Monday, May 23, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፫


ጻድቁ ዮሴፍ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፦ ሊጠብቃት፥ ሊያገለግላትና ሊላላካት፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከካህናቱ እጅ በአደራ ተቀብሏታል። ሰው ሰውኛውን እርሱ ይጠብቃት እንጂ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጠባቂዋ መንፈስ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር ለተዋሕዶ አካላዊ ቃል የመረጣት ስለሆነ፥ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍባት፥ ከአዳም በዘር ይተላለፍ የነበረው የውርስ ኃጢአት ሳያገኛት፥ በመንፈስ ቅዱስ ተጠብቃ ኖራለች። አምላክን በድንግልና ፀንሳ፥ በድንግልና እንደምትወልድ ያበሠራት መልአከ ቅዱስ ገብርኤል፦ «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤» ያላት ለዚህ ነው። ይህም፦ የምትፀንሺው፥ ከእናትሽ ማኅፀን ጀምሮ በጠበቀሽ፧ ለቅጽበተ ዓይን እንኳ ተለይቶሽ በማያውቅ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው፥ ሲላት ነው። ሉቃ ፩፥፴፰። ምክንያቱም በውስጧ ሆኖ የጠበቃት፥ በኋላም ያዋሐደ እርሱ ነውና።
          የባሕርይ አምላክ ፥ ከሰማይ ወርዶ፥ በማኅጸነ ድንግል ማርያም በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ምሥጢር ከሰው አእምሮ በላይ ነው። ይህ፦ አምላክ ሰው የሆነበት ጥበብ (የመንፈስ ቅዱስ ግብር) እጅግ ጥልቅና የማይመረመር ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፤ ፍርዱንም የሚያውቀው የለም።» ያለው ለዚህ ነው። ሮሜ ፲፩፥፴፫። ለልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱም ላይ፦ «ቤተ ክርስቲያኒቱ የእውነት ዐምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤት ናት። የዚህ የመልካም አምልኮ (አምላክ ሰው የሆነበት ምሥጢር) ታላቅ ነውና። ይኸውም በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የተረዳ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ ዘንድ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ ነው።» ብሏል። ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። እንኳን ይህ ታላቅ ምስጢር ቀርቶ፥ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ሥራ ከሰው ዕውቀት በላይ በመሆኑ ከማድነቅ በስተቀር እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር (በቃላት ለመወሰን) አስቸጋሪ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «እግዚአብሔርን ሥራህ ግሩም ነው፥ በሉት፤» ያለው ለዚህ ነው።
          ቅዱስ ዮሴፍ፦ እርሱ በማያውቀው ምሥጢር እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ፀንሳ በማግኘቱ እንደ ሰው ተቸግሯል። ምክንያቱም፦ ምንም ዓይነት ሥጋዊ ምክንያት አያገኘባትምና ነው። በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፥ በዓርቡ ክፍል እንደተጻፈው ቅዱስ ዮሴፍ ፦ ዮሐንስ የሚባል ፈላስፋ ወዳጅ ነበረውና በመልኳ  መፅነሷን አውቆ ነግሮታል። ይኽንን ይዞ ቢጠይቃት፦ «እኔስ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ በቀር የማውቀው የለም፤ በዚያውስ ላይ አዕዋፍ እንዲራቡ (እንዲባዙ)፥ አዕዋም እንዲያፈሩ የሚያደርግ ማን መስሎሃል?» ብላዋለች። ከዚህም ጋር ከደጅ ቆሞ የነበረ ደረቅ ግንድ አለምልማ አሳይታዋለች። ከዚህ በኋላ ለክብረ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም የሚወጡበት ጊዜ ደረሰ።
          ቅዱስ ዮሴፍ በአሳብ ውጣ ውረድ ኅሊናው ተወጠረ። ከቤት ትቷት እንዳይሄድም፥ ወደ በዓሉም ይዟት እንዳይወጣም ተቸገረ። ይኸውም አይሁድን ፈርቶ ነው። ወደ በዓሉ ይዟት እንዳይወጣ፥ ቀድሞም ሊቀ ካህናቱን ዘካርያስን አስጨንቀው አሥራ ሁለት ዓመት ከኖረችበት ቤተ መቅደስ እንድትወጣ ያስደረጉት ለምን እንደሆነ ያውቃል። «የፈራነው ደረሰ፤» ብለው፥ በሕግ ሽፋን ፅንሱን ቆራርጦ የሚያወጣና አንጀቷን የሚበጣጥስ፥ ማየ ዘለፋ እንደሚያጠጧት፥ በደንጊያ ቀጥቅጠው እንደሚገድሏት ከእርሱ የተሠወረ አይደለም። ከቤት ትቷት እንዳይሄድ ደግሞ አፋቸውን እንደ ጦር ፈራው። ከብዙ የአሳብ ውጣ ውረድ በኋላ ግን፥ በአይሁድ ፊት ተገልጣ ባላወቁት ምሥጢር እንዳይፈርዱባት በስውር ከቤት ትቷት ወደ በዓሉ ለመሄድ አሰበ።
፩፥፩፦ የእግዚአብሔር መልአክ በሕልም ታየው፤
          ቅዱስ ዮሴፍ፦ ጻድቅ ሰው በመሆኑ፥ አንድም እንዲጠብቅ የተሰጠችው አደራ መትኅተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን በመሆኗ በነገር ሁሉ ቅዱሳን መላእክት ይራዱት ነበር። በሕልም ይነጋገሩት ነበር። ለደጋግ ሰዎች ሕልም ከእግዚአብሔር ነው። ኢዮ ፪፥፳፰፣ የሐዋ ፪፥፲፯። ያዕቆብ፦ በቤቴል ድንጋይ ተንተርሶ በተኛበት ሌሊት ጫፉ ሰማይ ደርሶ እግዚአብሔር የቆመባት መሰላል፥ ቅዱሳን መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት (ጸሎት ሲያሳርጉባት፥ ምሕረት ሲያወርዱባት) አይቷል። ዘፍ ፳፰፥፲-፲፪። ይህች እግዚአብሔር ተገልጦ የታየባት መሰላል፥ አምላክ ሰው ኾኖ ለተገለጠባት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ላባን ለመገናኘት በተጓዘ ጊዜም የእግዚአብሔርን መላእክት በዙሪያው ከትመው ሲጠብቁት በገሀድ አይቷል። ዘፍ ፴፪፥፩-፪። በእግረ ሙሴ የተተካ ኢያሱ ወልደ ነዌም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘውን የሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ፊት ለፊት አይቷል። ኢያ ፭፥፲፫። ጌዴዎንንም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ አነጋግሮታል። መሳ ፮፥፲፪። የሶምሶንን ወላጆች ማኑሄን እና ሚስቱንም አነጋግሯቸዋል። በፊታቸውም ተአምራት አድርጓል። መሳ ፲፫፥፩-፳።
          ነቢዩ ኤልያስ መፍቀሪተ ጣዖት ኤሌዛቤል ባሳደደችው ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ኅብስት በመሶብ ወርቅ አድርጎ መግቦታል። ኅብስት የጌታ፥ መሶበ ወርቅ የእመቤታችን ምሳሌዎች ናቸው። ፩ኛ ነገ ፲፱፥ ፩-፰። ነቢዩ ኤልሳዕ በዶታይን የሶርያው ንጉሥ በፈረሶችና በሰረገሎች ባስከበበው ጊዜ፦ ቅዱሳን መላእክት በዙሪያው ከትመው የእሳት አጥር ሆነው ሲጠብቁት አይቷል። ሎሌውንም፦ «ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ።» በማለት አጽናንቶታል። በነቢዩ ጸሎት ለሎሌውም ተገልጠውለታል። ፪ኛ ነገ ፮፥፲፬-፲፯። ከዓይነ ሞት የተሰወረ ሄኖክ ቅዱሳን መላእክትን ፊት ለፊት አይቷቸዋል፥ እነ ቅዱስ ሜካኤልም ያነጋግሩት ነበር። ሄኖ ፲፮፥፩-፵፩። ዕዝራ ሱቱኤልን ቅዱስ ዑራኤል አነጋግሮታል፥ የጥበብንም ጽዋ አጠጥቶታል። ዕዝ ፫፥፳። ቅዱስ ሩፋኤል ደግሞ ጦቢያን እያነጋገረው በመንገዱ ሁሉ አልተለየውም ነበር። ጦቢት ፭፥፩-፳፪፣ ፮፥፩-፲፯፣፯፥፩-፲፰።
          ነቢዩ ኢሳይያስ የሱራፌልን መልካቸውን አይቷል፥ ቅዳሴአቸውንም ሰምቷል። ከሱራፌል አንዱም ከሰማይ ይዞት በመጣው እሳት አፉን ዳስሶ ከለምጹ ፈውሶታል። ኢሳ ፮፥፩-፯። ለነቢዩ ለዳንኤል ራእዩን የሚተረጉምለት ቅዱስ ገብርኤል ነበር። ዳን ፰፥፲፭-፳፯። በጾሙ ጊዜም እየተገለጠ ይዳስሰው፥ ያነጋግረውም ነበር። ይህ ታላቅ ነቢይ፥ «ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም።» በማለት መስክሯል። ዳን ፩፥፩-፲፩። ጻድቁ ዮሴፍ፦ አባቶቹን ቅዱሳንን በዘመነ አበው፥ በዘመነ መሳፍንት፥ በዘመነ ነገሥት፥ በዘመነ ካህናትም እየተገለጡ ያነጋገሩ ቅዱሳን መላእክት እርሱንም አነጋግረውታል። እርሱ ሰው ሰውኛውን ሲጨነቅ መንፈሳዊውን ምሥጢር ገልጠውለታል።
፩፥፪፦ «ከእርስዋ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነው፤»
          የእግዚአብሔር መልአክ ዮሴፍን፦ «ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ፥ እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።» ብሎታል። በዚህም የእመቤታችን ጽንስ በመንፈስ ቅዱስ ግብር መሆኑን አስረድቶታል። ይህንንም፦ «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤» ብሎ አስቀድሞ ለእመቤታችን ነግሯት ነበር። ሉቃ ፩፥፴፭። መልአኩ ዮሴፍን፦ «የዳዊት ልጅ» ብሎ በመጥራት ንጉሡን ዳዊትን ያነሣው ያለ ምክንያት አይደለም። ይኸውም፦ «ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ፤ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አዘጋጃለሁ። (በዙፋንህ አስቀምጠዋለሁ)።» ተብሎ ለቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን ሲያጠይቅ ነው። ፪ኛ ሳሙ ፯፥፲፪። ይህ ትንቢት ለጊዜው ለሰሎሞን ሲሆን ለፍጻሜው ለኢየሱስ ክርስቶስ ነበረ። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን በፍጹም ትህትና ባበሠራት ጊዜ፦ «እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል።» ያላት ለዚህ ነበር። ሉቃ ፩፥፴፪። የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሀንስ አባት ጻድቁ ካህን ዘካርያስም፦ አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ፦ «ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤» ብሏል። ሉቃ ፩፥፷፰። መልአከ አግዚአብሔር ዮሴፍን፦ «አትፍራ» ያለው፥ «ልትጠብቃት፥ ልታገለግላት ከካህናት እጅ በአደራ እንደተቀበልካት፥ ከመንፈስ ቅዱስ እጅ መቀበልንም አትፍራ፤»ሲለው ነው። ከዚህም አያይዞ፦ «ልጅም (ወልድን) ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው (በኃጢአት ከመጣባቸው ፍዳ) ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።» ብሎታል። በዚህም «ኢየሱስ» ብሎ ንባቡን፥ «ያድናቸዋል፤» ብሎ ትርጓሜውን ነግሮታል። የስም ኃይሉ ትርጉሙ ነውና። ምክንያቱንም ዘርዝሮ ሲነግረው፥ «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ልጅም (ወልድን) ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። ተብሎ ከእግዚአብሔር ዘንድ (ከእግዚአብሔር አግኝቶ) በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፤» በማለት ትንቢተ ኢሳይያስን ጠቅሶለታል። በዚህም ላይ ነቢዩ በንባብ ብቻ ያስቀመጠውን «አማኑኤል» የሚለውን ስም ተርጉሞለታል። «ወተንሢኦ ዮሴፍ እምንዋሙ ገብረ በከመ አዘዞ መልአከ እግዚአብሔር፤ ወነሥአ ለማርያም ፍኅርቱ። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ተነሥቶ (ነቅቶ) የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውን (እንዲጠብቃት እንዲያገለግላት፥ እንዲላካት የተመረጠላትን) ማርያምንም ወሰዳት።» የወሰዳትም ከቤቱ ወደ በዓሉ ነው።
፩፥፫፦ በዓላት፤
          በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተመዘገበው አይሁድ ሰባት የዓዋጅ በዓላት አሉአቸው። እንደ ስምንተኛ አድርገው የሚያከብሩት አንድ ሌላ በዓል የተጨመረው በመቃብያን ዘመን ነው። በአይሁድ ዘንድ በትእዛዝ የሚከበሩት እነዚህ በዓላት፦ ፩ኛ፦ የሰንበት በዓል፤ ዘሌ ፳፫፥፪፤ ፪ኛ፦ የቂጣ ወይም የፋሲካ በዓል፤ ዘጸ ፲፪፥፩-፳፣ ዘሌ ፳፫፥፭-፰፤ ፫ኛ፦ ሰባት ሳምንት ከፋሲካ በኋላ የሚከበረው የመከር በዓል፤ (በዓለ ሰዊት)፤ ዘጸ ፳፫፥፲፮፤ ፴፬፥፳፪፤ ዘኁ ፳፰፥፳፮፤ የሐዋ ፪፥፩፤ ፬ኛ፦ በሰባተኛው ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የሚከበረው የዳስ በዓል፤ ዘሌ ፳፫፥፴፱-፵፫፤ ፭ኛ፦ መለከቶች የሚነፉበት ቀን፤ ዘሌ ፳፫፥፳፫-፳፭፣ ዘኁ ፳፱፥፩፤ ፮ኛ፦ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የሚከበረው የማስተስረያ ቀን፤ ዘሌ ፳፫፥፳፮፤ ፯ኛ፦ በአስቴር ዘመን አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙባቸው ቀኖች ፉሪን፤ አሰ ፱፥፲፮-፳፰፤ ፰ኛ፦ የሶርያ ንጉሥ አውፋሬኖስ አንጥያኮስ ቤተ መቅደሱን ካረከሰ በኋላ መቃብያን እንደገና የቀደሱበት እለት የመቅደስ መታደስ መታሰቢያ እለት ናቸው።

«የበኽር ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤» ማቴ ፩፥፳፭።. . . .

6 comments:

 1. KALE HIWOT YASEMALEN!
  Bisrat

  ReplyDelete
 2. KALE HIWOT YASEMALEN! Tiru Timihirt Eyagene newna bedeneib yiketilubet

  ReplyDelete
 3. Kalehiwot Yasemalin
  (AGE)

  ReplyDelete
 4. be ewnu abatachin kale hiwotn yasemaln be ye agelglot zemonetn yarzimln yibarkln amlake kudusan minga gurum ena ke marr welela yetafete timert newhulim ekatatelalew emaralehum buzu lewedefi,kale hiwotn yasemaln kale hiwotn yasemaln kale hiwotn yasemaln !!!

  ReplyDelete