Thursday, September 13, 2012

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና ትምህርታቸው፤ ክፍል ፪


ሐ፦ ምሥጢረ ሥጋዌ፤
          በምሥጢረ ሥጋዌም ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ በፍጹም ባሕርያዊ ተዋሕዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ እኛን ለማዳን መወለዱን፥ መጠመቁን፥ በጲላጦስ ዘመን መሰቀሉን፥ መሞቱንና መነሣቱን፥ ወደ አባቱ ማረጉን፥ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን መላኩንና ኋላም ለፍርድ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው ወዶ ባደረገው አትሕቶ ርዕስ፥ በዚህ ድንቅ በሆነ ምሥጢር ከቅድስት ድንግል የተወለደው እርሱ፥ ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ነው። ተዋህዶውም እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ ነው። (የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ የሆነ ሰው፥ አንድ ሰው እንደሚባል፥ የመለኰትና የትስብእት ተዋሕዶ የሆነ አንድ ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው።) የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዚህ እምነቷ ከ፬፻፴፩ ዓም የኤፌሶን ጉባኤና ከቅዱስ ቄርሎስ ጋር በመተባበር ሥጋን ከመለኰት ነጥሎ፥ አካልና ባሕርይን ከፋፍሎ የሰበከ ንስጥሮስንና ተከታዮቹን ስታወግዝ ትኖራለች። (ዛሬም ሥጋን ከመለኰት ነጥለው በሥጋው ያማልዳል፥ በመለኰቱ ይማለዳል የሚሉ አሉ። እነዚህ ሰዎች፦ መለኰትን ከሥጋ የሚነጣጠሉ ከሆነ፥ መለኰት በዝግ መቃብር ወጥቶ ሥጋ እንደሥጋነቱ መቃብሩን አስከፍቶ ለምን አልወጣም? መለኰት ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ አንድነት ለምን ከመቃብሩ ወጣ? በዝግ ቤት ሲገባም በመለኰቱ ገብቶ ሥጋ ከደጅ ቀርቶ እንደ ሥጋነቱ በር አንኳኲቶ ለምን አላስከፈተም? ሲባሉ መልስ የላቸውም።) የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥጋን ከመለኰት ጋር ቀላቅሎና አጣፍቶ የተወገዘውን የአውጣኪንን ትምህርትም አትቀበልም። በ፬፻፶፩ ዓም  በመርቅያን በብርክልያና (ሱልኸሪያ) በሮማው ፓፓ በልዮን ቀዳማዊ አነሣሽነት ተረፈ ንስጥሮሳውያን፥ መለካውያን (የንጉሥ ፈቃድ ፈጻሚዎች) በጉባኤ ኬልቄዶን የወሰኑትን የምንታዌ ትምህርት (dualism) (አንድ አካል ሁለት ባሕርይ የሚለውን) ታወግዛለች።

በዚሁ በምሥጢረ ሥጋዌ «ርጉም ንስጥሮስ» ቅድስት ድንግል ማርያምን «ወላዲተ አምላክ አትባልም፤» ብሎ ስለነበር ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መሆኗን ትመሰክራለች። ከንስጥሮስ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ የተነሡ «አንዲ ዲኮማርያቶስ (አንጢንድቁ ማርያጦስ፣ ፀረ ማርያሞች) ድንግልናዋን ለማጉደፍ የሚናገሩትን ሁሉ ትቃወማለች። እነርሱ እንደሚሉት ቅድስት ድንግል ማርያም ክርስቶስን የወለደችው «በዘርዓ ብእሲ» ነው። በዚህም የሰደቡት እርሷን ብቻ ሳይሆን ልጇንም ጭምር ነው። እሩቅ ብእሲ ማለት «ወልደ ዮሴፍ ነው፤» ማለት ነውና። ይህም ዘለፋቸው የቅዱስ መጽሐፍን ምስክርነት እንዳልተቀበሉ ያስረዳል። ማቴ ፩፥፲፰፣ ሉቃ ፩፥፴፭። ከዚህም ሌላ «እርሱን ከወለደችውም በኋላ ሌሎች ልጆች ወልዳለች፤» የሚሉም አሉ። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እነዚህንም ታወግዛለች። ድንግል ማርያም፦ ቅድመ ጸኒስ፥ ጊዜ ጸኒስ፥ ድኅረ ጸኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፥ ጊዜ ወሊድ፥ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና። ከዚህ ጋር ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደጻፈው ጌታ በመልዕልተ መስቀል ላይ እንዳለ እናቱን እንዲጠብቅለት ራሱ ወንጌላዊው ዮሐንስ አደራ መቀበሉን ተናግሯል። ሌላ ልጅ ቢኖራትማ ለተማሪው «አደራ የእናቴን ነገር» ይለው ነበርን? ዮሐ ፲፱፥፳፭። ምሥጢረ ሥጋዌን እንደመሰላቸው አድርገው ለማቅረብ የሞከሩ መናፍቃን እነዚህ ከዚህ በላይ ስማቸውን የጠራነው መናፍቃን ብቻ አይደሉም። ባለፈው ብዙዎች ነበሩ፥ ወደፊትም መልካቸውን እየለዋወጡ ይነሣሉ። ከሆነ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመናፍቃን እጇን ሳትሰጥ ኖራለች፥ ብዙ የውጭ አገር ሰዎች «የወንጌል መልእክተኞች ነን፤» እያሉ ተመላልሰውባታል።
ካቶሊኮች የመጡት በግራኝ  መሐመድ ወረራ ጊዜ ከፖርቱጋሎች ጋር ነው። የፀረ ማርያም (ፕሮቴስታንት) የተባለው ቡድን ደግሞ መምጣት የጀመረው ከ፲፮፻፴፬ ዓም ጀምሮ ነው። መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ጀርመናዊው ጴጥሮስ (Hefling ነው፡፡ ከ፲፮፻፷፰-፲፯፻፸፫ ዓም) ጀምስ ብሩስ የተባለው እንግሊዛዊም የመጣው የኢትዮጵያን የሃይማኖት ይዞታ ለመሰለል ነው። በ፲፰፻፴፮ ዓም የፕሮቴስታንት ሚሲዮን ሳሙኤል ጎባት (Samuel Gobat) እና ክርስቲያን ኩግለር (Christian Kugar) የተባሉ ሁለት ሚሲዮኖች መጥተው ነበር። ከእነርሱም በኋላ ሲ ደብልዩ አይሰንበርግ እና ኑድ ዊንግ ክራፍት መጥተዋል። በ፲፰፻፶፰ ዓም ደግሞ ከሲውዘርላንድ እየተነሡ ብዙ ሚሲዮኖች መጥተዋል። በየጊዜውም ከስዊድን፥ ከኖርዌይ፥ ከሆላንድና ከጀርመን ብዙ የፕሮቴስታንት መልእክተኞች መጥተዋል። እነዚህም የሚመጡት ሕዝቡን በሃይማኖት ከፋፍለው ሀገሪቱን ቅኝ ግዛት ለማድረግ ነው። ለምሳሌ እነ ሊዎፖልድ ትራቤሊ፥ እነ አንጀሎ ቪንኪ፥ እነ ጁሴፔ ሳፔቶ፥ እነ ጉሊዮልም ማሳያን የመሳሰሉ የፖለቲካ ሰዎች፥ እንደ እስላም ኢማም እየጠመጠሙና ግልድም እየታጠቁ፥ ጦር እየያዙ፥ «አባ ዱላ» በሉን እያሉ በእስላሞቹ ቤት እየዞሩ በሃይማኖት ስም የፖለቲካ ጉዳያቸውን ያካሒዱ ነበር። (ሊምፔር ኮሎኔያል ፋሽስታ የተባለውን መጽሐፍ መመልከት ለዚህ ታሪክ አገላለጥ ደጋፊ ይሆነዋል)።
ከ፲፮፻፯- ፲፮፻፴፪ ዓም በነገሡት በሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት የነበረው ካቶሊካዊ አልፎንሱ ሜንዴዝ በሁለት ኢትዮጵያውያን በቊረንጭ መናፍቅ ኤዎስጣቴዎስና በርጉም ተክለሃይማኖት ላይ የዘራው የቅብዐትና የጸጋ እምነት የሀገሪቱን ሊቃውንትና መሪዎችንም ጭምር ከፋፍሏቸው ነበር። የቅብዐት ልጅ የሚባሉት፦ «ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ፤ ተዋሕዶ ሁለትነትን እንጂ ንዴትን ከሥጋ አላራቀም፥ ንዴት ከሥጋ የራቀው ሥጋ በመንፈስ ቅዱስ በማኅፀን በተቀባ ጊዜ ነው፤» ይላሉ። እነርሱም በሦስት ይከፈላሉ።
ሀ፦ አባታቸው ዓፄ ሱስንዮስ በ፲፮፻፴፪ ዓም ከሞቱ በኋላ በነገሡት በዓፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት የነበሩት እነ ዕውር ዘኢየሱስ፦ መጽሐፍ በ፪ኛ ቆሮ ፰፥፱ ላይ «አንደየ ርእሶ፤ ስለ እናንተ ራሱን ደሀ አደረገ፤» ይላልና «ቃል በተዋሕዶ ጊዜ ዜገ፥ ከሥጋ ጋር ሲዋሐድ የባሕርይ ክብሩን አጣ፥ ለቀቀ፥ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባ ጊዜ ግን ወደ ጥንተ ክብሩ ተመልሶ በሰውነቱም በአምላክነቱም አንድ ወገን የባሕርይ ልጅ ሆነ፤» ብለዋል። ተቀቢው ቃልም ሥጋም ነው፥ ምሥጢሩ እንደ በትረ ሙሴ ማለት ነው። ሚጠትንና ውላጤን በአንድነት ያሳያል። (የሙሴ በትር ቢጥላት እንጨትነቷን ለቅቃ ተለውጣ እባብ ሆነች፥  ውላጤ ማለት እንዲህ ነው። ዳግመኛ እጁን ዘርግቶ ቢያነሳት ተመልሳ በትር ሆነች፥ ሚጠት ማለት ደግሞ እንዲህ ነው። አምላክ ሰው የሆነው ግን በተዋሕዶ እንጂ በውላጤም በሚጠትም አይደለም)።
ለ፦ በቀዳማዊ ዮሐንስ (በጻድቁ በዮሐንስ) ጊዜ የነበሩት እነ አካለ ክርስቶስ ደግሞ «ዜገ፤» ማለትን ነቅፈው፥ አጸይፈው፥ መጽሐፍ፦ «ተዋሕዶ አእተታ ለምንታዌ፤» ይላልና «ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል ሆነ እንጂ የአምላክነትን ክብር አላገኘም፥ ሲቀባ ግን ክብር ተላልፎለት፥ ተፈጥሮ ተገብሮ ጠፍቶለት በቅብዓት የባሕርይ ልጅ የባሕርይ አምላክ ሆነ፤» ብለዋል። ምሥጢሩ መቀባትንና መለወጥን ለሥጋ ብቻ  መስጠት ነው። (ነገር ግን ሥጋ ተለውጦ ቢሆን ኖሮ በክርስቶስ መራብ፥ መጠማት፥ መታመም፥ መሞት አይኖርበትም ነበር)።
ሐ፦ በዓፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የነበሩት እነ አለቃ ጐሹ (አራት ዓይና) በቅብዓት ብቻ ማለትን ነቅፈው፥ መጽሐፍ፦ በሁለቱም ማለትም «በተዋሕዶ ከበረ፥ በቅብዓት ከበረ፤» ስለሚል «ቅብዕት ያለ ተዋሕዶ፥ ተዋሕዶም ያለ ቅብዓት ብቻ ብቻውን አያከብርም፥ በተዋሕዶና በቅብዓት በአንድነት የአምላክነት ክብር ከብሮ የባሕርይ ልጅ ሆነ፤» ብለዋል። ሦስቱም ሁሉ ፍጹም ውላጤ ነው። ቅብዓቶች «አብ ቀባዒ፥ ወልድ ተቀባዒ፥ መንፈስ ቅዱስ ቅብዕ ነው፤» በማለት በሁሉም ዘመን የተነሡት አንድ ናቸው። ይህም ሦስቱን አካላት በሀብት ከፋፍለው፦ አብን ሰጪ፥ ወልድን ተቀባይ፥ መንፈስ ቅዱስን ስጦታ ማድረጋቸው ነው።
መ፦ ምንም እንኳ በምሥጢር ከቅባቶች ጋር አንድ ቢሆኑም በንባብ የተለያየ ስም ስላላቸው የጸጋ ልጅ የሚባሉት ደግሞ ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ነበራቸው። ጸጐች የሚሉት፦ «አዳም በተፈጥሮ ያገኘውን ንጽሐ ጠባይዕ በፈጣሪው ላይ ባመጠ ጊዜ ጨርሶ አጣው፥ ቃል አዳምን ወደነበረበት ሀገሩ፥ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ የሚያስችለውን ሥልጣን ከአብ ዘንድ ተቀበለ። ይኸውም በፈለገ ዮርዳኖስ፥ በዕደ ዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ሲያርፍበት ነው። በዚህ በቅብዓተ መንፈስ ቅዱስ ቃል ሦስተኛ ተወለደ።» (ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን አንድ ልደት፥ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱን ሁለት ልደት፥ ኋላም በዮርዳኖስ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ሦስተኛ ተወለደ ብለው ሦስት ልደት የሚሉት እንደዚህ አድርገው ነው)። እነርሱ እንደሚሉት ተቀብዐ አንቀጹ የቃል ስለሆነ ሥጋን አይመለከትም፥ በእነርሱ እምነት መሠረት ቃል ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ከብሯል፥ «ቃል ግን ወልደ አዳም፥ ወልደ አብርሃም፥ ወልደ ዳዊት፥ ወልደ ማርያም ለመባል የበቃው በተዋሕዶ ሳይሆን በሦስተኛው ጊዜ መወለድ ነው። በዚህ በሦስተኛው ልደት ደቂቀ አዳም ከወልድ ጋር ተዛምዶ አላቸው፥ ልደት ያገናኛቸዋልና።» ይላሉ። ሃሳባቸውን ባጭሩ ለመግለጥ ያህል «የቃል ከሥጋ መዋሐድ ሥጋን ሲያከብር፥ ቃልን ፍጹም ሰው ለመባል ያበቃው ቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ነው፤» ይላሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ትምህርት በመቃወም፦ «እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ፥ ወእንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል በተዋሕዶ፤ በተዋሕዶ የቃል የሆነው ሁሉ ለሥጋ፥ የሥጋም የሆነውም ሁሉ ለቃል ሆነ፤ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱ አንድ ልደት፥ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ሁለተኛ ልደት ነው። ወልደ አብ፥ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ እያለች ትኖራለች።
ጸጐች ከቅብዓቶች የሚለዩት እንደሚከተለው ነው። ጸጐች «ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ የጸጋ (የማደጎ) ልጅ ሆነ፤» ሲሉ ቅብዓቶች ደግሞ፦ «ተቀብቶ የባሕርይ ልጁ ሆነ፤» ይላሉ። ሁለተኛ፦ ጸጐች መቀባትን ለቃል ብቻ ሲሰጡ፥ ቅብዓቶች ደግሞ ለቃልም ለሥጋም ነው፥ ይላሉ። ሦስተኛ፦ ጸጐች፦ «ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተቀበለው በዮርዳኖስ ነው፤» ሲሉ ቅብዓቶች ደግሞ «የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተቀበለው በማኅጸን ነው፤» ይላሉ።
የጸጐችና የቅብዓቶች ትምህርት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ የግኖስቲኮችንና በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡ የነጳውሎስ ሳምሳጢን የጸጋ ትምህርት ይመስላል። ኦዶፕሺኒዝም (Adoptinism) ልዩነቱ እነ ጳውሎስ ሳምሳጢ ቃል ቅድመ ሥጋዌ (ሰው ከመሆኑ በፊት) የነበረውን አካላዊ ህላዌ (ኩነት) ሲክዱ፥ እነዚህ ግን ይህን የሚሉ አይመስለኝም። በዚህ እምነታቸው በቤተክርስቲያናችን ላይ ብዙ ጊዜ ብጥብጥ ሲፈጥሩ እንደኖሩ ታሪክ መዝግቦታል።
ከጸጐችና ከቅብዓቶች ሌላ በምሥጢረ ሥጋዌ የወልድን አምላክነት የጠበቅን መስሏቸው «መለኮት በአካል ሦስት ነው፥ ወላዲ መለኮት፣ ተወላዲ መለኮት፣ ሠራፂ መለኮት፤» የሚሉ እንደነበሩ የሚታወስ ነው። በመሠረቱ ወላዲ፥ ተወላዲ፥ ሠራፂ የሚለው ቃል ለሥላሴ የአካል ግብር ይባላል። መለኮት ግን የሦስቱም አንድነት የሚነገርበት ቃል ነው። የሥላሴን አንድነት የሚያመለክተውን መለኮትን ለአካል ግብር ቅጽል አድርጎ ማቅረብ ሦስቱንም ወላድያን፥ ሦስቱንም ተወላድያን፥ ሦስቱንም ሠራፅያን ማለት ነው። ግብርንና ስምን ያፋልሳል፥ አንድነትን ሦስትነትን ያጠፋል፥ ያደናግራል። «ኢይፈልስ ስመ አብ እምከዊነ ስመ አብ ኀበ ከዊነ ስመ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፥ ወስመ ወልድኒ ኢይፈልስ እምከዊነ ስመ ወልድ ኀበ ከዊነ ስመ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፥ ወስመ መንፈስ ቅዱስኒ ኢይፈልስ እምከዊነ ስመ መንፈስ ቅዱስ ኀበ ከዊነ ስመ አብ ወወልድ። የአብ ስም ተለውጦ ስመ ወልድ ስመ መንፈስ ቅዱስ ወደ መሆን፥ የወልድም ስም ተለውጦ ስመ አብ ስመ  መንፈስ ቅዱስ ወደመሆን፥ ስመ መንፈስ ቅዱስም ተለውጦ ስመ አብ ስመ ወልድ ወደመሆን አይሄድም» የሚለውን ንባብ ያልተመለከተ አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ ቀድሞ በዮሐንስ ተዓቃቢ ብቅ ብሎ የጠፋ ነው። ወደ ሀገራችን ግን ማን እንዳመጣው አይታወቅም። ብዙ ጊዜ ገዳማቱን ሲያፋጅ ኑሯል። አሁንም በዋልድባ ርዝራዡ አለ ይባላል።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በምሥጢረ ሥላሴም ሆነ በምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርቷን በቅዱሳት መጻሕፍትና በሊቃውንት ትርጓሜ ላይ መሥርታ ከመናፍቃን የሚሰነዘርባትን ሁሉ በመከላከል ከፍተኛ ተጋድሎ ስታደርግ ኑራለች፥ ትኖራለችም። ሃሣባችንን ለማጠቃለል፦ በምሥጢረ ሥላሴ ቤተክርስቲያናችን በሦስት አካላት በአንድ መለኮት ታምናለች። በምሥጢረ ሥጋዌም ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን ታምናለች፥ ታስተምራለች፥ ተዋሕዶውም ባሕርያዊ ነው። «ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን አንድ ልደት፥ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱን ሁለት ልደት፤ ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ።» ብላ ታምናለች። የቤተክርስቲያናችን እምነት ይህ ነው።
                                      ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ
                                                በአባ ጎርጎርዮስ (  M.A ) ፲፱፻፸፬ እና ፲፱፻፹፮ ዓም

2 comments:

  1. abatachin kale hiwot yasemalin! betechemari gin 'sile eyesus kiristos yebetekiristiyan timihirt' bemil re'ese yejemerulin timihirt abktoal weyis matekaleya entebik? ameseginalehu!!

    ReplyDelete
  2. abatachin edme yistewot.......kale hiwot yasemalgn....... Gin lemin yemetshaf kidus tinat bemil eres ayitsfum? Egna ye orthodox lijoch ende enante ayinet sewoch enfelgalen........egzibher yistlgn

    ReplyDelete