Sunday, May 1, 2011

ክ.፩ «እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤» ማቴ፥ ፲፥፲፮፤ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ ከአሥራ ሁለቱም ነገድ የመረጣቸውን አሥራ ሁለቱን ደቀመዛሙርት ጠርቶ፦ ያወጧቸው ዘንድ፥ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ፥ በርኲሳን መናፍስት ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው። ይኽንን ሲያደርግ ይሁዳን ለይቶ አልተወውም። እርሱ፦ ለጻድቃንም ለኃጥአንም ፀሐይን የሚያወጣ፥ ዝናቡንም የሚያዘንብ አምላክ ነውና። ማቴ፥ ፩፥፵፭።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በነቢዩ በኢሳይያስ፦ «ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤» ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ፦ አጋንንትን በቃሉ በማውጣት፥ ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት፥ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት ፈውሶ አሳይቷቸዋል። ማቴ ፲፥፲፮። ሁሉን ትተው በመከተላቸውም ይኽንን የመሰለ ሥል ጣን ሰጥቷቸዋል። በማይታበል ቃሉም፦ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን (ወልድ ዋሕድ ብሎ ያመነ) እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤ ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል፤» ብሏል። ዮሐ ፲፬፥፲፪። ይኸውም ፍጡር ከፈጣሪ በላይ የሚሠራ ኹኖ አይደለም፤ እርሱ ለአብነት፦ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር አስተምሯል፤ ተከታዮቹ ደግሞ ሃያም፥ ሠላ ሳም፥ አርባም ዓመት የሚያስተምሩ ስለሆነ ነው። እርሱ ለአብነት ጥቂት በሽተኞችን ፈውሷል፥ ሙታንንም አንሥቷል፤ እነርሱ ደግሞ በሰጣቸው ሥልጣን በስሙ ቡዙ በሽተኞችን የሚፈውሱ፥ ሙታንንም የሚያስነሡ ናቸውና እንዲህ አለ።

ሲልካቸውም፦ «በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያን ከተማም አትግቡ። ነገር ግን ከእስራኤል ወገን ወደ ጠፉ በጎች ሂዱ፤» ብሏቸዋል።

፩፥፩፦ አሕዛብ፤

አሕዛብ ማለት ሕዝቦች ማለት ነው። በኦሪቱ የኖኅን ልጆች ትውልድ ከዘረዘረ በኋላ፦ «ከእነዚህም የአሕዛብ ደሴቶች ሁሉ በየምድራቸው፥ በየቋንቋቸው፥ በየነገዳቸው፥ በየሕዝባቸው ተከፋፈሉ።» ተብሎ ተጽፏል። ዘፍ ፲፥፩። በመጽ ሐፍ ቅዱስ፦ «አሕዛብ» የሚለው ቃል በተለይ ከእስራኤል ወገን ላልሆኑ ሕዝቦች ተነግሯል። ነቢዩ ኢሳይያስ፦ የእስራ ኤልን ከስደት መመለስ በተናገረበት አንቀጽ፦ «በዚያ ቀን የእሴይ ሥር ይቆማል፤ የተሾመውም የአሕዛብ አለቃ ይሆናል፤ አሕዛብም በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ማረፊያውም የከበረ ይሆናል፤» ብሏል። ትርጉሙም፦ ፩ኛ፦ ከነገደ እሴይ የተወለደ ሕዝቅያስ አንድም ዘሩባቤል ይነግ ሣል፥ አንድም ነገደ እሴይ ዘመናይ ይሆናል፤ የአሕዛብም አለቃ ይሆናል፤ (አሕዛብ ይገ ዙለታል)፤ ማለት ነው። ፪ኛ ነገ ፲፰፥፱፤ ዕዝ ፫፥፪፤ሐጌ ፩፥፩፤ ዘካ ፬፥፮። ፪ኛ፦ ከነገደ እሴይ ከተወለደች ከእመቤታችን የተወለደ ጌታ ያን ጊዜ ይነግሣል፤ የአሕዛብም መምህር ይሆናል፤(ወንጌልን ያስተምራል) ሉቃ ፪፥፮፤ ማቴ ፬፥፲፯። አሕዛብ በእርሱ ያምናሉ፥ ከእርሱ የተገኘ ክብር የሕዝቡ የአሕ ዛቡ ማረፊያ  መሳፈሪያ ይሆናል፥ ማለት ነው። ማቴ ፲፩፥፳፰። ፫ኛ፦ ከነገደ እሴይ የተወለዱ ምእመናን ጽንአ ነፍስን አግኝተው በሃይማኖት በምግባር ይጸናሉ፥ ማለት ነው። ኢሳ ፲፩፥፲።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ አሕዛብ ከእስራኤል ወገን እንዳልሆኑ ሲናገር፦ «ወደ ክብሩ የጠራንና የሰበሰበንም እኛ ነን፤ ነገር ግን ከአሕዛብም ነው  እንጂ ከአይሁድ ብቻ አይደለም፤» ካለ በኋላ፦ ነቢዩ ሆሴዕ የተናገረውን ትንቢት፥ አን ድም፥ እግዚአ ብሔር በነቢዩ አድሮ የተናገረውን ቃል፦ «ወገኔ ያልነበረውን ወገኔ አድርገዋለሁ፤ ወዳጄ ያልነበረችውንም ወዳጄ አደርጋታለሁ። የእግዚአብሔር ወገኖች አይደላችሁም ይባሉ በነበሩበት ሀገርም የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ፤»ብሏል። ሮሜ ፱፥፳፬፣ ሆሴ ፪፥፳፫።

አሕዛብ የኖሩት ጣዖት ሲያመልኩ ለጣዖት ሲሠዉ ነው። ይኸንን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ «ምድራቸውም በእጆቻቸው በሠሩአቸው ጣዖታት ተሞልታለች፤ በጣቶቻቸውም ለሠሩአቸው ይሰግዳሉ፤»ብሏል። ኢሳ ፪፥፰። እስራኤል ዘሥጋም ጣዖትን በማምለክ እግዚአብሔርን ያስቆጡበት ጊዜ ነበረ። መሳ ፪፥፲፩ ፪ነገ ፲፯፥ ፯፤፳፩፥ ፲፩። ጣዖትን ማምለክ አእምሮን ያሳውራል፤ ኢሳ ፵፬፥፰። ከአጋንንት  ጋር አንድ ያደርጋል፤ ፩ኛ ቆሮ ፲፥፳። ከዚህም ጋር የሥጋ ሥራ ተብለው የ ተዘረዘሩት፦ ዝ ሙት፥ ርኲሰት፥ መዳራት፥ ጣዖት ማምለክ፥ ሥራይ ማድረግ፥ (ከሚበላና ከሚጠጣ ጋር አደገኛ መርዝ በመስጠት ሰውን እን ዲታመም፣ እንዲያብድ፣ እንዲሞት ማድረግ)፥ መጣላት፥ ኲራት፥ የምንዝር ጌጥ፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ጥር ጥር፥ ፉክክር፥ ምቀኝነት፥ መጋደል፥ ስካር፥ ይህን የመሰሉ ሁሉ ግብረ አሕዛብ በመባል ይታወቃሉ። ገላ ፭፥፲፱፣፩ኛ ቆሮ ፮፥፱።

ክርስትና፦ እስራኤልን እና አሕዛብን፦ በወንጌል፥ በጥምቀት አንድ አድርጋቸዋለች። ይኽንን አስመልክቶ፥ ሐዋ ርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በውኑ እግዚአብሔር ለአይሁድ ለብቻቸው ነውን? ለአሕዛብስ አይደለምን? አዎን ለአሕዛብም ነው፤» ብሏል። ሮሜ፫፥፳፱። መምሕረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እናንተ አሕዛብ አስቡ፤ ቀድሞ በሥጋ ሥርዐት ነበራ ችሁ፤ ያልተገዘሩም ይሏችሁ ነበር፤ እንዲህ የሚሏችሁም የተገዘሩ ሰዎች ናቸው፤ ግዝረት ግን በሥጋ ላይ የሚደረግ የሰው እጅ ሥራ ነው። ያን ጊዜ ክርስቶስን አታውቁትም ነበር፤ ከእስራኤል ሕግ የተለያችሁ ነበራችሁ፤ ተስፋም አልነበራችሁም፤ በዚህም ዓለም እግዚአብሔርን አታውቁትም ነበር። አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክ ርስቶስ ደም ቀረባችሁ። ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና፤» እያለ አሕዛብን አስተምሯል። ኤፌ፪፥፲፩። ይህ እንዲህ ከሆነ፦ «ለምን? በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ አለ፤» እንል ይሆናል፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክር ስቶስ፦ የአሕዛብ መንገድ ያለው የአሕዛብን ሥራ ነው። በመሆኑም፦ የአሕዛብን ሥራ አትሥሩ ሲላቸው ነው። ለምሳሌ፦ «እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፤» ማለት ሥራቸ ውን ያውቃል ማለት ነው። መዝ ፩፥፮።

፩፥፪፦ ሳምራውያን፤

          ሳምራውያን በሰማርያ የኖሩ ሕዝብ ናቸው። ሰማርያ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ስድሣ አምስት ኪ,ሜ, ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። የአሶር ነገሥታት ስልምናርና ሳርጎን ሰማርያን ከያዙ በኋላ ዋና ዋና ሰዎችን ማርከው ወሰዱ። በእነርሱም ፈንታ ሰዎችን ከልዩ ለዩ አገር አምጥተው በሰማርያ አሰፈሩአቸው። እነርሱም ከቀሩት አይሁድ ጋር እየተጋቡ ተደባ ለቁ። በሂደትም ሃይማኖታቸውን ሥርዓታቸውን በረዙባቸው፥ ባሕላቸውንና ወጋቸውን አጠፉባቸው፡፡ ሕዝቡም ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው እግዚአብሔርንም የማይፈሩ ሆኑ። በዚህም ምክንያት፦ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መዓት የአንበሳ መንጋ ተሰድዶባቸው ነበር። በኋላም አንበሶች እንዳይገድሏቸው እግዚአብሔርን ማምለክ ፈለጉና የሙሴን ሕግ እንዲያውቁ ካህን ተላከላቸው ፪ነገ ፲፯፥፳፬።

          አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ ሳምራውያን ከእነርሱ ጋር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ቀርበው ነበር፤ ዘሩባቤል ግን ጥንታውያን የእስራኤል ዘሮች ባለመሆናቸው አልተቀበላቸውም፤ ዕዝ ፬፥፩። ነህምያም፦ ለሃይማኖትና ለሥርዓት ግድ የለሾች  በመሆናቸው ከኢየሩሳሌም አስወጥቷቸዋል። ነህ ፲፫፥፬። በዚህ ምክንያት በገሪዛን ተራራ መቅደስ ሠርተው ይሰግ ዱ ነበር፤ ዮሐ ፩፥፳። አይሁድ ከሳምራውያን ጋር በማኅበራዊ ኑሮም አይገናኙም ነበር፤ ዮሐ ፬፥፱። እንዲያውም ሳምራዊ መባል እንደ ንቀት ነበር፤ ሉቃ፲፥፴፫፣፴፯፣፲፯፥፲፮፣ክብር ምስጋና ይግባውና፥ አይሁድ ጌታችንን፦ «አንተ ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ መናገራችን በሚገባ አይደለምን?» ያሉት ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፥፵፰።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «ወደ ሳምራውያን ከተማ አትግቡ፤»  ያለው፥ ሳምራውያን ኦሪትን እንጂ ትንቢተ ነቢያትን ስለማይቀበሉ ነው። ከትንሣኤው በኋላ ግን፥ ከማረጉ በፊት፦ «ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፥ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤» ብሏቸዋል። የሐዋ ፩፥፰።

፩፥፫፦ ቤተ እስራኤል፤

          እስራኤል፦ ከአሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች የተገኙ ናቸው። ዘፍ ፵፱፥፯፤ ዘጸ ፲፬፥፴። እስራኤል ለያዕቆብ ሁለ ተኛ ስሙ ነው፤ ከእግዚአብሔር ጋር ሌሊቱን በሙሉ ሲታገል አድሮ «ካልባረክኸኝ አልለቅህም፤» በማለቱ፦ «እስራኤል» ብሎ ሰይሞታል። ዘፍ ፴፪፥፳፪። በዚህም ምክንያት ከእርሱ ወገን የተወለዱ ሁሉ «የእስራኤል ልጆች» ተብለው ይጠራሉ።

          እስራኤል ዘሥጋ የኖሩት በቃል ኪዳን አገር በከነዓን ነው። ከነዓን የአብርሃም ርስት ናት። ዘፍ ፲፪፥፩። የያዕቆብ ልጆች በሙሉ ከዚች አገር ተሰደው በግብፅ በባርነት ይኖሩ ነበር። ዘመኑም ከአንድ ሺህ ሰባት መቶ እስከ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ነው። በመጨረሻም ከጌታ ልደት በፊት አንድ ሺህ ሦስት መቶ ዓመት ገደማ በሙሴ መሪነት ከግብፅ ወጥተዋል፡፡ በኢያሱ መሪነት ደግሞ ምድረ ርስትን ወርሰዋል፡፡ ዘፀ ፲፰፥፫፣ ኢያ ፳፬፥፳፭። በዘጠኝ መቶ ሃያ ሁለት ዓመት ከጌታ ልደት በፊት አሥራ ሁለቱ ነገድ በአገዛዝ ተጣልተው በሮብዓም ዘመነ መንግሥት ለሁለት ተከፍለዋል። ፩ኛ ነገ ፲፩፥፵፫። አሥሩ ነገድ በሰሜን ፍልስጥኤም በሰማርያ ሲቀመጡ ከተማቸው ሴኬም ነበረች። ሁለቱ ነገድ ደግሞ በደቡብ ፍልስጥኤም ሲኖሩ ከተማቸው ኢየሩሳሌም ነበረች። በሰባት መቶ ዘጠና ሁለት ዓመት ከጌታ ልደት በፊት የሰሜኑን ክፍል አሦራውያን በስልምናሶር መሪነት መጥተው አጠፏት ፪ኛነገ ፲፯፥፫ ሕዝቡም ተማረኩ፤ ይህ ሲሆን፥ በደቡብ ክፍል የነበሩት ሁለቱ የተማረኩትን አሥሩን ነገድ እንደጠላት ይቈጥሯቸው ስለነበር ሳይደሰቱ አልቀሩም፤ ነገር ግን ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ለእነርሱም ጽዋው ደረሳቸው፡፡ በአምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመት ባቢሎናውያን በናቡከደነጾር መሪነት መጥተው ኢየሩሳሌምን አጠፉ። ፪ኛ ነገ ፳፬፥፩፣ ኤር ፵፮፥፪። ሕዝቡንም ማርከው ወሰዱ፤ ሰባ ዓመት በምርኮ ቆይተው ከተመለሱ በኋላም ጥቂት እንደቆዩ በፋርሶች ተወረሩ። አሁንም እንደገና በሦስት መቶ ሠላሳ ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ግሪኮች በዚች ምድር ላይ ቅኝ ገዥዎች ሆኑ፡፡ በመጨረሻም ከስድሣ ሦስት ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ሮማውያን ተረከቧት። በዚህ ረጅም የተፋልሶ ጊዜ ሕዝቡ ብዙ የባህልና የሃይማኖት ቀውስ ደርሶ በታል፥ እሥራኤላዊ ያልሆኑ ጠባዮችንም ሳያውቀው ሸምቷል። ክርስትና በፍልስጥኤም ሲመሠረት የነበረውን ሁኔታ ለማወቅ የሚቻለው ይህ ሲታይ ነው።

          በሮም ቅኝ ግዛት ስር የነበረች ይህች አገር ሕዝቦቿ የተከፋፈለ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድን ነበራቸው። ከነዚህም ዋናዎቹ የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ቡድኖች ነበሩ። ከእነዚህም ሌላ ኤሴዎች ነበሩ፡፡

፩፣፫፥፩፦ ፈሪሳውያን

          ፈሪሳዊ፦ «ፓራሽ» ከሚለው ከዕብራይስጥ ቃል የወጣ ነው። ትርጉሙም የተለየ ማለት ነው። እነዚህም ምንም የቅኝ አገዛዝ ቀንበር መላልሶ ቢያደቃቸውም፥ ባህልና ልምዳችን አይነካ፥ በሃይማኖትም የሙሴን ሕግና የነቢያትን መጻሕ ፍት የምንጠብቅ እኛ ብቻ ነን ባዮች ነበሩ። ስለዚህ ከአይሁድ ዘር ውጭ ከሆነ ከማንኛውም ጎሳና ዘር ጋር በባህልና በሥልጣኔ መቀራረቡን እንደ መርከስና ሕግ እንደመተላለፍ ይቆጥሩት ነበር። የመሲሕንም መምጣት ነቅተውና ተግተው ይጠብቁ ነበር። ለዚህም ዋናው ምክንያታቸው ሀገራቸው ፍልስጥኤምን ከሮም ግዛት ነጻ ለማውጣት የቆየ ጉጉት ስላ ላቸው ነው። እንደነርሱ አስተሳሰብ መሲሕ ሲመጣ የጦር ኃይል አቋቁሞ፥ ራሱ የጦር መሪ ሆኖ፥ የሮማን የቅኝ ግዛት ቀንበር አውልቆ ጥሎ የዳዊትን ቤተመንግሥት የሚያድስ መሲሕ ይጠባበቁ ነበር። ምንም አንኳ ከትንሣኤ በኋላ ሥጋዊ ኑሮ አለ ብለው ቢያምኑም ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ያውቁ ነበር፡፡ በዕለታዊ ኑሯቸውም ብዙ ሀብት የሌላቸውና በዕው ቀትም መጠነኞች ነበሩ።

፩፥፫፥፪፦ ሰዱቃውያን

          የሰዱቃውያን ቡድን የሀብታሞችና የካህናት ቡድን ነው። ይህ ቡድን ለባህል፥ ለሥነሥርዓትና ለሃይማኖት ግድ የሌለው፥ ከቅኝ ግዥዎች ጋር ተስማምቶ በነርሱ ሥልጣኔ መጠቀምን ብቻ የሚፈልግ ቡድን ነበር። ከሃይማኖት መጻሕ ፍትም የሙሴን ሕግ ብቻ እንጂ የነቢያትን ትንቢትና ሌሎችንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አይቀበሉም ነበር። የሙታንን ትንሣኤና የመሢሕንም መምጣት አያምኑም ነበር።

፩፥፫፥፫፦ ኤሤዎች

          እነዚህ፦ «መሲሕ መጥቶ፥ የጦር ኃይል አቋቁሞ፥ በጦር ኃይል ፍልስጥኤምን ነጻ ያወጣል፤» የሚለውን የፈሪሳውያን እምነትና ተስፋ በመቃወም ከፈሪሳውያን ተከፍለው በሙት ባሕር አካባቢ ገዳም መሥርተው ይኖሩ ነበር። የእነርሱም ዓላማቸው እንደ ፈሪሳውያን መሲሕን መጠባበቅ ነው። ኤሤይ በመባል የታወቁት እነዚህ ክፍሎች ከፈሪሳዊያን የሚለዩት፥ ፈሪሳውያን በጦር ኃይል ነፃ እንወጣለን ሲሉ፥ ኤሤይ የሚባሉት ደግሞ በተአምራት፥ በእግዚአብሔር ኃይል ፍስስጥኤም ነፃ ትወጣለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ በቤተልሔም በስተደቡብ ልዩ ስሙ ኩምራን በሚባል ቦታ የሚኖሩ እነዚህ ሰዎች መጻሕፍትን በመጻፍ፥ ጸሎትን በማድረስ፥ ብዙ ጊዜ ቆይተዋል። ኤሤዎችና ፈፊሳውያን በአንዳንድ አስተ ሳሰብ ቢለያዩም መሲሕ መምጣቱን እና የተወሰነ ምርጥ ጐሳዎችን ነፃ እንደሚያወጣ፥ ዓለም አቀፋዊ መሲሐዊ መንግሥት እንደሚያቋቁምና እነርሱም የመንግሥቱ ባለሟሎች እንደሚሆኑ፥ ሁለቱም ቡድኖች ያምኑ ነበር። (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ ገጽ ፲፰)፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙር ቱን፦ «ከእስራኤል ወገን ወደጠፉት በጎች ሂዱ፤» ያላቸው፥ እነ ርሱ የተነገረውን ትንቢት፥ የተቈጠረውን ሱባዔ ስለሚያ ውቁ ነበር።     

፩፥፬፦ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች፤»

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ደቀመዛሙርቱን፦ «ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደጠፉት በጎች ሂዱ፤» ያላቸው፦ መምህር፥ አብነት፥ ትምህርት፥ አጥተው በመጐዳታቸው ነው። አንድም፦ ጌታችን ወደ ዚህ ዓለም እንደ ሚመጣ የተነገረውን ትንቢት፥ የተቆጠረውን ሱባዔ ስለሚያውቁ ነው። የሚሰብኩትንም ሲነግራቸው «መ ንግሥተ ሰማያት ቀርባ ለች፤» ብላችሁ ስበኩ ብሏቸዋል። ይኸውም፦ በሃይማኖት የምትሰጥ ልጅነት፥ በልጅነትም የምት ሰጥ (የምትወረስ) መንግሥት ቀርባለች ብላችሁ አስተምሩ ሲላቸው ነው። ይህች ለእግዚአብሔር መንግሥት የምታበቃ ልጅነት የምትገኘው በጥምቀት ነው፡፡ ምክንያቱም፦ ለመምህረ ኦሪት ለኒቆዲሞስ እንዳስተማረው፥ ሰው በጥምቀት ዳግመኛ ከእግዚአብሔር ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልምና ነው። ዮሐ ፫፥፭። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌ ላዊ፦ «ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአ ብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም» ያለው ይኽንን ነው። ዮሐ ፩፥፲፪።

          ልጅ፦ የአባቱን ሀብት፥ ርስት ወራሽ ነው፤ እግዚአብሔር አብርሃምን፦ «ነገር ግን ከአብራክህ የሚወጣው እርሱ ይወርስሃል» ያለው ለዚህ ነው። ዘፍ ፲፭፥፬። ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማየ ዮርዳኖስ የተወለዱ ምእመናንም የአባታቸውን ር    ስ ት ይወርሳሉ። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሠሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ዳግመኛም አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሀት የባርነት መንፈስን አልተቀበላችሁምና። እኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆን ለልቡናችን ምስክሩ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን ወራሾቹ ነን፤ የእግዚአብሔር ወራሾች ከሆንም የክርስቶስ ወራሾቹ ነን፤ በመከራ የመሰልነውም በክብር እንመስለዋለን፤» ብሏል። ሮሜ ፰፥፲፬። በገላትያ መልእክቱም፦ «በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነና ልና። በክርስቶስ የተጠመቃችሁ እናንተማ ክርስቶስን ለብሳችኋል። (መስላ ችኋል)። በዚህም አይሁዳዊ፥ ወይም አረማዊ የለም፤ ገዢ ወይም ተገዢ የለም፤ ወንድ ወይም ሴት የለም፤ ሁላችሁ በኢየ ሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁና። ለኢየሱስ ክርስቶስ ከሆናችሁም እንግዲህ ተስፋውን የምትወርሱ የአብርሃም ዘር እናንተ ናችሁ፤» ብሏል። ገላ ፫፥፳፮።

          ምእመናን የሚወርሷት ሀገር መንግሥተ ሰማያት ናት። ይህችውም፦ «እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ።» ተብሎ በጌታ አንደበት የተነገረላት ናት። ማቴ ፳፭፥፴፬ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎ ስ፥ «ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን?» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፮፥፱። ዳግመኛም፥ «ሥጋዊና ደማዊ (በሥጋዊ በደማዊ ግብር በኃጢኣት ጸንቶ የኖረ) የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፤» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፭። ምክንያቱም የተዘጋጀችው፥ ሃይማኖት ለሚይዙ፥ ምግባር ለሚሠሩ ነውና፤ እግዚአብሔር እንዳዘጋጃትም ሲና ገር፦ «ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።» ብሏል።


፩፥፭፦ ተአምራት፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የደቀመዛሙርቱን፦ ትምህርታቸውን በተአምራት የሚያጸናላቸው ስለሆነ፥ በስሙ ተአምራት እንዲያደርጉ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም፦ «ድውዮችን ፈውሱ፥ ሙታንን አስነሡ፥ ለምጻሞችን አንጹ፥ አጋንንትን አውጡ፤» ብሏቸዋል። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ፦ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደውን በጌታችን ስም ፈውሰውታል። የሐዋ ፫፥፩-፰። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ፦ «በሐዋርያት እጅም በሕዝቡ ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፤» ያለው ለዚህ ነው። የሐዋ ፭፥፲፪። በተጨማሪም፦ «እስጢፋኖስም የእግዚአብሔር ጸጋና ኃይል የመላበት ሰው ነበር፤ በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ ነበር።» ብሏል። የሐዋ ፮፥፰። የሰማርያ ሰዎች የፊልጶስ ን ስብከት በአንድ ልብ ሆነው አምነው የተቀበሉት በእጁ ይደረጉ የነበሩትን ተአምራት አይተው ነው። የሐዋ ፰፥፭። ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስ፦ በእጃቸው ድንቅ ሥራና ተአምራት እያደረጉ በኢቆንዮን ብዙ ወራት ኖረዋል። የሐዋ ፲፬፥፫። ቅዱስ ጳውሎስ በልስጥራን ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የነበረ ውን፥ ከቶም ሄዶ የማያውቀውን ሰው ፈውሶታል። የሐዋ ፲፬፥፰። ቅዱስ ጴጥሮስ፦ ስምንት ዓመት ሙሉ ከአልጋው ተጣብቆ የኖረውን በሽተኛ ኤንያን ፈውሶታል። የሐዋ ፱፥፴፪። ጣቢታንም ከሞተች በኋላ አስነሥቷታል። የሐዋ፱፥፵። ቅዱሳን ሐዋርያት፦ አጋንንትንም በቃላቸው እያዘዙ ያስወጧቸው ነበር። የሐዋ ፲፮፥፲፰።

፪፦ «ያለዋጋ የተቀበላችሁትን ያለዋጋ ስጡ፤»

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱን፦ «በከንቱ ዘነሣእክሙ ሀቡ በከንቱ፤ ያለዋጋ የተቀበላችሁትን ያለዋጋ ስጡ፤» ብሏቸዋል። ይህም፦ «በለጋስነት የተማራችሁትን በለጋስነት አስተምሩ፥ ዋጋ ሳትሰ ጡ የተማራች ሁትን ዋጋ ሳትቀበሉ አስተምሩ፥ በተአምራት የተማራችሁትን በተአምራት አስተምሩ፥ ሳትጥሩ የተማራችሁትን ሳይጥሩ አስተምሩ፤» ሲላቸው ነው።

          የተነበበውን ተርጉሞ፥ የተተረጐመውን አመስጥሮ፥ ለሰው ኅሊና እንዲመች አድርጐ ማስተማር፤ ታላላቅና ድንቅ ድንቅ ተአምራት ማድረግ እንዲሁ ያለዋጋ የተገኘ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ሃይማኖትን ማስተማር እና በሃይማኖት ተአም ራት ማድረግ ብቻ ሳይሆን፥ ሃይማኖት (ማመን፥ መታመን) በራሱ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ። «እጅግ ተግቼ እጽፍላች ኋለሁ፥ ለቅዱሳን የተሰጠችውንም ሃይማኖት ትጋደሉላት ዘንድ እማልዳችኋለሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ይሁ ፩፥፫። ወንድሙ ቅዱ ስ ያዕቆብ ደግሞ፦ «ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር፥ ሳይነቅፍና ሳይነፍግ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል፤» በማለት ሁሉ ነገር የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ተናግሯል። ያዕ ፩፥፭።

          የእግዚአብሔር ጸጋ የሚገዛም የሚሸጥም አይደለም፤ የሶርያ ሠራዊት አለቃ የነበረው ለምጻሙ ንዕማን፦ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በነቢዩ በኤልሳዕ ምክር በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ ተፈውሷል። የተጠመቀውም ሰባት ጊዜ ነው። (ወላጆቻችን አንድ ሰባት፥ ሁለት ሰባት ልጠመቅ፥ የሚሉት ለዚህ ነው)። ተመልሶም ነቢዩን፦ «እነሆ በእስራኤል ነው እንጂ በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ ዐወቅሁ፤ አሁንም ከአገልጋይህ በረከት ተቀበል፤» አለው። ነቢዩ ግን፦ «በፊቱ የቆም ሁት ሕያው እግዚአብሔርን አልቀበ ልም፤» ሲል መለሰለት። ይኽንንም ያደረገው፦ ንዕማን አዲስ አማኝ በመሆኑ፦ የሚሰጠው ነገር ከዳነበት የእግዚአብሔር ጸጋ ጋር ተመጣጣኝ ዋጋ መስሎ እንዳይታየው ነው። ወደ ሀገሩም ተመልሶ ለዳን ኩበት ይኽን ያህል ከፍያለሁ እንዳይል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲሁ በልግስና የሚሰጥ በመሆኑ ነው። በእምነት የጸና ሰው ቢሆን ኖሮ ተቀብሎ በስሙ ለነዳያን ይመጸውትለት ነበር። ይህ ሰው ታላቅ ባለሥልጣን ቢሆንም በነቢዩ ፊት የቆመው ራሱን በጣም ዝቅ አድርጎ እንደ አንድ አገልጋይ ነው፡፡ ፪ኛ ነገ ፩፥፩።

          በዘመነ ሐዋርያት ሲሞን የተባለው ጠንቋይ የእግዚአብሔርን ጸጋ ለመግዛት ፈልጐ ነበር። ይህ ሰው ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት ቀርቦ ገንዘብ አመጣላቸውና፦ «እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ሰጡኝ፤» አለ። ቅዱስ ጴጥሮስ ግን፦ «የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም።» ብሎታል። የሐዋ፰፥፲፯። ይህች ዓለም ሥጋውያን በገንዘባቸው የሚያዙባት ዓለም ናት። ይህም ነገር በመንፈሳዊውም ዓለም ጥላውን ሲያጠላ ይታያል። መንፈሳዊውን ሥልጣን በገንዘብ የመሸመት ፍላጐት ይንጸባረቃል። ለመንፈሳዊው ሥልጣን ለመብቃት የማይችሉ ባዕለጸጎች ደግሞ፦ መንፈሳዊ ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ተጠግተው በገንዘባቸው ሲያዙን፥ ከጀርባ ሆነው ሲመሩን እየታየ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «ወንድሞች ሆይ፦ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤያችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም አንተስ ወደዚያ ቁም፤ ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳ ችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ ባለጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን?  ወደ ፍርድ ቤትም የሚጐትቷችሁ እነርሱ አይደሉምን? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን?» ያለ ው ይኽንን ነው። ያዕ ፪፥፩-፯። ይኽንንም ማለታችን በምንበዛው መናገራችን እንጂ ለሰው ፊት የማያደሉ መንፈሳውያን፥ በገንዘባቸው በትህትና የሚያገለግሉ ባዕለጸጎች ፈጽሞ የሉም፥ ለማለት አይደለም።


ይቀጥላል . . .

5 comments:

 1. Kale Hiwot Yasemalin
  Rejim Edme ena Tena Yistilin
  Ersiwon Ayasatan

  ReplyDelete
 2. ቃለ ህይወት ያሰማልን ዕድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን።

  ReplyDelete
 3. Kale Hiwot Yasemalin

  ReplyDelete
 4. አባታችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን። እንደርስዎ ያሉትን እግዚአብሔር ያብዛልን።

  ReplyDelete
 5. kale hiywet yasemie leke!

  ReplyDelete