Wednesday, May 2, 2012

፩፥፫፦ ምክረ ወልደ አዴር ንጉሠ ሶርያ፤


      የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር በየጊዜው፣ በየምክንያቱ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ይዋጋ ነበር። በሰዋራ ቦታም ተሸሽጎ የእስራኤልን ንጉሥ ለመግደል ከአገልጋዮቹ ጋር በምሥጢር ይመክር ነበር፡፡ ነገር ግን የሩቁም የቅርቡም ምሥጢር አድሮበት በሚኖር የእግዚአብሔር መንፈስ የሚገለጥለት ነቢይ ኤልሳዕ፦ «ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ፤» እያለ መልእክተኛ በመላክ የእስራኤልን ንጉሥ ብዙ ጊዜ ከሞት አዳነው። ከቅዱሳን ጋር መኖር ጥቅሙ እንዲህ ለመዳን ነውና፡፡ የሶርያው ንጉሥ ወልደ አዴር ምክሩ ስላልተሳካለት በመንፈሱ እጅግ ተበሳጨ፡፡ ከአገልጋዮቹም መካከል ምሥጢር የሚያባክን ያለ መስሎት፦ «ለእስራኤል ንጉሥ ማን እንደሚነግረው አትነግሩኝምን?» አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ፦ «ጌታዬ ሆይ በእስራኤል ሀገር ነቢዩ ኤልሳዕ አለ፥ አይደለምን? በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውንና ቃልህን ሁሉ ለእስራኤል ንጉሥ እርሱ ይነግረዋል፤» አለው። በዚህም ጊዜ ምክሩን ወደ ኤልሳዕ አዙሮ «ልኬ አስይዘው ዘንድ ሄዳችው ወዴት እንደሆነ ዕወቁ፤» ብሎ ቢጠይቃቸው «እነሆ በዶታይን አለ፤» ብለው ነገሩት፡፡

          ንጉሡ ወልደ አዴር ፈረሶችና ሰረገላዎችን ብዙ ጭፍራም ወደ ዶታይን ላከ፥ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበብዋት፥ የኤልሳዕ ሎሌ ማልዶ ተነሥቶ ይህንን በማየቱ ደነገጠ። ሰው ሰውኛውን ዙሪያቸው ታጥሮ፥ መሸሻ ሜዳ፥ መሽሎኪያ ቀዳዳ፥ መሸሸጊያ ዋሻ፥ መመከቻ ጋሻ አልነበራቸም። በዚህ ምክንያት «ጌታ ሆይ! ወዮ ምን እናድርግ?» ብሎ ጮኸ። ነቢዩ ኤልሳዕ «ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ፤» ቢለውም መረጋጋት አልቻለም፡፡ በዚህን ጊዜ «አቤቱ ያዩ ዘንድ ዓይኖቹን እባክህ ግለጥ፤» ብሎ ጸለየለት። የሎሌው አይኖች ያዩ የነበረው ምድራዊውን ሠራዊት እንጂ ሰማያዊውን ሠራዊት አልነበረም። እግዚአብሔርም የብላቴናውን የውስጥ ዓይኖች በነቢዩ ምልጃ ገለጠለት፥ እነሆም የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ከልለውት አየ።
          የሶርያው ንጉሥ ሠራዊት ወደ ነቢዩ በወረደ ጊዜ፦ «አቤቱ እነዚህን ሰዎች አሳውራቸው፤» ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። መሣሪያው ጸሎቱ ነውና እግዚአብሔር እንደ ኤልሳዕ ቃል አሳወራቸው። የእግዚአብሔር ቃል በቅዱሳን ዘንድ የከበረ እንደሆነ ሁሉ የቅዱሳንም ቃል (ልመና ጸሎትና ምልጃ) በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው። ቃሉን እግዚአብሔር ያከበረለት ኤልሳዕ፦ «መንገዱ በዚህ አይደለም ከተማይቱም ይህች አይደለችም፥ የምትሹትን ሰው አሳያችሁ ዘንድ ተከተሉኝ፤» ብሎ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው።
           ሁሉም የሶርያ ሠራዊት ዓይኖቻቸውን ታውረው በኤልሳዕ መሪነት ወደ ሰማሪያ በገቡ ጊዜ፦ «አቤቱ ያዩ ዘንድ የእነዚህን ሰዎች ዓይኖች ግለጥ፤» ብሎ ዳግመኛ ጸለየ። እግዚአብሔር ዓይኖቻቸውን ቢገልጥ በሰማርያ መካከል እንዳሉ አወቁ። የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ፥ ኤልሳዕን፦ «አባቴ ሆይ ልግደላቸውን?» ቢለው «በሰይፍህና በቀስትህ የማረካቸውን ግደል እንጂ በሰይፍህና በቀስትህ የማረካቸው አይደሉምና አትግደላቸው፤ ይልቁንስ እንጀራና ውሃ አቅርብላቸው፥ በልተውና ጠጥተውም ወደ ጌታቸው ይመለሱ አለው፡፡ እርሱም የተባለውን ፈጽሞ ወደ ሀገራቸው አሰናበታቸው፡፡
          የዚህ ዓለም ባለስልጣኖች እንደ ሶርያ ንጉሥ ናቸው። በምስጢር የሚመክሩት ሁሉ የእውነት ምስክሮችን ለማጥፋት ነው፡፡ የሚመኩትም በሠራዊታቸው ነው፡፡ ሠራዊታቸውም «ሂድና አጥፋ፤» ሲባል «ለምን»? አይልም፥ እውነቱን ቢያውቀውም ኅሊናውን ሸጧል፡፡ በመንፈሳዊው ነገር ግን በውስጠ ሥጋዊውም ዓለም እንዲሁ ነው፥ የሾማቸውን ሰማያዊ ንጉሥ በምድራዊው ንጉሥ ለውጠው እንደ ንጉሡ የሚያጎነብሱ በዝተዋል። እነዚህም ለንጉሡ ለክርስቶስ መስቀል እያሰገዱ መኖር ሲገባቸው የከበረውን መስቀል በምድራውያን ጫማ ስር ጥለው የሚኖሩ ናቸው፡፡ በክርስቶስ ቤዛነት በነፍስም በሥጋም የከበሩበትን መስቀል ያዋረዱ፥ አብያተ ክርስቲያናት ቢቃጠሉ፥ ገዳማት ቢመዘበሩ፥ ምዕመናን በነፍስም በሥጋም ቢራቡ፥ ፍትሕ መንፈሳዊ ፍትሕ ሥጋዊ ቢያጡ፥ ምንም የማይደንቃቸው ናቸው፡፡
          የእስራኤል ንጉሥ ሕይወት የሚጠበቀው በነቢዩ በኤልሳዕ አማላጅነት መሆኑን ያወቀ የሶርያው ንጉሥ ፊቱን ያዞረው፥ ሠራዊቱን ያዘመተው ወደ ኤልሳዕ ነው፡፡ ሰይጣንም የሀገሪቱና የሕዝቡ ሕይወት ተጠብቆ የሚኖረው በቤተክርስቲያኒቱ ሃይማኖትና ሥርዓት፥ በማያቋርጥም የሃያ አራት ሰዓት ጸሎት መሆኑን ስለሚያውቅ፥ ከጥንት ጀምሮ ሠራዊቱን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ እንዳዘመተ ነው፡፡ የምዕመናኑ ሕይወት የሚጠበቀው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱሳን ሁሉ አማላጅነት መሆኑን ስለሚያውቅም እነዚህን ከምዕመናን ልቦና ለማጥፋት ሠራዊቱን አሕዛብንና መናፍቃንን አዝምቷል፡፡ እንግዲህ ይኸንን አውቀን የሰይጣንን ምክር ለማፍረስ፥ እንደ ነቢዩ እንደ ኤልሳዕ ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር ልናዞር፥ በጾምና በጸሎትም ልንጠመድ ይገባል፡፡ እንደ እርሱም የይቅርታ ሰዎች መሆን ይጠበቅብናል። ፪ኛ ነገ ፮፥፯-፳፫። ይልቁንም እንደ መስቀሉ ጌታ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤» እንበል፡፡ እንደ ኤልሳዕ ሎሌ ምድራዊውን ሠራዊት አይቶ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ ቀና ብሎ ሰማያዊውን ሠራዊት መመልከት ያስፈልጋል። አይተው የሚያሳዩ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ ያሉ አባቶችም ያስፈልጉናል፡፡ ከፈለግናቸው እናገኛቸዋለን። የምናገኛቸው ግን በሥልጣን መሰላል ላይ ተንጠልጥለው ከፍ ብለው ሳይሆን ዝቅ ብለው ከዋሻ ከጉድጓድ ውስጥ ነው፡፡ በባንክ ገንዘብ አከማችተው ሳይሆን በቤተክርስቲያን ደጅ ወድቀው እንደ የኔቢጤ ምጽዋት ሲቀበሉ ነው። ይኸውም የተመጸወቱትን መልሰው ለሌላው በስውር ለመመጽወት ነው። ቤተክርስቲያኒቱ ተጠብቃ ያለችው በእነዚህ ነው። እኛ አላወቅናቸውም፥ ለማወቅም ፍላጎት የለንም፥ እግዚአብሔር ግን ያውቃቸዋል፡፡ ዓለም ቤተክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ሲመክር ይውላል፥ ሲመክርም ያድራል፡፡ እነርሱ ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ እንድትጠበቅ በጸሎታቸው ከእግዚአብሔር ይማከራሉ። እግዚአብሔርም «ስለእኔ (ስለ ቸርነቴ) ስለ ባሪያዬም ስለዳዊት (በአጸደ ሥጋም በአጸደ ነፍስም ስላሉ ቅዱሳን) ይህችን ከተማ (ኢየሩሳሌምን፥ ቤተክርስቲያንን) እረዳታለሁ አድናታለሁ፤» ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡

፩፥፬፦ ምክረ አድራሜሌክ ወሳራሳር፤

          አድራሜሌክና ሳራሳር የአሦር ንጉሥ የሰናክሬም ልጆች ናቸው፡፡ አሦር ስምዋን ያገኘችው አሦር ከተባለው ከሴም ሁለተኛ ልጅ ነው፡፡ ዘፍ ፲፥፳፪። እርሱም አሦርውያን ለተባሉት ሕዝቦች የመጀመሪያ አባት ነው። ሰናክሬም ከ ፯፻፭- ፮፻፹፩ ዓ.ዓ. ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሦራውያን ላይ ነግሧል፥ በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥትም በይሁዳ ከተሞች ላይ ወረራ አካሂዷል። በእግዚአብሔር ላይ ሲገዳደርም «ሕዝቅያስ፦ እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ አያታልላችሁ፥ በውኑ የአሕዛብ አማልክት ሀገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? ሰማሪያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ ሀገሮች አማልክት ሁሉ ሀገሩን ከእጄ ያዳነ አለን?» በማለት በመልእክተኛው በኩል የትዕቢት ቃል ተናግሮአል፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስ ግን ይህን ሰምቶ በፍፁም ሐዘን ልብሱን ለሁለት ቀዶ፥ ማቅ ለብሶ ወደ እግዚአብሔር  ቤት ገባ፡፡ የቤቱን አዛዥ ኤልያቄምን፥ ጸሐፊውን ሳምናስን እና የካህናቱን ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው የሚሆነውን ሁሉ እንዲጠይቁት ወደ ነቢዩ ወደ ኢሳይያስ ላካቸው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም «ለጌታችሁ (ለንጉሡ ለሕዝቅያስ) እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለሰደቡኝ ስለ ሰማኸው  ቃል አትፍራ፥ እነሆ መንፈስን በላዩ እሰድዳለሁ፥ ወሬንም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፥ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት፤» ብሎ መልሶ ላከበት። ኢሳ ፴፮፥፩-፳፪፣ ፴፪፥፩-፯።   
          ንጉሡ ሕዝቅያስ ሰናክሬም ዳግመኛ እግዚአብሔርን ሰድቦ የላከውን ደብዳቤ ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ ካነበበው በኋላ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። ወደ እግዚአብሔርም «አቤቱ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ  የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ! አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምለክ ነህ፥ ሰማይና ምድርን ፈጥረሃል፥ አቤቱ ጆሮህን አዘንብል፥ ስማ፥ አቤቱ ዓይንህን ክፈትና በህያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ተመልከት፤» ሲል ጸለየ። እግዚአብሔርም ነቢዩ ኢሳይያስን ወደ ሕዝቅያስ ልኮ በሚያጽናና ቃል ተናገረው። «የአሦር ንጉሥ ወደዚያች ከተማ አይመጣም፥ ፍለጻውንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ አያጥራትምም፥ በመጣበትም መንገድ በዚያ ይመለሳል፥ ወደዚህም አይመጣም ይላል እግዚአብሔር፥ ስለ እኔም ስለባሪያዬም ስለዳዊት ይህቺን ከተማ እረዳታለሁ አድናታለሁም፤» አለው፡፡ እግዚአብሔር ስለ ቸርነቱና ለቅዱሳን ስለሰጣቸው የምህረት ቃል ኪዳን ሲል እንደሚያድን ተናገረ፡፡ ቅዱሳን በሥጋ ቢሞቱም ቃልኪዳናቸው እንደማይሞትና በአጸደ ነፍስም እንደሚያማልዱ ሲናገር ነው፡፡ በዚህም መሠረት እርሱ እግዚአብሔር በአጸደ ነፍስ ያለውን ቅዱስ አንሥቶ ስለ ዳዊት ብዬ እንዳለ፥ እኛም በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንን እያነሣሣን ስለ ቅዱስ ተክለሃይማኖት፥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብለህ እንለዋለን፡፡
          እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድንበት፥ አሦራውያንን የሚበቀልበት ጊዜ ሲደርስ የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ሰዎችን ገደለ። ማልደውም በተነሡ ጊዜ እነሆ ሁሉንም በድኖች ሆነው አገኟቸው፡፡ የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ፡፡በዚህን ጊዜ የገዛ ልጆቹ አድራሜሌክ እና ሳራሳር በአባታቸው ላይ ክፉ መከሩበት። «ሕዝቡን አስጨርሶ የመጣው እኛ በማን ላይ ልንነግሥ ነው? አሉ።» በአንድ መልኩ እውነታቸውን ነው፥ የሚነገሠው በሕዝብ ላይ ነው። አእምሮ ላለው ሰው ሕዝብ፦ መንገሻ፥ መክበሪያ ነው። ስለሆነም ሕዝብ መከበር መፈራት አለበት። በዓለም ላይ የሚታየው ግን እንዲህ አይደለም፥ በሕዝብ ስም ምለው ተገዝተው፣ ገድለው ተጋድለው ሥልጣን የያዙ ሁሉ፦ ሕዝቡን ሲንቁት፥ መፈጠሩን እስከሚረግም ድረስም አስጨንቀው ሲገዙት ይታያል፡፡ የሚመኩት በሠራዊታቸው ነው፡፡ ዳሩ ግን አንድ ቀን ጊዜው ሲደርስ እንደ ሰናክሬም ሠራዊት ይረግፋል፥ ወይም ልብ ገዝቶ ግፍ ከመፈጸም እጁን ይሰበስባል። ሰናክሬም በመጨረሻ ብቻውን ቀርቶአል፥ ልጆቹም መክረውበታል፥እነርሱ እንኳን ዘመድ አልሆኑትም። ወደ ቤተ ጣዖት ገብቶ (በናሳራክ ቤት)ሲሰግድ እንደመከሩት በሰይፍ ገድለውታል። በዚህም ምክንያት ወደ አራራት ሀገር ኮበለሉ፥ የጓጉለትን ሥልጣን ግን አላገኙም። በሰናክሬም ፈንታ የነገሠው ሌላኛው ልጅ አስራዶን ነው። በእግዚአብሔር ላይ የሚገዳደር ሁሉ መጨረሻው እንዲህ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬማ እንኳን ሥጋውያኑ መንፈሳዊያን ተብዬዎችም እግዚአብሔርን ንቀነዋል፥ ቤተ መቅደሱንም አርክሰነዋል፥ በፍቅረ ሢመት ሰክረናል፥ በፍቅረ ንዋይም ተቃጥለናል፥ መንጋውን ለተኩላ አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት፥ ሰውን ማክበር ታሪክ ሆኖ ቀርቷል። ምክራችን ሁሉ እንደ አሕዛብ ለማጥፋት ነው። ከእግዚአብሔር ይልቅ ምድራዊ ባለሥልጣኖችን እንፈራለን፥ ሁላችንም የምንመስለው ሰናክሬምንና ልጆቹን ነው፡፡ ሕዝቅያስንና ኢሳይያስን የሚመስል አልተገኘም፡፡ ሰናክሬም የተገኘው ከጣዖት እግር ስር ተንበርክኮ ነው፡፡ እኛም ሥልጣኑ፥ ገንዘቡ፥ ዘረኝነቱ ጣዖት  ሆኖ አንበርክኮናል፡፡ ሕዝቅያስ በችግሩ ጊዜ የጠየቀው ኢሳይያስን ነው፥ የሄደው ወደ ቤተመቅደስ ነው፥ የጸለየው ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡ መላቅጡ በጠፋበት በዚህ ዘመን እርሱን አብነት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢሳይያስን እንደመጠየቅ ቅዱሳንን መጠየቅ፥ ዘወትር በሃይማኖት ወደ ቤተ መቅደስ መገስገስ፥ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ማመልከት ያስፈልጋል፥ ያን ጊዜ እግዚአብሔር መልስ ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ በኲል ለንጉሡ ለሕዝቅያስ መልስ እንደሰጠው፥ በእመቤታችን እና በቅዱሳን በኩል መልስ ይሰጠናል፡፡

፩፥፭፦ ምክረ ፈሪሳውያን፤

          ፈሪሳውያን ከአይሁድ ሦስት የሃይማኖት ወገኖች መካከል አንዱ ክፍል ናቸው፡፡ የተቀሩት ሰዱቃውያን እና ኤሴይ ይባላሉ፡፡ ፈሪሳውያን ሀብታሞችና የምኲራብ አለቆች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች የሙሴን ህግ በጥንቃቄ የተረጎሙ ናቸው፡፡ክርስቶስ ሲመጣ የጦር ሠራዊት አቋቁሞ እስራኤልን ከቀኝ ግዛት ነጻ ያወጣል፥ የዳዊትንም መንግሥት ያድሳል፥ እኛም የመንግሥቱ ባለሟሎች እንሆናለን ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን እነርሱ በጠበቁት መንገድ ስላልመጣ ተቃወሙት፥ ሊገድሉትም ተማከሩ። «ከዚህም በኋላ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝብ ሽማግሌዎች፥ ስሙ ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰባሰቡ። ጌታችን ኢየሱስንም በተንኮል ይዘው ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ፤» ይላል። ማቴ ፳፮፥፫። ለምክራቸው ማስፈጸሚያ ይሁዳን በ 30 ብር ገዙት። እርሱም ክርስቶስን ለእነርሱ አሳልፎ ይስጥ ዘንድ ምቹ ግዜ ይሻ ነበር። ማቴ ፳፮፥፲፬-፲፮።  ጊዜው ሲደርስም እንደሰላማዊ ሰው ሰላም ላንተ ይሁን ብሎ ጉንጩን ስሞ አሳልፎ ሰጠው። ማቴ ፳፮፥፵፱። በመጨረሻ ግን «ንጹህ ደምን አሳልፌ የሰጠሁ እኔ በድያለሁ፤» ብሎ ብሩን ለካህናት አለቆች እና ለሕዝቡ ሽማግሌዎች ከመለሰ በኋላ ታንቆ ሞተ፡፡ ማቴ ፳፯፥፫፣ የሐዋ ፩፥፭። ይህንን ሰው ጌታችን አምላካችን መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል፤» እያለ አስጠንቅቆት ነበር። እንደሌሎቹ ደቀመዛሙርት «መምህር ሆይ፥ እንግዲህ እኔ እሆን?» ባለም ጊዜ «አንተ እራስህ አልህ፤» ብሎታል፡፡ ማቴ ፳፮፥፳-፳፭። ይሁዳ ግን አንድ ጊዜ ሰይጣን ወደ ልቡ ስለገባ፥ አንድም የተነገረበት ክፉ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ አልተመለሰም። ዮሐ ፲፫፥፳፯፣ መዝ ፷፰፥፳፭፤ ፩፻፰፥፰።
          ቤተክርቲያንም የከርስቶስ አካል በመሆኗ እድሏ ይኸው ነው። ሁልጊዜ አሳልፈው የሚሰጧት የገዛ ልጆቿ ናቸው፡፡በጥምቀት ወልዳ፥ በትምህርት ኮትኩታ፥ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ያሳደገቻቸው፥ በሥልጣንም ከዲቁና እስከ ሊቀ ጵጵስና ድረስ ቀብታ የሾመቻቸው፥ ቁልፏን የሰጠቻቸው፥ መንጋዋን  ያሰረከበቻቸው ልጆቿ እንደ ይሁዳ  ሲሆኑባት ይታያል። ከቤተክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው፥ በዘመናችንም በገሃድ እንደምናየው፥ ባእድ ከጎዳት ይልቅ የገዛ ልጆቿ ከውስጥ ሆነው ያቆሰሏት ቁስል ይጸናል፥ የውስጥ ደዌ ደግሞ ከሁሉ ይከፋል፡፡
          ይሁዳ ከክርስቶስ አጠገብ እንደ እርሱ ከተመረጡ ሐዋርያት ጋር ተቀምጦ ለክርስቶስ ጠላቶች መሣሪያ እንደሆነ ሁሉ፥ በቤተክርስቲያንም ከታች እስከላይ ባለው የሥልጣን እርከን ላይ ተቀምጠው ከቤተክርስቲያን ጠላቶች ከመናፍቃን እና አልፈውም ከአሕዛብ ጋር የሚሠሩ፥ ምንም መንፈሳዊነት ከሌላቸው ፖለቲከኞችም ጋር የሚያሽቃብጡ አሉ። እንደነዚህ አይነቶች ሰዎች እንደ ይሁዳ እስከመጨረሻው የማይመለሱ ናቸው፡፡ እንዳይመለሱም ወደ ልቡናቸው የገባ ሰይጣን መልካም እንደሠሩ አድርጎ እያሳያቸው ተብትቦ ይይዛቸዋል፡፡
          እርግጥ ለሀገር የሚበጁ፥ ቤተክርስቲያንን የማይዳፈሩ ፖለቲከኞች አሉ። በሚበዛው ስንናገር ግን ቤተክርስቲያንን የሚዳፈሩት ይበዛሉ፡፡ እንዲያውም የራሳቸው ታዛዦች የሆኑ ሰዎችን ከላይ እስከታች በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ያስቀምጣሉ። የሚያስቀምጡትም ዓይን ባወጣ መልኩ በቀጥታ፥ ወይም በተዘዋዋሪ ይሆናል። እነዚህም የሚመክሩት ለራሳቸው ዓላማ ካስቀመጧቸው ሰዎች ጋር እንጂ ለቤተክርስቲያኒቱ ደሙን ካፈሰሰው ከኢየሱስ ክርስቶስና ከእርሱ ባለሟሎች ጋር አይደለም። በመሆኑም ይሁዳ እንኳን «ንጹሑን ደም አሳልፌ የሰጠሁ እኔ በድያለሁ፤» ብሎአል፡፡ እነዚህ ግን ለዚህም የማይበቁ ናቸው። ብዙ ጊዜ የኛ ትኩረት በቃልና በግብር በተገለጡት ላይ ብቻ ነው፥ ይሁን እንጂ የቤተክርስቲያን ልጆች የሚመስሉ ነገር ግን ያልሆኑ ብዙዎችን እያየን ነው። ይሁዳስ በመሳም ነው አሳልፎ የሰጠው፥ እነዚህ ግን በመንከስ ነው ቤተክርስቲያንን አሳልፈው የሚሰጡት፡፡
          በቤተክርስቲያን ያልመከረና የማይመክር የለም። ፕሮቴስታንቶቹ፥ ካቶሊኮች፥ እስላሞቹ፥ ፖለቲከኞቹ በውስጥ ከተፈጠሩ የእናት ጡት ነካሾች ጋር ሆነው ይመክራሉ፡፡ ዓላማቸውም ቤተክርስቲያንን ለማጠፋት (ለመግደል) ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ግን አትጠፋም (አትሞትም)፥ ምክንያቱም አንድ ጊዜ ራሷ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሥዋዕት በግ ሆኖ ስለእርሷ ሞቶላታልና። ከሞተም በኋላ እንደ ኦሪቱ የመሥዋዕት በግ ሞቶ አልቀረም፥ በሦስተኛው ቀን ሙስና መቃብርን አጠፍቶ፥ ሞትን ድል ነስቶ በመለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል፡፡
          በቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው፥ ሥልጣኗን ጨብጠው፥ ደሞዟን እየበሉ፥ እንደ ይሁዳ ሙዳየ ምጽዋቷን እየገለበጡ፥ ታሪኳን እየደለዙ፥ ሃይማኖቷን እየበረዙ፥ ሥርዓቷን እያጠፉ፥ ንዋየ ቅድሳቷን እየሸጡ፥  ከፖለቲከኞችም ጋር የሚሠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ አብያተክርስቲያናት በአሕዛብ ሲቃጠሉ፥ ታላላቅ ገዳማት በመሣሪያ ሲደፈሩ፥ የውስጥ መናፍቃን በገሃድ ሲፈነጩ፥ ምንም የማይሰማቸው በዝተዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ላይ የሚመክሩ እንጂ ለቤተክርስቲያን የሚመክሩ አልተገኙም፡፡ ከተገኙም የተለያየ ስም እየተሰጣቸው ራስ ራሳቸውን ይቀጠቀጣሉ። እነዚህም እድል ፈንታቸው፥ ጽዋ ተርታቸው በዘመኑ ይሁዳዎች ለመከራ ተላልፈው መሰጠት የሆነባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ስለ ቤተክርስቲያን መስቀል መሸከም ክብር መሆኑን ስለሚያውቁት በጸጋ ይቀበሉታል። በፍቅረ ሢመት የተቃጠሉ፥ በፍቅረ ንዋይም የታወሩ ሰዎች ከቢጤዎቻቸው ጋር መክረው የሚያመጡባቸውን ሁሉ በትእግሥት ያሳልፉታል፡፡

9 comments:

 1. Abatachen kalehihowt yesemalen. Bizugize honowt minhonew new? ene yemiteretirew USA balew tehadiso chiger yehon bey assibalehu. Neger gen bertu engi lefeten ayenberkeku, telot, mihila, etc lebetekristina ena leenunutgnchu agelgayoch betame yemiyasfeligebet gize newna. Betru, tigu, asenanune, seleyoulen, etc.

  ReplyDelete
 2. አባታችን ቀሲስ ደጄኔ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ እግዚአብሔር በእድሜ፣ በጸጋ፣ በጤና ይጠብቅልን፡፡

  ተመስገን!! አስተማሪና መካሪ መንፈሳዊ ጽሑፎቹ በመዘግየታቸው አባታችንን ምን አገኛቸው ብለን ግራ ተጋብተን ነበር አሁን በመቀጠላቸው ደስታችን ገደብ የለውም፡፡ በነገር ሁሉ የሚጠብቀን በደላችንን ሳይቆጥር ቅዱስ ቃሉን የሚመግበን የአባቶቻችን አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡

  ReplyDelete
 3. Kesis Dejene,
  Welcome back. I would prefer to write in Amharic but as I don't have the Ge'ez software, I am obliged to express my idea in English. First of all, I would like to thank God for you are well and have come back to feed us with God's word. I feel like crying when I read your articles. They remind me of the good old days when I used to sit at Sunday School gatherings to learn from our fathers. I now live abroad and even though I attend the weekly Holy Liturgy, it has been quite a while since I sat down at a Sunday School program. Your teachings, however, make me feel as if I was back home in a church learning the truth and the way to eternal life. I wish God give you the strength and the patience to continue what you are doing now as it is a source of comfort and hope to most of us. The second point I like to raise is about the temptation our country, our church and the Orthodox Christian population are facing at this point in time. You have rightly mentioned what is really happening around the church. I think our sin has surpassed its limit and God has turned His face away from us. I sometimes feel sad and helpless. I feel as if we are left alone by ourselves with no real fathers beside us. It gives me a great hope to read what you wrote about the presence, even at this time, of true fathers whom God respects. This is a hope which shows that God is trusted to change our history and bring back our Church to stand on its feet once again. We need to cry for this to happen and let God give us broken hearts which kneel in front of Him with sorrow and regret.
  Egziabher Amlakachin Hagerachinin, Haymanotachinin, Hizbachinin yasibilin. Benefisina besiga balu abatochachin tselot yihenin kifu gize asalifo melkamun zemen, lijochachin beselam behaymanot yeminorubetin zemen yamitalin.
  Kesis Dejene, Egziabher yistilin, Egziabher yabertalin. Selamin lelibachin yemisetewin yihenin melkam timihirit hulgize endiyakebilun ye Egziabher fekadu yihun. Amen.

  ReplyDelete
 4. Enquan dehina metu Abatachin kale hiwot yasemalin tesfa megiste semayn yaworsiln!Ebakiwo endezih aytifubin beyegizew melkamun migib yimegibun.

  ReplyDelete
 5. ቃለህይወት ያሰማልን አባቶቻችን እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር ይላሉ እውነትም ለጊዜው ይደብቋታል እንጂ ተቀብራ አትቀርም አምላካችን ስለእመቤታችንና ስለቅዱሳን ብሎ እደማይተወን ሙሉ እምነት አለን።

  ReplyDelete
 6. Kesis, I always try to read your posts but never able to do so. Please I really want keep up with your posts if they posted as a PDF format,

  ReplyDelete
 7. Kale hiwot yasemalen!! Enem betesebem bezhi kal teberkenal. Lemefesem yabkan, amen.

  ReplyDelete
 8. kesis, please posted also as a PDF formate if possible.

  ReplyDelete