Sunday, December 9, 2012

“በውኑ ሞት እንዲህ መራራ ነውን ?”


          ይኽንን ኃይለ ቃል በቀቢጸ ተስፋ የተናገረው የአማሌቃውያን ንጉሥ አጋግ ነው። አማሌቃውያን ከዔሳው የልጅ ልጅ ከአማሌቅ የተገኙ ነገዶች ናቸው። ዘፍ ፴፮ ፥፲፪ ኑሮአቸው ከእሥራኤል አገር በስተደቡብ ነበር። ከነቢያት አለቃ ከሙሴ ጀምሮ እስከ ንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ድረስ እስራኤልን ይቃወሙ ነበር። “አማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል ጋር በራፊድ ተዋጋ። ሙሴም ኢያሱን፦ ጐልማሶችን ለአንተ ምረጥ፥ ሲነጋም ወጥተህ ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፥ እኔም በተራራው ራስ ላይ እቆማለሁ፥ የእግዚአብሔርም በትር በእጄ ናት፥ አለው። ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ወጥቶም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮን ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። እንዲህም ሆነ፥ ሙሴ እጁን በአነሣ ጊዜ (በአምሳለ መስቀል እጆቹን ግራና ቀኝ በዘረጋ ጊዜ) እስራኤል ድል ያደርግ ነበር፥ ደክሞትም እጁን በአወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር። ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፥ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፥ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ተዘርግተው ነበር። ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ።” ይላል። ዘጸ ፲፯፥፰-፲፫። (ሙሴ በአምሳለ መስቀል እጆቹን ዘርግቶ በእሥራኤል ዘሥጋ ኃይል መንፈሳዊን አሳድሮባቸው ድልን እንዳጐናጸፋቸው፦ እኛም በመስቀሉ ኃይል በአጋንንት ላይ ድልን እንጐናጸፋለን)።

          የእሥራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ መሥራትን በሚያበዙበት ጊዜ ለአማሌቃውያን ተላልፈው ይሰጡ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ከኢያሱ በኋላ በዘመነ መሳፍንት የሆነውን ሲናገር፦ “የእሥራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ዔግሎሞን በእስራኤል ልጆች ላይ አበረታባቸው። የአሞንን ልጆችና አማሌቅን ወደ እርሱ ሰበሰበ፥ ሄዶም እስራኤልን መታ፤” ይላል። መሳ ፫፥፲፪-፲፫፤ ፮፥፫። ብዙ ጊዜ ከታናናሹ ጀምሮ እስከ ታላላቁ ድረስ እጅግ የከፉ መሪዎችን የሚያዝብን ኃጢአታችን በእግዚአብሔር ፊት ሲበዛ ነው። ይልቁንም በዚህ ዘመን “መንፈሳውያን ነን፤” ከምንል መሪዎች እንኳ በጎነት እና ርኅራኄ አልተገኘብንም። መንጋውም እረኞችም ሁላችንም በደለኞችን ነን። ቅዱስ ዳዊት፦ “ሁሉ ተካክሎ በአንድነት በደለ፤” ያለው ይኽንን ነው። መዝ ፶፪፥፫። ይህም በሚበዛው ለመናገር እንጂ ከእረኞችም ከበጎችም ለምልክት የቀሩ አብነቶች ፈጽመው አልጠፉም።
          እሥራኤል ዘሥጋ በእግዚአብሔር ኃይል ከባርነት ቤት ወጥተው ወደ ምድረ ርስት በሚጓዙበት ጊዜ ከላይ እንደጠቀስነው አማሌቃውያን መንገድ አላሳልፍ ብለው አስቸግረዋቸው ነበረ። “የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች፤” እንዲል በሙሴ የምልጃ ጸሎት እግዚአብሔር ባይረዳቸው ኖሮ በመንገድ በቀሩ፥ ለዘርም ባልተረፉ ነበር። ነገር ግን ስለ አብርሃምና ስለ ይስሐቅ፥ ስለ ያዕቆብም ብሎ ቃል ኪዳኑን ከሕዝቡ ጋር ያጸና አምላክ፥ ከመላእክት ወገን ቅዱስ ሚካኤልን፥ ከሰው ወገን ሙሴን፥ ከእርሱም በኋላ ኢያሱን ሰጥቶ፥ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር አውርሶአቸዋል። (ማር ምሳሌነቱ ለሕገ ኦሪት፥ ወተት ደግሞ ለሕገ ወንጌል ነው፥ ምድረ ርስት ደግሞ የቤተ ክርስቲያን እና የገነት የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት።) ለእኛም እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሰጥቶናል። ዮሐ ፲፱፥፳፮። ቅዱሳን መላእክት፥ ቅዱሳን ጻድቃንንም ሰጥቶናል፡ ማቴ ፲፥፵፣ ዕብ ፩፥፲፬። ከሁሉም በላይ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን አንድ የባሕርይ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰጥቶናል። ዮሐ ፲፫፥፲፮። ሐዋርያው ቅሱስ ጳውሎስ፦ “እንግዲህ ስለዚህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይችለናል? (እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ፥ ከነፍሳችንም ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ከሆነ ማን ያሸንፈናል?) ለልጁ ስንኳ አልራራም፥ ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጎ አሳልፎ ሰጠው እንጂ፥ እንግዲህ እርሱ ሁሉን እንዴት አይሰጠንም? (አንድ ለጁን እንኳ ያልከለከውን ሁሉን ይሰጠናል)። ያለው ይኽንን ለማስገንዘብ ነው። ሮሜ ፰፥፴፩።
          እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ስለተፈጸመባቸው በደል አማሌቃውያንን የሚበቀልበት ጊዜ ሲደርስ ነቢዩ ሳሙኤልን ወደ ሳኦል ላከው። ነቢዩም፦ “በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እቀባህ ዘንድ እግዚአብሔር ላከኝ፤ አሁንም የእግዚአብሄርን ቃል ስማ።” ካለው በኋላ አማሌቃውያንን ሀብት ንብረታቸውን ጭምር እንዲያጠፋ የእግዚአብሔርን መልእክት ነገረው። ሳኦልም አማሌቃውያንን ከኤውላጥ ጀምሮ በግብፅ ፊት እስካለችው እስከ ሱር ድረስ መታቸው። ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ ሁሉ አጋግን፥ ከከብቱና ከበጉ መንጋ መልካም መልካሙን፥ እህሉንም፥ ወይኑንም፥ መልካም የሆነውን ሁሉ አዳኑ። ፈጽመውም ሊያጠፉአቸው አልወደዱም።
          ንጉሥ ሳኦል እግዚአብሔርን ከመከተል ይልቅ የራሱን አሳብ በመከተሉ ለእግዚአብሔር ሳይታዘዝ ቀረ፥ እግዚአብሔርም አዘነበት። ማዘኑንም ለነቢዩ ለሳሙኤል ነገረው። እግዚአብሔር ሐዘኑንም ሆነ ደስታውን ለወዳጆቹ ለቅዱሳን ይገልጥላቸዋልና። ነቢዩ ሳሙኤልም ያጠፋውን ጥፋት ለንጉሡ ከነገረው በኋላ “የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነህ እንዳትቀጥል ናቀህ፤” ብሎት ሊሄድ ሲል “እባክህ ተመለስ፤” ብሎ የነቢዩን ልብስ ቢይዝ ተቀደደ። በዚህን ጊዜ፦ “እግዚአብሔር ከእስራኤል መንግሥትህን ዛሬ ከእጅህ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለባልንጀ ራህ አሳልፎ ሰጣት፤ እስራኤል ለሁለት ይከፈላል፥ ከእንግዲህም አይሰበሰብም። እግዚአብሔርም እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይጸጸትም።” ብሎ የልብሱን መቀደድ ምሥጢር ተረጐመለት። ሳኦልም፦ “በድያለሁ፥ አሁንም በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት እባክህ አክብረኝ፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመ ለስ፤” አለው። ሳሙኤልም ከሳኦል ጋር ተመለሰ፥ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ። ዛሬ ማነው? መሪዎችን “ተሳስታችኋል፤” የሚላቸው። ከመሪዎችስ “በድያለሁ፤” የሚሉ እነማን ናቸው? ይህ ዘመን የሚገሥጽም የሚገሠጽም የጠፋበት ዘመን ነው። የተግሣጹ ሥልጣን የተሰጠን ሰዎች ሰማዕትነትን ፈርተናል። ይህም ብቻ ሳይሆን እኛው ራሳችን እጥፍ ድርብ ተግሣጽ የሚገባን ሰዎች ሆነን ተገኝተናል።
          በመጨረሻም፦ ነቢዩ ሳሙኤል፦ “የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ፤” አለ። አጋግም እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ። ብዙ መሪዎች በሠራዊት ታጅበው፥ በጦር መሣሪያ ታጥረው፥ ሲናገሩ ጀግና ይመስላሉ እንጂ፥ ለብቻቸው ሲያዙ የመጨረሻ ፈሪዎች ናቸው። እውነተኞቹ ጀግኖች ግን ከሠራዊት ጋር ሆኑ፥ ለብቻቸውም ሆኑ ያው ናቸው። ሞትን አይፈሩም። ጀግና ሰው፦ “ዘጠኝ ሞት መጣ፤” ቢሉት “አንዱን ግባ በለው፤” አለ፦ የተባለው ለዚህ ነው። እነ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሞትን አልፈሩም። ለሃይማኖታቸውም ለሀገራቸውም ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። በፋሽስት ኢጣሊያ እና በባንዳ ኢትዮጵያውያን እጅ ተይዘው ከመረሸናቸው በፊት “ዓይኔን በጥቁር ጨርቅ አትሰሩኝ፤ ሞትን አልፈራውም፤ እያየሁት እሞታለሁ፤” ያሉት ለዚህ ነው። በሞት አጠገብ ሕይወት፥ በመቃብር አጠገብ ትንሣኤ እንዳላቸው ስለሚያውቁ ሞትን ናቁት። በዚህም ሕዝቡን ከባርነት ቤተክርስቲያኒቱን ደግሞ ከካቶሊክነት አዳኑ። አርበኛውን ጀግነው አጀገኑት። ጣልያኖች ከሰባ ሁለት ዓመታት በኋላ ግፉ የተረሣ መስሏቸው ለፋሽስቱ መሪያቸው ለግራዝያኒ በሀገራቸው ላይ ሐውልት ሲያቆሙ፥ እኛ ደግሞ ቅዱስ ተብለው ጽላት ተቀርጾላቸው ቤተክርስቲያን የታነጸላቸውን ሰማዕት የአቡነ ጴጥሮስን ሐውልት እንደ ዋዛ ይነሣል፥ እያልን ነው። የእርሳቸው ሐውልት እኮ ንዋይ ቅዱስ ነው። በዚህ ዘመን ተመልሶ ከቦታው ላይ እንደሚተከል እርግጠኞች መሆን አንችልም።
          አጋግ ግን ሃይማኖት ስለሌለው፥ የእጁንም እንደሚያገኝ ስላወቀ ፈራ፥ ተንቀጠቀጠ። ከጭንቀት ብዛት ጅማቶቹ እርስ በርሳቸው ተለያዩ፥ አጥንቶች ጉልጥምቶቹ ተላቀቁ። ይህ ሰው የብዙ ንጹሐንን ደም አፍስሷል። ወላጆችን ገድሎ ልጆችን፥ ልጆችን ገድሎ ወላጆችን፥ ባልን ገድሎ ሚስትን፥ ሚስትን ገድሎ ባልን አስለቅሷል። ሌላው ሲያለቅስና ሲያዝን እርሱ ይስቅ ይደሰትም ነበር። ዘመዶቹም መኳንንቱም አብረውት ይደሰቱ ነበር። ጨካኝ መሪዎች ከዚህም አልፈው የሰው ልጅ ለሟች ወገኑ እንዳያለቅስ የሚከለክሉበትም ጊዜ አለ። ተራቸው ደርሶ፥ ሞት ዓይኑን አፍጥጦ ሲመጣባቸው ግን ሜዳው ገደል፥ ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል። ሰይፋቸው በሰው ደም እንዳልሰከረ፥ ሰይፍ ሲመዘዝባቸው ኅሊናቸው ይደነግጣል፥ ልባቸው ይፈራል፥ ጉልበታቸው ይንቀጠቀጣል። ከመቅጽበት ገጻቸው ይለወጣል፥ ይከሳሉ፥ ይሟሽሻሉ፥ ይጠቁራሉ። አጋግ፥ “በዉኑ ሞት እንዲህ መራራ ነውን?” ያለው ለዚህ ነው። ለእርሱ ሲሆን መረረው፥ ጐመዘዘው። ሰይፍ ሳይደርስበት በቁሙ ሞተ። ነቢዩ ሳሙኤልም በቁሙ በፍርሃት የሞተውን አጋግን “ሰይፍህ ሴቶችን፦ ልጆች አልባ እንዳደረጋቸው እንዲሁ እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች።” ብሎት በጌልጌላ በእግዚአብሔር ፊት ወጋው። እግዚአብሔር አጋግን በነቢዩ በሳሙኤል እጅ ተበቀለው። በዚህን ጊዜ የአጋግ እናትና ዘመዶቹ፥ ከእርሱ ተጠግተው የተጠቀሙ ግብረ በላዎቹም ተራቸውን ጥቁር ለበሱ፥ በአደባባይ አለቀሱ፥ አስለቃሾች አቁመው ደረታቸውን ደቁ፥ ፊታቸውን ነጩ፥ ድንኳን ተክለው አስተክለው ሐዘን ተቀመጡ፤ ከንጉሡ ከአጋግ ሞት አልተማሩም፥ እንዲያውም የአጋግ መንገድ መልካም መስሎአቸው እርሱ በጀመረው መንገድ፥ በቀደደውም ጐዳና እንቀጥልበታለን ብለው ለራሳቸው ቃል ገቡ። ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፥ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው፤” ያለው እንዲህ ዓይነቱን ጐዳና ነው። የአሕዛብ ነገሥታትን ታሪክ ስናነብ የምንረዳው ከአጋግ ጥፋትና ሞት አለመማራቸውን ነው።
          ለክፉዎች ሞት መራራ ነው። ይልቁንም ሁለተኛው ሞት ምረረ ገሃነም ይጠብቃቸዋል። በእግዚአብሔር ዳኝነት ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ፥ ሥቃያቸውም አያልቅም። ራእ ፲፬፥፲፩፤ ፳፥፲፫። በማርቆስ ወንጌል “ትሉ ወደማያንቀላፋበት እሳቱ ወደማይጠፋበት፤” ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ነው። ማር ፱፥፵፬-፵፰ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ “እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስንም ወንጌል የማይሰሙትን ይበቀላቸዋል። ከጌታችን ፊት፥ ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘለዓለም ጥፋት ፍዳቸውን ያገኛሉ።” ብሏል። ፩ኛ ተሰ ፩፥፱። ከነቢያትም ነቢዩ ኤርምያስ፦ “እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያል ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፥ ስለዚህ አሳዶቼ ይሰናከላሉ፥ ለዘለዓለምም የማይረሳ ጉስቍልናቸውን አላወቁምና ፈጽመው አፈሩ።” በማለት ተናግሯል። ኤር ፳፥፲፩። ነቢዩ ዳንኤል ደግሞ፦ “በምድርም ትቢያ ውስጥ ከአንቀላፉት ብዙዎች እኵሌቶቹ ለዘለዓለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ለእፍረትና ለዘለዓለም ጉስቍልና ይነሣሉ።” ብሏል። ዳን ፲፪፥፪።
          እንግዲህ የነፍስና የሥጋ መለያየት እንደ አጋግ የመረረን ወይም የሚመርረን ሰዎች ሁለተኛው ሞት (ምረረ ገሃነም) ሲመጣ “እንዴት ልንሆን ነው?” ማለት ይገባል። ከዚህም ተነሥተን የመጀመሪያውንም የሁለተኛውንም ሞት መራራ የሚያደርገው ክፋታችን መሆኑን አውቀን ከክፋት ወደ በጎነት መመለስ ይኖርብናል። ያን ጊዜ ሞታችን እንቅልፍ (እረፍት) ይሆንልናል። ፩ኛ ነገ ፪፥፲፣ የሐዋ ፯፥፷፣ ራእ ፲፬፥፲፫። በክርስቶስ ሞት የተሻረ ሞት በእኛ ላይ ሥልጣን አይኖረውም። ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፶፫-፶፯፣ ፪ኛጢሞ ፩፥፲፣ ዕብ ፪፥፱፤ ፲፬፥፲፭፣ ራእ ፲፰። ሞት ከክርስቶስ ጋር ለዘለዓለም የሚያኖረን መንገድ ይሆንልናል። ኢሳ ፴፭፥፲፤ ፵፭፥፲፯፣ ዳን ፯፥፲፬፤ ፲፪፥፪፣ ሉቃ ፳፫፥፵፫፣ ዮሐ ፭፥፳፬፣ ፩ኛተሰ ፬፥፲፫። እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፦ “እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፤ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛል፥ ይበልጥብኛልም።” እንላለን። ፊል ፩፥፳፫። እንደ ቅዱስ ጴጥሮስም፦ “እግዚአብሔር የሚመጣበትን፥ ሰማያትም ቀልጠው የሚጠፉበትን፥ ፍጥረትም ሁሉ ተቃጥሎ የሚጠፋባትን ዕለት በተስፋ እየጠበቃችሁ ፍጠኑ። እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርባቸውን አዲሶቹን ሰማያትና አዲሲቱን ምድር ተስፋ እናደርጋለን።” እያልን በተስፋ መንግሥተ ሰማያት እንኖራለን። ፪ኛ ጴጥ ፫፥ ፲፪-፲፫። እንደ ቅዱስ ዮሐንስ “ዓለሙንና በዓለም ያለውን አትውደዱ፤ ዓለሙን የሚወድ ግን የአብ ፍቅር በእርሱ የለም። በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት፥ ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም እንጂ ከአብ አይደለም። ዓለሙ ያልፋል፥ ምኞቱም ያልፈል፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል።” በማለት በሕይወት እንተረጉመዋለን። ፩ኛ ዮሐ ፪፥፲፭-፲፯። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፥ አሜን።

8 comments:

 1. እግዚአብሔር የአገልግሎት ዘመንዎን ያርዝምልን የሕይወት ቃል ያሰማልን

  ReplyDelete
 2. የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል።ቃል ሕይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 3. tatek fekadu December 12, 2012 6:04 AM

  እግዚአብሔር የአገልግሎት ዘመንዎን ያርዝምልን የሕይወት ቃል ያሰማልን

  ReplyDelete
 4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መድኅኒዓለም ሲፈቅድ አንድ ቀን ወደ ኢጣሊያን ጎብኙን

  ReplyDelete
 5. Egziabher yibarkiwot melkam timihirt new. Klale hiwot Yasemalign

  ReplyDelete
 6. kale hiwet yasemalen

  ReplyDelete
 7. kale hiwet yasemalen

  ReplyDelete
 8. የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው ግን ለዘለዓለም ይኖራል።ቃል ሕይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete