Wednesday, July 22, 2015

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እና ትምህርታቸው፤ ክፍል-፯፤

   በእንተ አፍሪቃ ወኢትዮጵያ፤

አንድ ሕዝብ ወይም አንድ መንግሥት ራሱን ችሏል የሚባለው የፖለቲካ ነፃነት ሲኖረው ነው እየተባለ በዓለም ሸንጐ ይለፈፋል፥ይሰበካል።ይሁን እንጂ ይህ ዕድል ለሁሉ አልተገኘም። በማደግ ላይ ያሉ (ሦስተኛው ዓለም የሚባሉ) ብዙ አገሮች የፖለቲካ ነፃነት ቢኖራቸውም በኢኰኖሚ ደካሞች ስለሆኑ የእጅ አዙር አገዛዝ አልቀረላቸውም። ነፃነታቸውም ቢሆን ግማሽ ነው። ይልቁንም ከአፍሪካነታቸው ጋር የማይስማማ ከቅኝ ገዥ ዎቻቸው የወረሱት ብዙ የባህል ውጥንቅጥ ስላለባቸው፥ ከዚህ ሁሉ ለመላቀቅ በመጣር ላይ ይገኛሉ፤ ምናልባትም አንድ ቀን ካሰቡት ሊደርሱ ይችሉ ይሆናል የሚል የተስፋ ድምፅ ይሰማል።                                                         
ከዚህም ሁሉ ጋር፥ሲሆንም፡-በቅድሚያ ሊታሰብበት የሚገባው ደግሞ የሃይማኖቱ ነፃነት ጉዳይ ነው። አፍሪካ የጨለማ ክፍለ ዓለም ተብላ ትጠራ እንጂ ብዙ ታሪካውያን ሰዎች ተፈጥረውባታል።ብዙ የሃይማኖት ሰዎ ችም ነበሩባት፤ ነገር ግን ከጊዜ ብዛት፥ ከተተኪም መጥፋት የተነሣ ታሪኳ ሰርዶ እየለበሰ ሄደ።ሕዝቧም በልዩ ልዩ ቅኝ ገዦች ባህልና ሃይማኖት ስለተዋጠ ራሱን የማወቅ ችግር ገጠመው።                                                   
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር አንዷ ብትሆንም በሌሎቹ አፍሪካውያን ወንድሞቿ የደረሰው ግፍ አልደረሰባትም። ከሦስት ሺህ ዓመታት የበለጠ የነፃነት ዕድሜ ይቆጠርላታል። በዚህም የነፃነት ጉዞዋ ከባዕድ ያልተቀ ላቀለ አፍሪካዊ (ኢትዮጵያዊ) ባህል አላት፤ በሃይማኖትም በኩል በዘመነ ኦሪት ብሉይ ኪዳንን እንደተቀበለች ሁሉ ሐዲስ ኪዳንንም ከሁሉ አስቀድማ ተቀብላለች። ይህም ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላውን የአፍሪካን ሕዝቦች የሚያኰራ ነው።                                                                                             

ምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች አፍሪቃን እንደ ቅርጫ ሥጋ የተቀራመቷት ወንጌልን እናስተምራለን ብለው፥ ማለትም የበግ ለምድ ለብሰው ነው። ለምሳሌ፡-ደቡባዊት አፍሪካን ይዘው ወገኖቻችንን የሚያሰቃዩ ነጮች ለመጀ መሪያ ጊዜ የአፍሪካን መሬት የረገጡት በ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን፥ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባልነት የተለዩ የካልቢኒስት ሚሲዮናውያን ነበሩ። ወደ አፍሪካ ለመግባት ምክንያት ያደረጉትም ሃይማኖት ማስተማርን ነበር። ያን ጊዜ የበግ ለምድ ለብሶ ወደ አፍሪካ የገባው ተኵላ የብዙ አፍሪቃውያንን ደም እየመጠጠ እስካሁን አለ። አሁንም ቢሆን አፍሪቃን በየአቅጣጫው ቅኝ ግዛት ለማድረግ የሚጥሩ ጥቂቶች አይደሉም።ብዙዎችም አፍሪ ቃውያን እየተሸጡና እየተለወጡ ወደ ባዕድ አገር በመወሰድ፥ እነርሱ በባዕድ አገር እየኖሩ አገራቸው የባዕድ መኖሪያ ሆኖ ቀርቷል።ለምሳሌ ሰሜን አፍሪቃን ብንጠቅስ አባባሉን ያጐላዋል።                                                
ኢትዮጵያ ነፃነትዋን እና አንድነትዋን አክብራ አስከብራ የቆየችው፥ ለውጭ ወራሪም አልመች ያለችው፥በሃይማኖቷ እና በታሪኳ እየተከላከለች ነው።ማንኛውም የሃይማኖት ሰባኪ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ምክንያት አልነበረውም። በእርግጥ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ አደጋ ደርሶባታል፤ነገር ግን የደረሰባትን ሁሉ መከራ በትዕግ ሥት አሳልፋ ዛሬ ካለችበት ደርሳለች። ዛሬ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ዓለም ቢጓዝ በራሱ ስም የሚጠራ ፥በራሱ ትውፊትና ሃይማኖት የሚመራ ስለሆነ የበላይነት እንጂ ዝቅተኝነት አይሰማውም። ይህች አገር ከክርስትና በፊትም ሆነ በክርስትና ዕድሜዋ በሥልጣኔ በነፃነት ይልቁንም ደግሞ በፊደል እና በሥነ ጽሑፍ ከጥንታውያን ግብጾች እና ከግሪኮች ጋር የምትወዳደር ናት። እንዲያውም በሌላ ዓለም የጠፉ መጻሕፍት የሚገኙት በኢትዮጵያ ነው። ለምሳሌ፡-መጽሐፈ ሄኖክ፣ኵፋሌ (ኢዮቤልዩ የሚሉት)።                       
ይህችን ትንሽ መጽሐፍ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ታሪክ) ለመጻፍ ያነሣሣኝ ዋናው ምክንያት የሚከተለው ነው። በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. ለትምህርት ወደ ውጭ አገር በሄድሁበት ጊዜ ፥ብዙ ፈረንጆች፡- እኔንም ሆነ ጓደኛዬን የሚጠይቁን “የቅብጥ” የኮፕት ቤተክርስቲያን መነኰሳት ናችሁ ወይ? እያሉ ነበር። በትምህርት ገበታችንም ላይ እንዳለን ፥ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን፡- የቅብጥ ቤተክርስቲያን እያሉ ሲጠሯት በመስማቴ ኀዘን አደረበኝ። በመሠረቱ “ኮፕት፣ቅብጥ” ግብፅ ወይም ምስር ማለት ሲሆን “ሂኩፕታህ” በጥንት የግብፅ ቋንቋ ቤት ማለት ነው፤ ከሱ የወጣ ነው።ግሪኮች ግን “ሀ” ፊደል ስለሌላቸው “ኢጊፕቶስ” ወይም ኮፕት ይሉታል።እንግ ዲህ “ኮፕት”፡-የአገር ወይም የነገድ ስም ነው፥ ማለት ነው። ስለዚህ የግብፅ ክርስቲያኖች በአገራቸው፥በነገዳ ቸው የኮፕት ወይም የቅብጥ ክርስቲያኖች ይባላሉ። ዐረቦችም እል አቅባጥ ይሏቸዋል። የቃሉ ትክክለኛ ፍች ይህ ሳለ፥ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የቅብጥ ቤተክርስቲያን ብሎ መሠየም፥ ሀገረ ትውልድን የሚያቃውስ፥ ዜግነትን የሚደመስስ መስሎ ይታያል።                                                                     የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፡- ከቅብጥ ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን ብዙ ወርቅ እየከፈለች እያስመጣች ለ፩ሺ፮፻ ዓመታት መቆየቷን አንክድም። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ፩፻፲፩ ጳጳሳት መጥተዋል።በዚህ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በእኩልነት ተዐቅቦ አብረው ኑረዋል። የሃይማኖት ቀኖናቸውና ሥርዓታቸው አንድ ነው። በዚህ ዓይነቱ ግንኙነት፥የግብፅና የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆኑ፥ከነሱ ጋር የአርመን፣የሶርያና የህንድ አብያተ ክርስቲያናትም አንድነት አላቸው። እነዚህም አምስቱ አብያተ ክርስቲያናት ተጠቃለው፡-የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Churchs) ይባላሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በዶግማና በቀኖና አንድ ይሁኑ እንጂ፥በሀገረ ስብከት የየራሳቸው ድርሻ ስላላቸው፥ ባንዱ ስም ሌላው አይጠራበትም። ስለዚህ በስማችን ሌላ እንዲ ጠራበት አንፈልግም፥ እኛም በሌላ ስም መጠራት አንሻም።                                                                
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከታቻቸው ስጦታዎች ብዙ ናቸው። ከነዚህም፡-ሙሉ ትምህርት፥ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ፥ሥነ ጽሑፍ ከነጠባዩ፣ ከነሙያው፥ ኪነ ጥበብ በየዓይነቱ፥ ሥነ ጥበብ በየመልኩ፥ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ፥እምነት ከነፍልስፍናው፥ነፃነት ከነክብሩ፥አንድነት ከነጀግንነቱ፥ አገር ከነድንበሩ፣ ከነፍቅሩ፥ ስም ከነምልክቱ (ከነትርጉሙ)፤ አሁንም ቢሆን ትውልዱ፡- ጀግንነትን፥ አገር ወዳድነትን፥ ለታሪክ፣ ለባህልና ለሃይ ማኖት ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ በማስተማርና በማበረታታት ቤተ ክርስቲያን የበኵሏ ድርሻ አላት።                                   ኢትዮጵያ  በጥንት የግብፃውያን ቋንቋ፡-“ጱንጥ ቶ ኔቶር ኩሽ” እየተባለች ትጠራ ነበር።ጱንጥ የሚለው ቃል፡-በብሉይ ኪዳን ካለው “ፉጥ” ከሚለው ስም ጋር ይመሳሰላል።ዘፍ፡፲፥፮።“ቶ ኔቶር” ማለትም ሀገረ እግዚአብ ሔር ማለት ነው ይላሉ።ሙሴ ብሉይ ኪዳንን ሲጽፍ ይህችኑ አገር “የኩሽ ምድር” እያለ የጻፈው፥በግብፅ ተወልዶ ያደገ እንደመሆኑ መጠን፥የግብፃውያንንም ቋንቋ ያውቅ ስለነበር ነው እንጂ፥ “ኩሽ” የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ቃል አለመሆኑ ታውቋል።ኢትዮጵያ የኩሽ ምድር ለመባል የበቃችበት ዋናው ታሪካዊ ምክንያት፡-የካም የመጀመሪያ ልጅ የኩሽ ዘሮች ስለ ሰፈሩባት ነው።ይህችው አገር በሌላ አጠራር፡-“የሳባ ምድር”፥አንዳንድ ጊዜም “አቢሲኒያ” እየተባለች ትጠራለች።ምናልባት ይህ ስያሜም የተገኘው፥እነዚሁ የኩሽ ልጆች ሳባና አቢስ (ሰብታ) ስለ ሰፈሩባት በስማ ቸው አስጠርተዋታል ማለት ነው።ዘፍ፡፲፥፮።በሳባ የሳባ ምድር፥በሰብታ (አቢስ) ደግሞ አቢሲኒያ እየተባለች ለብዙ ዓመታት ቆይታለች።ዐረቦች ግን፥አቢሲኒያ የሚለውን ስያሜ “ሐበሻ” ብለው፥ድብልቅ፣ ውጥንቅጥ ለማለት ይቃጣቸዋል፤ነገር ግን ምንጭ የለውም። ምዕራባውያን አሁንም አቢሲኒያ እያሉ ይጠሯታል።                            
ኢትዮጵያ በ፫ሺ፮፻ ዓመት ከጌታ ልደት በፊት በየመን ይኖሩ የነበሩ ከነገደ ሴም የተከፈሉ ነገደ ዮቅጣን ፥በባብ እልመንደብ (በመከራ በር) በኵል ገብተው ሰፍረውባታል።እነርሱም፡-በዚች አገር ይኖሩ ከነበሩ የኵሽ ዘሮች ጋር እየተጋቡ እየበረከቱ ሄደዋል። ዘፍ፡፲፥፳፭።ይህችንም አገር፡-“ምድር አግዐዚት፥ምድረ አግዐዝያን፤ነፃ ሀገር፥ነፃነት ያላቸው ሰዎች መኖሪያ” ብለው ጠሯት።በመጨረሻ ለዚች አገር የተሰጣት ስያሜ “ኢትዮጵያ” የሚል ነው።በሀገራ ችን እንደሚተረከው “ኵሽ” ሁለት ስም ነበረው፤ሁለተኛው ስሙ “ኢትዮጲስ” ይባላል።አቅኝዎቹ በአባታቸው ስም ይህችን አገር “ኢትዮጵያ” ብለዋታል፤እነርሱም ኢትዮጵያውያን ተብለዋል፥እየተባለ ይተረካል።አንዳንዶች እንደሚ ሉት ደግሞ፡-“ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ከግሪክኛ የተወረሰ ነው፤“ኤቶስ” ማለት፡-ዋዕይ (ቃጠሎ) ማለት ሲሆን፥“ኦፕ” ማለት ደግሞ ገጽ፣አርአያ፣ፊት ማለት ነው።እነዚህ ሁለት ቃላት ሲጣመሩ “ኤቴኦፒያ” ወይም “ኤቴኦፕስ” የሚል ቃል ይወጣዋል።ይህም፡-እንደ መጀመሪያው “ኤቲኦፕያ” ቢል የአገሪቱን ቆላነት ያመለክታል፤ቆላ፣በረሀ፣የዋ ዕይ፥የትኵሳት አገር ማለት ነው።እንደ ሁለተኛው “ኤቴኦፕስ” ቢል ግን የሕዝቧን ምንነት ያመለክታል፤በዋዕየ ፀሐይ ፊቱ የበለዘ፣የጠቆረ ፣የበረሀ ፥የቆላ ሻንቅላ ማለት ነው።በሆሜር መጽሐፍ ደግሞ ቀዩን ወይን ኢትዮጵያ ብሎት ስለሚገኝ፡-“ኢትዮጵያ” ማለት ቀይ፣የቀይ ዳማ ቀለም ያለው ሕዝብ ማለት ነው ይላሉ።                              
የኢትዮጵያውያን አባት ኩሽ በሞተ በ፪ሺ፬፻፶ ዓመት፥በ፪፻፹፬ ዓ.ዓ. ከጌታ ልደት በፊት፥መጻሕፍተ ብሉ ያትን ከዕብራይስጥ ወደ ፅርዕ ቋንቋ የመለሱ ሰባው ሊቃውንት፥ ሙሴ፡-“ኩሽ” እያለ በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን የጻፈውን ኢትዮጵያ በሚል ቃል ለውጠውታል።                                                                    
በታሪክ ሰዎችና በፈላስፎች ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ የተነገረውን በመጠኑ ለመግለጥ ያህል፡-ሆሜር የተባለው የግሪኮች ባለ ቅኔ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብዙ ተናግሯል።“የኢትዮጵያ ሕዝብ በጉልበት ኃያላን፥በውበት የተደነቁና በጠባይ ጭምቶች፥ትሕትናን የተመሉ ናቸው። ከዚህም የተነሣ ከግሪክ ፲፪ አማልክት አንዱ ፥የመጀመሪያ ውና ትልቁ እንደ አባት የሚቆጠረው ዜውስ፥ ኃያላኑን ኢትዮጵያውያንን ለማየት፥ ከነሱ ጋር ለመብላት ወደ ውቅያ ኖስ አካባቢ ወረደ።” ብሏል። ከ፬፻፺ ከጌታ ልደት በፊት የነበረው፥ምዕራባውያን የታሪክ አባት የሚሉት ሔሮዶቶስ፡-ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ባነሣበት መጽሐፍ፡- “ኢትዮጵያውያን በውበት፥ በቁመትና በኃይል ከሰዎች ሁሉ ይበልጣሉ።”ብሏል። (ሔሮዶቶስ ፫ኛ መጽሐፍ ምዕ፡፳፥፩፻፲፬)።                                                                
ኢትዮጵያ በታሪክ ሰዎችና በፈላስፎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስም የታወቀች አገር ናት። የሕዝቧም ማንነት በቅዱስ መጽሐፍ ተገልጧል። ሙሴ የሥነ ፍጥረትን አቀማመጥ በተናገረበት በመጀመሪያው መጽሐፍ ፥ ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ የተከበበች አገር መሆኗን ተናግሯል። ዘፍ፡፪፥፲፫።መጽሐፍ ቅዱስ የኢትዮጵያን ሕዝብና ምድር ሁልጊዜ ከግብፅ ጋር በማያያዝ ይጽፋል። ኢሳ፡፳፥፫-፮፣ሕዝ፡፳፥፬፣ዳን፡፲፩፥፵፫፣ናሆ፡፫፥፱። በጂኦግራፊ አቀማመጥም ኢትዮጵያ ከግብፅ ደቡብ የምትገኝ አገር መሆንዋ በቅዱስ መጽሐፍ ተነግሯል። ሕዝ፡፳፱፥፲፣ዮዲ፡፩፥፲። ሱዳንን እና ግብፅን ሲመግቡ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ወንዞች ዐባይና ተከዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የታወቁ ናቸው። ኢሳ፡፲፰፥፩።ኢትዮጵያ በማዕድን የከበረች እንደመሆንዋ አልማዟና ወርቋም በዓለም ተደናቂ ነበሩ። ኢዮ፡፳፰፥፲፱። ሕዝቧም በንግድ ሥራ የታወቁ ነበሩ፥በንግዳቸውም በልጽገውና ተደስተው ይኖሩ ነበር። ፵፫፥፫። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ድንክ አጭር፥እንደ አዛሔል ቀውላላ ሳይሆኑ ልከኛ መጠነኛ ናቸው። ኢሳ፡፵፭፥፲፬።መልካቸውም እንደ ቁራ ያልጠቆረ፥እንደ ለምጻም ያልተንቦገቦገ አሳ የሚመስል ጠይም ነው። ኤር፡፲፫፥፳፫። የኢትዮጵያ ግዛት በጣም ሰፊ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል።በዜና መዋዕል ካልዕ እንደተተረከው፥ ኢትዮጵያውያን ዜራህ (ዝሪ) በሚባ ለው ንጉሣቸው እየተመሩ ዘምተው ምድረ ይሁዳን ከያዙ በኋላ በንጉሥ አሳ ድል ሆነዋል።፲፬፥፱።ኢትዮጵያውያን በኃይላቸው ተመክተው በሚሠሩት ሥራ ነቢያት ይገሥጿቸው ነበር። ሶፎ፡፪፥፲፪። በእግዚአብሔርና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የማያቋርጥ ፍቅርና ግንኙነት ሲገልጡ ደግሞ፡-“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። በፊቱ ኢትዮጵያውያን ይሰግዳሉ።ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው።...... ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ቍርባኔን ያመጡልኛል።......የእስራኤል ልጆች ሆይ፥እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ብለዋል።መዝ፡፷፯፥፴፩፤፸፩፥፱፤፸፫፥፲፬፣አሞ፡፱፥፯፣ሶፎ፡፫፥፲።                                         
        ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክ፤(አባ ጎርጎርዮስ -፲፱፻፸፬ ዓ.ም.)         

No comments:

Post a Comment