Monday, October 8, 2012

መንፈሳዊነት


፫ኛ፦ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ነው። (የመንፈስን ፍሬ ማፍራት)፤
         ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እላችኋለሁ፥ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ” እንዳለ መንፈሳዊ ሰው ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ አስገዝቶ ይኖራል። በመንፈስ መኖር ማለት ለፈቃደ ነፍስ ማድላት ወደ ፈቃደ ነፍስ ማዘንበል ነው። ይኸውም አሥራ አምስቱን ፈቃደ ሥጋ ትቶ ለዘጠኙ ፈቃዳተ ነፍስ ተገዝቶ መኖር ነው። ገላ ፭፥፲፮-፳፮።
       ሀ. ፍቅር፦ ለመንፈሳዊ ሰው ጠላትን እስከ መውደድ የዘለቀ ፍቅር አለው፣ የሚረግመውን ይመርቃል፣ ለሚጠላው መልካም ያደርጋል፣ ለሚያሳድደው ይጸልያል ማቴ ፭፥፵፩-፵፭። ምክንያቱም ለበጎ ነገር ሁሉ አብነት የሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ጠላቶቹን ወድዶ ሞቶልናልና። ሮሜ ፭፥፲።

       ለ. ደስታ፦ መንፈሳዊ ሰው ከሁሉ በላይ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ ደስ ይለዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር  አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ። እንኪያስ እናንት ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፥ ልጆች ከሆናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ (በእርሱ ቤዛነት፥ በመስቀል ላይ ስለካሰላችሁ) የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ። (የማታልፍ ርስት መንግስተ ሰማያትን ትወርሳላችሁ)።” ያለው ለዚህ ነው። ገላ ፬፥፮-፯ አንድም “ወዳጆች ሆይ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ። ነገር ግን በጌትነቱ በተገለጠ ጊዜ ደግሞ ደስ ብሎአችሁ ሐሴት እንድታደርጉ ክርስቶስን በመከራ ትመስሉት ዘንድ ደስ ይበላችሁ።” እንደተባለ በመከራም ደስ ይለዋል። ፩ኛ ጴጥ ፬፥፲፪-፲፫። “ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፉአቸው እንግዲህ ወዲህም በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ገሥጸው ተውአቸው። እነርሱም ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ። ስለ ስሙ መከራ ይቀበሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አድሎአቸዋልና።” ይላል። የሐዋ ፭፥፵-፵፩።
  ሐ ሰላም፦ “በአንተ ላይ ታምናለችና በአንተ የምትደገፍ ነፍስን (ሰውነትን) ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።” እን ዲል፦ መንፈሳዊ ሰው በመከራ ውስጥም ሆኖ ሰላም አለው። ኢሳ ፳፮፥፫። ጌታችን በወንጌል”ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ አትፍሩም።” ያለው ይህንን ነው። ዮሐ ፲፬፥፳፯። ለመንፈሳዊ ሰው ሰላም የሚሰጠው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከኃጢአት ዕዳ ነጻ በመሆኑ ነው። ሮሜ ፭፥፮ ፣ ኤፌ ፪፥፲፬-፲፯። ቅዱስ ጴጥሮስ ሞት ተፈርዶበት፥ በሰንሰለት ታስሮ፥ ከወኅኒ ቤት ተወርውሮ ሳለ ውስጣዊ ሰላም ስለነበረው ንጹሕ እንቅልፍ ተኝቶ ነበር። የሐዋ ፲፪፥፮። ቅዱስ ጳውሎስ እና ሲላስ ልብሳቸውን ተገፍፈው፥ ተደብድበው ወደ ወኅኒ ቤት ተወርውረው፥ ከግንድ ጋርም ተጠርቀው ታስረው፥ ውስጣዊ ሰላም ስለነበራቸው፥ በመንፈቀ ሌሊት ነቅተው በዜማ ያመሰግኑ ነበር። የሐዋ ፲፮፥፳፪-፳፭።
       መ. ትዕግሥት፦ የመንፈሳዊ ሰው ትልቁ ሀብቱ ትዕግሥት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «ወንድሞች ሆይ፥ ልዩ ልዩ መከራ በሚመጣባችሁ ጊዜ በሁሉ ደስ ይበላችሁ። በሃይማኖታችሁ የሚመጣው ፈተና ትዕግሥትን እንደሚ ያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ጤነኞች ትሆኑ ዘንድ ትዕግሥት ፍጹም ግብር አላት። . . . እንግዲህ ወንድሞቻችን ሆይ፥ እነሆ ገበሬ የፊተኛውንና የኋላኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እየታገሠ የምድርን ፍሬ እንደሚጠብቅ፥ ጌታችሁ እስከሚመጣበት እስከኋላኛይቱ ቀን ድረስ ታገሡ። . . . ወንድሞቻችን ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን፥ በጌታም ስም የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። እነሆ የታገሡትን ብፁዓን እንላቸዋለን፥ የኢዮብን ትዕግሥት ሰምታችኋል፥ እግዚአብሔርም የፈጸመለትን አይታችኋል፥ የእግዚአብሔር ቸርነት ብዙ ነውና፥ ይቅር ባይ ነውና።» ያለው ለዚህ ነው። ያዕ ፩፥፪-፬፣ ፭፥፯-፲፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «በእግዚአብሔርም ክብር ተስፋ እንመካለን። የምንመካው በእርሷ ብቻ አይደለም፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን እንጂ፤ መከራ በእኛ ላይ ትዕግሥትን እንደሚያመጣ እናውቃለንና። ትዕግሥትም መከራ ነው፥ በመከራም ተስፋ ይገናል።» ብሏል። ሮሜ ፭፥፩-፬። በሕይወቱ የገጠመውንም ሲናገር፦ «እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጎሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፥ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፬፥፲፩-፲፫። የትዕግሥትና የመጽናናትም አምላክ እግዚአብሔር ነው። ሮሜ ፲፭፥፭።
        ሠ. ምጽዋት፦ «የሰማይ አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።» እንደተባለ መንፈሳዊ ሰው ርኅሩኅ ነው። ሉቃ ፮፥፴፮። ለተቸገሩ አዝኖ በልግስና ይሰጣል ዘዳ ፲፭፥፲፩። ለታይታ ሳይሆን እግዚአብሔር ብድራቱን ይመልስልኛል ብሎ ይመጸውታል። ማቴ ፮፥፩-፬። ምጽዋት ኃጢአትን ያስተሠርያል፥ በደልንም ያስወግዳል። ዳን ፬፥፳፯። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሀብታቸውን ለድሆች ያካፍሉ ነበር። የሐዋ ፬፥፴፪፣ ፮፥፩-፮።  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለድሆች የሚሆን ምጽዋት ይሰበስብ ነበር። ሮሜ ፲፭፥፳፭-፳፯። ምጽዋት መስጠትንም ሕግ አድርጐ ደንግጐላቸዋል። ፩ኛ ቆሮ ፲፯፥፩-፬። በትምህርቱም፦ «በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። እግዚአብሔር በደስታ የሚዘራውን ይወዳልና፥ እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ተብሎ እንደተጻፈ፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፱፥፮-፱፣ ዘጸ ፳፭፥፪፣ ዘዳ ፲፭፥፲፣ መዝ ፩፻፲፩፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ «እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ በዚህ ፍቅርን አውቀናል እኛም ስለወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፫፥፲፮-፲፯።
ምጽዋት ከርኅራኄ ወገን የምትሆን ርኅራኄ ናት፤ ሰው ምጽዋቱን ለሚሹት ሰዎች በገንዘቡ የሚደርገው ርኅራኄ ነው። አበድሬ እቀበላለሁ ሳይል እግዚአብሔር ሀብታችሁን ሸጣችሁ ለነዳያን ምጽዋት ሰጡ ብሎ ስላዘዘ የሚፈጽም ነው። ማት 19፡16። ምጽዋት መስጠት ገንዘብን ብልና ዝገት በማያጠፉት፥ ሌቦችም ቆፍረው በማይሰርቁት ቦታ በሰማዯት ማከማቸት ነው። ማቴ 6፡19። ሥራችንን ሁሉ ንጹሕ የሚደርግልን ምጽዋት ነው። ለሰው መራራት ከአምላክ ባሕርይ የተገኘ በመሆኑ ሰው የተቻለውን ያህል በመመጽወት ፈጣሪውን ይመስላል። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለምጽዋት ሲናገሩ፦ «ለአምላክ የሚያበድራት ብድራት፥ ወደ አምላክ የሚነግዳት ንግድ፥ ወድዶ እስከሚያስነሣት ድረስ ብልህ ሰው ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያኖራት አደራ፥ ከረሰ ነዳያንን መቅደስ አድርጎ እግዚአብሔር የሚቀበላት ቁርባን ናት፤» ይላሉ።   
       . ቸርነት፦ መንፈሳዊ ሰው ቸር ነው። ይህም በዚህ ምድር ከሰው ብድራትን ሳይሹ መለገስን ያመለክታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ መረጣቸው ቅዱሳንና ወዳጆች፥ ምሕረትንና ርኅራኄን፥ ቸርነት ንና ትሕትናን፥ የውሃትንና ትዕግሥትን ልበሱት።» ያለው ለዚህ ነው። ቈላ ፫፥፲፪። ቸርነት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። መዝ ፴፪፥፭፣ ሮሜ ፪፥፬። ሌላው ቀርቶ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን፥ አንድ የባሕርይ ልጁን አልከለከለንም። ሮሜ ፰፥፴፩-፴፪።
       ሰ. እምነት፦ መንፈሳዊ ሰው እምነቱ ሙሉ ነው፥ አያወላውልም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ የአቤልን የእምነት መሥዋዕት፥ የሄኖክን በእምነት ከዓይነ ሞት መሰወርን፥ የኖኅን በእምነት የጽድቅ ወራሽ መሆንን፥ የአብርሃምን በእምነት ወደ ከነዓን መጓዝን፥ የሳራን ካረጀች፣ ካፈጀች በኋላ በእምነት መጽነስን፥ የአብርሃምን በእምነት ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን፥ ያዕቆብ ልጆቹን በእምነት መባረክን፥ የዮሴፍንም ልጆች በእምነት እጁን አመሳቅሎ መባረክን፥ በበትሩ ጫፍም ላይ በእምነት መስገድን፥ ዮሴፍ የእሥራኤልን ልጆች ከግብፅ መውጣት በእምነት ማሰብን፥ የሙሴ ወላጆች ሙሴን ለሦስት ወር ያህል በእምነት መሸሸግን፥ የሙሴን የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እምቢ ማለትን፥ የግብፅንም አገር በእምነት መተውን፥ የፋሲካንም በግ በእምነት ማዘጋጀትን፥ የእስራኤልን በእምነት ባሕረ ኤርትራን መሻገርን፥ ታላቁ የኢያሪኮ ቅጽር በእምነት መውደቅን፥ ዘማዊ ረዓብም የእሥራኤልን ሰላዮች በእምነት ተቀብላ መሸሸግን እስከ ውጤቱ መስክሯል። ጊዜ ባያጥረው ኖሮ ስለ ጌዴዎን፥ ስለ ባርቅ፥ ስለ ሶምሶን፥ ስለ ዮፍታሔ፥ ስለ ዳዊት፥ ስለ ሳሙኤልና ስለተቀሩትም ነቢያት እምነት ሊያስተምር ነበር። እነርሱ በእምነት ተጋድለው፥ ነገሥታትን ድል እንደነሡ፥ ጽድቅን አድርገው ተስፋቸውን እንዳገኙ፥ የአናብስትን አፍ በእምነት እንደዘጉ፥ የእሳትን ኃይል በእምነት እንዳጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት በእምነት እንዳመለጡ፥ ከድካማቸውም እንደበረቱ መስክሯል። በአንፃሩ ደግሞ፦ የምትበልጠውን ሕይወት ለማግኘት፥ የሞትን ፍርድ በእምነት በጸጋ እንደተቀበሉ፥ መገረፍን፥ መዘባበቻ መሆንን፥ መታሠርን፥ በመጋዝ መሰንጠቅን፥ በድንጋይ መቀጥቀጥን፥ በሰይፍ መታረድን፥ በእምነት መቻላቸውን አስተምሯል። በእምነት መንነውም ማቅ፤ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው መዞራቸውን፥ መጨነቃቸውን፥ መቸገራቸውን፥ መከራ መቀበላቸውን፥ መራብ መጠማታቸውን፥ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፣ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም መንከራተታቸውን ለአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች አስታውሷቸዋል (ገድለ ቅዱሳንን አንብቦላቸዋል)። ዕብ ፲፩፥፩-፴፰።
ለመንፈሳዊነት መሠረቱ እምነት ነው። ምግባርና ትሩፋት (ከታዘዘው አብልጦ፥ አትርፎ መሥራት) እንደ ጣራና ግድግዳ ናቸው። እምነት ያለ ምግባር ምግባርም ያለ እምነት አይሆንም። ያዕ ፪፥፲፬-፳፮። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ደቀመዛሙርቱን፥ ስለ እምነታቸው ማነስ አጋንንትን ማውጣት እንደተሳናቸው ከነገራቸው በኋላ፦ «የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል (ጥርጥር የሌለው) እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ፦ (ልቡ በትዕቢት ተራራ የሆነ ይህን ሰይጣን) ከዚህ ወደዚያ እልፍ ብትሉት ያልፋል፥ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም።» ብሎአቸዋል። ማቴ ፲፯፥፳። በለሲቱን በረገመ ጊዜም፦ ጥርጥር የሌለው እምነት ካላቸው፥ ተራራውን ነቅለው ወደ ባሕር እንደሚወረወሩት፥ አምነውም በጸሎት የሚለምኑትን እንደሚቀበሉ ነግሯቸዋል። ማቴ ፳፩፥፳፩። በታንኳ በባሕር ላይ በሚጓዙበት ጊዜ ደግሞ፥ ብርቱ ማዕበል ተነሥቶ፥ እርሱ አብሯቸው እያለ እንሰጥማለን ብለው በመፍራታቸው፦ «እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ ለምን ትፈራላችሁ? “ በማለት እምነት መሠረት መሆኑን አስተምሯቸዋል። ማቴ.፫ ፥ ፳፫ - ፳፮  ከጎደሎ እምነት፥ ከጥርጥር ራስን ለማዳን መድኃኒቱ፥ ጋኔን እየጣለ አረፋ ያስደፍቀው ለነበረ ብላቴና አባት፥ “ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” በተባለ ጊዜ “ አምናለሁ አለማመኔን እርዳው፤” እያለ እንደተማጸነው ሆኖ መገኘት ነው። እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና። ፩ኛ ተሰ. ፪ ፥ ፱
የሰው ልጅ ከልቡ ሲያምን ያንጊዜ የሚያጸድቃውን ሥራ ይሠራል። ሮሜ. ፲፥ ፱ ፣ ገላ.፪ ፥ ፲፮ ማመኑም ወልድ ዋሕድ ብሎ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ነው። ያን ጊዜ የዘላለም ሕይወት ይኖረዋል። ዮሐ.፫ ፥ ፲፮ መንፈሳዊ የሚሆንበትንና የሚያደርግበትን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ይቀበላል። የሐዋ. ፪ ፥ ፴፰ ፣ ፲፱ ፥ ፪ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፤ “እናንተም ልትድኑበት የተማራችሁትን የእውነት ቃል ሰምታችሁና አምናችሁ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ።” ብሏል። ኤፌ. ፩ ፥ ፲፫ በመሆኑም መንፈሳዊነት የመንፈስን ፍሬ ለማፍራት በመንፈስ ቅዱስ መታተም ነው።
ሸ. ገርነት፦ መንፈሳዊ ሰው ገር ነው፥ ለሌላው ያስባል፥ በቃልም በግብርም አይበድልም፥ ሰውን አይጎዳም፥ በሰው ላይ አይጨክንም፤ ገርነቱም ለሁሉም ማለትም ለሚወዱትም ለሚጠሉትም ነው። ፩ኛ  ጴጥ. ፪ ፥ ፲፰ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ “ ገርነታቸው ለሰው ሁሉ ይታወቅ፤” ብሏል። ፊል. ፬፥፭ ለጢሞቴዎስ በላከው መልዕክቱም ላይ “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ፥ በትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም ” ብሏል። ፪ኛ ጢሞ ፪፥ ፳፬ ቲቶንም፦ “ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ ማንንም የማይሳደቡ፥ የማይከራከሩ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው።” ብሎታል። ቲቶ ፫ ፥ ፩- ፪ ገርነት ከሰማይ የሚሰጥ ጥበብ ነው።ይኽንንም ሐዋርያው ያዕቆብ -“ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት ጥርጥር ግብዝነት የሌለባት ናት” በማለት ገልጧታል። ያዕ. ፫ ፥ ፲፯ ቅዱስ ዳዊት ይህ ጸጋ ስለነበረው “ አቤቱ ዳዊትን ገርነቱን ሁሉ አስብ” እያለ ዘምሮአል። መዝ. ፻፴፩ ፥ ፩። ገርነቱም በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን በወዳጆቹም በጠላቶቹም ሁሉ ፊት ነበር። ንጉሥ ሳዖል እጁ ላይ በወደቀ ጊዜ ሊገድለው እየቻለ ምሕረት ያደረገለት፥ ባለሟሎቹም ግደለው እያሉ ሲገፋፉት “እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው” ያለው በገርነቱ ነው። ፩ኛ  ሳሙ ፳፬ ፥ ፮
ቀ. ንጽሕና፦ በባህርዩ ንጹሕ እግዚአብሔር ነው። አቤል ከበጎቹ በኩራት ነውር የሌለበትን ጠቦት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው በባሕርዩ ንጹሕ የሆነ አምላክ ንጹሕ መሥዋዕት ያቀርቡለት ዘንድ ይገባል ብሎ ነው። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና መሥዋዕቱ ተመለከተ። ዘፍ. ፬ ፥ ፬ ኖኅም ከንጹሐን እንስሳት ወገን መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቅርቧል። እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ(ተቀበለ)። ዘፍ. ፰፥፳-፳፩ የአዲስ ኪዳን የመሥዋዕት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ.፩፥ ፳፱፣ ፩ኛ ቆሮ ፭፥፯፣ ዕብ. ፱፥፳፮ ፣ ፲፥፲፪ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን ነውርና ዕድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክብር በክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ” ብሏል፤  ፩ኛ  ጴጥ. ፩ ፥ ፲፰ ፥ ፲፱። እንግዲህ እርሱ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ለሰው ልጅ እንደሰጠ መንፈሳዊም ሰው ራሱን ንጹሕ መሥዋዕት አድርጎ ለክርስቶስ ይሰጣል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞቻችን ሰውነታቸሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋል። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው ” ያለው ለዚህ ነውና ሮሜ ፲፪ ፥፩። ስለራሱም “በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፤ የምሄድበትም ጊዜ ደርሷል” ብሏል። ፪ኛ ጢሞ ፬፥ ፮።
       መንፈሳዊ ሰው በሥጋውም በነፍሱም ንጹሕ መሆን ይጠበቅበታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ ከዝሙት ሽሹ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው ፣ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ “ ያለው ፈቃደ ሥጋን ገንዘብ ማድረግ ስለማይገባ ነው። ፩ኛ ቆሮ. ፮ ፥፲፰-፳። ቅዱስ ዳዊት ደግሞ የአፍአ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ንጽሕናም እንደሚያስፈልግ አውቆ “አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ“ ሲል እግዚአብሔርን ተማጽኗል። መዝ. ፶፥፲። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የንጹሕ ልብን ዋጋ ሲናገር “ ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና “ ብሏል። ማቴ. ፭ ፥ ፰
          መንፈሳዊ ሰው በሥጋ ድካም በኃጢአት ቢቆሽሽ፥ በበደልም ቢረክስ፥ በንስሐ ራሱን ንጹሕ ማድረግ ይጠበቅበታል። በንስሐ ኃጢአት ይሠረያል፥ በደልም ይደመሰሳልና። የሐዋ. ፪፥፴፰። እግዚአብሔርም፦ “ኃጢአተኛው ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትዕዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፥ የበደለውም በደል ሁሉ አይታሰብበትም፥ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል“ ብሏል። ሕዝ. ፲፰፥፳፩-፳፪። በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበትም “ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፥ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።” ብሏል ኢሳ ፩-፲፰። ይኽንን የሚያውቅ ነቢይ ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ፥ ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ “ሲል እናገኘዋለን። መዝ. ፶፥፩- ፪።   


                                                                                                      ይቀጥላል. . .

12 comments:

 1. kale hiwot yasemalin abatachin

  ReplyDelete
 2. Thanks abatachin. KHY

  ReplyDelete
 3. ትልቅ መልእክት የያዘ ትምህርት ነው። ቃለ ህይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 4. ቃለ ህይወት ያሰማልን!!! አምላክ ጤና እና ረጅም እድሜ ይስጥህ፡፡

  ReplyDelete
 5. ሁሌም ጽሁፎችህን አነባለሁ ምንም ብዬ ግን አላውቅም ሰዓት እያጠረኝ ነው፣ የሚደነቀውን ነገር ያለማድነቅ ምቀኝነት ወይም ያለመረዳት ነው ይባላል፣ አንተ የምትጽፈው ለመደነቅ ሳይሆን ለህይወት መሆኑን ጠንቅቄ አውቃለሁ፣ ምሳሌው ለራሴ ነው፡ ጥሩ ትምህርት ነው፣ ቃለ ህይወት ያሰማልን እኛንም በዚህ ትምህርት ለመጠቀም ያብቃን ፣ ጽናቱን ይስጥህ፣

  ReplyDelete
 6. አባታችን እባክዎትን መግቦትዎን አያቋርጡብን. እግዚአብሄር ጸጋዉን እንዲያበዛልዎት እንለምነዋለን

  ReplyDelete
 7. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ጸጋውን ያብዛሎት።
  ቤተሰቦን ይባርክ።

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  ReplyDelete
  Replies
  1. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
   ጸጋውን ያብዛሎት።
   ቤተሰቦን ይባርክ።

   Delete
  2. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
   ጸጋውን ያብዛሎት።
   ቤተሰቦን ይባርክ።

   Delete
 8. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 9. አባታችን እባክዎትን መግቦትዎን አያቋርጡብን. እግዚአብሄር ጸጋዉን እንዲያበዛልዎት እንለምነዋለን

  ReplyDelete