Monday, May 16, 2011

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል፦ ፰

ካለፈው የቀጠለ . . .

የአካባቢ ለውጥ፤

            የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ ከአገር አገር እጅግ ይለያያል። በአንድ አገር ውስጥ እንኳን የአንዱ ክፍለ ሀገር ከሌላው ክፍለ ሀገር፥ የአንዱ አውራጃ ከሌላው አውራጃ፥ የአንዱ ወረዳ ከሌላው ወረዳ፥ ይነስም ይብዛም ልዩነቶች አሉ። በመሆኑም ተወልደን ካደግንበት መንደር ወይም ሀገር ትንሽ ራቅ ስንል ቶሎ ለመልመድ፥ ፈጥነን ለመዋሐድ እንቸገራለን። ከአጠገባችን ያለ አላማጅ የተባለ ሰውም ቢሆን አብሮን መቸገሩ አይቀርም። ምክንያቱም ፦ እርሱ ራሱ ቢቸግር ተመሳስሎ ይኖራል እንጂ መቼ ለመደውና ነው። እንዲያውም በቀን ብዛት ሊረሳው የሞከረውን ሁሉ እንደገና እያስታወሰ ውስጡ ይጐዳል። ያደግንበት ባህልና ሥርዓት፥ የኖርንበት ልማድ፥ ከሌላው ዓለም ፈጽሞ የተለየ ነው። በመሆኑም የውጪውን ነገር ቋንቋውንም ጭምር እስክንለምደው ድረስ ለመግባባት አስቸጋሪ ነው። በሀገር ቤት የለመድናቸው ፦ በየዕለቱ ጧት ማታ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፥ ከጐረቤት ቡና መጠራራት፥ እቁቡ፥ ዕድሩ፥ ሰንበቴው፥ የጽዋ ማኅበሩ፥ መከባበሩ፥ ይሉኝታው፥ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባሉ፥ ይቅር ለእግዚአብሔር ማለቱ፥ ዘመድ አዝማድ መጠያየቁ፥ በነፃነት መውጣት መግባቱ፥ በራስ ቋንቋ መግባባቱ፥ ክብረ በዓላቱ፥ አሁን አሁን መሠረቱን እየለቀቀ መጣ እንጂ አለባበሱ፥ ወጋወጉ፥ ተረታተረቱ፥ ሥነ ቃሉ፥ ሥነ ጽሑፉ፥ ሥነ ሥዕሉ፥ ፊደሉ፥ ወዘተ. . .  እነዚህን ሁሉ በአንድ ጊዜ ማጣት ከባድ ነው።

          ከቤተሰብ መካከል ወጥቶ፥ ባዶ ቤት ታቅፎ ቴሌቪዢን ላይ አፍጥጦ መዋሉ ሆድ ያስብሳል፥ ያስከፋል፥ ያስለቅሳል፥ ለምን መጣሁ ያሰኛል። የሚጠይቅ ዘመድ፥ የሚያነጋግር ጐረቤት ባለመኖሩ ያስጨንቃል። ወደ ሀገር ቤት ስልክ ስንደውልም፦ «ቤት ተዘግቶብኝ ነው የምውለው፤» የዘወትር ሮሮ ነው። መማረራችንን ለሚመለከተው ወድደን ፈቅደን ሳይሆን እንደ ብሔራዊ ውትድርና በግዳጅ የመጣን ነው፥ የሚመስለው። በአውሮፓ የኢትዮጵያ ስደተኞች፥ አንድ ስደተኛ ለፖሊስ እጁን ሰጥቶ ጥገኝነት ሲጠይቅ «ቀዘቀዘ፤» ይሉታል። አገር ቤት ቪዛ ስናገኝ የጋለው ሰውነታችን፥ ባሕር ማዶ ከደረስን በኋላ ይቀዘቅዛል፥ ከዜሮ በታች ይወርዳል፥ በረዶ ይሠራል። የትዳሩም ኹኔታ እንደዚያው ነው፥ የምንጠብቀውና የሚኾነው የተለያየ ነው፥ ያንጊዜ ትዳሩ ማሞቂያ የማያድነው ቀዝቃዛ ይሆናል፥ በተለይም በክረምት ወራት አገር ምድሩ በረዶ፥ ትዳሩም በረዶ ሲሆን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል።

          ቀድሞ የሄደው ወይም የሄደችው፥ የሀገሩን ባሕል ለምደው፥ የኑሮውን ዘይቤ ተዋህደው፥ የሀገሩን ሰው መስለው ስለሚኖሩ፥ «ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ፤» ከሆኑት የትዳር ጓደኞቻቸው ጋር ጠባይ ለመግጠም ትንሽ ይቸገራሉ። «ያመጣኸኝ፥ ያመጣሽኝ ለዚህ ነው? በል ተጫወትብኝ፥ በይ ተጫወቺብኝ፤» መባባሉ የዘወትር ጸሎት ነው። አዲስ የመጣነው የቀደሙትን መረዳት እንደሚያቅተን ሁሉ፥ የሰነበቱትም አዲስ የመጣነውን ለመረዳት ያቅታቸዋል። የሰነበቱት፥ የለመዱት፥ አባሻ እንዳልሆኑ ሁሉ፥ «አይ የአበሻ ነገር፤» እያሉ ያማርራሉ፤ አዲስ የመጣነው ደግሞ፦ «ምን ጉራቸውን ይነዛሉ፤» እንላለን። ሳናውቀው ተለያይተናል፥ ተራርቀናል። እዚህ የሚያስቀው እዚያ ያናድድ ይሆናል፥ እዚያ የሚያናድደው ደግሞ እዚህ ያስቅ ይሆናል። በባቢሎን መግባባት ያቃታቸው እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ለያይቶባቸው ነው፥ እኛ ግን አንድ ዓይነት ቋንቋ እየተነጋገርን መግባባት ያቅተናል። በውይይት እንዳንፈታው ለጊዜው የአመለካከት ልዩነት አለ፥ አንድም አልለመደብንም። ለሰው እንዳንነግረው፥ ይቅርታ ይደረግልኝና ሰው በራሱ ችግር ፈጣሪ እንጂ ችግር ፈቺ አይደለም። ትንሽ ነገር የሰማ እንደሆነ በዚያ በመከረኛ ስልክ በአራቱም ማዕዘን ያዳርሰዋል፥ ለአንደኛው የተቆረቆረ መስሎ ያባብሰዋል። ዘመድ አዝማድም ቢሆን ያው ነው።

          እርግጥ አበሻው እንደ ጨው ዘር ተበትኖ የሌለበት ሀገር የለም። ከሀገር ቤቱ ባይተካከልም እንግዳ መቀበልና ሀገር ማስለመድ ተከትሎን መጥቶ አብሮን አለ። በመሆኑም በእንግድነት ወራት እንደ ታቦት የሚያጅበን፥ ልነጠፍላችሁ ልጐዝጐዝላችሁ የሚለን ብዙ ነው። ነገር ግን የሀገር ቤቱን የቻይና ዕቃ ይመስል አይበረክቱም፥ አይሰነብቱም። ወረተኝነት ከሀገር ቤቱ ይልቅ በውጪው ዓለም ይጸናል። የትዳር ጓደኞቻችንም ቢሆኑ እንደ እንግድነት ወራት አይሆኑልንም፥ እኛም ብንሆን መጠበቅ የለብንም። ምክንያቱም ሁልጊዜ ሙሽርነት የለምና። 

          በሌላ በኲል ደግሞ የሁሉ ነገር መሠረት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም መስፋፋት፥ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ችግሮችን እየቀረፈልን ነው። ብቸኝነትን እያስረሳን ነው። በሳምንት አንድ ቀንም ቢሆን፦ እሑድ፥ እሑድ ሕዝቡ ለቅዳሴው ስለሚሰበሰብ፥ ወንጌልም ስለሚሰበክ፥ ከሃይማኖታችን እንዳንናወጥ፥ ከሥርዓታችን እንዳንወጣ፥ ትውፊታችንን እንዳንለቅ ሆነናል። ከዚህም በተጨማሪ ማኅበራዊ ኑሮአችንን እንድናጠነክር ረድቶናል። በሐዘንና በደስታ ጊዜ መፈላለጉ አለ። በዓል ሲሆን፥ ልጅ ወልደው ክርስትና ሲያስነሡ፥ ዝክር ሲያዘክሩ፥ ተዝካር ሲያወጡ፥ ልጅ ሲያስመርቁ፥ ልክ እንደ ሀገር ቤቱ «ጠበል ቅመሱ፤» ይባላል። ሠርግ ሲኖር፦ «የደስታችን ተካፋይ ሁኑ፤» የሚል በወርቅ ቀለም የተጻፈ ካርድ ይደርሰናል። የጠፋው በወርቅ ቀለም የተጻፈ ንጹሕ ፍቅር ነው። ስንታመም የጠያቂ ችግር የለም፥ ሐዘን ሲያጋጥመንም የሚያጽናናን ሞልቷል። ለካስ ኢትዮጵያ ማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት የምንለው ዝም ብለን አይደለም።  ምክንያቱም፦ ሃይማኖቱ፥ ሥርዓቱ፥ ትውፊቱ፥ ባህሉ፥ ዜማው፥ ሁሉም ነገር ያለው በወስጧ ስለሆነ፥ እርሷ እስካለች ድረስ ኢትዮጵያ አለች፤ በመሆኑም ከሀገራችን የወጣን አይመስለንም። እንዲህም ሲባል፦ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ችግር የለም ማለት አይደለም። የዓለምን እርሾ ማለትም የፖለቲካውን እና የዘረኝነቱን አሮጌ እርሾ ይዘን በመምጣት፥ የማንድን የቤተ ክርስቲያን በሽታ የሆንን ጥቂት አይደለንም። ቤተ ክርስቲያንን የንግድ ቤት ያደረግን፥ እንደመዥገር ተጣብቀን ደሟን የምንመጥጥ፥ ርግቦችን የምንሸጥ (የዋሃንን የምናታልል)፥ «ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል የሚል ጽሑፍ አለ፤ እናንተ ግን የሌቦችና የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት፤» የሚለው ተግሣፅ የወደቀበን አመጸኞች መሆናችን ገሀድ ከወጣ ሰንብቷል። በመሆኑም የያኔው ዘመን የጌታችን ጅራፍ፥ የሐዋርያት ዘመን የመንፈስ ቅዱስ አለንጋ ዛሬም ያስፈልጋል። ስለዚህ ዓይናችሁን ከእኛ ላይ አንሥታችሁ፥ እንዳትሰናከሉ ወደ መስቀሉ መመልክት ነው፥ ወደ ርኅርኅተ ልቡና ወደ እመቤታችን ማንጋጠጥ ነው፥ በመከራ መካከል በትዕግሥት ያለፉትን ቅዱሳንን የጸኑትን ማሰብ ነው።

          እንግዲህ፦ የቤተ ክርስቲያን መፍትሔነት እንደአለ ሆኖ ከእኛ የሚጠበቅ ብዙ ነገር አለ። ይኸውም፦ አስቀድመን ወደ ውጪው ዓለም በመውጣት የሀገሩን ኑሮ የለመድን ሰዎች የሀገር ቤቶቹን ከመምጣታቸው በፊት በደንብ ማስረዳት ይኖርብናል፥ የምንሸሽገው ነገር መኖር የለበትም። ድብብቆሽ መጫወቱ ለማንኛችንም ቢሆን የሚበጅ አይደለም። ሁሉ ነገር ታውቆ ከተመጣ ሸክሙን ቢያንስ ግማሽ ያህል ይቀንሰዋል። ያንጊዜ የመጣንበትን አዲስ አካባቢና አዲስ የኑሮ ዘዴ ቶሎ ለመልመድ እንችላለን። ይኸውም ተመሳስሎ ለመኖር ያህል እንጂ ፈጽሞ የመለወጥ አይደለም። እርግጥ መሆን ላይቻል ፈረንጅ የሆኑ መስሏቸው አበሻነታቸውን ሙሉ በሙሉ የለቀቁ አይጠፉም። እነዚህም፦ የራሳቸውን አጥተው የሌላውን ናፍቀው አውላላ መንገድ ላይ የወደቁ፥ ወደፊትም ወደኋላም ማለት አቅቷቸው መካከል ላይ ተቀርቅርው የቀሩ ናቸው። ፈረንጅ እንዳይሏቸው፦ የፈረንጅ ሥነ ሥርዓት የላቸውም፥ አበሻ እንዳይሏቸው፦ የአበሻ ይሉኝታ የላቸውም። ስለሆነም፦ አዲሱን አካባቢ መስለን እንኑር ማለት፦ የራሳችንንም ሳንለቅ መሆኑን መርሳት አይገባም። ማንም ሳያስገድደን የራስን መጣል፥ ማንነትን ማጥፋት እብደት ነው።

          ሌላው ልናስተውለው የሚገባን ቁም ነገር ደግሞ በውይይት ማመን እና ማሳመን መቻልን ነው። በምንወያይበት ጊዜም ከአገር ቤት የመጣነው ሰዎች ለጊዜው ማሰብ የምንችለው እንደ ሀገር ቤት መሆኑን ሌላው ክፍል መረዳት ይኖርበታል። ይኽንንም ሀገር ቤታዊ አስተሳሰብ አክብሮ መቀበል እንጂ በሰለጠነ ሀገር ስለተኖረ ብቻ እንዲሁ በባዶ፥ የሀገር ቤቱን አስተሳሰብ ማጣጣሉና ማብጠልጠሉ ጥቅም የለውም። የውይይት ዓላማው የሌላውን አሳብ አክብሮ ማድመጥ እንጂ ማጣጣል አይደለም። ውይይት ሲባል ደግሞ፦ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንጂ ውኃ በቀጠነ ትዳሩን የቀበሌ የውይይት ክበብ ወይም የግምገማ መድረክ ልናደርገው አይገባም። አለበለዚያ ስሕተት ፈላጊዎች፥ ነገር አነፍናፊዎች፥ ጠጉር ሰንጣቂዎች ሆነን ነው የምንቀረው። በዚህ በውጭው ዓለም የኖሩ ሰዎችም የሚያስቡት እንደሰነበቱበት አካባቢ በመሆኑ ከሀገር ቤት የመጣነው ደግሞ ያንን ልንረዳላቸው ይገባል፡፡ እርግጥ ከአገር ቤት መጥቶ እንደ ሀገር ቤት የማያስብ አጉል ሰለጠንኩ ባይ እንዳለ ሁሉ፥ በሰለጠነውም ዓለም ተቀምጦ እንደ ፊውዳል ዘመን የሚያስብ አይጠፋም። ይህም በትዳርም ይሁን በሌላ ወደ ውጭው ዓለም በመጡትና በሰነበቱት መካከል የሚፈጠር ክፍትት ነው።

          እንኳን የውጪውን አካባቢ ከለመዱት ጋር ቀርቶ፥ በሀገር ቤትም ቢሆን በአንድ አካባቢ ኖረን፥ ወደ ትዳር ዓለም በምንገባበት ጊዜ በአንድ ጀንበር ወደ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ መምጣት አይቻልም። ጊዜ ይጠይቃል፥ ሆደ ሰፊ፥ ነገር አላፊ፥ ትዕግሥተኛ መሆን ያስፈልጋል። በሂደትም ቢሆን በመቻቻል ትንሽ እናቀራርበው ይሆናል እንጂ ሙሉ በሙሉ በአስተሳሰብ አንድ መሆን ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። እርግጥ ለክፉም ሆነ ለበጎ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው አይጠፉም። እነዚህም፦ «ባል እና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ፤» የሚባሉት ዓይነት ናቸው።

          የውጪውን ዓለም የአኗኗር ዘዴ ስለሰማነው ወይም ስላነበብነው ብቻ አወቅነው ማለት አይደለም። በውስጡ ማለፍ ያስፈልጋል። «ዛፍ የሚቆረጠው በመጥረቢያ ነው፤» የሚለውን ማወቅና ዛፉን በመጥረቢያ መቊረጥ ይለያያል። ለምሳሌ በአውራ ጐዳና ላይ (High way) ስለመንዳት መስማትና ሲነዳም ማየት ከባድ ነው፥ ከገባንበት ከለመድነው በኋላ ግን፦ ሰዓት ለመቆጠብም፥ መንገድ ለማሳጠርም የምንመርጠው፥ የሚቀልለንም እርሱ ነው። ስለሆነም፦ ስንሰማው የከበደን ነገር ስንገባበት ቀላል ሊሆን ይችላል፥ ስንሰማው የቀለለን ነገር ደግሞ ስንገባበት ከባድ ሊሆን ይችላል። እንግዲህ ወደ ውጪው ዓለም ስንመጣ ሁለት አዲስ ነገር ይገጥመናል፤ አንደኛው፦ ሀገሩ አዲስ ነው፥ ሁለተኛ፦ ትዳሩም አዲስ ነው፤ በመሆኑም ለመልመድ የምንሞክረው በአንድ ጊዜ ሁለት አዲስ ነገር ነው። ስለ ትዳርም ሆነ ስለውጭ ሀገር የሰማነው ክፉም ሆነ በጎ ነገር ተፅዕኖ ማድረጉ ስለማይቀር በውስጥ በኅሊና ፈተና መሆኑ ግድ ነው። የምናየውንና የምንሰማውን ነገር ቀድሞ ከሰማነው ጋር ቶሎ በማገናኘት ያድጋል። እንዲህ ዓይነት ችግር የሚመጣው፥ ከሀገር ቤት የመጣነው ሰዎች ነገሮችን ሁሉ በሀገር ቤት መዝገበ ቃላት ብቻ ስንተረጉም፥ በውጪው ዓለም የሰነበቱት ደግሞ በውጭው ሀገር መዝገበ ቃላት ብቻ ሲተረጉሙት ነው። ትዳር ደግሞ የሚፈልገው የጋራ በሆነ በአንድ አይነት መዝገበ ቃላት መተርጐምን ነው።
         
          መቼም ውለን አድረን አዲሱን አካባቢ መልመዳችን አይቀርም። ነገር ግን የኑሮውን ዘዴ ከመልመድ ባሻገር ጭልጥ ብለን በውጭው ባሕል ተጠልፈን እንዳንጠፋ ከምንም በላይ ልንጠነቀቅ ይገባል። ጥሩ የሆነውን ባሕላቸውን መያዝ፥ ከመጥፎው ባሕላቸው ግን አርባ ክንድ መራቅ ያስፈልጋል። ያዕቆብ በሴኬም የእርሻ መሬት በመቶ በጎች ገዝቶ ነበር። በዚያም መሠዊያውን አቆመ፤ የእስራኤልንም አምላክ ጠራ። ዘፍ ፴፬፥፲፱። ሀገሪቱ የአሕዛብ መኖሪያ ናት። የያዕቆብን ልጅ ዲናን የአሕዛብ ጎረምሳ ያስነወራት፥ ከክብር ያሳነሳት በዚያ ነው። ያዕቆብም ልጁን ዲናን የኤሞር ልጅ እንዳስነወራት ሰማ፤ ሰምቶም ልጆቹ ከብቶቻቸውን ይዘው ከምድረ በዳ እስኪመለሱ ዝም አለና ሲመለሱ ጠብቆ ነገራቸው። እነርሱም ፈጽመው ደነገጡ፥ እጅግም አዘኑ፥ ተቈጡም። በዚህም ምክንያት ብዙ ደም አፈሰሱ። ዘፍ ፴፬፥፩-፴፮። ይህም የሆነው የእስራኤል ሃይማኖት፥ ሥርዓትና ባሕል ከአሕዛብ ጋር ፈጽሞ ስለማይገጥም ነው። በሂደት ግን በአሕዛብ ባሕል ሙሉ ለሙሉ ሊዋጡ ትንሽ ቀርቷቸው ነበር፥ በጣኦቶቻቸውም ተስበው ነበር። በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር፥ ያዕቆብን፦ «ከሴኬም ወጥተህ ወደ ቤቴል ሂድ፤» አለው። ያዕቆብም ቤተሰቦቹንና ከእርሱ ጋር ያሉትን፦ «ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶች አማልክትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ንጹሐንም ሁኑ፤ ልብሳችሁንም እጠቡ፤ ተነሡና ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ቀን ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው፥ ከመከራም አድኖ ላሻገረኝ ለእግዚአብሔር መሠዊያን እንሥራ፤» አላቸው። እነርሱም በእጃቸው ያሉትን እንግዶች አማልክት ሁሉ፥ በጆሮአቸውም ያሉትን ጉትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው ዛፍ በታች ቀበራቸው። ዘፍ ፴፭፥፩-፬። እግዚአብሔር አብርሃምንም «ከሀገርህ፥ ከዘመዶችህም፥ ከአባትህም ቤት ተለይተህ ውጣ፤ እኔ ወደማሳይህም ምድር ሂድ።» ብሎት የነበረው፥ ካራን የጣኦት ምድር፥ አባቱ ታራም ጣዖት ሠርቶ ሻጭ በመሆኑ፥ ከዚህ መካከል እንዲወጣ ነው። ምክንያቱም ለመንፈሳዊ ሕይወት ከማይስማማ ቦታ መዋል ማደር፥ ብርቱውን ደካማ፥ ትጉኁን ሐኬተኛ፥ ሊያደርገው ስለሚችል ነው። ዘፍ ፲፪፥፩።

          በውጭው ዓለም ያለው ሌላው ትልቁ ችግር ልቅ የሆነው ነፃነት ነው። ነፃነት ደግሞ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘው ጸጋ ነው። ይሁን እንጂ አጠቃቀሙን ካላወቁበት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። አዳም፦ እግዚአብሔር እየነገረው፥ የሚሞትበትን ፍሬ የበላው፥ በተፈጥሮ የተሰጠውን ነፃነት ተጠቅሞ ነው። እግዚአብሔር «አትብላ፤» ብሎ የጾምን ሕግ የሠራለት፥ ነፍጐት ሳይሆን በልቅ ነፃነት እንዳይጐዳ ልጓም ሲያበጅለት ነበር። ዘፍ ፪፥፲፯፣ ፫፥፮። በውጭው ዓለም ልጅን መቅጣት፥ የትዳር ጓደኛን ቀና ብሎ ማየት፥ ፖሊስ ሊያስጠራ ወደ እስር ቤት ሊያስወስድ ይችላል። የትዳር ጓደኛን እንኳን መምታት መገፍተር እንኳ ትልቅ ዕዳ ነው። ይህ ልቅ ነፃነት ለነጮቹም ቢሆን አልጠቀማቸውም። በእነርሱ ዘንድ የሰመረ ትዳር ውድ ነው። ፍርድ ቤቶችን ያጨናነቀው የትዳር ጭቅጭቅ ነው። ከዚህ የተነሣ ሳይጋቡ በጓደኝነት ብቻ አብረው ይኖራሉ፥ ለመውለድም አይፈልጉም።

          ሴት ልጅ ከፍላጐቷ ውጪ ባለቤቷ ከቀረባት ደፈረኝ ብላ መክሰስ ትችላለች፥ የዓይኑ ውኃ ካላማራትም ውጣልኝ ልትለው ገደብ የሌለው መብቷ ነው፤ በፍርድ ቤት ከተለያዩም ተጠቃሚዋ ሴት ልጅ ናት። ለልጆች ተብሎ በየወሩ ከደሞዙ ይገብራል። ከዚህም ሌላ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ታገኛለች። መኖሪያ ቤትም በአነስተኛ ኪራይ ይሰጣታል። ለምሳሌ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ዶላር የሚከራየውን ቤት በአንድ መቶ ሃምሣ ዶላር ብቻ ልትከራይ ትችላለች። ነጮቹ ይኽንን ለምደው፥ ሁለት ወልደው፦ «ትዳር በቃኝ፤» የሚሉበት ጊዜ ይበዛል። ከዚህ የተነሣ ወንዶቹ ለትዳር ብለው ባርነትን ወይም ተፋትተው ባርነትን፥ ከሁለት አንዱን ይመርጣሉ። የእኛም ሴቶች ይኽንን ቍም ነገር ብለው፥ ከሃይማኖትም፥ ከሀገር ባሕልና ወግም ውጪ በሆነ መንገድ ሲጓዙ እጅግ ያሳዝናል። ወንዶችም ብንሆን ለፍቺው የምናደርገው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፤ ለትዳራቸው የማይታመኑ ደካሞች ብዙ ናቸው። በሃምሣ በስድሣ ዓመታቸው፥ የልጆቻቸውን እናት አሰናብተው የአሥራ ሁለት ዓመት ልጃገረድ ያምራቸዋል፥ በዕድሜ ልጆቻቸው ከሆኑት ጋር መቅበጥ ያስደስታቸዋል። ሀገር ቤት ለእረፍት የገቡ እንደሆነ በስመ ውጪ የብዙ እኅቶችን ሕይወት ሳያጨልሙ አይመለሱም።  «This is America» እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በየቦታው ይጠቀሳል። እርግጥ፥ ሀገሩ አሜሪካ ወይም አውሮፓ መሆኑ በማንም ዘንድ የታወቀ ነው። ያላወቅነው ነገር ቢኖር፥ እኛ፥ በወረቀት አንጂ በሌላ አሜሪካዊ ወይም አውሮፓዊ አለመሆናችንን ነው። ማንነትን አለማወቅ ደግሞ የድንቊርና ድንቊርና ነው። ማንነታችን ደግሞ፦ ሃይማኖታችን፥ ሥርዓታችን፥ ትውፊታችን፥ ባሕላችን፥ ቋንቋችን፥ ፊደላችን ወዘተ. . .  ነው።

          የሚገርመው ነገር ወንዶችም ሆኑ ሴቶቹ ትዳራቸውን ካፈረሱ በኋላ ለአንድም ቀን ደስተኛ አይሆኑም። እንዲያውም በእልህ፥ አንዱ ሌላውን ለማብሸቅ ያልሆነ ነገር ውስጥ ሲገቡ ይታያሉ። ነገር ግን ሕይወታቸውን፥ ኑሮአቸውንም፥ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ከማጐስቆል በስተቀር የሚያገኙት ትርፍ የለም። በመጨረሻም ተደፍቶ የማይታፈስ ውኃ ይሆንባቸውና የጸጸት እሳት ታቅፈው ይቀራሉ። መድኃኒቱ የበደልነውን ሰው ይቅርታ ጠይቀን፥ እግዚአብሔርንም በንስሐ ምሕረትን ለምነን ከጠፋንበት መመለስ፥ ከወደቅንበት መነሣት ብቻ ነው። ያንጊዜ ያረጀው ይታደሳል፥ የተሰበረው ይጠገናል፥ ክፍተቱ ይሞላል፥ የሞተው ሕያው ይሆናል። ጠፍቶ እንደተገኘው ልጅ ልንሆን ይገባል፤ የጠፋው ልጅ፥ «ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ። እንግዲህ ወዲህስ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ፤» አለ። ወደ አባቱም ተመለሰ። አባቱም ከሩቅ አየውና ራራለት፤ ሮጦም አንገቱን አቅፎ ሳመው። ያማሩ ልብሶችን አለበሰው፥ ለጣቱ የወርቅ ቀለበት፥ ለእግሩም ጫማ አደረገለት፥ የሰባም ፍሪዳ አረደለት። ሉቃ ፲፭፥፲፩-፳፫። ለእኛም ይህ ድፍረት ያስፈልገናል፤ «ከእንግዲህ ወዲህ ባልሽ ልባል አይገባኝም፥ አንደ ቤት ሠራተኛ ቁጠሪኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስትህ ልባል አይገባኝም፥ እንደ ቤት ሠራተኛ ሆኜ ላገልግልህ፤» እያልን ወደ ትዳራችን እንመለስ። ልባዊ በሆነ ትኅትና የማናሸንፈው ኃይል በዚህ ምድር ላይ የለም። ክርስቶስ ስለ ፍቅር በመስቀል ላይ መሸነፉን አንርሳ፤ እርሱ ማሸነፍ እየቻለ ለጠላቱ በመስቀል ላይ ከተሸነፈ፥ እኛ ማሸነፍ የማንችለው፥ ለጠላታችን ሳይሆን፥ ለአካላችን (ለትዳር ጓደኛችን) ብንሸነፍ ምንድነው? ክርስቲያን የሚለውን ከስም በላይ የሆነውን ስም መሸከማችን ክርስቶስን መስለን ለመኖር አይደለምን?

8 comments:

 1. EgizehAbiher yistiln, Kale Hiywotn Yasemalin,Mengiste Semayat Yawrsiln Abatachin!Silitidar kastemarun zend, betam yemiyaschenkegn neger silalegn- yesowon erdata/mikir/timhirt be Eyesus sim efelgalehu. Ene yeminorew ke set godegnaye gar and-bet wiste new. Esua Muslim nat. Himanotuan endemitkeyrilgn tesfa gebtalign sileneber abiragn enditinor wosenku. Abiragn eyenorech sahle saytaseb argiza lidj woledech. Himanotuan gin lemekeyer eskahun alefelegechim. Endewum fekadegna yehonech alemehonan negerechign. Enen lemayez ena lemasser yaderegechu chewata ena matalel endehone teredichalehu. Bemenfessawi neger lay meweyayet atifelgim. Ahun, enem gira gebitognal, Min marege endalebign alawkim. Lijunim kirstina enkuan alasnesahutim. Enem sirayen silemawk, ke betekirstian eyeraku new yalehut. Este Ebakowon yirdugne. Akibarewo, from Minnesota, America.

  ReplyDelete
 2. What a lecture...i really like it keep it up..May God be with you Guys..

  ReplyDelete
 3. Kale Hiwetn Yasemawot!
  Mechem befikr abro lemenor yemifelg ye-bete-kirstian sew kebeki belay yehone timhrt ena mekr new. እኛ ማሸነፍ የማንችለው፥ ለጠላታችን ሳይሆን፥ ለአካላችን (ለትዳር ጓደኛችን) ብንሸነፍ ምንድነው?ክርስቲያን የሚለውን ከስም በላይ የሆነውን ስም መሸከማችን ክርስቶስን መስለን ለመኖር አይደለምን? yehe becha beke new.
  Tsgawon Yabzalot!!!

  ReplyDelete
 4. አባታችን ቃለሕይወት ያሰማልን፡፡

  የውጭዎቹ ብቻ እንዳይመስሉዎት እኛ እዚህ መግቢያ መውጫው ጠፍቶናል፡፡

  ዛሬ ለዘመናት ኢትዮጵያዊነት በሚባለው ማንነት ውስጥ የኖረውን መሠረታዊ የመንፈስ ልዕልና ከኢትዮጵያ ተጠራርጎ ሊወጣ ጫፍ ላይ የደረሰ ይመስለኛል (እንደው ጨርሶ ሞቷል ላለማለት)፡፡ ዛሬ ሳይጋቡ ተዳብለው የሚኖሩ፣ ከተጋቡ በኋላ አሥረሽ ምቺው ሲያጧጡፉ የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው የትየለሌ ነው፡፡ እድሜ ለሳተላይት ዲሽ! እስከጋብቻ ድረስ በድንግልና ጸንቶ መኖርማ “ከፋራነት” ከተቆጠረ ሰንብቷል፡፡

  የዩኒቨርሲቲዎቻችንን የኤችአይቪ መናኸሪያ መሆን ለጊዜው እንተወውና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በየቦታዎቹ የሚያዘጋጇቸውን ፓርቲዎች መመልከቱ ነፍስን ያሳቅቃል፡፡ “መጥኔ ለወለደ!” ያሰኛል፡፡ ሥልጣኔ ማለት ኤምቲቪን ከነምናምንቴው መገልበጥ ሆኗል፡፡ ወላጆችም ታላላቆችም ይህንን ፊትለፊት ሲገሥጹ አይታይም፡፡ አንዳንድ ኤንጂኦዎች (አንዳንድ ሰዎች ኤንጅቦዎች ይሏቸዋል፡፡) ተዋልዶንና የተዋልዶጤናን በተመለከተ “በየትምህርት ቤቱና በሬድዮ ጣቢያዎች ትምህርት እንሰጣለን፡፡” ቢሉም ትምህርቱ ማሰሪያው “ኮንዶም ተጠቀሙ፡፡” “ላልተፈለገ እርግዝናም ሆነ ለአባለዘር በሽታዎች መፍትሔ ኮንዶም ነው፡፡” “ኮንዶምን በመጠቀም እንደልባችሁ ተዝናኑ፡፡” የሚሉ መልእክቶች ገንነው ይደመጡባቸዋል፡፡ በአንዳንድ የሬድዮ ፕሮግራሞች ላይ “ከወጣቶች ጋር የተደረጉ” እየተባሉ የሚቀርቡ ቃለምልልሶችም ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ተራክቦን “በጥንቃቄ” እስከ ተከወነ ድረስ ምንም ዓይነት ችግር የሌለውና ሰው ሁሉ የሚያደርገው እጅግ አስፈላጊ ነገር አስመስለው ያቀርቡታል፡፡ የሚያመጣውን ማኅበራዊ ምስቅልቅል አያነሡትም፡፡ እነዚህ “ለወጣቶች” እየተባሉ የሚቀርቡት መርሐግብሮችና ሳተላይት ዲሽ ጉድ እያፈሉ ነው፡፡ ደግሞ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡ በየሬድዮ ጣቢያው ላይ ያገኟቸዋል፡፡ ወንዶች አስተማሪዎች ዘንድ ቀርበው “የምትፈልገውን ሁሉ አደርግልሃለሁ፡፡” በሚል ራስን የሚያዋርድ ተማጽኖ የፈተና ውጤት እንዲሻሻልላቸው የሚፈልጉ ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ ኤች አይ ቪ እንደድሮው መፈራቱ ቀርቷል፡፡ ፈረንጆቹ የሚያቀርቡልን እድሜ ማራዘሚያ እያለ ምንችግር አለ?! እርግዝናም ጥንቃቄ እስካለ ችግር አይሆንም፡፡ አደባባይ ላይ በተሰቀለ የኮንዶም ማስታወቂያ ላይ “Make your life sensational” ተብሎ ከታወጀ ቆየ፡፡ እርሱን ማስታወቂያ በጎንዮሽ ሳየው “your life will never be sensational without it. So, use it!” የሚል ይመስለኛል፡፡

  ቤተክርስቲያናችንም በቀድሞ ዘመን የነበራትን መንፈሳዊ ልዕልናዋን ጠብቃ ሕዝቡን ለመንፈሳዊ ልዕልና የማብቃት ዐቅም በተበተቧት አስተዳደራዊ የነቀርሳ ገመዶች አጥታዋለች፡፡ አስተዳደሩ ራሱ ቆሞ በቤተክርስቲያኗ ያሉ ነገሮችን ሥርዓት ከማስያዝ ይልቅ እርስበርሱ እየተባላ መቆም ስላቃተው ዛሬ በአዲስ አበባ ያሉ በርካታ ካህናት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ አይታመኑም፡፡ አይከበሩም፡፡ በፍቅረ ንዋይ፣ በአመንዝራነት፣ ሥር በሰደደ አላዋቂነት ክፉኛ ይታማሉ፡፡ አርአያ ክህነትን በማይጠብቁ እንደመጠጥ ቤት ባሉ ቦታዎች ቆብ ደፍቶ መስቀል አንጠልጥሎ መታየት በትእዛዝ የተነገረ እስኪመስል ድረስ በርክቷል፡፡ ክህነት ጸጋ መሆኑ ቀርቶ ሙያ (ፕሮፌሽን) ተደርጎ እየተቆጠረ ነው፡፡ በፈረንጆቹ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ የምንሰማቸው ኃጢአቶች መሰማት ከጀመሩም ሰንበትበት አሉ፡፡ ከእኛ ቤት ይልቅ ግን እኛ ሀገር ያሉት የፈረንጆቹ ቤቶች የተሻለ ዝምታ ሰፍኖባቸዋል፡፡

  በዚህ ከቀጠልን የሚቀጥለው ትውልድ የትናንቷ አባቶቻችን ያስረከቡን ቤተክርስቲያን ትኖረው ይሆን? እንጃ! እርሱስ በቤተክርስቲያን ይኖር ይሆን? እንጃ!

  እስኪእርስዎ ትንሽ ሀገርቤት ያለነውን የሚገሥጽ ነገር ይበሉን፡፡

  እግዚኦ ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ!

  ReplyDelete
 5. Abatachen Bewenet kale Hiwoten Yasemalen menegeset semayaten yawereselene.
  Be hiwotachen yalewen eweneta sele asetemarun bewnew betame dese yemile new

  ReplyDelete
 6. Ze-Nazareth(የናዝሬቱ)June 10, 2011 at 2:26 AM

  Abatachin Kalehiwot Yasemalin.
  @Mehari Gebremarqos
  Try to have your own blog. Your comments on most of the blogs is really Interesting.

  ReplyDelete
 7. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መልአከሰላም፡፡ምነዉ አንጠልጥለዉ ተዉት? እየጠበቅንዎት ነዉ ፡፡ቀጣዩ ክፍል ይቅረብልን ፡፡

  ReplyDelete
 8. Abatachjn burakewo yidresen.It is really really very interesting, true and informative. Please keep it up!!!

  ReplyDelete