Tuesday, July 5, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፬

፦ “ የበኩር ልጅዋንም እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” ማቴ ፩፥፳፭
ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከመናገራችን በፊት፥እርሷ የእግዚአብሔር ብቻ ቤተመቅደስ፥ የ እግዚአብሔር ብቻ እናት፥ የእግዚአብሔር ብቻ ዙፋን፥ እንደሆነች ማመን ያስፈልጋል። ነቢዩ ሕዝቅኤል ይኸንን ታላቅ ምሥጢር በብሉይ ኪዳን ዘመን ኾኖ፥ዐረፍተ ዘመን ሳይጋርደው ተረድቶት ነበር። ያስረዳውም እግዚአብሔር ነው። እንዴት እንዳስረዳው ሲናገርም፦ “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደ አለው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ተዘግቶም ነበር።
እግዚአብሔርም አንዲህ አለኝ፥ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች፥ አለኝ” ብሏል። ሕዝ ፵፬፥፩-፪ ይህች፦ ሕዝቅኤል በመንፈሰ ትንቢት አሻግሮ ያያት፦ የተዘጋች፥ የታተመች፥ የተቈለፈች ምሥራቃዊት ቤተ መቅደስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለሕዝቅኤል እንደነገረው ሰው ከቶ ሊገባባት የማይቻለው የእግዚአብሔር ብቻ ልዩ ቤተ መቅደስ ናት። እርሱ ብቻ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወጥቷል። (በድንግልና እንድትጸንሰው በድንግልናም እንድትወልደው አድርጓል)። ቅዱስ ዳዊትም፦ በጾምና በጸሎት የተገለጠለትን ምሥጢር ሲናገር፦ “እግዚአብሔር ጽዮንን (ለሥጋም ለነፍስም፥ ለጻድ ቃንም ለኃጥአንም መጠጊያ የምትሆን ድንግል ማርያምን) መርጦአታልና፥ ማደሪያውም (እናቱ፥ዙፋኑ፥መቅደሱ) ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ አለ፤” ብሏል። መዝ ፻፴፩፥፲፫-፲፬። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለዳዊትም እንደነገረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ ማኅደርነት እስከምት ወልደው ድረስ ብቻ አልነበረም ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ፦ “ይህች ለዘዓለም ማረፊያዬ ናት፤” ብሎአልና ነው። በመሆ ኑም በድንግልና እንደፀናች ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ ስትባል የምትኖር እንጂ ወደ ወላዲተ ሰብእነት የምትመለስ አይደለችም።
፪፦ በኲር፤
በኲር የሚባለው በመጀመሪያ የሚወለድ ነው። ተከታይ ልጅ ኖረውም አልኖረውም፥ በመጀመሪያ የሚወለድ የሰውም ሆነ የእንስሳት ልጅ በኲር ይባላል። ብኲርና ታላቅ በመሆኑ፥ የበኲር ልጅ ርስት (ሀብት፤ንብረት) ሲካፈል የሚደርሰው ሁለት እጥፍ ነው። ዘዳ ፳፩፥፲፭-፲፯። በወንድሞቹም ላይ ጌታ ነው፡፡ ዔሳው ብኲርናውን አቃልሎ፥ ለወንድሙ ለያዕቆብ በምሥር ንፍሮ ለውጦ፥ በረከትን በማጣቱ፥ “አባቴ ሆይ፥ ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን?” ብሎ ነበር። አባቱ ይስሐቅ ግን፦“እነሆ ጌታህ አደረግሁት፤ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች አደረግኋቸው፤ ወይኑንና ዘይቱንም አበዛሁ ለት፤” ሲል መልሶለታል። ዘፍ ፳፯፥፴፮። በኦሪቱ ለሰዎችም ለእንስሳትም የበኲራት ቤዛ ልዩ ልዩ ሕግ ነበረ፤ ዘኊ ፫፥፵፪-፶፩፤፲፰፥፲፭-፲፯
ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ ፥ቅዱስ ዮሴፍን ፦ “የበኲር ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” ማለቱ ስለ ብዙ ነገር ነው። በመሆኑም የመፍቻውን (የመተርጐሚያውን) ቁልፍ ማግኘት ያስፈልጋል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን፦ “ ከእናንተም ጋራ ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ። ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።” እንዳላቸው መንፈስ ቅዱስ ምሥጢር ገላጭ ነው።አባቶቻችን ይህንን የምሥጢር ቁልፍ በማግኘታቸው በአፍም በመጽሐፍም አስተምረው አልፈዋል። ዮሐ ፲፬፥፳፭። እንግዲህ እንደ አባቶቻችን አማናዊ ትምህርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ “በኲር የሚሆን ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” መባሉ፦
፪፥፩፦ የመጀመሪያ ልጇን እስከምትወልድ ድረስ ማለት ነው፤
ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ፥ መተርጎምና ማመስጠር በማያስፈልገው ደረቅ የትንቢት ቃል፦ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም (ወልድን) ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ብሎ በተናገረው መሠረት ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን የመጀመሪያ ልጇን ወልዳለች። ኢሳ፯፥፲፬።  በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷም በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው። ይህንንም ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል የእርሷ መፅነስና መውለድ እንደ አንስተ ዓለም አለመሆኑን አስቀድሞ ሲነግራት፦ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤(በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው)፤” ብሏት ነበር። ሉቃ ፩፥፴፭። በከብቶች በረት በወለደችውም ጊዜ፦ “ እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።” የሚል የቅዱሳን መላእክት ብሥራት ለእረኞች ተነግሯቸዋል። ሉቃ ፩፥፲።
          አንዳንድ ጊዜ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በኲር(የመጀመሪያ) ካለ ቀጣይ ልጅ እንደአለ አያመላክትም ወይ? የሚሉ አሉ። ለእነዚህም፥ ማለትም ባለማወቅ ለሚጠይቁትም ሆነ በክፋት ለሚጠይቁት አባቶቻችን በቅንነት መልስ ሰጥተዋል። ይህም መልስ፦ ለእነዚህ (በቅንነት ለሚጠይቁት) ትምህርት፥ ለእነዚያ (በክፋት ለሚጠይቁት) ደግሞ ተግሳፅ ነው።
፪.፪፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ የበኲር ልጅ ነው
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበኲር ልጅነቱ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ሳይሆን ለባሕርይ አባቱ ለእግዚአብሔር አብም ነው። ይህም፦ “እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ እኔም ዛሬ ወለድሁህ።” በሚለው ቃለ እግዚአብሔር ታውቋል። መዝ ፪፥፯። እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድን (ኢየሱስ ክርስቶስን)፥ “አንተ ልጄ ነህ፤” ማለቱ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ መወለዱን፥ የአብ የበኲር ልጅ መሆኑን ያመለ ክታል። “እኔም ዛሬ ወለድሁህ፤” የሚለው ደግሞ፤ ድኅረ ዓለም ያለ አባት፤ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለ ዱን፤ ለእመቤታችንም የበኲር ልጅ መሆኑን የሚያመለክት ነው።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ይዞ የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት፥ ፈጣሪነት፥ ከባህርይ አባቱ ከአብ ጋር ትክክል መሆኑን፥ ሲመሰክር ፦ ”ከጥንት ጀምሮ እግዚአበሔር በብዙ ዐይነት እና ጎዳና (ብብዙ ኅብረ ምሳሌና በብዙ ኅብረ ትንቢት)   ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ። በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን። እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የመልኩ ምሳሌ ሆኖ፥ (እግዚአብሔር አብን በባሕርይ የሚመስለው የባሕርይ ልጁ ስለሆነ፥ በክብርም ስለሚተካከለው)፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ (ከባሕርይ አባቱ ጋር በሥልጣን አንድ ስለሆነ) ኃጢአታችንን በራሱ (በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ ባፈሰሰው ደሙ፥ በቆረሰው ሥጋው፥ አሳልፎ በሰጠው ነፍሱ) ካነጻ በኋላ፥ በግርማው ቀኝ (በአብ ቀኝ፥ ከአብ ተካክሎ) ተቀመጠ። በዚህን ያህል መብለጥ (ፈጣሪ እንደመሆኑ) ከመላእክት በላይ ሆኖ (ፈጣሪያቸው፥ ገዢያቸው በመሆኑ) ከስማቸው የሚበልጥና የሚከብር ስምን ወረሰ። (የእርሱ ስም ፍጡር የማይጠራበት የፈጣሪ ስም ነው)። ከመላእክትስ ከሆነ ጀምሮ፥ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤ ዳግመኛም እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማነው? ዳግመኛም በኲርን ወደ ዓለም በላከው ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል፥ አለ። ስለ መላእክቱም፥ መላእክቱን ነፋሳት፥ የሚላኩትንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፥ አለ። ስለ ልጁ ግን፥ ጌታ ሆይ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ በትር ነው፥ አለ፤» ብሏል። ዕብ ፩፥፩-፰፣ ፪ኛ ሳሙ ፯፥፲፬፣ ፩ኛ ዜና ፲፯፥ ፲፫፣ ዘዳ ፴፪፥፵፫፣ መዝ ፩፻፫፥፬፣ መዝ ፵፬፥፮-፯። እንግዲህ ለእግዚአብሔር አብ «የበኲር ልጅ»፥ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ተቀዳሚም ተከታይም የሌለው የአብ የባሕርይ ልጅ እንደሆነ ሁሉ፥ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ ልጅ ነው።
፪፥፫፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን በኲር ነው፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱሳን አምላክ ነው። ቅዱስ ቶማስ፦ በዓይኖቹ አይቶ፥ በእጆቹ ከዳሰሰ በኋላ «ጌታዬ፥ አምላኬም» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፥፳፰። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም፦ «የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው»። ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እኒህም ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥ ተስፋም የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው። እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፥ አሜን፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፬-፭።
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የባሕርይ አምላክ ብሎ የሚያምንበትን ኢየሱስ ክርስቶስን «የቅዱሳን በኲር፤» ብሎታል። ይኽንንም፦ «መንፈስ ቅዱስም ከድካማችን ይረዳናል፤ እንግዲያስ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል። እርሱም ልባችንን ይመረምራል፤ ልብ የሚያስበውንም እርሱ ያውቃል፤ ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ (በሕልውና ከአብ ከወልድ ጋር አንድ ሆኖ) ይፈርዳል። እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። ልጁ (የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ) በብዙ ወንድሞች (በቅዱሳን) መካከል በኲር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል። ያዘጋጀውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን  አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ፤» በማለት አብሯርቷል። ሮሜ ፰፥፳፮-፴።
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን፥ «ለቅዱሳን በኲር» ያለው ለበጎ ነገር ሁሉ ምሳሌያቸው፥ አብነታቸው እርሱ ስለሆነ ነው። ምክንያቱም የተከተሉት የእርሱን መንገድ ነውና። የሰማዕታት አለቃ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊገድሉት በድንጋይ ሲቀጠቅጡት፦ «ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል፤ . . . አቤቱ፥ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው፤» ያለው የጌታውን መንገድ ሲከተል ነበር። የሐዋ ፯፥፶፱-፷። ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በመስቀል ላይ ሆኖ፥ «አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤. . .  አባት ሆይ፥ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ፤» ብሏልና ነው። ሉቃ ፳፫፥፴፬፣ ፵፮። ይኽንን በተመለከተ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲናገር፥ «በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ጸጋን ያገኛልና። በድላችሁ የመጣባችሁን ብትታገሡ፥ ምስጋናችሁ ምንድርነው? ነገር ግን መልካም እየሠራችሁ፥ የደረሰባችሁን ግፍ ብትታገሡ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የምታስመሰግን ይህቺ ናት። ለዚህ ተጠርታችኋልና፤ ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአል። እርሱ ኃጢአትን አልሠራም፤ በአንደበቱም ሐሰት አልተገኘበትም። ሲሰድቡት አልተሳደበም፤ መከራ ሲያጸኑበትም አልተቀየመም፤» ብሎአል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፲፱-፳፫። መምሕረ ትኅትና፥ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የደቀመዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ፦ «ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን? እናንተ መምህራችን፦ ጌታችንም ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና። እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልንጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም፤ ከላከው የሚበልጥ መልእክተኛም የለም። ይህንም ዐውቃችሁ ብትሠሩ ብፁዓን ናችሁ።» ያላቸው ለዚህ ነበር። ዮሐ ፲፫፥፲፪-፲፯። ቅዱሳንም የጌታቸውን ቃል አክብረው፥ ለበጎ ምግባር ሁሉ በኲር የሆነላቸውን አምላክ መንገድ በመከተላቸው እርሱን መስለው ተገኝተዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው (እንደመሰልኩት) እኔን ምሰሉ፤» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆር ፲፩፥፩። «ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔን እንድትመስሉ እማልዳችኋለሁ፤ ስለዚህም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዳስተማርሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሄድሁበትን መንገድ ይገልጣላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር የታመነና ልጄ ወዳጄ የሆነ ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ።» ያለበትም ጊዜ አለ። ፩ኛ ቆሮ ፬፥፲፮። በፊልጵስዩስ መልእክቱም ላይ «ፍፁማን የሆናችሁ ሁላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖር፥ እርሱን እግዚአብሔር ይገልጥላችኋል። ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ። ወንድሞቼ ሆይ፥ እኔን ምሰሉ፤ እንዲህ ባለ መንገድ የሚሄዱትንም እኛን ታዩ እንደነበረበት ጊዜ ተጠባበቁአቸው፤» ብሏል። ፊል ፫፥፲፯፡፡

ይቀጥላል፤ . . .

8 comments:

 1. I heard you lost some of your books and persoal stuff May God help u , Do not worry , Berta berta berta , This how we know we are son of God berta

  ReplyDelete
 2. ቃለ ህይወትን ያሰማልኝ መንግስተ ሰማያትን ያውርስልኝ!!!!
  Sara Adera

  ReplyDelete
 3. kale hiwot yasemalen

  ReplyDelete
 4. Kale hiwot Yasemalen Yagelglot zemenehih Yabzaleh

  ReplyDelete
 5. Kalehiwot yasemalin

  ReplyDelete
 6. kalehiwot yasemalen egzeabehere yanurelen

  ReplyDelete
 7. kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete