቀረበችው። እርሷም አንዴ ሰፋ፥ አንዴ ጠበበ እያለች(በምክንያት እየተመላለሰች)አስቸገረችው። ቢቸግረው፡- “ጫማውን እንደሆነ በሥርዓት ሰፍቼ አስረክቤሻለሁ፥ ለምን እየተመላለስሽ ሥራ ታስፈቺኛለሽ?” ሲል ጠየቃት። እርሷም፡- “ይህ ሁሉ (ጫማው ሰፋ ጠበበ ማለቴ )ለምክንያት ነው፥ እኔስ የምመላለሰው አንተን ብወድ ነው፥ እጅግ መልከ መልካም ነህና፤አለችው። እርሱም፡-“እኔ ለራሴ ከመንገድ ዳር የተጣልሁ ደሀ ጫማ ሰፊ ነኝ፥ ምኔ መልካም ነው?” ቢላት፥ ሁለንተናህ መልካም ነው፥ ይልቁንም በዓይንህ ይጸናብኛል፤አለችው። መልሶም፡-“ዓይኔን ትወጂዋለሽን?” ቢላት። አዎን እወደዋለሁ፤አለችው። በዚህን ጊዜ፡- “ይህማ ምን ቁም ነገር አለው፥ ውሀ አይደል?”ብሎ፥ በጫማ መስፊያው አውልቆ ሰጥቷታል።                                                                                      
በሌላ በኵል ደግሞ፥ዓይን የተባሉ የትዳር ጓደኞች፥እጅ የተባሉ ልጆች፥እግር የተባሉ ደግሞ ዘመድ አዝ ማድ ናቸው።ትርጉሙም፡-የትዳር ጓደኞቻችሁ ወይም ልጆቻችሁ ወይም የሥጋ ዘመዶቻችሁ፥ ያልሆነ ሥራ እናሠ ራችሁ ቢሏችሁ፥ዛሬ የእነርሱን ፈቃድ ፈጽማችሁ፥ በኋላ ተያይዛችሁ ወደ ገሃነም እሳት ከምትገቡ፥ዛሬ የእነርሱን ፈቃድ አፍርሳችሁ፥የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ ፈጽማችሁ፥ እነርሱን አጥታችሁ፥ እግዚአብሔርን አግኝታችሁ፥ ብቻችሁን ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገቡ ይሻላችኋል፤ ማለት ነው።                         ይህን ተራራ፡-ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤    
                                         
የጌታ ደቀ መዛሙርት፡- ከታቦር ተራራ ስር ያገኙትን በሽተኛ፥ የተቆራኘውን ሰይጣን አስወጥተው ሊፈው ሱት አልቻሉም ነበር። ምክንያቱም፡- ኃይል የሚሆናቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ገና ስለ አልተሰጣቸው ነው።ጌታ ክብረ መንግሥቱንና ግርማ መለኰቱን በተራራው ራስ ገልጦ ሲመለስ፥ የበሽተኛው አባት ሰገደለትና፥ ጌታ ሆይ ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ይሰቃያልና፤ ብዙ ጊዜ በእሳት፥ ብዙ ጊዜም በውኃ ይወድቃልና። ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፥ ሊፈውሱትም አልቻሉም፤አለው። እርሱም ደቀ መዛሙርቱን ስለ እምነታቸው መጉደል ከወቀሳቸው በኋላ፥ ጋኔኑን ገሥጾ ከበሽተኛው እንዲወጣ አድርጓል። ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው፡- “እኛ ልናወጣው ያልቻልነው ስለ ምን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም፡- “ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ፡- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤የሚሳናችሁም ነገር የለም። ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጾም በቀር አይወጣም፤ አላቸው።ይላል። ማቴ፡፲፯፥፲፬። ይህንን የጌታ ቃል ተፈጽሞ የምናየው፥ በቅዱሳን ገድል እንጂ፥ ቅዱሳንን ከሚጠሉ መናፍቃን መካከል አንዳቸውም ፈጽመው ሊያሳዩን አይችሉም።                                                                                         
ይህ በወንጌል የተጻፈ ቃል፥በአብርሃም ሶርያዊ ጊዜ ተፈጽሟል። ለሊቀ ጳጳሱ አንድ አይሁዳዊ ወዳጅ ነበራቸው። ሁለቱም (ሊቀ ጳጳሱም አይሁዳዊውም) ለንጉሡ ለመኳንንቱም ወዳጆች ናቸው። ሁለቱም ወዳጆቻቸውን ለመጠየቅ በየፊናቸው (በየራሳቸው)ሲሄዱ፥ እግረ መንገዳቸውን የሃይማኖት ጉዳይ እያነሡ ይከራከራሉ። ነገር ግን፡- ሊቀ ጳጳሱ አይሁዳዊውን፡- ሁል ጊዜ ምላሽ ያሳጡት ነበር። በዚህ የሚበሳጭ አይሁዳዊም፡- በሌላ ጊዜ ለብቻው  ገብቶ፥ እነዚህ ክርስቲያኖች እንጂል(ወንጌል) የምትባል መጽሐፍ አለቻቸው፥ በውስጧም፡- የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፥ የሚል ተጽፎ ይገኛል፥ አድርጉ ቢሏቸው ግን አይሆንላቸውም።ብሎ፥ በሊቀ ጳጳሱ ላይ ነገር ሠራ። ከዚህ በኋላ፡- ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ሲገናኙ ነገሩን እየረሳ፥ ነገሩን ሲያስታውስ ደግሞ ሊቀ ጳጳሱን እያጣቸው፥ ብዙ ቀን ቆየ። ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን፥ ሊቀጳጳሱ ባሉበት ነገሩ ትዝ አለውና፡- “አባቴ የምጠይቅህ ኑሮኝ፥ አንተን ሳገኝህ ነገሩን እያጣሁት፥ ነገሩ ትዝ ሲለኝ ደግሞ አንተን እያጣሁህ ብዙ ቀን ቆየሁ። ዛሬ ግን አንተ ባለህበት ነገሩ ትዝ ብሎኛል።አላቸው። ነገሩ ምንድነው?”ብለው ቢጠይቁት፥ ወንጌላችሁ፡- የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ያለው ሰው ተራራ ያነሣል፥ የምትለውን ማድረግ ትችላላችሁን?” አላቸው። እርሳቸውም፡- “አዎን እንችላለን፤አሉት። በዚህን ጊዜ፡- “እንግዲያውማ የዚህ ሁሉ ክርስቲያን ሃይማኖት ቢደመር ከሰናፍጭ ቅንጣትነት አልፎ ተራራ አያህልምን? አድርገህ አሳየኝ፤ቢላቸው፥ ሦስት ቀን ብቻ እንዲሰጣቸው ጠይቀው፥ ከእመቤታችን ሥዕል ስር ወድቀው አመለከቱ። እመቤታችንም፡- “ይህ ነገር ለአንተ አይቻልህም፥ የሚቻለው ለባለ አንድ ዓይኑ ለስምዖን ነው፤ ተርታ ሰው መስሎ ከገበያ መካከል ተቀምጦ እንጨት ሲሸጥ ታገኘ ዋለህና ሂደህ ንገረው፥ እሺ ብሎም ስለ ማይቀበልህ፥ እመቤታችን ነገረችኝ በለው፤አለችው። ሄዶም አገኘውና እየፈራ በስተኋላው ልብሱን ያዘው። ስምዖንም፡- አወቀብኝ ብሎ፥ ምን አድርግ ትለኛለህ? በሀገርህ ድኃ አይኖርምን?”አለው፥ እጅግም ተቆጣ። በዚህን ጊዜ ሊቀ ጳጳሱ፡- እመቤታችን እንደላከችውና የመጣበትንም ጉዳይ አስረዳው።                  

         ስምዖን ሁሉን ነገር ከሊቀ ጳጳሱ ከተረዳ በኋላ፥ እንኪያስ እኔን አትግለጠኝ፥ ክርስቲያኑን ከተራራው ፊት ለፊት፥ አሕዛብን ደግሞ ከተራራው ጀርባ ሰብስበህ፥ ካህናትንም አልብሰህ ቆየኝ። አንተ እኔ የምሠራውን እያየህ ትሠራለህ፥ ሕዝቡ ደግሞ አንተ የምትሠራውን እያዩ ይሥሩ፤አለው። ሊቀ ጳጳሱም የተባለውን ሁሉ አደረገ፤ አርባ አንድ ኪራያላይሶን እያደረሱ ሰግደው ሲነሡ፥ ተራራው ብድግ አለ። ተደፍተው ሲሰግዱ እየተመለሰ፥ ከሰገዱበት ሲነሡ ደግሞ ወደ ላይ እየተነሣ ተአምር ተደረገ። ክርስቲያኖችና አሕዛብም በተራራው ስር ፊት ለፊት ተያዩ፥ ይህ ተአምር የተደረገው ለሦስት ጊዜ ነው፥ በአራተኛውም፡- እየወጣ የሚያውካቸው ውኃ ስለ ነበረ፥ ሂደህ ተጋረድላቸው፤ቢለው፥ ቦታውን ለቅቆ ሂዶ ተጋርዶላቸዋል። 

3 comments:

  1. abatachen eragem yagalglowt gzana regem edma ktana gar egezabher amlak ystlen!! Aman!!

    ReplyDelete
  2. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን :: አባቶቻችንን በሃይማኖት ያጸና አምላክ እኛንም እንከን በሌላት በተዋሕዶ እምነታችን እንድነጸና ይርዳን:: ቤተክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነት ካሉ ተኲላዎች ከሆድ አምላኪዎች ይጠብቅልን::

    ReplyDelete
  3. አባታችን ፀጋውን ያብዞሎት፤ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

    ReplyDelete