Saturday, July 7, 2012የቤተ ክርስቲያን መሠረትም ጉልላትም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ቤተክርስቲያን የሚለው ስያሜ ሦስት ዓይነት ትርጉም አለው። በአንደኛው ትርጉሙ፦ «እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደቤትህ እገባለሁ፥ አንተን በመፍራት በቤተ መቅደስህ እሰግዳለሁ።» እንዲል መዝ ፭፥፯። ክርስቲያኖች ተሰብስበው የሚጸልዩበት የቅድስናው ስፍራ ነው። እርሱ እግዚአብሔርም፦ «አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።» ብሏል። ፪ኛ ዜና ፯፥፲፭። የቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ትርጉም የክርስቲያኖች ማኅበር፥ አንድነት ማለት ነው። በግብረ ሐዋርያት ላይ እንደተጻፈው ቅዱስ ጴጥሮስን ለማታለል የሞከሩ ባልና ሚስት (ሐናንያና ሰጲራ) በየተራ ተቀሥፈው በመሞታቸው «በየአብያተ ክርስቲያናትና ይህንንም ነገር በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ፤» ይላል። የሐዋ ፭፥፲፩። በዚህ ምዕራፍና ቁጥር ላይ አብያተ ክርስቲያናት የተባሉት ማኅበረ ምዕመናን ናቸው። በሌላም ስፍራ፦ «በይሁዳ በሰማርያና በገሊላ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት (ማኅበረ ምዕመናን) ሁሉ በሰላም ኖሩ፤ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በዙ።» የሚል አለ። የሐዋ ፱፥፴፩። ሦስተኛው የቤተ ክርስቲያን ትርጉም የሚያመለክተው የእያንዳንዱን ምእመን ሕይወት ነው። ይኸውም ከያዕቆብ ወገን የተወለደ ሁሉ ቤተ-ያዕቆብ እንደሚባል ፥ በጥምቀት ምሥጢራዊ ልደት ከክርስቶስ የሚወለዱትም ፥ ቤተ ክርስቶስ እንደማለት ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ። ይኽንንም በተመለከተ፦ «በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው።» የሚል ተጽፏል። የሐዋ ፲፪፥፩።

 ቤተ ክርስቲያን በሐዲስ ኪዳን አያሌ ምሳሌዎች አሏት። ጌታ በወንጌል እንዳስተማረው ወደ ባሕር ተጥላ ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብ፥ መልካም ስንዴ የተዘራባት የእርሻ መሬት፥ የሰማይ አዕዋፍ መጥተው በቅርንጫፎቿ እስኪሰፍሩ ድረስ ታላቅ ዛፍ የሆነች የሰናፍጭ ቅንጣት፥ ንጉሥ ልጁን ሊድር ታላቅ ድግስ በደገሰባት ሠርግ ቤት ትመሰላለች። ማቴ ፲፫፥፳፬፣ ፴፩፣ ፵፭፣ ፵፯።
ሊቃውንት የቤተክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ከፍለው አመሥጥረው ይናገራሉ። የመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት። ሁለተኛይቱ ቤተክርስቲያን ከየዋሁ አቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ናት። ሦስተኛይቱ  ቤተክርስቲያን ግን በክርስቶስ ደም  የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት። እርሷም  የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ብዙ ልዩ ልዩ የሆነች የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፥ ዓለም ሳይፈጠር የወሰናት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም የፈጸማት፥ እኛ ጸጋንና ባለሟልነትን ያገኘንበት በሃይማኖት ወደሚገኘው ተስፋም ያደረሰበት፥ ስለዚህም ስለ እናንተ ለክብራችሁ የምታገኘኝን መከራዬን ቸል እንዳይላት እግዚአብሔርን እማልደዋለሁ።» በማለት የተናገረው ይኽንኑ እውነት የሚያረጋግጥ ነው። ኤፌ ፫፥፲። በብሉይ ኪዳን ዘመን ወደ ኖኅ መርከብ የገቡ ሁሉ እንደዳኑ፥ በእምነት ወደ ቤተክርስቲያን የሚገቡም የመዳን (ወደ መንግስተ ሰማያት የመግባት) ተስፋ አላቸው። ጌታ በወንጌል፦ «አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም።» እንዳለ። ዮሐ ፮፥፴፮። ይህም «እናንተ ደካሞች፥ ሸክማችሁም የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።» ካለው ጋር አንድ ነው። ማቴ ፲፩፥፳፰። የኖኅ መርከብ ያዳነችው በሥጋ ሲሆን ቤተክርስቲያን ግን የምታድነው በነፍስ ነው።
ቤተክርስቲያን በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል በመሆኗ መከፈል የለባትም፤ መቼም መች አንዲት ናት። «ወንድሞቻችን በአንድ ቃል እንድትናገሩ እንድታዝኑ ፍጹማንም እንድትሆኑ ሁላችሁንም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ አሳብ ሆናችሁ ኑሩ። ወንድሞቻችን ሆይ እንደምትጣሉና እንደምትከራከሩ ከቀሎኤስ ወገኖች ስለ እናንተ ነገሩኝ። እነሆ እርስ በርሳችሁ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔ የክርስቶስ ነኝ፥ የምትሉትን እነግራችኋለሁ። ክርስቶስ ተከፍሏልን?» እንዳለ። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲።  
ቤተክርስቲያን የሁሉ ናት። በመሆኗም በዘር፥ በቋንቋ፥ በአካባቢ አትከፈልም። «በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናልና። በክርስቶስ የተጠመቃችሁ እናንተማ ክርስቶስን ለብሳችኋል፦ (መስላችኋል)። በዚህም አይሁዳዊ ወይም አረማዊ የለም፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁ።» እንዳለ። ገላ ፫፥፳፮። ቤተክርስቲያን በሰማይም በምድርም ያለች ናት። በምድር በሕይወተ ሥጋ ከከሐድያን፥ ከመናፍቃን፥ ከፍትወታት እኩያትና ፥ ከኃጣውእ ጋር የሚያጋድሉ፦ በአጸደ ነፍስ ደግሞ ተጋድሏቸውን ፈጽመው የጽድቅና የድል አክሊል ተቀዳጅተው የሚኖሩ ምእመናን አንድነት ናት። ራእ ፭፥፱-፲፪።
፩፥፩፦ ሰላም፤
ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። «ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፥ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም።» እንዳለ። ዮሐ ፲፬፥፳፯። በተጨማሪም «በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ፥ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፥ ነገር ግን ጽኑ፥ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና።» ብሏል። ዮሐ ፲፮፥፴፫። በአዳም ኃጢአት ምክንያት በነፍስም በሥጋም ሰላምን አጥቶ የነበረው የሰው ልጅ ሰላምን ያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል በፈጸመው ቤዛነት ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ ለደቀመዛሙርቱ በዝግ ቤት በተገለጠላቸው ጊዜ፦ «ሰላም ለእናንተ ይሁን።» ብሏቸዋል። ዮሐ ፳፥፳። ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ ፦ «በአንተ ላይ ታምናለችና በአንተ የምትደገፍ ነፍስን ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።» በማለት የተናገረው በእርሱ ከእርሱ ስለሚገኘው ሰላም ነው። ኢሳ ፳፮፥፫። ይኽንን በተመለከተ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ « አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀረባችሁ። ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና። በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ። ሁለቱንም አድሶ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ በሥርዓቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕርቅንም አደረገ። በመስቀሉም በአንድ ሥጋው ሁለቱን ወደ እግዚአብሔር (ወደ አብ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) አቀረባቸው፤ በእርሱም ጥልን አጠፋ። መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን አሰጠ።» ብሏል። ኤፌ ፪፥፲፫። ይህም፦ «መንፈስ ከእኔ ይወጣልና፥ የሁሉንም ነፍስ ፈጥሬአለሁና ለዘላለም አልቀስፋችሁም፥ ሁልጊዜም አልቆጣችሁም። ስለ ኃጢአቱ ጥቂት ጊዜ መከራ አመጣሁበት፥ ቀሠፍሁትም፥ ፊቴንም ከእርሱ መለስሁ፥ እርሱም አዘነ፥ እያዘነም ሄደ። ከዚህም በኋላ መንገዱን አይቻለሁ፤ ፈወስሁትም፥ እጽናናሁት፥ እውነተኛም ደስታ ሰጠሁት። በሩቅም በቅርብም ላሉ በሰላም ላይ ሰላም ሰጠሁት። በሩቅም በቅርብም ላሉ በሰላም ላይ ሰላም ይሁን፤ እፈውሳቸውማለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።» ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ ትንቢት የተነገረበት ነው። ኢሳ ፶፯፥፲፮።

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው ቤዛነት በሰውና በፈጣሪ፥ በሰውና በመላእክት፥ በሰውና በሰው፥ በነፍስና በሥጋ፥ በሕዝብና በአሕዛብ መካከል ፍጹም ሰላም ወርዷል። በመሆኑም ይህንን ሰላም ይዞ ሰላማዊ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል።  «እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤»  እንዳለ። ሮሜ ፭፥፩። ይኽንን ሰላም የያዘ ሰው ከአውሬም ጋር ቢሆን መኖር እንደሚችል፥  «ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይሰማራል፥ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፥ ጥጃና በሬ የአንበሳ ደቦልም በአንድነት ይሰማራሉ፥ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያድጋሉ፥አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጉድጓድና  በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። እነርሱም አይጎዱትም፤ በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ማንንም አይጎዱም ፤ አያጠፉምም፤ ብዙ ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።» ተብሏል። ኢሳ ፲፩፥፩። ይህም እንደ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከአናብስትና ከአናምርት ጋር መኖርን ያመለክታል፥ አንድም ስለ ክፉ ሥራቸው አራዊት የሚባሉ ሰዎችን በትዕግስት ብዛት ማሸነፍን ይጠይቃል።
ክርስትና ሰላም፥ ክርስቲያን ሰላማዊ፥ ቤተክርስቲያን የሰላም ወደብ ናቸው። በመሆኑም ይኽንን በክርስቶስ የተገኘውን ሰላም በሃይማኖት መጠበቅ፥ በጾምና በጸሎት መንከባከብ ያስፈልጋል። ለዚህም ነው ጌታችን፦ «እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአቸሁ መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድሉአችሁና ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ። በሰማያት ላለው አባታቸሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ጸሐይን ያወጣልና፥ለጻድቃንና ለኃጥአንም ዝናምን ያዘንማልና። የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንደዚህማ ቀራጮችስ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ ሰማያዊው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጻማን ሁኑ።» ያለው። ማቴ፭፥፵፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «የሚያሳድዷችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚለው ጋራ ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ፥ እርስ በርሳችሁም በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፥ ትዕቢትን ግን አታስቡ፥ ራሱን የሚያዋርደውንም ሰው ምሰሉ፥ እናንተ ዐዋቆች ነን አትበሉ። ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፥ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ።ቢቻላችሁሰ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።» በማለት ከጌታው ጋር አንድ የሆነ ትምህርት አስተምሯል። ሮሜ ፲፪፣፲፬።
የዘላለምን ሕይወት የሚወድና የሚፈልግ ሁሉ ክርስቶስ ሰላማዊ እንደሆነ ሁሉ እርሱም ሰላማዊ መሆን አለበት።ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦  «ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድ ማነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህንም ሽንገላን እንዳይናገሩ፥ ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፥ ሰላምን ሻት፥ ተከተላትም።»  እንዳለ። ሮሜ ፲፪፥፲፬።
፩፥፪፦ የቤተክርስቲያንን ሰላም የሚያደፈርሰው ምንድነው?
   ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እርሻ በምትባል በቤተክርስቲያን የዘራው ንጹሕ ስንዴ ነው። በኋላ  ግን እንክርዳዱም አብሮ በመታየቱ ጠባቂዎቹ   ከወዴት መጣ?  ብለው ጠይቀዋል። እርሱም፦ «ጠላት ይኽን አደረገ፤»  ብሏቸዋል። ጠላት የተባለው ዲያቢሎስ እንደሆነም  ለደቀመዛሙርቱ ተርጉሞላቸዋል። ማቴ ፲፫፥፳፬።ይህም የሚያመለክተው ጠላት የተባለ ዲያቢሎስ እንክርዳድ ጠብን በቤተክርስቲያን እየዘራ ሰላምን እንደሚያደፈርስ ነው።
 ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «እንግዲህ በጎበኛችሁ ጊዜ ከፍ ከፍ ያደርጋችሁ ዘንድ ከጸናችው ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ራሳችሁን አዋርዱ። እርሱ ስለእናንተ ያስባልና  የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። እንግዲህ  አዋቂዎች ሁኑ፤ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና። እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፤ እንዲህም ያለ መከራ በዓለም ባሉ ወንድሞቻችሁ ሁሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ፤ ፍቅርንም አጽንታችሁ ያዙአት። በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ  ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል።»  ብሏል። ፩ኛጴጥ ፭፥፮።
፩፥፫፦ የቤተክርስቲያን መከራ
ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ መስቀል ላይ ናት። በደሙ የመሠረታት ኢየሱስ ክርስቶስን ወገኖቹ የሆኑ እስራኤልና ባእዳን የተባሉ አሕዛብ ተባብረው እንደሰቀሉት፥ የቤተክርስቲያንም ዕጣ ፈንታ ይኽንኑ የመሰለ ነው። ፈተና የተፈራረቀባት ከውስጥም ከአፍአም ነው። ጌታ በወንጌል «ነገር ግን ይህን የምናገር ስለሁላችሁ አይደለም፤ የመረጥኋቸው እነማን እንደሆኑ እኔ አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ እንጀራዬን የሚመገብ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሣ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። በሆነም ጊዜም እኔ እንደ ሆኑህ ታምኑ ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ ከመሆኑ አስቀድሞ እነግራችኋለሁ።» እንዳለ ቤተክርስቲያንም እንጀራዋን በልተው ያደጉ፥ በእርስዋ የተሾሙና የተከበሩ ሳይቀር ከጥንት ጀምሮ ሲነሡባት ታይተዋል። ዮሐ ፩፻፴፩፥፰።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ቢሆኑም እኔም እንደሰነፍ ለራሴ እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ እጅግም ደከምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ።አይሁድ አንዲት ጊዜ ስትቀር አምስት ጊዜ አርባ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ መቱኝ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤ በጥልቁ ባሕር ውሰጥ ስዋኝ አድሬ፥ ስዋኝ ዋልሁ። በመንገድ ዘወትር መከራ እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከራ ተቀበልሁ፤ ወንበዴዎችም አሰቃዩኝ፤ ዘመዶቼም አስጨነቁኝ፤ አሕዛብ መከራ አጸኑብኝ፤ በከተማ መከራ ተቀበልሁ፤ በበረሃም መከራ ተቀበልሁ፤ ሐሰተኞች መምህራን መከራ አጸኑብኝ። በድካምና በጥረት፥ ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በመራብና በመጠማት፥ አብዝቶም በመጾም፥ በብርድና በመራቆት ተቸገርሁ። የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። ታሞ እኔ የማላዝንለት ማን ነው? በድሎስ እኔ የማልደነግጥለት ማን ነው?» በማለት የተናገረው ፈተና የሚመጣው ከተለያየ አቅጣጫ መሆኑን ለማመልከት ነው። ፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫።  
ከቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ጀምሮ አያሌ ቅዱሳን ሰላምን የሰበኩለት ዓለም ሰላም አሳጥቷቸው፥ በመከራ ተፈትነው የሰማዕትነትን ጽዋ በሃይማኖት ጨልጠዋል። ጀርባቸው እስኪተላ ድረስ ተገርፈዋል፥ በሰይፍ ተመትረዋል፥ በመጋዝ ተተርትረዋል፥ በእሳት ተቃጥለዋል፥ ለአራዊት ተሰጥተዋል፥ በሕይወት እያሉ ቆዳቸውን ተገፈዋል። «ተፈርዶባቸው የሞቱም አሉ፤ የምትበልጠውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ ሊድኑ አልወደዱምና። የገረፉአቸው፥ የዘበቱባቸውና፥ ያሰሩአቸው፥ ወደ ወህኒ ያስገቡአቸው አሉ። በመጋዝ የሰነጠቁአቸው፥ በድንጋይ የቀጠቀጡአቸው፥ በሰይፍም ስለት የገደሉአቸው አሉ፤ ማቅ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብስው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፥ ተጠሙ። ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፥ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ።» እንዳለ። ዕብ ፲፩፥፴፭።
ቤተ ክርስቲያን የዲዮቅልጥያኖስንም ዘመን አልፋለች። ክርስቲያኖች ስቃዩ ሲጠናባቸው ወደ ቤተ ጣዖት ይመለሱ ይሆናል በማለት በሕይወት እያሉ ሕዋሳቶቻቸውን እየቀነጣጠሱ ያሰቃዩአቸው ነበር።
የሚቆራርጡትን አካላቸውንም እየወሰዱ ለጣዖቶቻቸው ያጤሱት ነበር። ክርስቲያኖች ግን ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸምባቸው መከራውን ተሰቅቀው ከእምነታቸው ወደ ኋላ አላሉም፥ እምነታቸውን በደማቸው አተሙት እንጂ። ክርስቶስ በችንካር የቆሰሉ እጆቹን ዘርግቶ «ሰላም ለእናንተ ይሁን» እንዳለ፥ እነርሱም በስለት በቆሰለና በተቆራረጠ አካላቸው፥ በፈሰሰው ደማቸው ሰላምን ሰበኩ፥ ስለ ሰላም ጸለዩ። ዲዮቅልጥያኖስ ከቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ የከተማይቱ ክርስቲያኖች ሲታረዱና አብያተ ክርስቲያናቱም ሲቃጠሉ እንደ ትርዒት ይመለከት ነበር። ይህ ሁሉ የጭካኔ እልቂት ቢፈጸምባቸውም ክርስቲያኖች ሲቆርጡት ከሥሩ እንደሚያቆጠቁጥ ዛፍ ቁጥራቸው እየጨመረ ሄደ። ልባቸው በተስፋ መንግስተ ሰማያት በመሞላቱ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ሰላም ነበራቸው። በመከራውም ደስተኞች ነበሩ። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «ወንድሞች ሆይ፥ ልዩ ልዩ መከራ በሚመጣባችሁ ጊዜ በሁሉ ደስ ይበላችሁ። በሃይማኖታችሁ የሚመጣው ፈተና ትዕግሥትን እንደሚያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ጤነኞች ትሆኑ ዘንድ ትዕግሥት ፍጹም ግብር አላት።» እንዳለ። ያዕ ፩፥፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ፥ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ። ነገር ግን በጌትነቱ በተገለጠ ጊዜ ደግሞ ደስ ብሏችሁ ሐሴት እንድታደርጉ ክርስቶስን በመከራ ትመስሉት ዘንድ ደስ ይበላችሁ።» እንዳለ። ፩ኛ ጴጥ ፬፥፲፪።
እነ አርዮስ፥ እነ ንስጥሮስ፥ እነ መቅዶንዮስም በኑፋቄቸው ማዕበል በቤተ ክርስቲያን ላይ ያስነሡት መከራም ከአረማውያኑ የሚተናነስ አይደለም። አያሌ አባቶችና ምእመናን ለመከራ ተዳርገዋል። መናፍቃኑ ከዘመናቸው ባለስልጣናት እየተጠጉ እውነተኞቹን ከዋሉበት አላሳድር፥ ካደሩበትም አላውል እያሉ ያሳድዷቸው ነበር። እነ ቅዱስ አትናቴዎስ ብዙ ጊዜ ለስደት ተዳርገዋል። እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥርሳቸው እስኪረግፍ፥ ጽሕማቸው እስኪነጭ ተደብድበዋል። አያሌ ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሲሉ ከአባቶቻቸው ጋር መሥዋዕት ሆነዋል። አንዲቱ ቤተክርስቲያን ስትከፈል ከምናይ ብለው ሞታቸውን መርጠዋል።
በዚያን ጊዜ መናፍቃኑ የተከሉት እሾህና የረጩት መርዝ አንዲቷን ቤተክርስቲያን ከፋፍሏት እስከዛሬም ድረስ ከችግር አልተላቀቀችም። ልጆቻቸውም ያባቶቻቸውን ወርሰው «ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ» እንደተባለ ከቀደሙት በከፋ ሁኔታ ክፍፍሉን አባብሰውታል። ጌታችን በወንጌል፦ «የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት (መምህራን) ተጠንቀቁ፤» በማለት ያስጠነቀቀው ለዚህ ነበር። ማቴ ፯፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁዋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀመዛሙርትን ወደ ኋላ ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።» ያለው ለዚህ ነበር። የሐዋ ፳፥፳፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይኖራሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታን እንኳ ክደው የሚፈጥን ጥፋትን በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያስገባሉ። ብዙ ሰዎችም እነርሱን ስለ ዝሙታቸው ይከተሏቸዋል። የጽድቅ መንገድንም ያሰድባሉ። በፈጠሩት ቃል ይከራከራሉ፤ በእርሱም ይሄዳሉ፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም፤ ጥፋታቸውም አይዘገይም።» በሏል። ፪ኛጴጥ ፪፥፩።
፩፥፬፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፦ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውን ፥ ሐዋርያት ያስተማሩትን፥ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን አበው በ፫፻፳፭ ዓ.ም በኒቅያ፣ አንድ መቶ ሃምሣ ቅዱሳን አበው በ፫፻፹፩ ዓ.ም በቁስጥንጥንያ፣ ሁለት መቶ ቅዱሳን አበው በ፬፻፴፩ዓ.ም በኤፌሶን ያስተማሩትንና የወሰኑትን የተቀበለች ዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ናት። ይህች ቤተክርስተያን በመከራ መካከል እየተጓዘች ሀገሪቱን ባለታሪክ፥ ሕዝቡንም የሃይማኖት፥ የሥርዓት፥ የባህልና የቅርስ ባለቤት ያደረገች ናት። በአጠቃላይ ሙሉ ትምህርት ፥ ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ፥ሥነጽሁፍ ከነጠባዩ፥ ኪነጥበብ በየዓይነቱ፥ ሥነጥበብ በየመልኩ፥ ነፃነት ከነክብሩ፥ አንድነት ከነጀግንነቱ፥ ሀገር ከነድንበሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስረከበች ታላቅ ቤተክርስቲያን ናት።
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በእሳትና በስለት ላይ ተረማምዳ ነው ከዚህ የደረሰችው። ከ፰፻፵፪ ዓ.ም. እስከ ፰፻፹፪ ዓ.ም. ዮዲት በተባለች የአይሁድ ደም ባላት ሴት (ፈላሲት) መሪነት ለአርባ ዓመታት አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ከነሙሉ ቅርሳቸው ተቃጥለዋል። በአብርሃና በአጽብሃ የታነጸችው የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የተቃጠለችው በዚያን ጊዜ ነው። ከክርስትና በፊትና በኋላ የተሠሩ ሐውልቶች ፈራርሰዋል። በ፲፪፻፶ ዓ.ም. በግብፆች ይደገፉ በነበሩ የአዳል እስላሞች ንቅናቄም ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራ ደርሶባታል።
የቤተክርስቲያናችን ታሪክ በብዙ የለዋወጠው በዓጼ ልብነ-ድንግል ዘመን የተፈጸመው የግራኝ መሐመድ የአሥራ አምስት ዓመት ወረራ ነው። ይኽውም ከ፲፭፻፳፮ ዓ.ም. እስከ ፲፭፻፵፪ ዓ.ም. ነው። በሺህ የሚቆጠሩ ገዳማትና አድባራት ተቃጥለዋል። በዚህም ከዮዲት ጥፋት ተርፈው የነበሩ ቅርሶች ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል። ሊቃውንትና ምእመናን ከቱርክ በመጣ ሳንጃ እንደ ከብት ታርደዋል፥ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ በክርስቲያኖች ደም ተጥለቅልቃለች። ይህ ሁሉ መከራ ቢወርድም ተገደው የሰለሙ ከአስር አንድ ብቻ ነበሩ። እነዚህም ከመከራው በኋላ በደብረ ሊባኖሱ እጨጌ በአባ እንባቆም መጽሐፈ ቄድር እየተደገመ ጸበል ተረጭተው ተመልሰዋል።
ከዚህም ሌላ ከአውሮፓ እየተላኩ ይመጡ በነበሩ በካቶሊክና የፕሮቴስታንት መልእክተኞች ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ እሳት ላይ እንደተጣደች ነበር። ሕዝቡን በዘርና በሃይማኖት እየከፋፈሉ ለማፋጀት ያደረጉት ጥረት ከግራኝና ከዮዲት የሚተናነስ አልነበረም። ዓጼ ገላውዴዎስ ከሞቱ በኋላ በልጃቸው በዓጼ ሚናስ ዘመን ካቶሊኮቹ እንዳያስተምሩ በመታገዳቸው ከእስላሞቹ ጋር ግንባር ፈጥረው ንጉሡን ለማስገደል ይጥሩ ነበር። ይልቁንም በዓጼ ሱስንዮስ ዘመን፦ ንጉሡን እስከነቤተሰቦቻቸው አጥምቀው ወደ ካቶሊክነት ከለወጡዋቸው በኋላ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እሳት ነደደባት። ይህም የሆነው በ፲፮፻፳፪ ዓ.ም. ነው። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ካቶሊክ ይሁን ተብሎ ታወጀ። ክርስቲያኖች እንደገና በካቶሊካዊያን እጅ እንዲጠመቁ፥ አብያተ ክርስቲያናቱ እንደገና እንዲባረኩ፥ ካህናቱ እንደገና እንዲካኑ፥ ሥዕሎች ወጥተው ከድንጋይ የተጠረበ ሐውልት እንዲቆም፥ የሮማውያን የቅዳሴ ሥርዓትና የቀን መቁጠሪያ እንዲተካ፥ የዓርብና የረቡዕ ጾም ቀርቶ ቅዳሜ እንዲጾም ተባለ። ይህንን ያላከበረ የአካል ቅጣት እንደሚፈጸምበት (እጅ እግሩ እንደሚቆረጥ) ተነገረ። ጳጳሱ ብጹዕ አቡነ ስምዖን፥ አያሌ ሊቃውንትና ምእመናን ያለ ርኅራኄ ተጨፈጨፉ። የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን አጽምም ካረፈበት እየወጣ እንዲቃጠል ተደረገ። ከመላው ሀገሪቱ ሰማዕትነት አያምልጥህ እያሉ መጥተው በሱስንዮስ አደባባይ ከስምንት ሺህ በላይ ሕዝብ ረገፈ። በዚህም የተነሣ ለሰባት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ የሃይማኖት ጦርነት ሆነ። ዓጼ ሱስንዮስ በነገሡ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ታመው አንደበታቸው ተዘጋ። በዚህን ጊዜ ልጃቸው አቤቶ ፋሲል ደንግጠው፦ «እግዚአብሔር ይህን ደዌ በአባቴ ላይ ያመጣባቸው የክርስቲያኖችን ደም በከንቱ ስላፈሰሱ ተቀይሞ ነው።» ብለው፦ «አትርሱኝ፥ በጸሎት አስቡኝ፤» እያሉ በየገዳማቱ ላኩ። ያን ጊዜ በጣም ዝነኛ የነበሩት ባሕታዊ የማኅበረ ሥላሴው አባ ዓምደ ሥላሴ የገዳማቸውን መነኮሳት አስከትለው በመምጣት፥ ሦስት ሱባዔ ይዘው ቢያጠምቋቸው የንጉሡ አንደበት ተፈታ። ቤተክርስቲያን ስለ ክፉ ፈንታ ክፉ አልመለሰችም። ንጉሡም አንደበታቸው በመፈታቱ «የተዋሕዶ ሃይማኖት ትመለስ፥ የካቶሊክ ሃይማኖት ትርከስ፥ ፋሲል ይነገሥ።» ብለው አዋጅ አናገሩ።   
የካቶሊኮች ተንኰል በዚህ አላበቃም። ኦርቶዶክስ ቅብዓት፥ ኦርቶዶክስ ጸጋ የሚል ባሕል ፈጥረው ሊቃውንቱንና ሕዝቡን በመከፋፈልና በማጨቃጨቅ ያደረሱት በደል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። የመጨረሻው ዓላማቸው ሀገሪቱን ቅኝ ግዛት ማድረግ ስለሆነ በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. በሕዝቡ ላይ ጦርነት በማወጅ ክርስቲያኑን ለአምስት ዓመታት በአውሮፕላን ቦንብና በመትረየስ ፈጅተውታል። አብያተ ክርስቲያናትን እና ገዳማትን አቃጥለዋል። ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስን አዲስ አበባ ላይ፥ ብጹዕ አቡነ ሚካኤልን ጐሬ ላይ የረሸኑት ካቶሊኮቹ ናቸው።
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በመናፍቃንና በአሕዛብ የሚደርስባት መከራ አሁንም ቢሆን አላበቃም። የታሪክና የሃይማኖት አሻራ የሆኑትን ቅርሶቿን በማዘረፍ ካልተቻለም በእሳት በማቃጠል እየተፈተታተኗት ነው። ይልቁንም በቅርብ ጊዜ የሆነውን ሁላችንም የምናውቀው ነው። በጂማ አካባቢ ካህናትና ምእመናን በአገልግሎት ላይ እንዳሉ በአሕዛብ ስለት ታርደዋል። አብያተ ክርስቲያናትም ተቃጥለዋል። በመቀጠልም ገዳማትን ለማቃጠል በነበራቸው እቅድ መሠረት የታላቁን የዝቋላ የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን ገዳም የተፈጥሮ ደን በእሳት አውድመዋል። ይህ ነገር በአሰቦት ገዳምና በዋልድባ ገዳምም ላይ ተደግሟል። ከአሁን ቀደምም በአሰቦት ገዳም መነኰሳት ታርደው እንደነበረ በሐዘን የምናስታውሰው ነው።
እንግዲህ በአጭሩ እንደተመለከትነው አባቶቻችን ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ክብር  ሲሉ የከበረ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ከዚህ አንፃር ከቤተክርስቲያን አንድነት ይልቅ የራሳቸውን ሥልጣንና ክብር የሚያስቀድሙ ሰዎችን ስንመለከት እጅግ የሚያሳዝን ተግባር ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ብቻ ሳይሆን በቀደሙ አባቶቻችንን መሥዋዕትነት መቀለድ ነው። አባቶቻችን በችግር  ውስጥ ሆነው ለ2000 ዓመታት ያህል የጠበቁትን የቤተክርስቲያን አንድነት እኛ ሳንቸገር ለሦስት ከፍለናት ስትታይ ወደፊት ደግሞ ለስንት ትከፈል ይሆን የሚያሰኝ ነው።
፩፥፭፦ ጸሎት
«ጸሎትሰ ተናግሮተ ሰብእ ይዕቲ ምስለ እግዚአብሔር ልዑል። ጸሎትስ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት።» በመሆኑም የቤተክርስቲያን ችግር የሚፈታው በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እንጂ በሌላ አይደለም። ጌታ በጌቴሴማኔ የአትክልት ሥፍራ ለደቀመዛሙርቱ ለጸሎት አብነት ከሆናቸው በኋላ፦ «ወደ ፈተናም እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ይሻልና (ነፍስ መጸለይ ትፈልጋለችና)፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።» ያላቸው ለዚህ ነው። ማቴ ፳፮፥፵፩። ስለ ዓለም መጨረሻ ምልክቶች ከነገራቸውም በኋላ፦ «ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች። በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደተዘረጋች ወጥመድ ትደርሳለችና። እንግዲህ ከዚህ ከሚመጣው ሁሉ በጸሎታችሁ ማምለጥ እንድትችሉ በሰው ልጅ (በተዋሕዶ ሰው በሆነ በክርስቶስ) ፊትም እንድትቆሙ ሁል ጊዜ ትጉ» ብሏል። ሉቃ ፳፩ ፥፴፬። በመሆኑም፦
ሀ. በእምነት መጸለይ አለብን።
የጌታ ደቀመዛሙርት ገና ሰው ሰውኛውን ይጓዙ በነበረበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት በሽተኛ መፈወስ ተስኗቸው ጌታን በጠየቁት ጊዜ፦ «ስለ እምነታችሁ መጉደል ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍንጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ ተነቅለህ ሂድ ብትሉት ይፈልሳል፤ የሚሳናችሁ ነገር የለም። ይህ ዓይነት ግን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም፤» ብሏቸዋል። ማቴ ፲፯፥፳። የእምነትን ጸሎት በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም፦ «ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን፤ አይጠራጠርም፤ የሚጠራጠር በነፋስ የሚገፋና የሚነዋወጥ የባሕር ማዕበልን ይመስላልና። ለዚህ ሰው ከእግዚአብሔር ምንም የሚያገኝ አይምሰለው። ሁለት ልብ የሆነ ሰው በመንገዱ ሁሉ ይታወካልና።» ብሏል። ያዕ ፩፥፭። ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ለእግዚአብሔር በጸሎት የነገርነውን ሁሉ ልክ በእጃችን የጨበጥነው ያህል እንድንቆጥረው ሲነግረን፦ «በእግዚአብሔር ዘንድ ያለችን መውደድ ይህች ናት፤ በስሙ ከእርሱ ዘንድ የምንለምነውን ይሰማናልና። የምንለምነውንም እንደሚሰማን ካወቅን፥ እንግዲያስ በእርሱ ዘንድ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለን።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፲፬።
ለ. ስንጸልይ ኃጢአታችን  እየተናዘዝን መሆን አለበት።
ቅዱስ ዳዊት በልቡ ያሰበውን እንኳ አንድ ሳያስቀር በእግዚአብሔር ፊት በመናዘዙ ጸሎቱ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ መልስ አግኝቷል። ይኽንንም «እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሁሉ፥ ኑ፥ ስሙኝ፤ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ። በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፥ በአንደበቴም ከፍ ከፍ አደረግሁት። በልቤስ በደልን አይቶ ቢሆን እግዚአብሔር አይሰማኝም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ፤ የልመናዬንም ድምፅ አደመጠ። ጸሎቴን ያልከለከለኝ፥ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ፥እግዚብሔር ይመስገን።» በማለት በመዝሙሩ ገልጦታል። መዝ ፷፭፥፲፮። ሰው ኃጢአቱን ከሰወረ እግዚአብሔር አይምረውም። «በውኑ የእግዚአብሔር እጅ ማዳን አትችልምን? ጆሮውስ አይሰማምን? ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ለይታለች፤ ይቅርም እንዳይላችሁ ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። እጃችሁ በደም ጣታችሁም በኃጢአት ተሞልቷል፤ ከንፈራችሁም ዓመፅን ተናግሯል፤ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቷል።» እንዳለ። ኢሳ ፶፱፥፩።
ሐ. ጸሎታችን የሚሰማው ይቅር ባይ ልቡና ሲኖረን ነው።
ጌታ በወንጌል እንደምን ባለ ሰውነት መባ ማቅረብ እንዳለብን ሲያስተምር «መባህን በመሠዊያው በምታቀርብበት ጊዜ፥ በዚያም ሳለህ የተጣላ ወንድምህ እንዳለ ብታስብ፥ መባህን ከዚያ በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድና አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤» ብሏል። ማቴ ፭፥፲፬። በቅዱስ ማርቆስ ወንጌልም፦ «በምትጸልዩበትም ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ በወንድማችሁ ያለውን በደል ይቅር በሉ። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።» የሚል የጌታ ቃል ተጽፏል። ማር ፲፩፥፳፭።
የጸሎት ዘርፍ ይህ ብቻ ሳይሆን ብዙ ነው። ይልቁንም ሐዋርያው ይሁዳ፦ «ወንድሞቻችን ሆይ፥ እናንተ ግን በተቀደሰች ሃይማኖት ራሳችሁን አንጹ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ።» እንዳለ በመንፈስ ቅዱስ በተቃኘ በተጎበኘ ሰውነት መጸለይ ይገባል። ይሁዳ ፩፥፳። ከሁሉም በላይ ሳይሰለቹ መጸለይ ያስፈልጋል። ሉቃ ፲፩፥፭። እንግዲህ በመንፈስ ሆነን በሥርዓተ ቅዳሴው፦ «ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በኀበ እግዚአብሔር ።» የተባለውን ይዘን ስለ ቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ሁላችንም ተግተን ልንጸልይ ይገባናል። ቤተክርስቲያን ሰላም ከሆነች ሕይወታችን ትዳራችን ሰላም ይሆናል። ሀገራችንም ሰላም ትሆናለች። የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን። አሜን።

10 comments:

 1. የህይዎት ቃልን ያሰማልን አባታችን!!! ለቤተክርስቲያናችን ሰላምን ይስጥልን።

  ReplyDelete
 2. Kale Hiwot Yasemalin. Egziabiher Be-edime betsega Yitebiqilin Abatachin.

  ReplyDelete
 3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን
  ረጅም የአገልግሎት ዕድሜና በረከቱን አይንፈግብን

  ReplyDelete
 4. amen abatachen, kale hiwoten yasemalen

  ReplyDelete
 5. Melkam new berta daju eskahun baltsfilhm hulem eyanebeku new tiru timhrt new
  simun tastawsaleh biye egemtalehu

  ReplyDelete
 6. ቃለ ህይወት ያሰማወት አባታችን...እግዚታብሄር እስከመጨረሻዉ ይጠብቆት

  ReplyDelete
 7. የሰው ልጆች እንደጥሪያቸውና እንደሥራቸው ከፈጣሪአቸው ከእግዚአብሔር ፊት ቆመው ሲገኙ አጠቃላይ ምድራዊ የቅድስና ሕይወታቸው የመሰከረላቸው የሃይማኖትና የመልካም ሥነ-ምግባር አባቶች ናቸው

  ReplyDelete
 8. ቃለ ሕይወት ያሰማል ረጅም የአገልግሎት ዕድሜ ይስጥልን

  ReplyDelete
 9. Kale hiywet yasemalen Kesis rejim edeme ketena gar yestelin.

  ReplyDelete