Wednesday, November 2, 2011

ነገረ ቅዱሳን ክፍል፦ ፲፭

፩፥፲፦ በእንተ ኢያሱ፤
ኢያሱ፦ የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ማለት ነው። ስሙ ከግብሩ የተስማማለት ሰው ነው። ከግብፅ የወጣው በብላ ቴናነቱ ቢሆንም በእምነት በሚሠራው ሥራ አዋቂ ከሚባሉ ሰዎች በላይ ነበር። ሙሴ ከአማሌቅ ጋር እንዲዋጋ አዝዞት አሸን ፏል። ዘጸ ፲፯፥፰-፲፫። በሙሴ እግር እስኪተካ ድረስ በፍጹም ትኅትና የሙሴ ሎሌ (አሽከር) ነበር። ዘጸ ፳፬፥፲፫፣ ፴፪፥፲፯፣ ፴፫፥፲፩፣ ዘኁ ፲፩፥፳፰። የከነዓንን አገር እንዲያዩ ከቃዴስ ከወጡት አሥራ ሁለት ሰላዮች መካከልም አንዱ እርሱ ነበር። እርሱና ካሌብ «እግዚአብሔር ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ያወርሰናል፤» ብለው በእምነት በመናገራቸው ከግብፅ ከወጡት ሕዝቦች መካከል እነርሱ ብቻ ምድሪቱን ወርሰዋል። ዘኁ ፲፫ እና ፲፬።
በሙሴ እግር የተተካ ይህንን ኢያሱን የመረጠ እግዚአብሔር ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ወደ ናባው ተራራ እንዲ ወጣ በዚያም እንደሚያርፍ እግዚአብሔር በነገረው ጊዜ፥ «የሥጋና የነፍስ ሁሉ አምላክ(የሥጋዊና የደማዊ ሁሉ ፈጣሪ) እግዚ አብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የሚሆነውን ሰው ይሹም፤ በፊታቸው የሚወጣውንና የሚገባውን፥ የሚያስወጣቸውንና የሚያስገ ባቸውንም፥ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን።» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፦ «መንፈስ ቅዱስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ በካህኑም በአልዓዛር ፊት አቁመው፤ በማኅበሩም ፊት እዘዘው፤ ስለ እርሱም በፊታቸው እዘዝ። (በካህኑ  በአልዓዛር ፊት ቁመው በእግዚአብሔር የሚናገረውን ፍርድ ይጠይቁት)። የእሥራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ ስጠው።» ብሎታል። በዚህም ስለ ኢያሱ መስክሮለታል። ዘኁ ፳፯፥፲፪-፳። ከዚህም ሌላ፦ «አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላቸዋል፤ ቃሌንም በአፉ አኖራለሁ፤ እንደ አዘዝሁትም ይነግራቸዋል፤ በስሜም በሚናገረው ሁሉ ያን ነቢይ የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀለዋለሁ። (ከወንድ ሞቻቸው እንደ አንተ ያለ መምህር አስነሣላቸዋለሁ፤ ሕጌንም በአንደበቱ አኖራለሁ፥ እንዲያስተምር አደርገዋለሁ፥ ለአንተ የነገርሁህን ሁሉ እነግረዋለሁ፥ ንገራቸው ብዬ ያዘዝኩትን ሁሉ እንዳዘዝሁት ያስተምራል)።» ተብሎ ለታል። ዘዳ ፲፰፥፲፭-፳። ይህ ቃለ ትንቢት ለጊዜው ለኢያሱ ሲሆን ለፍጻሜው ለክርስቶስ ነው። ሙሴ ሊመጣ ላለው ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንደ ሆነ ሁሉ በሙሴ እግር የተተካ ኢያሱም ምሳሌው ነውና። ትርጉሙም፦ «ሥጋን አዋህጄ ክርስቶስን አስነሣላቸዋለሁ፤ ሕገ ወንጌል በሱ ቃል እንድትነገር አደርጋለሁ፤» ማለት ነው። ሕገ ወንጌልን በተዋሕዶ ሰው ሆኖ የሠራት በደሙም ያጸናት ወልድ ቢሆንም በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ የሥላሴ (የሦስቱም) ሕግ ናት። ለዚህም ነው ጌታችን፦ «ትምህርትየስ ኢኮነት እንቲአየ፥ አላ እንቲአሁ ለዘፈነወኒ፤ ትምህርቴ የላከኝ ናት እንጂ የእኔ አይደለም። (የላከኝ የአብ የመንፈስ ቅዱስም ናት እንጂ የእኔ ብቻ አይደለም)። ያለው። ዮሐ ፯፥፲፯።
እግዚአብሔር ኢያሱን፦ «በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም። ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወር ሳለህና ጽና፥ በርታ። አገልጋዬ ሙሴ እንደ አዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አንብበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል፤ አስተዋይም ትሆናለህ። እነሆም አዝዝሃለሁ፤ በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ በርታ፤ አትፍራ አትደ ነግጥም።» በማለት ቃል በቃል አነጋግሮታል። ኢያ ፩፥፭፥፱። ኢያሱም ሕዝቡን  ከተአምራት ጋር በመምራት እስከ መጨረ ሻው ጸንቷል። ዮርዳኖስንም በታቦቱ ላይ በተገለጠ የእግዚአብሔር ኃይል ለሁለት በመክፈል ሕዝቡን በደረቅ መሬት ካሻገረ በኋላ ምድረ ርስትን በገመድ አከፋፍሏቸዋል። በዚህም በቤዛነቱ አዳምን አስከልጆቹ ባሕረ እሳትን በማሻገር ምድረ ርስት ገነ ትን ላወረሰው ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኗል።
፩፥፲፩፦ በእንተ ዳዊት፤
            ብላቴናው ዳዊት ከወንድሞቹ ሁሉ ትንሹ እርሱ ቢሆንም በእሥራኤል ዙፋን ይቀመጥ ዘንድ እግዚአብሔር መር ጦታል። ነቢዩ ሳሙኤል አንዳቸውን ቀብቶ እንዲሾም በላከው ጊዜ አባታቸው እሴይ ከልጆቹ ሰባቱን በፊቱ አሳልፏቸው ነበር። ነገር ግን ሁሉንም እግዚአብሔር አልመረጣቸውም ። ነቢዩ ሳሙኤል ገና ከመጀመሪያው ኤልያብን ተመልክቶ፥ «በእ ውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው፤» ብሎ ነበር። እግዚአብሔር ግን፥ «ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንደ ሚያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል፤» ብሎታል። ሳሙኤልም እሴ ይን፥ «ልጆችህ እነዚህ ብቻ ናቸውን?» አለው። እርሱም፥ «ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎች ይጠብቃል፤» አለ። ሳሙኤ ልም እሴይን፥ «እርሱ እከሚመጣ ለማዕድ አንቀመጥምና ልከህ አስመጣው፤» አለው። ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ «ይህ መልካም ነውና ተነሥተህ ዳዊትን ቅባው፤» በማለት ስለ ዳዊት መሰከረለት። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፩-፲፫። ከዚህም በላይ፦ «እንደልቤ የሆነ ፈቃዴን የሚያደርግልኝ የእሴ  ይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤» በማለት መስክሮለታል።
          ቅዱስ ዳዊት ታላቅና ገናና ንጉሥ ከመሆኑ የተነሣ መንግሥቱ የመሲሕ መንግሥት ምሳሌ ሆኖአል። መሲሑም ራሱ ብዙ ጊዜ በዳዊት ስም ተጠቅሶ ይገኛል። ፪ኛ ሳሙ ፯፥፰-፲፯፤ ኢሳ ፱፥፯፤ ኤር ፳፫፥፭-፮፣ ፴፫፥፲፬-፲፯፤ ሕዝ ፴፬፥፳፫፣ ፴፫፥ ፳፬። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዳዊት ወገን በመወለዱ የዳዊት ልጅ ተብሎ ተጠርቷል። ማቴ ፩፥፩፣ ፱፥፳፯፤ ሕዝ ፲፪፥፳፫። ንጉሥ ዳዊት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታዬ እያለ ጠርቶታል። ይኸውም የእርሱን ባሕርይ ይዞ ከእርሱ ወገን ቢወለድም ፈጣሪው እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። መዝ ፩፻፱፣፩፣ ማቴ ፳፪፥ ፵፬።
፩፥፲፪፦ በእንተ ኢዮብ፤
መጽሐፈ ኢዮብ፦ «አውስጢድ (ዖፅ) በሚባል ሀገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ነበር። ሰባትም ወንዶች፥ ሦስትም ሴቶች ልጆች ነበሩት። ከብ ቶቹም፦ ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም አንስት አህዮች ነበሩ፤ እጅግ ብዙም አገልጋዮች ነበሩት፤ ሥራውም በምድር ላይ ታላቅ ነበረ፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ገናና ነበረ።» ይላል። ኢዮብ፦ «ምናልባት ልጆቼ በልባቸው በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር ያስቡ ይሆናል።» በማለት እየላከ ይቀድሳቸው፥ በየስማቸውም መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ልጆች (ቅዱሳን መላእክት) በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መ ጡ፤ ሰይጣንም ከእነርሱ ጋር መጣ። ከእነርሱ ጋር መሆኑ፥ በእግዚአብሔርም ፊት መቆሙ አላሳፈረውም። መልእክተኞቹ መ ናፍቃንም እንዲሁ ናቸው። ከእውነተኞቹ መምህራን እና ምእመናን ጋር ተቀላቅለው በቤተክርስቲያን ውስጥ ሲኖሩ አያ ፍሩም፥ ከፍ ብለው እግዚአብሔርን ዝቅ ብለው ሰውን አይፈሩም። ደፋሮች ናቸው። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ «ከወዴት መጣህ?» አለው። ሰይጣንም፥ «ምድርን ሁሉ ዞርኋት፥ ከሰማይ በታችም ተመላለስሁና መጣሁ።» ብሎ ለእግዚአብሔር መለ ሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ «በባሪያዬ በኢዮብ ላይ የምታስበው ነገር እንዳይኖር ተጠንቀቅ! በምድር ላይ እንደ እርሱ ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ሰው የለምና።» አለው። እግዚአብሔር እንዲህ ቢለውም ሰይጣን መቼም ቢሆን በቅዱሳን ላይ የሚያቀርበውን ክስ አያቆምም። ለዚህም ነው እስከዛሬም ድረስ በመናፍቃንና በአሕዛብ ላይ እያደረ ቅዱሳንን ሲከስስ ሲያስከስስ የሚኖረው።
እግዚአብሔር ለጻድቁ ለኢዮብ የመሰከረለት ምስክርነት የማያዳግም ምስክርነት ቢሆንም ሰይጣን ግን መቀበል አል ፈለገም። መናፍቃንም እንዲሁ ናቸው፤ ምክንያቱም ስለ ቅዱሳን ምን ቢነገራቸው፥ እንኳን ሰው እግዚአብሔርም ቢመሰክ ርላቸው ልቡናቸው ዝግ ነው። ሰይጣን በእግዚአብሔር ምስክርነት ላይ አምጾ፥ «በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚያመል ከው በከንቱ ነውን? አንተ ቤቱን በውስጥም በውጭም በዙሪያው ያለውንም ሁሉ አልሞላህለትምን? የእጁንም ሥራ ባርከህ ለታል፥ ከብቱንም በምድር ላይ አብዝተህለታል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብ ሃል።» በማለት ክሱን ቀጠለ። ጻድቁ ኢዮብ ሰይጣን ባመጣው ፈተና ያን ሁሉ ሀብት በአንድ ጀንበር አጣ፥ አሥር ልጆቹም ሞተውበት በአንድ ጉድጓድ ቀበረ። በዚህ ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገነ እንጂ አልበደለም፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ። «ከእናቴ ማኅፀን ራቁቴን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደ ምድር እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔር ነሣ፤ እግዚአብ ሔር እንደፈቀደ ሆነ፥ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤» አለ። ይህ የጻድቁ የኢዮብ ገድል ለሰይጣን አልተዋጠለትም። ዳግመኛ ሌላ ክስ ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ቀረበ። ሰይጣን በጻድቁ በኢዮብ ላይ ምን ክስ ቢያበዛ የእግዚአብሔር ምስክርነት አልተለወጠም። ሰይጣን ግን፦ «ቊርበት ስለ ቊርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅ ህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳስስ፤ (ጤና ንሳው)፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል፤» ብሎ ወተወተ።
ጻድቁ ኢዮብ ሰይጣን ባመጣው ፈተና ጤናውን አጥቶ መግል እስኪፈስሰው ትልም እስከሚባለው ድረስ መላው አካሉ ቢቆስልም ከሃይማኖቱ አልተናወጠም። በአመድ ላይ ተኝቶ ቊስሉን በገል እስከማከክ ደረሰ። ሚስቱም አራት ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን ከተናገረችው በኋላ፥ «አሁን እግዚአብሔርን ስደብና ሙት፤» አለችው። እርሱ ግን፥ «አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉውን ነገር አንታገስምን?» አላት። በዚህ በደረ ሰበት ሁሉ ኢዮብ በእግዚአብሔር ፊት በከንፈሩ አልበደለም። እግዚአብሔር እንደመሰከረለት ሆኖ ተገኘ። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝ የጻድቁ የኢዮብ ገድል ነው። ኢዮ ፩፥፩-፳፪፣ ፪፥፩-፲። መጽሐፍ ቅዱስም በቅዱሳን ገድል የተሞላ ነው።
እግዚአብሔር ስለ ጻድቁ ስለ ኢዮብ ሃይማኖትና በጎ ምግባር ብቻ ሳይሆን ስለ ኢዮብ አማላጅነትም መስክሮለታል ። እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን «እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ አንዲት ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና አንተና ሁለ ቱ ባልንጀሮችህ በድላችኋል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘን ድ ሂዱ፥ እርሱም የሚቃጠል መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ ያሳርግላችሁ። ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልይ፥ እኔም ፊቱን እቀ በላለሁ። ስለ እርሱ ባይሆን ባጠፋኋችሁ ነበር። በባሪያዬ በኢዮብ ላይ ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና።» ያለው ለዚህ ነው።
ጻድቁ ኢዮብ በገድል ተቀጥቅጦ ሰይጣንን ካሳፈረው በኋላ፥ እግዚአብሔር ከደዌው ሁሉ አዳነው። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ ጸለየ፥ እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ተወላቸው፤ እግዚአብሔርም ቀድሞ በነበረው ገንዘቡ ሁሉ ፈንታ ሁለት እጥፍ ከዚያም በላይ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው። ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ባረከለት፤ ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሶስት ሴቶች ልጆች ተወለዱለት። ኢዮ ፵፪፥፩-፲፫።

5 comments:

 1. Kesis, Kale Hiwot Yasemalin. Egziabiher Yitebiklin.

  ReplyDelete
 2. kale hiwet yasemalim abatachin

  ReplyDelete
 3. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ፀጋውን ያብዛሎት።

  ReplyDelete
 4. Kalehiwot Ysemalin, be-edimie ena be tsega yitebikilin!!!!!!! Ermias

  ReplyDelete
 5. kalihiwet yasemalen betam astemari new

  ReplyDelete