Monday, April 11, 2011

ትምህርተ ጋብቻ፤ ክፍል፦ ፯

       የውጭ አገር ኑሮ የሁላችንም ህልም ነው፤ የተሻለ እንኖራለን የሚል የፍጹማን ፍጹም እምነት ስላለን በድንበር፥ ወይም በአየር፥ ወይም በባሕር፥ ወይም ክንፍ አውጥተን በተአምር፥ ወይም ረቅቀን በመሰወር፥ ዓላማችን ሁሉ ውጭ አገር ነው። ጫማችን ልብሳችን እንኳን ሙሉ በሙሉ የውጭ አገር ቢሆን እንመርጣለን። ሌላው ቀርቶ ከመርካቶ ወይም ከፒያሳ የገዛነውን ዕቃ፦ «እህቴ፥ ወይም ወንድሜ፥ ወይም ዘመዴ፥ ከውጭ አገር ልኮልኝ ነው፤» ማለት ይቀናናል። ባይኖረንም፦ «ዘመዶቼ ሁሉ ውጭ አገር ናቸው፤» ማለት ያስደስተናል። ለቊሉቢ ገብርኤልም፥ ለካዛንቺስ ዑራኤልም የምንሳለው ስዕለትም ከዚህ የወጣ አይደለም። ከሌላው የተሻለ ደመወዝ፥ ከሌላው የበለጠ ሀብት ቢኖረንም ይህ ውጭ አገር ልባችንን እየሰለበው፥ ዓይናችንን እያማለለው ያስቸግረናል። ዘመድ አዝማድ ያለን ደግሞ ደብረ ዘይት ይመስል፦ «ለምን አትወስዱኝም?» የዘወትር ውትወታችን ነው። በውጭው አገር ያለንም፦ «ለወንድሜ ፈርሜለት፥ ለእኅቴ ፈርሜላት በጋብቻ ስም ባመጣሁት፥  ባመጣኋት፤» በሚል ተስፋ የዘወትር ጥረት ከማድረግ ቦዝነን አናውቅም፤ ወይም፥ «እኔ ለእኅቱ  ፈርሜላት፥ እርሱም ለእኅቴ ፈርሞላት በለውጥ ባመጣኋት፤» የሚለውም እንደ መደበኛ ሥራ እየተተገበረ ነው። ወይም፦ ወደ ኬንያ፥ ወደ ደቡብ አፍሪካ አስወጥቼያቸው ከዚያ ይሞከርላቸዋል እንላለን። ካልሆነም እንደማንኛውም ሰው ዓረብ አገር ሄደው ዕድላቸውን ይሞክሩ ብለን ገንዘብ እንልክላቸዋልን። የአራዳ ልጆችም፦ «ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሆኜ ከምፈጠር፥ ውጭ አገር ድንጋይ ሆኜ በተፈጠርኩ፤» እያሉ በራሳቸው ይቀልዳሉ።
          ይኽንን ሁሉ ያመጣው የፍላጎታችን እጅግ ታላቅ መሆን ነው። አገልግሎት ጋንቤላ ሲባል የማይመቸን፥ ውጭ አገር ከተባለ በከብት ጀርባም ቢሆን ይመቸናል። «ሰው ቅድስት አገሩን ጥሎ እንዴት ይሰደዳል፥ በዲቪስ እንዴት ይጓዛል፤» ብለን እንዳልሰበክን እንዳልገዘትን በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሾልከን እዚያው የማይቀረው አገር የተገኘን ጥቂቶች አይደለንም። እንዲህም ሲባል የዓላማ ሰዎች የሉም ለማለት አይደለም። በአብዛኛው ተምሮ ከቊም ነገር ለመድረስ፥ ወይም ምንም ይሁን ምን የተገኘውን ሠርቶ ራሱን ለመቻልና ለድሆች ቤተሰቡ ለመትረፍ ነው። ይህም ሊበረታታ ሊጠበቅም የሚገባው ጥሩ ባሕላችን ነው፥ መሠረቱም ሃይማኖት ነው። ከዚህም ጋር፥ ማለትም፦ ከሀገር ለመውጣት የኢኰኖሚው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ ከማንም ይሁን ከማን የፖለቲካው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም፤ የፖለቲካው ነገር ተስማምቷቸው የሚያስገሳቸው ቢኖሩም የማይስማማቸው ይበዛሉ። ተስማምተው ያስገሳቸውም ውሎ አድሮ ቃር የሚሆንባቸው ጊዜ አለ። የሚስማማውም ክፍል ቢሆነ፦ በሰበብ በአስባቡ፥ ልቡም ገንዘቡም፥ቤተሰቡም ከአገር ውጭ ናቸው። ባይስማማውም የሚስማማው ክፍልም አካሉ አገር ቤት ይሁን እንጂ ልቡ ውጭ አገር ነው። ይህ ነገር ፀሐይ የሞቀው አገር ያወቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው። ይሁን እንጂ የትዳር ነገር ሲታሰብ የሁሉም ልብ ያለው አገር ቤት ነው።
          እገሌ ወእገሌ ሳይባል፥ ይህ ጥላ ያጠላብን፥ ይህ መንፈስ የሰረፀብን ሰዎች ነን። እንግዲህ አስቡት፥ በዚህ መንፈስ ውስጥ ያለን ሰዎች ከውጭ አገር የትዳር ጓደኛ ሲገኝልን፥ ከሲኦል ወደ ገነት ያመለጠችን ነፍስ ያህል ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል። ህልማችን በመፈታቱ፥ ዕድላችን በመቃናቱ ፈጣሪን እናመሰግናለን። እንዲህም የሆነው ወድደን እንዳልሆነ የታወቀ ጉዳይ ነው። በባሕር እንሻገራለን ብለው ከነጀልባቸው የሰመጡ፥ በየበረሀው በውኃ ጥም የረገፉ፥ አውሬ የበላቸው፥ በየዓረቡ አገር የሚንገላቱት ሁሉ ወድደው የገቡበት ነው ማለት ፍርደ ገምድል መሆን ነው። ችግርንና ሞትን እንዲጋፈጡ የሚያደርጋቸው በውስጣቸው የሰነቁት የነገ ተስፋ ነው። በዚህም ላይ ተሳክቶላቸው፥ ውጭ አገር ደርሰው፥ መኖሪያ ፈቃድ ኖራቸው አልኖራቸው፥ ተመቻቸው አልተመቻቸው፥ ሞላላቸው አልሞላላቸው፥ ገንዘብ እየላኩ የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ የለወጡ ሰዎች የሚያሳድሩትም ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው። ቤተሰብም ቢሆን፦ «የሰው ልጅ ባገኘው መንገድ እየወጣ የቤተሰቡን ኑሮ ይለውጣል፥ እናንተ ግን እኛ ትከሻ ላይ ተቀምጣችሁ፥ የወጣት ተጧሪ ሆናችሁ፤» እያለ ግፊት ያደርጋል።
          እንግዲህ ወንድም ይሁን፥ ሴትም ትሁን፥ በዚህ ኅሊና ውስጥ እያለን የትዳር ጓደኛ በሚመጣልን ጊዜ፦ ልክ እንደ ሀገር ቤቱ መልክ አይታይም፥ ዕድሜ አይጠየቅም፥ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ነገር አይታሰብም። ዋናው ቁም ነገር ውጭ አገር መሆኑ ነው። ከውጭ አገር የሄድነውን ደጅ የሚጠኑ፥ ሴቶችም ቢሆኑ ይሉኝታውን ተቋቁመው አፍ አውጥተው የሚጠይቁ፥ አልፎ አልፎ ያጋጥማሉ፤ ቤተሰብም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን ዕድል ለልጆቹ መመኘቱ አልቀረም። እንዲያውም ከውጭ አገር እጮኛ ከመጣ የአገር ቤት እጮኞቻቸውን እንዲተዉ የሚያስገድዱ ይበዛሉ። ቤተሰብ ሳያስገድዳቸውም፦ «በጨረታው አንገደድም፤» ብለው ግራ ኋላ የሚዞሩም ሞልተዋል። ከውጭ አገር ለመጣነው በአብዛኛው ምርጫው የሚካሄደው በቤተሰብና በባልንጀራ ነው። «ትዳር ይፈልጋል፥ ቅረቢው፤ ትዳር ትፈልጋለች፥ ቅረባት፤» ይባላል። የአገር ቤቶቹ ይጠናሉ፥ ይመረመራሉ፤ የውጪዎቹ ግን አንጠናም፥ አንመረመርም፤ የውጪዎቹ ውሻ በጨው የማይልሰንም ብንሆን ሌሎቹን «መልክ የላቸውም፤» ማለት እንችላለን። የእኛ ዕድሜ የአባት አልፎም የአያት ቢሆንም፦ የአገር ቤቶቹን ግን የዕድሜያቸውን ነገር መተቸት እንችላለን። በሴቶቹም በኲል ቢሆን በስመ ውጪ በዕድሜ በጣም ከሚያንሷቸው ጋር የሚቃናጁ አሉ። ትዳር ደግሞ መቀናጀት ሳይሆን መዋሐድ ነው።
          መቼም የውጪዎቹ ሰዎች ከውጭ እንደገባው ዕቃ ቆዳችንን ማዋደዳችን፥ እንደ መላእክት ለመታየት መቃጣታችን አልቀረም። ችግሩ ትዳሩ ከተጀመረ በኋላ የውጪውን ቀርቶ የአገር ቤቱን ምርት መሆን ሲያቅተን ነው፤ ከመላእክትም እንደ አንዱ ሳይሆን ከሰዎች እንደ አንዱ መሆን ሲሳነን ነው። የአገር ቤቶቹም ብንሆን የተመኘነው እሲሳካልን ፍጹም ትሑታን፥ ፍጹም ትዕግሥተኞች ለመምሰል ታግለን የሚሳካልን ሰዎች ነን። «ብቻ ልውጣ እንጂ፤» ብለን «ሙያ በልብ ነው፤» እንዲል፥ የሆዳችንን በሆዳችን የመያዝ ችሎታ አለን። ከወጣን በኋላ ግን ውስጣዊ ማንነታችን አፍጥጦ ይወጣል።
          በውጭው ዓለም አሁን እየታየ ያለው ነገር በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። በወንዶቹ በኲል፦ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለው ያመጧቸው የትዳር ጓደኞቻቸው እየተለወጡባቸው፥ እየከዷቸው ተቸግረዋል። ወንዶቹም ቢሆኑ ከአገር ቤት ስላመጧቸው ብቻ በገንዘባቸው እንደገዟቸው ሸቀጥ ለመቊጠር የሚዳዳቸው አሉ። የዛሬ አሥራ አንድ ዓመት ለአገልግሎት ወደ አውሮፓ በሄድኩበት ጊዜ፦ ለጋብቻ ወደ አገር ቤት የሚሄዱ ሰዎች «የትዳር ጓደኛ ለመግዛት ሄደዋል፤» እየተባለ እንደሚቀለድባቸው ሰምቻለሁ። «ለምን ሄዳችሁ አታገቡም?» ሲባሉም፦ «አንዳቸው ገዝተው ያመጡትን እረከባለሁ፤» የሚሉም እንዳሉ ተነግሮኛል። ቀድሞም ቢሆን ትዳሩ የሚመሠረተው በሥጋት ላይ ነው። «ካመጣኋት በኋላ ብትከዳኝስ? ካመጣሁት በኋላ ቢከዳኝሰ?» የሚል ሥጋት አልነበረም ማለት አይቻልም። በሴቶቹም በኲል ቢሆን ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለው ያመጧቸው የትዳር ጓደኞቻቸው፥ የመኖሪያ ፈቃዳቸው እስኪያልቅላቸው ድረስ ጠባይ አሳምረው፥ እየተንሸራተ ቱበቸው፥ የተልባ ስፍር እየሆኑባቸው፥ ከባሕር እንደወጣ ዓሣ እየተሙለጨለጩባቸው ተቸግረዋል። እነርሱም ቢሆኑ ወንዶቹን፦ «ይሄ እንደ ኢትዮጵያ መሰለህ እንዴ? ፖሊስ ነው የምጠራብህ፤» እያሉ አሳቅቀው እንደ ባሪያ የመግዛት ፍላጐት አለ። ከዚህም ሌላ በማያውቁት አገር «ውጣልኝ፤» ብለው የሚያባርሩም አሉ። በመጣ በሳምንቱ የተባረረ ልጅ አውቃለሁ። ከዚህ የባሰው ደግሞ፦ በትዳር ካስመጣችው በኋላ ተሳክቶለት አሜሪካ ሲደርስ፦ «አልቀበለውም፥ ዓይኑን እንዳላይ፤» የተባለም አጋጥሞኛል።
          በሌላ በኲል ደግሞ፦ ከሁለት አንዳቸው አገር ቤት ከሆኑ፥ አገር ቤት ያለው አካል፦ ቦታ ገዝተን ቤት ብንሠራ፥ እ ንዲህ ዓይነት ቢዝነስ ብንጀምር እያሉ ያጓጓቸዋል። በውጭው ያሉትም፦ ቀንም ሌሊትም ሁለት ሥራ እየሠሩ በፍጹም እም ነት ይልኩላቸዋል። እነዚያም፦ «ከዚህ ደርሷል፤» እያሉ፥ የአንዱን ሰው ሕንፃ ፎቶግራፍ እያነሱ ይልኩላቸዋል። «በርታ፥ በርቺ፥ ትንሽ ነው የቀረው፤» እያሉም ያጣድፏቸዋል። ሌላው ቀርቶ ከገዛ ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደብቀው ይገፉበታል። ለዚህም ምክ ንያት አይጠፋም፥ እናስደንቃቸዋልን፥ (surprise) እናደርጋቸዋለን ይባላል። እንደ ላሜ ቦራ ሲታለቡ ከከረሙ በኋላ አገር ቤት ሲደርሱ፥ በምድርም በሰማይም የተሠራ ቤት፥ የተጀመረም ቢዝነስ ያጣሉ። በዚህ ዓይነት የአማርኛውን ጉድ የሆኑ ብዙ ዎች ናቸው።
          ይህ ሁሉ የሚያሳያን የእምነትን መድከም፥ የሥነ ምግባርን መውደቅ ነው። የሽንገላ ሕይወት የሰፋው የተስፋፋው ለዚህ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማነው?» ካለ በኋላ፥ «አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላና እንዳይናገሩ። ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምንም ሻት፥ ተከተላትም።» በማለት የመከረው የሰው ልጅ ከገባበት አዝቅት እንዲወጣ ነው። መዝ ፴፫፥፲፪-፲፬። ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ደግሞ፦ «አንተ በደልን የሚወደድ አምላክ አይደለህምና፤ ክፉዎች ከአንተ ጋር አያድሩም። ዐመፀኞችም በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ አመፅ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ። ሐሰትን የሚናገሩትን ሁሉ ትጠላቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል። . . . አቤቱ በጽድቅህ ምራኝ፤ ስለ ጠላቶቼ መንገዴን በፊትህ አቅና። በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸው ከንቱ ነው፥ ጉሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ (ሞት ቢገድል፥ መቃብር ቢቀበል፥ በቃኝ፥ ጠገብሁ እንደማይሉ፥ እነርሱም ክፉ ሲናገሩ በቃን ጠገብን አይሉም፤ አንድም እንደተለሰነ መቃብር ናቸው፥ የተለሰነ መቃብር ከላይ ሥዕለ ቅዱሳን ይሥሉበታል፥ ያማረ ሐረግ ያደርጉበታል፥ አበባ ያስቀምጡበታል፤ ከፍተው ያዩት እንደሆነ፥ መግነዙ ተበጣ ጥሶ፥ እዡ ፈስሶ፥ ሥጋው ተልከስክሶ፥ አጥንቱ ተከስክሶ፥ ለዓይን ያስጸይፋል፤ ለአፍንጫ ይከረፋል። እነርሱም፦ ሰውንም እግዚአብሔርንም የሚያሳዝን ነገር ሲናገሩ ይኖራሉ)፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ። አቤቱ ፍረድባቸው፥ በነገረ ሠሪነታቸውም ይውደቁ፤ እንደ ሐሰታቸውም ብዛት አሳድዳቸው፥ አቤቱ፥ እነርሱ አሳዝነውሃልና፤» ብሏል። መዝ ፭፥፬-፲። ጌታችንም በወንጌል፦ «በውጪያቸው አምረው የሚታዩ፥ በውስጣቸው ግን የሙታን አጥንትንና ርኩሰትን ሁሉ የተመሉ የተለሰኑ መቃብሮችን የምትመስሉ እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! እንዲሁ እናንተም በውጭ ለሰው ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ዐመጽንና ግብዝነትን፥ ቅሚያንም የተሞላችሁ ናችሁ፤» ብሏል። ማቴ ፳፫፥፳፯።
          በሚበዛው እንነጋገር ብለን እንጂ ፍጹም ታማኞች የሆኑ ከሁለቱም ወገን አሉ። ውጪ በመኖራቸው የማይኰሩ፥ ያለወን ውጣ ውረድ በግልጥ የሚናገሩ፥ ገቢያቸው ምን ያህል እንደሆነ እና ምን እንደሚሠሩ በትክክል የሚያስረዱ፥ ከሽንገላ ጋር ፍጹም የማይተዋወቁ፥ የእግዚአብሔር ሰዎች እንዳሉ ምስክሮች መሆን እንችላለን። እነዚህም የሚያምኑት በፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑ ተጥባበ ነገር ውስጥ አይገቡም። ሰውን እንደ ሰው እንጂ እንደ ሸቀጥ አይመለከቱም። «አምጥቼህ፥ አምጥቼሽ፤» ብለው አይመጻደቁም። «እግዚአብሔር ቢፈቅድ ነው፤» ብለው ክብሩን ለእግዚአብሔር ይሰጣሉ። የተደረገውን ሁሉ፦ «ለራሴ ብዬ ነው፤» ይላሉ። አንድ ሥጋ ከሆኑ በኋላ በገዛ አካላቸው ላይ አይገዳደሩም። እንዲያውም፦ «ባዕድ አገር አምጥቼህ ተንገላታህ፥ ባዕድ አገር አምጥቼሽ ተንገላታሽ፤» ይላሉ።
          አገር ቤትም ቢሆን፥ በዕድሜ አንመጣጠንም፥ በሃይማኖት አንመሳሰልም የሚሉ፥ ወደ ውጭ ለመውጣት ብለው ያልሆነ ነገር ውስጥ የማይገቡ ጠንቃቆች አሉ። በሃይማኖት ተመሳስለው፥ በዕድሜም ተመጣጥነው፥ የመንፈሳዊነት ጉድለት ካለ ደግሞ ወንድ ከሆነ ሴቷን፥ ሴትም ከሆነች ወንዱን መክረው አስተምረው ለንስሐ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ ያደርጓቸዋል። ከውጭ አገር ለጋብቻ የሚሄዱ መንፈሳዊያን ወጣቶችም በሃይማኖት እስካልመሰሏቸው ድረስ በሥጋዊ ነገር ተሸፍነው ያልሆነ ነገር ውስጥ አይገቡም። በተቻላቸው መጠን በምክርም፥ በትምህርትም ሕይወታቸውን ለውጠው ወደ ትክክለኛው መንገድ ያስገቧቸዋል። በዚህም እምንጭ ላይ ተቀምጠው የተጠሙትን የብዙዎችን ሕይወት ታድገዋል። ቅዱስ ዳዊት፦ «ከጻድቅ ሰው ጋር ጻድቅ ትሆናለህ፤ ከቅን ሰው ጋርም ቅን ትሆናለህ፤ ከንጹሕም ሰው ጋር ንጹሕ ትሆናለህ፤» ያለው እንዲህ አይነቱን ሕይወት ነው። መዝ ፲፯፥፳፭።
          በሌላ በኲል ደግሞ ፍጹም ዓለማውያን ሲሆኑ፥ መንፈሳዊ መስለው፥ ንስሐውንም፥ ተክሊሉንም፥ ቊርባኑንም፥ እሺ ብለው በድፍረት በመቀበል፥ የብዙ መንፈሳውያንን የሕይወት ጉዞ ያሰነካከሉ አሉ። እነዚህም፦ «የቀበሮ ባሕታዊ እበጎች ሥር ይሰግዳል፤» እንደሚባለው ዓይነት ናቸው። ማስመሰል ደግሞ የሰይጣን ግብሩ ነው። ሰይጣን ወደ ገነት ገብቶ አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳታቸው እባብን ተዋሕዶ፥ እባብን መስሎ ነው። ዘፍ ፫፥፩። እርሱ መላእክትንም መምሰል ይችልበታል፤ ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፲፬-፲፭። ቅዱስ ቊርባንንም በተመለከተ፦ «አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ፥ ይህንም ጽዋ የጠጣ፥ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት። አሁንም ሰው ራሱን መርምሮና አንጽቶ ከዚህ ኅብስት ይብላ፤ ከዚህም ጽዋ ይጠጣ። ሳይገባው (በድፍረት)፥ የጌታችን ሥጋም እንደሆነ ሳያውቅ፥ ሰውነቱንም ሳያነጻ፥ የሚበላና የሚጠጣ፥ ለራሱ ፍርዱንና መቅሰፍቱን ይበላል፤ ይጠጣልም።» ብሏል። ፩ኛ ቆ ፲፮፥፳፯።
          የሰው ልጅ የሚኖረው እግዚአብሔር በፈቀደለት ቦታ እግዚአብሔር የፈቀደለትን ኑሮ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «ለእግዚአብሔር ምድር በምልዓ፥ ዓለምኒ ወኲሎሙ እለ ይነብሩ ውስቴታ። ወውእቱ በባሕር ሣረራ፥ ወበአፍላግኒ ውእቱ አጽንዓ። ምድር በሞላዋ የእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ። እርሱ በባሕሮች መሥርቶአታልና፥ በፈሳሾችም አጽንቶአታልና።» እንዳለ፦ ዓለሙ በጠቅላላ የእግዚአብሔር በመሆኑ የት እንደምንኖር፥ እንዴት እንደምንኖር እርሱ ያውቃል። መዝ ፳፫፥፩-፪። ስለዚህ በነገር ሁሉ ፈቃደ እግዚአብሔርን ልናስቀድም ይገባል። የእርሱ ፈቃዱ በአገር ቤት እንድንኖር ከሆነ፥ ሐዘንና ደስታ፥ ጤንነትና በሽታ፥ ማግኘትና ማጣት፥ ሰላምና ጦርነት፥ ቢፈራረቁብን፥ ሁሉን እንደየአመጣጡ የምንሸከምበት ጸጋ ይሰጠናል። ከሁሉም በላይ በሃይማኖት የሚገኘው የቤተ ክርሰቲያን ጸጋ ከምንም ነገር ጋር የሚነጻጸር አይደለም። ቅዱስ ዳዊት፦ «እግዚአብሔር ያበራልኛል፥ ያድነኛልም፤ ምን ያስፈራኛል? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ ምን ያስደነግጠኛል? ክፉዎች ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ፥ የሚያሰቃዩኝ እነዚያ ጠላቶቼ ደከሙ፥ ወደቁም። ሠራዊትም ቢጠላኝ ልቤ አይፈራብኝም፤ ሠራዊትም ቢከቡኝ በእርሱ እተማመናለሁ። እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት፥ እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያስኘውንም አይ ዘንድ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ በቤተ መቅደሱም አገለግል ዘንድ። በመከራዬ ቀን በድንኳኑ (በረድኤቱ ጥላ) ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሰውሮኛልና፥ በዓለትም ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።» ያለው በእግዚአብሔር ቤት ያለውን ጸጋ ስለሚያውቅ ነው። መዝ ፳፮፥፩-፭። በዚህም ከቤተ መንግሥቱ ኑሮ ይልቅ የቤተ እግዚአብሔር ኑሮ የበለጠ መሆኑን ነግሮናል። ይህም የበለጠውን ትተን የቤተ መንግሥትን ፍርፋሪ ለምንለቅም፥ ትልቅ ትምህርት ነው።
          የእግዚአብሔር ፈቃዱ በውጭ አገር እንድንኖር ከሆነ፥ በባዕዳን መካከል የሚያጋጥመንን ሐዘንም ሆነ ደስታ፥ ጤንነትም ሆነ በሽታ፥ መረጋጋትም ሆነ ጭንቀት፥ ማግኘትም ሆነ ማጣት፥ ሁሉንም የምንችልበት ጸጋ ያድለናል። ምክንያቱም ሰዎች ስንባል፦ በሐዘን ጊዜ ቶሎ ተስፋ የምንቆርጥ፥ በደስታ ጊዜ ደግሞ ፈንጠዝያ የምናበዛ ነንና። ሁለቱም አጉል ነው፤ ምክንያቱም በውጪው ዓለም ከሐዘን እና ከጭንቀት ብዛት በራሳቸው ላይ እርምጃ የሚወስዱ አሉና። በፈንጠዚያ ብዛትም፦ ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር የሚጋጩም አሉና። ስለዚህ በሐዘን ጊዜ፦ ማርያምንና ማርታን ያጽናና፥ በደስታ ጊዜ ደግሞ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ዶኪማስን የጐበኘ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛንም እንዲጐበኘን መጸለይ አለብን። ዮሐ ፪፥፩፤ ፲፩፥፲፯።
          የውጪውን ዓለም በምናስብበት ጊዜ ዓላማ ሊኖረን ይገባል። ፩ኛ፦ ተምሬ አንድ ደረጃ መድረስ አለብኝ፤ ፪ኛ፦ ላቤን አፍስሼ፥ ወዜን አንጠፍጥፌ ገንዘብ በማግኘት ራሴን መቻል አለብኝ፤ ፫ኛ፦ ወላጆቼን በሚገባ መጦር አለብኝ፤ ፬ኛ፦ ገንዘብ እየላኩኝ ወንድሞቼን እኅቶችን ማስተማር አለብኝ፤ ፭ኛ፦ ልጆች ወልጄ ለቁም ነገር ማብቃት አለብኝ ፮ኛ፦ የአቅሜን ያህል የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት አለብኝ፤ ፯ኛ፦ አሥራቴን ለቤተክርስቲያን መስጠት አለብኝ፤ ፰ኛ፦ ገዳማትን፥ አድባራትን እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን መደጐም አለብኝ፤ ልንል ያስፈልጋል። ሰው፦ የተፈጠረው ለራሱ ብቻ እንዲኖር አይደለምና። እነዚህን ነገሮች እግዚአብሔር እንደፈቀደ በአገር ቤትም ልናደርጋቸው የምንችላቸው ናቸው። በምናገኘው በአቅማችን መኖር የምናውቅበት ከሆነ የኑሮውን ጫና ያቀልለዋል። ይህንንም የምንለው በአገር ቤት፥ የተማረውም ያልተማረውም፥ ያለውም የሌለውም የኑሮው ውድነት እያጐበጠው እንደሆነ ከመገንዘብ ጋር ነው። አመንም፥ አላመንም፥ በአብዛኛው ወደውጪው ዓለም የምንጐርፈው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው። የተሻለ ኑሮ ሲባልም ሰላማዊ ኑሮ ማለትም ጭምር እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል። ስለዚህ በአገር ቤት ያለንም ሆንን በውጪው ዓለም የምንኖር ሰዎች፥ ወገኖቻችንን፦ ባዕድ ዘመድ፥ ሳንል ልናስባቸው ያስፈልጋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ድሆችን እናስብ ዘንድ ለመኑን፥ ይህንንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ፤» ያለው ለዚህ ነው። ገላ ፪፥፲። በተጨማሪም፦ «እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።» ብሏል። ገላ ፮፥፲። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፦ «ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ሊኖር ይችላል? ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።» በማለት አስተምሮናል። ፩ኛ ዮሐ ፫፥፲፯። በኦሪቱም፦ «አምላክህ እግዚአብሔር በረከት እንደሰጠህ መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደችሎታው ይስጥ፤» የሚል ተጽፏል። ዘዳ ፲፮፥፲፯።
          የትዳሩንም ነገር ስናስብም ሆነ ስንወስን ከትዳር መሠረታዊ ዓላማዎችና ከትዳር ቅዱስነት አንፃር ሊሆን ይገባል። ወደ ውጭ መውጣቱ ሁለተኛ ነገር ነው። በትዳር ወደ ውጪው ዓለም ወጥተው የተሳካላቸውም አሉ። እነዚህም መሠረታዊ ነገሮች ላይ ትኲረት ያደረጉ ሰዎች ናቸው። ተሳካ ስንልም መቶ በመቶ አይደለም። ብንቀበለውም ባንቀበለውም በዚህ ዓለም ላይ የተሟላ ነገር የለም፤ ጧት ብንደሰት ማታ የምናዝንበት ነገር አናጣም፤ እቤት ውስጥ ተደስተን ብንወጣ ከቤት ውጭ የሚያስቀይመን ነገር አይጠፋም፤ ወይም ከቤት ውጭ ደስ ብሎን፥ ፈንጥዘን፥ ስንገባ እቤት ውስጥ የሚያበሳጭ ነገር ይገጥመናል። በምድር ላይ ወጥ ነገር የለም፥ ሁሉም ነገር ተለዋዋጭ ተገለባባጭ ነው።
          በውጭው ዓለም በአንድም ይሁን በሌላ የሰውን አእምሮ የሚጐዳ ብዙ ነገር አለ። በመሆኑም አእምሮአችን ትንሽ ነገር እንኳ መሸከም ወይም መታገሥ ያቅተውና ወደ ቊጣ እናዘነብላለን። በዚህን ጊዜ አንደኛው ክፍል ነገር ማብረድ ካልቻለ ችግር ይፈጠራል። ርብቃ፦ ልጇን ያዕቆብን፦ «የወንድምህ ቊጣ ከአንተ እስኪበርድ ድረስ ከፊቱ ዘወር በል፤» ያለችው ችግር እንዳይፈጠር በማሰብ ነው። ዘፍ ፳፯፥፵፬። ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «ድንጋይ ከባድ ነው፥ አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን ያላዋቂ ቊጣ ይከብዳል። ለቊጣና ቊጣን ለሚያፋጥን ምሕረት የለውም፥ ቀናተኛን ግን የሚተካከለው የለም።» ብሏል። ምሳ ፳፯፥፬። ስለዚህ አንዳችን ስንቆጣ ሌላኛችን ቊጣን ማብረድ መቻል ይኖርብናል። ይኽንንም በተመለከተ፦ «የለዘበ ቃል ቊጣን ይመልሳል፤» ብሏል። ምሳ ፲፭፥፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «መራርነትንና ቊጣን፥ ብስጭትን እና ርግማንን፥ ጥፋትንና ስድብን ሁሉ ከክፉ ነገር ሁሉ ጋር  ከእናንተ አርቁ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኁርኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔርም በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።» በማለት መክሯል። ገላ ፬፥፴፩-፴፪። እንዲህም ሲባል ቊጣ ፈጽሞ አያስፈልግም ማለት አይደለም። ምክንያቱም የሚገባ ቊጣ አለና ነው። እርሱንም ቢሆን ቶሎ ማብረድ ይገባል። ይኽንንም በተመለከተ፦ «ተቈጡ፤ አትበድሉም፤ ፀሐይ ሳትጠልቅም ቁጣችሁን አብርዱ። ለሰይጣንም መንገድ አትስጡት።» ብሏል። ኤፌ ፬፥፳፮።
ይቀጥላል . . .

11 comments:

 1. Kalehiowten Yasemalen! I realy Like it. Andandu Demo Funny New.

  ReplyDelete
 2. Kale Hiwotn Yasemaln Abatachin. yenen Yetdar hiwot yimeleketal ena yemiketlewn kifil eyetebeku new.

  ReplyDelete
 3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ቀሲስ

  ReplyDelete
 4. ቃለ ሕይወት ያሰማልን
  በእውነት ግሩምና ድንቅ ትምህርት ነው ቀሲስ፤ ለረጅም ጊዜ ያብላሉት ሀሳብ መሆኑም ግልጽ ነው!በአሁኑ ዘመን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪው ዓለም ለሚኖሩት ለቤተ ክርስቲያን ልጆች በጣም ትልቅ ችግርም ፈተናም ሆኖል እና እባኮን በእዚህ ዙሬያ ጨምረው ጨምረው አስተምሩን!
  እግዚአብሔር ይስጥልን ቀሲስ!

  ReplyDelete
 5. mehari gebremarqosApril 19, 2011 at 10:00 AM

  የተወደዱ አባታችን መልአከ ሰላም ልዑል እግዚአብሔር ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ስምዎን በዓምደ ወርቅ ይጻፍልን፡፡
  እዚህ ሀገር ቤት ወጣቶች ስደትንና እግዚአብሔር የሌለበትን ኑሮ እንዲመርጡ እያደረጓቸው ካሉ ነገሮች አንዱ በአብዛኞቹ ወላጆቻችን ዘንድ የሚስተዋለው ልጆችን እንደመጦሪያ ኢንቬስትመንት አልያም ደግሞ በኑሮ ግዴታ እንደተፈጠረ ሸክም መቁጠር ይመስለኛል፡፡ ብዙዎች ወላጆቻን ይህንን የሚያደርጉት ካለማወቅ ቢሆንም ከክፉ ራስ ወዳድነትና መፍቀሬ ንዋይነት የሚያደርጉትም ቁጥራቸው ቀላል አይመስለኝም፡፡
  እኔ ባደግሁበት የድሆች ሰፈር አብረውን ካደጉት ታላላቆቻችን፣ እኩዮቻችንም ሆነ ታናናሾቻችን በጣት የምንቆጠር ስንቀር ብዙዎቹ ለወላጆቻቸው ገቢ ለማስገኘት፣ የኑሮዬን ቀይሩልኝ ጭቅጭቅ ለመገላገል ሲሉ ወደ ዐረብ ሀገራት ነጉደዋል፡፡ ሌሎቹ ከወላጆች ግድ የለሽነት የተነሣ ለአጓጉል ሱሶች ተዳርገዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉትም አንዳንዴ በይፋ የሚገለጥ አብዛኛውን ጊዜ ግን በሥውር የሚካኼድ ሴተኛ አዳሪነት (ወንድ አሳዳሪነት)ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ወላጆቻቸው ልጆቹ ገንዘቡን ያምጡት እንጂ ከየትም ቢያመጡት የሚጨንቃቸው ጉዳይ ያለም አይመስልም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም “ታዲያ ምን ችግር አለው፡፡” እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ “እኔም እንደዚህ ሁኜ ነው እነርሱን ያሳደግሁት፡፡” የሚሉም አይጠፉም፡፡ የሚያሳዝነው ልጆቹ የልጅነት ገላቸውን እሳት ላይ ጥደው የሚያመጡትን ገንዘብ ዘላቂነት ያለው ነገር ላይ እንኳ አያውሉትም፡፡ ገንዘቡ ሲላክ የእንጨት የነበረውን ሊወድቅ የደረሰ ቤት በር ወደ ብረትና መስታወት ይቀይሩታል፡፡ ቀጥሎ ሶፋ ይገዙበታል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ቴሌቪዥንና ሲዲ ማጫወቻ ይሸምታሉ፡፡ ከዚያ የግብጽ ካባ ለብሰው መንደር መንደሩን እየዞሩ ቡና መጠጣት ነው፡፡ በቃ!
  ልጆቹ የልጅነት ወዛቸው በዐረብ ሀገር ዋዕይና በዐረቦች ግልምጫ እየለበለበ፣ ዕንቅልፍ ብርቅ ሆኖባቸው፣ ሳቅ እንደ ሰማይ ርቋቸው የሚልኩት ብር ትንሽ ጠርቀምቀም ያለ እንደሆነም ቦታ በራሳቸው ስም ይገዙና ቤት ይሠሩበታል- ለራሳቸው፡፡ ለልጆቹ ምንም የሚተርፍ ነገር አይኖርም፡፡ ለእነርሱ ልጆቻቸው ማለት ገንዘብ ባስፈለገ ጊዜ ሁሉ ሊያስተፉት የሚችሉትና የመትፋትም ግዴታ ያለበት የኤቲኤም ማሽን ማለት ናቸው፡፡ ሥራ መሥራት፣ ራስን መቻል የሚባሉ ነገሮች በእነርሱ ዘንድ ጨርሶ ቦታ የላቸውም- ከቤት ቁጭ ብለው የሚላክ ገንዘብ እያለ፡፡
  በቅርብ የማውቀውን የአንዲት እኅቴን ታሪክ ልተርክ፡፡ ልጅቱ ትምህርት ተምራ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማለፍ ሳይሆንላት ይቀራል፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ልጆቹን ሁሉ ዐረብ ሀገር ልኮ እነርሱ በሚልኩለት ገንዘብ ንጹሕ ሸሚዝ ለብሶ የሚኖር ሰው ወደ ልጅቱ እናት ጠጋ ይልና “ለምን እንደኔ ዐረብ ሀገር ልከሽ ዘና ብለሽ አትኖሪም?” የሚል “ምክር” ለገሳት፡፡ አሁን ሳስበው የምክሩ መነሻ ሐዘኔታ ብቻ አልነበረም የድለላ ገንዘብ ፍለጋ ጭምር እንጂ፡፡ ደግነቱ እናትየው በሥራ ብቻ የምታምን ግብረገብ የገባት ሴት ነበረችና ግሥላ ሆነችበት፡፡ “ልጄ ከኔ ጋር ሠርታ ትሞታለች:: ካስፈለገም ኮረንቲ ልጬ እሰጣታለሁ እንጂ እሷን በዐረብ ሀገር እሳት ቀቅዬ አልበላም፡፡” አለችው፡፡ ዛሬ ያቺ በእናቷ የተጠበቀችው ልጅ ችግሩም አልፎ፣ እርሷም ተድራ፣ ዛሬ እናቷን ለሁለት ወንዶች ልጆች አያትነት አብቅታለች፡፡

  ሌሎቹ በወላጆቻቸው ማባበል፣ ግፊት አለፍ ሲልም ንትርክና ግልምጫ ወደዐረብ ሀገራት የተሰደዱት የዕድሜ አቻዎቿ ከፊሉ ዛሬም እዚያው ዐረብ ሀገር በሰው ፊት ይጠበሳሉ፡፡ ከፊሉ የያዝነውን ይዘን ወደሀገራችን እንመለሳለን ቢሉም ሲመጡ የሚጠብቃቸው ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሮ ራስን መለወጥን ሳይሆን የተገኘን ገንዘብ በልቶ የመጨረስ ጠባይ የተጠናወተው ቤተሰብ ስለሆነ ወዛቸውን፣ ሰው የመሆን ክብራቸውንና አካላቸውን ጭምር ለአደጋ አጋልጠው ያመጡት ገንዘብ እንደዱር ፍሬ አንድ በአንድ ተለቅሞ ይበላል፡፡ የአንዳንዶቹ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው ሲመጡ የሚቀበሉት እጃቸውን ለናፍቆት ዕቅፍ ሳይሆን ለገንዘብ ዘርግተው ነው፡፡ ገና እግራቸው ከቤት እንደደረሰ “እስኪ ገንዘቡን ሰብሰብ ላድርግልሽ፡፡ ለሰው ዓይንም ጥሩ አይደለም፡፡” በሚል አጉል ተንከባከቢ ምክንያት በባሌም በቦሌም ብለው ገንዘቡን ከእጃቸው ካወጡ በኋላ ለዓይናቸው ይጠየፏቸዋል፡፡ “ተመልሼ አልኼድም፡፡ እዚሁ የራሴን ሥራ እየሠራሁ ወይም ተምሬ ራሴን ችዬ እኖራለሁ፡፡” የሚል ውሳኔ እኔ እንዳየሁት ብዙ ዋጋ ያሰከፍላል፡፡ ግልምጫው፣ ማመናጨቁ፣ የገዛ ገንዘብን አልሰጥም ብሎ መከልከሉ ከወላጅ አይደለም ከጎረቤት የሚጠበቅ አይደለም፤ ግን እውነታው እርሱ ነው፡፡ በእነርሱው ወዝ በታደሰው ቤት ውስጥ ማረፍን እንኳ የሚከለክል ወላጅም አለ፡፡ ይህን ሁሉ የምናገረው ካየሁት እኔው ራሴ የዓይን ምስክር ከሆንኩት ተነሥቼ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንዲት እኅቴ ከዐረብ ሀገር ለዓመታት ስትጠበስ ቆይታ ስትመለስ የኮምፒውተር ትምህርት መማር ትጀምራለች፡፡ ከትምህርት ቤት ስትመለስም ይዛ በመጣችው ኮምፒውተር የተማረችውን መከላለስ ትሞክራለች፡፡ ይኼኔ ይዛ በመጣችው 34 ኢንች ቴሌቪዥን በእርሷ ገንዘብ በተገዛው ጉንጫም ሶፋ ላይ ቁጭ ብለው ፊልም ሲያዩ የመብራት ነገር ፈጽሞ ትዝ ያላላቸው ወላጆቿ “መብራት ይቆጥርብናል!” ብለው በግልምጫ ሲያሳቅቋት አስታውሳለሁ፡፡
  በእነዚህ ወላጆች ገንዘብ አምላኪነት ምክንያት ገንዘብ እንጂ ግብረገብ ከሌለው መጥፎ ሰው ጋር የተጣመዱ፣ ከሃይማኖታቸው ውጪ የሆነን ሰው እንዲያገቡ የሆኑ እኩዮቻችንንም ኑሯቸው ይቁጠራቸው፡፡ ለገንዘብ ብለው ከኤችአይቪ ጋር ከሚኖር ሰው ጋር ትዳር የመሠረቱም አሉ፡፡ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ልጆቹን በገንዘብ አምልኮ ይጠምዷቸዋል፡፡ በወላጅነትና ልጅነት ትስስር አልጠመድ ሲሏቸው በረኀብ ያስገድዷቸዋል፡፡ እምቢኝ ብለው ቀንበር ከሰበሩ ደግሞ የእርግማኑ፣ የማግለሉ፣ ስም የማጥፋቱ ዘመቻ አጀብ ያሰኛል፡፡ ከእንዲህ ዓይነት “ልጅ መጦሪያ ኢንቬስትመንት ነው፡፡” ብለው ከሚያስቡ ራስ ወዳድ ወላጆች መወለድ መከራ ነው፡፡

  ReplyDelete
 6. ቓለ ሕይወት ያሰማልን አባታችን አስተማሪ የሆነ ዽሁፍ ነው ቸሩ መድሀኒያለም ማስተዋልን ይስጠን

  ከሰንፍራንሲስኮ

  ReplyDelete
 7. መላከ ሰላም ደጀኔ ሽፈራው ቃለ ህይወት ያሰማልን ፦ እግዚአብሔር አገልግሎቶን ይባርክ ። ጥሩ ምልከታ ነው ዲያቆን ዳንኤል ብርሃኑ ከ ሚዙሪ

  ReplyDelete
 8. kale hiwot yasemawot kesis,Egig astemarinew mekerot ayeleyen. calgery,ca.

  ReplyDelete
 9. Lib yaleh Lib bel Kale hiwot yasemalin Amen!!

  ReplyDelete
 10. እግዚአብሔር አገልግሎቶን ይባርክ

  ReplyDelete
 11. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  ReplyDelete