Sunday, June 5, 2011

ክ.፫ «እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤» ማቴ ፲፥፲፮፤


ክፍል ፫

፪፦ በግ እና ተኲላ፥ እባብና ርግብ፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን፦ ወደ የት እንደሚልካቸውና ምን መሆን እንዳለባቸው ሲነግራቸው፦ «እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ እንግዲህ እንደ እባብ ብልሆች፥ እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ፤» ብሏቸዋል፡፡ በዚህም ከክፉዎች ሁለት ከደጋጎችም ሁለት ጠቅሷል፡፡

፪፥፩በግ 

          በሕገ ልቡናም በሕገ ኦሪትም በግ ለመሥዋዕትነት ይቀርብ ነበር። «እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤» ይላል። ዘፍ ፬፥፬። እግዚአብሔር የተመለከተው፥ የወደደው፥ የተቀበለው የአቤል መሥዋዕት በግ ነበረ። አቤል፦ ከበጎቹ በኲራት፦ ቀንዱ ያልከረከረውን፥ ጠጉሩ ያላረረውን፥ ጠፍሩ ያልዘረዘረውን ንጹሕ ጠቦት ለእግዚብሔር አቅርቧል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «አቤል ከቃኤል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ እንኳ ተናገረ።» በማለት መስክሯል። ዕብ ፲፩፥፬። በኦሪትም ይሠምርላቸው ዘንድ የበግ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ እግዚአብሔር ለሙሴ ነግሮታል። ዘሌ ፳፪፥ ፲፱።

          አብርሃም፦ እግዚአብሔር አዘጋጅቶለት፦ ስለ ልጁ ስለ ይስሐቅ ፈንታ በሞሪያ ተራራ የሠዋው በግ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር። ይህ በግ የተገኘው ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተተብትበው ነው። ዕፀ ሳቤቅ የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ይስሐቅ ደግሞ የአዳም ምሳሌ ነው። ከዕፀ ሳቤቅ የተገኘ በግ ስለ ይስሐቅ ፈንታ እንደተሠዋ፥ ከድንግል ማርያም የተወለደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አዳም ፈንታ ተሠውቷል። ዘፍ ፳፪፥፪። እስራኤል ዘሥጋ ከግብፅ የባርነት ቤት ለመውጣት እግዚአብሔር አዝዟቸው ለነፃነታቸው የሠዉት የፋሲካ በግም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው። ዘጸ ፲፪፥፫። እነርሱ በበጉ ደም ከባርነት ቤት እንደወጡ፥ ነፍሳትም በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሲኦል ወጥተዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦«የኢየሱስ ክርስቶስም ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፯።

          ከነቢያት፦ ነቢዩ ኢስይያስ፦ «እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቶቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።» በማለት ትንቢት የተናገረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢሳ ፶፫፥፯። ይኽንንም ቅዱስ ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ተርጉሞለታል። የሐዋ ፰፥፳፮,

፪፥፪  የአዲስ ኪዳን በግ 
           ከላይ በምሳሌ በትንቢትም እንደተመለከትነው የአዲስ ኪዳን በግ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይኸንንም በተመለከተ፦ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፦ አንድ ጊዜ በዮርዳኖስ፥ ሁለተኛም ለደቀመዛሙርቱ፦ «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤» በማለት መስክሮለታል። ዮሐ ፩፥፳፱፤፴፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። (ኃጢአትን፥ ክህደትን፥ ፍዳን፥ ከአዳም፤ አንድም ክህደትን ፍዳን ከዲያብሎስ እንደወረሳችሁ አትዘነጉትም፤ የተቤዣችሁት)። ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደበግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፯። ምክንያቱም መርገመ ሥጋን፥ መርገመ ነፍስን ያመጣ የአዳምን ኃጢአት ያስወገደ የመሥዋዕት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ በራእይ መጽሐፍ ላይ፦ «በዙፋኑና በአራቱ እንሰሶች መካከልም፥ በሊቃናቱም መካከል እንደታረደ ቆሞ አየሁ፤ --- አራቱ እንሰሶች (ኪሩቤልና) ሃያ አራቱ ሊቃናት (ሱራፌል) በበጉ ፊት ወደቁ፤ --- አየሁም፤ እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፤» ብሏል። ራእ ፭፥፮፤፰፤፲፬፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በበኲሉ፦ «ፋሲካችን ክርስቶስ (የፋሲካ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ) ታርዶአልና፤ (በመስቀል ተሰቅሎ እንደታረደ በግ ደሙን አፍስሷልና)፤» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፭፥፯።

፪፥፫፦ ምእመናን፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምእመናንን በበጎች መስሏቸዋል። በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል፦ «በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ --- እውነት እውነት እላችኋለሁ የበጎች በር እኔ ነኝ። --- ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። --- የእኔ የሆኑትን መንጋዎቼን አውቃለሁ፤ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል። --- ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። --- ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ወደዚህ አመጣቸው ዘንድ ይገባኛል፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ ለአንድ እረኛም አንድ መንጋ ይሆናሉ።» የሚል ተጽፏል። ዮሐ ፲፥፩-፲፮። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ለደቀመዛሙርቱ በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ተገልጦ፥ የዓሣ በረከት ሰጥቶ፥ አብሮአቸው ከተመገበ በኋላ «በጎቼን ጠብቅ፤ . . . ጠቦቶቼን አሰማራ፤. . . ግልገሎቼን ጠብቅ፤» በማለት ምእመናንን በቅዱስ ጴጥሮስ በኲል ለሐዋርያት አደራ ሰጥቶአል። ዮሐ ፳፩፥፲፭- ፲፯። ግልገሎቼ የተባሉት ሕፃናት አንድም ወጣንያን (ጀማሪዎች) ናቸው፥ ጠቦቶች የተባሉት ወጣቶች አንድም ማእከላውያን ናቸው፥ በጎች የተባሉት አረጋውያን አንድም ፍጹማን ናቸው። በዕለተ ምጽአትም በጎች የተባሉ ጻድቃን በቀኙ እንደሚቆሙ ተነግሯል። «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ፥ ያንጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል። አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ ለየራሳቸው ይለያቸዋል። በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።» ይላል። ማቴ ፳፭፥፴፩። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ አንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፵፫፥፳፪፣ ሮሜ ፰፥፴፮።

፪፥፬፦ የበግ ምሳሌነት፤

ሀ. በግ ትሑት ነው፥ መሬት እያየ ይሄዳል፤ ጻድቃንም ትሑታን ናቸው፥ መሬት እያዩ ይኖራሉ፤        
   ትርጉሙም ዕለተ ሞታቸውን እያሰቡ ይኖራሉ ማለት ነው። «አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም   
   ትመለሳለህ፤» የተባለውን መቼም መች አይዘነጉትም። ዘፍ ፫፥ ፲፱።

ለ. በግ ኃፍረተ ሥጋዋን በላቷ ትሸፍናለች፥ ጻድቃንም የራሳቸውን ኃጢአት በንስሐ የባልንጀራቸውን
   ደግሞ በትዕግሥት ይሸፍናሉ። «ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል፥ ሰባት ጊዜ ይነሣል፤» እንደተባለ
   ፍጹም ኃጢአት ቢሠሩ ፍጹም ንስሐ ገብተው ይሸፍኑታል። ባልንጀራቸው ሲበድላቸው፦
   አይተው እንዳላዩ፥ ስምተው እንዳልሰሙ ፈጽመው ይታገሡታል። በኃጢአት ቢወደቅ
   ያዝኑለታል (ያለቅሱታል) እንጂ አይፈርዱበትም፥ አያስፈርዱበትም።

ሐ. በግ ከዋለበት አይታወቅም፥ ድምፁ አይሰማም፥ ከሰው እህል፣ ከሰው ተክል አይገባም፤      
ጻድቃንም ከዋሉበት አይታወቅም፥ ድምፃቸው አይሰማም፥ ከሰው ነገር አይገቡም ሲጣሉ
ሲጨቃጨቁ አይገኙም።

መ. በግ ጭቃውን አይጸየፍም፥ ጻድቃንም መከራውን አይሳቀቁም፥ መስቀሉን ተሸክመው    
    (መከራውን ታግሠው) ይኖራሉ። ጌታ «እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን    
     መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ።» ባለው ቃል እስከመጨረሻ ይጸናሉ። ማቴ ፲፮፥፳፬።

ሠ. በግ ያገኘውን ሁሉ ከባልንጀራው ጋር ተካፍሎ ይበላል፥ በመብል ምክንያት አይጣላም፤ ጻድቃንም ያገኙትን ሁሉ ከድሆች ጋር ተካፍለው በፍቅር ይመገባሉ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድሆች የተመገቡትን፦ እርሱ እንደተመገበው አድርጎ እንደሚቀበልላቸው ያውቃሉ። ማቴ ፳፭፥፴፬። «ርኅሩኅ የተባረከ ይሆናል፥ ከእንጀራው ለድሀ ሰጥቷልና፤» የተባለላቸው ናቸው። ምሳ ፳፪፥፱። ጠላትም ቢሆን ተርቦና ተጠምቶ ካገኙት ያበሉታል፥ ያጠጡታል። ምሳ ፳፭፥፳፩፣

ረ. በግ ከመንጋው መካከል አንዱን አውሬ የነጠቀው እንደሆነ ሌሎቹ ይሸሻሉ፥ ወደ ኋላ አይመለሱም፤ ይኸውም በባልንጀራቸው ላይ የደረሰ እንዳይደርስ ነው። ጻድቃንም ከባልንጀሮቻቸው መካከል አንዱን አውሬ (ሰይጣ ን ያሰናከለው እንደሆነ፥ ባልንጀራቸው በተጠመደበት ኃጢአት እንዳይጠመዱ፥ በወደቀበትም በደል እንዳይወድቁ ያን ስፍራ ትትው ይሸሻሉ (ፈጽመው ይመንናሉ)። «በግ ከበረረ፥ ሞኝ ካመረረ አይመለስም፤» እንደተባለው ዓለምን ትተው ከመነኑ በኋላ ወደ ዓለም አይመለሱም። «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፥ ነፍሱንም ቢያጣ፥ ለሰው ምን ይረባዋል? ሰውስ ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር?» በተባለው ጸንተው ይኖራሉ። ማቴ ፲፮፥፳፮።

ሰ. የበግ መኖሪያ ከፍ ባለ ስፍራ በደጋ ነው፤ የጻድቃንም መኖሪያቸው ከፍ ባለች ስፍራ በመንግሥተ ሰማያት ነው። ጊዜው ሲደርስ፦ «እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ፤» ይላቸዋል። ማቴ ፳፭፥፴፬ ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በምድር ያለው ምድራዊ ቤታችን ቢፈርስም፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን፤» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፭፥፩።

፪፥፭ ተኲላ፤

          ተኲላ ክፉ የዱር አውሬ ነው፥ በጎችን፥ ፍየሎችን እየነጠቀ ይበላል። ይኽንን በተመለከተ ጌታ በወንጌል፦ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኲላም ይነጥቃቸዋል፥ በጎቹንም ይበትናቸዋል።» ብሏል። ነጣቂ ተኲላ የተባለ ሰይጣን ነው ዮሐ ፲፥፲፩። በማቴዎስ ወንጌል ደግሞ «የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኲላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤» የሚል ይገኛል። እነዚህም፦ መንፈሳውያን መምሕራን መስለው የሚመጡ ፍጹም ሥጋውያን የሆኑ መናፍቃን ናቸው። ማቴ፮፥፲፭።

          ከጌታችን ቃል እንደምንረዳው ተኲላ አስመሳይ ነው። ከመንጋው መካከል ገብቶ እንደነርሱ ሣር የሚነጭ ይመስላል፥ አድፍጦ ከቆየ በኋላ አዘናግቶ አንዱን በግ ይነጥቀዋል። ማስመሰል የመናፍቃንና የግብር አባታቸው የሰይጣን ጠባይ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ፥ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደሥራቸው ይሆናል።» ያለው እነርሱን ነው። ፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፲፫።

          ተኲላ ጥበበኛ ነው፤ ይኸውም አንድን በግ ከመንጋው ለይቶ ከባልንጀሮቹ ጋር ሆኖ በሚያሳድድበት ጊዜ ሁሉም አንድ ላይ አያባርሩም። አንዱ ተኲላ በሙሉ ኃይሉ በጉን ሲያባርር የተቀሩት ተረጋግተው ይከተሉታል። ካቃተው አንገቱን ወደ ኋላ ያዞራል፥ በዚህን ጊዜ ሌላ ተኲላ ይተካለትና ወደ ኋላ ቀርቶ ከሌሎች ይደባለቅና ትንፋሽ ይሰበስባል። የተተካውም ተኲላ ባለ በሌለ ኃይሉ ሞክሮ ካልተሳካለት አንገቱን መለስ ያደርጋል፥ አሁንም ከኋላ በአጀብ ከሚከተሉት መካከል ሌላ ተተኪ ይላክለታል። እንዲህ እያሉ ተራ በተራ ተፈራርቀው ያደክሙትና ይበሉታል። መናፍቃንም በአንድ ጥቅስ ስትረቷቸው ተረታን ብለው እጅ አይሰጡም፥ ሌላ ጥቅስ ይጠቅሳሉ። በዚያም ስትረቷቸው ሌላ ጥቅስ ይጠቅሳሉ። እንዲህ እያሉ ጥቅስ በማፈራረቅና ጥቅስ በማብዛት እንደ በግ የዋሃን የሆኑ ምእመናንን ያደክማሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በመልካምና በሚያቈላምጥ ንግግር ተንኰል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ፤» ያለው እነርሱን ነው። ሮሜ ፲፮፥፲፰። ሰይጣንም በአንድ ነገር ድል ስንነሣው በሌላ ይፈትነናል፤ በዚያም ድል ስንነሣው ሌላ ፈተና ያመጣል፤ እንዲህ እያለ ፈተና እያፈራረቀ በምግባርም በሃይማኖትም ሊያዳክመን እስከ መጨረሻው ይታገላል። ለዚህም አብነታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፦ በስስት የፈተነውን ሰይጣን በትዕግሥት ድል ቢያደርገው በትዕቢት መጣበት። በትኅትና ድል ቢያደርገው በፍቅረ ንዋይ ፈተነው። ጌታም በጸሊአ ንዋይ ድል አደረገው። ሰይጣንም በአይሁድ ልቡና አድሮ የተለያዩ ፈተናዎችን እስኪያመጣ ድረስ ለጊዜው ዘወር አለ። ማቴ ፬፥፩-፲፩። ከዚህ የምንማረው፦ በአንድ መንገድ ድል ሆኖ ዘወር ያለ ሰይጣን ሌላ ፈተና ይዞ መመለሱ አይቀርም። ጌታችን በወንጌል፦ «ርኲስን መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ (በጸሎት በጠበል በለቀቀ ጊዜ) ዕረፍት (የሚያድርበት) እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል (ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ወደ አልተወለዱት ወደአልተጠመቁት ይሄዳል)፥ በዚያን ጊዜም ወደ ወጣሁበት ቤት እመለሳለሁ ይላል፤ በመጣም ጊዜ፦ ባዶ ሆኖ ተጠርጎ አጊጦ (ከጸሎት ተለይቶ፥ ከጠበል ርቆ ፍጹም ሥጋዊ ሆኖ) ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን (ፍጹም ኃጢአት የሚያሠሩትን) አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ (ሰውነቱን ማደሪያ ያደርጉታል)፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል።» ያለው ይኽንን ነው። ማቴ፲፪፥፵፫።

፪፥፮፦ ርግብ፤

          ርግብ የምትታወቀው በየዋህነቷ ነው። ጌታችን በወንጌል፦ «እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፲፥፲፮። ምክንያቱም መንግሥተ ሰማያትን የሚወርሱት የዋሃን በመሆናቸው ነው። ማቴ ፭፥፭። ለጻድቁ ለኖኅ መልስ ይዛ የተመለሰች ርግብ ናት። የጥፋት ውኃ ጐደለ፥ የጥፋት ውኃ ቆመ፥ ስትል ለምለም የወይራ ቅጠል ይዛ ወደ መርከቡ ተመልሳለች። ዘፍ ፰፥፰-፲፪። ርግብ በየዋህነቷ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ጠቢቡ ሰሎሞን «ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት፥ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሷት፥ ንገሥታትና ቊባቶችም አመሰገኗት።» ያለው እመቤታችንን ነው። መኃ ፮፥፱። ርግብ የመንፈስ ቅዱስም ምሳሌ ናት። «ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።» ይላል። ሉቃ፫፣፳፩-፳፪።

          በኖኅ ዘመን ወደ መርከቧ የገባ እባብ (ዘንዶ) አፉን ከፍቶ ሲተኛ ያየች ርግብ በየዋህነት ከዘንዶው አፍ ውስጥ ገብታ እንቊላሏን ጥላለች። ከዚህም ሌላ ርግብ ከአንድ በላይ አታገባም፤ ባሏ የሞተ እንደሆነ ምላሷን ሰንጥቃ በብቸኝነት ትኖራለች፥ ሌላ ርግብ የመጣ እንደሆነ የተሰነጠቀ ምላሷን እያሳየች ትመልሰዋለች። ርግብ በሐዘኗም ትታወቃለች፤ ይኽንን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳያይስ፦ «ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፥ እንደ ርግብ እንለቃቀሳለን።» ብሏል። ኢሳ ፶፱፥፲፩። በመሆኑም እንደ ርግብ የዋህ፥ ኃዳጌ በቀል፥ ታማኝ መልእክተኛ፥ በቃል ኪዳን የጸና፥ መሆን ያስፈልጋል።

፪፥፯፦ እባብ

          ሰይጣን አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳታቸው በእባብ አድሮ፥ እባብን ፈጽሞ ተዋሕዶ ነው። በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ፥ እባብ በክፋት ከሁሉ ይጸና ነበር ይላል፤ ጥንቱን ሲፈጠር፦ በግመል ልጅ አምሳል የግመል ወሳብሬ አህሎ ነበር፤ በኋላ ግን፦ እግዚአብሔር፦ «በደረትህ ሂድ፥የምድርን ትቢያ ብላ፤» ብሎ በረገመው ጊዜ አራት እግሩ ተስቦ ወደ ሆዱ ገብቷል። ለምድር ቀርቦ በልቡ የሚሄድ ስለሆነ አርዌ ምድር (የምድር አውሬ) ተብሏል። አንድም ከምድር የተፈጠረ አዳምን ስላሳሳተ አርዌ ምድር ተብሏል።

          አዳምና ሔዋን በገነት ሰባት ዓመት ሲኖሩ፥ የስሕተት ምክንያት አጥቶላቸው ይጠባበቃቸው ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን፦ እንስሳት፥ አራዊት፥ አዕዋፋት፥ ለደጅ ጥናትና ለተልዕኮ ከአዳም ደርሰው ሲመለሱ በጐዳና አገኛቸው። ወደ እሪያ ቢቀርብ መልኩ ስላስፈራውና ስላስደነገጠው አላስጠጋ አለው። በዚህን ጊዜ ሰይጣን ጥቂት ፈቀቅ ብሎ፦ «ወዴት ሄዳችሁ ነበር?» አላቸው፥ እነርሱም፦ «ከንጉሣችን ከአዳም ዘንድ ለደጅ ጥናት ሄደን ነው፤» አሉት። መልሶም፦ «አዳም ምን አላችሁ? ምን ነገራችሁ?» አላቸው። እነርሱም፦ «ከእኛ አንዳችንን አርደህ ብላ፥ አልበህ ጠጣ ብንለው፦ እኔን ከአንዲት ዕፅ በቀር የከለከለኝ የለም፥ ሁሉን ግዛ፤ ንዳ፥ ሁሉን ብላ፤ ጠጣ ብሎ ሰጥቶኛል፤ ይህችንም የከለከለኝ ነፍጎኝ፥ ተመቅኝቶኝ አይደለም ሞተ ሥጋ፣ ሞተ ነፍስ እንዳልሞት ነው እንጂ አለን፤» አሉት።

          ሰይጣን ይኽንን ምሥጢር ካወቀ በኋላ፦ «አዳምን ማሳሳት ከገደል አፋፍ ላይ የቆመን ሰው የመገፍተር ያህል ቀላል ነው፤» አለ። እባብን ወደ አዳም ለደጅ ጥናት ስትሄድ ከጐዳና አገኛት፥ «ወዴት ትሄጃለሽ?» ብሎ ቢጠይቃት የምትሄድበትን ነገረችው፥ «መልካም ነው አብረን እየተጨዋወትን እንሂድ፤» አላት፤ እርሷም፦ «ነገሩስ ደግ ነበር፥ ነገር ግን የእኔ መልክ ያማረ፥ መዓዛዬም የሠመረ ነው፤ የአንተ ግን መልክህ የከፋ፥ መዓዛህ የከረፋ ስለሆነ እንዴት ይሆናል?» አለችው። በዚህን ጊዜ፦ «የአንቺ መልከ መልካምነት የሚታወቀው ከእኔ መልክ ጥፉነት አንጻር ነው። በዚያውም ላይ የአንቺ መልክ የኔን ክፉ መልክ ያስወድደዋል፥ መዓዛሽም የእኔን ክርፋት ይለውጠዋል፥ ያስመሰግነዋል እንጂ የሚጐዳሽ ነገር የለም፤» ብሎ በውዳሴ ከንቱ ልቧን ደቃት። በከንቱ ውዳሴ የማይነደፍ የለምና እርሷም በውዳሴ ከንቱ ተነደፈች። ተከታትለውም ሲሄዱ፦ «የዚህች የገነት ጎዳናዋ አቀበቷ የማይመች ጐጻጉጽ ነውና እንወቅባት፤» አላት። እርሷም፦ «ምን እናድርግ?» አለችው። እርሱም፦ «ተራ በተራ እንተዛዘል፤» አላትና ግማሽ መንገድ አዘላት። ከዚህ በኋላ፦ «አንዳዘልኩሽ እዘይኝ፤» ቢላት አዘለችው። በዚህን ጊዜ ቅቤን ከጋለ ድንጋይ ላይ ሲያኖሩት እየቀለጠ እንደሚሠርፅ በእርሷ ሠርፆ በመግባት ተዋሐዳት። ዘፍ ፫፥፩-፭።

          እባብ መርዛም አውሬ ነው እስራኤል ዘሥጋ በምድረ በዳ በሚጓዙበት ጊዜ በበደላቸው ምክንያት እባቦች ታዘውባቸው ስኰና ስኰናቸውን እየነደፉ በዙዎችን ገድለዋቸዋል። ዘኁ ፳፩፥፮። እባብ ጥበበኛም ነው። ከመንገድ ዳር ሲተኛ ራሱን ቀብሮ ነው፥ ምክንያቱም ራሱን ካልተመታ በስተቀር ስለማይሞት ነው። ውኃ ሲጠጣ ከምላሱ ስር ያለውን መርዙን አስቀምጦ ነው። ምክንያቱም ከነመርዙ የጠጣ እንደሆነ በመላ አካሉ ተሰራጭቶ ቆራርጦ እንደሚገድለው ስለሚያውቅ ነው። በኖኅ ዘመን ርግብ በየዋህነት ከአፉ ገብታ ዕንቁላል ጥላ፥ ጫጩቶች ብትፈለፍል፦ ሳይበላት ታግሧል። ምክንያቱም የበላት እንደሆነ፥ ኖኅ ከመርከብ አውጥቶ እንደሚጥለውና ዘሩም እንደሚጠፋ ያውቃልና ለዚህ ነው። በሌላ በኲል ደግሞ ዕባብ የሚበላት ዕፅ አለች፥ «ዘዌ» ትባላለች። ጥላዋ ያረፈበት እንደሆነ አድክማ ትገድለዋለች፥ በዚህ ምክንያት ለመብላት የሚሄደው ጥላ ባላረፈበት በኲል ነው። ማለዳ ሲሆን ጥላ የሚያርፈው በምዕራብ በኲል ስለሆነ ለመብላት በምሥራቅ በኲል ይሄዳል፥ ሠርክ ሲሆን ጥላ የሚያርፈው በምሥራቅ በኲል ስለሆነ ለመብላት በምዕራብ በኲል ይዞራል።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ወንጌልን እንዲሰብኩ ወደ ዓለም የሚልካቸውን ደቀመዛሙርት ከርግብ የዋህነትን፥ ከዕባብ ደግሞ ልባምነትን እንዲወስዱ መክሯቸዋል። ምክንያቱም በጎች ተኲላዎች ከሚበዙበት አካባቢ እንደሚሰማሩ፥ እነርሱም ለአገልግሎት የሚሰማሩት ክፉ ሰዎች፥ መናፍቃን፥ አጋንንት ፈተና ወደሚያበዙበት ዓለም ነውና። ለዚህም ነው፥ «እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤» ያላቸው። በመሆኑም እባብ ራሱን ቀብሮ በራሱ ተማምኖ እንደሚተኛ፥ እነርሱም የሕይወታቸው ራስ በሆነ በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲተማመኑ፥ እባብ መርዙን አስቀሞጦ ውኃ እንደሚጠጣ፥ እነርሱም ቂም በቀል ሳይዙ እንዲጸልዩ፥ እባብ ርግብ ከአፉ ገብታለት እንደታገሠ፥ እነርሱም ኃጢአትን አመቻችታ በምታቀርብ ዓለም ትዕግሥተኞች እንዲሆኑና የሚጠፉበትን ሥራ እንዳይሠሩ፥ እባብ የዕፀ ዘዌን ጥላ እንደሚሸሽ፥ እነርሱም ዲያብሎስ ጥላውን ካጠለበት ስፍራ (ሞተ ነፍስን ከሚያመጣ በደል) እንዲሸሹ ነግሯቸዋል።

          ይህ ምክር፦ በእውነት ተከትለን ከሆነ፥ የቅዱሳን ሐዋርያትን አሠረ ፍኖት ለተከተልን ሁሉ ነው። ከሁሉም በላይ ይህ ዓለም፦ ክርስቶስን ገርፎ የሰቀለ ዓለም መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መርሳት አይገባም። ይህ ዓለም፦ ፈጽመው ራሳቸውን ከዓለም ለይተው፥ በጾም በጸሎት ተወስነው፥ በሐዋርያነት ተንገላተው፥ ዕውር በማብራት፥ ሙት በማስነሣት፥ የተለያዩ ገቢረ ተአምራት ያደረጉትን ቅዱሳን፦ በሰይፍ መትሮ፥ በመጋዝ ተርትሮ፥ በእሳት አቃጥሎ፥ ለአራዊት ሰጥቶ፥ የገደለ ዓለም ነው። ስለዚህ፥ ከዚህ አንፃር እኛ ምንም የደረሰበን ነገር የለም፤ ብንሰደድም ባንሰደድም በዓለመ ሥጋ ካሉት ይልቅ በሥጋ ምቾት የምንኖር ሰዎች ነን። ለክብራችን እንጂ ለእግዚአብሔር ክብር የቆምን ሰዎች አይደለንም። «ከእባብ ጥበቡን ውሰዱ» ብንባል «መርዙን ይሻለናል፤» ያልን ሰዎች እንመስላለን።

          ብዙ ሰው ላዩ ርግብ ይመስላል፥ ውስጡ ግን እባብ ነው፥ ላዩ በግ ይመስላል ውስጡ ግን ተኲላ ነው። ይኽንንም በተመለከተ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኲላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት (ከመናፍቃን) ተጠንቀቁ፤» ብሏል። ሜቴ ፯፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁለና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኲላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ (ያስከትሉ) ዘንድ ጠማማ ነገርን (ኑፋቄን) የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ፤» ብሏል። የሐዋ ፳፥ ፳፰።

          እንግዲህ፥ አገልግሎታችን የተገለጡም ያልተገለጡም ተኲላት (መናፍቃን) ባሉበት፥ ለሥጋቸው ብቻ ያደሩ፥ ለክብራቸው ብቻ የሚኖሩ ሰዎች በበዙባት ቤተክርስቲያን ስለሆነ አብዝቶ መጾም፥ አብዝቶ መጸለይ ያስፈልጋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አብዝቶ የጾመው ለዚህ ነውና። ፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፯። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላችነት አይለየን አሜን።

7 comments:

 1. KALEHIWOT YASEMALEN ABATACHIN!!!

  ReplyDelete
 2. I AM VERY HAPPY BY YOUR WRITING, I AM ATTENDING EACH AND EVERY THINNING WRITTEN IN YOUR BLOG.

  DESTA

  ReplyDelete
 3. Egziabher erezem edeme yisteilen

  ReplyDelete
 4. kale hiywot yasemaliin
  wondu

  ReplyDelete
 5. May God brighten your way. This time is the time we need to front against the reformationalist and protestants who are disturbing the church and its way tot the heaven. Let's pray for God, St. virgin Mary and all saints to aid us and the church.

  ReplyDelete
 6. KALEHIWOT YASEMALEN ABATACHIN!!! I really impressed by your explanation. ይህ በእውነቱ ክርስቶስ በስጋው ወርዶ ያስተማረን በየዘመኑም ሊከሰት የሚችለውን ነገር የሚያሳይ እና ዘመኑን የሚዋጅ ትምህርት ነው፡፡

  ReplyDelete
 7. kale hiwot yasemalen egzabeher regem edemin selamn yestlen.

  ReplyDelete