Sunday, December 2, 2012

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፬


የቅዱሳን መላእክት ክብርና ምልጃ፤
          የምልጃ ትምህርት ሐዋርያዊ ውርስ (Apostolic succession) ባላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የታወቀና የሚሠራበት ነው። ቅዱሳን መላእክት ረቂቃን ፍጥረታት ናቸው። በእግዚአብሔርም ፊት በባለሟልነት የሚቆሙ ናቸው። ሉቃ ፩፥፲፱። የእግዚአብሔርን ኃይል ለመግለጥ የሚላኩ ናቸው። ኢያ ፭፥፲፫-፲፭። የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ ለሰው ልጅ፥ የሰውን ልጅ ትሩፋትና ማናኛውንም በጎ ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ናቸው። የሐዋ ሥራ ፲፥፫፣ ዕብ ፩፥፲፭። ከዚህም ሁሉ ጋር በክርስትና ታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔር ምሥጢር ተካፋዮችና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው። በመጀመሪያ አምላክ ሰው ሊሆን ነው ብሎ የምሥራች የተናገረ የእግዚአብሔር መልአክ ነው። ሉቃ ፩፥፳፮። በተወለደም ጊዜ የዓለም መድኃኒት ተወለደ ብሎ መጀመሪያ ለሰው የሰበከው መልአክ ነው። ሉቃ ፪፥፰። የሕፃኑን መሢህ ሕይወት ለማጥፋት እነ ሄሮድስ ያጠመዱትን ወጥመድ በመግለጥ፥ ድንግል እመቤታችን እና ዮሴፍ ወደ ምድረ ግብፅ እንዲሸሹ ያደረጉ መላእክት መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ መዝግቦታል። ማቴ ፪፥፲፫።

          ክርስቶስ ወዶ ባደረገው አትሕቶ ርዕስ በዲያብሎስ ተፈትኖ ሦስቱን አርዕስተ ኃጣውእ (ስስትን፥ ትእቢትን፥ ፍቅረ ንዋይን) ድል ባደረገ ጊዜ የድል አድራጊነቱ ምልክት የሆኑት መላእክት መጥተው አገልግለውታል። ማቴ ፬፥፲፩። የማስተማር ጊዜውን ፈጽሞ ለሰው ልጆች መሥዋዕት ለመሆን ወደ መስቀል በሚመጣበት ጊዜ ሊፈርድበት ለተቀመጠው ለጲላጦስ፦ “እኔ ከፈለግሁ ከአንተ ፊት እንዳልቆም ለማድረግ የሚችሉ መላእክትን ለማዘዝ እችላለሁ።” በማለት እንግዳ የሆነ አስደንጋጭ ነገር ነግሮታል። ዮሐ ፲፰፥፴፮። በመስቀል ከተሰቀለና ከሞተ በኋላ በመቃብሩ ዙሪያ የተገኙና የትንሣኤውንም የምሥራች ለሰው ያሰሙ መላእክት ናቸው። ማቴ ፳፰፥፩፣ ማር ፲፮፥፭፣ ሉቃ ፳፬፥፬፣ ዮሐ ፳፥፲፩። ጌታ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ወደ ሰማያዊ ክብሩ በተመለሰበት ዕለት አንጋጠው ሰማይ ሰማይ እያዩ ያለቅሱ የነበሩ ሐዋርያትን አጽናንተው ዳግመኛ መምጣቱንም ነግረዋቸዋል። የሐዋ ፩፥፲፩። መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የክርስቶስን ትንሣኤ ለመመስከር ይሯሯጡ የነበሩ ሐዋርያትን ወኅኒ ቤት ከፍተው ፥ እግረ ሙቅ ፈትተው አይዟችሁ በማለት ይረዷቸው የነበሩ መላእክት ናቸው። የሐዋ ፭፥፲፱፣ ፲፪፥፮። ሰማዕታት የዐላውያን ነገሥታትን ግርማ እንዳይፈሩ የሚያበረታቱ፥ ጻድቃን ግርማ ሌሊትን፣ ድምፀ አራዊትን፣ ጸብአ አጋንንትን እንዳይሰቀቁ የሚያደርጉ መላእክት ናቸው። በመጨረሻም በፍርድ ቀን ጌታን ተከትለው ይመጣሉ። የእግዚአብሔርንም ምርጦች ከአራቱ ማዕዘን ይሰበስባሉ። ማቴ ፳፬፥፴፩።
          ስለዚህ ሁሉ ነገር (ስለዚህ ሁሉ ምክንያት) የመላእክት አገልግሎት የእግዚአብሔርን አምልኮት ለምትመሰክር ለቤተ ክርስቲያን ኃይል ድጋፍ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን መላእክትን ታከብራቸዋለች፥ በአማላጅነታቸውም ትማጠናለች። ድርሳናቸውን በማጻፍ ከፈጣሪያቸው እየተላኩ ያደረጉትን ተአምራት ሁሉ መዝግባ በማንበብና በመጸለይ ለመላእክት ያላትን አክብሮት ትገልጣለች። በዓላትን በቀኖናዋ ወስና ዛሬ በዓለ ሚካኤል ነው፥ ዛሬ በዓለ ገብርኤል ነው፥ እያለች በዓላቸውን ታከብራለች። ዝክረ ማኅበር ትዘክራለች። በስማቸው መታሰቢያ ቤተ ክርስቲያን ትሠራለች። ልጆችን በስማቸው ትሠይማለች። በቤተ ክርስቲያን የምዕመናን ሕይወትና የመላእክት አገልግሎት የተሰናሰለ ነው።
የቅዱሳን ክብርና ምልጃ፤
          ቅዱሳን በገድል ብዙ ክፍል አላቸው። እስከ ደም ጠብታ ድረስ ለክርስቶስ የመሰከሩ ሰማዕታት ቅዱሳን ናቸው። አንቀጽ አውጥተውና አልበው መናፍቃንን ተከራክረው የረቱ፥ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ያስጠበቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቆች (Apologaties) መምህራንም ቅዱሳን ናቸው። ከጣዕመ ዓለም ተለይተው ክርስቶስ ለሞተለት የሰው ዘር እየጸለዩና ፈጣሪያቸውን እየማለዱ በበረሀ ድምጸ አራዊትን፥ ግርማ ሌሊትን ታግሰው ሕይወታቸውን ያሳለፉ አበው ጻድቃን ቅዱሳን ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሥራ የተለያየ ድርሻ ቢኖራቸውም ዓላማቸው አንድ ነው። አገልግሎታቸውም ለቤተ ክርስቲያን ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንም መታሰቢያቸውን ታከብራለች። (ቅዱስ ዳዊት፦ “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል።” ብሏልና። መዝ ፻፲፩፥፮። ጠቢቡ ሰሎሞንም፦ “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው።” ብሏልና። ምሳ ፲፥፯።) ምሳሌነታቸውን በመግለጥ ሌሎች አማኞች እነርሱን እንዲመስሉ ታስተምራለች። (ቅዱስ ጳውሎስ፦ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ፤”ብሏልና። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን የምታከብረውና በአማላጅነታቸውም የምታምነው ቅዱሳት መጻሕፍትን እና ትውፊተ አበውን ተመርኵዛ ነው። (እግዚአብሔር አቤሜሌክን፦ “አሁንም የሰውየውን (የአብርሃምን) ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፤ ትድናለህም።” ብሎታልና። ዘፍ ፳፥፯። የኢዮብንም ወዳጆች፦ “ወደባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ እርሱም የሚቃጠልን መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ ያሳርግላችሁ። ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም ፊቱን እቀበላለሁ።” ብሎአቸዋልና። ኢያ ፵፪፥፰።) ቤተ ክርስቲያናችን ስለ አማላጅነት የምታስተምረውን ትምህርት አንዳንድ ሰዎች የተሳሳተ ትርጉም ይሰጡታል። እመቤታችን ድንግል ማርያም መላእክትና ቅዱሳን ያማልዳሉ ማለት እግዚአብሔርን መድፈርና ዳኝነቱን ማቃለል አምልኮቱንም መቀነስ ይመስላቸዋል። እነዚህ ሰዎች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ወደ ፕላቶን አስተሳሰብ የተጓዙ ናቸው። ፕላቶን ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረ የግሪክ ፈላስፋ ነበር። እሱ በአረማዊ አስተሳሰቡ፦ “እግዚአብሔር ከፍጡራን የተለየ የማይታወቅ ነው፤” ይል ነበር። በፕላቶን አስተሳሰብ “እግዚአብሔር የማይታወቅ የማይመረመር ስለሆነ ሰው ስለ እግዚአብሔር የሚናገረው ሁሉ ቅዠት ነው። ሰውና እግዚአብሔር ምንም ግንኙነት የላቸውም፤” ይላል። በክርስትና ትምህርት ግን እግዚአብሔር ሰው ሆነ፥ በሰው ቋንቋ ተናገረ፥ ከኃጢአት በስተቀር እንደ ሰው ኖረ። የማይታየው ታየ፥ የማይታወቀው ተገለጠ። በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ግንኙነት በፈጣሪና በፍጡር፥ በገዥና በተገዥ ዓይነት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የቤተሰብነትና የዝምድና ግንኙነት ተጀመረ። የሐዋ ፲፯፥፳፰። በምልጃ ትምህርታችንም ውስጥ የእግዚአብሔርን ዳኝነት ለማቃላል፥ አምልኮቱንም ለመቀነስ ሳይሆን እርሱ ወድዶ በሰጠን የቤተሰብነት ዝምድና ለመጠቀም ነው። ወደ እርሱ ለመቅረብ የምንጠቀምበትን ቋንቋ እርሱ ያውቀዋልና። ሰውን ለማዳን የተደረገውን የእግዚአብሔርን ስንፍና ሳይመለከቱ በሕግ ጠባይአዊ (Ratinalism) ብቻ የክርስትና ትምህርት ለመረዳት አይቻልም። ሰውን ለማዳን የተደረገው የእግዚአብሔር ስንፍና ከሰው ጥበብ ይበልጣልና። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፳፭።

  ምንጭ፦  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
(በአባ ጎርጎርዮስ የተዘጋጀ፤ 1974 ዓ.ም. እና 1986 ዓ.ም. የታተመ)

3 comments:

 1. Selam le enanete Yehun,

  I really like to read all your "Temhert or Sebket" but I don't have amharic software on my computer. Please Please post as .pdf version too.

  Thank you.

  ReplyDelete
 2. ቃለሕይዎት ያሰማልን ቀሲስ።
  ከመጨረሻዉ አንቀጽ ፫ኛዉ መሥመር የእግዚአብሔርን ስንፍና የሚለዉ ቢስተካከል።

  ReplyDelete
 3. ቃለ ሕይዎት ያሰማልን ።

  ReplyDelete