Sunday, January 29, 2012

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል፦ ፲፪


እግዚአብሔር፦ ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጅ ሲሰጥ፥ የጋብቻ መሠረታዊ ዓላማ፦ ፩ኛ፦ በፍትወተ ሥጋ ላለመቸገር፤ ፪ኛ፦  ለመረዳዳት፤ ፫ኛ፦ ወልዶ ዘር ለመተካት እንደሆነ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። ዳሩ ግን የሰው ልጅ በሦስቱም ሲቸገርና ሲያስቸግር ይታያል፤ ለዛሬው የምንመለከተው በሦስተኛው ረድፍ  የተመለከተውን ነው።

          ወልደው  ዓይናቸውን በዓይናቸው ለማየት፥ ዘራቸውን ተክተው ለማለፍ ሁሉም ይፈልጋሉ። በተጋቡ በዓመቱ ልጅ ይጠብቃሉ፥ ዓመቱ አልፎ ሁለተኛውና ሦስተኛው ዓመት ሲደገም ማሰብ፥ መጨነቅ፥ ከዚያም አልፎ መጨቃጨቅ ይጀመራል። የባልንጀራና የቤተሰብ ጣልቃገብነትም ቀላል አይደለም። የሚያገባውም የማያገባውም፥ የቅርቡም የሩቁም፥ ከልብ ያሰበውም ግድየለሹም፥ «ምነው እስከዛሬ?» የሚለው ይበዛል። በተለይ በቤተሰብ በኲል፦ «የእኛ ዘር ወላዶች ናቸው፥ መካንነቱ ከእሱ ነው፥ አይደለም ከእሷ ነው፤» በሚል ሐሜት ከመታመስ አልፈው  በአሽሙር መነካካት ይጀምራሉ። በመጨረሻም ክፉ ደግ ወደ መነጋገር ይደርሳሉ። የባሰባቸው ደግሞ የተክሊልን እና የቅዱስ ቁርባንን ድንበር አፍርሰው፥ «እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለየው፤» የሚለውን የጌታ ቃል ንቀውና አቃልለው፥ ቅዱሱን ጋብቻ ያፈርሱታል። የሚገርመው ነገር በመካንነት ምክንያት ጦርነት የሚያነሡና የሚያስነሡ ሰዎች፥ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ ልጅ ቢወለድ እጃቸውን ከዚያ ትዳር ላይ አያነሡም። ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ «ምን ቢሟላ ክፉ ሰው የሚለው አያጣም፤» እንዳሉ፥ ክፉዎች ለጸብ ምክንያት አያጡም። የልጅ ልጅ ያዩትን እንኳ እስከማፋታት ይደርሳሉ። ለነገሩ የውጪዎቹ ድርሻ ባለትዳሮቹ በለኰሱት እሳት ላይ ነዳጅ መጨመር ነው። ጥንትስ መካንነቱ ከማን እንደሆነ ላይታወቅ ይችላል፥ አሁን ግን ተመርምሮ መካንነቱ ከማን እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። ለክርስቲያን የሚጠቅመው ግን በዚህ መንገድ መጓዝ ሳይሆን የእምነትን ሥራ መሥራት ብቻ ነው። ይኸውም «እግዚአብሔር ባይፈቅድ ነው፥ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው፤» እያሉ መተው መንፈሳዊ ጥቅም አለው። ከዚህም ሌላ እግዚአብሔር አዘግይቶ የማታ ማታ «የኋላ እሸት፥ የማታ እንጀራ» እንዲሉ ይሰጠንም ይሆናል። ጨርሶ ቢቀርም ተመስገን ነው። እምነቱ ካለ የችግረኛን ልጅ እንደራስ ልጅ አድርጎ ማሳደግ ይቻላል። ምናልባት መካንነቱ የመጣው ይኽንን የጽድቅ ሥራ እንድንሠራ ይሆናል። ነጮቹ ከድሆች አገሮች የችግረኞችንና የሙት ልጆችን ያውም ብዙ ገንዘብ እያወጡ ለእኛ ያልታየንን ሥራ እየሠሩ ነው። የእነርሱ ችግር አለው፥ ምክንያቱም ልጆቹን ከሃይማኖታቸው፥ ከሥርዓታቸው፥ ከባሕላቸው፥ ከቋንቋቸው ለያይቶ ያስቀራቸዋል። ሲያድጉም ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ፈልገው ከውስጣቸው ሲያጡ ባዶነት ይሰማቸዋል። «የሰው ወርቅ አያደምቅ፤» ይሆንባቸዋል። ስለዚህ እነርሱ ያደረጉት እኛ ፈጽሞ ያላሰብነውን በመሆኑ እነርሱን ሳይሆን ራስን መውቀስ ይገባል።
          በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጨረሻ እግዚአብሔር የጎበኛቸው መካኖች ታሪክ ለአብነት ተመዝግቦ ይገኛል። አብርሃም ከሕግ ሚስቱ ከሣራ ልጅ ከመውለድ በመዘግየቱ፥ «አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምን ትሰጠኛለህ? እነሆ፥ ልጅ ሳልወልድ እሞታለሁ፤ የቤቴም ወራሽ ከዘመዴ ወገን የሚሆን የደማስቆ ሰው የማስቄ ልጅ ይህ ኢያውብር ነው። . . . ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፥ የዘመዴ ልጅ እርሱ ይወርሰኛል።» እስከ ማለት ደርሶ ነበር። እግዚአብሔር ግን፦ «እርሱ አይወርስህም፥ ነገር ግን ከአብራክህ የሚወጣ እርሱ ይወርስሃል። . . . ወደ ላይ ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ልትቈጥራቸው ትችል እንደሆነ ከዋክብትን ቊጠራቸው፥ ዘርህም እንደዚሁ ነው።» በማለት አጽናንቶታል። ዘፍ ፲፭፥፪-፭። አብርሃም ግን እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ መጠበቅ አቅቶት አጋር ከተባለች ግብፃዊት ገረዱ እስማኤልን ወልዷል። «እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፥ ከእርስዋ ትወልድ ዘንድ ወደ አገልጋዬ ሂድ።» ብላ ያሰናበተችው ደግሞ ሣራ ናት። ዘፍ ፲፮፥፩-፲፭። ይሁን እንጂ በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴ ድንኳኑ ድረስ በመምጣት «የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፥ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች፤» ብለውታል። ዘፍ ፲፰-፲ ሣራም ከማርጀቷ የተነሣ እውነት እውነት አልመስላት ብሎ «እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል፤» ብላ በልቧ አሰበች። ልብ ያሰበውን፥ ኲላሊት ያጤሰውን የሚያውቁ ሥላሴም፦ «ሣራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት? እስከዛሬ ገና ነኝን? በእውነትስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅቷል ብላ። እነሆ፥ እንደዛሬው ወደአንተ እመለሳለሁ፥ ሣራም ልጅን ታገኛለች።» አሉ። ዘፍ ፲፰፥፩-፲፬። ሥላሴ እንደተናገሩት ሣራን ጎበኟት፥ ለአብርሃምም ወንድ ልጅን ወለደችለት፥ ስሙንም ይስሐቅ ብሎ ጠራው። ዘፍ ፳፮፥፩-፫። የይስሐቅ ሚስት ርብቃም መካን ስለነበረች ፈጥና አልወለደችለትም ነበር። «ይስሐቅም ስለ ሚስቱ ስለ ርብቃ እግዚአብ ሔርን ለመነ፥ መካን ነበረችና፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ሚስቱ ርብቃም ፀነሰች። ልጆችዋም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤» ይላል። የምትወልድበትም ወራት ሲፈጸም መልኩ እንደ ጽጌሬዳ ቀይ፥ መላ አካሉም ፀጉራም የሆነውን ዔሳውንና የወንድሙን ተረከዝ ይዞ ከማኅፀን የወጣውን ያዕቆብን በአንድ ጊዜ ወለደች። ዘፍ ፳፭፥፲፱-፳፮። እግዚአብሔር አንድ ሲለምኑት ሁለት ስለጥቂት ነገር ደጅ ሲጠኑት ብዙ መስጠት ያውቅበታል።
          የያዕቆብ ሚስት ራሔልም ለአያሌ ዓመታት መካን ሆና ኖራለች። ያዕቆብ እርስዋን ለማግኘት አሥራ አራት ዓመታት ለላባ በእረኝነት ተገዝቶአል። ዘፍ ፳፱፥፩-፴። እግዚአብሔር ደግሞ በአባቷ በላባ በያዕቆብም የተገፋችውን ልያን አሰባት። እነርሱ የጠሏትን እርሱ ወደዳት። እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን በአየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፥ ራሔል ግን መካን ነበረች። ልያም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች። «እግዚአብሔር መዋረዴን አይቶአልና፥ እንግዲህስ ባሌ ይወድደኛል ስትል ስሙን ሮቤል አለችው። ሁለተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት። «እኔ እንደተጠላሁ እግዚአብሔር ስለሰማ ይህን ጨመረልኝ፤» ስትል ስሙን ስምዖን ብላ ጠራችው። ሦስተኛም ወለደች፥ «ከእንግዲህ ወዲህስ ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል፥ ሦስት ወንድ ልጆችን ወልጄለታለሁና፤» ስትል ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው። አራተኛም ወለደች፥ «እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤» ስትል ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። ዘፍ ፳፱፥፴፩-፴፭። በዚህም ምክንያት መካኗ ራሔል በእኅቷ ላይ ቀናችባት፥ ያዕቆብንም፦ «ልጅ ስጠኝ፥ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ፤» አለችው። ያዕቆብም፦ «የማኅፀንሽን ፍሬ የምከለክልሽ እኔ እንደ እግዚአብሔር ነኝን?» ብሎ ተቈጣት። እርስዋ ግን በእልህ ከገረዶቿ ከባላ እና ከዘለፋ ዳንን፣ ንፍታሌምን፣ ጋድን፣ እና አሴርን እንዲወልድ አደረገችው። ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር የልያን ጸሎት ሰምቶ እንደገና ፀነሰች፥ አምስተኛ ወንድ ልጅም ወለደች። «የልጄን እንኮይ ለራሔል አሳልፌ ስለሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ፤» ስትል ስሙን ይሳኮር ብላ ጠራችው። ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ «እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፥ እንግዲህስ ከዛሬ ጀምሮ ባሌ ይወድደኛል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና፤» ስትል ስሙን ዛብሎን ብላ ጠራችው። በመጨረሻም ሰባተኛ ሴት ልጅ ወልዳ ስሟን ዲና አለቻት። እግዚአብሔር ቸርነቱ ብዙ በመሆኑ መካኒቱን ራሔልንም አሰባት። ልመናዋን ተቀብሎ ማኅፀንዋን ከፈተላት፥ ለያዕቆብም ወንድ ልጅ ወለደችለትና «እግዚአብሔር ሽሙጤን ከእኔ አስወገደልኝ፤» አለች። «እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ፤» ስትልም ዮሴፍ ብላ ጠራችው። ዘፍ ፴፥፩-፳፬። እንደተመኘችውም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ፀነሰች፥ መውለጃዋ ሲደርስም በምጥ ተጨነቀች፥ አዋላጂቱም «አትፍሪ ይኸኛው ደግም ወንድ ልጅ ይሆንልሻልና፤» አለቻት። ምጥ ስለበረታባትም ነፍስዋ ልትወጣ ደረሰች፥ ሞትዋ በእርሱ ሆኖአልና «የጭንቀቴ ልጅ ነው፤» ስትል ስሙን ቤንኦኒ ብላው ሞተች። አባቱ ያዕቆብ ግን «የቀኝ እጄ ልጅ ነው፤» ሲል ስሙን ብንያም ብሎ ለወጠው። ዘፍ ፴፭፥፲፮-፲፰።
          የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐናም ለብዙ ዘመን መካን ነበረች። እግዚአብሔርም ማኅፀኗን ዘግቶት ነበርና። እንደ መከራዋና እንደ ሃዘንዋም እግዚአብሔር ልጅ አልሰጣትም ነበር። ስለዚህም ታዝን ነበር። ከዚህም የተነሣ ትበሳጭና ታለቅስ ነበር። እህልም አትበላም ነበር። ባለቤቷ ሕልቃና ሊያጽናናት ቢሞክርም አልተሳካለትም ነበር። ሐና ግን በሴሎ በእግዚብሔር ፊት ቆማ ከልቧ አለቀሰች፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየች። እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጣት መልሳ ለእግዚአብሔር እንደምትሰጠው ስዕለት ተሳለች። ጸሎቷን በእግዚብሔር ፊት ባበዛች ጊዜም ካህኑ ዔሊ የሰከረች መስሎት ነበር። ሐዘኗንና ጭንቀቷን ካስረዳችው በኋላ ግን «በሰላም ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ ከአንቺ ጋር ይሁን፥ የለመንሽውን ልመና ሁሉ ይስጥሽ፤» ብሎ መረቃት። ጊዜው ሲደርስም ነቢዩ ሳሙኤልን ወልዳ በካህኑ በዔሊ እጅ ለእግዚአብሔር አስረከበች። «መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው መውለድ አልቻለችም፤» ብላም ዘመረች። ፩ኛ ሳሙ ምዕ ፩ እና ምዕ ፪።  
          የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ በመሥራታቸው፥ ለአርባ ዓመታት ያህል ለፍልስጥኤማውያን ተላልፈው በተሰጡበት ዘመን፥ ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ሚስቱም መካን ነበረችና ልጅ አልወለደችለትም ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ «እነሆ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፥ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤» አላት። ሴቲቱም ከመልአኩ የሰማችውን ሁሉ ለባልዋ ነገረችው። ማኑሄም መልአኩ ወደ እርሱ ዳግመኛ እንዲመጣ እግዚአብሔርን ለመነ። መልአኩም ዳግመኛ ለሴቲቱ በተገለጠ ጊዜ ማኑሄን ጠርታ እርስዋ የሰማችውን እርሱም እንዲሰማ አድርጋለች። ጊዜው ሲደርስም ወንድ ልጅ ወልዳ ስሙን ሶምሶን ብላ ጠራችው። መሳ ፲፫፥፩-፳፬።
          ከሚስቱ ከኤልሳቤጥ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ የነበረው ካህኑ ዘካርያስም ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ መካን ነበረች። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፥ በእግዚአብሔር ሥርዓትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ። ሁለቱም አርጅተው ዘመናቸው አልፎ ነበር። ጻድቁ ካህን በእግዚአብሔር ፊት (በቤተ መቅደስ) የክህነትን ሥራ በሚሠራበት፥ የዕጣን መሥዋዕት በሚያሳርግበት ጊዜ፥ በዕጣን መሠዊያው በስተቀኝ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት። በቀኝ መገለጡም ከግራ ወደ ቀኝ (ከሲኦል ወደ ገነት) የምትመለሱበት ጊዜ ደርሷል ሲለው ነው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ረዓድም ወረደበት። መደንገጥ የኅሊና፥ መፍራት የልቡና፥ መንቀጥቀጥ የጉልበት ነው። መልአኩም፦ «ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአልና፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ሐሴትም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ አይጠጣም፥ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል። ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል። እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓድያንንም አሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልሰ ዘንድ፥ ሕዝብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ፥ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።» አለው። ዘካርያስም «ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅቻለሁ የሚስቴም ዘመኗ አልፏል።» አለ። መልአኩም መልሶ «እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ። አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኸኝምና ይህ እስኪሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፥ መናገርም ይሳንሃል።» አለው። እንዲሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያመላከታቸው ኖረ። ከዚህም በኋላ የማገልገሉ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ። ሚስቱ ኤልሳቤጥም ፀነሰች፥ ፅንስዋንም ለአምስት ወራት ሸሸገች። ጊዜው ሲደርስ መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን ወለደች። ሉቃ ፩፥፭-፳፬፣ ፶፯።
          ልጅ መውለድ የእግዚአብሔር ትእዛዝ፥ የእግዚአብሔር በረከት ነው። «እግዚአብሔርም ሰውን በእግዚአብሔር አምሳል ፈጠረው። ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት አላቸው።» ይላል። ዘፍ ፩፥፳፯-፳፰። በመሆኑም ልጆች የእግዚአብሔር ጸጋ ናቸው። ይህም ይታወቅ ዘንድ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ «እነሆ፥ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፥ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው።» ብሏል። መዝ ፩፻፳፮፥፫። ጻድቃኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ሌሎችም ልጅ ለመውለድ መላ ዘመናቸው የጸለዩት ለዚህ ነው። የተወለዱትንም ልጆች እግዚአብሔር ይባርካቸዋል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፦ «ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፥ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉት ናትና።» በማለት በአንብሮተ ዕድ (እጅን በመጫን) ባርኰአቸዋል። ማቴ ፲፱፥፲፫-፲፭። ከመወለዳቸውም በፊት ገና በማኅፀን እያሉም እግዚአብሔር ይቀድሳቸዋል። ለዚህም ነው፥ ነቢዩ ኤርምያስን፦ «በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፤» ያለው። ኤር ፩፥፬። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስም «ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል፤» ተብሎለታል። ሉቃ ፩፥፲፭።
          መካንነት በትዳር ውስጥ ፈተና እንደሆነ ሁሉ ደጋግሞ ልጆችን መውለድም ፈተና ሆኗል። «አሁንም አረገዝሽ? ለምን አትጠነቀቂም?» ብሎ የሚቆጣ ባል አለ። «ተው እያልኩህ ይኸው ደስ ይበልህ፥ የወር አበባዬ ቀረ» ብላ የምትቆጣ ሚስትም አለች። «እናስወርድ፥ አናስወርድ፤» ጠብ ይነሣል፥ ወይም ተስማምቶ በማስወረድ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ይመጣል። አንዳንድ ቤተሰብም «ልጅ በመውለድ ለምን ትጎጂያለሽ? ምን በወጣሽ?» ይላል። በወንዱም በኲል «አንድ ወይም ሁለት ከተወለደ መች አነሰ? እርሷ ምንቸገራት?» ይባላል። እየመሰለን ነው እንጂ፥ «እናቱ ወንዝ የወረደችበትም የሞተችበትም እኲል ያላቅሳሉ፤» እንዲል ጥቂት የወለዱም ብዙ የወለዱም እኲል ነው የሚያማርሩት። መፍትሔው እግዚአብሔር የሰጠንን ያህል በጸጋ ተቀብለን እነርሱን ለማሳደግ በገድል ብንቀጠቀጥ እግዚአብሔር በሁሉ ይረዳናል። ድሃይቱ ሴት ባሏ በሞተባት ዘመን ባለዕዳ መጥቶ ልጆቿን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስድባት ባለ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ዕዳውን የምትከፍልበትንና ልጆቿን የምታሳድግበት በረከት በነቢዩ በኤልሳዕ አማላጅነት ሰጥቶአታል። ፪ኛ ነገ ፬፥፩-፯። እምነታችን ደካማ ከሆነብን ደግሞ በተፈጥሮ ፅንስ የሚይዝበትና የማይዝበት ጊዜ ስላለ ራስን በመግዛት መቆጣጠር ነው። ከዚህ አልፈን በተጥባበ ነገር መጓዝ ከክርስትና ሕይወት ውጪ ያደርገናል።
          መካንነት እና ወላድነትን በተመለከተ ሰውነታችንን መርምረን የምንደርስበት የጋራ ነጥብ አለን። እርሱም፥ ሁላችንም እኲል የማማረራችን ጉዳይ ነው። መካኖች ባለመውለዳችን ከመጠን በላይ እናማርራለን፥ የወለድንም በልጆቻችን እናማርራለን። ለመሆኑ መካኖች እግዚአብሔር ልጅ በልጅ ቢያደርገን እናመስግን ይሆን? ታዲያ ወላዶች ለምን አናመሰግንም? ላለመውለድ ለምን መድኃኒት እንጠቀማለን? ሲፀነስስ ለምን እናስወርዳለን፥ በአራርቆ መውለድ ሰበብስ ለምን መከራ እናያለን? የወለድናቸውን ልጆች ለማሳደግና ለማስተማር አቅቶን፥ ካደጉም በኋላ እንደፍላጐታችን አልሆንልን ብለው፥ «ከዚህ ሁሉ ምነው መካን ሆነን በቀረን ኖሮ፤» ለምን እንላለን? እንደቃላችን መካን ሆነንስ ቢሆን ኖሮ እናመሰግነው ነበር? ታዲያ መካኖች ለምን አላመሰገኑትም? ባለመውለዳቸው ለምን ዕድሜ ልካቸውን ያዝናሉ?
          እንግዲህ በክርስትና ሕይወት የምንኖር ሰዎች መካንነትንም ሆነ ወላድነትን በጸጋ ተቀብለን እግዚአብሔርን ልናመሰግነው ይገባል። የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐና፦ «እግዚአብሔር ደሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል።» እንዳለች፥ የልጅ ደሀ ቢያደርገንም፥ የልጅ ባለጠጋ ቢያደርገንም፥ ሁሉም ከእርሱ ነው ብለን በምስጋና መኖር ነው። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፯። መካንነትና ወላድነት የጽድቅ ወይም የኃጢአት መመዘኛ አይደለም። ጻድቃንም ኃጥአንም ይወልዳሉ ይዋለዳሉ፥ በአንፃሩም ከጻድቃንም ከኃጥአንም መካንነት ይኖራል። «እርሱ ለክፉዎችና ለደጋጎች ፀሐይን ያወጣልና፥ ለጻድቃንና ለኃጥአንም ዝናምን ያዘንማልና።» ይላል። ማቴ ፭፥፵፬። እርግጥ የሳኦል ልጅ ሜልኮል፥ በታቦተ እግዚአብሔር ፊት ከተርታው ሕዝብ ጋር ተሰልፎ የዘመረውን ንጉሥ ዳዊትን በማሽማጠጧ፥ እግዚአብሔር እስከመጨረሻው እንዳትወልድ ማኅፀኗን ዘግቶታል። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፳፫። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለሣራ ሊበቀል የጌራራውን ንጉሥ የአቤሜሌክን ሚስት፥ ሴቶች ልጆቹን፥ በቤቱ ውስጥ ያሉትን ሴቶች አገልጋዮቹን፥ ሁሉ ማኅፀን ዘግቶት ነበር። ዘፍ ፳፥፩-፲፰። አሁን ግን እንዳይወለድ ማኅፀንን እየዘጋን ያለነው እኛው ነን። በሌላ በኲል ደግሞ ብዙ ክፉ ሰዎች ሲወልዱ እናያለን። «ለምን?» የሚል ጥያቄ በአእምሮአችን ቢያስነሣም የእግዚአብሔር ፍርድ ስለማይመረመር ለእርሱ መተው ነው። «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት፥ እንዴት ጥልቅ ነው! ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፤ ፍርዱንም የሚያውቀው የለም።» ይላል። ሮሜ ፲፩፥፴፫። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን።  

16 comments:

 1. qale hiywet yasemaln

  ReplyDelete
 2. kele hiwet yesmalna

  ReplyDelete
 3. sintayehu (italy)

  ቃለ ህይወት ያሰማለን ለአባታችን ለቀሲስ ደጀኔ እጅግ ግሩምና ድንቅ የህይወት መነጽር ነው።

  "መካንነትና ወላድነት የጽድቅ ወይም የኃጢአት መመዘኛ አይደለም። ጻድቃንም ኃጥአንም ይወልዳሉ ይዋለዳሉ፥ በአንፃሩም ከጻድቃንም ከኃጥአንም መካንነት ይኖራል።"

  ReplyDelete
  Replies
  1. kele hiwet yasemalen mengeste semyen yawerslen amen

   Delete
 4. Be tedar wust sostum alamawoch baysakus mefatat ayshalem? Min telaleh kesis, be tidar lay lela mafkerens endet tayawaleh?

  ReplyDelete
 5. "መካንነት እና ወላድነትን በተመለከተ ሰውነታችንን መርምረን የምንደርስበት የጋራ ነጥብ አለን። እርሱም፥ ሁላችንም እኲል የማማረራችን ጉዳይ ነው። መካኖች ባለመውለዳችን ከመጠን በላይ እናማርራለን፥ የወለድንም በልጆቻችን እናማርራለን። ለመሆኑ መካኖች እግዚአብሔር ልጅ በልጅ ቢያደርገን እናመስግን ይሆን? ታዲያ ወላዶች ለምን አናመሰግንም? ላለመውለድ ለምን መድኃኒት እንጠቀማለን? ሲፀነስስ ለምን እናስወርዳለን፥ በአራርቆ መውለድ ሰበብስ ለምን መከራ እናያለን? የወለድናቸውን ልጆች ለማሳደግና ለማስተማር አቅቶን፥ ካደጉም በኋላ እንደፍላጐታችን አልሆንልን ብለው፥ «ከዚህ ሁሉ ምነው መካን ሆነን በቀረን ኖሮ፤» ለምን እንላለን? እንደቃላችን መካን ሆነንስ ቢሆን ኖሮ እናመሰግነው ነበር? ታዲያ መካኖች ለምን አላመሰገኑትም? ባለመውለዳቸው ለምን ዕድሜ ልካቸውን ያዝናሉ?"

  Kesis, Kale hiwot yasemalin. Egziabiher be-edime betsega yitebikilin.

  ReplyDelete
 6. Abataching Kale hiwot yasemalen. Please continue writing. I am always eager to read your new posts. Egziabher yistelen

  ReplyDelete
 7. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ጸጋውን ያብዛሎት።
  ቤተሰቦን ይባርክ።

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  ReplyDelete
 8. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን እድሜና ጤና ጸጋ በረከቱን ያብዛሎት አሜን!!!

  ReplyDelete
 9. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ጸጋውን ያብዛሎት።ለኛም ይህን ምክርዎን ሰምተን የምናገናዝብበት ህልና ይስጠን::

  ReplyDelete
 10. ቃለ ህይወት ያሰማለን

  ReplyDelete
 11. ቃለ ሕይወት ያሰማልን::

  ReplyDelete
 12. ቃለ ህይወት ያሰማልን ቀሲስ፡፡ ዛሬ ለብዙ ጋብቻ መፍረስ ምክንያት እየሆነ ያለው እንዲህ ያለ ቀናነት ያለመኖርና እግዚአብሔርን በተስፋ ያለመጠበቅ ችግር ነው፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡

  ReplyDelete
 13. kale hiwot yasemalen

  ReplyDelete
 14. Tiru new Sile minkusnam char btareg.....

  ReplyDelete
 15. kal hiwot yasemalin beatm yemigerm timirt new bezarew ken enenu siyasechenikegne leneberhu negr new melse yagegnehut .

  ReplyDelete