Monday, December 17, 2012

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፭


በእንተ ታቦት
            ታቦት፦ ከብሉይ ኪዳንና ከእሥራኤል የነፃነት ሕይወት ጋር የተያያዘ ታሪክና የት መጣ አለው። ታሪኩና የት መጣው የታወቀ ቢሆንም ለመግቢያ ያህል በመጠኑ ከዚህም እናነሣለን። እሥራኤል በግብፅ ለአራት መቶ ሠላሳ ዓመታት ያህል በባርነት ቀንበር ሲገዙ ከኖሩ በኋላ በሙሴ መሪነት በእግዚአብሔር ተአምራት ከግብፃውያን የአገዛዝ ቀንበር ነፃ ወጡ።ወደ አገራቸውም ለመመለስ አርባ ዗ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሀ ሲኳትኑ ኖሩ። በግዞት ሳሉም ሆነ አሁን በጉዟቸው ከአባቶቻቸው የወረሱትን ሃይማኖት አልረሱም። “ የአብርሃም ፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብም አምላክ፤” አድነን ፥ ፍረድልን ከማለት አቋርጠው አያውቁም ነበር። ይህን ጽኑ እምነታቸውንና በስሙ ስለተጠሩ የሚደርስባቸውን ሥቃይና ግፍ ተመልክቶ ነፃ አወጣቸው። ነፃ ካወጣቸውም በኋላ በድብቅ በግዞት ያቀርቡ የነበረውን አምልኮት ነፃ ሕዝብ ሁነው በነፃ እንዲያመልኩት ራሱ ስለፈለገ፥ በዚያው ሲጓዙበት በነበረው በረሀ ውስጥ በምትገኝ በሲና ኮረብታ ላይ ለመሪያቸው ለሙሴ ተገልጦ የወለባ የቃል ኪዳንና የመታዘዝ ምልክት የሚሆኑ አሥር ሕግጋትና ትእዛዛት የተጻፈባቸው ሁለት የዕብነ በረድ ገበታዎችን (ሠሌዳዎችን) ሰጠው። ለእሱም ማስቀመጫ ታቦትና እንደ መቅደስም የምታገለግል የምስክር ድንኳን እንዲሠራ ሙሴን አዘዘው ዘጸ ፳፬፥፲፪፤ ፲፭፥፲፰፤ ፳፭፥፲፣፳፪። ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው። ታቦት  ዘጸ ፳፭፥፲፣ ዘሌ ፲፮፥፲፪። ምናልባትም በግዕዝ አወጣጥ “ቤተ፥ አደረ፤” ከሚለው ግሥ የወጣ ሳይሆን አይቀርም። የታቦት ትርጓሜው ማደሪያ፥ መሠወሪያ ማለት ብቻ ሳይሆን መታያ፥ መገለጫም ነው። ንጉሥ በዙፋኑ እንዲገኝ፥ እንዲገለጥ፥ ታቦት ለእሥራኤል የአምላክ መገለጫ ነውና። እሥራኤል በጉዟቸው ሁሉ ታቦት ይዘው ሲጓዙ የኖሩት፥ እነ ሰሎሞን ለታቦቱ የሚሆን ቤተ መቅደስን በከፍተኛ ወጭ ያሠሩትና ለታቦት ይሰግዱ፥ ይንበረከኩ የነበረው፥ በታቦቱ ውስጥ በነበረው በጽላቱ ዐሠርቱ ቃላት ስለተጻፉ ብቻ አልነበረም። እሥራኤል ኃጢአት ሠርተው አምላካቸውን ባስቀየሙት ጊዜ በአባር፥ በቸነፈር፥ በምርኮ፥ በጦር ይቀጣቸዋል። ንስሐ ሲገቡና ሲለምኑት ደግሞ አባት ለልጁ እንደሚራራ ራርቶ ይምራቸው ነበር። የእግዚአብሔር ምሕረት እንደመጣላቸው የሚያውቁትም በታቦቱ ላይ ብርህት ደመና መጥታ ስታርፍ ነበር። ይህንንም ዕብራውያን “ሸኺናሐ፤” ይሉታል፤ ለምሕረት መገለጥ፥  ለምሕረት መምጣት ማለት ነው። 

            በአጠቃላይ አነጋገር ታቦት በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለምሕረት ለሕዝቡ በሚገለጥበት ጊዜ ዙፋኑ ነው፥ ማለት ነው። ዘጸ ፲፫፥፳፩-፳፪፤ ፲፱፥፲፮-፲፰፤ ፳፬፥፲፮-፲፯፤ ፴፫፥፲-፲፩፤ ፵፥ ፴፬-፴፭፤ ፳፭፥፳፪፤ ፮፥፯፤ ዘዳ ፭፥፬፣ ዘኁ ፱፥፲፭-፲፮ ፤ ፯፥፰-፱፤ ፲፬፥፲፤ ፲፮፥፲፱-፵፬፤ ፳፥፮። ዘዳ ፭፥፬፣ ዘሌ ፲፮፥፪፤ ፱፥፮-፳፫። 1ኛ ነገ ፰፥፲-፲፩፣ ዮሐ 1፥14፣ ሐጌ ፬፥፱። ወደ ዋና አሳባችን  እንመለስና ታቦት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በልማድ ያለ አይደለም፥ ወይም አንዳንድ የዋሆች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ኦሪትን ከሥርዓተ ወንጌል ጋር በባላንጣነት የምታታግል አይደለችም።
          በኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ እንደሚታወቀው፥ መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚመሰክረው፥ ከክርስትና በፊት የብሉይ ኪዳን አገር የነበረችው ኢትዮጵያ፥ በክርስትና ጊዜም ከብሉይ ኪዳን ያገኘቻቸውን ጠቃሚ ነገሮች በክርስትና መንፈስ እየተረጎመች ትጠቀምባቸዋለች። ከብሉይ ኪዳን ከወሰደቻቸው አንዱ ጽላተ ኪዳን ታቦተ ሕግ ነው። አዲስ ቤተክርስቲያን በሚሠራበት ጊዜ፥ ከዕፅ ወይም ከዕብነ በረድ ተቀርጾ በላዩ የእግዚአብሔር ምሥጢራዊ (ኅቡዕ) ስም “አልፋና ዖጋ (የመጀመሪያውና የመጨረሻው)” ተብሎ ከተቀረጸበት በኋላ በኤጲስ ቆጶሱ እጅ ተባርኮና ሜሮን ተቀብቶ በመንበሩ ይሠየማል። በቅዳሴም ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ቄሱ ሥርዓተ ቅዳሴውን የሚያከናውነው፥ ኅብስቱን ሥጋ መለኮት ወይኑን ደመ መለኮት ወደ መሆን የሚለውጠው በዚህ በታቦት ላይ ነው። የደብተራ ኦሪት ጽላት እግዚአብሔር በደመና ተከናንቦ ሙሴን እና አሮንን የሚያነጋግርበት፥ ለእሥራኤል ብቻ በረድኤት የሚገለጥበት ዙፋን ነበር። በአዲስ ኪዳን ግን የአምላክ ሥጋና ደም የሚፈተትበት፥ “ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ ሥጋዬን ብሉ፥ ደሜን ጠጡ፤” እያለ መኑትን ሁሉ የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ ነው። ክብርና ስግደት የሚደረግለት ለዚህ ነው።
          የኢትዮጵ ቤተክርስቲያን ስለ ታቦተ ያላት ትምህርታዊ መመሪያ ያልገባቸው አንዳንዶች እንደመሰላቸው ቢተረጉሙት ቤተክርስቲያናችን፦ በሙሴና በክርስቶስ፥ በብሉይና በሐዲስ፥ በጣኦትና በታቦት፥ በምሳሌና በአማናዊ መካከል ያለውን ልዩነት ስለምታውቅ ለሚጠይቋት ሁሉ ይህንን እምነቷን ከማስረዳት ተቆጥባ አታውቅም።
          ከኢትዮጵያ ሌላ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት  (Oriental churches) ታቦት የተለመደ ሕግ ነው። ሥጋውን ደሙን የሚፈትቱት በታቦት ላይ ነው። ለምሳሌ ግብፃውያን ታቦቱን፦ “ሉሕ” ይሉታል፥ ጽላት ሠሌዳ ማለት ነው። ያለሱ ሥጋውን እና ደሙን አይፈትቱም። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ተብለው የሚጠሩ፦ የግሪክ፥ የሩስያ፥ የሩማንያ እና ሌሎችም ወደ ክርስትና የተመለሱት ከአረማዊነት ስለሆነ የታቦትን ምሥጢር አያውቁትም፤ በታቦቱ ፈንታ ከመንበር የማይነሣ እንደ ታቦት የሚከብር የጌታ የስቅለቱ ወይም የግንዘቱ ሥዕል ያለበት የነጭ ሐር መጐናጸፊያ አላቸው። ያለሱ ሥጋውን እና ደሙን አይፈትቱም። ይህንንም በፅርዕ ቋንቋ “አንዲሚኒሲዮን” ይሉታል፥ ህየንተ ታቦት ማለት ነው። ከዚህም ጋር እነርሱ፦ ከአምስቱ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ከኢትዮጵያ፥ ከግብፅ፥ ከሕንድ፥ ከሶርያ፥ ከአርመን በቀር፥ አዲስ ቤተክርስቲያን በሚሠየምበት ጊዜ በመንበሩ ላይ የዐፅመ ቅዱሳን ሽራፊ እንዲቀመጥ ቀኖናቸው ያዛል። እንግዲህ በእኛ በኵል ስለ ታቦት ክብር ለሚጠይቁን ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ትውፊታዊ መረጃችን ( Tradition proof ) በመጠኑ ይህ ነው።
          ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ
         (በአባ ጎርጎርዮስ የተዘጋጀ፤ ፲፱፻፸፬ እና ፲፱፻፹፮ ዓ.. የታተመ።)

8 comments: