Friday, October 9, 2015

ተሀድሶ ክፍል ፭

                              የጽድቅና የሕይወት አገልግሎት፤                                                      
      የአዲስ ኪዳን አገልግሎት የጽድቅና የሕይወት አገልግሎት ነው። ምክንያቱም፡- ጌታችን  አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት ሁሉን ነገር አዲስ አድርጐታልና ነው። “ስለ  ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፤” ያለው ለዚህ ነው። ማቴ፡፳፮፥፳፰። በዚህም፡- የአዲስ ሕግ የወንጌል፥የአዲስ ርስት የመንግሥተ ሰማያት መጽኛ ፥ በመስቀል ላይ የሚፈሰው የእርሱ ደም መሆኑን፥ዓርብ ሊሰቀል ሐሙስ ማታ ተናግሮአል። ሞትን እና ኵነኔን ያመጣብንን የአዳምን ኃጢአት በመስቀል ላይ በፈጸመው ቤዛነት በመደምሰሱ (በማስወገዱ)፥ ጽድቃችን፡- የሞት አገልግሎት፣ የመርገም ጨርቅ መባሉ ቀርቶልናል። በመሆኑም፡- ስንዴ ዘርቶ እሾህ ማጨድ፥ ደክሞ መና መቅረት፥ ወደ ሲኦልም መንጐድ፥ ያለፈ ታሪክ ሆኗል። ጌታችን በወንጌል፡- “ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ . . . የሰው ልጅ(በተዋህዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ) ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር (ከባህርይ አባቱ ከአብ ጋር እኵል በሆነ ጌትነቱ) ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤” በማለት የነገረን ለዚህ ነው። ማቴ፡፭፥፲፪፣፲፮፥፳፯። ዋጋችን ደመወዛችን በሰማይ እንደሚቆየን በአማናዊ ቃሉ ሲያስተምረንም፡- “እናንተን (ቅዱሳንን) የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥እኔንም የሚቀበል የላከኝን (አብን መንፈስ ቅዱስን) ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል ። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር (በቅዱሳን) ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም። . . . እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ(በተዋህዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ) በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት (በጌትነቱ በሚገለጥበት) ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ (በተዋህዶ ሰው የሆንኩ የባህርይ አምላክ መሆኔን ያመናችሁ) በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ (በእስራኤል ዘሥጋ በአይሁድ፥ በእስራኤል ዘነፍስ በክርስቲያኖች ላይ) ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ (ፍጹም ዋጋ) ይቀበላል፥ የዘለዓለምን ሕይወት ይወርሳል።”ብሎናል። ማቴ፡፲፥፵፣፲፱፥፳፰።ቃሉ እንዲህ ቢልም አንዱን እንኳ ትተን ልንከተለው አልቻልንም፥ ቅዱሳን ግን ሁሉን ትተው በመከተል ባለ ዋጋ ሆነዋል።                            

በብሉይ ኪዳን ዘመን ደማቸውን እስከ ማፍሰስ ድረስ የጸኑት ሁሉ፥ በአዳም ኃጢአት ምክንያት ወደ ሲኦል ቢወርዱም በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቀዋል። በዚያን ዘመን በሃይማኖት ምክንያት ስለፈሰሰ የቅዱሳን ደም፥ጌታችን በወንጌል፡- ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ሲወቅስ፥ “ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እሰከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ (ይፈርድ ባችሁ) ዘንድ።”ብሏል። ማቴ፡፳፫፥፴፭። በአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ እንኳን የሰማዕትነት ደም፥ በቅዱሳን ስም የተዘከረ ቀዝቃዛ ውኃ እንኳ የማይጠፋ ዋጋ እንደ  አለው ነግሮናል። ቆርሶ ማጉረስ፥ ቀድዶ ማልበስ፥ቀድቶ ማጠጣት፥የታመመ  መጠየቅ፥የታሰረ መጐብኘት፥በጌታ ቀኝ የሚያቆም፥“እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ።” የሚለውን ቃለ ሕይወት የሚያሰማ ሆኗል።ማቴ፡ ፳፭፥፴፬።ቅዱሳን ይህችን ሀገር በሃይማኖት ፊት ለፊት እያዩ በማገልገላቸው፥“ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለ እናውቃለን። . . . ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃል እንጠብቃለን። . . . አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ፥ባሕርም ወደ ፊት የለም።ቅድስቲቱም ከተማ አዲስቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።”ብለዋል።፪ኛ፡ቆሮ፡፭፥፩፣ ፪ኛ፡ጴጥ፡ ፫፥፲፫፣ራዕ፡፳፩፥፩።ከነቢያት እነ ኢሳይያስም ፡-“እነሆ፥አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤(ፈጥሬ አዘጋጅቼ አለሁና፤) የቀደሙትም አይታሰቡም፥ወደ ልብም አይገቡም።ነገር ግን በፈጠር ሁት(ፈጥሬ ባዘጋጀሁላችሁ) ደስ ይበላችሁ፥ለዘለዓለምም ሐሤት አድርጉ።”የሚለውን የእግዚአብሔርን ድምፅ ሲያስተጋቡ ኖረዋል። ኢሳ፡፷፭፥፲፯።                                   
በብሉይ ኪዳን ዘመን መሥዋዕቱ እና መሥዋዕት አቅራቢው ሙታን ሲሆኑ፥መሥዋዕት ተቀባዩ እግዚአብሔር ብቻ ሕያው ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን ግን፥ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱንም ሆኖ ተገኘ።ሕያው መሥዋዕት፥ሕያው መሥዋዕት አቅራቢ፥ ሕያው መሥዋዕት ተቀባይ እርሱ ሆነ።ሕያው መሥዋዕት በመሆኑ፥“ሥጋዬን የሚ በላ፥ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤” አለ።ዮሐ፡፮፥፶፫።በመሆኑም የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ማታ ፥ሥርዓተ ቍርባንን ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው ጊዜ፥ኅብስቱን ለውጦ ሥጋ መለኰት፥ ወይኑንም ለውጦ ደመ መለኰት ካደረገው በኋላ አቍርቧቸዋል። ፈጽሞ መለወጡንም ሲነግራቸው፡-“ኅብስቱን አንሥቶ ባረከ፥ቈርሶም ለደቀ መዝሙርቱ ሰጠና፡- እንካችሁ፥ብሉ፤ይህ ሥጋዬ ነው አለ።ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ስለ ብዙዎች ለኃጢ አት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፥አላቸው፤” ይላል።ማቴ፡፳፮፥፳፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡-“ስለዚህ ሳይገባው (ንስሐ ሳይገባ ወይም ሳያምን) ይህን ኅብስት የበላ  ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን (ሰውነቱን በካህን አስመርምሮ ንስሐ ይግባ)፥ እንዲሁም ከኅብስቱ ይብላ፥ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና ይጠጣልምና።” ብሏል። ፩ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፳፯። በመሆኑም አንድ ጊዜ ተሠውቶ፥ሕያውና ዘለዓለማዊ የሆነ መሥዋዕት ሥጋውንና ደሙን ስለሰጠን፥ዕለት ዕለት የምንቆርበው ቅዱስ ቍርባን አማናዊ የክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሆነ እናምናለን።                
ሕያው መሥዋዕት አቅራቢ በመሆኑም፥“ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለ ሁና፥ስለ ዚህ አብ ይወደኛል።እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም።ለኖራት ሥልጣን አለኝ፥ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፤” ብሏል። ዮሐ ፡፲፥፲፯።በዮሐንስ ራዕይም ላይ፥“ፊተኛ ውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፥የሞትና የሲኦል መክፈቻ አለኝ።” ሲል እናገኘዋለን።ራዕ፡፩፥፲፰።በመስቀል ላይ፥በሞተ ሥጋ ነፍሱ ከሥጋው ብትለይም፥ በተዋህዶ የነበረ ሕያው መለኰት ከሥጋም ከነፍስም አልተለየም።በመሆኑም ከሥጋ ጋር ወደ መቃብር፥ ከነፍስም ጋር ወደ ሲዖል ወርዷል።ይኸንንም፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፥“ክርስቶስም ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሞቶአልና፤ጻድቅ እርሱ እኛን ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ፥ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) ያቀርበን ዘንድ ስለ እኛ ስለ ኃጢአታችን በሥጋ ሞተ፥ በመንፈስ (በመለኰት) ግን ሕያው ሆነ።በእርሱም በወኅኒ (በሲ ዖል) ወደ አሉ ነፍሳት ሄዶ ነፃነትን ሰበከላቸው።“በማለት አስረድቷል።፩ኛ፡ጴጥ፡፫፥፲፰።ወልድ ዋህድ ብለው በእርሱ ያመኑ ቅዱሳንም በእርሱ ሕያዋን ናቸው።ይኸንንም፡-“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፥ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም” በማለት ለእኅተ አልዓዛር ነግሮአታል።ዮሐ፡፲፩፥፳፭።                                
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ራሱን ሕያው መሥዋዕት አድርጐ ያቀረበ ሕያው ሊቀ ካህናት ነው።ይኸንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፥“ቅዱስና ያለ ተንኰል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል፤እርሱም እንደነዚያ (እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን) ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ  ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ (በየዕለቱ መከራ ሊቀ በልና ሊሞት) አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ  ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና። ሕጉ ድካም ያላቸውን (በአዳም ኃጢአት የተያዙትን አንድም ድካመ ሥጋ ያለባቸውን) ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘለዓለም ፍጹም የሆነውን (የማይ ለወጠውን)ልጅ(ወልድን)ይሾማል።(ሾመልን።)”በማለት ነግሮናል።ዕብ፡፯፥፳፯።በተጨማ ሪም፡- “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ላልተማሩ ትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል።እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም።እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ነገር ግን፡-አንተ ልጄ ነህ፥አኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ (የባህርይ አባቱ አብ) ነው፤እንደዚሁም በሌላ ስፍራ ደግሞ፡-አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት (ክህነት) ለዘለ ዓለም ካህን ነህ፥ይላል።”ብሎናል።በዚህም፡-በብሉይ ኪዳን ዘመን ወደ ሥልጣነ ክህነት የመጡ ትን ሰዎች የጠራ፥ክብሩንም የሰጣቸው፥ እግዚአብሔር እንደነበረ ነግሮናል።                                
እንግዲህ በዚህ ሁሉ ምክንያት፥አገልግሎቱን የሞትና የኵነኔ አገልግሎት ያሰኙት ነገሮች ሁሉ በመሻራቸው፥በታቦቱ ፊት የምናገለግለው አገልግሎት የጽድቅና የሕይወት አገልግሎት ነው ነው።በጽላቱ ላይ የተቀረጹት ቃሎቹና ቅዱስ ስሙም ዘመን የማይሽራቸው ሕያውና ዘለዓለማዊ ናቸው።እርሱ ራሱ፥“ሰማይና ምድር ያልፋል፥ቃሌ ግን አያልፍም፤” ብሎናል። ማቴ፡፭፥፲፰። ለጽላቱ  ስንሰግድ፥ የምንሰግደው ለቅዱስ ቃሉ እና ለቅዱስ ስሙ ነው።አንድም ለቃሉ ባለቤት ነው። “ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው።(የተዋሀደውን ሰውነት አምላክ አደረገው)።ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምን ሰጠው። (ሰውነት በተዋህዶ አምላክ በመሆኑ በመለኰታዊ ስም ተጠራ)።ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድር በታች ያለ ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው።”ይላል። ፊል፡፫፥፱።                                            
በብሉይ ኪዳን ዘመን፥እግዚአብሔር ሙሴን፡-“ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረ ጋሉ፥የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ።የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። በዚያም ከአንተ ጋር እገናኝለሁ።”ብሎታል።ዘጸ፡፳፭፥፳።ይልቁንም የአዲስ ኪዳን ዘመን፥የኃጢአት መጋረጃ ተቀድዶ ሰውና እግዚአብሔር ፊት ለፊት የተያዩበት ዘመን በመሆኑ፥ሥጋውና ደሙ በሚፈተትበት መንበረ ታቦት አጠገብ ያገኘናል፥ እናገኘዋለን፤ ያነጋግረናል፥እናነግረዋለን።ሕገ ኦሪትን ያከበሩ ሰዎች፥ከላይ በዝርዝር ባየናቸው ምክንያቶች ወደ ሲዖል ወርደዋል፥ ሕገ ወንጌልን ያከበሩ እና የሚያከብሩ ሰዎች ግን ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ይጓዛሉ።በቀኙ ተሰቅሎ የነበረ ወንበዴ እንኳ፥በመጨረ ሻዋ ሰዓት አምኖ ንስሐ በመግባቱ፥በውንብድና ውስጥም ሆኖ ከሠላሳ ዓመት በፊት ሠርቶት የነበረውንም ጽድቅ ቆጥሮለት፥“ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ፤” ብሎታል።ሉቃ፡፳፫፥፵፫ ።በመ ሆኑም ከክብረ ኦሪት ክብረ ወንጌል ይበልጣል።ኦሪት ለወንጌል አምሳልና መርገፍ ነች።እኛ የታነጽነው በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ነው፥የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ፤በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤በእርሱም እኛ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብረን እንሠራለን ።ኤፌ፡፪፥፳።                                                  
 ሕገ ልቡና- ምሳሌ ኦሪት - ትንቢተ ነቢያት፤                                          
ሕግ ሳይሠራ በፊት በሕገ ልቡና ዘመን፥እግዚአብሔር፡- ወዳጆቹን እንደመረጠና ከወዳጆቹም ጋር እንደነበረ የታወቀ ነው።ሄኖክን ከዓይነ ሞት ሰውሮ ወስዶታል።ዘፍ፡፭፥፳፬።ኖኅን  ጽድቁን ከመሰከረለት በኋላ ከጥፋት ውኃ ሰውሮታል።ዘፍ፡፯፥፩።ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-“ኖኅም ስለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፤ቤተሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላት መርከብን ሠራ፤በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፤በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። ” ብሏል።ዕብ፡፲፩፥፯።አብርሃምን፥ይስሐቅን እና ያዕቆብን የመረጠ፥የእነርሱም አምላክ እኔ ነኝ፥ያለ እግዚአብሔር ነው።ዘጸ፡፫፥፮።በአዲስ ኪዳንም ሕያዋን ብሎአቸውል።፳፪፥፴፪፣ዕብ፡፲፩ ፥፰።ሐዋ ርያው ቅዱስ ያዕቆብ ይኸንን ይዞ፥“አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊ ያው ባቀረ በው ጊዜ፥በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር፥ በሥ ራውም እምነቱ እንደመላችና ፍጽምት እንደሆነችም ታያለህን? መጽሐፍ፡-አብርሃም በእግዚአብ ሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቆጠረለት የሚለው ተፈጸመ፤የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፤”ብሏል። ያዕ፡፪፥ ፳፩።አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ለሞት አሳልፎ በመስጠቱ፥ተቀዳሚና ተከታይ የሌለ ውን አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ለሰጠ ለእግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖአል።ዮሐ ፡፫፥፲፮።ይስሐቅም ለመታረድ በመታዘዙ፥ ለባህርይ አባቱ ለአብ፥ ለመስቀል ሞት ለታዘዘ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ለመሆን በቅቶአል።ፊል፡፪፥፰።                                       
እግዚአብሔር፡-ሕገ ኦሪትን እስከ አምልኰ ሥርዓቱ ሠርቶ የሰጠው ለሙሴ ነው። ሙሴም ፡-እግዚአብሔር የነገረውን እና ያሳየውን ሁሉ፥ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ኦሪት ዘዳግም ድረስ በአምስት መጻሕፍት ጽፎ አስተምሯል።በሥራው ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር።ዘጸ፡፫፥፲፪ ።ፊት ለፊትም ይነጋገረው ነበር።ዘኁ፡፲፪፥፰።ስለ ሕዝቡ ኃጢአት በሚማልድበ ትም ጊዜ፥ እግዚአብሔር፡-“እንደ ቃልህ (የምልጃ ቃልህን ተቀብዬ) ይቅር አልሁ፤”ይለው ነበር ። ዘኁ፡፲፬፥ ፳፩።ጌታ ችን ክብረ መንግሥቱን፥ምሥጢረ መለኰቱን በደብረ ታቦር በገለጠ ጊዜ፥ ሙሴን ከመቃብር አስነ ሥቶ በአጠገቡ አቁሞታል።ማቴ፡፲፯፥፫።ይህም የሆነው፥“ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር ያያል፤” ብሎ አስቀድሞ ስለ ተናገረለት ነው።ዘኁ፡፲፪፥፰።በደብረ ሲና ፊቱ የበራ ሙሴ፥በደብረ ታቦር ፊቱ እንደ ፀሐይ ለበራ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ፡-ሙሴ ግብጻዊውን ገድሎ እስራኤላዊውን ማዳኑ፥ኢየሱስ ክርስቶስ የዲያብሎስን ሥራ ገድሎ አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው። ዘጸ፡፪፥፲፪።በበትሩ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ማሻገሩ ደግሞ፥ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ባሕረ እሳትን ከፍሎ ነፍሳትን ለማሻገሩ ምሳሌ ነው ።ዘጸ፡፲፩፥፳፩። በዚህን ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገር፥ ለምሳሌ፡- በመሪነቱ፣በዳኝነቱ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው።ዘዳ፡፲፰፥፲፭፣የሐዋ፡፫፥፳፪፣ዕብ፡፫፥፩፤፰፤፱፤የሐዋ፡፯፥ ፴፭።ጌታችን በወንጌል፥ስለ ሙሴ ሲመሰክር፥“እኔ በአብ ዘንድ የምከስሳችሁ አይምሰላችሁ፤የሚከስሳችሁስ አለ፤እርሱም እናንተ ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ሙሴንስ አምናችሁት ቢሆን እኔንም ባመናችሁኝ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።ሙሴ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?” ብሎአል። ዮሐ፡፭፥፵፭፣ዘጸ፡፴፬፥፳፱-፴፭።ከትንሣኤውም በኋላ በኤማሁስ ጐዳና ላገኛቸው ለሉቃስና ለቀለዮጳ፥ ከሙሴና ከነቢያት፥ ከመጻሕፍትም ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን ተርጉሞላቸዋል።ሉቃ፡፳፬፥ ፳፯።                                                                    
ለቅዱሳን ነቢያት ለዓበይቱም ለደቂቃኑም ሀብተ ትንቢትን የሰጠ እርሱ ነው፤በመሆ ኑም የራቀውን አቅርቦ፥የረቀቀውንም አጉልቶ ስለገለጠላቸው፡-የሚያልፈውንም የሚመጣውንም በእ ርግጠኝነት ተናግረዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፥“ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ፥ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተና ገሩ።”ያለው ለዚህ ነው።፪ኛ፡ጴጥ፡፩፥፳።ለምሳሌ፡-ነቢዩ ኢሳይያስ፥“እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም (ወልድን) ትወልዳለች፥ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። . . . ሕፃን ተወልዶልና፥ወንድ ልጅም (ወልድም) ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ስሙም ድንቅ መካር፥ኃያል አምላክ፥የዘላለም አባት፥የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” በማለት፥ትርጓሜ የማያስፈልገው ደረቅ ትንቢት የተናገረው ለዚህ ነው።ኢሳ፡፯፥፲፬፣፱፥፮፣ማቴ፡፩፥፳፪።ስለዚህ ኦሪቱም ነቢያቱም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገሩ እናስተውላለን።ይኸውም ይታወቅ ዘንድ፥ፊልጶስ ናትናኤልን፡-“ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል።” ብሎታል ።ዮሐ፡፩፥፵፮።

2 comments:

  1. Kale Hiwot Yasemalin!

    ReplyDelete
  2. Kale Hiywot Yasemalin ENkuan Beselam Wede Dihire Geswo Temelesulin .. Egziabhere Yageliglot Zemenun Yebarklo

    ReplyDelete