Thursday, August 18, 2011

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል፦ ፲

ካለፈው የቀጠለ . . .
፩፦ የወላጆች ጠባይ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ፤

እልኸኝነት፦ ልብን ለክፉ ነገር ማጽናት ነው፤ እኛ ያልነው ብቻ ይሁን ብሎ መድረቅ፥ መጨከን ነው፤ የያዝነው መንገድ ገደል ቢከተንም እኛ ትክክል ነን ማለት ነው። እልከኛ የሆኑ ሰዎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፥ ከልጆቻቸው ፥ ከወላጆቻቸው፥ ከዘመዶቻቸው፥ ከጓደኞቻቸው፥ ከጎረቤቶቻቸው፥ ከመሥሪያ ቤት ባልደረቦቻቸው፥ ከሁሉም ጋር እልኽ ይያያዛሉ። የሌላውን በጎ የሆነ አሳብ መቀበል መሸነፍ፥ እጅ መስጠት ይመስላቸዋል። ከዚህም አልፎ ከእግዚአብሔር ጋር እልኽ ይያያዛሉ። እነርሱ ሲናገሩትና ሲያደርጉት ትክክል ነው ብለው ያመኑበትን  ነገር ሌላው ሰው በእነርሱ ላይ ሲናገረውና ሲያደርገው  ግን ፍጹም ስህተት ነው፥ ብለው በእልኽ ይናጣሉ። ከዚያ በኋላ ምንም ነገር ቢሆን ከማጥፋት ወደ ኋላ አይመለሱም።
        ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ ከባርነት ቤት ከግብፅ ወጥተው ወደ ከነዓን  የተጓዙ እስራኤል ዘሥጋ፥ የምድረ በዳ ጉዟቸው ምን ይመስል እንደነበር፥ በዘመኑ ለነበሩት የእስራኤል ልጆች ሲናገር፦ «አሁንም ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞቻችን  ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ። (መከራ ብንቀበል ማን አብነት ይሆነናል አትበሉ፥ የምታምኑትን ፊታውራሪያችሁን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርጉ)። ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ፥ እርሱ ለላከው የታመነ እውነተኛ ነው። (ሙሴ መና ከሰማይ አውርዶ፥ ውኃ ከዓለት አፍልቆ እስራኤልን በመመገብ ታማኝ እንደሆነ፥ እርሱም ምእመናንን ኅብስት አበርክቶ ምግበ ሥጋ፥ ሥጋውን ቆርሶና ደሙን አፍስሶ፥ ምግበ ነፍስ በመመገብ የታመነ ነው)። ነገር ግን የባለቤት ክብሩ ከቤቱ እንደሚበልጥ፥ ክብሩ ከሙሴ ክብር ይልቅ እጅግ ይበልጣል፤ (ያለመለወጥ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ፥ አንድም ምሳሌው በመሆኑ ከሙሴ ባነጻጽረውም፥ ከቤት የባለቤት ፥ ከቤተሰብ የጌታው ክብር እንደሚበልጥ፥ የባህርይ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር፥ ይበልጣል፤ ሙሴ ፍጡር ክርስቶስ ፈጣሪ፥ ሙሴ ቤት ክርስቶስ ባለቤት፥ ሙሴ የቤተሰብ አባል ክርስቶስ ደግሞ የቤተሰቡ ጌታ ነውና)፤ ቤትን ሁሉ ሰው ይሠራዋልና፤ ለሁሉ ግን ሠሪው (ሙሴን ጭምር ሁሉን የፈጠረ) እግዚአብሔር ነው። ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ (እንደ እግዚአብሔር አሽከርነቱ) የታመነ ነበረ። ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ (እንደ እግዚአብሔር የባህርይ ልጅነቱ) በቤቱ ላይ (ቤት በተባሉ ምእመናንን ላይ አድሮ ጸጋውን በመመገብ) የታመነ ነው፤ እኛም የምንደፍርበት፥ የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን። (ቤቱም የተባልን ያመንበት እኛ ነን፥ ሃይማኖታችንን እና ምግባራችንንም ብንጠብቅ፥ የማያልፍ ዋጋችን ይቆየናል)።» ካለ በኋላ፥ «መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብሏልና፥ ዛሬ ቃሉን ብትሰሙ አባቶቻችሁ ኤኔን የፈተኑበት፥ የመረመሩበትም፥ አርባ ዓመት ሥራዬን ያዩበት፥ በምድረ በዳ በፈተና ቀን እንደሆነ በማስመረር ልባችሁን አታጽኑ። (ትንሣኤ፥ ዕርገት፥ ዕረፍት፥ በዓት፥ መንግስተ ሰማይ እንዳለ ብትሰሙ፥ የለም በማለት ልባችሁን እልኸኛ አታድርጉት፤ ስለዚህ ያን ትውልድ ተቆጥቼ፦ ዘወትር በልባቸው ይስታሉ፥ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ፤ እንዲሁ፦ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ። ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልኸኛ እንዳይሆን ዛሬ ብሎ ሲጠራ ሳለ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ (እንኪያስ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን ሃይማኖት የሌለው የሚጠራጠር፥ ከሕያው እግዚአብሔር አንድነት የሚለይ ክፉ አእምሮ ያለው ሰው እንዳይገኝ እወቁ፤  ዛሬ የሚባል ዕድሜያችሁ ሳለ ሰውነታችሁን መርምሩ፥ ከእናንተ ወገን ማንም ማን ኃጢአት ባመጣው ቀቢፀ ተስፋ ጸንቶ አይኑር)፤» ብሏል። ዕብ ፫፥፮-፲፫ ፣ ዘፀ ፲፯፥፯፣ ዘኁ ፳፥፪-፲፫።
         እልኸኝነት እንደ እስራኤል ዘሥጋ ከእግዚአብሔር እንኳ ይለያል። ማኅበራነ አይሁድ፥ የኢየሱስ ክርስቶስን የቃሉን ትምህርት እየሰሙ፥ የእጁን ተአምራት እያዩ፥ ለሚጠይቁትም ጥያቄ በቂ መልስ እያገኙ፥ እስከመጨረሻው በክፋት የጸኑት በእልኽ ነው። «አልዓዛርንም ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ሲያስነሣው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ይመሰክሩለት ነበር። ስለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ይህን ምልክት እንዳደረገ ስለሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። ስለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፦ አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል፤ » ተባባሉ፥ ይላል። ዮሐ ፲፪፥፲፯-፲፱።   
          ወደ ትዳር ዓለም ስንመለስ ብዙ የምናስተውለው ነገር አለ። ይኸውም የብዙዎቻችን ትዳር ሲበጠበጥ የሚኖረውና አልፎ ተርፎም እስከ መፍረስ የሚደርሰው በእልኽ ነው። ምክንያቱም ከወላጆቻችን የወረስነው እልኸኝነትን ስለሆነ ነው። የወላጆች ተፅዕኖ ልጆቻቸው አብረዋቸው እስካሉ ድረስ ብቻ አይደለም። በጋብቻ ከተለይዋቸው በኋላም ጥላቸውን ያጠሉባቸዋል። አንድ ነገር በሰሙ ቁጥር የእልኽ ሥራ እንዲሠሩ ይገፋፏቸዋል። የእኔ ልጅ ሆነሽማ፥ የእኔ ልጅ ሆነህማ፥ የማንም መጫወቻ አትሆኚም፥ አትሆንም እስከ ማለት ይደርሳሉ። እንዲህ እያደረጉ ነገሩን ያባብሱታል። ይህም የሁሉም ወላጅ ጠባይ ሳይሆን በተወሰኑት ላይ ብቻ የሚንጸባረቅ ነው። «የእኛን ቤተሰብ በእልኽ የሚችለን የለም፤» ብለው እንደ ቁም ነገር ሲናገሩ የሰማሁበት ጊዜ አለ። ከዚህም በላይ «በእልኽ ሰይጣንም አይወዳደረኝም፣» ሲባልም ሰምቻለሁ። «እልህ ከማር ይጣፍጣል፤» የሚል ሰውም አጋጥሞኛል። ታሪኩ እንዲህ ነው፤ ሰውየው ሚስቱን ጠልፈውበት ፍርድ ቤት ይመላለሳል። ለስሙ ጠለፋ ይባል እንጂ የእርሷም ስምምነት  ያለበት ይመስለኛል። የሚመላለሰው ከባላገር ነው፤ አንድ ዘመዱ ይኽንን አስተውለው፦ «ምን አደከመህ? ይህች ሴት እኮ ተመልሳ ገንዘብ (ትዳር) አትሆንህም፤» ይሉታል። እርሱም መልሶ፦ «ተመልሳ ትዳር እንደማትሆነኝማ አውቃለሁ፥ መች አጣሁት፤» ይላል። እርሳቸውም፦ «ታዲያ ምን አደከመህ? ጊዜህን፥ ገንዘብህንና ጉልበትህን ለምን ትጨርሳለህ?» ይሉታል። እርሱም፦ «እልኹ ነዋ፤» ይላቸዋል። በዚህን ጊዜ፦ «እልኽ ምን ያደርግልሃል?» ቢሉት፥ «አይ ጋሼ እልህ እኮ ከማር ይጣፍጣል፤» ብሎአቸዋል። ከዚህ የምንማረው፥ እልህ እንደማር እየጣፈጠ  መራራ ነገር ላይ እንደሚጥል ነው። ይህ ሰው አልተጎዳም ለማለት ፈልጌ አይደለም፥ ተመልሳ ገንዘብ ላትሆነው እልኹ ይበልጥ ይጎዳዋል ለማለት ነው።
                በትዳር ዓለም በእልኸኝነታቸው እንደ ጥሩ ነገር (እንደ ጀብዱ ቆጥረውት) የሚኮሩ ሰዎች አሉ። ባለቤቷ ዘወትር ሱሪ ባትለብሺ፥ ቤተክርስቲያን ስትሄጂ እንኳ ቀሚስ ብትለብሺ ሲላት በእልኽ ቁምጣ የምትለብስ፥ ጓደኛ አታብዢ ሲላት በእልኽ ከነበረው እጥፍ የምታደርግ፥ የአንቺ ነገር እኮ ቀኑን ሙሉ ስልክ ላይ ሆነ ሲላት በእልኽ የምታድርበት፥ የቤት ወጪያችን ከአቅማችን በላይ ሆኗል ሲላት፦ ይኽን ያህል ምን የማያስፈልግ ነገር ገዛሁና ነው ብላ በእልኽ የዕረፍት ጊዜዋን ሁሉ ወደ ገበያ የምትሮጥ፥ በእቅድ እንመራ ሲላት በእልኽ ድንገት ያሰበችውን ሁሉ በቅጽበት ካልፈጸምኩ የምትል፥ በየወሩ ለቤተሰብ የምትልኪው ከእኛ ገቢ ጋር የሚመጣጠን አይደለም ሲላት እንዲያውም ባለፈው በስልክ ሳነጋግራቸው የሆነ ችግር ሲያወሩ ነበርና ተጨማሪ ካልላክን ሞቼ እገኛለሁ ብላ በእልኽ የምትፎክር፥ ትምህርት ጀምራ ለምን ዛሬ ቀረሽ ሲላት በእልኽ እንዲያውም ከዛሬ ጀምሮ አልሄድም ብላ የምትቆጣ፥ እስከዛሬ የባከነው ገንዘብና ጊዜስ ስትባል ገደል ይግባ ስትል የማይዘገንናት፥ ከዚያም አልፋ እማዬም  ትምህርቷን ያቋረጠችው በአባዬ እልኽ ነው ብላ ታሪክ የምትጠቅስ፤ ቤተሰቦቼ ባለፈው በመጡ ጊዜ በመስተንግዶሽ አልተደሰቱም ሲላት በእልኽ ከዚያ በላይ ምን እንዳደርጋቸው ፈልገው ነው? እንዲያውም ከዛሬ ጀምሮ በደጄ እንኳ እንዳያልፉ ብላ የምትወስን፥ ያቺን ጓደኛሽን አልወደድኳትም ካላት በእልኽ አንተ ትቀራለህ እንጂ እሷ አትቀርም ብላ የምትደመድም፥ በየቤቱ አለች። በወንዶችም በኩል ተመሳሳይ ነው፤ የትዳር ጓደኞቻቸውን ምክር አልቀበል ብለው በእልኽ የሱስ ተገዢዎች፥ አመንዝሮች የሆኑ ብዙዎች ናቸው፤ ምነው አመሸህ ሲባል በማግስቱ በእልኽ እስከ መንፈቀ ሌሊት የሚቆይ፥ ምነው እስከ ሌሊት ሲባል በማግስቱ የምታመጪውን አያለሁ ብሎ በእልኽ የሚያድር ፥ ምነው አደርክ ሲባል በእልኽ ሳምንት የሚሰነብት፥ ቤተሰቦቼ የሆነ ነገር ቸግሮአቸዋል፥ የመርዳት ሃላፊነት ስላለብን በአቅማችን ትንሽ ነገር እንላክላቸው ብላ በሥርዓት ስትጠይቀው በእልኽ እኔ አንቺን እንጂ እነርሱን አገባኋቸው እንዴ? የሚል፥ እንደምንም  ትንሽ ገንዘብ ለመላክ ከተስማማ በኋላ ሊያንስ ይችላል ሲባል ደግሞ በእልኽ እንዲያውም ይኸንንም አልክም የሚል፥ ከእገሊት ጋር ያላችሁ ቅርበት አላማረኝም ስትለው ከተጠረጠርኩ ካልቀረ ብሎ በእልኽ ሌላ ነገር ውስጥ የሚገባ፥ በእልኽ አንጀትሽን አሳርረዋለሁ የሚል፥ በየቤቱ ሞልቷል።     
እልህ ከዚህም በላይ ነው፥ በእልህ ብዙ ገንዘብ ያወጡባቸውን የቤት ዕቃዎቻቸውን የሚሰባብሩ፥ የቀረበላቸውን ማዕድ በእርግጫ የሚደፉ፥ ለአንደበትም ለጆሮም የሚከብድ ስድብ የሚሳደቡ፥ አልፈውም ቤተሰብን የሚናገሩ፥ ለትዳር ጓደኛቸው ማናቸውም ዓይነት ፍላጐት የማይጨነቁ፥ የራስህ ጉዳይ፣ የራስሽ ጉዳይ የሚሉ አሉ። ከዚህ የከፋው ደግሞ በእልህ የትዳር ጓደኛቸውን ወይም ራሳቸውን ለማጥፋት ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ናቸው። እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለው መርዝ ለመጠጣት፥ ለመሰቀል ያስባሉ፥ ይሞክራሉ። በዚህ ዓይነት አሳባቸውን ፈጽመው በከንቱ የቀሩ፣ በከንቱ ያስቀሩ ብዙዎች ናቸው።
  ወገኖቼ፥ እንኳን ሳንበደል ብንበደል እንኳ ፍጹም ትዕግስተኞች መሆን ይጠበቅብናል። ይኸንን ነገር የሚያደርጉት አሕዛብ ቢሆኑ አይደንቅም፣ የሚደንቀው እኛ ክርስቲያኖች ነን የምንለው ሰዎች መሆኑ ነው። ክርስቲያን ማለት እኮ ክርስቶስን የመሰለ  ማለት ነው። ስለዚህ እርሱን አብነት አድርገን በነገር ሁሉ እርሱን ልንመስል ይገባል። የዚህ ዓለም ነገር እልኽ አስጨራሽ ቢሆንም መፍትሔው ትዕግስት ብቻ ነው። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ሎሌዎች ሆይ ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ። በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገስ ምስጋና ይገባዋልና። ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት ? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሱ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ።» ብሏል። እንግዲህ ሎሌዎች ጠማሞች ለሆኑ ጌቶቻቻው እንኳን መገዛት ካለባቸው እኛ ደግሞ ከዚህ በበለጠ ለትዳር ጓደኞቻችን እንደባሪያ ልንገዛላቸው፥ ልንታገሳቸው ይገባል። እያንዳንዳችን ለትዳራችን የምንከፍለው መሥዋዕትነት እንዳለ መዘንጋት የለብንም። ትንሽም ሆነ ብዙ እየቆሰልን የትዳር ጓደኞቻችንን ልናድናቸው እንችላለን። እነርሱን ብቻ ሳይሆን፥ በእኛ ትዳር መፍረስ ሊሰናከሉ፥ ተስፋም ሊቆርጡ ይችሉ የነበሩትንም ሰዎች እናድናቸዋለን። ልንሸከመው የተሰጠን መስቀል ይህ ከሆነ እንሸከመው ዘንድ ግድ ነው። ክርስቶስ የታገሰው ያዳነውም የገረፉትን፥ ያቆሰሉትን፥ የሰቀሉትንም ጭምር ነውና።
እንግዲህ ላይጠቅም እልኽ መያያዙን ትተን ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመከረን ምክር ጸንተን እንኑር። ሐዋርያው ሎሌዎችን፦ «ለጌቶቻችሁ ተገዙ፤» ብሎአቸው ስለነበር፥ ከዚያው አያይዞ ሴቶችን ደግሞ፦ «እንዲሁ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከእነርሱ አንዳንዱ ለቃሉ የማይታዘዝ ቢኖሩ ከሴቶች መልካም ሥራ የተነሣ ያዩ ዘንድ፥ ያለጥርጥርም ሰውነታቸውን ይጠቅሙአት ዘንድ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ እየፈራችሁም በንጽሕና አካሄዳችሁን አሳምሩ። (እግዚአብሔር ይፈርድብናል ብላችሁ ግብራችሁን አከናውኑ)። ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ዋጋው ብዙ የሆነ ልብስን በመጎናጸፍ የውጭ ሽልማት አይሁንላችሁ።( የባላችሁን አፍአዊ ዓይኑን ለማስደሰት አይሁን)። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ጸጥ ያለ መንፈስ ያለው፥ የማይጠፋና የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። (ካደረ ለማይለይ፥ ከተሰጠ ለማይነሳ፥ ሲያድርም እንደ ሻኩራ ነጉዶ፥ እንደ ግምጃ ኳ ብሎ ለማይሰማ፥ ለመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ለመሆን የባላችሁን ዓይነ ልቡናውን ደስ በማሰኘት ይሁን)። ቀድሞም እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ የተቀደሱ ሴቶች እንዲሁ ለባሎቻቸው በመገዛት ራሳቸውን ያስጌጡ ነበር። (በባዶ ሳይሆን ለባሎቻቸው ከመገዛት ጋር ያጌጡ ነበር፥ ማጌጣቸው በአፍአ ብቻ ሳይሆን በመገዛት በውስጥም ነበር)። እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ትታዘዘው ነበር፤ ጌታዬም ትለው ነበር፣ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር ምንም ሳትፈሩ በበጎ ሥራ ልጆቿ ሁኑ። (እናንተም ልጆቿ እስራኤል በበጎ ሥራ ጸንታችሁ ኑሩ፥ አንድም እናንተም አሕዛብ በሥጋ ባትወለዷትም በበጎ ምግባር ልጆቿ ሁኑ)።» ብሎአቸዋል። ቅዱስ ጴጥሮስ ሴቶቹን ተናግሮ ወንዶቹን አልተዋቸውም። እነርሱንም፦ «እንዲሁም እናንተ ባሎች ሆይ፥ ከሚስቶቻችሁ ጋር ስትኖሩ፥ሚስቶቻችሁን አታቃልሉ፤ («ሴቶችን ለባሎቻችሁ ተገዙ እንዳልሁ ሚስቶቻችሁን አክብሩ፥ አትናቁ፥ አታቅልሉ እላችኋለሁ)፤ የሴቶች ተፈጥሮ ደካማ ነውና፤ (ብንይዝ እናስቀራቸዋለን፥ ብናስር እናጠብቃቸዋለን፥ ብንሮጥ እንቀድማቸዋለን ብላችሁ አትመኩባቸው)፤ ጸሎታችሁ እንዳትሰናከል ሚስቶቻችሁን አክብሩ፥ እነርሱ ከእናንተ ጋር ክብርንና ሕይወትን ይወርሳሉና። (የቂመኛ ሰው ጸሎት በእሾህ መካከል እንደወደቀው ዘር ስለሆነ፥ የቂመኛ ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ስለሌለው፥ አንድ ልብስ ለብሳችሁ፥ አንድ ቀለበት አድርጋችሁ፥ አክሊል ተቀዳጅታችሁ፥ የተደረገላችሁ ጸሎተ ተክሊል እንዳይፈርስባችሁ ስትሉ በባሕርያቸው ደካማ የሆኑትን ሚስቶቻችሁን ወጥታችሁ ወርዳችሁ እርዱ። ወደ ፈተና እንዳይገቡ በጸሎት ጠብቋቸው። እነርሱም እንደ እናንተ ከእናንተ ጋር ክብርን ሕይወትን ይወርሳሉና)፤» ብሎአል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፮-፯።        


15 comments:

 1. MElkam New kesis Eleh Lemanem Aytekmem Kale hiwot Yasemalen.F.

  ReplyDelete
 2. Girum timihrt, kale hiwot yaselamalin kesis. Medihanealem yabertalin!

  ReplyDelete
 3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 4. Qale Hiwot Yasemalign!!

  ReplyDelete
 5. kale hiwet yasemaln kesis betam grum tmhrt ebakewetn bezih zuriya bedenb yitafu ene egziabyer yimesgn tiru yetdar megbabat alen neger gn bebalebet alebabes hulgize enchekachekalen enam yemilebsew enen des yemayl new enenm mnm blebs mnm aylem enem egziabher ymesgen bebete krstiyan sletegaban kesreat yeweta lbs melbes alwedm enam esu des endemlew akalehu ene gn yetchemadede melbes menfesawunet new blo yamnal enam ene endlebs baygefafagnm esu gn ylebsal enam kebetesebe sayker tichit yedersbgnal ena ebakh yhn astekakl slew aysemagnm endawum yibas blo yemiyanadedegn yadergal enam yhew 5 amet hone chigra chinn sanfeta esti slealebabes beteley yewendoch krstiyanawuye alebabes yetechemadede mehon alebet yemil kale asredugn

  ReplyDelete
 6. kalehiwot yasemalin

  ReplyDelete
 7. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 8. kala heiwate yasamalene

  ReplyDelete
 9. kalehiwot yasemalen

  ReplyDelete
 10. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
  ድኅረ ገጾን በተቻለኝ እየተከታተልኩ ነዉ።
  ለዛሬ አንድ ጥያቄ አልኝ፤መልሱን እጠብቃለሁ።
  በቁርባን ያልተጋቡ ባልና ሚስት ለመጀመሪያ ጊዜ ለቁርባን ሲቀርቡ በአንድነት መሆን እንዳለበት ተዋህዶ ሃይማኖታችን ታስተምራለች፤ሆኖም አንዳንድ ግለሰቦች አንዳቸዉ ባል ወይም ሚስት በቅድሚያ ንስሐ ገብተዉ ከተዘጋጁ ተለያይተዉ መቁረቡን አምናለሁ ይላሉ።መከራከሪያ ነጥባቸዉ በፍርድ ቀን ነፍሳችን ተለያይታ በጌታዋ ፊት ለፍርድ ትቀርባለች እንጂ በአንድነት ትቀርባለች አይልም ይላሉ።
  ብዙ ምእመናን በዚህ መልኩ ከክቡር ሥጋዉና ከክቡር ደሙ ከመቀበል እየታቀቡ ሊሆን ስለሚችል ትምህርቱን በሰፊዉ ከእርሶ እንጠብቃለን።
  ፈጣሪ በእርሶ አድሮ እንዲያስተምረን ፈቃዱ ይሁንልን።
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  ReplyDelete
 11. kal hiwoten yasemalen

  ReplyDelete
 12. ቃለ ህይወት ያሰማልን እግዚያብሄር አምላክ እንደዚህ አይነት አባቶቻችንን አያሳጣን

  ReplyDelete
 13. አባታችን ቡራከዎት ይድረሰን፣ ቃለ ህይዎት ያሰማልን፦
  በጣም ልብ የሚነካ ትምህርት ነው፣ደስ ይላል፣
  አሁንም በትዳር ፣በማህበራዊ ንሮ፣በቤተሰብ ዙሪያ ትምህርት ያስፈልገናል
  በተልይ በውጭ ሃገር የምንኖር ክርስትያኖች
  ቅዱስ ዕግዚአብሄር ጸጋውን ያብዛልን።

  ReplyDelete
 14. kal hiwoten yasemalen

  ReplyDelete