Sunday, June 12, 2011

ነገረ ቅዱሳን፦ ክፍል ፲፫

ቅዱሳን፦ በቃልም በሕይወትም እስከ ሞት ድረስ እንደመሰከሩለት ሁሉ እግዚአብሔርም ለቅዱሳን መስክሮላቸዋል፥ ወደፊትም ይመሰክርላቸዋል። (ይፈርድላቸዋል)። ይኽንንም ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፤ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ። (ዘመን የወለደውን፥ ንጉሥ የወደደውን ሳይል በሰው ፊት ያመነብኝን በሰማያዊ አባቴ ፊት ልጄ ወዳጄ እለዋለሁ)።» በማለት አረጋግጦልናል። ማቴ ፲፩፥፴፪። የእግዚአብሔር ምስክርነት ከምንም በላይ የታመነ ነው። በባቢሎን ምርኮ የነበሩ እስራኤላውያን አማላጃቸውን ነቢዩ ኤርምያስን፦ «አምላክህ እግዚአብሔር ወደ እኛ የላከህን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን ታማኝ ምስክር ይሁን።» ያሉት ለዚህ ነው። ኤር ፵፪፥፭። ይልቁንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የባሕርይ አምላክነቱን ላላመኑ አይሁድ፦ «ነገር ግን ለእኔ የሚመሰክረው ሌላ ነው፤ (አብ ነው)፤ ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ አውቃለሁ።» ብሏል። ዮሐ ፭፥፴፩።
          መናፍቃን፦ ስለ ቅዱሳን መመስከር ከሰው ይመስላቸዋል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የእግዚአብሔርን ስምና ክብር መሸፈን ነው ይላሉ፥ ነገር ግን አይደለም፤ ስለ ቅዱሳን መመስከር ከእግዚአብሔር ነው። ገድላቸው፥ ተአምራቸው፥ ትምህርታቸው፥ ቃል ኪዳናቸው፥ የእግዚአብሔር ስምና ክብር የሚገልጥ እንጂ የሚሸፍን አይደለም። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከቅዱሳን አንዱ ለሆነው ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር፦ «ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእሥራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና፤» ያለው ለዚህ ነው። የሐዋ ፱፥፲፭። በመሆኑም ስለ ቅዱሳን የምንመሰክረው ምስክርነት የእግዚአብሔርን ስምና ክብር ገልጦ፥ እግዚአብሔርን የሚያስመሰግን ብርሃን ነው። ይኽንንም ራሱ ጌታችን፦ «መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።» በማለት በወንጌል ተናግሯል። ማቴ ፭፥፲፮። ይህ እግዚአብሔርን የሚያስመሰግን በሰው ፊት የሚበራ ብርሃን  የቅዱሳን ገድል ነው።
          ስለ ቅዱሳን የሚመሰከረው፦ እግዚአብሔር ጠራቸው፥ እግዚአብሔር መረጣቸው፥ የእግዚአብሔር መንፈስ አደረባቸው፥ በእግዚአብሔር ስም አስተማሩ፥ በእግዚአብሔር ስም ተአምራትን አደረጉ፥ በእግዚአብሔር ስም መከራን ተቀበሉ፥ ጾሙ፥ ጸለዩ፥ ሰገዱ፥ ወደ እግዚአብሔር አማለዱ፥ በእግዚአብሔር ስም በእሳት ተቃጥለው፥ በሰይፍ ተመትረው፥ በመጋዝ ተተርትረው፥ ለአራዊት ተሰጥተው፥ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥለው በሰማዕትነት አረፉ፤ በእግዚአብሔር ስም ከዓለም ተለይተው፥ በረሀ ወድቀው፥ ደንጊያ ተንተርሰው፥ ጤዛ ልሰው፥ ጸብአ አጋንንትን፥ ድምፀ አራዊትን፥ ግርማ ሌሊትን ሳይሰቀቁ ኖሩ፥ ተብሎ ነው። እንግዲህ ይህ ምን የተለየ ጥቅስ ያስፈልገዋል? ብሉያቱም አዲሳቱም የሚናገሩት ይኽንኑ ነው። ምክንያቱም፦ እግዚአብሔር የመረጣቸው ነቢያትና ሐዋርያትም ስለ ቅዱሳን ያልተናገሩበት ጊዜ የለምና ነው። ታዲያ ምኑ ላይ ነው፥ «ማኅበረ አጋንንት» የሚያሰኘው? ስለ ቅዱሳን የመሰከረ የሚመሰክርም እግዚአብሔርንስ ምን ሊሉት ነው? ለመሆኑ አጋንንት መቼ ነው፥ ስለ ቅዱሳን መስክረው የሚያውቁት? አጋንንት የሚታወቁበት ግብራቸው ቅዱሳንን መክሰስና በቅዱሳን ላይ መከራ ማጽናት ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ «በሰማይ ሰልፍ (ጦርነት) ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱም ዘንዶውን ተዋጉት፤ ዘንዶውም ከነሠራዊቱ ተዋጋቸው። አልቻላቸውምም፤ ከዚያም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘላቸውም። ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። በሰማይም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፥ የአምላካችን ማዳንና ኃይል፥ መንግሥትም፥ የመሢሑም ሥልጣን ሆነች፤ አባቶቻችንን (ቅዱሳንን) በእግዚአብሔር ፊት በቀንና በሌሊት ሲያጣላቸው የነበረው ከሳሽ ወድቆአልና።»የሚል ተጽፏል። ራእ ፲፪፥፲። ሰይጣን፥ ኢዮብን፦ «በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚያመልከው በከንቱ ነውን? አንተ ቤቱን በውስጥም በውጭም፥ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ አልሞላህለትምን? የእጁንም ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱንም በምድር ላይ አብዝተህለታል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።» እያለ ከስሶታል። ኢዮ ፩፥፱። በትንቢተ ዘካርያስም ላይ፦ «እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፤ ሰይጣንም ይከስሰው ዘንድ በስተቀኙ ቆሞ ነበር።» የሚል ተጽፏል። ዘካ ፫፥፩። ሰይጣን እንኳን እኛን ደካሞችን እግዚአብሔርን አንኳ ከቅዱሳን ጋር ለማጣላት የሚታገል ጉድ ነው።
          ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለው ሀገረ ገዥ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ፥ ቅዱስ ጳውሎስንና በርናባስን ወደ እርሱ አስጠርቶ ነበር። ጠንቋዩ ኤልማስ ግን አገረ ገዢውን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። (ቅዱሳኑን ከሰሳቸው)። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ተመለከተውና፦ «አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያቢሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤»አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚህን ጊዜ አገረ ገዢው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ፥» ይላል። የሐዋ ፲፫፥፯-፲፪። ይህ ታሪክ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ከቅዱስ በርናባስ ገድል አንዱ ክፍል ነው። የጻፈውም ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ነው። ከዚህ የቅዱሳን ገድል የምንማረውም በቅዱሳን እጅ የተደረገውን የጌታን ኃይልና ሥልጣን ነው። በተጨማሪም ቅዱሳንን የሚቃወሙ (የሚከስሱ) ዲያቢሎስና ልጆቹ መሆናቸውን እንማራለን። ይህ እንዲህ ከሆነ «ማኅበረ አጋንንት» እነማናቸው? ወገኖቼ! እውነቱን እውነት፥ ሐሰቱን ሐሰት ማለት ይገባል።
          ከዚህ በመቀጠል እግዚአብሔር ስለ ቅዱሳን እንዴት እንደመሰከረላቸው በአጭር በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን።
፩፥፩፦ በእንተ አቤል፤
          አቤል ከወንዱሙ ከቃየል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን (ከበጎቹ በኲራት፥ ቀንዱ ያልከረከረውን፥ ጠጉሩ ያላረረውን፥ ጥፍሩ ያልዘረዘረውን ነውር የሌለበት ጠቦት) በበጎ ኅሊና ለእግዚአብሔር አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና መሥዋዕቱ ተመለከተ። ዘፍ ፬፥፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽንን ይዞ፦ «አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው።» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፬።
፩፥፪፦ በእንተ ሄኖክ፤
          ሄኖክ ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ ነው። በሁሉ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶታል፥ ዓለምን ንቆ ከእግረ ገነት ሰባት ዓመት በጾም በትኅርምት ኖሯል። በዚህ ዓለም የኖረው ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ነው። ሄኖክ እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው አልተገኘም፤ አግዚአብሔር ሰውሮታልና። ዘፍ ፬፥፲፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንንም ይዞ፦ «ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለወሰደው አልተገኘም፤ ሳይወሰድም እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘው ተመስክሮለታል፤» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፭።
፩፥፫፦ በእንተ ኖኅ፤
          ኖኅ በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ በነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶታል፤ ደስ ማሰኘቱም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው መሆኑ ነው። እግዚአብሔር አምላክም፦ «የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤» አለው። መርከቡን ከሠራ በኋላም፦ «አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፥ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና፤» ብሎታል። ዘፍ ፮፥፱-፲፫፣ ፯፥፩። በዚህም የኖኅን ጽድቅ እግዚአብሔር እንደመሰከረለት እናያለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዚህ ላይ ተመሥርቶ «ኖኅም ስለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፤ ቤተሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላት መርከብ ሠራ፤ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ፤» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፯። የኖኅ መርከብ የቤተ ክርስቲያንም የእመቤታችንም ምሳሌ ናት።  ኖኅና ቤተሰቦቹ በመርከቧ እንደዳኑ፥ ቤተ ክርስቲያን በጸጋዋ፥ እመቤታችን በአማላጅነቷ ያድናሉ። አንድም፦ እግዚአብሔር ኖኅን እና ቤተሰቦቹን መርከቧን ምክንያት አድርጎ እንደ አዳነ፥ እመቤታችንንም ምክንያት አድርጎ ዓለምን አድኗል። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፥ እመቤታችንን፦ «ለእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መሣሪያ ሆና ተገኝታለችና፤» የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
፩፥፬፦ በእንተ አብርሃም፤
          አብርሃም እግዚአብሔርን ፈልጎ በማግኘቱ፥ «ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤» ተብሏል። ዘፍ ፲፪፥፩-፫። በዚህ ትንቢት መሠረት ከወገኑ የተወለደች እመቤት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን ለፍጥረቱ ሁሉ የምታሰጥ ሆናለች። ከእርሷ የተወለደ ኢየሱስ ክርስቶስም በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን በልግስና ሰጥቷል። ዘሩ እንደ ምድር አሸዋ እና እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዛለትም ተነግሮታል። ዘፍ ፲፪፥፲፮፣ ፲፭፥፭። በአሸዋ የተመሰሉት ከእርሱ ወገን ተወልደው ኃጥአን የሚሆኑትን ሲሆን፥ በከዋክብት የተመሰሉት ደግሞ ከእርሱ ወገን የሚወለዱ ጻድቃን ናቸው። ሥላሴን በድንኳኑ አስተናግዷል። ዘፍ ፲፰፥፩-፲፭። የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ሚስቱን ሣራን በወሰደበትም ጊዜ እንዳይቀርባት አድርጎ እግዚአብሔር ጠብቆለታል፥ ንጉሡንም በሕልም ገሥፆለታል። በመጨረሻም፦ ስለ አብርሃም፦ «አሁንም የሰውየውን ሚስት መልስ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ ዕወቅ።» በማለት ለንጉሡ ነግሮታል። ዘፍ ፳፥፩-፯። እግዚአብሔር የመሰከረው የአብርሃምን ቅድስና ብቻ ሳይሆን ጸሎቱም እንሚያድን ጭምር ነው። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር. . . አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ፥ አየም ደስም አለው።» እያለ መስክሮለታል። ይኸውም አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ መልከጼዴቅን በማየቱ ክርስቶስን እንዳየ ተቆጥሮለታልና ነው። ዮሐ ፰፥፴፱፤ ፶፮። ከዚህም ሌላ «ድሀውም (አልዓዛርም) ሞተ፥ መላእክትም በአብርሃም እቅፍ አስቀመጡት።»በማለት ተናግሮለታል። በዚህም የመንግስተ ሰማያትን ክብር በአብርሃም እቅፍ መስሎታል። ሉቃ ፲፮፥፳፪። ከዚህም፦ ከቅዱሳን እቅፍ መውጣት ማለት፥ ከመንግሥተ ሰማያት መውጣት እንደሆነ እንማራለን።
፩፥፭፦ በእንተ አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብ፤
          እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ቃል ኪዳን ለልጁ ለይስሐቅ፥ ለልጅ ልጁ ለያዕቆብም አጽንቶላቸዋል። በምድር ላይ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ረሀብ በላይ ረሀብ በሆነ ጊዜ፥ ይስሐቅ ወደ ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቤሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ። በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ተገለጠለትና፦ «ወደ ግብፅ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። በዚህች ምድር ተቀመጥ፥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥ እባርክሃለሁም፤ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና።» አለው። ዘፍ ፳፮፥፩-፮። ይስሐቅ የአብርሃም የቃል ኪዳን ልጅ በመሆኑ በአዲስ ኪዳን ዘመን ከውኃና ከመንፈስ ተወልደው (በሥላሴ ስም ተጠምቀው) የእግዚአብሔር ልጆች ለሚሆኑ ክርስቲያኖች ምሳሌ ሆኗል። ሮሜ ፱፥፮-፱፣ ገላ ፬፥፳፩-፴፩።
          እግዚአብሔር ለያዕቆብም በፍኖተ ሎዛ ጫፏ ሰማይ በደረሰ መሰላል ላይ ተገልጦለታል፦ «የአባትህ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። እነሆ፥ አኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድበትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።» ብሎታል። ዘፍ ፳፰፥፲፫-፲፭። እግዚአብሔር የተገለጠባት መሰላል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ምክንያቱም እግዚአብሔር በተዋሕዶ ሰው ሆኖ ተገልጦባታልና ነው። ጫፏ ሰማይ መድረሱም የወላዲተ አምላክ ክብሯ ሰማያዊ መሆኑን ያጠይቃል። እግዚአብሔር በደብረ ሲና ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜም፦ «እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክነኝ፤» በማለት መስክሮላቸዋል። የደኅና ልጅ አባት በልጁ ተመክቶ የእገሌ አባት ነኝ እንደሚል፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ተመክቶ የእነርሱ አምላክ ነኝ በማለት መስክሮላቸዋል። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፥ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።» በማለት ተናግሮላቸዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን ላይ ተመሥርቶ፦ «አብርሃም በተጠራ ጊዜ ርስት አድርጎ ይወርሰው ዘንድ ወደአለው ሀገር ለመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚደርስም ሳያውቅ ሄደ። በእምነትም ከሀገሩ ወጥቶ ተስፋ በሰጠው ሀገር እንደ ስደተኛ በድንኳን፥ ተስፋውን ከሚወርሱአት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ኖረ። መሠረት ያላትን ሠሪዋና ፈጣሪዋ እግዚአብሔር የሆነላትን ከተማ ደጅ ይጠኑ ነበርና።» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፰-፲። በዚህም፦ የቅዱሳን በረከት ለልጅ ልጅ እንደሚተርፍ ሕያዋንም እንደሆኑ መስክሮላቸዋል። ከዚህም ሌላ፥ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ከቅዱሳን ጋር እንደምንኖር ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያትም ከእነርሱ ጋር እንደምንኖር፥ ጌታችን መስክሯል። «እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤» ብሏል። ማቴ ፰፥፲፩።
፩፥፮፦ በእንተ ሙሴ፤
          እግዚአብሔር ሙሴን በጠራው ጊዜ፥ «እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ፤. . . ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደኅና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ዳግም ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ፥ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንሃል፥ አንተም በእግዚአብሔር ፈንታ ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ።» ብሎታል። ዘጸ ፬፥፲፬-፲፯። ከዚህም በላይ፦ «ረሰይኩከ አምላኮ ለፈርዖን፤ ወአሮን እኁከ ይኩንከ ነቢየ፤ ለፈርዖን አምላክ (የጸጋ ገዥ አድርጌሃለሁ)፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሁንልህ፤» ብሎታል። ዘጸ ፯-፩።
          የነቢያት አለቃ ሙሴ፥ ኢትዮጵያዊቷን ሴት በማግባቱ፥ ወንድሙ አሮን እና እኅቱ ማርያም አምተውት ነበር። «በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ የተናገረ አይደለምን?» ማለታቸውን እግዚአብሔር ሰምቶ፥ ሦስቱንም ወደ መገናኛው ድንኳን ከጠራቸው በኋላ በደመና ዓምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ ከቆመ በኋላ፥ «ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም።» ብሎ ድምፁን አሰምቶአቸዋል። ዘኁ ፲፪፧፩-፰። በዚህም በቅዱሳን ላይ በድፍረት መናገር እንደማይገባ አስተምሯል። ማስተማር ብቻም ሳይሆን በአሮን እና በማርያም ላይ ተቆጥቶባቸዋል። በዚህ ምክንያት ማርያም እኅተ ሙሴ በለምፅ ነድዳለች። አሮንም ወደ ሙሴ ተመልሶ፦ «ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና፤ እባክህ ኃጢአት አታድርግብን።» ብሏል። ዘኁ ፲፪፥፱-፲። ከዚህም በቅዱሳን ላይ መናገር ስንፍና፥ በደል፥ ኃጢአት መሆኑን እንማራለን። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፦ «እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ሙሴንም ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ? ብሏል። ዮሐ ፭፥፵፭።

ይቀጥላል. . .   

6 comments:

 1. ቃለ ሕይዎት ያሰማልን!!!

  ReplyDelete
 2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መንግሥተ ሰማያትን ያውርስልን አባታችን። ቅድስት ተዋህዶ ሃይማኖትን ባሉበት ሆነው በዓለም ላሉ ሁሉ ለማዳረስ የሚያደርጉትን ጥረት እግዚአብሔር አምላክ ይጨመርበት። የድንግል ማርያም ጸሎት እና ምልጃ ከእርስዎ ጋር ይሁን።

  ReplyDelete
 3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!
  I am impressed with your way of preaching and presentation. The almighty God and St.Marry Bless you.

  ReplyDelete
 4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!

  ReplyDelete
 5. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!

  ReplyDelete
 6. egzabeher kalwe hewet yasemaln

  ReplyDelete