Sunday, August 2, 2015

ተሀድሶ፤(ክፍል ፫

                                     መስቀል፤                                  
      መስቀል፡-ድኅነታችን የተፈጸመበት ነው፤ዮሐ፡፲፱፥፴። የሥጋና የነፍስ እርግማን የተወገደበት ነው፤ዘዳ፡፳፩፥፳፫፣ ገላ፡፫፥፲፫። ዲያብሎስ የተሸነፈበት ነው፤ኤፌ፡፪፥፲፮። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነው፤ ኤፌ፡፪፥፲፭። እግዚአብሔር ለሰው ያለው ፍቅር የተገለጠበት ነው፤ ዮሐ፡ ፫፥፲፮፣፩ኛ፡ዮሐ፡፬፥፱። በሰውና በእግዚአብ ሔር መካከል እርቅ የተፈጸመበት ነው፤ ሮሜ፡፭፥፲፣ኤፌ፡፪፥፲፮። የገነት በር የተከፈተበት ነው፤ሉቃ፡፳፫፥፵፫። የይቅርታ ዙፋን ነው፤ሉቃ፡፳፫፥፴፬። የሰላም አደባባይ ነው፤ ኤፌ፡፪፥፲፯። ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ከጌታችን ከኢየሱስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፤ ”ያለው ለዚህ ነው። ገላ፡፮፥፲፮። መስቀል የእግዚአብሔር ኃይል የተገለጠበት፥ እየተገለጠበትም የሚኖር መሆኑን ተናግሯል፤ ፩ኛቆሮ፡፩፥፲፰። ቅዱስ ዳዊትም፡-የእግዚአብሔር ወዳጆች፥ ከሰይጣን ጦርነት የሚያመል ጡበትና የሚድኑበት ኃይል ያለው ምልክት መሆኑን አስቀድሞ በትንቢት ተናግሮ ነበር። መዝ፡፶፱፥፬።“እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን፤”በማለትም ለመስቀሉ ስግደት እንደሚገባ ተናግሯል። መዝ፡፩፴፩፥፯። ምክንያቱም የጌታ እግሮች በመስቀል ችንካር ላይ ቆመው ውለዋልና።
ያዕቆብ በጣም የሚወደውን ልጁን ዮሴፍን ከባረከው በኋላ፥የልጅ ልጆቹን ደግሞ፡-“አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ፥እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ስሜም፥የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፥ይብዙ ።”እያለ እጆቹን አመሳቅሎ ባርኰአቸዋል። ዘፍ፡፵፰፥፲፭።እኛም ክርስቶስ በደሙ በቀደሰው መስቀል እንባርካለን፥እንባረካ ለንም።ያዕቆብ በግንባሩ ወደ በትሩ ጫፍ ተጠግቶ ይሰግድ እንደነበረ፥ግንባራችንን ወደ መስቀሉ አስጠግተን እንሳለማለን፥ እንሰግዳለን። ዕብ፡፲፩፥፳፩። ሙሴ፡-እጆቹን ግራና ቀኝ ዘርግቶ፥የመስቀል ምልክት ሠርቶ በሚጸልይበት ጊዜ፥እስራኤል ኃይል አግኝተው ጠላቶቻቸውን ያሸንፉ ነበር፤ደክሞት በሚያሳርፍበት ጊዜ ደግሞ ይሸነፉ ነበር። በዚህ ምክንያት አሮን እና ሖር እስኪመሽ ድረስ እጆቹን ደገፉት፤እስራኤልም አሸነፉ። ዘጸ፡፲፯፥፲፪። እኛም በመስቀሉ ኃይል በአማሌቅ የሚመሰሉ አጋንንትን ድል እናደርጋለን። ሥዕል፤                                      
     የቤተክርስቲያን ሥዕላት የተቀደሱ ናቸው፤እግዚአብሔርን ለማምለክ የምንገለገልባቸው የቤተ መቅደስ ንዋያት (ዕቃዎች) ሁሉ፥በቅብዓ ሜሮን ተቀብተው እንደሚቀደሱ፥ቅድስተ ቅዱሳንም እንደሚሆኑ ለሙሴ የነገረ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ፡፴፥፳፪-፴፰። የኪሩቤልንም ሥዕሎች ሠርቶ፥በቤተ መቅደስ ውስጥ ከታቦቱ አጠገብ እንዲያስቀምጥ፥ በዚያም ላይ አድሮ እንደሚያነጋግረውም ነግሮታል። ዘጸ፡፳፭፥፲፰-፳፪። “ሙሴም ወደ መገናኛው ድንኳን እርሱን (እግዚአብሔርን)  ለመነጋ ገር በገባ ጊዜ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ፥ ከኪሩቤልም (ከሥዕሎቹ) መካከል ድምፁ ሲናገ ረው ይሰማ ነበር፤እርሱም ይናገረው ነበር።”ይላል። ዘኁ፡፯፥፹፱። ጠቢቡ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤተ መቅደሱን በሠራ ጊዜ፥ሥዕለ ኪሩብንም ሠርቶ በቅድስተ ቅዱሳን አስቀምጧል። እግዚአብሔርም ወድዶ፥ፈቅዶ ተቀብሎለታል።፪ኛ፡ ዜና፡፯፥፲፩-፴፮። ለቤተክርስቲያን ሥዕሎች መነሻ መሠረት፥ ይህ የእግዚአብሔር ትምህርት ነው። አባቶቻችን ከቅዱሳት መጻሕፍት ያገኙትን እና በራዕይ የተገለጠላቸውን በሥዕል አስቀምጠውልናል። መጽሐፍ ቅዱሱም የሚያስተምረን ይኸንኑ ነው። ለምሳሌ፡-ነቢዩ ኢሳይያስ፥ እግዚአብርሔር በንጉሥ አምሳል፥ከሱራፌል ጋር የተገለጠለትን መገለጥ  በሥዕላዊ መግለጫ ጽፎታል። ኢሳ፡፮ቁ.፩-፫። ነቢዩ ሕዝቅኤልም እግዚአብሔር መንበሩን ከሚሸከሙ ኪሩቤል ጋር የተገለጠለትን መገለጥ በሥዕላዊ መግለጫ ጽፎታል። ሕዝ፡፩፥፩-፳፰። ነቢዩ ዳንኤልም በበኩሉ ስለተገለጠለት መልአክ የጻፈው ጽሑፍ ሥዕላዊ ነበር። ዳን፡ ፲፥፭። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌ ላዊ ደግሞ፡- “ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥እነሆም አምባላይ ፈረስ፥የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥በጽድቅም ይፈርዳል፥ይዋጋልም። ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፏል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሏል።በሰማይም ያሉ ጭፍራዎች ነጭና ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።”በማለት በራዕይ የተገለጠለትን ጽፎልናል። ራዕ፡፲፱፥፲፩-፲፬። በቤተክርስቲያናችን ቅዱሳን ሰማዕታትን በፈረስ አስቀምጠን የምንስለው ለዚህ ነው።  
      ቅዱሳት ሥዕላት ምልክት ብቻ አይደሉም፥ከሥዕላቱ ባለቤቶች በረከት የሚገኝባቸው ናቸው። በመሆናቸውም ክብርና ስግደት የሚገባቸው ናቸው። መናፍቃን አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት የእግዚአብሔርን ሥራ ከአጋንንት ሥራ ያሳን ሳሉ። አጋጋንንት በጣኦታት አድረው በምስላቸው ይናገራሉ።“የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ፥ለአውሬውም ምስል የማይሰ ግዱትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው።” ይላል።ራዕ፡፲፫፥፰። ጌታችን በወንጌል፡-በሐሰት“ ክርስቶስ ነን፥ነቢያት ነን፤”የሚሉ እንደሚመጡ ከተናገረ በኋላ፡-“ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” ብሏል። ማቴ፡፳፬፥፳፬።እንግዲህ ከሥልጣኑ የተሻረ፥ከማዕረጉ የተዋረደ ሰይጣን እንዲህ ካደረገ፥“የእግዚአብሔር ቅዱሳን በሥዕሎቻቸው ድንቅ ድንቅ ተዓምራት አያደርጉም፤”ማለት፥የሰይጣንን ሥራ ማስበለጥ፥ የእግዚአብሔርን ሥራ ደግሞ ማሳነስ ነው። እኛ ግን፥እንደ ቅዱስ ዳዊት፡-“አቤቱ፥ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፤...... እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤”እያልን እናመሰግነዋለን። መዝ፡፹፭፥፲፣ ።                           
                                            ጸበል፤                                                             በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፡- ገዳማት፥አድባርትና አብያተ ክርስቲያናት ባሉበት ሥፍራ ሁሉ፥ የጸበል ቦታዎች አሉ።የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን ብቻ ሳይሆኑ፥የእስልምና ተከታዮች ሳይቀሩ እየተጠመቁ ይፈወ ሳሉ። የውስጥ ደዌ የሆኑ ተሀድሶዎች (የውስጥ መናፍቃን)፥በፕሮቴስታን አንደበት ሲነገር የኖረውን ክህደት፥እንደ አዲስ፡-“ተርታ ውኃ ነው፥አያድንም፤”ይላሉ። ሕሙማን ሲፈወሱ በዓይናቸው እያዩ ይክዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃ ላይ እንደሚያርፍ ነው። ዘፍ፡፩፥፪። እንኳን ከደዌ መፈወስ፥ የእግዚአብሔር ልጆች እንኳ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ባረፈበት ውኃ ተጠምቀን ነው።“ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግ ሥት ሊገባ አይችልም፤”ይላል። ዮሐ፡፫፥፭።በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ሶርያዊው ንዕማን በዮርዳዮስ ጸበል ተጠምቆ ከለ ምጹ ተፈውሷል። የተቀደሰውንም አፈር ወደ አገሩ ወስዶ፥ለአፈሩ ሲሰግድ ኖሯል። ይኸንንም ያደረገው ነቢዩ ኤልሳዕን እስፈቅዶ ነው። ፪ኛ ነገ፡፭፥፩-፲፱። በወንጌል እንደተጻፈው፥ በቤተሳይዳ ጸበል እየተጠመቁ ብዙ በሽተኞች ይፈወሱ ነበር። “አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጠው ነበርና፤እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ (የተጠመቀ) ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር።”ይላል። ዮሐ፡፭፥፩-፬።ጌታም፡-ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለ ደውን ብላቴና፥በምራቁ አፈሩን ጭቃ ካደረገው በኋላ በሰሊሆም ጸበል ተጠመቅ ብሎታል። “ስለዚህም ሄዶ ታጠበ (ተጠመቀ)፥ እያየም መጣ፤”ይላል። ዮሐ፡፱፥፩-፯። የመስቀል ነገር ሲነሣ፡-“እንጨት ነው፤” ፥የጸበል ነገር ሲነሣ፡-“ውኃ ነው፤”፥የሥዕል ነገር ሲነሣ፡-“ወረቀት ነው፥ ጨርቅ ነው፤” ማለት የእግዚአብሔርን ኃይል መካድ ነው። የሙሴ በትር እንጨት ብትሆንም እግዚአብሔር ኃይሉን አሳድ ሮባት ባሕር እስከመክፈል ድረስ ብዙ ተአምራት አድርጋለች። (ዘጸአት ከምዕራፍ ፬ እስከ ፲፬)። የአሮን በትር የደረቀ እንጨት ብትሆንም የእግዚአብሔር ኃይል አድሮባት፥በቤተ መቅደስ ውስጥ፥ ለምልማ፣ አብባ፣ አፍርታ ተገኝታለች። ዘኁ፡ ፲፯፥፰፣ዕብ፡ ፱፥፬። የኤልያስ መጐናጸፊያ ጨርቅ ብትሆንም የእግዚአብሔር ኃይል ስላረፈባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሁለት ጊዜ ከፍላለች። ፪ኛ ነገ፡፪፥፯-፲፬። የኤልሳዕ ማሰሮና ጨው የእግዚአብሔር ኃይል ያደረበት በመሆኑ፥መርዛማው የኢያሪኮ ውኃ ተፈውሷል። ፪ኛ ነገ፡፪፥፲፱-፳፩። ከነቢያት ወገን ሚስቶች የሆነች፥ባሏ የሞተባት ሴት፥ የዘይት ማሰሮዋ ስለተባረከላት እንደ ውኃ ምንጭ ሆኖላታል። ፪ኛ፡ነገ፡፬፥፩-፯። የኤልሳዕ የእንጨት ቅርፊት የእግዚአብሔር ኃይል አድሮበት፥ከዮርዳኖስ ባሕር ውስጥ ብረቱን አውጥቷል። ፪ኛ፡ነገ፡፮፥፩፲-፯። የጌታ ልብስ ጨርቅ ቢሆንም ፲፪ ዓመት ሙሉ ደም ይፈሳት የነበረች ሴት ድናበታልች። “እነሆም ፥ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና፡- ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት።” ይላል። የሚያስፈልገው ማመን ብቻ ነው። በመሆኑም  እምነታችን ፍጹም ነው።ቅዱስ ጴጥሮስ፡- በአካሉ ጥላ እንኳ ይፈውስ ነበር። የሐዋ፡፭፥፲፭። ምእመናን፡- ከቅዱስ ጳውሎስ ልብስ እየቆረጡ በመውሰድ፥በጨርቁ እየተዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፤አጋንንትም እየጮኹ ይለቁ ነበር። እንግዲህ ልቡና ላለው ይህ ከበቂ በላይ ነው።የእግዚአብሔር ቸርነት፥የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፥አሜን።      

2 comments:

  1. Kale Hiwot Yasemalin!

    ReplyDelete
  2. አባታችን ቀሲስ ደጀኔ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ይህንን ብሎግ የሚያነብ ሁሉ ኢንተርኔት ለማይጠቀሙ እንዲደረስ የራሳችንን ስራ በመስራት አባቶቻችንን እናግዝ፡፡ በፊስ ቡክም ሆነ ወደ ሀርድ ኮፒ በበራሪ ወረቀት በመበተን እናግዛቸው እባካችሁ፡፡ ተኩላው ይሰራል፤ እኛ ዝም በለናል፡፡ እንበርታ ለእግዚአብሔር እራሳችንን እየሰጠን የሚለንን እየሰማን ታዛዦች እንሁን፡፡ አሁን የምንሰራበት እንጂ የምንቀልድበትና ዝም ብለን የምናልፍበት ዘመን አይደለምና፡፡

    ReplyDelete