Saturday, November 12, 2011

«ሰው የለኝም፤» ዮሐ ፭፥፯

«ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፤» እንዲል፥ ምድር በሰው ተሞልታ ሳለ ሰው ማጣት ከባድ ነው። ከሰው ተፈጥረው በሰው መካከል እየኖሩ ሰው አልባ መሆን ተስፋ አስቆራጭ ነው። ይህ ክፉ ዓለም ኤልያስን ያህል ታላቅ ነቢይ እንኳ ተስፋ አስቆርጦ፥ «ሁሉን ለሚገዛ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእሥራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፥ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ።» በማለት ደጋግሞ ለእግዚአብሔር እንዲናገር አድርጐታል። እግዚአብሔር ግን፦ «እኔም ከእሥራኤል ጉልበታቸውን ለበዓል (በዓል ለተባለው፥ ጣኦት) ያላንበረከኩትን ሁሉ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ።» ብሎ በአምላካዊ ቃሉ አጽናንቶታል። ፩ኛ ነገ ፲፱፥፱-፲፰። በዘመናችንስ ለበዓል ያልተንበረከክን ስንት አባቶች፥ ስንትስ ምእመናን እንገኝ ይሆን? የዘመናችን በዓል፦ ገንዘብ፥ ሥልጣን እና ዘር ነው። ምክንያቱም በሀገር ቤትም ሆነ በውጪው ዓለም ያለው ኹኔታ ሲታይ የቀረ ሰው ያለ አይመስልምና ነው። ነቢዩ ዳዊትም፦ «አቤቱ ደግ ስው አልቆአልና አድነኝ።» ያለው። ይኽንን የመሠለ ችግር ስላጋጠመው ነው።
          «ሰው የለኝም፤» በማለት በተሟጠጠ ተስፋ የተናገረው መጻጉዕ ነው። «ወእምድኅረዝ ኮነ በበዓሎሙ ለአይሁድ፥ ዓርገ እግዚእ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም፤ ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፥ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።» ይላል። አይሁድ በትእዛዝ፥ በአዋጅ፥ የሚያከብሯቸው ሰባት በዓላት አሏቸው። እነርሱም፦ የሰንበት በዓል፣ የቂጣ በዓል፣ የመከር በዓል፣ የዳስ በዓል፣ መለከቶች የሚነፉበት ቀን፣ የማስተስረያ ቀን፣ እና ፉሪም ናቸው። ዘሌ ፳፫፥፪፣ ዘጸ ፲፪፥፩-፳፣ ዘጸ ፳፫፥፮፣ ዘሌ ፳፫፥፴፱፣ ዘኁ ፳፱፥፩፣ ዘሌ ፳፫፥፳፮፣ አስ ፱፥፲፮። የመቅደስ መታደስ መታሰቢያ በዓል ስምንተኛ ሆኖ የተጨመረው ከኦሪትና ከነቢያት በኋላ በመቃብያን ዘመን ነው። ዮሐ ፲፥፳፫።
          በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ አንዲት መጠመቂያ ነበረች፥ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ ይሏታል፥ ትርጉሙም ቤተ ሣሕል (የምሕረት ቤት) ማለት ነው። አምስት እርከኖች (መደቦች፥ ደረጃዎች) ነበሯት። እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር (የምሥጢረ ሥላሴ፥ የምሥጢረ ሥጋዌ፥ የምሥጢረ ጥምቀት፥ የምሥጢረ ቊርባን፥ የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን) ምሳሌዎች ናቸው። እነርሱም መሠረታውያን የሃይማኖት ትምህርቶች ናቸው። በአምስቱ እርከኖች ላይ አምስት ዓይነት በሽተኞች ፩ኛ፦ ዕውራን ፪ኛ፦ አንካሶች ፫ኛ፦ የሰለሉ ፬ኛ ልምሾ የሆኑ ፭ኛ የተድበለበሉ ሰዎች ተኝተው ፈውስን ይጠባበቁ ነበር። እነዚህም የአምስቱ ፆታ ምዕመናን፦ የአዕሩግ፥ የወራዙት፥ የአንስት፥ የካህናት እና የመነኰሳት ምሳሌዎች ናቸው። የአዕሩግ በሽታቸው ፍቅረ ንዋይ ነው፥ የወራዙት (የወጣቶች) በሽታቸው ዝሙት ነው፥ የአንስት (የሴቶች) በሽታቸው ትውዝፍት (የምንዝር ጌጥ) ነው፥ የካህናት በሽታቸው ትዕቢት ነው፥ (አእምሮአችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ ነው ይላሉ)፥ የመነኰሳት በሽታቸው ስስት ነው። እነዚያ በጠበል ተጠምቀው ይፈወሳሉ፤ እነዚህ ደግሞ፦ በፍቅረ ንዋይ፥ በዝሙት፥ በትውዝፍት፥ በትዕቢት፥ በስስት የሚፈትናቸውን ሰይጣን በጥምቀት ባገኙት ኃይል ድል ይነሡታል። ኃይላቸውን በኃጢአትና በበደል አድክመው የሚሸነፉም አሉ።
          በቤተ ሳይዳ፦ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ፥ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ማንኛውም በሽተኛ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበር። መልአኩ ከሰማይ የሚወርደው ውኃውን ለመቀደስ፥ የሚሠዋውን መሥዋዕት ለማሳረግ ነበር። በየሳምንቱ ቅዳሜ፣ ቅዳሜ፥ አንድ፣ አንድ በሽተኛ ይፈወስ ነበር። ይህም የማይቀር የማይደገምም ነበር። አንድ በሽተኛ ሳይፈወስ የማይቀርበት ምክንያት፦ «ተአምራት በአባቶቻችን ዘመን ይደረግ ነበር፥ በእኛ ዘመን ግን ቀረ፤» ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ ነው። አለመደገሙ ደግሞ በዘመነ ኦሪት ፍጹም የሆነ ድኅነት አለመሰጠቱን (አለመገኘቱን) ያጠይቃል። ቤተሳይዳ የቤተክርስቲያን፥ መልአኩ ደግሞ የቀሳውስት ምሳሌዎች ናቸው።
«ልትድን ትወዳለህን?» ዮሐ ፭፥፮
          ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው ድውይ በዚያ ነበረ። ደዌ ጸንቶበታል፥ ዘግይቶበታልም። ጌታም በደዌ ዳኛ በአልጋ ቊራኛ ተይዞ ብዙ እንደቆየ ስለሚያውቅ «ልትድን ትወዳለህን?» አለው። መዳን እንደሚፈልግ እያወቀ የጠየቀበት ምክንያት፦ አላዋቂ የነበረን ሥጋ እንደለበሰ (እንደተዋሐደ) ለማጠየቅ ነው። አንድም አስፈቅዶ ለመፈወስ ነው። ምክንያቱም፦ ሳያስፈቅድ ቢፈውሰው ኖሮ፥ በዕለተ ዓርብ በጥፊ መትቶት በሚመሰክርበት ጊዜ መጻጉዕ ምክንያት ያገኝ ነበር። ይኸውም፦ «ምነው ያዳነህን?» ሲባል፥ «በቀለብላባነቱ አዳነኝ እንጂ መች አድነኝ ብዬ ለመንኩት፤» ይል ነበርና ነው። መጻጉዕ ለተጠየቀው ጥያቄ፦ «ውኃው በተናወጠ ጊዜ ከመጠመቂያው አውርዶ የሚያስጠምቀኝ የለም እንጂ መዳንስ እወድ ነበር፥ እኔ በመጣሁ ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይጠመቃል፤» ሲል መለሰ። እንዲህም ማለቱ ስለ ሁለት ነገር ነው። ፩ኛ፦ ይህ የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ ጉልበት ስላለው ወደ ጠበሉ አውርዶ ያስጠምቀኛል ብሎ ነው። ፪ኛ፦ ከተከታዮቹ መካከል አንዱን ጉልበታም ሊያዝልኝም ይችላል ብሎ ነው። እኛስ ለመዳን እንወዳለን? ይኽንን ጥያቄ መመለስ ያለብን ዛሬ ነው። ምክንያቱም የመዳን ቀን ዛሬ፥ የተወደደም ሰዓት አሁን ነውና። መፍትሔውም ኃጢአት እንቅፋት እንዳይሆንብን ከኃጢአታችን መመለስ፥ የበደልነውንም በደል ሁሉ ከእኛ ቆርጠን መጣል ነው። ሕዝ ፲፰፥፴-፴፩።
«ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤» ዮሐ ፭፥፰
          ጌታችን አምላካችን መዽኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጻጉዕን የመዳን ፍላጐት እንዳለው አውቆ፦ «ተነሥተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤» አለው። ጌታ በማዳኑ ጸጸት የለበትም፥ ያዳነው ወደፊት እንደሚበድለው እያወቀ ነው። በዚህም መልካም  ለሚያስቡልን ብቻ ሳይሆን ክፉ ለሚያስቡብንም መልካም መሥራትን አስተምሮናል። ያም ሰው ፈጥኖ ተነሥቶ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ። ዕለቱ ቅዳሜ በመሆኑ በአካባቢው የነበሩ አይሁድ «በሰንበት አልጋህን ተሸክመህ ልትሄድ አይገባህም፤» አሉት። ይኸውም፦ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፤ በኢየሩሳሌምም በሮች አታግቡ፥ ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፤ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፤ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ፤» የሚለውን ይዘው ነው። ኤር ፲፯፥፳፫። የሰንበትን ቀን የባረከና የቀደሰ እግዚአብሔር ነው። «ሰማይና ምድር ዓለማቸውም ሁሉ ተፈጸሙ። እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በስድስተኛው ቀን (ዓርብ) ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ። (ፍጡር ደክሞት እንደሚያርፍ እርሱም በባሕርዩ ድካም ኖሮበት ዐረፈ ማለት አይደለም፥ ሊሠራው ያሰበውን አከናወነ፥ ፈጸመ ማለት ነው)። እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ባረካት ቀደሳትም፤ ሊፈጥረው ከጀመረው ሥራ ሁሉ በእርስዋ ዐርፎአልና፤» ይላል። ዘፍ ፪፥፩-፫። ከዐሠርቱ ትዕዛዛትም አንዱ፦ «የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን ለእግዚአብሔር ሰንበት ናት፤» ካለ በኋላ ሰውም ሆነ እንስሳ በዚያች ቀን ምንም ሥራ እንዳይሠሩ ያዛል። ዘጸ ፳፥፰-፲፩።
          በአዲስ ኪዳን፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኲራብ በሚያስተምርበት ጊዜ፥ እጁ የሰለለች ሰው በዚያ ነበረ። ይከሱትም ዘንድ «በሰንበት መፈወስ ተፈቅዷልን?» አሉት፤ ይኸውም «አይገባም፤» ቢላቸው «የእግዚአብሔር ወገን ነኝ እያለ የሰው ስቃይ አያሳዝነውም፤» ለማለት ነው። «ይገባል፤» ቢላቸው ደግሞ «የሙሴን ሕግ አፈረሰ  ብለን እንጣላዋለን፤» ብለው ነው። እርሱ ግን «ከእናንተ አንድ በግ ያለው ሰው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት ይዞ የማያወጣው ማነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንዴት አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዷል፤» አላቸው። ሰውየውንም «እጅህን ዘርጋ፤» ብሎ አድኖታል። ፈሪሳውያን ግን እንዴት እንዲያጠፉት ተማከሩ፥ ይላል። ማቴ ፲፪፥፱። ተርበው የነበሩ የጌታ ደቀመዛሙርትም በሰንበት እሸት ቀጥፈው በበሉ ጊዜም ያለ ክስ ሥራ የሌላቸው አይሁድ ከስሰዋቸው ነበር። ጌታ ግን፦ «እርሱ በተራበ ጊዜ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ ዳዊት ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደገባ፥ ከካህናትም ብቻ በቀር እርሱ ሊበላው የማይገባውን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሊበሉት የማይገባቸውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደበላ አላነበባችሁምን? በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ካህናት (በመንፈሳዊ አገልግሎት ምክንያት) ሰንበትን እንደሚሽሩ አላነበባችሁምን? እኔም ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ እዚህ እንዳለ እላችኋለሁ። (እነዚያ ለእኔ ምሳሌ የነበረውን ቤተ መቅደስ ሲያገለግሉ ነበር፥ እኔ ግን አማናዊው ቤተ መቅደስ ነኝ፤ ደግሞም ከምሳሌው አማናዊው ይበልጣል)። ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እመርጣለሁ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኖሮ ያልበደሉትን ባልፈረዳችሁባቸው ነበር። (በረሀብ አለንጋ ተገርፈው ይሙቱ ባላላችኋቸው ነበር፥ አንድም ምሳሌ የሆነውን ቤተ መቅደስ ሲያገለግሉ በአገልግሎቱ አስገዳጅነት ምክንያት ሰንበትን የሚሽሩ ካህናተ ኦሪት ኃጢአት ሆኖ ካልተቆጠረባቸው፥ አማናዊውን ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ የአዲስ ኪዳን ካህናት ሐዋርያት በሰንበት ምክንያት እንዴት ይኰነናሉ)። የሰንበት ጌታዋ (ፈጣሪዋ) የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) ነውና።» ብሎአቸዋል። ማቴ ፲፪፥፩-፰።
ጌታን እንኳ ከመክሰስ ወደ ኋላ ያላሉ አይሁድ መጻጉዕን ከመክሰስ ይቆጠባሉ ተብሎ አይታሰብም። «በሰንበት አልጋህን ተሸክመህ ልትሄድ አይገባህም፤» ያሉት ለዚህ ነው። እርሱ ግን «ያዳነኝ እርሱ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ፤» አላቸው። እነርሱም፦ «አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬ ማነው?» አሉት። «ያዳነህ መድኃኒት ማነው?» አላሉትም። ጌታ በዚያ ቦታ ባሉ በብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ስለነበር፥ መጻጉዕ ያዳነው ማን እንደሆነ አላወቀም። ይህ ቅሉ ስንፍና ነው፥ ምክንያቱም፦ እንኳን ይኽንን ያህል ታላቅ ተአምር የሠራለትን ቀርቶ ጥቂት የሠራለትን እንኳ ጠይቆ ማወቅ ነበረበት። ከዚህም በኋላ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያንን ያዳነውን ሰው በቤተመቅደስ አገኘውና፥ «እነሆ ድነሃል፤ ነገር ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ፤» ብሎታል። ይኸውም ዳግመኛ እንደሚበድል ስለሚያውቅ ነው። የመጀመሪያ በደሉ ለደዌ ሥጋ አሳልፎ እንደሰጠው፥ ሁለተኛ በደሉ ለደዌ ነፍስ አሳልፎ የሚሰጥ ነውና።
          መጻጉዕ ያዳነውን ጌታ በጥፊ በመምታት እስኪፈጽማት ድረስ በዚያው ዕለት መበደል ጀመረ። ወዲያውኑ ሂዶ ያደነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ለጌታ ጠላቶች ለአይሁድ ነገራቸው። ስለዚህም አይሁድ ጌታን ያጣሉት፥ ያሳጡት፥ ያካሰሱት ነበር፤ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። የቤተክርስቲያንም ዕድሏ እንደ ጌታ ነው። የእርሱ አካል በመሆኗ ከሳሾቿ ብዙዎች ናቸው፥ የምትከሰስበት ፋይልም ብዙ ነው። ክርስቶስን መስለው የተገኙ ቅዱሳንም እንዲሁ ናቸው፥ ከሳሾቻቸው በዝተዋል። አይሁድ በትንሣኤውና በዕርገቱ ባያሳፍራቸው ኖሮ ክፋታቸውን እስከ መስቀል ድረስ ገፍተውበት ነበር። ትንሣኤውንም ለማሳበል ብዙ ደክመዋል። ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተው፥ «ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ።» ብለዋል። ማቴ ፳፯፥፴፭፤ ፳፰፥፲፪። የክርስቶስ አካል ቤተክርስቲያንም ጠላቶቿ የሚታገሏት አይሆንም እንጂ እስክትጠፋ ድረስ ነው። ነገር ግን «እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት (መሠረት) ነህ፥ በዚያች ዐለት (መሠረት) ላይም ቤተክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም (የሲኦል በር ጠባቂ አጋንንት) አይበረታቱባትም።» እንደተባለ አይችሉአትም። ማቴ ፲፮፥፲፰።
ደዌ በአራት ምክንያት ይመጣል፤
፩ኛ፦ ደዌ ዘንጽሕ፤ ይህ እንደ ጢሞቴዎስ ነው። እነ ዴማስ ሆዳችን ይሙላ፥ ደረታችንም ይቅላ ብለው ወደ ተሰሎንቄ ሲኰበልሉ ጢሞቴዎስ ግን ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳይል የክርስቶስ አገልጋይ ሆኖ መምሕሩን ቅዱስ ጳውሎስን  እስከመጨረሻው ተከትሎታል። ፪ኛ ጢሞ ፬፥፱። ለሊቀጵጵስናም በቅቷል። ጢሞቴዎስ የነበረበት ደዌ የሆድ ሕመም ነበር። በዚህም ምክንያትም መምሕሩ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ስለ ሆድህ በሽታና ስለ ዘወትር ደዌህ ጥቂት ወይን ጨምር እንጂ ውኃ ብቻ አትጠጣ።» ሲል ጽፎለታል። ፩ኛ ጢሞ ፭፥፳፫።
፪ኛ፦ ደዌ ዘዕሴት፤ ይህ እንደ ኢዮብ ነው። ሰይጣን ኢዮብን ለመክሰስ ዳግመኛ በእግዚአብሔር ፊት በቆመ ጊዜ፥ እግዚአብሔር፦ «ከባሪያዬ በኢዮብ ላይ እንዲህ እንዳታስብ ተጠንቀቅ፤ በምድር ላይ እንደ እርሱ ያለ ገር፥ ጻድቅና ንጹሕ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ከክፋትም ሁሉ የራቀ፥ ዳግመኛም ቅን የሆነ ሰው የለምና፤ እንተ ግን ሀብቱን በከንቱ አጠፋ ዘንድ ነገርኸኝ።» አለው። ሰይጣንም መልሶ ለእግዚአብሔር፥ «ቊርበት ስለ ቊርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል።ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል፤» ብሎ መለሰ። የኢዮብን ጽናት የሚያውቅ እግዚአብሔርም፦ «እነሆ ሥጋውንና አጥንቱን በእጅህ ሰጠሁህ። ነገር ግን ሕይወቱን ተው።» ብሎ አሰናብቶታል። ሰይጣንም  ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፣ ኢዮብንም ከእግሩ ጀምሮ  እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው ። ኢዮ ፪፣፩-፯።
      ፫ኛ፣ደዌ ዘመቅሠፍት፤ ይህ እንደ ሳኦል እንደ ሄሮድስ ነው፤ ንጉሡ  ሳኦል እግዚአብሔርን  ከመከተል ወደ ኋላ በመመለሱ፥ «እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት  ተጸጸትሁ፤» ተባለ። እንዲህ ያለው በነቢዩ  በሳሙኤል እጅ ቀብቶ  ያነገሠው  እግዚአብሔር ነው። ይኽንን የእግዚአብሔር ቃል የሰማ ነቢይ ሳሙኤልም ንጉሡን ሳኦልን ጠርቶ የሰማውን  ሁሉ በዝርዝር ነገረው። በመጨረሻም «የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ። . . . እግዚአብሔር ከእስራኤል መንግሥትህን ዛሬ ከእጅህ ቀደዳት፤ ከአንተም ለሚሻል ለባልንጀራህ አሳልፎ ሰጣት፤ እስራኤል ለሁለት ይከፈላል፤ ከእንግዲህ አይሰበሰብም፤ እግዚአብሔር እንደሰው የሚጸጸት አይደለምና አይጸጸትም፤» አለው። ፩ኛሳሙ ፲፭፥፩-፴፩። የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉ መንፈስም ተቆራኝቶት የሚሰቃይ በሽተኛ ሆኗል። ፩ኛሳሙ ፲፮፥፲፬። ሄሮድስ ደግሞ ከ፵፩-፵፬   ዓ.ም. በይሁዳ ነግሧል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብን የገደለ፥ ቅዱስ ጴጥሮስንም ያሰረ እርሱ ነው። የሐዋ ፲፬፥፩-፭። መጽሐፍ ቅዱስ የሄሮድስን መጨረሻ ሲናገር፦ «ሄሮድስም በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ተቈጥቶ ነበር፤ በአንድነትም ወደ እርሱ መጥተው የንጉሡን ቢተወደድ በላስጦስን እንዲያስታርቃቸው ማለዱት፤ የሀገራቸው ምግብ ከንጉሥ ሄሮድስ ነበርና። ከዚህም በኋላ አንድ ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በአደባባይ ተገኝቶ ይፈርድ ጀመረ። ሕዝቡም፥ የእግዚአብሔር  ቃል ነው፥ የሰው አይደለም እያሉ ጮኹ። (እርሱ ግን የእኔ ቃል የእግዚአብሔር ቃል አይደለም ብሎ መቃወም ነበረበት)። ለእግዚአብሔርም ክብር ስለ አልሰጠ የእግዚአብሔር መልአክ ቀሠፈው፥ ተልቶም ሞተ፤» ይላል፤ የሐዋ ፲፪፥፳-፳፫።
          ፬ኛ፦ ደዌ ዘኃጢአት፤ ይህ እንደ መጻጉዕ ነው። ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ከአልጋ ጋር ያጣበቀው ደዌ የመጣበት በኃጢአቱ ምክንያት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለፈው ኃጢአትህ ለዚህ ደዌ ዳርጐህ ነበር፥ እንደማለት፦ «እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ፤» ያለው ለዚህ ነው።
          መጻጉዕ የሚረዳው ሰው አጥቶ በተቸገረ ጊዜ የደረሰለት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እኛም እንዲሁ ነን፤ ከሰዎች ጋር እየኖርን፥ ሰው አልወጣልን ብሎ፥ ሰው አጥተን የምንኖር ሰዎች ነን። እኛም ለሌላው ሰው መሆን አቅቶን ሰውን ሰው አልባ ያደረግን ሰዎች በመሆናችን ፍርዱ የጋራ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «ሁሉ ተካክሎ በአንድነት በደለ፥ አንድ ስንኳ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም።» ያለው ስለዚህ ነው። መዝ ፶፪፥፫። «ነገር ግን የሰው ልጆች ሁሉ ከንቱ ናቸው፥ የሰው ልጆችም ሐሰተኞች ናቸው፥ በሚዛንም ይበድላሉ፥ እነርሱስ በፍጹም ከንቱ ናቸው።» ያለበትም ጊዜ አለ። መዝ ፷፩፥፱። ኑሮአችን ሁሉ በሰው ቊስል እንጨት እየሰደድን፥ በቊስላችንም እንጨት እየሰደዱብን ነው። የልብ ሰው መሆን ባለመቻላችን ሰውን ችግር ላይ የሚጥል እንጂ ለችግር የሚደርስ አልተገኘም። «ኃጢአተኛ ወገንና ዐመፅ የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ በደለኞች ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ተዋችሁት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጣችሁት። እንግዲህ በበደል ላይ በደል እየጨመራችሁ ለምን ትቀሠፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕማም ፥ልብም ሁሉ ለኀዘን ሆኖአል። ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቊስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፤ አልተጠገነምም፤ በዘይትም አልለዘበም።» እንዲል ጤነኛ ሰው የለም። ኢሳ ፩፥፬-፮። እግር የተባሉ ተርታ ሰዎች ሲሆኑ ራስ የተባሉት ሥጋውያን ባለሥልጣኖች ናቸው። አንድም እግር የተባሉት ምእመናን ሲሆኑ ራስ የተባሉት ከታች እስከ ላይ በየማዕረጋቸው ያሉ መንፈሳዊያን ባለሥልጣኖች ናቸው። እነዚህም፦ «ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያስተማሩአችሁን ሁሉ አድርጉ፥ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እንደሚሠሩት አታድርጉ፤ የሚያስተምሩትን አይሠሩትምና። ትልቅና ከባድ ሸክም አስረው ሰውን በጫንቃው ላይ ያሸክሙታል፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።» የተባለባቸው ናቸው። ማቴ ፳፫፥፪-፬። በመሆኑም ቤተክርስቲያንም እየቆሰለች ነው።
          መጻጉዕ የቆሰለው በኃጢአቱ ምክንያት ነው። እናት ቤተክርስቲያን ግን ያለ ኃጢአቷ በውስጥ በአፍአ ቆስላ እየተሰቃየች ነው። ጠላቶቿ ሥጋዋን ጨርሰው አጥንቷን እየቆረጠሙ ነው። መናፍቃን እየተሸለሙባት እየተሾሙባት ነው። በልጆቿ መሥዋዕትነት የዮዲትን እና የግራኝ መሐመድን ዘመን ያለፈች ቤተክርስቲያን የወላድ መካን ሆና የሰው ያለህ እያለች ነው። እግዚአብሔር ሥራ የሚሠራው በሰው አድሮ ነውና። በመሆኑም ፈጣሪዋን «ሰው የለኝም፤» እያለችው ነው። ያለነውም ብንሆን ገና እንደሚገባ ሰው አልሆንላትም። ሰው የማያሰኝ ብዙ ጉድለት ብዙ ድካም አለብን። እንዲህም ሆኖ ተስፋ አንቆርጥም። ምክንያቱም ለነቢዩ ለኤልያስ እንደተነገረ፥ እናት ቤተክርስቲያን፦ ለመናፍቃን፥ ለሥልጣን፥ ለገንዘብ፥ ለዘር፥ ለፖለቲካ ያልተንበረከኩ፥ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው ሰባት ሺህ ነፍሳት አሉአት። ዮሴፍን ወንድሞቹ ሸጠውት ወደ ግብፅ ሲወርድ ሰው አልነበረውም፥ እግዚአብሔር ግን በጌታው በጲጥፋራ ቤት ከፍ ከፍ አደረገው። በጌታው ሚስት ተንኰል ወደ ወኅኒ ቤት በተወረወረ ጊዜም ሰው አልነበረውም፥ እግዚአብሔር ግን ከወኅኒ ቤት አውጥቶ በባዕድ ሀገር ገዥ አደረገው። ዘፍ ፴፱፥፩-፳፫፤ ፵፩፥፩-፶፯። ሙሴ በሕፃንነቱ ወንዝ ዳር ሲጣል ሰው አልነበረውም፥ እግዚአብሔር ግን ከተጣለበት አንሥቶ በፈርዖን ቤተ መንግሥት፥ የንጉሥ የልጅ ልጅ ተብሎ እንዲያድግ አደረገው። ዘጸ ፪፥፩-፲። ብላቴናው ዳዊት በኃያሉ በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜ ሰው አልነበረውም፥ ከወንጭፉ በስተቀር መሣሪያም አልነበረውም፥ እግዚአብሔር ግን ጐልያድን በአንዲት ጠጠር ግንባሩን ፈርክሶ ጣለለት። ፩ኛ ሳሙ ፲፯፥፵፭-፶፩። ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ ተማርከው ወደ ባቢሎን ሲወርዱ ሰው አልነበራቸውም፥ እግዚአብሔር ግን ጥበብን ሰጥቶ በባቢሎን ጠቢባን እና አውራጃዎች ላይ እንዲሾሙ አደረጋቸው። ዳን ፩ እና ፪፤ በሰዎች ተንኰል፥ ሠለስቱ ደቂቅ ወደ ዕቶነ እሳት፥ ዳንኤል ደግሞ ወደ አናብስት ጉድጓድ በተጣሉም ጊዜ ሰው አልነበራቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ቅዱስ ሚካኤልን እና ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ አዳናቸው። ዳን ፫፥፳፬፣ ፮፥፮። አልዓዛር በሞት ተይዞ፥ ተገንዞ፥ ወደ መቃብር በወረደ ጊዜ ሰው አልነበረውም፤ ጌታ ግን ከመቃብር አወጣው። ዮሐ ፲፩፥፴፰-፵፬። ቅዱስ ጴጥሮስ በሰንሰለት ታስሮ ወደ ጨለማው ወኅኒ ቤት ሲወረወር ሰው አልነበረውም፥ ጌታ ግን መልአኩን ልኰ ከወኅኒ ቤት አወጣው። የሐዋ ፲፪፥፩-፲፩። ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ወደ ወኅኒ ቤት ተወርውረው፥ ከግንድ ጋርም አጣብቀው ሲያስሯቸው ሰው አልነበራቸውም። በመንፈቀ ሌሊትም ይጸልዩ፥ እግዚአብሔርንም በዜማ ያመሰግኑ ነበር። ጌታም የእግር ብረቱን፥ የእጅ ሰንሰለቱን ፈትቶ፥ በሩንም ከፍቶ አውጥቶአቸዋል። የሐዋ ፲፮፥፲፮-፴። ስለዚህ፦ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት፥ እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።» እንዳለ፥ ቤተክርስቲያንም እንጀራዋን የሚበሉ ሰዎች ከጠላት ጋር ተሰልፈው ተረከዛቸውን ቢያነሡባትም በደሙ የመሠረታት ኢየሱስ ክርስቶስ ይታደጋታል። እኛም በዚህ ምክንያት ብዙ ሰው እናትን፥ አባትን፥ ወንድምን፥ እኅትን፥ ልጅን፥ የትዳር ጓደኛንም ልናጣ እንችላለን። በዚህን ጊዜ፦ «ለሰውም ጠላቶቹ ቤተሰቦቹ ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱንና እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ከእኔም ይልቅ ወንድ ልጁንና ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።» የሚለውን ማሰብ ነው። ማቴ ፲፥፴፮።

12 comments:

 1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 2. Awo Egziabher Yehunen. ቃለ ህይወት ያሰማልን Kesis.

  ReplyDelete
 3. ርብቃ ከጀርመንNovember 16, 2011 at 10:29 AM

  ቃለህይወት ያሰማልን ቀሲስ ደጀኔ ሰውማለትሰውማለት ሰውየሚሆን ሰውነው ሰውየጠፋለት ይልነበር አባቴ እውነትነው ቤተክርስቲያናችን ሰውአጥታለች ሰውየላትም እርሱ መድሀኒአለም ሰውአድርጎን ለቤተክርስቲያናችን በመከራዋሰአት አለን የምንልያድርገን !አሜን

  ReplyDelete
 4. ቃለ ህይወት ያሰማልን Kesis

  ReplyDelete
 5. እባካችሁ የጾለት አዋጅ ይታወጅ።
  ቃለ ህይወት ያሰማልን Kesis

  ReplyDelete
 6. Kesis Egziabhere yakberwot we need wongel LIKE This.Ebakwoten tell to Dr Efrem WE Don't need Politics on Deje selam.

  ReplyDelete
 7. Keise Yehetune! Kesis ebakewon kechalu PDF yaderegeulne, ena manbeb alechalkume.

  ReplyDelete
 8. Kal hiwote yiasemalen,yegeru marefia ,yemelekotu maderia yehonechwun kidist betechritstian esu erasu yitebeklin.

  ReplyDelete
 9. መድሀኒአለም ሰውአድርጎን ለቤተክርስቲያናችን በመከራዋሰአት አለን የምንልያድርገን !አሜን

  ReplyDelete
 10. abatachen edmana tana yestelen ewnataga abate aysatane ewnat kerstos nawna selewnat yamtgadalu abatochachen yakoyelene amane.

  ReplyDelete
 11. ቃለ ህይወት ያሰማልን Kesis
  መድሀኒአለም ሰው አድርጎን ለቤተክርስቲያናችን በመከራዋ ሰአት አለን የምንል ያድርገን
  !አሜን

  ReplyDelete
 12. Kesis, kale hiwot yasemalin. Amen!

  ReplyDelete