Tuesday, November 8, 2011

«ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን፥ ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤»
ማቴ ፭፥፴፰።

ከሊቀ ኅሩያን ከፈለኝ ወልደ ጊዮርጊስ
            ይህ ቃል፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በምንም ነገር ቢሆን መማል ፈጽሞ እንደማይገባ ከተናገረ በኋላ የተናገረው ቃል ነው። እኔም እውነት የሆነውን እውነት፥ ሐሰት የሆነውን ደግሞ ሐሰት ለማለት ይኽንን ሕያው የሆነውን የጌታዬን የአምላኬን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል መነሻ አድርጌያለሁ።
               ቅዱሳን አባቶቻችን ጥንተ ጠላታቸው ሰይጣን የተለያየ ክብረ ነክ ስድብ ሲሰድባቸው በትእግሥት ያሳለፉት፥ በአኰቴት ይቀበ ሉት ነበር። ስለ ሃይማኖታችው መዋረድ ለእነርሱ ጸጋ ነውና። ቅዱስ ዳዊት ከዙፋኑ ወርዶ ከተርታው ሕዝብ ጋር ተሰልፎ በመዘመሩ ሜልኰል ወለተ ሳኦል አሽሟጣው ነበር፥ እርሱ ግን ሽሙጡን በጸጋ ተቀብሎ ስለ እግዚአብሔር ክብር ገና ከዚህ የበለጠ ራሱን እንደ ሚያዋርድ ነግሯታል። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፳-፳፪። የገዛ ልጁ አቤሴሎም አሳድዶት በስደት በሚንከራተትበትም ጊዜ የሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ፥ ሳሚ የሚባል ሰው በሕዝቡና በመኳንንቱ ፊት ሰድቦታል። ይህ በዳዊት ላይ የወረደ ስድብና ውርደት ያሳዘናቸውና ያበሳጫቸው የሶር ህያ ልጆች ሰይፋቸውን መዝዘው ነበር። በዚህን ጊዜ ቅዱስ ዳዊት፦ «ተዉት ይስደበኝ፤ (ይርገመኝ፥ ያዋርደኝ፤)፤» ብሎአቸዋል። በየዘ መኑ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም ስድቡን ብቻ ሳይሆን ሰይፉን፥ እሳቱን፥ ግርፋቱን ሁሉ ታግሠው እስከ ሞት ድረስ ጸንተዋል። «እስከ ሞት ድረስም የታመንህ ሁን፤ የሕይወት አክሊልንም እሰጥሃለሁ።» የተባለውን በተግባር ፈጽመዋል። ራእ ፪፥፲። በሃይማ ኖታቸው ሲመጡባቸው ግን ትእግሥት የላቸውም፥ «መናፍቅ» ሲሉአቸው ዝም አይሉም።
          እኔ ይኽንን መግለጫ ከአምስት ዓመታት በኋላ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ለማውጣት የተገደድኩት፥ በ2002 ዓ.ም. በተከበሩ በመምህር ሀብተ ማርያም ተድላ በተጻፈ መጽሐፍ ላይ እና በሰሞኑ ለቅድስት ተዋህዶ ሃይማኖት ለመሠዋት በተዘጋጁ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ወጣቶች ለቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ተሃድሶ መናፍቃን ባቀረቡት አቤቱታ ላይ «ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ፤» ሆኜ በመገኘቴ ነው።
          አባታችን መምህር ሀብተ ማርያም ተድላ፥ በዲሲ እና አካባቢዋ አብያተ ክርስቲያናት ትብብር ተቋቁሞ በነበረው የካህናት ማኅበር፥ በ«ቄስ» አስተርአየ ጽጌ፤ አቅራቢነት ተነሥቶ የነበረውን የሃይማኖት ክርክር 219 ገጽ በሆነው መጽሐፋቸው የማያዳግም ኦርቶ ዶክሳዊ መልስ ሰጥተዋል። ይህም በዘመናቸው ለተነሡ መናፍቃን በአፍም በመጽሐፍም መልስ ከሰጡ ጥንታውያን ሊቃውንት ጋር የሚያሰልፋቸው ነው። በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ዙሪያ፦ «ጥንተ አብሶ ነበረባት፤» በሚሉ ወገኖችና «ጥንተ አብሶ አልነ በረባትም፤» በሚሉ ወገኖች መካከል ዱላ ቀረሽ ክርክር በሚደረግበት ጊዜ እኔም በቦታው ተገኝቼ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የማገለ ግለው ዲሲ ማርያም ስለነበረ ነው። የጉባኤውም ቃለ ጉባኤ ጸሐፊ ነበርኩኝ። የጉባኤው ሰብሳቢም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ነበሩ።
          ይህ የሃይማኖት ክርክር በሚደረግበት ወቅት፦ የ«ቄስ» አስተርአየን ሃሳብ የደገፉ ሰዎች ዝርዝራቸው በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል። ይኽንን ፍጹም የሆነ ክህደት ከተቃወሙት መካከል ደግሞ እኔ እና ርዕሰ ደብር አብርሃም እንገኝበታለን። ይኽንንም በወቅቱ በስደት እዚህ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፥ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የነበሩት አቡነ ማትያስ፥ ያውቁታል። በኋላም ለሀገረ   ስብከቱ ተሹመው መጥተው ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሁሉንም ነገር አስረድቼ ማስረጃዎችን ሰጥቻቸዋለሁ። ጸሐፊው መምህር ሀብተማርያም ተድላ በመጽሐፋቸው ገጽ 34 ላይ፦ «ለቅዱስ ሲኖዶስ በተላከው በማኅበረ ካህናቱ ጽሑፍ አለመግባባት የተፈጠረበት ምክንያት ከሚለው አርእስት ቀጥሎ የሰፈረው ይነበባል። አንደኛው ወገን፦ < አንጺሖ ሥጋሃ ኃደረ ላዕሌሃ> የሚለውን  ቃል ተቀብሎ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነቢብ፥ የገቢር፥ የኀልዮ ኃጢአት ያልነበረባት የሌለባት ናት። ነገር ግን በአዳማዊ ዘር በኲል ከሚተላለፈው ውርስ መንፈስ ቅዱስ አንጽቷታል ሲል፤ ሁለተኛው ወገን ደግሞ ገና ሳትወለድ በዘር ይተላለፍ ከነበረው አዳማዊ ውርስ ነጻ ናት የሚል ነው፤» ብለዋል። ይህ ትክክል ነው። ትክክል ያልሆነው ይኽንን የተረጐሙበት መንገድ ነው። «ይህ ከዚህ በላይ የሚነበበው የማኅበረ ካህናት ጽሑፍ የተጣመመና የተዛባ (Distorted) በሆነ አጻጻፍ የተቀመጠ ወይም ለማደናገር ሆን ተብሎ የተደረገ አሻሚ ሁኔታ ይታይበታልና መስተካከል ይኖርበታል፤» ብለዋል። ይህም በወቅቱ «እመቤታችን ጥንተ አብሶ አልነበረባትም፤» ብለን የተከራከርነውን ሰዎች እምነት የነካ ነው። ምክንያቱም «ጥንተ አብሶ አልነበረባትም፤» የሚለው የገባው የእኛን እምነት ለማንጸባረቅ እንጂ ለማደናገር አይደለምና ነው። አባታችን መምህር ሀብተ ማርያም ይኽንን ያደረጉት ሆን ብለው እንዳልሆነ ስለሚገባኝ ለወደፊቱ እንዲስተካከልልኝ በትኅትና እጠይቃለሁ።
          ምንአልባት በወቅቱ ምን እርምጃ ወሰድክ የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፥ ተገቢም ነው። ኅዳር 1 ቀን 1998 ዓ.ም. ስድስት ገጽ የቅሬታና የአቋም መግለጫ በማውጣት በጽሑፍ አሰራጭቻለሁ፥ በሬድዮም አስነግሬአለሁ። በዚህም ምክንያት ከዲሲ ማርያም ከሥራዬ ተባርሬ እስከነ ቤተሰቤ በረሀብ አለንጋ ተገርፌአለሁ። በኋላም ቅዳሜ ቅዳሜ አገለግል ወደነበረበት በሪችመንድ ደብረ መንክራት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ብቻ ተወስኜ በምኖርበት ጊዜ፥ ቤተክርስቲያኗን ወደ እናት ቤተክርስቲያን በማስገባቴ ብዙ ፈተና ደርሶብኛል። ከፈተናውም አንዱ፥ የዲሲ ማርያም አስተዳደር ሪችመንድ ከሚገኘው ቦርድ ጋር በመመሳጠር ፍርድ ቤት ገትረውኛል። ይኽንንም ብፅዕ አቡነ ገብርኤል ያውቁታል። ምክንያቱም ቦርዱ በምስክርነት ጠርቷቸው ፍርድ ቤት ተገኝተው ስለነበረ ነው። መገኘታቸውም በእኔ ላይ ለመመሥከር ሳይሆን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለማክበር ሲሉ ብቻ ነበር። ነገር ግን ከሳሾቼ ምንም ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻሉ ክሳቸውን ለማቆም ተገደዋል። ዳኛውም ለእኔ ፈርዶልኝ ፋይሉን ዘግቶታል። የእኔ አቋም በግልፅ የታወቀ በመሆኑ ከአሁን ቀደም ከብፁዕ አቡነ ማትያስና ከብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ጋር አሁንም ከብፁዕ አቡነ አብርሃም ጋር እናት ቤተክርስቲያኔን እያገለገልኩ ነው። ሃይማኖቴም የጠራ ነው። በመሆኑም «መናፍቅ» መባልን እምቢ ብያለሁ፥ ነፍሴ ትጸየፈዋለች። በመሆኑም ከአምስት ዓመታት በፊት ያወጣሁትን አቋሜን ዛሬም እነሆ እላችኋለሁ። እስከ ሞት ድረስም ያው ነው፥ አይለወጥም።  
ኅዳር 1 ቀን 1998 ዓም
አቋሜ፣
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «ጥንተ አብሶ» የሚባል ነገር ፈጽሞ የሌለባት፣ ከአባታችን ከአዳም በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የወረደው የውርስ ኃጢአት እርሷን ግን በጭራሽ ያልነካት ያልደረሰባት፣ ይህም የሆነው የሰው ዘር ሳትሆን ቀርታ ወይም ልዩ ሰማያዊ ፍጡር ሆና ሳይሆን ከአባቷ ከቅዱስ ኤያቄምና ከእናቷ ከቅድስት  ሃና የተወለደች ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እናትነት አስቀድማ የተመረጠችና የታጨች በመሆኗ ለዚህ የመረጣት መንፈስ ቅዱስ ገና በእናቷ ማኅፀን ሳለች በዘር ይተላለፍ ወይም ይቆራኝ ከነበረው የውርስ ኃጢአት ጠብቋታል። እንዳይደርስባትም አንጽቷታል /ንፁህ አድርጓታል/። ምክንያቱም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ስለዚህም ከሴቶች ሁሉ የተለየች መሆኗን በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት በቤተ መቅደስ እያለች ከሦስቱ አካላት አንዱን ወልድን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንስ ተነግሯታል። ተበስሮላታል። በዚያን ሰዓትም የመልአኩን ቃል በመቀበል «እንደ ቃልህ ይደረግልኝ» ስትል ብስራቱን ተቀብላለች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
እንግዲህ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርቱ ከጥንት የመጣው የአባቶቻችንም ምስክርነቱ ዛሬ ደግሞ የእኔም እምነት ይሄ ነው። የማስተምረውም የምመሰክረውም ይህንኑ ነው። ይሁንና ዛሬ ዛሬ እንደሚሰማው «እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መንፈስ ቅዱስ አንጽቷተል ቀድሷታል» የሚለውን አባባል የግድ ከነጻች ኃጢአቱ ነበረባት ማለት ነው አለበለዚያ ከምን አነፃት? በሚል በማይገባ ስህተት ውስጥ ገብተው ይህንኑም በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች አልታጡም። ምንም እንኳ መለኮታዊ ጥበብን በሰው ቋንቋ ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ለማነጻጸርም ቢያዳግትም ለእኛ በሚገባን መንገድ በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ አንድ ሰው ከመኪና ግጭት አደጋ ለጥቂት ድኗል። ታዲያ ይህን ሰው እግዚአብሔር አዳነው እግዚአብሔር ጠበቀው እንላለን። ሆኖም አድኖታል ጠብቆታል ስላልን የግድ ተገጭቶ ነበር የሚለውን ሃሳብ አያስከትልም። ሳይገጭ እግዚአብሔር ጠብቆታልና። ለመዳን ለመትረፍ መገጨት ወይም ለአደጋው መጋለጥ የግድ የለበትም ፈጦ ከመጣው አደጋ ሊሰወር ይችላልና። ጠበቀው አዳነው ማለት እንችላለን። ነገር ግን አዳነው ስለተባለ ጠበቀው ስለተባለ አለበለዚያ ከምን አዳነው ከምን ጠበቀው ስለደረሰበት ስለተገጨ አይደለም ወይ? ብሎ ማሰብ አለማስተዋል ካልሆነ በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም። እንደዚሁም ሁሉ እመቤታችንን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከአዳም የውርስ ኃጢአት ጠበቃት፣ እንዳይደርስባት አነጻት ስለተባለ ብቻ ያነጸት ስለነበረባት ነው ብሎ ማመን መከራከር ለእኔ ኅሊናዬ የማይቀበለው ነገር ነው። ስለዚህ በትክክለኛው መልክ መሄድ ሲገባ አዲስ ሃሳብና አዲስ ፍልስፍና ማምጣት ትርፉ ውድቀት ነው። ከቶውንስ የፍልስፍና እናቱ መቸገር ነው ተብሎ የለ። ስለዚህ ለሁሉም የሚበጀው በእመቤታችን ላይ ምርምር ማካሄዱ ሳይሆን ይልቁንስ ለአሥራት ሀገሯ ለኢትዮጵያችን ሰላሙን በአማላጅነቷ እንድታወርድልን በረከቷ እንዲበዛልን ፍቅሯ እንዲጨምርልን መማፀን መለማመን እንጂ እግዚአብሔር ያከበራትን ለእናትነት የመረጣትን በማንና በምንም ምሳሌ የማይገኝላትን ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን በሆነች እናታችን ላይ ቃል መናገሩ አስተያየት መሰንዘሩ በራስ ላይ መልሶ ለመጣል ድንጋይ ማንሳት ነውና ከዚህ መቆጠብ ያስፈልጋል።  እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።

9 comments:

 1. "የእኔ አቋም በግልፅ የታወቀ በመሆኑ ከአሁን ቀደም ከአቡነ ማትያስና ከአቡነ ቀውስጦስ ጋር አሁንም ከአቡነ አብርሃም ጋር እናት ቤተክርስቲያኔን እያገለገልኩ ነው። ሃይማኖቴም የጠራ ነው። በመሆኑም «መናፍቅ» መባልን እምቢ ብያለሁ፥ ነፍሴ ትጸየፈዋለች። በመሆኑም ከአምስት ዓመታት በፊት ያወጣሁትን አቋሜን ዛሬም እነሆ እላችኋለሁ። እስከ ሞት ድረስም ያው ነው፥ አይለወጥም።"
  Des yemil Haymanotawi agelalets new. Endih be-Emnetachew tsentew yemiyatsenu Abatochin Yalasatan Egziabiher Yimesgen.
  Abatachin Kesis Kefelegn W/Giorgis Egziabiher eske mechereshaw Ayilewutibin.

  ReplyDelete
 2. "የእኔ አቋም በግልፅ የታወቀ በመሆኑ ከአሁን ቀደም ከአቡነ ማትያስና ከአቡነ ቀውስጦስ ጋር አሁንም ከአቡነ አብርሃም ጋር እናት ቤተክርስቲያኔን እያገለገልኩ ነው። ሃይማኖቴም የጠራ ነው። በመሆኑም «መናፍቅ» መባልን እምቢ ብያለሁ፥ ነፍሴ ትጸየፈዋለች። በመሆኑም ከአምስት ዓመታት በፊት ያወጣሁትን አቋሜን ዛሬም እነሆ እላችኋለሁ። እስከ ሞት ድረስም ያው ነው፥ አይለወጥም።" Gizew Yemiteyekewen semaetenet selehymanotew seletkebelu ejig Yakoral. Mchershawon Yasamerelew. Begeletse badebabaye Yemesekerulat woladit Amlak bemedereme besemayeme wagawon tekefelewo. Amen

  ReplyDelete
 3. እንዲህ ነው ክርስትና! አባታችን ትናንት የነበርዎ ዛሬም ያለዎት አቋም አንድ እንደነበረ በቅርብ የነበርን ልጆችዎ እናውቃለን። ያኔም ስንት መከራ እንደደረሰብዎ እርስዎን ያሰበ ሁሉ አይረሳውም። እርግጠኛ ነኝ ለመምህር ሀብተ ማርያም ተድላ ይህንን በግልጽ ቢያሳውቃቸው ከይቅርታ ጋር ምላሽ እንደሚሰጥዎ። ለማንኛውም ከማን ጋር እንደምትውል ልንገርህና ማንነትህን እነግርሃለሁ የሚለውን አባባል ትክክለኛ ተምሳሌትነቱን ከእርስዎ ማግኘት ይቻላልና በርቱ እላለሁ። እግዚአብሔር እስከመጨረሻዋ እቅታ ድረስ በሃይማኖትዎ ያፀናዎ ዘንድ ይርዳዎ። ቢችሉ ግን አዲስ አበባ ለሚገኘው የሰንበት ት/ቤት አንድነት ጽ/ቤት ቢያሳውቋቸው መልካም ነው እላለሁ።

  ReplyDelete
 4. kale hiwot yasemalen, lehulachinenm Egziabher ye neseha ena yebegonet lebuna becherenetu yadelen.

  ReplyDelete
 5. Amen Amen Amen Abatachen Kesis Kefelegn Welde Giorios Egziaber Emeberhanen Was Tebeka Tekerakari endehonwat Hulu, Erswam Beferd Ken Was Tebeka Hona Tekumelwot, Awon menafek mebalen ye hulachenem nefs tetseyefewaleche, Endalutem Egziabher Eskemechereshawa heqeta deresh yeketelwot zend mengezem tselote new . Emahoy Besrate Gebrel ke Holland.

  ReplyDelete
 6. "እውነት እውነትን እውነት ብለዋል::እግዚአብሔር ይስጥልን"

  ReplyDelete
 7. አባታችን ያበርታዉ እላለው

  ReplyDelete
 8. this is my firm stand about sent mariam egna keabatochachn anbeltim legziabher yemisanew yelem (mesfin kombolch)

  ReplyDelete
 9. kalewet yasemalen amen

  ReplyDelete