Thursday, November 8, 2012

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፫


ነገረ ማርያም፤
            በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፦ የእመቤታችን የድንግል ማርያም፥ የቅዱሳን መላእክት፥ የቅዱሳን ጻድቃን ክብርና አማላጅነት እንደ ሌሎቹ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት በሰፊው የታወቀ ነው። ከመላእክትና ከቅዱሳንም በክብርም ሆነ በአማላጅነት ቅድሚያ ያላት አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት። ለማንኛውም ክርስቲያን ይልቁንም የቤተክርስቲያንን ታሪክ ለሚከታተል የሃይማኖት ሰው የድንግል ማርያም ሕይወትና የቤተ ክርስቲያን አመሠራረት እንግዳ አይሆንበትም። ይህም ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ መወለዱ እና መወለዱም እኛን ለማዳን ብቻ መሆኑ ከታወቀ፥ የሰውን ልጅ የመዳን ቀን ከሰው ልጆች በቅድሚያ ያወቀች፥ ለእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መሣሪያ በመሆን አዳኙን መሢሕ የወለደች፥ የእግዚአብሔር ታማኝ የምሥጢር  መዝገብ ናትና ነው። በመዳን ትምህርት (Sotereology) የእመቤታችን ሕይወት ከእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ጋር የተዋሐደ ነው። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ድንግል ማርያም ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ሆና ትከበራለች። በመዝሙራችንም ሆነ በቅዳሴአችን ከስመ ሥላሴ ቀጥለን የምንዘምረው የድንግል ማርያምን ውዳሴ ነው። አምላክ ሰው በመሆኑ ለሰው ልጆች የዋለውን ውለታ፦ ስደቱን፥ መንከራተቱን፥ ስቅለቱንና ሞቱን በምናስታውስበት ጊዜ ድንግል ማርያምን ለመለየት አይቻለም። ወልዳ ያስገኘች ናት፥ አዝላ የተሰደደች ናት፥ በማስተማር ጊዜው አብራ ተንከራትታለች፥ በተሰቀለበት ዕለት ከመስቀሉ ሥር አልተለየችም። ይህ ሁሉ የሚያሳው እመቤታችን የሰውን ልጆች ለማዳን ከተደረገው አምላካዊ ጉዞ አለመለየቷን ነው።

          ከአዲስ ኪዳን ቀደም ብሎ ስለ እመቤታችን ክብርና ልዕልና በነቢያት የተነገሩ ትንቢቶች አያሌ ናቸው። መዝ ፵፬፥፱-፲፯። አምላክን የወለደችውም በነቢያት ተነግሮላት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬። በአዲስ ኪዳንም ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም በቀር «ቡርክት አንቲ እምአንስት፥ ተፈሥሒ ፍስሕት፥ ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ፥ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላእሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ። ደስ ያለሽ፥ ጸጋንም የተመላሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፥ ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ። . . . መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፥ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፤” ተብሎ የተመሰገነ አልነበረም። ሉቃ ፩፥ ፳፰-፴፭ ። እርሷም “ናሁ እምይእዜሰ ያስተበፅዑኒ ኵሉ ትውልድ። ከእንግዲህስ ወዲህ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል።”  ብላ በተናገረችው መሠረት፥ በልጇ ያመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ መመኪያ ዘውዳችን፥ ጥንተ መድኃኒታችን፥ የንጽሕና መሠረታችን ድንግል ማርያም ናት እያሉ ይዘምራሉ። ሉቃ  ፩ ፥፵፰።
          ቤተ ክርስቲያናችን ስለ እመቤታችን አማላጅነት የምትሰብከው እና የምታስተምረው ፍጹም በሆነ ሐዋርያዊ ትውፊት ነው። እመቤታችን ድንግል ማርያም ከሰው ወገን፥ የሰው ችግር ቶሎ የሚገባት፥ ቶሎ የሚታያትና የሚሰማት ርኅርኅት ናት። ለምሳሌ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ያለውን ምንባብ ብንመለከት፦ ሠርግ ደግሰው፥ ተጋባዥ ጠርተው፥ ተጋባዡ ሕዝብ በመጋበዝ ላይ እንዳለ ድግሱ በመቋረጡ ደጋሾቹ አፈሩ። በዚህን ጊዜ የሰዎቹ ችግር ቶሎ ገብቷት ለልጇ ነገረችው፥ ከዚህም አስከትላ “ልጄ ያዘዛችሁን ሁሉ አድርጉ፤” ብላ አሳላፊ ለነበሩት ሰዎች ምክር ሰጠቻቸው። ልጇም የእናቱን አማላጅነት ተቀብሎ አሳላፊዎቹን ውኃ እንዲቀዱ አዘዛቸው። አሳላፊዎቹም የእመቤታቸውን ምክር ሰምተው፥ የጌታቸውን ትእዛዝ ስለፈጸሙ የሠርጉ ቤት ከኃፍረት ድኗል። ይህ አስደናቂ ተአምራት ሊደረግ የቻለው በእመቤታችን አማላጅነት መሆኑን ቤተክርስቲያን ታምናለች። ዮሐ ። ፪፥፩-፲።
          ምእመናን ከእዚህ ዓለም ሲለዩ፥ በዚህም  በሚያልፈው የሕይወታቸው ጉዞ ለሚደርስባቸው ችግር ሁሉ እመቤታችን በአማላጅነት እንደማትለያቸው የታመነ ነው። ዮሐ ፲፱ ፥፳፮። በዚሁ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል “ነዋ ወልድኪ፥ ነያ እምከ፤ እነሆ ልጅሽ፥ እነኋት እናትህ፤” ብሎ አደራ በሚሰጥ ሰው ቋንቋ ጌታ የተናገረው ቃል፥ እናቱ ድንግል ማርያም ከእርሱ በቀር ሌላ ልጅ እንዳልነበራት ከማሳየቱም ሌላ ምሥጢራዊ አደራው፦ እናቱን ለቤተክርስቲያን፥ ቤተክርስቲያንንም ለእናቱ አደራ መስጠቱ ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያን የተሰጣትን አደራ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ጠብቃ በእመቤታችን ስም እየተማጸነች ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ታካሒዳለች። እመቤታችንም በተሰጣት አደራ የቤተክርስቲያን ጉዞ የተሳካ እንዲሆን ልጇን ወደጅዋን በየጊዜው ትለምነዋለች፥ ታስታውሰዋለች።
          እመቤታችን ድንግል ማርያም የርኅራኄ ምንጭ ናት፥ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትና ለአራዊት እንኳ ታዝናለች፥ ትራራለች። በነገረ ማርያም ( Mareology ) ስለ እመቤታችን ርኅራኄ የሚተርክ አንድ ታሪክ አለ። እመቤታችን አንድ ቀን በሕፃንነት ዕድሜዋ ከጓደኞቿ ጋር ሁና ውኃ የጠማው ውሻ እየሮጠ መጣ፥ በዚህ ጊዜ ጓደኞቿ ያን የተጠማ ውሻ ሲያባርሩት፥ እርሷ ግን ፍጹም ርኅራኄን የተሞላች ስለሆነች፥ ማጠጫ ዕቃ እንኳ ብታጣ ጫማዋን አውልቃ የተጠማውን ውሻ በጫማዋ ውኃ ማጠጣቷ ይነገራል። ስለዚህም ኢትዮጵያዊው ደራሲ የሚከተለውን ተናግሯል።
«- ሴስይኒ ማርያም ለጸማድኪ አሳብ፣
ኅብስተ አእምሮ ሠናይ ወወይነ ጥበብ፤
እመኒ ፈድፈደ ኃጢአትየ እምሕዝብ፣
ተዘከሪ እግዝእትየ በርኅራኄኪ ዕፁብ፣
ከመ አስተይኪዮ ማየ ለጽሙእ ከልብ።
-ማርያም ሆይ ምንደኛ አገልጋይሽን፥
መልካም ዕውቀት ኅብስትንና ጥበብ ወይንም መግቢኝ፤
ኃጢአቴ ከሕዝብ ሁሉ ኃጢአት ቢበዛም፥
እመቤቴ ሆይ አስደናቂ በሆነ ርኅራኄሽ፥
ለተጠማው ውሻ ውኃ ማጠጣትሽን አስቢ።» ነው የሚለው ደራሲው። በጸሎቱ የገለጠው፦ የራሱን የኃጢአት ብዛትና የእመቤታችንንም አስደናቂ ርኅራኄ ነው። ምንም ኃጢአቱ ቢበዛ ለውሻው እንኳ ርኅራኄ ያደረገች ድንግል ለእርሱም የምሕረት ጥላዋን እንድትጥልበት፥ ከፈጣሪው ጋር የሚታረቅበትን መንገድ እንድታሳየው ልመናውን አቅርቧል።
          ስለ እመቤታችን ውዳሴና ክብር፥ እንዲሁም የአማላጅነት መብት በብዙ ሊቃውንት ተጽፏል። ስለ አማላጅነቷም አያሌ ሊቃውንት ብዙ አስተምረዋል። በልጇ ያመኑ ምእመናን ሁሉ ውዳሴዎቿን እና ቅዳሴዎቿን በማንበብና በመጸለይ አማላጅነቷን ይማጠናሉ። የእናት አማላጅ ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስ ነውና፥ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም ቤተክርስቲያን ይሠራሉ፥ በዐሎቿን ያከብራሉ፥ ዝክር ይዘክራሉ፥ አሥራተ ማርያም፣ ገብረ ማርያም፣ አስካለ ማርያም፣ አመተ ማርያም እያሉ በስሟ ይሠየማሉ። በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምዕመናን፦ መመኪያ አክሊላችን፥ ጥንተ መድኃኒታችን ፥ የንጽሕና መሠረታችን ድንግል ማርያም መሆኗን ያውቃሉ፥ አማላጅነቷም የታመነ ነው።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ (በአባ ጎርጎርዮስ) 

10 comments:

 1. kesis kalehiwot yasemalen ! Egziabehare rejeme edme ena tena yestelegn! tshufochwo hulu betam astemari nachew.

  ReplyDelete
 2. Kesis egziabher yeagelgelot zemenon yibarkelen!!
  ande asteyayet gen alegn post yemiareguachewen tsehufoch be PDF melku biazegagulen download adergen lemayet betam selemikel esun menged kechalu biketelu elalehu maletem leke Diakon Daniel Kibrete tsehufochon be PDF melku post endemiadergew.
  egziabher yibarekot

  ReplyDelete
 3. kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 4. kalehiwot yasemalen

  ReplyDelete
 5. Bereketua yideribin !!!

  ReplyDelete
 6. Abatchen Bezu Geza Yehen Temhert Ke Int. Laye Lemanbeb Bemokerm PDF Sel Lalew Memare Alchalqum Ebqewot Kises PDF Bemetkm Post Bydergulen Amesegnaluh!!!

  ReplyDelete
 7. kale hiwot yasemalin bedme betsega yitebkiln

  ReplyDelete
 8. kale hiwot yasemalin bedme betsega yitebkiln

  ReplyDelete