Monday, July 18, 2011

ነገረ ቅዱሳን፦ ክፍል ፲፬

የእግዚአብሔር ምስክርነት (ለ)
ካለፈው የቀጠለ  . . .
፩፥፯፦ በእንተ አሮን፤
አሮን፦ የሙሴና የማርያም ወንድም ነው፤ ዘጸ ፮፥፳፣ ዘኁ ፳፮፥፶፱። እግዚአብሔር ለሙሴ ተገልጦ፥ ምልክት አስጨብጦ፥ ወደ ግብፅ እንደሚልከው በነገረው ጊዜ፥ « ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ ትናንት፥ ከትናንት ወዲያ ባሪያህን ከተናገ ርኸኝ  ጀምሮ አፈ ትብዕ (አንደበተ ርቱዕ) ሰው አይደለሁም። እኔ አፈ ኰልታፋ፥ ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ።» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፦ «ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? ዲዳስ፥ ደንቆሮስ፥ የሚያይስ፥ ዕውርስ የሚያደርግ ማን ነው? እኔ እግ ዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም አንደበትህን አረታለሁ፤ ትናገረውም ዘንድ ያለህን አለብምሃለሁ፤ (ልብ እንድትል አደርግሃለሁ)፤» አለው። ሙሴም መልሶ፦ «ጌታ ሆይ እማልድሃለሁ፤ መናገር የሚችል የምትልከው ሌላ ሰው ፈልግ፤» አለ። እግዚአብሔርም በሙሴ ላይ እጅግ ተቆጥቶ፦ «ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ እንደሚና ገርልህ አውቃለሁ፤ እነሆም፥ እርሱ ሊገናኝህ ይመጣል፤ በአየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ፤ ቃሌንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ አንደበትህንና አንደበቱን አረታለሁ፤ የምታደርጉትንም አለብማችኋለሁ። (ልብ እንድትሉ አደርጋች ኋለሁ)። እርሱ ስለ እናንተ ከሕዝቡ ጋር ይነጋገራል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል፤ አንተም በእግዚአብሔር ዘንድ ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግበትን በትር ያዝ፤» ብሎታል። ዘጸ ፯፥፩-፪።
ሙሴ ወደ ፈርዖን በቀረበ ጊዜ፥ ከዚያም በኋላ የአርባው ዓመት የምድረ በዳ ጉዞ እስኪያልፍ ድረስ፥ አሮን፦ ሙሴ በሚሠራው ሥራ ሁሉ የቅርብ ረዳቱ ነበር። የእስራኤል ልጆች ከአማሌቅ ጋር በተዋጉ ጊዜ አሮንና ሖር ለጸሎት የተዘረጋ የሙሴን እጆች ይደግፉ ነበር። ዘጸ ፲፯፥፱-፲፪። እስራኤል ዘሥጋ በዳታን በአቤሮን እና በቆሬን መሪነት በሙሴና በአሮን ላይ (የሙሴን ምስፍና፥ የአሮንንም ክህነት በኃይል ለመንጠቅ) በተነሡ ጊዜ እግዚአብሔር ተቆጥቶባቸው ነበር። ከእስራኤልም ልጆች በምክር የተመረጡ፥ ዝናቸውም የተሰማ ሁለት መቶ ሃምሣ የማኅበሩ አለቆች ከዓመጻኞቹ ጋር ተሰልፈው ነበር። ሙሴንና አሮንንም፦ «ለአናንተ ይበቃችኋል፤ (እናንተ ከሌላው ሕዝብ በምንም አትለዩም)፤ ማኅበሩ፦ (ሕዝቡ) ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና፤ በእግዚአብሔርስ ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?» አሉአቸው። ሙሴ ግን በፍጹም ትኅትና በግንባሩ ከፊታቸው ተደፍቶ ለመናቸው፥ ፍርዱንም ከእግዚአብሔር እንዲጠብቁ (ቅዱሳን የሆኑትንና ያልሆኑትን እንዲያሳያቸው) ወደ እርሱ አሰናበታቸው። ቆሬንና ሁለቱ መቶ ሃምሣዎቹ ሰዎች ሊያጥኑ በድፍረት ወደ ታቦተ ጽዮን በገቡ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንደተለበለበ ግንድ ሆኑ፥ ሁሉም በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ። ዳታንና አቤሮን ቤተሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ከብቶቻቸውንም ሁሉ መሬት ተከፍታ ዋጠቻቸው። እነርሱም፥ ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፤ በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ፥ «ምድሪቱ እንዳትውጠን» ብለው ሸሹ።
በነጋውም የእስራኤል ልጆች የተደረገውን ተአምራት አይተው ከክፋት ከመመለስ ይልቅ፦ «እናንተ የእግዚአብ ሔርን ሕዝብ ገድላችኋል፤» ብለው በሙሴና በአሮን (እግዚአብሔር በመረጣቸውና በመሰከረላቸው ቅዱሳን) ላይ አጉረመ ረሙ።» በዚህን ጊዜ፥ እግዚአብሔር በደመና ዓምድ ወረደ፥ በመገናኛው ድንኳን ላይ ክብሩን ገለጠ። ሙሴንና አሮንንም፦ «ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ፤» አላቸው። እነርሱም እግዚአብሔርን ስለ ሕዝቡ ሊማ ልዱት በግንባራቸው ወደቁ። መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፥ ነገር ግን በሙሴ አማላጅነት፥ በአሮንም ማዕጠንት ቆመ። በቆሬ ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ይህ ሁሉ የሆነው እግዚአብ ሔር ለቅዱሳኑ ሲመሰክርላቸው ነው። ዘኁ ፲፮፥፩-፶። ከዚህም ሌላ፦ በእግዚአብሔር ትእዛዝ በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ ወደ ቤተ መቅደስ ከገቡት አሥራ ሁለት ደረቅ በትሮች መካከል፥ በሙሴ ጸሎት የአሮንን በትር እንደትለመልም፥ እንድታብብና ለውዝ እንድታፈራ በማድርግ መስክሮላቸዋል። ሙሴም በትሮቹን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፤ እያንዳንዱም ደረቅ በትሩን ወሰደ። እግዚአብሔርም፦ «ማጉረምረማቸው፤ ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ፥ እነርሱም እንዳይሞቱ ለማይሰሙ ልጆች ምልክት ሆና ትጠብቅ አንድ የአሮንን በትር በምስክሩ ፊት አኑር፤» አለው። ዘኁ ፲፯፥፩-፲፪። ሳይተክሏትና ውኃ ሳያጠጧት ለምልማ፥ አብባና አፍርታ የተገኘች፥ በቤተ መቅደስም የኖረች የአሮን በትር፥ እንበለ ዘርዕ ፀንሳ አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት።
፩፥፰፦ በእንተ ኢያሱ ወአልዓዛር፤
እግዚአብሔር፦ የነቢያት አለቃ የሆነውን ሙሴን ወደ ናባው ተራራ ጠርቶት በዚያ እንደሚሞት በነገረው ጊዜ፥ ያሳሰበው ትልቅ ነገር ቢኖር፥ ከእርሱ በኋላ ማን እንደሚተካው ነበር። በመሆኑም፦ «የሥጋና የነፍስ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር፥ በዚህ ሕዝብ ላይ የሚሆነውን ይሹም፤ በፊታቸው የሚወጣውንና የሚገባውን፥ የሚያስወጣቸውንና የሚያስገባቸውንም፥ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን።» በማለት ለእግዚአብሔር ተናገረ። በዚህም ለሕዝቡ ከፊት መሪ፥ ከኋላ ተከታይ እየሆነ፥ የሚያወጣቸውንና የሚያገባቸውን (መልካም እረኛ) እንዲመርጥላቸው እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም የወዳጁን ልመና ተቀብሎ፥ «መንፈስ ቅዱስ ያለበትን (ያደረበትን) የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ (ሹመው)፤ በካህኑም በአልዓዛር ፊት አቁመው፤ በማኅበሩም ፊት እዘዘው፤ ስለ እርሱም በፊታቸው እዘዝ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ ስጠው። (ክብርህን፥ ጸጋህን፥ ሹመትህን አሳድርበት)። በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ፍርድ ይጠይቅለት፤ (በካህኑ በአልዓዛር ፊት ቁመው በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚናገረውን ፍርድ ይጠይቁለት)፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፤ በቃሉም ይግቡ። (ኢያሱና የእስራኤል ልጆች ሠራዊቱም ሁሉ በአልዓዛር ቃል ይግቡ፥ ይውጡ)፤» አለው።
አልዓዛር የስሙ ትርጓሜ «እግዚአብሔር ረድቶናል፤» ማለት ነው።ከአባቱ ከአሮንና ከተቀሩት ሦስት ወንድሞቹ ጋር በክህነት እንዲያገለግል እግዚአብሔር የመረጠው ሰው ነው። ስማቸውም፦ ናዳብ አብዩድ እና ኢታምር ይባላል። እግዚአብሔር ሙሴን፦ «አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤» ያለው ለዚህ ነበር። ዘጸ ፳፰፥፩። በመጨረሻም፦ «በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም፤» ብሎታል። ዘጸ ፴፥፴።  
            ተቀድሶ መርከስ፥ ከብሮ መዋረድ፥ ተቀብቶ ተርታ መሆን ስለሚያጋጥም፥ ናዳብና አብዩድ ሥርዓተ ቤተ መቅደስን በመተላለፋቸው፥ የእግዚአብሔርን ቤት በመድፈራቸው፥ ከሰማይ በወረደ እሳት ተቃጥለው፥ በእግዚአብሔር ፊት ሞተዋል። ዘሌ ፲፥፩-፪። አልዓዛር ግን አሮን ከሞተ በኋላ በምትኩ ሊቀ ካህናት ሆኗል። ዘኁ ፫፥፴፪። እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፥ በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ በሖር ተራራ፦ «አሮን ወደ ወገኑ ይጨመር፤ (በሞት ከሞቱት ወገኖቹ ጋር ይቀላቀል)፤ በክርክር ውኃ ዘንድ ስለአሳዛናችሁኝ እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደሰጠኋት ምድር አትገቡም። አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ በማኅበሩ ፊት ወደ ሖር ተራራ አምጣቸው፤ ከአሮንም ልብሱን አውጣ፤ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኖቹ ይጨመር፤ በዚያም ይሙት።» ብሎት ነበር። ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ። ዘኁ ፳፰፥፳፪-፳፱።
ኢያሱ፦ የስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር አዳኝ (መድኃኒት) ማለት ነው። ከግብጽፅ የወጣው ገና ታናሽ ብላቴና እያለ ነው። አያቱ ኤሊሳማ የኤፍሬም ነገድ አለቃ ነበረ። ፩ኛ ዜና ፯፥፳፮-፳፯፣ ዘኁ ፩፥፬-፲። ኢያሱ፦ በሙሴ ትእዛዝ ከአማሌቃውያን ተዋግቶ አሸንፏል፤ የረዳውም የሙሴ ጸሎት ነው። ዘጸ ፲፯፥፰-፲፫። (አማሌቃውያን፦ ከአማሌቅ የተገኙ ነገዶች ናቸው፥ ከእስራኤል አገር በስተደቡብ በኲል ይኖሩ ነበር። ከሙሴ እስከ ሕዝቅያስ ዘመን ድረስ እስራኤልን ይቃወሙ ነበር። ዘጸ ፲፯፥፰፣ መሳ ፫፥፲፫፣፮፥፫። ፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፫፣ ፩ኛ ዜና ፬፥፵፫። አማሌቅ የዔሳው የልጅ ልጅ ነው። ኢያሱ፦ በሙሴ እግር እግዚአብሔር እስኪተካው ድረስ የሙሴ አገልጋይ ነበር። ዘጸ ፳፬፥፲፫፣ ፴፪፥፲፯፣፴፫፥፲፩፣ዘኁ ፲፩፥፳፰። ሙሴ ምድረ ርስትን እንዲሰልሉ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ከላካቸው አሥራ ሁለቱ ሰዎች መካከል አንዱ ኢያሱ ነበር። ኢያሱና ካሌብ እግዚአብሔር ምድረ ርስትን እንደሚያወርሳቸው በእምነት በመናገራቸው የተስፋው ወራሾች ሆነዋል። ዘኁ ፲፫ እና ፲፬። በመጨረሻም በሙሴ እግር ተተክቶ የእስራኤል መሪ ሆኗል። ዘኁ ፳፯፧፲፭_፳፫፤ ዘጸ ፫፧፳፱፣፴፩፥፳፫።
እግዚአብሔርም፦ «በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም። ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ በርታ፤ አገልጋዬ ሙሴ እንደአዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አንብበው፣ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል፤ አስተዋይም ትሆናለህ። እነሆ አዝዝሃለሁ፤ በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም።» ብሎታል። ኢያ ፩፥፭-፱። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ተገልጦለታል። ኢያ ፭፥፲፫። በመጀመሪያ እግዚአብሔር፥ ሁለተኛም የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ያበረታቱት ኢያሱ በታቦተ እግዚአብሔር ላይ በተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ ለሁለት ከፍሎታል፥ የኢያሪኮንም ግንብ አፍርሷል። ኢያ ፫፥፩-፲፯፣ ፮፥፩-፳፯። ከኢያሪኮ ነገሥታት ጋር በሚዋጉበትም ጊዜ፥ «በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፤ በኢሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤» አለ። እግዚአብሔርም አደረገለት። ኢያ ፲፥፲፪-፲፫።
ከታሪኩ እንደምንረዳው፥ በመስፍኑ በሙሴ እግር ኢያሱን የተካ፥ በካህኑ በአሮንም ፈንታ ልጁን አልዓዛርን የተካ እግዚአብሔር ነው። መተካት ብቻ ሳይሆን፥ ስለ ኢያሱ፦ «መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነው፤» በማለት መስክሮታል። ስለ አልዓዛርም፦ «ኢያሱና የእስራኤል ልጆች ሠራዊቱም ሁሉ በአልዓዛር ቃል ይግቡ፥ ይወጡ፤ (ይታዘዙለት)፤» በማለት መስክሮለታል። ከዚህም ክህነት ከፍ ያለ ሥልጣን መሆኑን እንማራለን። አስተማሪውም እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም፦ የዚህ ዓለም መሳፍንት «በዚህ ውጡ፥ በዚህ ግቡ፤» እያሉ እንደ ጠፍ ከብት ሲነዱን፥ እንደ በግ ሲጐትቱን ልናፍር ይገባናል። ከሁሉም የሚያሳፍረው መነዳታችንና መጐተታችን በፈቃዳችን መሆኑ ነው።
፩፥፱፦ በእንተ ባስልኤል ወኤልያስ፤
እግዚአብሔር ሙሴን፦ «እይ! ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ።  በሥራ ሁሉ ያስተውል ዘንድ በጥበብም፥ በማስዋልም፥ በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ (መንፈሰ ረድኤትን) ሞላሁበት፤ (አሳደርሁበት)፤ የአናጺዎች አለቃ ይሆን ዘንድ ወርቅንና ብርን፥ ናስንም፥ ብጫና ሰማያዊ፥ እጥፍ ሆኖ የተፈተለ ነጭና ቀይ ሐርን ይሠራ ዘንድ፤በሥራውም ሁሉ የሚደረገውን የድንጋይ ማለዘብ፥ ከእንጨትም የሚጠረበውን ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ፥ ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ። (ኤልያብን ለባስልኤል አጋዥ አድርጌ ሰጠሁት)፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ዕውቀትን ሰጠሁ ። የምስክሩን ድንኳን፥ የቃል ኪዳኑንም ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን መግጠሚያም ይሠሩ ዘንድ)፤ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፤ (ንዋየ ቅዱሳቱን) የዕጣን መሠዊያውን፥ ገበታውንም፥ ዕቃውንም፥ ከዕቃውም ሁሉ የነጻውን መቅረዝ፥  (ዕጣን የሚታጠንበት ማዕጠንቱን ፋና የሚበራበት መቅረዙን ከጠራ ወርቅ ይሠሩ ዘንድ፤ አዕፁቋን ምንባረ ፈትሏንም ይሠሩ ዘንድ)፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ (ስብ የሚጤስበት ምሥዋዓ  ብርቱን መሣሪያውንም ሁሉ ይሠሩ ዘንድ)፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም፥ (ኲስኲስቱን ከነመቀመጫው)፥ በክህነት አኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥ የሚቀቡትንም የቅብዐቱንም ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚያጥኑትን ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ ፤» ብሎታል። ዘጸ ፴፮፥፩-፲፩። በዚህም ለባስሌኤልና ለኤልያብ፦ መንፈሰ ረድኤትን እንዳሳደረባቸው፥ ጥበብን እንደሰጣቸውና እውቀትንም እንደገለጠላቸው መስክሮላቸዋል።
ይቀጥላል . . .  

6 comments:

 1. e/r yestelen... Ye'abrehamen edme yadelelen

  ReplyDelete
 2. kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 3. የጀመረውን ማስጨረስ ልማዶ የሆነው ዓምላክ ይርዳወት።ትልቅ ትምህርት ነው።
  ቃለ ሂወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 4. የጀመረውን ማስጨረስ ልማዶ የሆነው ዓምላክ ይርዳወት።ትልቅ ትምህርት ነው።
  ቃለ ሂወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 5. welete michael

  kale hiwot yasemalen tesfa mengiste semayat yawrsilen

  ReplyDelete