Tuesday, January 22, 2013

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፮


            ሥዕል፦ ከክርስትና በፊት ሥዕል በቤተ አሕዛብም ሆነ በቤተ አይሁድ የታወቀና ከአምልኮት ጋር የተያያዘ ነበር። በቤተ አሕዛብ እንጨት ጠርቦ ደንጊያ አለዝቦ ማምለክ የተለመደ ነበር። እንዲያውም የሮማ ነገሥታት አማልክት ተብለው ከመመለካቸው በላይ ከሞቱ በኋላ ሥዕላቸው በደንጊያና በእንጨት እየተቀረጸ ሲመለኩ መኖራቸው በታሪክ ይታወቃል። ክርስትና በመጣ ጊዜም ከክርስትና ጋር ያጣላቸው ይኸው ልማዳቸው ነው። በክርስትና ትምህርት ይህ አምልኮ ጣዖት ነውና፤ በቤተ አይሁድም እንደ አሕዛብ ሳይሆን በታቦተ ሕጉ በጽላተ ኪዳኑ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲሥል ራሱ እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት ነበር። ዘጸ 25፥19። ነገሥ ቀዳ 6፥23። ሕዝ 9፥3፣ 10፥3፣ 10፥1። ሔኖ 14፥11 ዘጸ 25፥20፤ ዘፍ 3፥24። እነዚህ የኪሩቤል ሥዕሎች ከታቦቱ አይለዩም። ምክንያቱም ታቦት የእግዚአብሔር መገለጫ ዙፋን ስለሆነ የመንበረ ፀባዖት አምሳል ነው። ሥዕለ ኪሩቤልም የጸወርተ መንበር ኪሩቤል አምሳል ነውና፥ የሚሳሉትም እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ሁነው ነው። የንጉሥ አንጋች ንጉሡ በተቀመጠበት በዙፋኑ ፊት ነቃ፥ ቆጣ፥ ብሎ እንደሚቆም።
          ሥዕል በቤተ ክርስቲያን የተጀመረበት ግን ከዚህ የተለየ ታሪካዊ ምክንያት አለው። በጥንታውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የሥዕል ክብር እንዴት ተጀመረ። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ተገለጠው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ትምህርታቸውን ያስፋፉት ዋሻ ፈልፍለው ጉድጓድ ቆፍረው በዋሻ በፍርክታ ውስጥ ነው። ካታኮምብ (ግበ በምድር) ይሉታል፥ በዚህ ዋሻ ውስጥ የሰማዕታትን አፅም እየሰበሰቡ ጸሎት ይጸልዩ ትምህርት ያስተምሩ ነበር። በዚሁ ውስጥ ብዙ አማኞች እየመጡ የማኅበራቸው አባል መሆን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የክርስትናን ትምህርት አስፋፍቶ ለመስጠት በቂ መጻሕፍት አልነበሩም። እንደ ልብ ወጥቶ ለመፈለግና ለማዘጋጀት ነፃነት ስላልነበራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ምሳሌዎችን በሥዕል እያሰፈሩ ማስተማር ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ሥዕል ማስተማሪያ ሁኖ ቆይቷል። ሥዕሎችም የሚሣሉት በምሳሌነት “ሲምቦል” ሲሆን የሚሳሉትም በአመድና በከሰል በዋሻው ዙሪያ ነው። በዋሻው ፊት ለፊት ላይ (በአፈ ጽዮን) የሚሥሉት እረኛው በጉን እንደተሸከመ አድርገው ነው። “ክርስቶስ ያመኑበትን ሁሉ በሱም አምነው የሞቱትን ሁሉ የሚያድናቸው ቸርና ታማኝ ጠባቂ መሆኑን ለማስረዳት ነው።” ሌላውን ሥዕላቸውን የሚጀምሩት በብሉይ ኪዳን ታሪክ ነው። ለምሳሌ የቀደሙ ሰዎች አዳምና ሔዋን እንዴት እንደተሳሳቱና ያሳታቸውንም እባብ በመካከላቸው እንዳለ አድርገው ይስሏቸው ነበር። ዘፍ ፫፥፩-፯ በምህላና በጸሎት ላይ ያለች የምዕመንን ነፍስ በመርከብ ውጥ ያለውን ኖኅን አስመስለው ይስሏት ነበር። ዘፍ ፯፥፩-፳፬ የአቤልን መሥዋዕት ለክርስቶስ መስዋዕትነት ምሳሌ፤ ዘፍ ፬፥፬። በውኃ ተጠምቆ መዳንን ወይም መዳን በጥምቀት መሆኑን ሲገልጡ ሙሴ በበትሩ ደንጊያውን መትቶ ለተጠሙ እሥራኤል ውኃ ማፍለቁን ይሥላሉ፤ ዘፀ ፲፯፥፮። የኢዮብ መከራ፦ የሰማዕታትና የምዕመናን መከራና ትዕግሥት ምሳሌ መሆኑን፤ ኢዮ ፩፥፳፪።  የእስራኤል ጉዞ በሐቅለ ሲና  የምዕመናን በዚህ ዓለም የመኖር ምሳሌ፤ የሙሴ ደብረ ሲናን መውጣት አምላኩንም ማየት፥ የምዕመናን ክብርና ልዕልና ምሳሌ፤ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ውስጥ ከገብርኤል ጋር፥ ምዕመናን በዚህ ዓለም በመከራ ቢሰቃዩም ታዳጊ መልአክ የማይለያቸው ለመሆናቸው ምሳሌ፤ ኤልያስ ሐሜሌቱን ለኤልሳዕ ጥሎ ማረጉ፥ ክርስቶስ በረከቱን ለምዕመናን ሰጥቶ ለማረጉ እና ምዕመናንም በሱ አምነው ገነት መንግስተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ፤ ዳንኤል በግበ አናብስት፥ ሰማዕታት በዐላውያን ሸንጎ ለመቆማቸው ምሳሌ፤ ጦቢት ከዓሣው ጋር፥ ምዕመኑ ከአዳኙ ከክርስቶስ ጋር ለመሆኑ ምሳሌ፤ በጥንት ግሪኮች ዓሣ ሲሉ፦ “ኢኽቲስ” ይላሉ። የዚህ ፊደል እያንዳንዱ ምህጻረ ቃልነት አለው። ኢ - ኢየሱስ፣ ኽ - ኽርስቶስ፣ ቴ - ቴው ኢዮስ፥ (የእግዚአብሔር ልጅ) ስ - ሶቴር (መድኅን) አዳኝ፥ ማለት ነው፤ ሁሉንም ቃላት አገናኝተን ስናነበው፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር መድኅን” የሚል ትርጉም ይሰጣል። ሶስና ከሁለት ዳኞች ጋር፥ ሰማዕታት በዐላውያን ነገሥታት ፊት የመቆማቸው ምሳሌ፤ ዮናስ ወደ ባሕር ሲጣል፥ አንበሪ ሲውጠውና በየብስ ሲተፋው፥ የነበረባት ጎጆ በዱባ ቅጠል ተሸፍና ሲደሰት፥ በኋላም በደረቀችበት ጊዜ ሲያዝን፥ ይህ ሁሉ በአንድ ላይ የክርስቶስን ሞትን ትንሣኤ ያስረዳል።
          የሐዲስ ኪዳንንም ታሪክ እንደዚሁ በግበ በምድር ውስጥ ይሥሉት ነበር። የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት፥ የጌታ በቤተልሔም ዘይሁዳ መወለድ፥ የሰብአ ሰገል ስግደትና አምኃ፥ ሕፃኑን ለታቀፈችው ለድንግል ማርያም አምኃውን ሲያስረክቡ፥ የምድረ ግብፅ ስደት፥ ዮሴፍና ሰሎሜ ጓዛቸውን ተሸክመው አብረው ሲሰደዱ፥ የጌታ ጥምቀትና የሦስቱ ዓመት ትምህርት ከተአምራት ጋር፥ የቃና ሠርግ፥ የዕውሩ ዓይን መከፈት፥ የመጻጉዕ መዳን፥ ልብሱን ስትዳስስ ደሟ የደረቀላት ሴት (እንተ ደም ይውኅዛ)፥ በአምስቱ እንጀራና በሁለቱ ዓሣ ቡራኬ፥ አምስት ሺ ሰው መመገቡና አሥራ ሁለት ቅርጫት ማትረፉ፥ ሳምራዊት ማድጋዋን ተሸክማ ወይም ውሃውን ከዐዘቅቱ በሸንከሎዋ ስትስብ፥ ጌታ ሳምራዊትን ሲያነጋግር፥ የሰነፎቹና የብልሆቹ ደናግል ሁኔታ፥ የጴጥሮስ ክህደትና ጸጸት፥ የይሁዳ ክህደትና መምህሩን አሳልፎ መስጠት፥ በመጨረሻም ሞቱና ትንሣኤው፥ ማርያም መግደላዊትና የተነሣው፥ ክርስቶስ እመቤታችን ምስለ ፍቍር ወልዳ፥ በግራዋ በኩል ኢሳይያስ ወደሷ እያመለከተ፤ ይህም “ናሁ ድንግል ትፀንስ፥ ወትወልድ ወልደ፥ ብዬ የተናገርሁላት ይቺ ናት፤” እንደማለት ነው። ይህንና ይህን የመሳሰሉ ሌሎችም ሥዕሎች በጥንት የክርስቲያኖች መሸሸጊያ ዋሻዎች በከሰልና ባመድ ተሥለው ተገኝተዋል። ይህን ሁሉ ያደርጉ የነበረው በፊት እንደ ተባለው የሃይማኖታቸውን ታሪክ ለማስተማር ነው።
          ከዚህ ሌላ የምዕመናንን ልቡና ለማጽናናት በሰማዕትነት የሞቱት ወንድሞቻቸው ዐፅም ባረፈበት አኳያ አሟሟታቸውንም በሥዕል ይገልጹት ነበር። በዚህ አኳኋን የሥዕል ክብር በቤተ ክርስቲያን እንደ ተጠበቀ እስከ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ከቆየ በኋላ በሥዕል ምክንያት በሮምና በቢዛንታይን ግዛት በሚኖሩ ምዕመናን ዘንድ አለመግባባት ተፈጠረ። ለዚህም አለመግባባት ዋናው ምክንያት አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥዕሎችን ከመውደዳቸው የተነሣ  አማልክት ናቸው እስከ ማለት ደርሰው ስለ ነበረ ነው፤ (ኢኮኖላትሪያ)። ሌሎች ደግሞ ወደ ሌላ ጎን በማጋደል ሥዕሎችን ጨርሰን ማጥፋት አለብን ብለው የከረረ የተቃውሞ በር ከፈቱ፤ (ኢኮኖማኺያ)። በመካከሉ ደግሞ እንደነዚያም ሳያመልኩ እንደነዚህም በጥላቻ ሳይመነችኩ የጥንቱን ትምህርት ተከትለው ሥዕሎችን የሚወዱና የሚያከብሩ ምዕመናን ነበሩ። ነገር ግን በዘመኑ የነበሩት ገዢዎች ሥዕልን ማጥፋት አለብን የሚለውን ክፍል ስለ ደገፉ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመን ያቆየቻቸው ቅርሶቿ እና የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊ ኪነ ጥበብ የሚያሳዩ ሥዕሎቿ ሁሉ በእሳት ጋዩ። ብዙ ምዕመናንም በዚሁ ምክንያት አለቁ። የሥዕሎቹ መጥፋት ጉዳይ በባለ ሥልጣኖች ቢደገፍም ሥዕሎቻችን አይቃጠሉብን የሚለው ክፍል እያየለ ድምጹም እየተሰማ ሄደ፤ እንዲያውም ጠቡ እየተባባሰ ሄዶ የሮምንና የቢዛንታይንን መንግሥት የሚያናጋው ሆነ።
          ይህን በክርስቲያኖች መካከል የተነሣ ብጥብጥ በጉልበት ሳይሆን ሁለቱንም ክፍሎች በሚያግባባ የጋራ ሐሳብ ላይ ለመድረስ፥ ጠቡ በተነሣበት አካባቢ የነበሩ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች  በ፯፻፹፯ ዓ.ም. ጉባኤ አድርገው እንደ ሁለቱም ሳይሆን (እንደ ሥዕል አምላኪዎችና እንደ ሥዕል አጥፊዎች ሳይሆን) ስለ ሥዕል ክብርና ስግደት የሚገባውን ቀኖና ሠርተዋል። ከዚህም ጉባኤ በኋላ በማከታተል የተነሡ የሮማና የቢዛንታይን መለካውያን ሊቃውንት ስለ ሥዕል ክብርና የት መጣ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል። ለምሳሌ በዚያው ዘመን በዚያው አካባቢ የነበረው ስመ ጥር ሊቅ ዮሐንስ ዘደማስቆ ስለ ሥዕል ብዙ ቀዋሚና ጠቃሚ የሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። ዮሐንስ ዘደማስቆ እንደሚለው፦ ሥዕል በቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ጥቅም አለው፤ ከነዚህም አንዱ በዋሻው እንደነበሩት ክርስቲያኖች ተአምራት ነክ የቅዱሳት መጻሕፍትን ታሪኮችን ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ለማስረዳት ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ ሃይማኖቱን ሳይፈራ እና ሳያፍር መስክሮ በሰማዕትነት የሞተ ወይም ስለ ዓለምና ስለ ራሱ በመጸለይ መላ ሕይወቱን ከፍትወታት፥ ከእኩያት፥ ከአጋንንት ጋር በመጋደል ያሳለፈውን ሰማዕት ወይም ጻድቅ በሥዕል ለማስታወስ፥ በሥዕሉም አማካይነት እያንዳንዱ ምዕመን ለሥዕሉ ባለቤት ያለውን ክብርና ፍቅር ለመግለጥ ነው።
          በሥዕል ፊት ቆሞ መጸለይ ከባለ ሥዕሉ ረድኤት፥ በረከት እና ምልጃ መለመን፥ መማጠን ነው። ለሥዕል መስገድ እና ሥዕልን መሳም ደግሞ በፊት የሥዕል ተዋጊዎች ወይም ፀረ ሥዕሎች (ኢኮኖማኺ) እንደሚሉት ዛሬም ብዙ ፀረ ማርያሞች እንደሚያጥላሉት ለጣዖት መስገድ ጣዖት መሳም አይደለም። ከላይ እንደገለጥነው በሥዕሉ አማካይነት ለሥዕሉ ባለቤት ክብርና ፍቅርን ለመግለጽ ነው። ይኸውም የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ጥንታዊ ትውፊት (Tradition) ነው። በእምነትና በፍቅር የሆነ ነገር ደግሞ ያንጻል እንጂ አይንድም። የእግዚአብሔር መንግሥት የሚወረሰው በፍጹም እምነት ቅንነት በተሞላበት ፍቅርና ትሕትና እንጂ በተጥባበ ነገር (Rationalism) አይደለምና።
          በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት መሠረት ሥዕል የሚሣለው በቀለም ነው። ላቲኖች ግን ቅርጽ ይቀርጻሉ። ስለ ሥዕል ክብር በቤተ ክርስቲያን ስለተጀመረበት ምክንያት በመጠኑ ገልጠናል። አሁን ደግሞ ስለ ሥዕል ከተነሣ ዘንድ አከራካሪ ስለሆነው የጌታና የእመቤታችን ሥዕል የትመጣ እንደዚሁ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት መሠረት በማድረግ በመጠኑ እንገልጣለን።  
          ስለ ጌታ ሥዕል ብዙ ታሪኮችና ትውፊታዊ ትምህርቶች ይነገራሉ፤ በዚሁ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታን ሥዕል የሣለው ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው ይባላል። ታሪኩም ከሞላ ጐደል እንደሚከተለው ነው። ከ፲፬-፴፯ ዓ.ም. ሮምን ይገዛ የነበረው ጢባርዮስ ቄሣር ነው። በሱ ዘመነ መንግሥት ነው ጌታ የተሰቀለው፤ ይኸው ጢባርዮስ በልጁ መሞት በጣም አዝኖ ሬሣውን ሳያስቀብር ሰነበተ፥ ከጥቂት ቀንም በኋላ ጌታ በኢየሩሳሌም ያደርገው የነበረውን ታምራት ያውቅ ስለነበር፦ “ከጢባርዮስ ቄሣር ምድራዊ ንጉሥ የተላከች ጦማር (መልእክት) ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሠ ሰማይ ወምድር ትድረስ” ብሎ ልጁን እንዲያስነሣለት የምልጃ የልመና ጽሑፍ ጽፎ ይህችን መልእክትና የልጁን ሬሣ ወስደው ጐልጐታ (የጌታ መቃብር) ላይ እንዲያኖሩለት ባለወጐቹን ላከ። እነሱም ሄደው ደብዳቤዪቱንና ሬሣውን በጌታ መቃብር ላይ ሲያኖሩት ሬሣው አፈፍ ብሎ ተነሥቷል። ጢባርዮስም ከደስታው ብዛት የተነሣ የጌታን ውለታ ለመክፈል የዚህንስ ሰው እናቱን አምጥሉኝ እኔ ቋሚ ለጓሚ፥ ሚስቴ ገረድ ደንገጡር ሁነን እናገለግላታለን ብሎ እንደገና ሰው ቢልክ፥ የድንግል ማርያም ክብር ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ ስላልሆነ ተሰውራባቸው አላገኟትም። ጢባርዮስ ግን ተስፋ እንዳይቆርጥ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዕለተ ዓርብ በመስቀሉ ላይ እንዳየው አድርጐ ከለሜዳ አስታጥቆ ጌታን ሥሎለታል። ስለ ሥዕሉ እውነተኛነትም ለማረጋገጥ ዮሐንስ የሣለው ይህ ሥዕል “አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደ ሰቀሉኝ አንተ ደግሞ ሁለተኛ ሰቀልከኝን?” የሚል ድምጽ አሰምቷል። ሥሎ ሲጨርስ ዮሐንስ ቢስመው ከንፈሩ ከሥዕሉ ጋር ተጣብቆ ቆይቷል። ይህ ሁሉ ከሥዕሉ የታየው ተአምራት ነው። “አይሁድ የሰቀሉት ራቁቱን ነበር፥ ከለሜዳ አስታጥቆ መሣል የተጀመረው ከዚያ ወዲህ ነው፤” እያሉ የሀገራችን ሊቃውንት ይተርካሉ።
          ስለ ጌታ ሥዕል ሁለተኛው ምንጭ (መነሻ) ጴላጦስ ለጢባርዮስ ቄሣር ስለ ጌታና ስለ እናቱ ስለ እመቤታችን የላከው ሥዕላዊ መግለጫም አለ። ጲላጠስ በቅዱስ መጽሐፍ እንደሚታወቀው በፍልስጥኤም የሮማ መንግሥት እንደራሴ የነበረና በጌታም ሞት የፈረደ ነው። ወደ ጢባርዮስ ቄሣር የላከው መልእክት እንደሚከተለው ነው። “ለጢባርዮስ ቄሣር፤ ሰላም ላንተ ይሁን፥ ኢየሱስ ስለሚባለው ሰው ግርማዊነትህ ለማወቅ የጠየቀውን ለማሟላት ከዚህ የሚከተለውን እጽፍልሃለሁ። በዚህ እኔ እንደራሴህ አድርገህ በሾምኸኝ በፍልስጥኤም ምድር፥ እጅግ በጣም የተለየ መልክና ሥልጣን ያለው አንድ ሰው ተነሥቷል። ታላቅ መምህርና ነቢይም ነው ይሉታል። ደቀመዛሙርቱ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ነው ይላሉ። ስሙ ኢየሱስ ይባላል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ቄሣር ሆይ ይህ ኢየሱስ የተባለው ክርስቶስ በየጊዜው ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርጋል፤ ሙታንን ያስነሣል፥ ድውያንን ከማናቸውም ደዌና ሕመም ይፈውሳል። ከዚህም ጋር ጥልቅና መንፈሳዊ በሆነ ትምህርቱ መላዋን ኢየሩሳሌምን አስደንቋታል። አቋሙና አካሉ ግርማ ያለው፥ መልኩም አንጸባራቂ እና ጸጋ የተሞላበት በመሆኑ ማናቸውም የሚያየው ሁሉ ይወደዋል፥ ይፈራዋልም። አንዳንድ ጊዜ ቀላ ያለው መልኩና መሐል ለመሐል ተከፍሎ የሚታየው ጽሕሙ የሚሰጠው ውበት ፍጹም ግምት የሌለው ነው። የፊቱ ቅርጽ  መልአካውያን ዓይኖቹና የጥቁር ወርቃማ ጠጉሮቹም አወራረድ በሚሰጡት የተንጸባረቀ ውበት ማንም ሰው ቢሆን ለረጅም ጊዜ አተኩሮ ሊመለከተው አይችልም። የሚመስለው እናቱን ነው። እሷም ደግሞ በዚህ ክፍለ ሀገር በማንም ላይ ያልታየ ውበትና የትሕትና መልክ ያላት ናት። ቆራጥ ከባድና የሚያከራክሩ ንግግሮቹም በውስጣቸው የሚገኘው ፍጹም የሆነ የመንፈስ ልዕልናና የዕውቀት መጠናቸው ከታላላቅ አዋቂዎች ተብለው ከሚገመቱት ሰዎች እጅግ አድርጐ የራቀ የጠለቀ ምሥጢር አላቸው። በተግሣጽና በእዝናት ጊዜም በጣም ኃይለኛ ነው። በማስተማርና በማበረታታት ጊዜ ደግሞ ትሑት ተወዳጅና ልብ የሚመስጥ ነው። ራሱን ሳይከናነብና መጫሚያ ሳይጫማ በእግሩ ይሄዳል። በሩቅ የሚያዩት አንዳንዶች ይስቁበታል፥ ነገር ግን ወደፊቱ ሲቆሙና ሲቀርቡ በመንቀጥቀጥ ያደንቁታል። ማንም ቢሆን ሲስቅ አየሁት የሚል የለም። ነገር ግን ብዙዎች ሲያለቅስ አይተውታል። የቀረቡት ሁሉ ብዙ ሥራና ፈውስ ማግኘታቸውን ይናገራሉ። ነገር ግን ገዥና ተገዥ ሁሉም (ባባቴ ፊት) በእግዚአብሔር ፊት እኩል ናቸው፥ ምንም ልዩነት የላቸውም ብሎ ስለሚያስተምር የግርማዊነትህ አጥፊ ሳይሆን አይቀርም በማለት ብዙ ሰዎች እየመጡ ይነግሩኛል። ስለዚህ ጉዳይ ብታዝዘኝ ወዲያውኑ ትእዛዝህ የሚፈጸም ይሆናል። ጤና ሁን፥ ፒ ሌንቱሎ”

               በቤተ ክርስቲያን አባቶች የታሪክ መዝገብ ደግሞ ስለ ጌታ ሥዕል በተአምራታዊ አገላለጥ የተጻፉ ብዙ አስተያየቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳብዮስ እንደጻፈው አብጋር የተባለው የዑር ንጉሥ ከደዌው የተፈወሰው የጌታን ሥዕል ባየ ጊዜ ነው ይላል። ሙሉው ታሪክ እንደሚከተለው ነው። “አብጋር” ስመ መንግሥት ነው። ዓፄ ጃንሆይ እንደ ማለት ነው፤ “አባጋር” እንዲሉ ዛር አንጋሹን። ዑር በእመስጰጤምያ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት። ጽርዓውያን “ኤዴሣ” ይሏታል፥ በኛም “ሮሐ” ትባላለች። አብጋሮች በዑር መንገሥ የጀመሩት ከ፩፻፴፪ - ፪፻፲፮ ከጌታ ልደት በኋላ ነው። በጌታ ጊዜ የነበረው አብጋር ዮካማ (ዑካማ) ይባል ነበር። አምስተኛው ወይም ሰባተኛው አብጋር ነው። ይህ አብጋር ዮካማ ከጌታ ጋር ይጻጻፍ እንደነበር አውሳብዮስ ይተርካል። አውሳብዮስ ታሪኩን ሰፋ በማድረግ ሲያብራራ እንዲህ ይላል። በማይድን በሽታ ተይዞ የሚሰቃይ በኤፍራጥስ ወንዝ በላይ የነገሠ አብጋር ንጉሥ ነበር። በዘመኑ ለነበረው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ መልእክት (ጦማር) ጽፎ የግል ታማኙ ለነበረው ለግምጃ ቤቱ ሹም ሰጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። ይህ ሰው በአብጋር ቤተ መንግሥት ሥዕል በመሳል የታወቀ ነበር። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነው፦ “ስለ አንተና ስለምታደርገውም ተአምራት እሰማለሁ፥ ያንተ ማዳን እንደሌሎች ዐቀብተ ሥራይ ስር ምሰህ፥ ቅጠል በጥሰህ አይደለም። አንተ ያዳንኸው ተረፈ ደዌ የለበትም። እንደሰማሁት ዕውራን እንዲያዩ ታደርጋለህ፥ ልሙጻንን ታነጻለህ፥ ርኩሳን መናፍስትን ታሳድዳለህ፥ በማይድን በሽታ የተያዙትንም በምሕረትህ ትፈውሳቸዋለህ፥ ሙታንን ታነሣለህ። ስለዚህ ወደኔ እንድትመጣና ከዚህ ከሚያሰቃየኝ ደዌዬ እንድትገላግለኝ፥ ለእኔም ምሕረት እንዲደርሰኝ ይህችን የልመና ደብዳቤ ጻፍሁልህ። አይሁድ ባንተ ላይ ክፉ ነገር እንዳሰቡና ክፉ ሊያደርጉብህም እንደከጀሉ እሰማለሁ፥ ከተማዬ በጣም ትንሽ ናት፥ ትነስ እንጂ በጣም ውብ ናት፤ ለሁለታችን ትበቃናለች፥ እባክህን ና።” የሚል ደብዳቤ ጽፎ ለጌታ ላከለት። ጌታም የሚከተለውን መለሰለት። “አብጋር ሆይ፥ ሳታየኝ ስላመንህብኝ ብፁዕ ክቡር ነህ፥ ስለእኔ ተጽፏልና የሚያዩኝ እንዲንቁኝ፥ የማያዩኝ ግን እንደሚያምኑብኝ። በኔ ያመኑ ሕያዋን ሁነው ይኖራሉ። እኔም አስቀድሜ የመጣሁበትን ሥራ መፈጸም አለብኝ፥ ከፈጸምሁም በኋላ ወደላከኝ እሄዳለሁ። ከሄድኩ በኋላ ከደዌህ እንዲፈውስህና ላንተና ለቤተ ሰዎችህም የሕይወትን ቃል እንዲያስተምራችሁ ከደቀ መዛሙርቴ አንዱን እልክልሃለሁ። ከተማህም የተባረከች ትሆናለች፥ ጠላቶችህ አይገዟትም።” ብሎ መልስ ላከለት። ጌታ ካረገ በኋላ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ (ዕፃው በእስያ ስለነበር) ከሰበአ አርድእት አንዱን ታዴዎስን ወደ ዑር ላከው፤ ታዴዎስም እዚያ እንደ ደረሰ ለጊዜው ያረፈው ጥንት በፍልስጥኤም በሚያውቀው በአንድ አይሁዳዊ ቤት ነበር። ከዚያ ሁኖ በማስተማርና ተአምራት በማድረግ ጥቂት እንደቆየ ወደ ቤተ መንግሥት ሄደ። ታዴዎስ ገና ሲገባ ንጉሡ አብጋር አስደናቂ ግርማ በታዴዎስ ገጽ ላይ አየ። በቤተ መንግሥቱ የነበሩት ባለሟሎቹና የወንድ መኳንንት፥ የሴት ወይዛዝርት ግን ምንም እንኳ ለአብጋር የተገለጸው ባይገለጽላቸውም፥ ታዴዎስ እዚያ በመገኘቱ አንክሮና ተመስጦ ሳያድርባቸው አልቀረም። ንጉሡና ታዴዎስ ሲወያዩ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ታዴዎስ፦ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እጄን እጭንብሃለሁ ብሎ እጁን ጫነበት፥ በዚህ ጊዜ አብጋር ከነበረበት ሁሉ ደዌ ተፈወሰ። ታዴዎስም የሕይወትን ቃል እያስተማረ በዚያች ቦታ ብዙ ቆዩ። የከተማዪቱም ነዋሪዎች ክርስቲያኖች ሆኑ፥ አውሳብዮስ ታሪኩን ከዚሁ ላይ ያበቃል።
          ሌሎች የኋላ አባቶች ግን ይህን ታሪክ ሳይለውጡ፥ አብጋር ወደ ጌታ የላከው ሰው ሠዓሊ ስለነበር፥ ወዲያው ጌታን ሲያይ ልቡ ስለተመሰጠ ሥዕሉን በንድፍ ለማስቀረት ፈለገ። ጌታን በሚያነጋግርበት ጊዜ ዓይኑን ጣል እያደረገ የጌታን ገጽ በወረቀት ነድፎት ነበር። ወደ ሀገሩ ሲመለስ ያንን ለአብጋር አሳየው፥ እሱም ባየው ጊዜ በፍጹም እምነት ከመሬት ወድቆ ሰገደ፥ ያን ጊዜም ከደዌው ተፈወሰ ይላሉ። ከዚህ በማያያዝ ይህ ሥዕል ገባሬ ተአምር ስለሆነ ሁሉ ሊሰግድለት ይገባል ብሎ በሕዝብ መሰብሰቢያ አደባባይ ከፍ ያለ ቦታ አበጅቶ እዚያ ላይ እንዲሰቀል አዘዘ፥ በአብጋርና በልጁ ዘመነ መንግሥት ሁሉም እየመጣ ለዚህ ሥዕል ሲሰግድ ኑሯል።
          አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ስለጌታ ሥዕል ሌላ ምንጭ ያመለክተናል፤ እሱ እንደሚለው፥ “በወንጌል የታወቀችው እንተ ደም ይውኅዛ ውለታ ለመክፈል ስትል የቅርጽ ሐውልት አሠርታለት ነበር” ይላል። የቤሮኒኪም ታሪክ ለጌታ ሥዕል ጥሩ መነሻ ነው። ጌታ በዕለተ ዓርብ ደሙን እያንጠፈጠፈ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ጐልጐታ በሚወጣበት ጊዜ መስቀሉ ከብዶት፥ ደሙ ዓይኑን ጋርዶት አይታ ልቧ በሐዘን ስለተነካ ለተከተሉት ለአንዱ ቤሮኒኪ ሻሿን አውልቃ ፊቱን እንዲያድፍበት ወረወረችለት፥ አድፎ ሲመልስላት ገጹ ከሻሿ ላይ ታትሞበት ቀረ ይባላል። ስለ ጌታ ሥዕል መነሻ ታሪካዊና ተአምራታዊ ምንጮች ብዙ አሉ። ዮሐንስ ወንጌላዊና ጴጥሮስ በባዶው መቃብር ውስጥ ገብተው ባዩት ጌታ ተገንዞበት በነበረው ከፈንና (ሰበን) መጠምጠሚያ ላይ የጌታ አካል ታትሞበት ነበር፥ የሚል የቤተ ክርስቲያን ትውፊት አለ። ስለ ጌታ ሥዕል የት መጣ ከመሉ በከፊሉ ይህ ነው። ስለ እመቤታችን ሥዕል ደግሞ በመጀመሪያ የሣላት ሉቃስ ነው ይባላል። በኛም ቤተ ክርስቲያን ያሉት የመዝሙርና የጸሎት መጻሕፍት የእመቤታችንን ሥዕል ሉቃስ መሣሉን ይናገራሉ። “ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዐላ በዓዱ፥ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ፤” ይላል።       

          ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ
        (በአባ ጎርጎርዮስ የተዘጋጀ፤ ፲፱፻፸፬ እና ፲፱፻፹፮ ዓ.. የታተመ።)


5 comments:

 1. this is the best article we should read. i feel confident in reading it. what ever the question raised it gave me clear picture about it.

  ReplyDelete
 2. ያስትማረን እግዚአብሔር ስሙ ይባረክ መንፈሳዊ ስጦታውንም ለአባታችን ያድልልን ውስጤ በጣም ተደስቶበታል በትምህርቱ በሀይማኖቴ አኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፍጹም ኮርቻለሁ ታሪክና የማንነት የራሷ የሆነ መገለጫ ያላት እውነተኛና ቀጥተኛ ሃይማኖት የምከተል ብመሆኔ አምላኬን አምሰግነዋለው የድንግል ልጅ ተዋህዶን ይባርክ ይጠብቅ አሜን!!

  ReplyDelete
 3. አባታችን ኦድሜና ጤና ይስጥልን። እባኩወትን አያቋርጡ።

  ReplyDelete
 4. ግሩም ነው ቃለ ሕይወት ያሰማልን
  አናውቅ ብለን እንጂ ታሪካችንማ ምን ማለቂያ አለው ?

  ReplyDelete
 5. ያስትማረን እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን እንደናንተ ያሉትን አገልጋዬች በዕድሜ በጤና ይጠበቅንል፡፡ይክበር ይመስገን እንደናንተ ያሉትን አገልጋዬች በዕድሜ በጤና ይጠበቅንል፡፡ መንፈሳዊ ስጦታውንም ለአባታችን አብዝቶ ያድልልን :፡ ውስጤ በጣም በትምህርቱ ተደስቶበታል:: በሀይማኖቴ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፍጹም ኮርቻለሁ ታሪክና የማንነት መገለጫ ያላት እውነተኛና ቀጥተኛ ሃይማኖት የምከተል ብመሆኔ አምላኬን አምሰግነዋለው የድንግል ልጅ ተዋህዶን ይባርክ ይጠብቅ አሜን!!

  ReplyDelete