Monday, May 9, 2011

ነገረ ቅዱሳን፦ ክፍል ፲፪

ካለፈው የቀጠለ. . . .
፫፥፫፦ ልሙጻንን ማንጻቱ፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ አያሌ ተአምራትን አድርጓል። «ጌታችን አየሱስም በምኲራባቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይመላለስ ነበር። ዝናውም በመላው ሶርያ ተዳረሰ፤ የታመሙትን ሁሉ፥ የተጨነቁትንም፥ ደዌያቸውም ልዩ ልዩ የሆነውን፥ አጋንንትም ያደሩባቸውን፥ ጨረቃ እያየ የሚጥላቸውን፥ ልምሾችንም ሁሉ አመጡለት፤ ሁሉንም ፈወሳቸው።» ይላል። ማቴ ፬፥፳፫-፳፬። ለምጻሙ ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ፦ «አቤቱ ከወደድህስ እኔን ማንጻት ይቻልሃል፤» እያለ በሰገደለት ጊዜ፦ «እፈቅዳለሁ ንጻ፤» ብሎታል። ያንጊዜም ከለምጹ ነጽቷል፤ ጌታም፦ ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሂድና ራስህን ለካህን አስመርምር፤ ምስክርም ሊሆንባቸው ሙሴ እንዳዘዘ መባህን አቅርብ፤» ብሎታል። ማቴ ፰፥፩-፬።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ወደ ኢየሩሳሌሞ ሲሄድ፥ በሰማርያና በገሊላ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ። ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው፥ «ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እዘንልን፤» አሉ። ባያቸው ጊዜ፥ «ወደ ካህና ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ፤ (ሳታውቁ በስሕተት፥ አውቃችሁ በድፍረት የሠራችሁትን ኃጢአት ተናዘዙ)፤ አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደነጻ ባየ ጊዜ፥ «ያዳነኝን ትቼ ወዴት እሄዳለሁ፤» ብሎ፥ በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ። በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ሰገደና አመሰገነው፤ ሰውዬውም ሳምራዊ ነበር። ጌታችንም፦ «የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ? ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?» አለ። እርሱንም፦ «ተነሥና ሂድ፥ እምነትህ አዳነችህ፤» አለው። ሉቃ ፲፯፥፲፩-፲፱።

፫፥፬፦ መጻጉዕን መፈወሱ፤

          ከዚህ በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም የበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ (የምሕረት ቤት) ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም (መደቦች፥ ደረጃዎች) ነበሩአት። እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ምሳሌዎች ናቸው። በዚያም እውሮችና አንካሳዎች፥ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር። (በሽተኞቹ፦ ዕውራን፣ አንካሶች፣ የሰለሉ፣ ልምሾ የሆኑ እና የተድበለበሉ አምስት ዓይነት ናቸው)። እነዚህም የአረጋውያን፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የካህናት እና የመነኰሳት ማለትም የአምስቱ ፆታ ምእመናን ምሳሌዎች ናቸው። እነዚያ (በሽተኞቹ) ተጠምቀው በጸበሉ ኃይል እንደሚፈወሱ፥ እነዚህ ደግሞ፦ ልጅነትን በምታሰጥ ጥምቀት ኃይል ሰይጣን የሚያመጣውን ፈተና ድል ያደርጋሉ።

          የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው (በሚባርከው) ጊዜ፥ ከውኃው መናወጥ (ከተባረከ) በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበር። መልአኩ የሚወርደው ውኃውን ለመቀደስና መሥዋዕት ለማሳረግ ነው። ቅዳሜ ቅዳሜ፦ አንድ አንድ በሽተኛ ይፈወስ ነበር፥ ይህም የማይቀር የማይደገምም ነው። አለመቅረቱ፦ «ተአምራት በአባቶቻችን ዘመን ይደረግ ነበር፥ በእኛ ዘመን ግን ቀረ፤» ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ ነው፥ አለመደገሙ ደግሞ በኦሪት ፍጹም የሆነ ድኅነት አለመሰጠቱን ለማጠየቅ ነው። መልአኩ የቀሳውስት ምሳሌ ነው።

          በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነ ድውይ ነበረ፥ ደዌ ጠንቶበታል፥ ዘግይቶበታልም። ጌታም፦ ያን ሰው በአልጋው ተኝቶ ባየ ጊዜ (በደዌ ዳኛ፥ በአልጋ ቊራኛ ተይዞ ብዙ ዘመን እንደቆየ ስለሚያውቅ) «ልትድን ትወዳለህን?» አለው። መዳን እንደሚፈልግ እያወቀ የጠየቀው፥ አንደኛ፦ አላዋቂ የነበረን ሥጋ መዋሀዱን ለማጠየቅ ነው፤ ሁለተኛም ለማስፈቀድ ነው። ሳያስፈቅድ ቢፈውሰው ኖሮ፥ በኋላ በዕለተ ዓርብ የጌታን ፊቱን በጥፊ ጸፍቶ በሚመሰክርበት ጊዜ፦ ምክንያት ባገኘ ነበር። ይኸውም፦ «ምነው ያዳነህን?» ሲሉት፥ «በቀለብላባነቱ አዳነኝ እንጂ መች አድነኝ ብዬ ለመንኩት፤» ባለ ነበር። ዛሬም ባለውለታዎቻቸውን በድለው ሲጠየቁ፦ «ለምኜሃለሁ?፥ ለምኜሻለሁ?፥ ለምኜዋለሁ?፥ ለምኜታለሁ?» የሚሉ አሉ።   

          በሽተኛው፦ የመዳን ጥያቄ በቀረበለት ወቅት፦ «ውኃው በተናወጠ ጊዜ፥ ከመጥመቂያው አውርዶ የሚያስጠምቀኝ ሰው የለም እንጂ መዳንሰ እወድ ነበር። ነገር ግን እኔ በመጣሁ ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይጠመቃል፤» ሲል መለሰ። እንዲህም ማለቱ፦ አንደኛ፦ ይህ የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ አውርዶ ሊያስጠምቀኝ ይችላል፥ ሁለተኛም፦ ከተከታዮቹ አንዱን ጉልበታም  ያዝዝልኛል ብሎ ነው። ጌታችን ኢየሱስም፦ «ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤» አለው። ወዲያውንም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ።

          ደዌ በአራት ምክንያት ይመጣል፤ ፩ኛ፦ ደዌ ዘንጽሕ (የንጽሕና ምልክት የሆነ ደዌ) ነው፥ ይህም፦ እንደ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ያለ ነው። እርሱም መምህሩ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ስለ ንጽሕና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ፤» ብሎታል። ፩ኛ ጢሞ ፭፥፲፭። ፪ኛ፦ ደዌ ዘዕሤት (ዋጋ ያለው ደዌ) ነው፤ ይህም እንደ ጻድቁ ኢዮብ ነው፤ «ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቊስል መታው፤» ይላል። ኢዮ ፪፥፯። ፫ኛ፦ ደዌ ዘመቅሠፍት ነው፤ ይህም እንደ ሳኦል እንደ ሄሮድስ ነው፤ «የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉ መንፈስም ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው።» ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፬። «ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው፥ በትልም ተበልቶ ሞተ፤» ይላል። የሐዋ ፲፪፥፳፫። ፬ኛ፦ ደዌ ዘኃጢአት እንደ መጻጉዕ ነው። ሠላሳ ስምንት ዓመት የታመመው በኃጢአቱ ነው።

፫፥፭፦ ሙታንን ማንሣቱ፤

          ኢያኢሮስ የሚሉት አንድ መኰንን ወደ እርሱ መጥቶ፦ «ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፤ ትድናለችም፤» እያለ ሰገደለት። ጌታችን ኢየሱስም ተነሥቶ ተከተለው፤ ደቀመዛሙርቱም አብረውት ነበሩ። ከመኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ አስለቃሾችን እና የሚንጫጩትን ሰዎች አየ። «ሹም ሲሞት ሃምሣ፥ የሹም ልጅ ሲሞት ደግሞ አንድ መቶ ሃምሣ፤» እንዲል ለቀስተኛው ብዙ ነበር። ጌታችንም፦ እንደሚያስነሣት ስለሚያውቅ፥ አንድም በነፍስ ሕያው መሆኗን ለማጠየቅ፥ «ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ የሞተች አይደለምና ፈቀቅ በሉ፤» አላቸው። እነርሱም፦ «የሞተና ያልሞተ መለየት የማይችለውን ይኽንን ያስነሣልኛል ብሎ ይዞት መጣ፤» ብለው በኢያኢሮስ ሳቁበት፤ አንድም፦ «መሞቷን አረጋግጠን ሬሣውን ያጠብን፥ የገነዝንም እኛ ነን፥ እንዴት አልሞተችም ይለናል፤» ብለው በጌታ ሳቁበት። ጌታም ሰዎቹ ከወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ብላቴናዪቱም ተነሣች። የተአምራቱም ዝና በሀገሩ ሁሉ ተሰማ። ማቴ ፱፥፲፰፥፳፮።

          የማርያም የማርታ አገር በምትሆን በቢታንያ አልዓዛር የሚባል ሰው ታሞ ነበር። ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው ፥ እግሩን በዕንባዋ ያጠበችው፥ በፀጉሯም ያበሰችው ናት። የአልዓዛር እህቶች ወንድማቸው በመታመሙ፦ «ጌታ ሆይ፥ ወዳጅህ ታሟል፤» ብለው ወደ ጌታ ላኩ፤ ጌታም እንደታመመ በሰማ ጊዜ፦ «ይህ ደዌ ለሞት የሚያበቃ አይደለም፥ አንድም ሙቶ ሊቀር አይደለም፥ እግዚአብሔር አብ በልጁ ህልው ሆኖ እርሱን አንሥቶ ጌትነቱ ይገለጥ ዘንድ ነው፥ አንድም የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ከሞት አንሥቶ በጌትነት ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ፤» አለ። ጌታችን፦ ማርያምን ማርታን እና አልዓዛርን የፍጹማን ፍቅር ይወዳቸው ነበር። ጌታችን የአልዓዛርን መታመም በሰማበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ፥ ከዚህም በኋላ ደቀመዛሙርቱን «ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ፤» አላቸው። ደቀመዛሙርቱም፦ ስለ እንቅልፍ የተናገረ መስሏቸው፥ «አቤቱ፥ ከተኛስ ይነቃል፤ ይድናልም፤ (የታመመ ሰው የተኛ እንደሆነ ጤና አግኝቶ ይነሣል)፤» አሉት። ጌታችን ግን የተናገረው ስለ ሞቱ ነበር። ከዚህ በኋላም፦ «ታምኑም ዘንድ (አስቀድሞ አውቆ የነገረን የባሕርይ አምላክ ቢሆን ነው ብላችሁ እንድታምኑ) በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እንሂድ፤» በማለት ገልጦ ነገራቸው። ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስም፦ አይሁድ ጌታን በክፉ እንደሚፈልጉት ስለሚያውቅ፥ ባልንጀሮቹን ደቀመዛሙርት፥ «እኛም ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሂድ፤» አላቸው።

          ጌታችን ቢታንያ በደረሰ ጊዜ፥ አልዓዛርን ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው፤ አልዓዛር የሞተው ረቡዕ ነው፥ ጌታ የደረሰው ቅዳሜ ነው። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አምስት ከ ሜ ርቆ ከደብረ ዘይት ወዲያ የሚገኝ መንደር ነው። ብዙ አይሁድ የአልዓዛርን እኅቶች ሊያጽናኗቸው በዚያ ነበሩ፤ ማርታ፦ ጌታችን እንደመጣ በሰማች ጊዜ፥ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን እንግዶችን ጥሎ መውጣት ስለከበዳት በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም፦ ጌታችንን ድውይ መፈወስ እንጂ ሙት ማንሣት የማይቻለው መስሏት፥ «ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ፤» አለችው። ጌታም፦ «አላመንሽም እንጂ ብታምኚ ወንድምሽ ይነሣል፤» አላት። ማርታም፦ የኋላውን የነገራት መስሏት፥ «ሙታን በሚነሡበት በኋለኛዪቱ ቀን እንዲነሣ አውቃለሁ፤» አለችው። ጌታም፦ «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል፥ (በእኔ ያመነ አይሞትም፥ በሥጋ ቢሞት በነፍስ ይድናል፥ ፈርሶ በስብሶ አይቀርም፥ ትንሣኤ ዘለክብር ይነሣል፥ አንድም በትንሣኤ ዘጉባዔ የማስነሣ እኔ አሁንም ላስነሣ እችላለሁ)። ይህንን ታምኛለሽን?» አላት። እርስዋም፦ «አዎን ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ፤» አለችው።

          ማርታ እምነቷን ከገለጠች በኋላ፥ ወደ ቤት ተመልሳ፥ «መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል፤» ብላ በቀስታ ለማርያም ነገረቻት። እርሷም ፈጥና ወደ እርሱ ሄደች፥ ጌታችን ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። በቤት የነበሩት ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሏቸው ተከተሏት። ጌታችን ካለበትም ደርሳ ከእግሩ በታች ሰገደችለትና፦ «ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤» አለችው። ጌታም ስታለቅስ፥ ከእርሷም ጋር የመጡ አይሁድ ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከና (መፍቀሬ ሰብእ ነውና በሐዘን ራሱን ነቀነቀና) «የት ቀበራችሁት?» አለ። እንዲህም ማለቱ፦ አላዋቂ የነበረን ሥጋ መዋሐዱን ለማጠየቅ ነው። አንድም አዳምን፦ አላዋቂ የሆነ የአንተን ሥጋ ለብሼ እፈልግሃለሁ ሲለው፦ «አዳም የት ነህ?» ብሎት ስለነበረ ያ እንደተፈጸመለት ለማጠየቅ ነው። አንድም፦ «ከሱናማዊቷ ሴት ለምን አነሳችሁ? እርሷ እንኳ ልጇ በሞተባት ጊዜ አጥባ፥ አጐናጽፋ፥ ከአልጋ ላይ አስተኝታ፥ በሯን ዘግታ ነቢዩ ኤልሳዕን ልትጠራ ሄደች እንጂ ለመቅበር አልቸኰለችም፤» ሲላቸው ነው። እነርሱም፦ «አቤቱ፥ መጥተህ እይ፤» አሉት። ጌታችንም ዕንባውን አፈሰሰ። አይሁድም፦ «ምን ያህል ይወድደው እንደነበር እዩ፤» ተባባሉ። ከእነርሱም መካከል፦ «ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይን ያበራው ይህ ሰው፥ ይህስ እንዳይሞት ሊያደርግ ባልቻለም ነበር?» ያሉ ነበሩ። እነዚህም ድውይ መፈወስ እንጂ ሙት ማንሣት የሚቻለው ስላልመሰላቸው ነው።

          ዳግመኛም ጌታችን በልቡ አዘነ፤ ወደመቃብሩም እያለቀሰ ሄደ፥ መቃብሩም ዋሻ ሆኖ በታላቅ ደንጊያ ተገጥሞ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ሳይደክሙ ዋጋ እንደማይገኝ ሊያስረዳቸው፦ «ድንጋዩን አንሡ፤» ብሎ ሥራ ሰጣቸው። ማርታም፦ «ጌታዬ ሆይ፥ አራት ቀን ሆኖታልና ፈጽሞ ሸትቶ (ተልቶ) ይሆናል፤» አለችው። ጌታም፦ «ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ አላልሁሽም ነበርን?» አላት። ድንጋዩንም ባነሡ ጊዜ፥ ጌታችን፦ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ፥ «አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ። እኔም ዘወትር እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤» አለ። ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ያቀናበት ምክንያት፦ «ይህን የማስነሣበት ሥልጣን ከአንተ ጋር አንድ ነው፤» ሲል ነው። ከዚህም ጋር ወደ አብ የጸለየበትን ምክንያት ሲናገር፦ «ነገር ግን አንተ እንደላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላሉት ሰዎች ይህን እናገራለሁ፤» ብሏል። አንድም ተአምራት እንዲደረግላችሁ በምትፈልጉበት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር አመልክቱ ለማለት፥ አብነት ለመሆን ነው። በታላቅም ድምፅ ጮኸ። አልዓዛርን ከመቃብር ውጣ አለው። የሥጋህም የነፍስህም ፈጣሪ እኔ ነኝ ሲል ነፍሱንና ሥጋውን አዋህዶ አስነሣው። ሞቶ የነበረውም እንደተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደታሰረ፥ ፊቱም በሰበን እንደተጠቀለለ ወጣ፤ ጌታም፦ ምትሀት እንደመሰላቸው ስላወቀ ፈጽመው ያምኑ ዘንድ፥ አንድም ያልጸና መስሏቸው ደግፈውት ነበርና፦ «እንግዲህስ ፍቱትና ተዉት ይሂድ፤» አላቸው። ከአይሁድም ብዙዎች አመኑበት፤ ከእነርሱም ወደ ፈሪሳውያን ሄደው የከሰሱት ነበሩ። ዮሐ ፲፩፥፩-፵፮።

፬፦ ቅዱሳን ያደረጉት ተአምራት፤

          የነቢያት አለቃ ሙሴ ተአምራታዊት በትር ነበረችው። እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፥ «ፈርዖን፦ ተአምራትንና ድንቅን አሳዩኝ ሲላችሁ ወንድምህን አሮንን፦ በትርህን ወስደህ በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት ጣላት፥ በለው፤ እባብም ትሆናለች።» ብሏቸው ነበር። እነርሱም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። የግብፅ ጠንቋዮችም በትራቸውን እባቦች አደረጉ። አሮን እባብ እንድትሆን የጣላት የሙሴ በትር ግን ሁሉንም ዋጠቻቸው። ይህን ብቻ ሳይሆን፦ ፩ኛ፦ ውኃውን ወደ ደም ለውጠዋል፤ ፪ኛ፦ የግብፅ ምድር እስኪሸፈን ድረስ ጓጉንቸሮችን (እንቁራሪቶችን) አውጥተዋል፤ ፫ኛ፦ በሰውና በእንስሳ ላይ ቅማል እንዲፈላ አድርገዋል፤ ፬ኛ፦ በግብፅ ምድር ሁሉ ተናካሽ ዝንቦችን አዝዘውባቸዋል፤ ፭ኛ፦ የግብፅ እንስሳት እንዲያልቁ አድርገዋል፤ ፮ኛ፦ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻሕኝ የሚያመጣ ቊስል እንዲወጣባቸው አድርገዋል፤ ፯ኛ፦ በሜዳ የቀረ ሰውና እንስሳ እስኪሞት ድረስ በረዶ አውርደውባቸዋል፤ ፰ኛ፦ የአንበጣ መንጋ ታዝዞ ከበረዶ የተረፈውን ሰብልና ዛፍ አጥፍቷል፤ ፱ኛ፦ ሦስት ቀን እና ሦስት ሌሊት ጽኑ ጨለማ ሆኗል፤ ፲ኛ፦ ከንጉሡ ከፈርኦን ጀምሮ የሁሉም ሰው የበኲር ልጆች ሞተው ምድሪቱ በጩኸት ተከድናለች። ዘጸ፯፥፲፬-፳፭፤ ፰፥፩-፴፪፤ ፱፥፩-፴፭፤ ፲፥፩-፳፱፤ ፲፩፥፩-፲። ከዚህም ሌላ ሙሴ፦ ቀይ ባሕርን በበትሩ ለሁለት በመክፈል ውኃው እንደ ግድግዳ እንዲቆም አድርጓል። ዘጸ ፲፬፥፳፩። እግዚአብሔር ያሳየውን እንጨትም ከመራራው ውኃ ውስጥ በመጣል እስራኤል ጣፋጭ ውኃ እንዲጠጡ ረድቷቸዋል። ዘጸ ፲፭፥፳፪-፳፮። መና ከሰማይ አውርዶላቸዋል፥ ከደረቅ ዓለትም ውኃ አፍልቆላቸዋል። ዘጸ ፲፮፥፩-፴፮፤ ፲፯፥፩-፯፤ ሌሎችንም ተአምራት እግዚአብሔር በሙሴ እጅ አድርጓል።

          ኢያሱ ወልደ ነዌም የዮርዳኖስን ወንዝ ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል። ኢያ ፫፥፩-፲፯። የኢያሪኮን ታላቅ የግንብ አጥር በጩኸት ብቻ አፍርሷል። ኢያ ፮፥፩-፳፯። ፀሐይ እንዳትጠልቅ ገዝቶ አቁሟታል። «ፀሐይም በሰማይ መካከል ቆመች፤ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል አልጠለቀችም፤» ይላል። ኢያ ፲፥፲፫።

          ነቢዩ ኤልያስ፦ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ፥ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናብ እንዳይዘንብ አድርጓል፥ ተመልሶም እንዲዘንብ ያደረገው እርሱ ነው። ፩ኛ ነገ ፲፯፥፩ ፤ ፲፰፥፵፪ ፣ ያዕ ፭፥፲፯። የሰራፕታዋን ሴት ዱቄትና ዘይት ባርኮላት የረሀቡ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ እንዳያልቅ አድርጎላታል፥ ልጇም ቢሞትባት አስነሥቶላታል። ፩ኛ ነገ ፲፯፥፰-፳፬። በመጐናጸፊያው የዮርዳኖስን ወንዝ ለሁለት ከፍሎ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ዐርጓል። ኛ ነገ ፪፥፩-፲፬።

          ነቢዩ ኤልሳዕ በመምህሩ በኤልያስ ስም እየተማጸነ በመምህሩ በኤልያስ መጐናጸፍያ ዮርዳኖስን ለሁለት ከፍሏል። ፪ኛ ነገ ፪፥፲፪-፲፬። ቢጠጡት ይገድል የነበረውን መርዛማ ውኃ ከአዲስ ማሰሮ ውስጥ ጨው አውጥቶ በመጨመር በእግዚአብሔር ስም ፈውሶታል። ማሰሮ የእመቤታችን፥ ጨው የኢየሱስ ክርሰቶስ፥ የውኃው መርዛማነት የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ ምሳሌዎች ናቸው። ከአዲስ ማሰሮ የወጣው ጨው የውኃውን መርዛማነት እንዳስወገደው፥ ከእመቤታችን የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስም መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አስወግዷል። ፪ኛ፥፲፱-፳፪።

          በቤቴል የሰደቡትንና ያዋረዱትን ብላቴናዎችም ረግሞ የዱር አራዊት ሰብረው አርባ ሁለቱን እንዲገድሏቸው አድርጓል። ፪ኛ ነገ ፪፥፳፫-፳፭። የደሀይቱን ሴት ዘይት ባርኮላት ዕዳዋን ከፍላ ልጆቿን ለባርነት ከመሸጥ አድኖላታል። ፪ኛ ነገ ፬፥፩-፯። ሱናማዊቷን ሴት በጸሎት ረድቷት ከሽማግሌ ባሏ ልጅ እንድትወልድ አድርጓታል፥ አድጐ በሞተባትም ጊዜ በጸሎቱ አስነሥቶላታል። ፪ኛ ነገ ፬፥፰-፴፯። በተመረዘው ምግብ ውሰጥ ዱቄት ጨምሮ ፈውሶታል። ሃያ የገብስ እንጀራና ጥቂትም የእህል እሸት ባርኮ መቶ ሰዎች ተመግበውት እንዲተርፍ አድርጓል። ፪ኛ ነገ ፬፥፴፰-፵፬። ሶርያዊው ንዕማንም በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከለምጹ እንዲድን አድርጐታል። ደቀመዝሙሩ ግያዝ ደግሞ «መምህሬ ልኮኝ ነው፤ ብሎ፥ በስሙ ዋሽቶ ፥ገንዘብና ልብስ በመቀበሉ፥  መንፈሰ እግዚአብሔር ገልጦለት በጠየቀው ጊዜ በመካዱ ረግሞ በለምጽ አንድዶታል።

          ከደቀመዛሙርቱ አንዱ እንጨት በሚቆርጠበት ጊዜ የምሳሩ ብረት ወልቆ ከዮርዳኖስ ወንዝ ገብቶበት ነበር። በዚህን ጊዜ፦ «ጌታዬ ሆይ፥ ወየው ወየው የተዋስሁት ነበር፤» ብሎ ወደ እርሱ ጮኸ። ኤልሳዕም ከእንጨት ቅርፊት ቀርፎ ወደ ባሕሩ ጣለው፥ ቅርፊቱም፦ ወደ ውስጥ ገብቶ ብረቱን ይዞ ወጣ። ብረት የአዳም፥ ባሕር የሲኦል፥ ቅርፊት የኢየሱስ ክርስቶስ፥ ኤልሳዕ የእግዚአብሔር አብ ምሳሌዎች ናቸው። ነቢዩ ኤልሳዕ ወደ ባሕር የላከው ቅርፊት ብረቱን ይዞ እንደወጣ፥ የባሕርይ አባቱ ወደ ዓለም የላከው ኢየሱስ ክርስቶስም፥ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር እንደወረደ፥ በአካለ ነፍስም ወደ ሲኦል ወርዶ አዳምን እና ልጆቹን አውጥቷል። ፪ኛ ነገ ፮፥፩-፯። ከሰማርያ በስተሰሜን ሃያ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ከተማ በዶታይን ተቀምጦ በሶርያ ቤተ መንግሥት በምስጢር የሚዶለተውን እግዚአብሔር እየገለጠለት ያውቅ ነበር። ይኽንንም ያወቀ የሶርያ ንጉሥ በፈረስ በሠረገላ በብዙ ሰራዊትም ባስከበበው ጊዜ የእሳት ሰይፍ ይዘው የሚጠብቁትን መላእክት አይቷል። የከበቡትንም ዓይናቸውን አሳውሮ ማርኳቸዋል። ፪ኛ ነገ ፮፥፰-፲፱።

          ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ   በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው አገኙ። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን  ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚሉት መቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር። እርሱም ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው። ቅዱስ ጴጥሮስም  ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና፦ «ወደ እኛ ተመልከት፤» አለው፤ እርሱም  ምጽዋት እንደሚሰጡት ተስፋ አድርጎ  ወደ እነርሱ ተመለከተ፤ ቅዱስ ጴጥሮስም፦  «ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ፤» አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤  ያን ጊዜም ቁርጭምጭሚቱ ጸና። ዘሎም ቆመ፤ እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእርሱ ጋር ወደ ቤተመቅደስ ገባ። ይህ ሰው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳዘዘው ወደ እነርሱ በመመልከቱ በሥጋም በነፍስም ተጠቅሟል። በሥጋ ተፈውሷል፥ በነፍስ ደግሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት ታድሏል። እኛም በስሙ ተአምር እንዲሠሩ ሥልጣን ወደተሰጣቸው  ቅዱሳን ብንመለከት የምንጠቀም እንጂ የምንጎዳ አይደለንም። የሐዋ ፫፥፩-፰።                   
          በሐዋርያት ዘመን ያመኑት ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ፤ «ይህ የእኔ ገንዘብ ነው፤» የሚል አልነበረም። የሐዋ ፬፥፴፪። ሐናንያና ሚስቱ ሰጲራ መሬታቸውን ሸጠው ለቤተ ክርስቲያን  ለመስጠት፥ ከአንድነቱ ለመግባት  ከወሰኑ በኋላ ሰይጣን ልባቸውን ከፈለባቸው፥ አሳባቸውን ሁለት አደረገባቸው። በዚህም ምክንያት ግማሹን በስውር አስቀምጠው፥ ግማሹን ብቻ ይዞ ሐናንያ ቀድሞ ሄደ፥ በሐዋርያትም እግር አጠገብ አስቀመጠ። ይህንንም ያደረጉት  «ሁሉን ካስረከብን በኋላ ማኅበሩ የፈረሰ እንደሆነ ተመልሰን ምን እንበላለን?» ብለው ተጠራጥረው ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት ቢጠይቋቸው  ተራ በተራ ገብተው፥ ምን ብለው መዋሸት እንዳለባቸው ተማክረዋል።
           ቅዱስ ጴጥሮስም፦  «ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልለው ዘንድ፥ የመሬትህንም ዋጋ ከፍለህ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ? ጥንቱን ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ይህን ነገር በልብህ ለምን አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አላታለልህም፤» አለው። ሐናንያም ይህንን ሰምቶ ሞተ። ይህ ከሆነ ከሦስት ሰዓት በኋላ ሚስቱ መጣች፥ የሆነውንም አላወቀችም ነበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስም፦  እስኪ ንገሪኝ መሬታችሁን የሸጣችሁት ይህን ለሚያህል ነውን? ብሎ በጠየቃት ጊዜ፥  «አዎን፤» ብላ ዋሸች።  እርሱም መልሶ፦ «እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንፈስ ትፈታተኑት ዘንድ እንዴት ተባበራችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግሮች በበር ናቸው፤ አንቺንም ይወስዱሻል፤» አላት። ያን ጊዜም ከእግሩ በታች ወድቃ ሞተች። ቅዱሳንን መድፈር አድሮባቸው የሚኖር መንፈስ ቅዱስን መፈታተን ነውና። የሐዋ ፭፥፩-፲። ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስ ጳፉ በምትባል ሀገር ገብተው ባስተማሩበት ጊዜ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለውን ሀገረ ገዢ ከማመን ለመከልከል፥ በርያሱስ የተባለው ጠንቋይ ተቃውሟቸው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ግን አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ትኲር ብሎ ከተመለከተው በኋላ፦ «ሽንገላንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ፥ የሰይጣን ልጅ፥ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ፥ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ (ወንጌልን) ከማጣመም አታርፍምን? እነሆ፥ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤» አለው። ወዲያውኑም ታወረ፤ ጨለማም ዋጠው፤ የሚመራውም ፈለገ። አገረ ገዢውም የሆነውን በአየ ጊዜ ተገረመ፤ በጌታችን ትምህርትም አመነ። የሐዋ ፲፫፥፬-፲፪።
        በቅዱሳን ሐዋርያት እጅ (ሥልጣን) በሕዝቡ ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የአካሉ ጥላ ያረፈባቸውን አያሌ በሸተኞችን ፈውሷል። የሐዋ ፭፥፲፪-፲፮። የአልጋ ቊራኛ ከሆነ ስምንት ዓመት የሞላውን ኤንያን፦ «ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስህ፥ ተነሥና አልጋህን አንጥፍ፤» ብሎ ፈውሶታል። በኢዮጴ፦ ጣቢታ የሚሏት ደግ ሴት በሞተች ጊዜ አስከሬኗን አጥበው በሰገነት ካስተኟት በኋላ ደቀ መዛሙርትን ልከው ቅዱስ ጴጥሮስን አስመጡት። እርሱም፦ «ጣቢታ ሆይ ተነሽ፤» በማለት ከሞት አስነሥቷታል።የሐዋ ፱፥፴፪-፵፪።
       ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ በልስጥራን፥ እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው አግኝቶ፥ «ተነሥና ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም፥ እልሃለሁ፤» በማለት ፈውሶታል። የሐዋ ፲፬፥፰-፲። በምዋርተኝነት መንፈስ እየጠነቈለች ለጌቶቿ ከፍተኛ ገቢ ታስገኝ የነበረችውንም ሴት ባገኛት ጊዜ፦ «መንፈስ ርኲስ፥ ከእርሷ እንድትወጣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ፤» በማለት ከቊራኝነት አላቋታል። የሐዋ ፲፮፥፲፮-፲፰።
          ቅዱስ ጳውሎስ እና ሲላስ፦ በዚህ ምክንያት በእግር ብረት ታስረው ተደብድበው ወደ ወኅኒ ቤት ተወርውረው ነበር። በዚህም እግዚአብሔርን አመሰገኑት እንጂ አላማረሩም። እስረኞቹም ተደንቀው ይሰሟቸው ነበር። በድንገትም የወኅኒ ቤቱ መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ። የሁሉም የእግር ብረቶቻቸው በተአምር ወለቁላቸው። የብረት መዝጊያዎችም በተአምር ተከፈቱ። የሐዋ ፲፮፥፳፭-፳፮። እግዚአብሔርም በቅዱስ ጳውሎስ እጅ ታላላቅ ሥራን ይሠራ ነበር። ከልብሱ ዘርፍና ከመጠምጠሚያው ጫፍ ቈርጠው እየወሰዱ በድውያኑ ላይ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ይፈወሱ ነበር፤ ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። የሐዋ ፲፱፥፲፩-፲፪።
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ በጢሮስ በሚያስተምርበት ጊዜ፥ ትምህርቱን እስከ መንፈቀ ሌሊት ድረስ አስረዝሞ ነበር። በዚያም ስሙ አውጤክስ የሚባል ጐልማሳ በመስኮት በኲል ተቀምጦ ሳለ ከባድ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ከእንቅልፉ ብዛት የተነሣ ከተኛበት ከሦስተኛው ፎቅ ወደ ታች ወድቆ፥ ሬሳውን አነሡት። ቅዱስ ጳውሎስም፦ ወርዶ በላዩ ላይ ወድቆ አቀፈውና፦ «ነፍሱ አለችና አትደንግጡ፤» ብሎ አረጋጋቸው። በመጨረሻም ከሞት አስነሥቶታል።

3 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete