Saturday, September 24, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፭


አንድ ቃል የሚፈታው፥ የሚተረጐመውና የሚመሰጠረው ከባለቤቱ ማንነት አንፃር ነው። ተናጋሪው ማነው? የተነገረውስ ለማን ነው? የሚለው መሠረት ነው። ቋንቋው የተነገረበት ዘመን እና ባሕልም ወሳኝነት አለው። በተጨማሪም የተነገረበትን ምክንያት እና ዓላማ ማስተዋል ያስፈልጋል።  በተለይም የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እንደ ሥጋ አሳብ መተርጐም አደገኛ ነው። አደጋውም ስለእመ ቤታችን እና ስለቅዱሳን ባለን እምነት ላይ ብቻ ሳይሆን፥ ስለእግዚአብሔር ማንነት ባለን እምነትም ላይ ነው። ለምሳሌ፦ «እግዚአ ብሔርም የሠራውን ሥራ በስድስተኛው ቀን ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።» የሚለውን ይዘን እግዚአብሔር በባሕርዩ ድካም ኖሮበት ያረፈ ልናስመስለው እንችላለን። ዘፍ ፪፥፪። ነገር ግን አይደለም። ከጥቅሱ እንደምንረዳው ሊሠራው ያሰበውን ሁሉ ማከናወኑን፥ መፈጸሙን ነው። እንዲሁም ሰባት ዕለታትን ፈጥሮ ሰባተኛዋን ቀን ለሰው ልጅ ዕረፍት ትሆን ዘ ንድ ሕግ መሥራቱን ነው። በተጨማሪም፦ «እግዚአብሔርም የሰዎች ክፉ ሥራ በምድር ላይ እንደበዛ፥ የልባቸው ዐሳብ ምኞትም ሁ ልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ ።» የሚለውን ይዘን የእግ ዚአብሔርን ጸጸት ከፍጡራን ጸጸት ጋር አመሳስለን ለእግዚአብሔር ባሕርይ የማይስማማ ነገር ልንናገር እንችላለን። ፍጡር ቢጸጸት «እንዲህ ነገር እንደሚመጣ አውቄው ቢሆን ኖሮ አላደርገውም ነበር፤» በሚል መንፈስ ነው። እግዚአብሔር ግን ሰውን ሳይፈጥረው በ ፊት ሰው እንደሚበድል ያውቃል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ጸጸት እንደ ሰው ያለ ጸጸት አይደለም። ቃሉ እንደሚያስረዳው እግዚአብ ሔር በሰው ልጅ ክፋት ያዘነው ሐዘን እጅግ ታላቅ መሆኑን ነው። በመሆኑም ቅዱሳን አባቶቻችን ያስተማሩትን ትምህርት ማስተዋል «የበኲር ልጅዋንም እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤» የሚለውን በጥልቀት እንድንገነዘብ ይረዳናል።
ፍጻሜ ያለው «እስከ»፤
          በቋንቋ አጠቃቀም ፍጸሜ ያለው «እስከ» አለ፤ ይህም የአንድን ድርጊት መጨረሻ ወይም ፍጻሜ የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ ነቢዩ ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ እግዚአብሔር መሥዋዕቱን በመቀበል መምለኬያነ ጣኦታትን አሳፍሮለት፥ ከሦስት ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ዝናብን ባዘነበለት ጊዜ፥ «ወዲያ ወዲህም እስኪመላለስ ድረስ ሰማዩ በደመናና በነፋስ ጨለመ፤ ትልቅም ዝናብ ዘነበ፤ አክዓብም በሰረገላ ተቀምጦ እያለቀሰ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። የእግዚአብሔርም እጅ በኤልያስ ላይ ነበረች፤ ወገቡንም ታጥቆ ወደ ኢይዝራኤል እስከሚገባ ድረስ በአክዓብ ፊት ይሮጥ ነበር።» ይላል። ፩ኛ ነገ ፲፰፥፵፭። የነቢዩ የኤልያስ ሩጫ ፍጻሜው ኢይዝራኤል በመሆኑ «እስከ ኢይዝራኤል» ተብሏል። ከንግሥቲቱ ከኤልዛቤል ፊት በሸሸም ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ያቀረበለትን ምግብ ተመግቦ፥ «በዚያው በበላው የምግብ ኃይል እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። ይላል። ፩ኛ ነገ ፲፱፥፰። የነቢዩ የኤልያስ የአርባ ቀን እና የአርባ ሌሊት ጉዞ መጨረሻው ፍጻሜው የኮሬብ ተራራ በመሆኑ «እስከ ኮሬብ፥» ተብሏል። ይህም ከኮሬብ አልፎ አልተጓዘም ማለት ነው። በእግዚአብሔር ፊት በባለሟልነት የሚገለጥ፥ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ በቤተ መቅደስ በዕጣኑ መሠዊያ በስተቀኝ፥ ለጻደቁ ካህን ለዘካርያስ በመገለጥ፥ መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን እንደሚወልድ በነገረው ጊዜ፥ «ይህ እንደሚሆን በምን አውቃ ለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅቻለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል፤» ብሎ ነበር። መልአኩም መልሶ፥ «እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ። አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽምና ይህ እስከሚሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም ይሳንሃል።» ብሎታል። እንዲሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያመለከተ ኖሯል። ሉቃ ፩፥፲፱። ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ በኋላ ግን አንደበቱ ተፈትቷል። «ያን ጊዜ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተናገረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፤» ይላል። ሉቃ ፩፥፷፬። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የዕለተ ምጽአትን ምልክቶች ለደቀመዛሙርቱ ከነገራቸው በኋላ፥ «ምሳሌውንም ከበለስ ዕወቁ፤ ጫፍዋ የለሰለሰ፥ ቅጠልዋም የለመለመ እንደሆነ እነሆ መከር እንደ ደረሰ ታውቃላችሁ። እንዲሁ እናንተ ይህን ሁሉ ባያችሁ ጊዜ፥ እንደቀረበና በደጃፍ እንዳለ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስ ከሚደረግ ድረስ ይቺ ትውልደ አታልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።» ብሎአቸዋል። ማቴ ፳፬፥፴፪። ይህም ፍጻሜ ያለው እስከ ነው። ከትንሣኤ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስን፥ በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለ ክተውም፦ «እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጎልማሳ ሳለህ በገዛ እጅህ ወገብህን ታጥቀህ ወደ ወደድኸው ትሄድ ነበር፤ በሸመገልህ ጊዜ ግን እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ወገብህንም ሌላ ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም (አትወደው ወደ ነበረ ሞት) ይወስዱሃል፤» ብሎት ነበረ። በዚህን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ፥ «ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል? (በምን ዓይነት አሟሟት ይሞታል)?» ብሎ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ ጠየቀ። ጌታም፦ «እስከምመጣ ይኖር ዘንድ ብወድድስ አንተን ምን አግዶህ፤ አንተ ግን ተከተለኝ፤» ብሎታል። ዮሐ ፳፮፥፲፰። የዚህም ፍጻሜው መጨረሻው ዕለተ ምጽአት ነው፥ ያንጊዜ ግን ሃይማኖቱን መስክሮ በሰማዕትነት ያርፋል። ምክንያቱም ካልሞቱ ትንሣኤ የለምና ነው።
ፍጻሜ የሌለው «እስከ»፤
          ፍጻሜ የሌለው «እስከ» ማለት የቃሉን መጨረሻነት ወይም ፍጻሜ አልፎ ቀጣይነትን ወይም ዘለዓለማዊነትን የሚያሳይ ነው። ይኽንንም የሚያስረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። በኖኅ ዘመን ምድር በጥፋት ውኃ  ተጥለቅልቃ ነበር። በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር ኖኅን በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊትን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ፥ አዕዋፍንም ሁሉ፥ የሚንቀሳቀሰውንም ሁሉ ዐሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አመጣ፤ ውኃውም ጐደለ፤ የቀላዩም ምንጮች የሰማይ መስኮቶች ተደፈኑ፤ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤ ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እየቀለለ ይሄድ ጀመረ፤ ከመቶ ሃምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጐደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር (በእኛ በጥቅምት) በወሩም በሃያሰባተኛው ቀን በአራራት ተራራ ላይ ተቀመጠች። ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር (በእኛ እስከ ጥር) ድረስ ይጐድል ነበር። በአሥራአንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን (በእኛ በየካቲት መባቻ) የተራሮቹ ራስ ተገለጡ። ከአርባ ቀን በኋላም ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፤ ከምድርም ላይ ውኃው ጐድሎ እንደሆነ ያይ ዘንድ ቊራውን ላከው፤ እርሱም ሄደ፤ «ነገር ግን ውኃው ከምድር ላይ እስከሚደርቅ ድረስ አልተመለሰም፤» ይላል። ዘፍ ፰፥፩-፯። ይህ፥ ፍጻሜ የሌለው «እስከ» ይባላል፤ ምክንያቱም ቊራ ውኃው ከደረቀ በኋለም አልተመለሰምና ነው።
          ታቦተ ጽዮን ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ ሠረገላ ተጭና ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰች ጊዜ፥ ንጉሥ ዳዊት በክብር ይቀበላት ዘንድ ሰባ ሺህ ሰዎችን ሰብስቦ ነበር። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳ አለቆች ጋር ተነሥተው በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም የተጠራባትን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። በዜማ መሣሪያዎች በበገናና በመሰንቆ፥ በከበሮና በነጋሪት፥ በጸናጽልና በዕንዚራ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር። ወደ ከተማውም አመጣት፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰች ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘምር አየችው፥ በልብዋም ናቀችው። ቤተሰቡን ሊመርቅ በተመለሰ ጊዜም ልትቀበለው መጥታ ሰላምታ ከሰጠችው በኋላ «ከሚዘፍኑት አንዱ እንደሚገለጥ (እንደተርታ ዘፋኝ) የእሥራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ ሚስቶች ፊት በመገለጡ ምንኛ የተከበረ ነው! » ብላ አሽሟጠጠችው፥ የልቧን ንቀት በአንደበቷ ገለጠችው። ዳዊትም ሜልኮልን፥ «በእግዚአብሔር ፊት ዘምሬአለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ፤ እዘምራለሁም፤ አሁንም እገለጣለሁ፤ በዐይንሽ ፊትና እንዴት ከበርህ ባልሽባቸው ሴቶች ልጆች ፊት የተናቅሁ እሆናለሁ፤» አላት። «የሳኦል ልጅ ሜልኮል እስከሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም»። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፩-፳፫። ይህም ፈጽሞ አልወለደችም ማለት እንጂ፥ ከሞተች በኋላ በመቃብር ሳለች ወለደች ማለት አይደለም።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከትንሣኤው በኋላ፥ ዐሥራ አንዱን ደቀመዛሙርት ወደ ገሊላ እንዲሄዱ አዝዟቸው ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ በመቃብሩ አጠገብ ለተገኙት ለመግደላዊት ማርያምና ለሁለተኛዋ ማርያም (ለዮሐንስ እና ለያዕቆብ እናት ለማርያም ባውፍልያ) «እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና። በዚህ የለም፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፤ ነገር ግን ኑና ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና፦ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ እነሆ፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ፤ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው፤» ብሎ ነግሮአቸው ነበር። እነርሱም ይህንን ሰምተ ው ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር ሲፋጠኑ፥ ጌታም አገኛቸውና፦ «ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» አላቸው፤ ወዲያው ከእግሩ ስር ተደፍተው ሰገዱለት። እርሱም «አትፍሩ ሂዱና  ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል፤» አላቸው።
          ዐሥራ አንዱ ደቀመዛሙርት ጌታችን ኢየሱስ ወደአዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ። ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት። እኲሌቶቹ ግን ተጠራጠሩ።(ቶማስን ለማጠየቅ ነው)። ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ፦ «ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። (ነፍሱና ሥጋው ተለያይተው ስለነበር የእነርሱን መልሶ መዋሐድ ለማጠየቅ ተሰጠኝ አለ እንጂ፥ ሥጋ ሥልጣን ያገኘው፥ በተዋሕዶ አምላክ ሰው እንደሆነ ሁሉ ሰውም አምላክ የሆነው መለኮት ሥጋንና ነፍስን በማኅፀን ተዋሕዶ የዕለት ፅንስ የሆነ ዕለት ነው)። እንግዲህ ሂዱና  በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው  ሕዝቡን ሁሉ አስተምሩአቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ።» ብሎአቸውል። ማቴ ፳፰፥ ፩-፳። ይህም ባላችሁበት ዘመን ሁሉ አድሬባችሁ እኖራለሁ ሲላቸው እንጂ፥ ከዓለም ፍጻሜ በኋላ የሚለያቸው ሆኖ አይደለም።
ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳለ፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?» ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ከማን ወገን እንደተወለደ ለማጠየቅ «የዳዊት ልጅ ነው፤» ብለውት ነበር። እርሱም መልሶ እንግ ዲያስ ዳዊት በመንፈስ (በመዝሙረ ትንቢት) ጌታ (እግዚአብሔር አብ) ጌታዬን (እግዚአብሔር ወልድን) ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስከ ማደርጋቸው በቀኜ ተቀመጥ እንዴት አለው? እርሱ ራሱ ዳዊት ጌታዬ ያለው፥ እንግዲህ እንዴት ልጁ ይሆነዋል?» ብሎ ጠየቃ ቸው። ከዚህ ጥያቄ በኋላ አንድም ቃል ሊመልስለት የቻለ የለም፤ ከዚያች ቀንም ጀምሮ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ማቴ ፳፪፥፵፩-፵፮፣ መዝ ፩፻፫፥፩። መዝ ፩፻፲፥፩። ከእግርህ በታች የተባለው ከሥልጣነ መለኰት በታች ማለት ነው። ጠላት የተባሉት ለጊዜው አይሁድ፥ ለፍጻሜው አጋንንት ናቸው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ፥ በትንሣኤውና በዕርገቱ አይሁድንም አጋንንትንም ድል አድርጓቸዋል። በአብ ቀኝ መቀመጡ (ከአብ ተካክሎ መኖሩ) እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ነው እንጂ እስከ የሚገታው አይደለም። እርሱም ራሱ፦ ሊቀ ካህናቱ፦ «አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆንህ ትነግረኝ ዘንድ በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤» ባለው ጊዜ፥ «አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰውን ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን) በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ (ከአብ ጋር አንድ የሆነ ክብሩን) በሰማይ ደመና (በክብር ሲመጣ) ታዩታላችሁ፤» ብሎታል። ማቴ ፳፮፥፷፫። ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ የደረሰ፥ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ፥ ወደ ሰማይ ተመልክቶ፥ «እነሆ ሰማይ ተከፍቶ (ሰማያዊ ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጦ) የሰው ልጅም (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስም) በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ (በክብር ከአብ ተካክሎ) አያለሁ፤» ያለው ለዚህ ነው። የሐዋ ፯፥፶፮። ሐዋርያውም ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው? የሚፈርድስ ማን ነው? ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፥ በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው፥ (ከአብ የተካከለው)፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤» ብሏል። ሮሜ ፰፥፴፫።
«አላወቃትም፤»
ዕውቀት እጅግ ጥልቅና ረቂቅ ነገር ነው፤  ከሁሉም በላይ የዕውቀት ባለቤት እግዚአብሔር ነው። ዕውቀቱም የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ ይደነቃል እንጂ ከምንም ከማንም ጋር የሚነጻጸር አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፤ ፍርዱንም የሚያውቀው የለም። የእግዚአብሔርን ዐሳቡን ማን ያውቃል? ወይስ ማን ተማከረው? ብድሩን ይከፍል ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ ማን አበደረው? ሁሉ ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱም ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይሁን አሜን።» ያለው ለዚህ ነው። ሮሜ ፲፫፥፴፫። ነቢዩ ዳንኤልም፦ «ጥበብና ምክር ኃይልም ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይመስገን፤» ብሏል። ዳን ፪፥፳።
ዕውቀቱ ፍጹም የሆነ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ዐዋቂ አድርጎ ፈጥሮታል። ዘፍ ፩፥፪፥፯። በየጊዜውም በተፈጥሮ በተሰጠው ዕውቀቱ ላይ በጸጋ ዕውቀት ይጨመርለታል። ይኽንንም ነቢዩ ዳንኤል፦ «ጥበብን ለጠቢባን፥ ዕውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። የጠለቀውንና የተሰወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን (እጅግ ጥልቅና ረቂቅ የሆነውን) ያውቃል፤ ብርሃንም (ዕውቀትም) ከእርሱ ጋር አለ። አንተ የአባቶቻችን ፈጣሪ! ዕውቀትንና ጥበብን አንተ ሰጥተኸኛልና፥ የለመንሁህንም ነግረኸኛልና፥ የንጉሡን ሕልም፥ ትርጓሜውንም ገልጠኽልኛልና እገዛልሃለሁ፤ አመሰግንህምአለሁ።» በማለት ገልጦታል። ዳን ፪፥፳፮። ነቢዩ ዳንኤልና ሦስቱ ወጣቶች አናንያ፥ አዛርያና ሚሳኤል ጥበብን፥ ዕውቀትንና ማስተዋልን ከእግዚአብሔር ያገኙት በጾምና በጸሎት በመወሰናቸው ነው። ዳን ፩፥፩-፲፯።
የሰው ልጅ ዕውቀት የጸጋ ስለሆነ ፍጹም አይደለም፤ የሚያውቀው ነገር እንዳለ ሁሉ የማያውቀው ነገር አለ፤ የሚገለጥለት ነገር እንዳለ ሁሉ የሚሰወርበት ነገር አለ። ለምሳሌ፦ ነቢዩ ኤልሳዕ በእስራኤል ተቀምጦ በሶርያ ቤተ መንግሥት የሚመከረውን ምክር እያወቀ ለእስራኤል ንጉሥ በመንገር ብዙ ጊዜ ሕይወቱን አድኖለታል። ፪ኛ ነገ ፮፥፩-፳፫። እርሱም የሰማርያ ንጉሥ ሊያስገድለው በምሥጢር ባለሟሉን በላከበትም ጊዜ፥ ከቤቱ ሁኖ ስለዐወቀ አብረውት ላሉ ሽማግሌዎች፥ መልእክተኛው ገና ሳይደርስ፥ «ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቆርጥ ዘንድ እንደላከ እዩ፤ መልእክተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት፤ በደጅም ይቆም ዘንድ ተዉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው፤» ብሏል። ከእነርሱም ጋር ሲነጋገር እነሆ፥ መልእክተኛው ወደ እርሱ ደረሰ ይላል። ፪ኛ ነገ ፮፥፴፩-፴፫። በነቢዩ በኤልሳዕ አማላጅነት፥ ወንድ ልጅ አግኝታ የነበረችው የሱነም ሴት፥ ልጇ በሞተባት ጊዜ፥ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ገስግሳ በመምጣት፥ ከእግሩ ስር ወድቃ ሰገደች። የነቢዩ የኤልሳዕ ሎሌ ግያዝ «እንዴት ትነካዋለች» በሚል መንፈስ ሊያርቃት መጣ። ኤልሳዕ ግን ፥ «ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያን ከእኔ ሰውሮታል፤ አልነገረኝምም፤» አለ። ፪ኛ ነገ ፬፥፰-፴፫። ነቢዩ ኤልሳዕ በተሰጠው ጸጋ ብዙ ነገር ቢያውቅም ስለ ሱነሟ ሴት ግን ያላወቀው ነገር ነበረ። ጻድቁ ዮሴፍም ልክ እንደዚሁ ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ያላወቀው ምሥጢር ነበረ።
መናፍቃን ግን አስተሳሰባቸው ሥጋዊ በመሆኑ፥ «ቃየልም ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ሄኖሕንም ወለደች።» በሚለው መንገድ ተጉዘው፥ የበኲር ልጅዋን እስከምትወልድ ድረስ በግብር አላወቃትም፥ ከወለደች በኋላ ግን በግብር ዐውቋታል፥ በማለት ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቃል ይናገራሉ። ዘፍ ፩፥፲፯። ይህም፥ ቁራ ከጥፋት ውኃ በኋላ ተመልሷል፥ ሜልኮል ከሞተች በኋላ በመቃብር ወልዳለች፥ ጌታ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከዓለም ፍጻሜ በኋላ ይለያቸዋል፥ ኢየሱስ በአብ ቀኝ መቀመጡ ጠላቶቹን እስኪያዝገዛለት ድረስ ስለነበር አሁን በቀኙ የለም፥ እንደ ማለት ነው። በዚህም መንገድ ቢሆን ፈጽሞ አላወቃትም ተብሎ ፍጻሜ በሌለው እስከ ይተረጐማል እንጂ ፍጻሜ ባለው እስከ አይተረጐምም። ለመሆኑ «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደአለው ወደ መቅደሱ በር ++መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ (በድንግልና እንደጸናች ትኖራለች)፤ ሰውም አይገባባትም፤ (ዕሩቅ ብእሲ ከእርሷ የሚወለድ አይደለም፥ እንደሔዋን ወንዶችን ለማገልገል የተፈጠረች አይደለችም)፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች። (አምላክ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በተዋሕዶ ከእርሷ ሰው ሁኖ ተወልዷልና፥ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልደዋለችና በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)።» የሚለውን የነቢዩ የሕዝቅኤልን ቃለ ትንቢት ወዴት ጥለውት ነው? ሕዝ ፵፬፥፩-፬።
«ስለ ጻድቁ ስለ ዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ፤»

4 comments:

 1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 2. Kesis, Kale Hiwot Yasemalin. Rejim Ye-agelgilot Edime kemulu Tena gar EGZIABIHER yadililin.

  M.A Ethiopia

  ReplyDelete
 3. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ፀጋውን ያብዛሎት።

  ReplyDelete
 4. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ፀጋውን ያብዛሎት።

  ReplyDelete