Monday, October 24, 2011

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል፦ ፲፩

        የሰው ልጅ አንድን ነገር በተደጋጋሚ የሚያየው ወይም የሚሰማው ከሆነ ቶሎ የመሰልቸት ጠባይ አለው። ሁልጊዜ አዲስ ነገር ይፈልጋል፥ ይናፍቃል። ቁርስ ላይ የበላው ምሳ ላይ፥ ምሳ ላይ የቀረበው ደግሞ እራት ላይ ሲመጣለት ያስጠላዋል። ሰውየው፦ ጧት ቂጣ፥ ቀን ቂጣ፥ ማታ ቂጣ፥ ቂጣ፣ ቂጣ የት አባክ ያለው ለዚህ ነው። ሁሉም እንደየአቅሙ ሽሮ ሰለቸኝ፥ ሥጋ ሰለቸኝ ይላል። ቂጣንም ሽሮንም ያጣ ሰው መኖሩ ይረሳል። የእሥራኤል ሕዝብ ከሰማይ እየወረደ እንበለ ድካም ያገኙት የነበረ መና (ምግብ) ሰልችቷቸው «ሥጋ ማን ያበላናል?. . . ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም፤» ብለው የለ! ዘኁ ፲፩፥፬-፮። እየበሉ ማመስገን ሲገባቸው፥ እየበሉ በማልቀሳቸው እግዚአብሔርን አስቆጥተዋል። የነቢያት አለቃ ሙሴም እግዚአብሔርን፦ «ለምን በአገልጋይህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ ሞገስ አላገኘሁም? (የነዚህን ወገኖች ጥፋት ወደእኔ ትመልስ ዘንድ በፊትህ ባለሟልነትን ለምን አላገኘሁም)? ለምንስ የዚህን ሁሉ ሕዝብ ሸክም በእኔ አደረግህ? አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ፦ ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቅፍ በብትህ እቀፋቸው የምትለኝ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወይስ ወለድሁትን? በፊቴ ያለቅሳሉና፥ የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና፥ ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከየት አለኝ? እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። (ይበዙብኛልና እኒህን ወገኖች እኔ ብቻዬን መጠበቅ አይቻለኝም)። እንዲህስ ከምታደርግብኝ በፊትህ ይቅርታን አግኝቼ እንደሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ፤» እስከማለት ደርሷል። ዘዳ ፲፩፥፩-፲፭።
          የሰው ልጅ ስልቹነቱ በአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነው። ጥሩ ቤት ሠርቶ ወይም ተከራይቶ ለመኖር ይናፍቃል፥ መናፈቅ ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቀው በላይ መሥዋዕትነት ይከፍላል። ከስድስት ወራት በኋላ ግን በውስጡ የነበረው ፍቅር ጠፍቶ ይሰለቻል። ልብስም፥ ጫማም፥ ጌጣ ጌጥም፥ የቤት ዕቃም፥ መኪናም እስከሚገዙ ድረስ ናፍቆት ናቸው፤ በቀጥታም ይሁን በአቋራጭ ከተገዙ በኋላ ግን የዓይን አምሮት ያልቅና፥ የልብም ናፍቆት ይጠፋና እንደ ተርታ ነገር ይሰለቻሉ። ምናልባት ቦታ የሚኖራቸው በሌላ ወገን ላይ የበላይነት ለማሳየት ሲፈለግ ብቻ ነው። አግልግሎታቸውም ራስን ለማስደሰት ሳይሆን በሌላው ላይ ለመኲራት ይሆናል። የውጪውም ሀገር አሜሪካም፥ አውሮፓም፥ አውስትራልያም፥ ካናዳም፥ ዓረብ አገርም ይናፍቃሉ። በባሌም በቦሌም ተብሎ ተሳክቶ ኑሮ ከተጀመረ በኋላ ግን በቅጽበት ይሰለችና በቦታው መቆዘምና መመረር ይተካል። በብዙ ናፍቆትና በብዙ መስዋዕትነት አሜሪካ ከተደረሰ በኋላ «በቃ አሜሪካ ማለት ይህቺ ናት?» ይባላል፤ ሌላ አሜሪካ ያለች ይመስል። ኧረ ለመሆኑ የሰው ልጅ የማይሰለቸው ምን ነገር አለው? ጸሎቱም፥ ጾሙም፥ ስብከቱም ሰባኪውም፥ ቅዳሴውም ቀዳሹም፥ ቡራኬውም ባራኪውም፥ ጠበሉም፥ ቊርባኑም፥ ቅስናውም መቅደሱም፥ ማኅሌቱም ቅኔ ማኅሌቱም፥ ምንኲስናውም ገዳሙም ሁሉም ነገር ሰልችቶታል። ይህም በምንበዛው መናገራችን እንጂ ሁሉም እንዲህ ነው፥ ማለት አይደለም።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት (የሚሰለቹበት) ጊዜ ይመጣልና፤» በማለት ለልጁ ለጢሞቴዎስ የጻፈው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፬፥፫።
          እንግዲህ እንዲህ ዓይነት መንፈስ ያለን ሰዎችን ነን፥ በትዳር ዓለም ውስጥም የምንኖረው። አንድን ትዳር ለመመሥረት የማይከፈል መሥዋዕትነት የለም። የአቅም ማነስ፥ ወይም የቤተሰብ ተፅዕኖ  ወይም የአካባቢ ጫና ቢያጋጥም፥ የጠባይ አለመስተካከልም ቢኖር፥ ዋናው ትዳሩ ይመሥረት እንጂ ሌላው ነገር ሁሉ በኋላ ይታሰብበታል ነው የሚባለው። የሰው ልጅ አስቦ ይሠራል እንጂ እንዴት ሠርቶ ያስባል? «አስቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ፤» የተባለው ያለ ምክንያት አይደለም። «የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ዳር ዳሩ ሰንበሌጥም፤» ተብሏል።
          የትዳር ነገር ሲታሰብ የዕለት ወይም የሳምንት፥ የወር ወይም የዓመት አይደለም። ወደ ትምህርት ተቋም ተገብቶ ትምህርቱ፣ ጥናቱ፣ ፈተናው ምን ቢሰለች ሁለቱ ዓመት ወይም አራቱ ወይም ስድስቱ ዓመት ሲያልቅ እገላገለዋለሁ፥ እንደሚባለው ዓይነት አይደለም። እርሱም ቢሆን እንደግልግል ከተቆጠረ ማለቴ ነው። ምክንያቱም ትምህርት እስከ ዕድሜ ልክ በመሆኑ በሥራም ላይ ሆኖ መማር ይቻላልና ነው። የሚያስተውል ሰው ከተገኘ እያንዳንዱም ዕለት በራሱ አስተማሪ ነው። የሥራውም ዓለም ቢሆን የራሱ የሆነ የማይቀርና መቼም ቢሆን የማይገላገሉት ከበድ ያለ ፈተና እና ገድል አለው። እንሰልች ከተባለ ሁሉም ነገር. አሰልቺ ነው። ሰው በጠባዩ የማይሰለቸው ኃጢአትንና በደልን ብቻ ነው። ስለዚህ ስለ ትዳር ነገር ሲታሰብም የዕድሜ ልክ መሆኑን ማወቅም ማመንም ያስፈልጋል። ማመን ብቻም ሳይሆን ለዚህ ለረጅም ጊዜ ገድል ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ምናኔ ብቻ ሳይሆን ትዳርም በራሱ የራሱ ገድል አለውና ነው። የጠብ ወይም የፍቺ ቀጠሮ ተይዞ ወደ ትዳር ዓለም አይገባም። መቼም «ተፈራርማችኋል ወይ?» የሚባለው ለፍቺ እንዲመች ይመስለኛል። ፍቺ ደግሞ በእሥራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው። «ይህንም የምጠላውን ደግሞ አደርጋችኋል፤ ዳግመኛም መስዋዕታችሁን እንዳልመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳልቀበለው የእግዚአብሔርን መሠዊያ በዕንባና በልቅሶ በኀዘንም ትከድናላችሁ። እናንተም፦ ስለምንድነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳን ሚስትህ ሆና ሳለች እግዚአብሔር በአንተና በፈታሃት በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለሆነ ነው። እርሱ የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እናንተም እግዚአብሔር የሚፈልገው ምንድነው? ዘር አይደለምን? ብላችኋል፤ ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ የልጅነት ሚስትህን አትፍታ። መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚሰውረውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር፥ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ።» የሚል ተጽፏል። ሚል ፲፫፥፲፮። ጌታችን አምካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ፍቺ እንደማይፈቀድ ለአይሁድ ባስተማራቸው ጊዜ፦ «እንኪያ የፍቺዋን ደብዳቤ ሰጥተው እንዲፈቱአት ሙሴ ለምን አዘዘ?» ብለውት ነበር። እርሱ ግን «ሙሴስ ስለ ልባችሁ ክፋት ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ፤ ቀድሞ ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ያገባ ያመነዝራል፤» አላቸው። ማቴ ፲፱፥፩-፱። «እግዚአብሔር ልቡናንና ኲላሊትን ይመረመራል፤» እንዲል፥ ጌታችን የባህርይ አምላክ፥ እግዚአብሔር ቃል፥ እግዚአብሔር ወልድ በመሆኑ የልባቸውን አውቆ ነግሯቸዋል። መዝ ፯፥፱። የልባቸው ክፋት፥ እርስ በርሳቸው ሲሰለቻቹ፥ ሌላ ለማግባት ሲሉ፥ በተለያየ ዘዴ የትዳር ጓደኛቸውን በምሥጢር ማጥፋት ነበር።
          ብዙ ሰዎች መልክ አይተው ወደ ትዳር ዓለም ይገቡና ያን ያመለኩትን መልክ አይተው አይተው ሲሰለቻቸው እስከዚህም ይሆናሉ፤ ያን አፍ አውጥተው ያደነቁትን፥ አሥር ገጽ ደብዳቤ የጻፉለትን፥ መዝሙር ስለማይገኝለት ዘፈን የሰሙለትን፥ ቅኔም የተቀኙለትን መልክ ቸል ይሉታል። እንዲያውም ትንሽ ዘግይተው ቢሆን ኖሮ የተሻለ መልከኛ ያገቡ እንደነበር አስበው ይጸጸታሉ። በዚህን ጊዜ ይህን ሁሉ ለምደው የነበሩ መልከኞች ይከፋሉ። በተለይም በመልካቸው ይመኩ የነበሩ ሰዎች ከሆኑ ሞራላቸው ይወድቃል። ሀብት አይተው የገቡ ሰዎችም እንዲሁ ናቸው። ሀብቱ እንደብዛቱ ቀዳዳውም ብዙ ስለሆነ ህልማቸው ቅዠት ይሆንባቸውና ትዳራቸውን እየሰለቹ ይመጣሉ። በሀብት ውስጥ ተደብቆ የነበረ ክፉ ጠባይም እንደ ሰኔ ሰርዶ ብቅ ብቅ እያለ ስለሚሄድ ሁሉ ነገር እጅ እጅ ይላቸዋል። ዕውቀትን፥ ሥልጣንን፥ ዘርን፥ ዝናን፥ ታዋቂነትን አይተው ወደ ትዳር ዓለም ዘለው የገቡ ሰዎችም እንዳሰቡት አልሆን ሲላቸው ወይም የተለየ ነገር ሲያጡበት፥ «ዕድለኛ ነኝ፥ ሎተሪ ነው የወጣልኝ፤» እንዳላሉ፥ በየሄዱበትም እንደ ገድል እንዳልተረኩ ሁሉ ተሰለቻችተው መነዛነዝ ይጀምራሉ፥ ከዚያም አልፈው በጓደኛም፥ በቤተሰብም፥ በባዕድም ፊት እስከመተማማት ይደርሳሉ። ቅዱስ ዳዊት፦ «አፍህ ክፋትን አበዛች፥ አንደበትህም ሽንገላን ተበተባት። ተቀምጠህ ወንድምሀን ታማዋለህ፥ ለእናትህም ልጅ ዕንቅፋትን አኖርህ። ይህን አድርገህ ዝም አልሁህ፤ ኃጢአት አማረችህን?» ያለው እንዲህ ዓይነቱን ክፉ ሕይወት ነው። መዝ ፵፱፥፳። ከዚህም ሌላ፦ «ባልንጀራውን በስውር የሚያማን እርሱን አሳደድሁ፤» የሚል ቃልም ተነግሯል። መዝ ፩፻፥፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ሐሜት መልካም እንዳልሆነ ሲናገር፦ «እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፥ ሐሰት መናገርንም ሁሉ፥ ጥርጥርንም፥ መተማማትንም፥ መቀናናትንም፥ ከእንንተ አርቁ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፩። በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር በአሮንና በእኅቱ በማርያም ላይ የተቆጣባቸው፥ ወንድማቸውን ሙሴን በማማታቸው ነበር። ዘኁ ፲፪፥፩-፰።
          በመንፈሳዊውም ዓለም በስም መንፈሳዊ፦ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፥ የማኅበር አባላት፥ የሠርክ ጉባኤ ተከታታዮች፥ ሰባክያን፥ መዘምራን፥ ቀዳሾች፥ ቆራቢዎች፥ በየገዳማቱ የሚዞሩ፥ በየንግሡ የማይቀሩ፥ በፍልሰታ ሱባኤ የሚይዙ፥ ጻድቃኔ ማርያም የሚያዘወትሩ ተብሎ የትዳር ምርጫውን ያልፉና ጉድና ጅራት ከበስተኋላ ነው የሚለውን ብሂል የሚሽር ጉድ ሳይውል ሳያድር ወዲያው ይከሰታል። ከሩቅ ያዩት የነበረው መንፈሳዊነት ሲቀርቡት እንደምትሐት ይሰወርባቸዋል። ተስፋ ያደረጉት ነገር ሁሉ ባዶ ይሆንባቸዋል። እርሱን ተጠግቼ በእርሱ እጸድቃለሁ ያሉት ሰው እንኳን ለሌላው ሊተርፍ ለራሱ እንኳ የማይሆን ከንቱ ሆኖ ያገኙታል። ከዚህ በኋላ የዚያን ሰው ጸሎት፥ መዝሙር፥ ስብከት፥ አገልግሎት ይሰለቻሉ። ከመሰልቸታቸው ብዛት ድምፁን መስማት፥ ዓይኑንም ማየት ያስጠላቸዋል። በመንፈሳዊ ቦታ ሲያገለግልና ሲያስገለግል የሚያዩት ሰው ሁሉ አንድ ይመስላቸውና በጅምላ መጥላት በጅምላ መኰነን ይጀምራሉ። ይህም መንፈሳዊ ነኝ በሚል ነገር ግን ባልሆነ ሰው ድካም የሚመጣ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «እነሆ በእናንተ ምክንያት አሕዛብ የእግዚአብሔርን ስም ይሰድባሉ።» ያለው ለእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ነው። ኢሳ ፶፪፥፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽንን ኃይለ ቃል ጠቅሶ አስተምሮበታል። ሮሜ ፪፥፳፬።
በሌላ በኲል ደግሞ መንፈሳዊነታቸውን ለመጠበቅ በሚጥሩ ሰዎች ላይ ሰይጣን የሚያመጣው ፈተና አለ። አንዳንዶች እስከ ጋብቻ ድረስ «ነገ እናስቀድስ፤» ሲባሉ «እንዲያውም ዛሬውኑ እዚያው እንደር፤» ይላሉ። «ሰባቱን አጽዋማት እንጹም፤» ሲባሉ፥ «ጾመ ጽጌንም ስምንተኛ እንጨምር፤» ይላሉ። እስከ ምሳ ሰዓት እንጹም ሲባሉ፥ «ጀንበር እስክትጠልቅ አሥራ ሦስተ ሰዓት እንጹም፤» ይላሉ። «ለአንድ ቀን ገዳም ደርሰን እንምጣ፤» ሲባሉ፥ «መሄዳችን ካልቀረ ለሁለት ሳምንት ሱባኤ እንያዝ፤» ይላሉ። ብቻ በስሜት ወይም በማስመሰል የማይሆኑት የማያደርጉት ነገር የለም። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት፥ ሠራተኞች ወደ መሥሪያ ቤት፥ ነጋዴዎች ወደ ሱቅ ሲሄዱ ነጠላ ለብሰው መሄድ ያምራቸዋል። ከጋብቻ በኋላ ግን ይህ ሁሉ ቀስ በቀስ ወይም በቅጽበት ይቆማል። ትናንት ያደነቁትን ሕይወት ዛሬ መተቸት ይጀምራሉ። የትናንቱን ሲያስታውሷቸው «መስሎኝ ነበር፤» ይላሉ። ያ ወደ ልባቸው ሳይገባ ዓይናቸው፥ ጆሮአቸውና አፋቸው ላይ የቀረ መንፈሳዊነት ይሰለቻቸዋል። ዔሳው ብኩርናውን እንደናቀ በተክሊል በቊርባን መጋባታቸውን ይንቁታል። በዚህም መንፈሳዊውን ሰው ይፈታተኑታል። እርሱም ቤተክርስቲያን እንዳትሰደብ፥ በዙሪያው ያሉ ሰዎችም እንዳይሰናከሉ ሲል «የተሰጠኝ መስቀል ነው፤» ብሎ ተሸክሞ ይኖራል።
እንግዲህ በትዳር ሕይወት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳያጋጥመን፥ ቢያጋጥመንም ፈተናውን እንድናልፍ ከማግባታችን በፊት ቆም ብለን ልናስብ ይገባል። የትዳርን ዓላማ ማወቅ በትዳርም የሚገኘውን ጸጋ ማስተዋል ያስፈልጋል። ትዳር በራሱ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑንም ለአንድአፍታም መዘንጋት አይገባም። ከትዳር በፊትም ከትዳር በኋላም በጸሎት መትጋትም የውዴታ ግዴታ ነው። «ወደ ፈተናም እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤» እንደተባለው ሆኖ መገኘት ነው። ማቴ ፳፮፥፵፩። ከሁሉም በላይ እኛ ሰዎች የሰውን መልኩን እና አንደበቱን እንጂ ልቡን ስለማናውቅ ሁሉን ለሚያውቅ ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል፥ ይህም ታላቅ እምነት ነው። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፮፣ ዮሐ ፪፥፳፬። በእምነት ላይ የተመሠረተ ትዳር ደግሞ በዓለት ላይ እንደተመሠረተው ቤት በምንም በማንም የማይናወጥ ይሆናል። ማቴ ፯፥፳፬።
የሰው ልጆች ትዳርን ያህል ክቡር ነገር ሲሰለች እንደሚለወጥ፥ ሲሰበር እንደሚተካ ቊሳቁስ ልንቆጥረው አይገባም። እንኳን ትዳር ሃላፊውም ጠፊውም ነገር ቢሆን በተሰጠን ማመስገን እንጂ ዕለቱን ሰልችተን ሌላውን መናፈቅ የስግብግብነት መንፈስ ነው። የትዳር ጓደኛን እንደ ሸሚዝ የለዋወጡ ሰዎች እኮ አይናገሩትም እንጂ ያተረፉት የኅሊናን ጠባሳ ብቻ ነው። የሀገሬ ሰው «ትሻልን ሰድጄ ትባስን አመጣሁ፤» ያለው ለዚህ ይመስለኛል። በተለይም ለፍላጐታችን ልጓም ካላበጀንለት የሰው ልጅ ፍላጐት ማቆሚያ የለውም። እስኪያገኝ ይንገበገባል፥ ካገኘ በኋላ ግን ይንቀዋል፥ ይሰለቸዋል፥ ይጠላዋል። ደግሞ ሌላ ነገር ይፈልግና በምኞት ፈረስ ይጋልባል። አብዛኞቻችን አቅም አጥተን ወይም ሕጉ አልፈቅድ ብሎን እንጂ ከዚህ የተለየን አይደለንም። «ከዚህ በኋላ እንዲህ ሆነ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፤ የዳዊትም ልጅ አምኖን ወደዳት። አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለተከዘ ታመመ፤ ድንግልም ነበረችና አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር። ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፤ ኢዮናዳብም እጅግ ብልህ ሰው ነበረ። እርሱም፦ የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለ ምን ቀን በቀን እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን? አለው። አምኖንም፦ የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን እወዳታለሁ አለው። ኢዮናዳብም፦ ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህም ሊያይህ በመጣ ጊዜ፦ እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንሞ እኔ እያየሁ እንድታዘጋጅልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ በል አለው። እንዲሁም አምኖን፦ ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊያየው በመጣ ጊዜ አምኖን ንጉሡን፦ እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ እያየሁ ሁለት እንጐቻ እንድታደርግልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላ እለምንሃለሁ አለው። ዳዊትም፦ መብልን ታዘጋጂለት ዘንድ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሂጂ ብሎ መልእክተኞችን ወደ ትዕማር ቤት ላከ። ትዕማርም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፥ ተኝቶም ነበር፤ ዱቄትም ወስዳ ለወሰች፥ እያየም እንጎቻ አደረገች፥ ጋገረችም። ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች እርሱ ግን ይበላ ዘንድ እንቢ አለ። አምኖንም፦ ሰውን ሁሉ ከእኔ ዘንድ አስወጡ አለ፤ ሰውም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ። አምኖንም ትዕማርን፦ ከእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው አላት፤ ትዕማርም የሠራችውን እንጐቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው። መብሉንም ባቀረበች ጊዜ ያዛትና፦ እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔም ጋር ተኚ አላት። እርስዋ መልሳ፦ ወንድሜ ሆይ፥ አይሆንም፤ እንዲህ ያለ ነገር በእሥራኤል ዘንድ አይገባምና አታሳፍረኝ፤ ይህንም ነውረኛ ሥራ አታድርግ። እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእሥራኤል ዘንድ ከምናምንቴዎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፤ እንግዲህስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም አለችው። ቃልዋን ግን አልሰማም፤ ከእርስዋም ይልቅ ብርቱ ነበርና በግድ አስነወራት፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ። ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ አምኖንም፦ ተነሥተሺ ሂጂ አላት። እርስዋም፦ አይሆንም ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ እኔን በማውጣትህ  የበለጠ ክፋት ትሠራለህ አለችው፤ እርሱ ግን አልሰማትም። የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ፦ ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት አለው። ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት። ትዕማርም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ኅብርም ያለውን ልብስዋን ተርትራ፥ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች።» ሳሙ ካልዕ ፲፫፥፩-፲፱።
በትዳር ዓለም አሰልቺ የሆነ ጠባይና ክፉ ግብር አያጋጥምም ማለት አይቻልም፤ በደንብ ያጋጥማል። ነገር ግን በእምነት የምንሸከመው ከሆነ እግዚአብሔር ያስችለናል። ሰው በሁሉም ፍጹም መሆን ስለማይችል በጠንካራ ጎኑ እየተጠቀሙ ደካማ ጎኑን ማስታመምና መሸከም ይገባል። የመረዳዳት ትርጉሙም ይኸው ነው። አንድ የምናውቃት በሃይማኖት የነቃች፥ ለበጎ ምግባርም የታጠቀች ጠንካራ እኅት አለች። በዚህ የሚመስላት የለም። ነገር ግን ሁልጊዜም ባይሆን አልፎ አልፎ ትቆጣለች። ችግሩ መቆጣቷ ሳይሆን ቊጣዋ ትንሽ ከበድ ይላል። ባለቤቷ ደግሞ ቊጣ የሚባል ነገር አያውቅም፥ ፈጽሞ አልሠራበትም። ታዲያ አንድ ቀን ንስሐ አባታቸውም ቤተሰባቸውም በሆኑ ካህን ፊት ትቆጣዋለች። የንስሐ አባትም «እንዴት እኮ፥ ተይ እንጂ፤» ይሏታል። በዚህን ጊዜ እርሱ፦ «ግድ የለም ትቆጣኝ፥ ያለ እኔ ማን አላት? ማንን ትቆጣ? ማን ላይ ትጩህ?» አለ። ምክንያቱም ቅንነቷን፥ የዋህነቷን፥ ደግነቷን ከማንም በላይ ያውቃል። «ቁጣዋ ይገባኛል፤» ብሎ ራሱን አሳምኗል። በሚገባም በማይገባም ብትቆጣው ይቀበላል፤ ከራሷ አብልጣም እንደምትወደው ያውቃል። ከዚህም ሌላ የእርሱን ድካም እንደተሸከመችለት ስለሚያውቅ የእርሷን ድካም ተሸክሞላታል። ከሁሉም በላይ በመካከላቸው ንጹሕ ፍቅር በመኖሩ መሰለቻቸት የሚባል ነገር የለም። አልፎ አልፎ ጊዜያዊ መኰራረፍ ያጋጥማል፤ ነገር ግን በውይይት ይፈቱታል። ውይይቱም ያው እንደተለመደው ከቊጣ ጋር የተቀላቀለ ነው። በዚህ ዓይነት ቊጣዋ ሳይናፍቀው ይቀራል? ሰው እኮ የለመደው ነገር ሲቀርበት ቅር ይለዋል። በአንፃሩ ግን እርሱ በስሕተትም ሆነ በግድፈት ቢቆጣ ጉድ ነው የሚፈላበት። ማን መክሮት ነው? ማን ገፋፍቶት ነው? ተብሎ ይተረጐማል። ምክንያቱም እርሷ የለመደችው ዝምታውን፥ ትዕግሥቱን ነው። እንግዲህ በየቤቱ የተለያየ ጉድለት ያለብን ሁሉ እነዚህን አብነት አድደርገን ተቻችለን ተላምደን የምንኖር ከሆነ መሰለቻቸት የሚባል ነገር የለም። በሂደትም እርስ በርስ ተሸናንፈን ደካማ ጠባያችንን ልናሻሽል እንችላለን። ዕድሜም ዘመንም ብዙ ነገር ያስተምረናል።

21 comments:

 1. kale hiwot yasemalen

  ReplyDelete
 2. kalehiwot yasemalen,

  ReplyDelete
 3. kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 4. Kale Hiwot yasemalen

  ReplyDelete
 5. KHY menigete semayate yawurseline rejem edime ketena gar yistelen

  ReplyDelete
 6. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 7. Kale Hiwot Yasemalen

  ReplyDelete
 8. Kesis, Kalehiwat Yasemalen.

  ReplyDelete
 9. kale hiwot yasemalen abatachen

  ReplyDelete
 10. Abetu! Geta hoye!! Ante Benegeroch Hulem Tastemregnaleh.Lezelealem Amesegnehalew.Amen! Kesis, Kalehiwat Yasemalen.

  ReplyDelete
 11. Abatachen edma ena tana yestelen

  ReplyDelete
 12. Kesis, Kalehiwat yasemalen regim edme ena tana yestelen.

  ReplyDelete
 13. Melake selam, Kalehiwet yasemawot!
  Egziabher mechem melkam new. serawem aymermerm ena lehulum bale tedaroch endezihum letdar felagiwoch meseret yalew timhert newna Amlakachnen Enamesegnewalen!
  Tsegawen yabzalot

  ReplyDelete
 14. Kesis,kalehiwot Yasemalen.Long life to you!

  ReplyDelete
 15. Yih Bezemenachin Ijig betam yemyasfeligen timhirt new, melkam Tidar yehulu neger meseret silehone. Igziabher bandim belelam yinageralina simu yetemesegene yihun.

  ReplyDelete
 16. fetari tsenatu,bertat,yestote

  ReplyDelete
 17. ከዚህም ሌላ የእርሱን ድካም እንደተሸከመችለት ስለሚያውቅ የእርሷን ድካም ተሸክሞላታል

  ReplyDelete
 18. Kesis, I can not read any of your post, I think if you load them as PDF format it may be better for me and for many of the others that wants to read your blog.

  ReplyDelete
 19. Kale Hiwot yasemalen

  ReplyDelete
 20. kale hiwot yasemalen

  ReplyDelete
 21. የትዳር ነገር ሲታሰብ የዕለት ወይም የሳምንት፥ የወር ወይም የዓመት አይደለም። ወደ ትምህርት ተቋም ተገብቶ ትምህርቱ፣ ጥናቱ፣ ፈተናው ምን ቢሰለች ሁለቱ ዓመት ወይም አራቱ ወይም ስድስቱ ዓመት ሲያልቅ እገላገለዋለሁ፥ እንደሚባለው ዓይነት አይደለም። እርሱም ቢሆን እንደግልግል ከተቆጠረ ማለቴ ነው። ምክንያቱም ትምህርት እስከ ዕድሜ ልክ በመሆኑ በሥራም ላይ ሆኖ መማር ይቻላልና ነው። የሚያስተውል ሰው ከተገኘ እያንዳንዱም ዕለት በራሱ አስተማሪ ነው። Kale hiwotn yasemaln !!!

  ReplyDelete