Saturday, November 7, 2015

ተሀድሶእኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ፤” ፩ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፩።

ክርስትና ክርስቶስን መምሰል ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በወንጌል፡-“እኔን መከተል የሚወድ (ሊመስለኝ የሚወድ) ራሱን ይካድ፤ (ፈቃደ ሥጋውን ይተው፥በፈቃደ ነፍስ ይኑር፥ ሥጋ ዊውን ዓለም ማለትም ሹመቱን ሽልማቱን ይናቅ፤) መስቀሉንም ተሸክሞ (መከራን ሁሉ ታግሶ) ይከተለኝ።ያለው  ለዚህ ነው። ማቴ፡፲፮፥፳፬። በተጨማሪም፡- “ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል። (ፍጹም ዋጋ አለው)። የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።የሚል አለ። ማቴ፡፲፱፥፳፱። በመሆኑም፡- ቅዱሳን ስለ ክርስቶስ ሁሉን ትተዋል። ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል።እያሉ፥ በቃልም በሕ ይወትም ሰብከዋል። ፩ኛ ዮሐ፡ ፪፥፲፭። ስለዚህ የዓለም ወዳጅ የሆኑና በዓለም ምኞት የሚቃጠሉ መናፍቃን፥ ከዓለም ፈጽመው በመለየት ክርስቶስን በመሰሉ ቅዱሱን ላይ፥ እንደ ተከፈተ መቃብር አፋቸውን ሲከፍቱ ሊያፍሩ ይገባ ቸው ነበር። 

ቅዱሳን ዓለምን በመተዋቸው፥ መከራን አጽንታባቸዋለች። ይኸንንም፡- “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።በማለት፥ ጌታችን አስቀድሞ ነግሮአቸዋል። ዮሐ፡፲፮፥፴፫። በመሆኑም፡-ጀርባቸው ቆስሎ እስኪተላ ድረስ ተገርፈዋል። የሐዋ፡፭፥፵። በሰንሰለት ታስረው ወደ ወኅኒ ቤት ተወርውረዋል። የሐዋ፡፲፪፥፮። በበትር እየተደበደቡ መከራን መቀበል ብቻ ሳይሆን፥እግሮቻቸውን ከግንድ ጋር አጣብቀው ጠር ቀዋቸዋል። የሐዋ፡፲፮፥፳፬። በሰይፍ ገድለዋቸዋል። የሐዋ፡፲፪፥፪። የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ (በዕለተ ምጽአት፡- ብርሃን ለብሰው፥ ብርሃን ተጐናጽፈው ለመነሣት) እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ(ቆዳ) ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ።ይላል። ዕብ፡፲፩፥፴፭። ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ፡- በአይሁድ፥ በአሕዛብና በመናፍቃን አድሮ አሰቃይቶአቸዋል። ተቀዳሚና ተከታይ በሌለው በአንድ ልጁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራቸው፥ የጸጋ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ግን፥ ከመከራው በኋላ፥ ፍጹማን አድርጐአቸዋል፥አጽንቶአቸዋል፥ አበርትቶአቸዋል። ፩ኛ፡ጴጥ፡ ፭፥፱።
ቅዱሳን፡-የመረጣቸውን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰሉት፥ወንጌልን በማስተማርና ተአምራትን በማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ ከላይ እንደተገለጠው ጽኑእ መከራን በመቀበልም ጭምር  ነው። ለምሳሌ፡-ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ፥ መከራ ስላጸኑበት ሰዎች አባት ሆይ፥የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤ብሎ እንደተናገረ፥ ቅዱስ እስጢፋኖስም፡-ጠላቶቹ የድንጋይ ናዳ እያወረዱበት፥ጌታ ሆይ፥ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው፤እያለ በታላቅ ድምፅ ሲጮኽ ተሰምቶአል።ሉቃ፡፳፫፥፴፬፣ የሐዋ፡፯፥፷። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-“እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ፤በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። ፩ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፩። ምክንያቱም፡- ቅዱሳንን በመምሰል ክርስቶስን ወደ መምሰል ስለምንደርስ ነው። በተጨማሪም በሮሜ መልእክቱ ላይ፥ እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጐ እንዲደረግ እናውቃለን።ልጁ(የባህርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ) በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ (ለቅዱሳን ሁሉ የበጐ ምግባር ምሳሌ ይሆናቸው ዘንድ) አስቀድሞ ያወቃቸው (የመረጣቸው) የልጁን (የኢየሱስ ክርስቶስን) መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።ብሎአል። ሮሜ፡፰፥፳፰። ከሁሉም በላይ፥ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፥ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ብሎ እንደተናገረ፥እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤በማለት ተናግሮላቸዋል። ማቴ፡፭፥፲፬፣ ዮሐ፡፰ ፥፲፪። በመሆኑም፡- ክርስቶስ የተቀበላቸውን፥ እርሱንም መስለው የተገኙትን ቅዱሳን መቀበል፥ እርሱን መቀበል እንደሆነ ማመን ይገባል። ይኸንንም፡-“እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤በማለት ተናግሮላቸዋል። ማቴ፡ ፲፥፵። ኧረ ለመሆኑ፥መናፍቃኑ፡- ቅዱሳኑን ሳይቀበሉ፥ጌታን ተቀብለናል፥ የሚሉት በየት በኵል አልፈው ነው
ቅዱሳን፡- በነገር ሁሉ እርሱን መስለው በመገኘታቸው፥ ስለ እነርሱ መስበክ ማለት፡-ስለ እርሱ መስበክ ማለት ነው። ምክንያቱም፡-ገድለ ቅዱሳን የተጻፈው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ተጋደሉት ገድል ነውና። ገድላቸው፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ እንደመረጣቸው ይናገራል። ይኼንን የመሰለ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስም ተጽፎ ይገኛል።ነቢዩ ኤርምያስ፡-“የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፡- በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥አለኝ።ብሎአል። ኤር፡፩፥፬። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልም፡- ስለ መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ልደት የምሥራች ሲናገር፥በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል።ብሎአል። ሉቃ፡፩፥፲፭።ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል፥ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ(ከዓለም ተለይተው በድንግልና እንዲያገለግሉት የተመረጡ)አሉ።በማለት ተናግሮአል። ማቴ፡፲፱፥፲፪። ገድል፡- ቅዱሳን፥ ሁሉን ትተው ጌታን እንደተከተሉት ይናገራል። ወንጌልም፡-“ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።. . .አባታቸውንም ዘብዴዎስንም በታንኳ ላይ ትተውት ተከትለውት ሄዱ።ይላል። ማር፡፩፥፲፰።ቅዱስ ጴጥሮስ፡-“እነሆ ፥እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?”ያለው ለዚህ ነው። ጌታም፡-“እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት (በመጨረሻዋ ቀን) የሰው ልጅ (በተዋህዶ ፍጹም ሰው የሆነ የባህርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ) በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ(በእስራኤል ዘሥጋ በአይሁድ፥ በእስራኤል ዘነፍስ በምዕመናን) ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።ብሎታል። ማቴ፡፲፱፥፳፯። በዚህም፡- የባህርይ ፈራጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እነርሱን የጸጋ ፈራጅ አድርጐ ራሱን አስመስሎአቸዋል። ቅዱስ ጳውሎስ፡-“በአጭር ቃል በእናንት መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል፤የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድ ታዝኑ አይገባችሁምን?ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ።ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ፡ቆሮ፡፭፥፩።
በአጠቃላይ አነጋገር፥ ገድል፡-ቅዱሳን፡- በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዳስተማሩ፥በስሙ መከራ እንደተቀበሉና ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረጉ፥ በመጨረሻም ቃል ኪዳን እንደተሰጣቸውና በሰማዕትነት እንደ አለፉ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስም በቅዱሳን ትምህርት፥ ገድልና ተአምራት የተሞላ ነው። ለምሳሌ፡-ቅዱስ ሉቃስ፡-ቅዱሳን ሐዋርያት፥ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ መሰሉበት ገድል፥ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው በመገኘታቸው ከሸን ጐው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።በማለት ጽፎአል። የሐዋ፡፭፥፵። የተአምር መጽሐፋቸውም ሲነበብ የሚሰብ ከው ኢየሱስን ነው።ጴጥሮስ ግን፡- ወርቅና ብር የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ተመላለስ አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭሚቱ ጸና፤ይላል። የሐዋ፡፫፥፮። ስለ ቅዱስ ጳውሎስም፡- ኤልማስ የተባለውን ጠንቋይ በገሠጸው(በፈረደበት) ጊዜ፥ስለሆነው ነገር፥ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው፡- አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥የቀናውን የጌታን መንገድ (ወንጌልን) ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ፥ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም አለው።ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ።የሚል ተጽፎአል። የሐዋ፡፲፫፥፱። በተጨማሪም፥እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር፥ ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር።የሚል አለ። የሐዋ፡፲፱፥፲፩። ቅዱስ ጴጥሮስም፡- በሐናንያና በሰጲራ ፈርዶባቸዋል።ሐናንያ ሆይ፥መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው። ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ ሞተም፤. . .ከሦስት ሰዓት ያህል በኋላም ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ ገባች። ጴጥሮስም መልሶ፡- እስቲ ንገሪኝ፥ መሬታችሁን ይህን ለሚያህል ሸጣችሁትን? አላት። እርስዋም፡- አዎን ይህን ለሚያህል ነው አለች። ጴጥሮስም፡- የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው፥ አንቺንም ያወጡሻል አላት። ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተችም፤ይላል። የሐዋ፡፭፥፩። ከዚህም፡- በቅዱሳን ላይ በድፍረት መናገር፥ በእግዚአብሔር ላይ መናገር እንደሆነ ትምህርት እንወስዳለን። እንግዲህ የቅዱሳን ገድልና ተአምር የሚባለው ይኸንን የመሰለ መሆኑን በሚገባ እናስተውላለን።በመሆኑም ነገረ ቅዱሳን የጌታን ስም ይበልጥ ይገልጠዋል እንጂ አይሸፍነውም። ምክንያቱም፡- እነርሱ በሕይወታቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ስም እንዲሸከሙ የተመረጡ ናቸውና። ይኸንንም፡- የጌታችን ቃል፥ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ(መሣሪያ)ነውና።በማለት ይነግረናል። ከዚህም በላይ ቅዱሳን የጸጋ አማልክት(ገዢዎች) ናቸው። እግዚአብሔር ሙሴን፡- “እይ፥እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ።ማለቱ የሚያረጋግጥልን የኼንኑ ነው። ዘጸ፡፯፥፩።በአዲስ ኪዳንም  ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ቅዱሳን የጸጋ አማልክት መሆናቸውን ጠቅሶ ሰብኰአል። መዝ፡፹፩፥፮፣ ዮሐ፡፲፥፴፬። እንግዲህ መናፍቃኑ፡- የሚያዋጣቸው ከሆነ፥ለምን እንዲህ አደረግህ?” ብለው እር ሱን ይጠይቁት።

ቅዱሳንን መቃወም እኮ የሰይጣን ሥራ ነው።ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን አጥቶ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤የተባለው ለዚህ ነው። ፩ኛ፡ጴጥ፡፭፥፰። በራእየ ዮሐንስም ላይ፥አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን (የቅዱሳን) ከሳሽ ተጥሎአልና።እነርሱም ከበጉ (ከአዲስ ኪዳን በግ ከኢየሱስ ክርስቶስ) ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም (ሰውነታቸውንም) እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም። ስለዚህ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።የሚል አለ። ራእ፡፲፪፥፲። መጽሐፈ (ገድለ) ኢዮብን ብንመለከት፡- “እግዚአብሔር ሰይጣንን፡-ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም፡- በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፡- በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፤ በከንቱም አጠፋው ዘንድ አንተ ምንም ብታንቀሳቅሰኝ እስከ አሁን ፍጹምነትን ይዞአል።ይላል። ኢዮ፡፪፥፪። ሰይጣን አይቻለውም እንጂ ቢቻለው፥ እግዚአብሔርን እንኳ በቅዱሳን ላይ ማነሣሣት ይፈልጋል። በትንቢተ ዘካርያስ ላይ ደግሞ፡-“እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ አሳየኝ፥ ሰይጣንም ይከስሰው ዘንድ በቀኙ ቆሞ ነበር።እግዚአብሔርም ሰይጣንን፡- ሰይጣን ሆይ፥ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይ ደለምን? አለው። ኢያሱም አድፋም ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር።እርሱም መልሶ በፊቱ የቆሙትን፡-እድ ፋሙን ልብስ ከእርሱ ላይ አውልቁ፥አላቸው። እርሱንም፡- እነሆ፥አበሳህን ከአንተ አርቄአለሁ፥ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ አለው። ደግሞ፡-ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉ አለ። እነርሱም በራሱ ላይ ንጽሕ ጥምጥም አደረጉ፥ልብሱ ንም አለበሱት፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በአጠገቡ ነበር።ይላል። ዘካ፡፫፥፩። ከዚህም የቅዱሳን ከሳሾች የሰይጣንን ሥራ እየሠሩለት እንደሆነ፥ የእግዚአብሔርም ተግሣጽ እንደወደቀባቸው እንረዳለን። በሌላ በኵል ደግሞ፥ መናፍቃን ከሰይጣን ጋር ተሰልፈው፥ ያላቸውን ጥላቻ ሁሉ ቢገልጡ፥ ቅዱሳንን ከክብራቸው ዝቅ ማድረግ እንደማይችሉ እንማራለን። ቅዱስ ጳውሎስ፡-“እግዚአብሔር የመረጣቸውን (የተመረጡ ቅዱሳንን) ማን ይከሳቸዋል?” ያለው ለዚህ ነው። ሮሜ፡፰፥፴፫።   

2 comments:

  1. abatachen kale hiwot yasanalen!!eragem yagalgalot gzana edma ktana gare egezabher amlak ystlen aman!!

    ReplyDelete