Tuesday, September 24, 2013

«የምሕረትህን አክሊል ትባርካለህ፤» መዝ ፷፬፥፲፩          ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፦ አዲስ ዘመንን ከበረከት ጋር የሚሰጠን እግዚአብሔር መሆኑን በፍጹም ሃይማኖት መስክሯል፡፡ ይኽንንም በገና እየደረደረ በዜማ እግዚአብሔርን በማመስገን ገልጦታል፡፡ «ምድርን ጐበኘሃት፥ አረካሃትም፤ (ይህችን ዓለም በረድኤት ጎበኘሃት፥ የዘሩባትን እንድታበቅል፣ የተከሉባትን እንድታጸድቅ አደረግሃት)፤ ብልጽግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኆችን የተሞላ ነው፤ (እግዚአብሔር የፈጠራቸው አራቱ የገነት ወንዞች፦ ኤፌሶን፣ ግዮን፣ ጤግሮስ፣ ኤፍራጥስ በውኃ የተሞሉ ናቸው፡፡ አንድም፦ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ እንዲመግቡ የፈጠራቸው ወንዞች ውኃን የተሞሉ ናቸው)። ምግባቸውን አዘጋጀህ፥ እንዲሁ ታሰናዳለህ። (አዳም ከመፈጠሩ በፊት ምግቡን እንዳዘጋጀህለት ሁሉ አሁንም አዘጋጀህላቸው)። ትልምዋን አርካው፤ (የታረሰውን መሬት እርሻውን በዝናም ምሕረትህ ጐበኘው)፤ መከሯንም አብጀው፤ (የተዘራው ዘር፥ የተተከለው ተክል፥ ፍሬው፥ ምርቱ በሚሰበሰብበትና በሚለቀምበት ጊዜ እንዲትረፈረፍ አድርገው)። በነጠብጣብህም ደስ ብሏት ትበቅላለች፤ (የተዘራችውን ዘር ጠብ ጠብ እያለ በሚዘንመው ዝናም ቀስ በቀስ ታሳድጋታለህ፤ በነጥብጣብ ባይወርድ ኖሮ የዝናሙ ኃይል ዘሩንም አፈሩንም ጠርጎት ይሄድ ነበር)፤ የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ፤ (በቸርነትህ ዘመን የተገኘውን እህሉን ታበዛዋለህ፤ አንተ የባረከው ሰው በራሱ አክሊል እንደሚቀዳጅ፥ ዘውድ እንደሚደፋ፥ የተባረከም ዘር በቅሎ አድጐ በራሱ ላይ ፍሬን እንደ አክሊል ይቀዳጃል፥ እንደ ዘውድ ይደፋል)። ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ። (በበረሃ የሚገኙ ተራሮች ልክ እንደ ዝናም ከሰማይ በሚወርድ ጠል ይለመልማሉ። ይኸውም ለዱር እንስሳቱ ነው)። ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። (ኮረብቶች የልምላሜን ዝናር ታጥቀው ለሚያያቸው ደስ ያሰኛሉ)። የበጎች አውራዎችም ስብን ይለብሳሉ)። (የለመለመውን ሣር ነጭተው፥ የጠራውን ውኃ ተጐንጭተው ይወፍራሉ፥ ይሰባሉ)። ሸለቆዎችም ስንዴን ይሞላሉ፤ (የምድር ሸለቆዎች ሳይቀሩ ከእግዚአብሔር በረከት መትረፍረፍ የተነሣ የስንዴ ምርት የሚታፈስባቸው ይሆናሉ)። እየጮኹ ያመሰግናሉ። (አድገው ለፍሬ የበቁ አዝርዕት ነፋስ ሲነካቸው ያፏጫሉ፥ ድምፅ ያሰማሉ። አንድም ይህ ሁሉ በረከት የተሰጣቸው ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ)።» ብሏል። መዝ ፷፬፥፱-፲፫። ምሥጢራዊ መልእክቱ ደግም፦ ከበረከተ  ሥጋ አንፃር በረከተ ነፍስን እንደሚሰጠን የሚያመለከት ነው። አጥተነው የነበረውን የእግዚአብሔር ልጅነት፥ ተዘግቶብን የነበረውን ገነት መንግሥተ ሰማያትን፥ ወንጌልን፥ ገቢረ ተአምራትን ፥ ሥጋውንና ደሙን፥ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን፥ የእመቤታችንን እናትነት፥ የቅዱሳንን አማላጅነት፥የመላእክትን ተራዳኢነት ሰጥቶን ደስ አሰኝቶናል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ፦ «ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው።. . . ይህ ሥጋዬ ነው፥ እንኩ ብሉ፤ ይህ ደግሞ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፥ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ።. . . መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።. . . እነኋት እናትህ። . . . በነቢይም ስም ነቢይን የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይቀበላል፥ በጻድቅም ስም ጻድቅን የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ይወስዳል። . . . በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና።» ብሎናል። መዝ ፺፥፲፩፣ ፲፥፩፤ ፲፥፵፩፤ ፳፮፥፳፯፤ ማቴ ፲፮፥፲፭፣ ሉቃ ፳፫፥፵፫፣ ዮሐ ፩፥፲፪፤ ፲፱፥፳፯፤ ፳፥፳፪።


አዲስ ዘመን የተሰጠን ለምንድን ነው?

           «ዘመን ለፍስሐ፥ ዕድሜ ለንስሐ፤» እንዲል፥ አዲስ ዘመን የተሰጠን፦ ከዘመኑ ጋር በተሰጠን በረከት ፍስሐ (ደስታ) እንድናደርግና በተሰጠን ተጨማሪ ዕድሜ ንስሐ ገብተን ከፍ ብለን እግዚአብሔርን ዝቅ ብለን ነፍሳችንን ደስ እንድናሰኝ ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ነገር ግን ስለ እነርሱ ይታገሣል፥ ማንንም ያጠፋ ዘንድ አይሻምና ንስሐ ይገቡ ዘንድ ለሰው ሁሉ ዕድሜን ይሰጣል እንጂ።» ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፫፥፱። ከዚህም የተነሣ ከእግዚአብሔርም ጋር ከእኛም ጋር ቅዱሳንም ደስ ይላቸዋል። ጌታችን በወንጌል፦ «እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል።» ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ ፲፭፥፲። ስለሆነም በተሰጠን በዚህ አዲስ ዘመን በንስሐ ታጥበን አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ለራሳችን ልናደርግ ይገባል። እግዚአብሔር በነቢዩ በሕዝቅኤል አንደበት፦ «ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአትም እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፥ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ለእናንተ አድርጉ፤» ብሎናል። ሕዝ ፲፰፥፴። ጌታችን አምካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብጹዓን ትምህርቱ (በተራራው ስብከቱ) «ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መጽናናትን ያገኛሉና።» በማለት የተናገረው ንስሐን የሚያመለክት ነው ማቴ ፭፥፬። ይኸውም፦ ኃጢአታቸውን እያሰቡ፥ በደላቸውን እየቆጠሩ፥ አላበጀንም እያሉ የሚያለቅሱ ሰዎች ሥርየት ኃጢአትን አግኝተው፥ ለፍጻሜው የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ወርሰው ይጽናናሉ፥ ደስ ይሰኛሉ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም፦ «እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፥ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፥ ከእናንተ ይሸሻል። እግዚአብሔርን ቅረቡት፥ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥአን እጆቻችሁን አንጹ፥ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ። እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ፥ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ። በእግዚአብሔርም ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፥ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።» ብሎናል። ያዕ ፬፥፯-፲።

ዕንባን ማፍሰስ፤

            ቅዱስ ዳዊትን የጠቀመው ዕንባው ነው። ይኽንንም ፦ «ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዓይኖቼ ፈሰሰ። . . . ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥበዋለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ። ዓይኔ ከቁጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች። (ሰብአ ትካትን፥ ሰብአ ሰዶምን፥ ሰብአ ገሞራን በአጠፋህበት መዓትህ ታጠፋኝ ይሆን ከማለቴ የተነሣ ዓይኔ ባከነች)። አመጻን የምታደርጉ ሁሉ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና። . . . ዓይኔም ከሐዘን የተነሣ ተፈጀች፤ (ታወከች)፤ ነፍሴም ሆዴም፤ ሕይወቴም በሐዘን አልቃለችና ፥ ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት። (ነፍሴም ሥጋዬም ባለመከራ ሆኑ፣ ሰውነቴ በመከራ አልቋልና፣ ዘመኔም በመከራ ተፈጽሟልና)። . . . ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረጉህ። (ማቅ ለብሼ አመድ ላይ ላይ ተኛሁ)። . . .  በደሌንም እናገራለሁ፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ።. . .  አቤቱ ጸሎቴን ስማኝ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ። . . . ዘወትር አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ፥ ይኽንን ሳስብ ነፍሴ (ሰውነቴ) በእኔ ውስጥ ፈሰሰች።» በማለት በመዝሙሩ ገልጦታል። መዝ ፮፥፮፤ ፴፥፱፤፴፬፥፲፬፤ ፴፯፥፲፰፤ ፴፰፥፲፪፤ ፵፩፥፫፤ ፩፻፲፰፥፴፰።

            ንጉሥ ሕዝቅያስንም የጠቀመው ዕንባው ነው። በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ በተያዘበት  ወራት፥ ነቢዩ ኢሳይያስ ከእግዚአብሔር ተልኮ በመምጣት፦ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርም እና ቤትህን አስተካከል። (ሕይወትህን በንስሐ አስተካክል)።» ብሎት ነበር። በዚህን ጊዜ ንጉሡ ሕዝቅያስ ፊቱን ወደ ግድግዳው በማዞር ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ መኝታው ርሶ ከአልጋው ሥር እስኪንጠባጠብ ድረስ እጅግ ታላቅ ልቅሶን አለቀሰ። እግዚአብሔርም፦  «ጸሎትህን ሰምቻለሁ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ አድናለሁ፥ ለዚችም ከተማ እቆምላታለሁ።» ሲል በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል መልስ ሰጥቶታል። ኢሳ ፴፰፥፩-፮። የንጉሥ የሕዝቅያስ ዕንባ የጠቀመው ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለወገኖቹም ጭምር ነው። እስራኤል ዘሥጋንም ከባርነት ቤት ከግብጽ ያወጣቸው በራሳችው ዕንባ ላይ የራሔል ዕንባ ተጨምሮ ነው። እግዚአብሔር ለሙሴ፦ «በግብጽ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአሠሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፥ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፥ አድናቸውም ዘንድ ወረድሁ።» በማለት መልስ የሰጠው ለዚህ ነው። ዘዳ ፫፥፯-፰። ስለ ራሔልም፦ «ራሔል ስለ ልጆቿ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ በራማ ተሰማ፥ መጽናናትንም እንቢ አለች፥ ልጆቿ የሉምና።» ተብሏል። ኤር ፴፩፥፲፭፤ ማቴ ፪፥፲፰። በአዲስ ኪዳንም በዝሙት ቆሽሻ፥ ረክሳ ትኖር የነበረችውን ሴት የጠቀማት ከጌታ እግር ሥር ወድቃ ያጎረፈችው ዕንባ ነው።» እነሆ፥ ከዚያች ከተማ ሰዎችም አንዲት ኃጢአተኛ ሴት በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ አውቃ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ገዝታ መጣች። በስተኋላውም በእግሮቹ አጠገብ ቆማ አለቀሰች፥ እግሮቹንም በዕንባዋ ታርስ ነበር፥ በራስ ጠጉሯም እግሮቹን ታብሰውና ትስመው ፥ ሽቶም ትቀባው ነበር።» ይላል። በዚህም ምክንያት «ኃጢአትሽ ተሰረየልሽ፤» ተብላለች። ሉቃ ፯፥፴፯-፴፰ ፣ ፵፰። ቅዱስ ጴጥሮስም በዕንባ ተጠቅሟል። ጌታ አስቀድሞ እንደተናገረበት «ኢየሱስ የምትሉትን ፈጽሞ አላውቀውም፤» በማለት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስቴ በአፉ በካደው ጊዜ፥ የዶሮውን ጩኸት ሰምቶ ምርር ብሎ አልቅሷል። ማቴ ፳፮፥፷፱-፸፭።

ምን እናድርግ?

            በእግዚአብሔር ቃል ተወቅሰው ስለ ኃጢአታቸው ከልባቸው የተጸጸቱ ሰዎች የመጨረሻ ቃላቸው «ወንድሞቻችን ሆይ ምን እናድርግ?» ነው። የቅዱስ ጴጥሮስ መልስ፦ «ንስሐ ግቡ . . . ኃጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፥ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ።» የሚል ነበር። ስለዚህ ከልጅ እስከ አዋቂ፥ ከተገልጋይ እስከ አገልጋይ «ኃጢአት የለብኝም፤» ለማለት ብቃቱ ስለሌለን ሁላችንም ንስሐ እንግባ፥ ምክንያቱም ሁላችንም በደለኞች ነንና። ቅዱስ ዳዊት፦ «በሥራቸው ረከሱ፥ ጐሰቆሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራትም የለም፥ አንድም እንኳ የለም። የሚያስተውል፥ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉ ተስተካክሎ በአንድነት ዐመፀ፥ በጎ ነገርን የሚሠራት የለም፥ አንድም እንኳ የለም።» ብሏል። መዝ ፲፫፥፩-፫። ጠቢቡ ሰሎሞን ደግሞ «በደሉን የሚሰውር ሰው መንገዱ አይቃናም፥ የሚናዘዝና ራሱን የሚዘልፍ ግን ይወደዳል።» ብሏል። ምሳ ፳፯፥፲፫።

   ይህ ዘመን «እኔ ጻድቅ ነኝ፤» ብለን በሐሰት ተኰፍሰን የምንኖርበት ዘመን አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ የቅዱስ ዳዊትን ቃል ተጠቅሞ «አንድስ እንኳ ጻድቅ የለም። አስተዋይም የለም፥ እግዚአብሔርንም የሚሻው የለም።» በማለት ያንኑ አጽንቶ አስተምሯል። ሮሜ ፫፥፲፩። ይህ ዘመን እንዳለፈው ዘመን ሌላውን እየኮነንን ራሳችንን ብቻ እያጸደቅን የምንኖርበት ዘመን አይደለም። «አንተ ሰው ሆይ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልስለታለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያንኑ ትሠራዋለህና፥ ይህም እንደዚህ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ቅጣት የሚያመጣ የእግዚአብሔር ፍርዱ እውነት እንደሆነ እናውቃለን።» ይላል። ሮሜ ፪፥፩-፪። እስከ ክፋታችን ዝም ብሎ መመላለሱ ጥቅም የለውም። «ያለፈው ዘመን ይበቃል፤» ማለት መቻል አለብን። ፩ኛ ጴጥ ፬፥፫። አሮጌው ዘመን እንደተወገደ አሮጌው ሰውነታችን መወገድ አለበት። (ሰውነታችንን አሮጌ ካሰኘው ኃጢአትና በደል መላቀቅ አለብን)። አሮጌው መንፈሳችን በጽድቅ መታደስ አለበት። ኤፌ ፬፥፳፫። «እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ። ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና፥ ዘመኑን ዋጁ።» ተብለናልና። ኤፌ ፭፥፲፮። ክፉ ቀን በኃጢአት ይጥላል፥ ወንድምን፥ ወገንን ፥ የትዳር ጓደኛን ያስበድላል። ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። ስለዚህ ሃይማኖት ይዘን፥ ምግባር ሠርተን ዘመኑ የሚጠይቀንን መሥዋዕትነት እንክፈል። ዘመኑ አጭር ነው። እንደ ማቱሳላ ዘጠኝ መቶ ሰድሣ ዘጠኝ ዓመት አንኖርም። ዘፍ ፭፥፳፯። ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረው ቢበዛ ሰባ ወይም ሰማንያ ነው። እርሱንም በተለያየ በሽታ እየተሰቃየን ነው። መዝ ፹፱፥፲። ጻድቁ ኢዮብም፦ «ሕይወቴ (ዘመኔ) እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ቀላል ሆነች፤ (ፈጠነች)፤» ብሏል። ኢዮ ፯፥፮። ስለዚህ ከሸማኔ መወርወሪያ የምትፈጥን ዕድሜያችን ሳትቀድመን እንቅደማት። በንስሐ ታጠበን፥ በሥጋ ወደሙ ተቀድሰን እንኑር። የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን። 


1 comment: