Sunday, June 26, 2011

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል፦ ፱

፩፦ የወላጆች ጠባይ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ፤

በሁሉ ዘንድ እንደሚታወቀው፥ ልጆች የሚያድጉት የወላጆቻቸውን ጠባይ እና ምግባር ይዘው ነው። ከልጅነት ጀምሮ የሚያዩትን የሚሰሙትን ገንዘብ አድርገው ያድጋሉ። ክፉም ቢሠሩ በጎም ቢሠሩ በወላጆቻቸው ዘንድ ያዩትን ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድን፦ «እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ።» በማለት ስለ ክፉ ሥራቸው የወቀሳቸው ለዚህ ነው። እነርሱም፦ «አባታችን አብርሃም ነው፤» ብለው መለሱለት። ጌታ ግን፦ «የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር፤» ብሎአቸዋል። ዮሐ ፰፥፴፰-፴፱።
          እመቤታችንን እና ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዞ ወደ ምድረ ግብፅ ተሰዶ የነበረ ጻድቅ ሰው ዮሴፍ፦ ከመልአከ እግዚአብሔር ሰምቶ ወደ እስራኤል ተመልሷል። ሲሄድም ሲመለስም እናቱንና ልጁን (ጌታን እና እመቤታችንን) ይዞ ነው። መልአኩ የነገረው፦ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት (እነ ሄሮድስ) ሞተዋልና ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ፤» ብሎ ነው። የእመቤታችን አገልጋይ ጻድቁ ዮሴፍ ግን በአባቱ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ ሀገር ሄደ፤ በነቢያት፦ ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ። ዮሴፍ የፈራው የክፉ ልጅ ክፉ ብሎ ነው። ማቴ ፪፥፲፱። በአንጻሩም የደግ ልጅ ደግ ነው። «ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤» ብሎ ቅዱስ ሉቃስ የጻፈላቸው፥ ጻድቁ ካህን ዘካርያስ እና ቅድስት ኤልሳቤጥ ልጃቸው ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ወላጆቹ ደግ እና ትሑት ነበር። ቅድስት ኤልሳቤጥ የአምላክ እናት እመቤታችን በጎበኘቻት ጊዜ አይገባኝም ብላለች። ቅዱስ ዮሐንስም የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ እጅ ሊጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ በመጣ ጊዜ አይገባኝም ብሏል። ማቴ ፫፥፲፬፣ ሉቃ ፩፥፮-፵፫።
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤» እንዳለ ወላጆች የምናጭደው ያንኑ የዘራነውን ነው። እኛን መስለው ያድጋሉ፥ እኛን መስለውና ሆነው ይኖራሉ። ገላ ፮፥፯። ጌታችን በወንጌል፦ «መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፯፥፲፯።
፩፥፩፦ ኃይለኝነት፤
          ጥሎባቸው ኃይለኞች የሆኑ ወላጆች አሉ። በዚህም ምክንያት እንኳን ልጆቻቸው፥ ጎረቤትም፥ አላፊ አግዳሚውም ይፈራቸዋል። ጠባያቸው አርዕድ፥አንቀጥቅጥ ነው። ፊታቸው ከባድ ነው፤ እየሳቁ፥ እየተጫወቱም ቢሆን ያስፈራሉ። ኃይለኞችን የትዳር ጓደኞቻቸው ሳይቀሩ ይፈሯቸዋል። አብረው የሚኖሩት የእህል ውኃ ነገር ሆኖባቸው ነው። በመካከልም ልጆች ስለሚፈጠሩ፥ «ጎሽ ለልጆቿ ስትል ተወጋች፤» የሚለውን እየጠቀሱ ችለው ይኖራሉ። በሂደትም ሰው እስኪገርመው ድረስ ይለምዱታል። የማይለመድ ነገር የሚለመደው ሰው ኅሊናውን ሲያሳምን ነው። ኅሊናቸውን ማሳመን የተሳናቸው ግን እስከ መለያየት የሚደርሱበት ጊዜ አለ።
          ኃይለኞች ሰዎች በውስጣቸው የሚታበዩበት ነገር አያጡም። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤» ብሏል። እነዚህ፦ሀገር ያወቃቸው፥ ፀሐይ የሞቃቸው ኃይለኞች ናቸው። ከእነዚህም ሌላ የማይታወቅባቸው ኃይለኞች አሉ። እነዚህኞቹ በውጭ በሰው ዘንድ የሚታወቁበት ጠባይ ሌላ፥ በቤት ወስጥ ያላቸው ጠባይ ደግሞ ሌላ ነው። ዓመላቸውን በጉያ መያዝ ይችሉበታል። «ለውጭ ሰው አልጋ፥ ለቤት ሰው ቀጋ፤» ናቸው። እነዚያ ፀሐይ የሞቃቸው ኃይለኞች ለኃይለኝነታቸው ቦታ አይመርጡም፥ እነዚህ ግን ቦታ ይመርጣሉ፥ ስለዚህ አይታወቅባቸውም። እንዲያውም «የእገሌ ሚስት ታድላ፥ የእገሊት ባል ታድሎ፥ የእነ እገሌ ልጆች ታድለው፤» ይባልላቸዋል። ከቤታቸው ጣራ በታች በሚኖሩት ኑሮ ግን ያልታደሉ ናቸው። እነዚህ እንደነዚያኞቹ፦ «ምን ፈረደበት? ምን ፈረደባት? ምን ፈረደባቸው?»የማይባልላቸው ናቸው። ገበናቸውን ሸፍነው እየተቃጠሉ ይኖራሉ። «ላይችል አይሰጥ፤» እንደሚባል ያስችላቸዋል።
          እንግዲህ እነዚህን ከመሰሉ ሰዎች የተወለዱ ልጆች አድገው ለትዳር ሲበቁ፥ ወደ ትዳር ዓለም ይዘውት የሚገቡት ጎጆ መውጫ ይኽንን ኃይለኝነት ነው። ይህም ለሥጋዊውም ሆነ ለመንፈሳዊው ኑሮ ትልቅ ፈተና ነው። በቤታቸው፥ በሰፈራቸው፥ በዕድራቸው፥ በዕቁባቸው፥ በሥራ ቦታቸው ሁሉ ኃይለኛ ይሆናሉ። በቤተ ክርስቲያንም፦ በሰንበት ት/ቤት፥ በሰበካ ጉባኤ፥ ኃይለኛ ይሆናሉ። ሰውን ማፈር፥ እግዚአብሔርን መፍራት የለም። በቅርብ የሚያውቅ ሰውም «በአባቱ ወይም በእናቱ ወጥቶ ነው፥ በአባቷ ወይም በእናቷ ወጥታ ነው፤» ይላል። ከዚህም ሌላ፥ «ዘር ማንዘራቸው በጠቅላላ እንዲሁ ናቸው፤» የሚባልላቸው አሉ።
ለክርስቲያኖች የሚያስፈልገን ሥጋዊ ኃይል ሳይሆን መንፈሳዊ ኃይል ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ደቀመዛሙርቱን፦ «እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤» ያላቸው ለዚህ ነው። ሉቃ ፳፬፥፵፱። ቅዱሳን ሐዋርያት አገልግሎታቸው የሰመረላቸው፥ ትምህርታቸው በተአምራት የጸናላቸው ይኽንን ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ኃይል በማግኘታቸው ነው። የሐዋ ፩፥፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «የተስፋ አምላክ እግዚአብሔርም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ ያበዛችሁ ዘንድ በእምነት ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይፈጽምላችሁ፤» ብሏል። ሮሜ ፲፭፥፲፫። ከዚህም አያይዞ፥ በዚህ ረገድ፥ ለእርሱ የተደረገለትን ሲናገር፥ «አሕዛብም እንዲያምኑ ክርስቶስ በቃልም በሥራም ያደረገልኝን እናገር ዘንድ እደፍራለሁ። በኃይልና በተአምራት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ድንቅ ሥራን በመሥራትም፥ ከኢየሩሳሌም አውራጃዎች ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እንዳስተማርሁ፥ የክርስቶስንም ወንጌል ፈጽሞ እንደሰበክሁ እናገር አንድ እደፍራለሁ። ወንጌልን ለማስተማር ተጋሁ፤» ብሏል። ሮሜ ፲፭፥፲፰-፳። የዚህን ዓለም ውጣ ውረድም መሸከም የሚቻለው፥ በዚህ ኃይል ብቻ መሆኑንም ሲናገር፦ «እኔ ችግሩንም፥ ምቾቱንም እችላለሁ፤ ራቡንም፥ ጥጋቡንም፥ ማዘኑንም፥ ደስታውንም፥ ሁሉን በሁሉ ለምጄዋለሁ፤ በሚያስችለኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ፤» ብሏል። ፊል ፬፥፲፪-፲፫። በቆሮንቶስ መልእክቱም ላይ፦ «ስለዚህም ቢሆን በብዙ ራእይ እንዳልታበይ ሰውነቴን የሚወጋ እርሱም የሚጐስመኝ (በራስ ምታት፥ በጎን ውጋት የሚያሰቃየኝ) የሰይጣን መልእክተኛ (ከሰይጣን የሆነ፥ አንድም እንደ ሰይጣን ጨካኝ የሆነ በሽታ) ተሰጠኝ። ስለዚህም ከእኔ ያርቀው ዘንድ ጌታዬን ሦስት ጊዜ ማለድሁት። እርሱም፥ ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኃይልስ በደዌ ያልቃል፤ (የሥጋ ኃይል በደዌ ይደቅቃል)፤ አለኝ። የክርስቶስም ኃይል በእኔ ላይ ያድር ዘንድ በመከራዬ ልመካ ወደድሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን፥ መሰደብን፥ መጨነቅን፥ መሰደድን፥ መቸገርንም ወደድሁ፤ መከራ በተቀበልሁ ጊዜ ወዲያውኑ እበረታለሁና።» ብሏል። ፪ኛ ቆ ፲፪፥፯-፲።
፩፥፪፦ ቊጣ፤
ውኃ በቀጠነ የሚቆጡ ሰዎች አሉ። እንዲያውም ልክ እንደ ቁም ነገር «አቶ እገሌ ወይም ወ/ሮ እገሊት ቊጡ ናቸው፤» እየተባለ ይነገርላቸዋል። የሚምሩት ሰው የለም፤ ይልቁንም ልጆቻቸው፥ የትዳር ጓደኞቻቸው፥ የቤት ሠራተኞቻቸውም ጭምር ቁርሳቸው፥ ምሳቸውና እራታቸው ቁጣ ነው። ምላሳቸው እንደ እሳት ወላፈን ይጋረፋል። ማዕድ በሀገራችን ክቡር ነው፤ ንጉሥም ቢሆን ከማዕድ ላይ መነሣት አይገባም፥ ይባላል። ቊጡ ሰዎች ግን፦ «አፈር ብላና ተነሥ፥ አፈር ብዪና ተነሺ፥ ደም ያስጠጣህና፥ ደም ያስጠጣሽና፤» ከማለት የሚከለክላቸው ኅሊና የላቸውም። ነፍስና ሥጋቸው ከቊጣ የተሠራ ይመስል በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ቦታ በሚረባውም በማይረባውም ሲቆጡ ይገኛሉ። በመሥሪያ ቤታቸውም የበታቾቻቸውንም የበላዮቻቸውንም ይቆጣሉ። በዚህ ዓይነት ቦታ ሳይመርጡ ሰውን የሚያሳቅቁ እና የሚያሸማቅቁ ብዙዎች ናቸው።
          የሚገባ ቊጣ እና የማይገባ ቊጣ አለ። ልጆች ከሃይማኖት እና ከምግባር ውጪ ሆነው እንዳያድጉ፥ ሠርቶ ቀጥቶ ማሳደግ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራል። በመጽሐፈ ምሳሌ፦ «በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ . . ልጁን የሚወድ ግን ተግቶ ይገሥጸዋል።. . . ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሯል፤ የተግሣፅ በትር ግን ከእርሱ ያርቃታል።. . . ሕፃንን ከመቅጣት ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታው አይሞትምና። በበትር ትመታዋለህ፥ ነፍሱንም ትታደጋለህ።. . . በትርና ተግሣጽ  ጥበብን ይሰጣሉ፤ ያልተቀጣ ብላቴና ግን እናቱን ያሳፍራል።» የሚል ተጽፏል። ምሳሌ ፲፫፥፳፬ ፣፳፪፥፲፭፣ ፳፫፥፲፫፣ ፳፱፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ተቈጡ፤ (ጊዜ ቢያነሣሣችሁ፥ የሚያስቆጣ ነገር ቢያጋጥማቸው ተቈጡ) ኃጢአትንም አታድርጉ፤ (ይቅር ሳትሉ ግን አትደሩ)፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ (ቊጣችሀን ሳታበርዱ አይምሽባችሁ)፥ ለዲያቢሎስ ፈንታ አትስጡት። (ለሰይጣን ምክንያት አትስጡት)።» ብሏል። ኤፌ ፬፥፳፮። በመሆኑም ሕፃናት አንማርም ቢሉ፥ ወይም የተማሩትን ቢገድፉ፥ መናፍቃን በጉባኤ እንዳይሰለጥኑ፥ ምእመናን ከሃይማኖት እንዳይወጡ፥ ከምግባር እንዳይናወጡ መቆጣት ይገባል። እንኳን ሰው እግዚአብሔርም ይቆጣል። እስራኤል ዘሥጋ በምድረ በዳ ጉዞአቸው እግዚአብሔርን አስቆጥተው ነበር። ዘዳ ፱፥፯፣ ዘካ ፰፥፲፬። «ወልድ ዋሕድ (በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው) ፥ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው፥» ብለው የማያምኑ ሰዎችም የእግዚአብሔር ቊጣ በእነርሱ ላይ ይኖራል። ዮሐ ፫፥፴፮። «እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል።» ሮሜ ፩፥፲፰። ራሳቸው ንጹሕ ሳይሆኑ በሌላው ላይ የሚፈርዱም ሰዎች የእግዚአብሔር ፍርድ በሚገለጥበት በቊጣ ቀን ቊጣን በራሳቸው ላይ ያከማቻሉ። ሮሜ ፪፥፭። በአጠቃላይ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል። ኤፌ ፭፥፮።
          በማይገባ፥ ባልሆነ ነገር፥ ዝም ብሎ መቆጣት ግን አይገባም። ይኽንንም በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅርኆች ሁኑ፤» ብሏል። ኤፌ ፬፥፳፱። ቊጣን በትዕግሥት፥ መዓትን በምሕረት መመለስ እንደሚያስፈልግም ሲናገር «እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት፤» ብሏል። ቈላ ፫፥፲፪።
          አብዛኛውን ጊዜ የሰው ቊጣ (የማይገባ ቊጣ) ከፍርሃትና ከኲራት ከስንፍናም ሊሆን ይችላል። የዔሳው ቊጣ በወንድሙ በያዕቆብ ላይ እንደ እሳት የነደደው፥ ሊገድለውም የፈለገው፥ ያለ መንገዱ ነው። ዘፍ ፳፯፥፵፭። ራሔል ልጅ ባለመውለዷ ምክንያት በተበሳጨችበት ጊዜ፥ ያዕቆብ ከማጽናናት ይልቅ መቆጣቱ ትክክል አልነበረም። ዘፍ ፴፥፪። ስምዖን እና ሌዊ በእኅታቸው ምክንያት መቆጣታቸው ትክክል ቢሆንም፥ ከገደቡ አልፎ ብዙ ደም በመፍሰሱ ግን አባታቸው ያዕቆብ አዝኖባቸዋል። በዚህም ምክንያት ከመሞቱ በፊት፦ ልጆቹን ሰብስቦ የሚመረቁትን በሚመርቅበት፥ የሚገሠጹትንም በሚገሥጽበት ወቅት፦ «ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፤ ከጉባኤያቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፤ በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና። ቊጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፤ ኲርፈታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ፤» ብሎአቸዋል። ዘፍ ፵፱፥፭-፯። ጠቢቡ ሰሎሞንም፦ «ድንጋይ ከባድ ነው፥ አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን የሰነፍ ቊጣ ይከብዳል። ቊጣ ምሕረት የሌለው ነው፥ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፤» ብሎአል። ምሳ ፳፯፥፫። የማይገባ ቊጣ የሥጋ ሥራ ነውና። ኤፌ ፭፥፳።
          እንግዲህ በቊጣ መካከል ተወልደው ያደጉ ልጆች ለትዳር ሲበቁ ኑሮአቸውን አንድ ብለው የሚጀምሩት በቊጣ ነው። እንዲያውም እስከ ጋብቻ ድረስ አይጠብቁም፥ ገና በጧቱ በተዋወቁበት እለት ቊጣ ቊጣ ይላቸዋል፤ «የቀጠሮ ሰዓት ለምን አሳለፍክ? ለምን አሳለፍሽ?» ብለው ይቆጣሉ። እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት የትዳር መቅሠፍት ነው። አድገውም፥ ትዳር ይዘውም፥ ወልደውም፥ ቊጣ ቀለባቸው የሆነባቸው ሰዎች ብዙ ናቸው፥ የተማረ ያልተማረ፥ ሀብታም ድሀ፥ ከተማ ገጠር፥ ሀገር ቤት ባሕር ማዶ፥አይልም፥ ሁሉም ያው ነው። ስለዚህ የለዘበች መልስ ቊጣን ትመልሳለች፤ . . . ስጦታ በስውር ቊጣን ታጠፋለች፥ የብብትም ውስጥ ጉቦ ጽኑ ቊጣን ታበርዳለች።» እንደተባለ ልናውቅበት ይገባል። ምሳ ፲፭፥፩ ፣ ፳፩፥፲፬።

5 comments:

 1. Kale Hiwetn Yasemawot!
  Melkam new Abatachen! Lehulachen Yemihon Timhert newena Des Belognal!
  Bertu Tsegawn Yabzalot!

  ReplyDelete
 2. that is true
  kaleyewot yasemalm
  kesis

  ReplyDelete
 3. Egziabher Tsegawen Yabzalot.Ye-Tidar guday Ye-Hager, Ye-Haimanot... yehulu mseret new. Yebelete tikuret yemisetew guday bemehonu hulachn sele Kidus gabcha tselot enadrg!
  Kale Hiwetn Yasmawot Melake Berhan!

  ReplyDelete
 4. YasadiribinYasadiribin

  ReplyDelete
 5. qale Hiwot yasemalin.Rejim yeagelglot zemen keTena gar yisTot

  ReplyDelete