Tuesday, July 7, 2015

ቤተ ደጀኔ (Betedejene.blogspot.com)

                                                                  
           የቤተ ደጀኔ ዐውደ ጦማር ትምህርተ ሃይማኖትን አዘጋጅታ በማቅረብ፥ጋንን በጠጠር የመደገፍ ያህል እጅግ አነስተኛ አስተዋፅኦ ስታበረከት መቆየቷ፥ በትጋት ሲከታተሉ በነበሩት ዘንድ የሚታወስ ነው። በመካከል ድንገት በመቋረጧም ተቆጭተው በተለያየ መንገድ “ትቀጥልልን፤” የሚለውን መልእክት ብዙዎች ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። እስከዛሬም ተስፋ ሳይቆርጡ አብዝተው የሚዘበዝቡኝ አሉ። ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹ፡- በዕድሜ ታናሼ፣ በክህነት እኩያዬ፣ በጸጋ ደግሞ ታላቄ የሆነው፥ በሰሜን አሜሪካ የኦሀዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መሥራችና አስተዳዳሪ፥ መልአከ ሰላም ያሬድ ገብረ መድኅን እና የአይቲ ባለሙያው ወንድሜ ቡሩክ ሺፈራው ዘሲያትል ናቸው። ይኸንንም ማድረጋቸው ነገረ ቤተክርስቲያን ስለሚገዳቸው እንጂ ከእኔ ምስጋናን ፈልገው አይደለም። ቢሆንም አመሰግናቸዋለሁ፥ እመርቃቸዋለሁ።                                                              
         መንፈሳዊ አገልግሎት የፍቅር አገልግሎት ነው፥ በመሆኑም ይህን አገልግሎት ለመፈጸም፥ “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንደትጠነክሩ፥ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር፥ እንደ ክብሩ ባለጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምንያህል መሆኑን ለማስተዋል ፥ ከመ ታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት  ደርሳችሁ ትሞሉ     ዘንድ። (እግዚአብሔርን ለማገልገል ፍጹምነት ባለው ሥራ ኹሉ ፍጹማን ልትኾኑ ያጸናችሁ ዘንድ።) እንዲል፥ የመንፈስ ጥንካሬ   ያስፈልጋል። ኤፌ፡፫፥፲፮-፲፱።                             
          በቤተክርስቲያን አገልግሎት መንፈስን የሚያዝሉ የውስጥ የአፍአ ፈተናዎች ያጋጥማሉ፥ እነዚያን ታግሎ ለማለፍ የጽሞና ጊዜ ያስፈልጋል። “ሕዝቤ ሆይ፥ና፥ወደ ቤትህም ግባ፥ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።”ይላል።ኢሳ፡፳፮፥፳።ፈተና ከአፍአው ይልቅ የውስጡ ይበረታል፥ከሩቁ ይልቅ የቅርቡ ይጠነክራል። ቢሆንም ተስፋ መቁረጥ አይገባም፥ ምክንያቱም፡- የምናገለግላት ቤተክርስቲያን፥ “የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፤” ተብላለች። ማቴ፡፲፮፥፲፰።እኛም፡- “ነገር ግን አይዞአችሁ፥እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፤” ተብለናል።ዮሐ፡፲፮፥ ፴፫               

          የቤተክርስቲያን አገልግሎት የትሕትና አገልግሎት ነው። እንደ አብርሃም፡- “እኔ አፈርና አመድ ነኝ፤” ዘፍ፡፲፰ቁ.፳፯ ፥ እንደ ሙሴ፡-“እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸይፍ ሰው ነኝ፤”ዘጸ፡፬ቁ.፲ ፥ እንደ ዳዊት፡-“እኔ የሞተ ውሻ ቁንጫም ነኝ፤” ፩ኛ፡ሳሙ፡፳፬ቁ.፲፬ ፥ እንደ ጌዴዎን፡-“እኔ በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ፤” መሳ፡፮ቁ.፲፭ ፥ እንደ ኢሳይያስ፡- “እኔ ከንፈሮቼ በለምፅ የረከሱብኝ ሰው ነኝ፤”ኢሳ፡፮ቁ.፭ ፥ እንደ ኤርምያስ፡-“እኔ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም፤ (እውቀት የለኝም፤) ኤር፡፩ቁ.፯ ፥ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፡-“እኔ ጭንጋፍ ነኝ፤” ማለትን ይጠይቃል። ፩ኛ፡ ቆሮ፡፲፭፥፰።ያን ጊዜ ጸጋው እየበዛልን ይሄዳል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፡-“ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፡- እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” ያለው ለዚህ ነው።ያዕ፡ ፬፥፮።                                                                 
           እንግዲህ፡-በእግዚአብሔር ፈቃድ፥ በወንድሞች የምክርና የሙያ ማበረታታት፥ ቤተ ደጀኔ ሰኔ ፴ ቀን ፪ሺ፯ ዓ.ም. የቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ዕለት ሥራዋን እንደገና ጀምራለችና በጸሎታችሁ እርዱኝ፥ በምክራችሁም አትለዩኝ። በመጨረሻም ቤተ ደጀኔ ከተጀመረች ጀምሮ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሥራውን ሲመራ የነበረውን ከተማ ተመስገንን እና ጽሑፎችን በመተየብ ትረዳን የነበረችውን ሳባ ፈረደን ሁልጊዜ እመርቃቸዋለሁ። ከልብ የሚያገለግሉት የዴንቨር መድኃኔዓለም በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስም እንዲያድላቸው ከልብ እጸልያለሁ። አሜን።

2 comments:

  1. ቤተደጀኔ እንደገና በመመለሷ በጣም ደስ ብሎኛል እግዚአብሔር ያበርታችሁ፡፡

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር ያበርታችሁ፡፡

    ReplyDelete