Friday, September 11, 2015

የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) _ ክፍል አንድ፤

                                                                                                                                             
          ባሕረ ሐሳብ፡- ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው። ይኸውም በግዕዙሐሰበ-ቆጠረ፤ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ነው። ባሕረ ሐሳብ የሚያስተምረን በዓላትን እና አጽዋማትን (የጾም ወቅቶችን) ለማውጣት፡- የመደመርን፥ የመቀነስን እና የማባዛትን ስሌት ብቻ ሳይሆን፥ ሐሳበ ፀሐይን፣ ሐሳበ ወርኅን፣ ሐሳበ ከዋክብትን፣ ሐሳበ አበቅቴን፣ ወዘተጭምር ነው። ይህን ሁሉ አጠቃሎ የያዘ እንደ ባሕርም የሰፋ በመሆኑ የሐሳብ (የቁጥር) ባሕር ተብሏል። የዘመን አቆጣጠር፡- ፩ኛ፡- ለማኅበራዊ ኑሮ ጥቅም፤ ፪ኛ፡- የሃይማኖት ተግባሮችን ለማከናወን እንዲያገለግል ተፈጥሮአዊውን የወቅቶች ክፍፍል እርስ በርሳቸው የማመቻቸት ጥበብ ነው። እንደ ባሕር አዝዋሪትም መንገዱ፥ ጥልቀቱና ስፋቱ፥ ረዥምና ሰፊ በመሆኑ ባሕረ ሐሳብ የሚለው ስያሜ ይስማማዋል።                                 

        በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር (የጊዜ ቀመር) አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች የተከፈለ ዐሥራ ሦስት ወራት አሉት። ፩ኛ፡- ከሰኔ ፳፮ - መስከረም ፳፭ ክረምት ነው፥ ትርጉሙም የውኃ ዘመን ማለት ነው። ቅዱስ ያሬድ በድጓው፡- “ያርሁ ክረምተ በበዓመት፥ ይሰምዑ ቃሎ ደመናት፤ በየዓመቱ ክረምትን ያገባል፣ ደመናት ቃሉን ይሰሙታል፤በማለት ይህን ወቅት የሰጠን እግዚአብሔር መሆኑን ነግሮናል። ፪ኛ፡- ከመስከረም ፳፮ - ታኅሣሥ ፳፭ መፀው (መከር) ነው፤ በግዕዙ፡- “መፀወ - አበበ፣ አበባ ያዘ፣ አረገዘ፤ማለት ስለሆነ፥ የአበባ ወር፥ የአበባ ወቅት ነው። ቅዱስ ያሬድም መፀውን ከክረምት ጋር አጣምሮ፡- “ግሩም በሆነው ኃይልህ እንመካ ዘንድ አንተ ዘመናትን ሠራህ፥ ክረምትን ለዝናማት መፀውን ለአበቦች ሰጠህ፤ብሏል። ኩፋሌ፥፪፤ ኢዮብ፥፪፥፳፫፣ ኤር፥፭፥ ፳፬። ፫ኛ፡- ከታኅሣሥ ፳፮ -መጋቢት ፳፭ በጋ (ሐጋይ) ነው፤ የፀሐይ ሙቀት የሚበረታበት ስለ ሆነ ድርቅ የድርቅ ወራት ማለት ነው። መዝ፥ ፸፭፥፲፯፣ ዘካ፥፲፬፥፲፣ ዘፍ፥ ፰፥፳፪። በመጽሐፈ ሲራክም ላይ፡- “በየጊዜያቸውና በየቁጥራቸው አዝመራንና ክረምትን በጋን ለየ፤የሚል አለ። ሲራ፥ ፴፮፥፱። ፬ኛ፡- ከመጋቢት ፳፮ - ሰኔ ፳፭ ጸደይ (በልግ) ነው። በልግ ሆነ፥ ለመለመ  ማለት ነው። በልግ አብ ቃይ በሆነው የሀገራችን ክፍል የበልግ አዝመራ የሚዘራበት፥ በልግ አብቃይ ባልሆነው ክፍል  ደግሞ መሬቱ ለክረምት የዘር ወቅት የሚዘጋጅበት ጊዜ ነው። ሦስቱ ወቅቶች እያንዳንዳቸው ዘጠና ዘጠና ቀናት ሲኖራቸው ክረምት ግን ጳጉሜን ጨምሮ ዘጠና አምስት ቀናትን ይዟል።                                              
                    የአሥራ ሦስቱ ወራት ስያሜና ትርጉም፤                                                        
       ሁሉም የኢትዮጵያ ወራት ራሱን የቻለ ትርጉም አላቸው፥መነሻቸውም መድረሻቸውም ነገረ እግዚአብሔር ነው፥እንደ ፈረንጆቹ ከጣዖት ጋር የተያያዘ አይደለም። ፩ኛ፡-መስከረም፡-“መስየ + ክረምትየሁለት ቃላት ጽምረት ነው፤ ትርጉሙም፡-“ምሴተ ክረምት(የክረምት ምሽት፣ የክረምት ማለቂያ)” ማለት ነው። በመስከረም ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታቸው ርዝመት ፲፪ ሰዓት ሲሆን፥ የሌሊታቸው ርዝመት እኵል ፲፪ ሰዓት  ነው። ፪ኛ፡-ጥቅምት፡- “ጠቀመ - ገነባ፤ከሚለው ግስ የወጣ  ነው። ገበሬው አዝመራውን በቡቃያነቱ ቀን ቀን ከብቶች እንዳይሰማሩበት፥ ሌሊት ሌሊት ደግሞ አራዊት እንዳይፈነጩበት ዙርያውን የሚያጥርበትና የሚገነባበት አንድም የታጠረውን ወይም የተገነባውን የሚያጠባብቅበት ወቅት ነው።በጥቅምት ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታቸው ርዝመት ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ሲሆን፥ የሌሊታቸው ርዝመት ፲፫ ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ነው። ፫ኛ፡- ኅዳር፡- “ኀደረ - አደረ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው። ይኸውም ገበሬው እግዚእብሔር ለፍሬ ያበቃለትን አዝመራ፥ ቤቱን ትቶ፣ ከዱር አድሮ የሚጠብቅበት ወቅት ስለሆነ ነው። በኅዳር ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው የመዓልታቸው ርዝመት ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ሲሆን፥ የሌሊታቸው ርዝመት ፲፬ ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ነው። ፬ኛ፡-  ታኅሣሥ፡-“ኀሠሠ - ፈለገ፤”  ከሚለው ግስ የወጣ ነው። አዝመ ራው ተሰብስቦ ወደ ጎተራ የሚገባበትና የሰው ፍላጐት የሚሟላበት ወር ነው። የሰውን ፍላጐት የሚያሟላው ደግሞ እግዚአብሔር ነው። በታኅሣሥ ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታ ቸው ርዝመት ሰዓት ሲሆን፥ የሌሊታቸው ፲፮ ሰዓት ነው። ፭ኛ፡- ጥር፡- “ጠየረ - በረረ፣ ከነፈ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው። ምሥጢ ሩም ምጥቀት፣ ርዝመት ማለት ነው። ይህም ከጥቅመ ሰናዖር (ከባቢሎን ግንብ) ጋር የተያያዘ ነው፤ ፭ሺ፬፻፴፫ ክንድ ከሁለት ስንዝር የሆነው የባቢሎን ግንብ ለአርባ ዓመታት ሲሠራ ቆይቶ ጥር ሰባት ቀን ሥላሴ አፍርሰውታል። ኩፋሌ፡፲፥፲፩፣ ዘፍ፡፲፩፥፩። በጥር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታ ቸው ርዝመት ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ሲሆን፥ የሌሊታቸው ርዝመት ፲፬ ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ነው። ፮ኛ፡-የካቲት፡-“ከተተ-ሰበሰበ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው።ከቲት ብሎ መከትከት፣ ማድቀቅ፣ መውቃት፣ ማምረት፣ መሰብሰብ፤ ይላል። የመከር ጫፍ፥መካተቻ፥ የበልግ መባቻ ማለት ነው። በየ ካቲት ወር ውስጥ የሚገኙ ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታቸው ርዝመት ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ሲሆን፥የሌሊታቸው ርዝመት ፲፫ ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ነው። ፯ኛ፡-መጋቢት፡-“መገበ - መገበ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው።በዚህ ወር የመዓልቱና የሌሊቱ ምግብና እንደ መስከረም እኵል ይሆናል።በዚህን ጊዜ መዓልቱ ፲፪ ሰዓት ሌሊቱም ፲፪ ሰዓት ነው። በሌሎቹ ግን ከላይ እንዳየነው ፥ ቀጥለንም እንደምናየው፥ መዓልቱ ወይም ሌሊቱ ይረዝማል፤ ለምሳሌ፡- በሀገራችን በገና ሰሞን  ቀኑ ቶሎ ይመሻል፥ ምክንያቱም መዓልቱ አጥሮ ሌሊቱ ስለሚረዝም ነው። ፰ኛ፡-ሚያዝያ፡-“መሐዘ-ጎለመሰ፥ ጎበዘ፥ አደገ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው። ልጆች አድገው ለሚዜነት የሚበቁበትን ዕድሜ ያመለክታል። ሚዜ፡- የሙሽራ ወዳጅ፥ ባለሟል፥ ባልንጀራ፥አብሮ አደግ፥ እኩያ፥ አምሳያ፥ ጓደኛ ማለት ነው። አንድም መሐዘ፡- ጎለመሰ፥ ጎበዘ፥ አደገ፥ ሚስት ፈለገ ማለት ነው። በሀገራችን ሚያዝያ የሠርግ ወር ነው። በሚያዝያ ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታቸው ርዝመት ፲፫ ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ሲሆን፥ የሌሊታቸት ርዝመት ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ነው። ፱ኛ፡- ግንቦት -“ገቦ-ጐን፣ አጠገብ፤ከሚለው ስም የወጣ ነው። ትርጉሙም ገቦ ክረምት (የክረምት ጐን፣ የክረምት አጠገብ፣ለክረምት የቀረበ)ማለት ነው። በግንቦት ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓል ታቸው ርዝመት ፲፬ ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ሲሆን፥የሌሊታቸው ርዝመት ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ነው።፲ኛ፡-ሰኔ፡-“ሰነየ - አማረ፣ ተዋበ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው። ይህም፡-በብዙ ድካም ታርሶና ተቆፍሮ የለሰለሰው የእርሻ መሬት ሙሉ በሙሉ በዘር ተሸፍኖ ማማሩን እና መዋቡን የሚያመለክት ነው። በሰኔ ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታቸው ርዝመት ፲፮ ሰዓት ሲሆን፥ የሌሊታቸው ርዝመት ፰ሰዓት ነው። ፲፩ኛ ሐምሌ፡-“ሐመለ - ለመለመ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው። የሚያመለክተውም በወርኃ ሰኔ ተዘርቶ የነበረው ዘር በቅሎ ቅጠል ማውጣቱን ነው። ትርጉሙም የቅጠል ወር ማለት ነው። በሐምሌ ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታቸው ርዝመት ፲፬ ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ሲሆን፥ የሌሊታቸው ርዝመት ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ነው። ፲፪ኛ፡-ነሐሴ፡-“ነሐሰ - ሠራ፣ገነባ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው። ናሕስ፡-ሲል ደርብ፥ ሰገነት፥ ፎቅ፥ የግንብ ጣራ፥ከበላይ ያለ ማለት ነው።ለልብስ ሲሆን ደግሞ የልብስ ዘርፍ፣ ጫፍ፣ ክፈፍ ማለት ይሆናል። በመሆኑም ነሐሴ፡-ለዓመቱ ወራት ጫፍ፣ ዘርፍ፣ክፈፍ ነው።በነሐሴ ወር ውስጥ የሚገኙት ዕለታት እያንዳንዳቸው፥ የመዓልታቸው ርዝ መት ፲፫ ሰዓት ከ፳ ደቂቃ ሲሆን፥ የሌሊታቸው ርዝመት  ሰዓት ከ፵ ደቂቃ ነው። ጳጉሜን ማለት ደግሞ ትርፍ ማለት ነው።                                                                                                                     
                  የፈረንጆቹ የወራት ስያሜ የመጣው ከየት ነው?                                                       
      የፈረንጆቹ የወራት ስያሜ የመጣው ከጣዖታትና ከግለሰቦች ስም ነው። ለአብነት ጥቂቶቹን እንመለከታለን። ፩ኛ፡-january (ጃንዋሪ)-janu's Month(የበር አምላክ)ተብሎ ከሚታ መን ጣኦት የመጣ ነው።፪ኛ፡-February(ፌብሩዋሪ)-Februa's Month ስርየትን ይሰጣል ተብሎ ይታመንበት ከነበረ ጣዖት የመጣ ስም ነው። ፫ኛ፡-March(ማርች) - Mars Month የጦርነት አምላክ ተብሎ ከሚታመን ጣዖት የመጣ ስም ነው። 4ኛ፡-April (አፕሪል) - Aphro dite's Month የፍትወትና የውበት አምላክ ተብላ ከምትታመን ጣዖት የመጣ ስም ነው።፭ኛ፡-june(ጁን)-Juno's Month ጋብቻን የምታሳካና ሴቶችንም ጥሩ ታደርጋለች ተብላ ትታመን ከነበ ረች ጣዖት ስም የመጣ ነው። ፮ኛ፡-July(ጁላይ) - Juliu's Month የንጉሡ የጁሊየስ ቄሣር መታሰቢያ ነው። ፯ኛ፡-August(ኦገስት) - August's Month የንጉሡ የአውግስጦስ ቄሣር መታ ሰቢያ ነው።                                                                                                                         
                የሰባቱ ዕለታት ስያሜዎች፤                                                                                                                              
       የሀገራችን የሰባቱ ዕለታት ስያሜዎች፥ እግዚአብሔር በስድስቱ ዕለታት ሃያ ሁለቱን ፍጥረታት ፈጥሮ በሰባተኛዋ ዕለት ከማረፉ ጋር የተያያዘ ነው። ዘፍ፥፩፥፩-፴፩።፩ኛ፡-እሑድ፡-“ አሐደ -አንድ አደረገ፥የመጀመሪያ ሆነ፤ከሚለው ግስ የወጣ ነው። በመሆኑም፡- እግዚአብሔር ፍጥረታትን አንድ ብሎ መፍጠር የጀመረባት ዕለት እሑድ ተብላለች። ፪ኛ፡-ሠኑይ(ሰኞ)- “ሠነየ - ሁለት አደረገ፤ማለት ነው።ይህም ለፍጥረት ሁለተኛ ቀን ማለት ነው። ፫ኛ፡-ሠሉስ (ማክሰኞ)- “ሠለሰ - ሦስት አደረገ፤ከሚለው የወጣ ነው። ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን ማለት ነው።፬ኛ፡-ረቡዕ፡- “ረብዐ - አራት አደረገ፤ከሚለው የወጣ ነው። ለፍጥረት አራተኛ ቀን ማለት ነው። ፭ኛ፡- ሐሙስ፡-“ሐመሰ - አምስት አደረገ፤ከሚለው የወጣ ነው። ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ማለት ነው። ፮ኛ፡-ዓርብ፡- “ዓረበ - ተካተተ፤ ከሚለው የወጣ ነው።እግዚአብሔር ፍጥረታትን በዕለተ እሑድ መፍጠር ጀምሮ ያካተተው ወይም የፈጸመው በዕለተ ዓርብ በመሆኑዓረበከሚለውዓርብየሚለው ስም ወጥቷል። ፯ኛ፡-ቅዳሜ፡-“ቀደመ - ቀደመ፣ፊት ሆነ፣ላቀ፣ጀመረ፤ከሚለው የወጣ ነው። በአዲስ ኪዳንሰንበተ ክርስቲያንተብላ ከተሰየመችው ከእሑ ድ አስቀድማ በዘመነ ኦሪት የነበረችሰንበተ አይሁድበመሆኗ ቅዳሜ ተብላለች። ይኸውም ቀዳሚት ሰንበት እንደ ማለት ነው።                                                          
                                 
ቅዱስ ድሜጥሮስ፤                                                                                                     
       ቅዱስ ድሜጥሮስ አባቱ አርማስቆስ ይባላል፣ልዕልተ ወይን ከምትባል ከአጎቱ ልጅ ጋር በአንድ ቤት አድገዋል። የነበሩበት ዘመን አሕዛብ የበዙበት፥ ክርስቲያኖች ግን እጅግ ያነሱበት ዘመን ነበር፤ በዚህም ምክንያት ሕንፃ ሃይማኖት ፈርሶ ከአሕዛብ ወገን ከሚያገባ ይልቅ ሕንፃ ሥጋ  ፈርሶ ክርስቲያን ዘመዱን ቢያገባ ይሻላል ብለው የአጎቱን ልጅ አጭተው ሠርግ አደ ረጉለት።በመሸም ጊዜ ሥርዓተ መርዓት ወመርዓዊ ያድርሱ ብለው ትተዋቸው ሄዱ። ሙሽሪ ትም፡- “ይህን ያደረግኸው የእርሷ ዝምድና አይረባኝም፥ አይጠቅመኝም ብለህ ነው?” አለችው። እርሱም፡-“የወላጆቼን ፈቃድ ለመፈጸም ብዬ እንጂ ዝምድናሽን ንቄ አይደለም፥ አሁንስ ፈቃድሽ ከሆነ ለምን አንተወውም?” አላትና ለመተው ተስማሙ። ከዚህም አያይዘው፡-“በገሃድ የተለያየን እንደሆነ እኔን ለሌላ ያጋቡኛል፥ አንቺንም ለሌላ ይድሩሻል፥ ስለዚህ የተጋባን መስለን አብረን እንኑር፤ ባንወልድ እንኳ መክነው ነው ይሉናል እንጂ አይጠረጥሩንም፤አላት። በአንድ አልጋ፥ በአንድ ምንጣፍ እየተኙ ለአርባ ስምንት ዓመታት በንጽሕና ኖሩ። ቅዱስ ሚካኤል፡- ክንፉን አልብሷቸው አድሮ ጧት ጧት ሲሄድ በነጭ ርግብ አምሳል በግልጥ ያዩት ነበር።                                                                                                                                                   
       ቅዱስ ድሜጥሮስ ገበሬ ነበርና የወይን አትክልቱን ሲጐበኝ ያለወቅቱ አብቦ ያፈራ ወይን አግኝቶ ለልዕልተ ወይን ሰጣት። እርሷ ግን፡-“ይኸንን እኔ ልመገበው አይገባኝም፥ ይልቅስ በመሶበ ወርቅ አድርገህ ለሊቀ ጳጳሱ ውሰድለትና ተመ ረቅ፤” አለችው። ሊቀ ጳጳሱ ዩልያኖስ አርጅቶ ስለነ በር ከእርሱ በኋላ በቅዱስ ማርቆስ መንበር የሚተካውን እግዚአብሔር እንዲገ ልጽለት ከሕዝቡ ጋር ጾም ጸሎት ይዞ ነበር። መልአከ እግዚአብሔርም ተገልጦ፡- “ያለወቅቱ ያፈራ የወይን ዘለላ የሚያመጣልህ ከአንተ በኋላ የሚተካው እርሱ ነው፤አለው። ይህንንም ለሕዝቡ ነገራቸው። በማግስቱም ወንጌል ዘርግቶ ሲያስተምር ቅዱስ ድሜ ጥሮስ በመድረሱ፡-“ያልኳችሁ ሰው ይህ ነው፤ አይሆንም ስለሚላችሁ ቢሆን በውድ፥ ካልሆነም በግድ ሹሙት፤አላቸው። ቅዱስ ድሜጥሮስ የሆነውን ሁሉ ሳያውቅ እጅ ነስቶ በቆመ ጊዜ፡-“የእግዚአብሔር ማደሪያ እንዴት ነህ?”አለው። እርሱም፡-“እግዚአብሔር ይመስገን፤” ብሎ ወይኑን አበረከተ፤ ሊቀ ጳጳሱም ድሜጥሮስን ባርኮት ዕለቱኑ ዐረፈ ።                                                                                   
      ቅዱስ ድሜጥሮስ ከቀብር በኋላ ለመሄድ ሲነሣ ሕዝቡአትሄድም፤ብሎ ያዘው። የተማርኩ ሰው አይደለሁም፥ በጋብቻ እንጂ በድንግልና አልኖርኩም፥ ሕጉን ሥርዓቱን አላውቅም፤ቢላቸውም፡-“የአባታችን ቃል አይታበልም፤ብለው አልሰሙትም። እንግዲያውስ እናንተ አስተ ምሩኝ፤ቢላቸው፡-“አባታችን አንቀጸ ብፁዓንን እና አንቀጸ አባግዕን (ማቴ፥፭ን እና ዮሐ፥፲ን)ተርጕሞ ያስተምረን ነበር፤ብለው ነገሩት። መልሶም፡-“እንኳንስ ትርጓ ሜውንና ምሥጢሩን ንባቡን እንኳ አላውቅምና መጽሐፉን አምጡ ልኝ፤አላቸው። ሊያመጡለት በሄዱበት ቅጽበት የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾለታል።                                                                                                                                                                                  
      ቅዱስ ድሜጥሮስ ቀድሶ በሚያቆርብበት ጊዜ የሕዝቡ ኃጢአት ስለሚገለጥለት፡-“አንተ በቅተሃል ቁረብ፥ አንተ ግን አልበ ቃህም ተመለስ፤ይላቸው ነበር። የበቁትን ብርሃን ለብሰው፥ መላእክት ከብበዋቸው ያያቸዋል፤ ያልበቁትን ግን ጨለማ ለብሰው፥ የጨለማ መልእክተኞች ከብበዋቸው ያያቸው፥ ንስሐ እንዲገቡም ይመክራቸው ነበር። እነርሱ ግን በጠላትነት ተነሥተ ውበት፡- “እርሱ ደግሞ ማን ሆኖ ነው የሚከለክለን? አግብቶ ሳለ እንደ ድንግል ሊቀ ጳጳስ መሆኑ ሳያንሰው ቁርባን ይከለክለናል?” እያሉ ያሙት ጀመር። ዓለም እንዲህ ነው፥ በመጀመሪያ፡- “ቅዱስ፥ ቅዱስእንዳላለ፥ ድካሙ ሲነገረው ሰውን የሚከስበት ኃጢአት ይፈልጋል። በዚህን ጊዜ መልአክ ተገልጦለት፡-“ሕዝቡ በሐሜት እየተጐዳ ነውና ራስህን ግለጥላቸው፤አለው። ቅዱስ ድሜጥሮስም ሕዝቡን ሰብስቦ ደመራ ካስደመረ በኋላ በእሳቱ ላይ ቆሞ ጸለየ፤ እርሷንም ጠርቶ የእሳቱን ፍም በእጁ እያፈሰ በቀሚሷ ካስያዛት በኋላ ሕዝቡን ሦስት ጊዜ ዞረች፤ ልብሷም አካሏም አልተቃጠለም። ከዚህ በኋላ በንጽሕና በድንግልና የመኖራቸውን ምሥጢር ነገራቸው። ሕዝቡም ከእግሩ ስር ወድቀው፡-“ኃጢአታ ችንን አስተስርይልን፧አሉት። እርሱም ይቅር ብሎ፥ ናዝዞ አስተሰረ የላቸው። በዚህን ጊዜ ኃጢአታቸው እንደ ሸማ ተጠቅልሎ ከፊታቸው ሲወድቅ አይተውታል ከቅዱስ ማርቆስ ጀምሮ ሲቆጠር ፲፪ኛ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ነው።                                                                              
                                 የቅዱስ ድሜጥሮስ ምኞት፤                  

       ቅዱስ ድሜጥሮስ፡- 1/የነነዌ ጾም፣ የዐቢይ ጾም እና የሐዋርያት ጾም መግቢያ ከሰኞ፤ 2/የደብረ ዘይት፣ የሆሣዕና፣ የትንሣኤ እና የጰራቅሊጦስ በዓል ከእሑድ፤ 3/ርክበ ካህናት እና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ ባይወጣ እያለ ይመኝ ነበር። መልአኩም መጥቶ፡- “በምኞት ብቻ ይፈጸማልን? ከመዓልቱ ሰባት ሱባዔ፣ ከሌሊቱ ደግሞ ሃያ ሦስት ሱባዔ ግባና ይገለጽልሃል፣ ይህንንም በሠላሳ በሠላሳ ገድፈህ /አጣፍተህ/ በተረፈው ውጤት ታገኘዋለህ ብሎታል። የመዓልቱን ሱባዔ አሳጥሮ የሌሊቱን ያስረዘመው ያለ ምክንያት አይደለም። ቅዱሱ፡- በመዓልት የተጣላ ሲያስታርቅ፣ የታመመ ሲጠይቅ፣የሞተ ሲቀብር፣ ሲፈርድ፣ ሲያስተምር፣ ቤተ እግዚአብሔርን ሲያገለግል ስለሚውል ሰዓት ያንሰዋል፤ በሌሊት ግን ይህ ሁሉ የለበትምና ለዚህ ነው። አንድ ሱባዔ ሰባት  ነው፣ በዚህ መሠረት የቀኑ ሰባት ሱባዔ በሰባት ሲባዛ አርባ ዘጠኝ ይሆናል ፣ ይህንንም በሠላሳ ስንገድፈው ወይም ስናጣፋው አሥራ ዘጠኝ ይቀራል። ይኸንንመጥቅዕበለው ብሎታል። መጥቅዕደወል ማለት ነው፣ ደወል ሲደወል የሩቁም የቅርቡም እንደሚሰበሰብ በመጥቅዕም በዓላትና አጽዋማት ይሰበሰባሉ። የሌሊቱን ሃያ ሦስት ሱባዔ ደግሞ በሰባት ስናባዛው አንድ መቶ ስድሳ አንድ ይሆናል፤ ይህንንም አምስት ጊዜ በሠላሳ ስንገድፈው/ስናጣፋው/አሥራ አንድ ይቀራል፤ ይኸንን አበቅቴ በለው ብሎታል። ጥንተ አበቅቴ የተባለው ይህ ነው። አበቅቴ ማለት፡- የወር ሕጸጽ/ጉድለት/፣ ሠርቀ ሌሊት፣ ሠርቀ ወርኅ/የጨረቃ ምላትና ጉድ ለት/ የሚታወቅበትና የሚገለጽበት ነው። ሠርቅ ማለት፡- በቁሙ ሲተረጐም፥ መውጫ፣ መገለጫ፣ መባቻ፣ የወር መጀመሪያ ማለት ነው። ምንግዜም ቢሆን የመጥቅዕ እና የአበቅቴ ድምር ከሠላሳ አይበልጥም ከሠላሳም አያንስም። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ የአጽዋማትና የበዓላትኢየዓርግ እና ኢይወርድተገልጾለት በሰባት አዕዋዳት አውዶ፣ በአንድ ዐቢይ ቀመር ወስኖ፣ በማኅተም አትሞ፡-በሮም፣ በሶርያ፣ በአንጾኪያ እና በኢየሩሳሌም ለነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት ልኰላቸዋል። እነርሱም ሐዋርያት በዲድስቅልያ ካስተማሩት ጋር አንድ ሆኖ ቢያገኙት ተቀብለው አስተምረውታል። ሠለስቱ ምዕትም ጉባዔ ሠርተው አስተምረውታል። ቅዱስ ድሜጥሮስ ያረፈው ባሕረ ሐሳብን ከተናገረ በኋላ ነው።

No comments:

Post a Comment