Sunday, April 17, 2011

ነገረማርያም ክፍል፦ ፲፪

             ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፦ በዘር በሩካቤ የተወለዱ የአበውን ልደት ሲናገር ከመጣ በኋላ፦ «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነው፤» በማለት፦  ልደቱ ልዩ መሆኑን ተናግሯል። ምስጢረ ልደቱን  ሲያብራራም፦ «ወሶበ ተፍኅረት እሙ ማርያም ለዮሴፍ፥ ዘእንበለ ይትቃረቡ ተረክበት ፅንስተ እንዘ ባ ውስተ ማኅፀና እመንፈስ ቅዱስ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ፥ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።» ብሏል። በዚህም የእመቤታችን ፅንሷ እንደሌሎች ሴቶች በዘር በሩካቤ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ግብር መሆኑን መስክሯል።
፩፥፩፦ የእመቤታችን እና የቅዱስ ዮሴፍ ዝምድና፤
          ቅዱስ ዮሴፍ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የቅርብ ዘመዷ ነው። ቅዱስ ማቴዎስ የአበውን ልደት እየተናገረ መጥቶ ወደ መጨረሻው ላይ፦ «አልዓዛርም ማትያንን ወለደ፤ ማትያንም ያዕቆብን ወለደ። ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለ ጌታ ኢየሱስ ከእርሷ የተወለደ የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ።» ብሏል። ለቅዱስ ዮሴፍና ለእመቤታችን የሥጋ ዝምድና ግንዱ አልዓዛር ነው። አልዓዛር የወለደው ማትያንን ብቻ ሳይሆን ቅስራንም ነው። ቅስራ ቅዱስ ኢያቄምን ወለደ፤ ቅዱስ ኢያቄም ደግሞ እመቤታችንን ወለደ። ዝምድናቸው የሦስት ትውልድ ነው። ለሁለቱም ቅድመ አያታቸው አልዓዛር ነው።

                                             አልዓዛር፤  

                                 ማትያን ፤         ቅስራ፤

                       ያዕቆብ፤                              ኢያቄም፤

            ዮሴፍ ፤                                      ድንግል ማርያም፤
          በዕብራዊያን ልማድ ሴትንና ወንድን ቀላቅሎ ትውልድ መቁጠር ሥርዓት አይደለም። በመሆኑም፦ ቅዱስ ማቴዎስ «ሥርዓት አፈረሰ፤» ይሉኛል፥ ብሎ የጌታን ልደት ስለ ዝምድናቸው በዮሴፍ በኲል ቆጥሯል፥ እርሷም እንዳትቀር በቅጽል አምጥቷታል።
፪፦ እመቤታችን ለምን ለዮሴፍ ታጨች?
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዮሴፍ የመታጨቷን ነገር መናፍቃን በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ አፈታት ፈት ተው (ተርጉመው) ስለሚያስተምሩ፦ የእንቅፋት፥ የመሰናከያ ድንጋይ ሆኖባቸዋል። ከመናፍቅነት የጸዱ ምዕመናን ደግሞ መናፍቃኑ በሚሉት ባይስማሙም የኅሊና ጥያቄ ስለሚሆንባቸው መልስ ይፈልጋሉ። ለዚህም የማያዳግም መልስ የሚሆ ነው፥  አባቶቻችን በአፍም በመጽሐፍም ያስተማሩት ትምህርት ነው ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጥንተ አብሶ ነጻ ሆና የተፈጠረችው፥ ከማኅፀን ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ የተጠበቀችው፥ አሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ የኖረ ችው፥ ሰማያዊ ምግብ የተመገበችው፥ በቅዱሳን መላእክት የተገለገለችው፥ ለአምላክ እናትነት ነው። ይህ እንዲህ ከሆነ ለምን ለዮሴፍ ታጨች?
፪፥፩፦ ኃይል አርያማዊት እንዳይሏት ነው፤
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ሰማይና ምድር የማይወስኑትን፥ ዓለምን በእጁ መዳፍ የያዘውን፥ መንበሩ እሳት፥ መጋረጃው እሳት፥ አጋልጋዮቹ እሳት፥ መለኰታዊ ባሕርዩም እሳት የሆነውን አምላክ በማኅፀኗ መሸከሟ ከሰው አእምሮ በላይ ነው። ምክንያቱም፦ እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ፥ በተዋሕዶ ሰው ሁኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣልና ነው። በመሆኑም፦ «በሰው አቅም እንዴት ይቻላል? ኃያላን የሚባሉ ኪሩቤል እንኳን እሱን ሳይሆን፥ የሚሸከሙት የእሳቱን መንበር ነው፤ ሱራፌልም የሚያጥኑት እርሱን ሳይሆን፥ የእሳቱን መንበር ነው፤ በዚህም ላይ ፊቶቻቸውንም እግሮቻቸውንም ይሸፍናሉ፤» እያሉ፥ የእመቤታችንን ከሰው ወገን መሆን የሚጠራጠሩ፥ «ኃይል አርያማዊት (ሰማያዊት ኃይል)» የሚሉ ሰዎች እንደሚመጡ እግዚአብሔር ያውቃል። በማወቁም፦ የሰው እጮኛ እንድትሆን ሳይሆን እንድትባል አድርጓል። ይኸውም፦ «ለሰው መታጨቷ ከሰው ወገን ብትሆን ነው፤» ለማሰኘት ነው።

፪፥፪፦ የጌታን ጽንስ ከአጋንንት ለመሰወር ነው፤
          አጋንንት፦ የሰውን ጥፋቱን እንጂ ድኅነቱን አይሹም፤ ጥንትም፦ እግዚአብሔርን ያህል አባት፥ ገነትን ያህል ርስት ያሳጡት እነርሱ ናቸው። የሰውን ልጅ ከአባቱ ለይተውት፥ ከርስቱ ነቅለውት፥ እስከ ልጅ ልጆቹ፥ በእጃቸው ጨብጠው፣ በእግራቸው ረግጠው በሲኦል ገዝተውታል፤ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ባለ ዕዳ አድረገው አሰቃይተውታል። የጌታ ወደዚህ ዓለም መምጣት ደግሞ ይኽንን ሁሉ ለመሰረዝ ነው፤ የሰውን ልጅ ከአጋንንት ቁራኝነት አላቅቆ ከሲኦል ለማውጣት፥ ከሞት ወደ ሕይወት ለማሸጋገር፥ ወደ ጥንተ ርስቱ ገነት ለመመለስ ነው።
          አጋንንት፦ የጌታን በመንፈስ ቅዱስ ግብር መፀነስ ሰምተውት ወይም አውቀውት ቢሆን ኖሮ፥ «ይህ ሳይሆን አይቀርም፤» እያሉ የብዙ ሴቶችን ጽንስ ባበላሹ ነበር። ለምሳሌ፦ በልደቱ ጊዜ፥ በሄሮድስ አድረው፥ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕጻናትን ያሳረዱት ከእነዚያ መካከል ሕፃኑ ኢየሱስ አይጠፋም በሚል ግምት ነው። ማቴ ፪፥፲፮። በመሆኑም አመቤታችን የዮሴፍ እጮኛ እንድትባል አድርጎ፥ በመንፈስ ቅዱስ  ግብር የሆነ ፅንሱን ከአጋንንት ሰውሮባቸዋል።
፪፥፫፦ ከርስት ገብቶ እንዲቆጠርላት ነው፤
          በእስራኤል ከርስት ገብቶ የሚቆጠረው ወንድ ብቻ ነው፥ ሴቶቹ ግን በወንዱ ሥር ሆነው ከርስት ገብተው ይቆጠራሉ። «በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቈጠር ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ ለሶርያ መስፍን በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ቈጠራ ሆነ። ሰው ሁሉ ሊቈጠር ወደየከተማው ሄደ። ዮሴፍም ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ቤተልሔም ወደምትባለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱም ከዳዊት ሀገርና ከዘመዶቹ ወገን ነበርና። ፀንሳ ሳለች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይቈጠር ዘንድ ሄደ።» እንዲል፦ ከርስት ገብቶ ሊቆጠርላት እግዚአብሔር ባወቀ እጮኛዋ ተባለ። ሉቃ ፪፥፩-፭።
፪፥፬፦ በመከራ ጊዜ እንዲከተላት ነው፤
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ብዙ መከራ እንደሚያጋጥማት በእርሱ ዘንድ አስቀድሞ የታወቀ ነው። በመሆኑም በሄሮድስ አሳዳጅነት፥ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በረሀ ለበረሀ በስደት በምትንከራተትበት ጊዜ፥ የሚከተላት፣ የሚያገለግላት ሰው ያስፈልጋታል። ይህም ሰው የሥጋ ዘመዷ የሆነ፥ እጮኛዋ የተባለ፥ አረጋዊው ዮሴፍ ነው። «እነርሱም (ሰብአ ሰገል) ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ፥ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ምድረ ግብጽ ሽሽ፤ እስከምነግርህም ድረስ በዚያ ኑር አለው፤» እንዲል፦ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ እርሷን እያገለገለ አብሯት ተንከራትቷል። «እርሱም በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ። ከእግዚአብሔር ዘንድ፥ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት ተብሎ በነቢይ (በነቢዩ በሆሴዕ) የተነገረው ይፈፀም ዘንድ፤ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።» ይሏል። ማቴ ፪፥፲፫-፲፭፣ ሆሴ ፲፩፥፩።
፪፥፭፦ በደንጊያ ከመገደል ሊያድናት ነው፤
          በኦሪቱ ሕግ ሴት ልጅ ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ ጸንሳ ስትገኝ፥ በአደባባይ ተፈርዶባት፥ በደንጊያ ተቀጥቅጣ ትገደላለች። ወንድም ቢሆን፦ «አመነዘረ፤» ተብሎ ሕጉ ይፈጸምበታል። «ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽሞ ይገደሉ።» ይላል። ዘሌ ፳፥፲። በተጨማሪም፦ «ለወንድ የታጨች ድንግል ልጅ ብትኖር፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርሷ ጋር ቢተኛ፥ ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጧቸው፤ ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዬውም የባልንጀራውን ሚስት አስነውሯልና በድንጋይ ወግረው ይግደሏቸው፤ እንዲሁ ክፉውን ነገር ከውስጥህ ታስወግዳለህ።» የሚል አለ። ዘዳ ፳፪፥፳፫።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ጽንሰቱን (በመንፈስ ቅዱስ ግብር መሆኑን) ከአይሁድም ሰውሮባቸዋል። በመሆኑም፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ፀንሳ በተገኘችበት ወራት፥ በስመ እጮኛ አረጋዊ ዮሴፍ በአጠገቧ ባይኖር ኖሮ፥ ሕገ ኦሪትን ለመፈጸም ብለው በደንጊያ ቀጥቅጠው ይገድሏት ነበር።
፪፥፮፦ ከስድብ ከነቀፋ ሊያድናት ነው፤
          በእስራኤል አንዲት ድንግል ሳትታጭ ከቆየች፥ ሁሉ ይሰድባታል፥ ሁሉ ይነቅፋታል፤ እንደ አገራችን ባሕል፦ «ቆማ የቀረች፥ ፈላጊ ያጣች፤» ትባላለች። ምክንያቱም ለጋብቻ መታጨት፥ ለቁም ነገር መፈለግ፥ የጨዋነት ምልክት ነውና። በመሆኑም ያጨም፥ የታጨችም በሰው ዘንድ ክብር አላቸው። እንዲህ ካልሆነ ግን በቀጥታም ሆነ በአሽሙር የሚጐነትላቸው  ይበዛል።
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ አድሮባት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ተጠብቃ፥ በእሳታውያን መላእክት ተከብባ፥ በክንፎቻቸውም ተሸፍና የምትኖር ለእግዚአብሔር እናትነት የተመረጠች፥ የተቆለፈች፥ ተቆልፋም ለዘለዓለሙ የምትኖር፥ እግዚአብሔር ብቻ ሳይከፍት ገብቶ ሰይከፍት የሚወጣባት፥ ሰው የማይገባባት፥ የእግዚአብሔር ቤተ መቅድስ ናት። ቅዱስ ኤፍሬም፦ በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ፣ በእሑዱ ክፍል፦ «በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ አንቺ ነሽ፤»  ያለው ለዚህ ነው። በቅዳሜውም ክፍል፦ «የማትፈርሽ መቅደስ ነሽ፤» ብሏታል። ቅዱስ ዳዊትም፦ «እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዷታልና፤ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።» በማለት ትንቢቱን አስቀድሞ ተናግሯል። መዝ ፻፴፩፥፲፫። ነቢዩ ሕዝቅኤልም፦ «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም፦ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች፣አለኝ፤» ብሏል።ሕዝ ፵፬፥፩-፪። በመሆኑም፦ ሰዎች እመቤታችንን፦ በሥጋ ምኞት እንዳያስቧት ኀሊናቸውን ጠብቆላታል። ይኽንን በተመለከተ አባ ሕርያቆስ፦ መንፈስ ቅዱስ በገለጠለት በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ፦ «ድንግል ሆይ፥ የሚያታልሉ ጎልማሶች ያረጋጉሽ  አይደለሽም፥ የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ፤ (ተድላ ዓለም ፥ ብዕለ ዓለም ፥ ያታለላቸው ፣አንድም አጋንንት በውዳሴ ከንቱ የሚያታልሏቸው፥ አንድም በሎሚ በቀለበት የሚያታልሉ፥ አንድም ፈቃደ ሥጋቸው ያታለላቸው ወጣቶች ያረጋጉሽ አይደለሽም፤ መላእክት ጐበኙሽ፥ አጫወቱሽ እንጂ፤» ብሏል። ቊ ፵፫። በሌላ በኩል ደግሞ፥ እንደ ሌሎች ሴቶች መስላቸው ወደ ነቀፋና ወደ ስድብ እንዳይሄዱ፥ ዘመዷን ዮሴፍን በአጠገቧ አስቀምጦላታል። ምክንያቱም፦ «ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤» የሚለውን ስለማያውቁት ነው፥ አንድም እግዚአብሔር ባወቀ ስለተሰወረባቸው ነው። የዮሴፍ እጮኝነት፥ ምሥጢር ለተሰወረባቸው አይሁድና ለአጋንንት ሌላ ነው፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ማደሪያውን የጠበቀበት ጥበብ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ እግዚአብሔርን፦ «አቤቱ ሥራህ እጅግ ታላቅ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፤» ብሎታል። መዝ ፻፫፥፳፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት ፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!» ብሏል። ሮሜ፲፩፥፴፫።
፪፥፯፦ እንዲጠብቃት እንዲያገለግላት ነው፤
 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ለዮሴፍ የታጨችበት ዋናው ዓላማ እንደ አባት ሊጠብቃት፥ እንደ አሽከር ሊያገለግላት ነው። አንድም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ድንግል ማርያምን እንዲጠብቅ እንዲያገለግል ከብዙ አረጋውያን መካከል የተመረጠ ታማኝ አገልጋይ ነው። አባ ሕርያቆስ፥ ከላይ እንደገለጥነው፥ መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት፥ እመቤታችንን ባመሰገነበት ድርሰቱ፥ በቅዳሴ ማርያም ላይ፦ «ድንግልሆይ፥ ለዮሴፍ የታጨሽ ለትዳር አይደለም፥ ንጹሕ ሆኖ ሊጠብቅሽ ነው እንጂ፤» ያለው ለዚህ ነው። ቊ ፵፬።
ኢያሱ ወልደ ነዌ፥ ሙሴን እንዲያገለግል በመታጨቱ (በመመረጡ) እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ (ሙሴ ከዚህ ዓለም እስኪለይ) ድረስ አገልግሎታል። በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ፦ «እንዲህም ሆነ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ከሞተ በኋላ፥ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤» ይላል። ኢያ ፩፥፩። ኢያቡር የተባለው የአብርሃም ሎሌ፥ ጌታውን አብርሃምን እስኪሸመገል፥ ዘመኑም እስኪያልፍ ድረስ ታጥቆ አገልግሎታል። ዘፍ ፳፬፥፩። ሌዋውያን ካህኑን አሮንን እንዲያገለግሉ እግዚአብሔር መርጧቸው ነበር። «እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው፤» ይላል። ዘኁ ፫፥፭።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ማገልገልን ነው፤ ይኽንንም፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ ሊያገለግሉት አልመጣምና፤» በማለት ነግሮናል። ማር ፲፥፵፭። ይኽንን በተናገረበት አንቀጽ ላይ፥ ደቀመዛሙርቱንም፦ «ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤» ብሎአቸዋል። ማር ፲፥፵፫። ከዚህም የምንማረው፥ መልዕልተ ፍጡራን ለሆነች ለአምላክ እናት ቀርቶ፥ ለሚመስለን ወንድማችን እንኳ ባሪያ መሆን እንደሚገባ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ፤» ብሏል። ገላ ፭፥፲፫። ስለራሱም ሲናገር፦ «እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፱። ሐዋርያው ራሱን ባሪያ አድርጐ ያስገዛው ከእርሱ ለሚያንሱት እንኳ ነው።
ስምዖን የተባለው ቁርበት ፋቂ ቅዱስ ጴጥሮስን በቤቱ ተቀብሎ አገልግሎታል፤ የሐዋ ፲፥፵፮። በብሉይ ኪዳን ዘመንም እግዚአብሔር ያዘጋጃት መበለት፥ የሰራፕታዋ ሴት፥ ነቢዩ ኤልያስን አገልግላዋለች። «የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፥ እንዲህም አለው፦ ተነሥተህ በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ በዚያም ተቀመጥ፤ እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት መበለት አዝዣለሁ፤» ይላል። ፩ኛ ነገ ፲፯፥፰። ሱናማዊቷም ሴት ነቢዩ ኤልሳዕን ቤት ሠርታ እስከመስጠት ድረስ አገልግላዋለች። ሱናማዊቷ ሴት ባሏን፦ «ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው (ነቢዩ ኤልሳዕ) ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደሆነ አውቃለሁ። ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋና ጠረጴዛ፥ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደእኛም ሲመጣ ወደዚያ ይግባ አለችው፤» ይላል። ፪ኛ ነገ ፬፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ ቅዱሳንን ማገልገል እንደሚገባ ሲናገር፦ «ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት መላልሰው ማለዱን። እነርሱ አስቀድመው በፈቃዳቸው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔርም፥ ለእኛም አሳልፈው ሰጥተዋልና እኛ እንደአሰብነው አይደለም፤ ይህንም የቸርነት ሥራ እንደጀመረ ይፈጽምላቸው ዘንድ ቲቶን ማለድነው። በሁሉም ነገር በእምነትና በቃል፥ በዕውቀትም፥ በትጋትም በእናንተ ዘንድ በሆነው ሁሉ እኛን በመውደዳችሁ ፍጹማን እንደሆናችሁ፥ እንዲሁም ደግሞ ይህቺን ስጦታ አብዙ።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፰፥፬። 
፫፦ ዮሴፍ የተመረጠበት መንገድ፤
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ለእናት ለአባቷ የስዕለት ልጅ ናት፤ ከዚያ በፊት መሐኖች ነበሩ። በዘመነ ኦሪት፦ የሕልቃና ሚስት ሐና፦ «ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤» ብላ እንደተሳለች፥ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐናም ልጅ ቢሰጣቸው መልሰው ለእግዚአብሔር እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል። ፩ኛ ሳሙ ፩፥፲፩። ከፍጥረት ሁሉ በላይ የከበረች ልጅ እንደሚወልዱም ሁለቱም በየራሳቸው በህልም ተረድተዋል። እግዚአብሔርም፦ ህልማቸውን እስኪፈታላቸው፥ ስእለታቸውን እስኪፈጽምላቸው ድረስ መኝታ ለይተው ጾም ጸሎት ይዘዋል፤ ሱባኤም ገብተዋል።
ጊዜው ሲደርስ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል መኝታቸውን አንድ እንዲያደርጉ ነግሯቸው፥ ነሐሴ ሰባት ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀነሰች። ይኽንንም አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ፦ «ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ፥ አላ በሩካቤ  ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ። ድንግል ሆይ፥ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፥ በሕግ በሆነ በሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ።» በማለት ተናግሯል። ቊ ፴፰። የተወለደችውም ግንቦት አንድ ቀን ነው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሞላት፥ «አባ፥ እማ» ማለት ስትጀምር፥ ወስደው ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተዋታል። ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ነበር፤ እርሱም፦ ከፀሐይ ይልቅ የጠራች፥ ከጨረቃ ይልቅ የደመቀች፥ ይህችን የመሰለች ልጅ፥ «ምን አበላታለሁ? ምን አጠጣታለሁ? ምን አለብሳታለሁ? ምን አነጥፍላታለሁ? ምንስ እጋርድላታለሁ?» ብሎ ሰው ሰውኛውን ሲጨነቅ፥ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ፥ አንድ ክንፉን አነጠፈላት፥ በአንድ ክንፉ ደግሞ ጋረዳት። ኅብስት ሰማያዊ፥ ጽዋ ሰማያዊም መገባት። ይኽንንም በተመለከተ አባ ሕርያቆስ፦ «ኦ ድንግል፥ አኮ ኅብስተ ምድራዌ ዘተሴሰይኪ፥ አላ ኅብስተ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘበሰለ፤ ኦ ድንግል አኮ ስቴ ምድራዊ ዘሰተይኪ፥ አላ ስቴ ሰማያዊ እምሰማየ ሰማያት ዘተቀድሐ፤ ድንገል ሆይ፥ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለሽም፥ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ፥ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለሽም፥ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤» ብሏል። ቅዳ ማርያም ቊ ፵። ይህም በግብር አምላካዊ የተገኘ ነው። ዘካርያስም የምግቧ ነገር ከተያዘ ብሎ ወደ ቤተመቅደስ አስገብቷታል።
በቤተ መቅደስ፦ መላእክት እየመገቧትና እያረጋጓት አሥራ ሁለት ዓመት ተቀምጣለች። በዚያም በአጭር ታጥቃ፣ ማድጋ ነጥቃ፣ ውኃ በመቅዳት፥ ሐርና ወርቅ እያስማማች በመፍተል መጋረጃ በመሥራት፥ በአገልግሎት ኖረች እንጂ በሥራ ፈትነት አይደለም። ይህ ነገር በጎ ኅሊና የጐደላቸውን አይሁድን አላስደሰታቸውም። «ቤተ መቅደሳችንን ታረክስብናለች፤» ብለው በቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ላይ በጠላትነት ተነሡባት። የእነርሱ ቤተ መቅደስ የሚፈርስ ቤተ መቅደስ ነው፤ ይኽንንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፤ (ይህ ቤተ መቅደስ እንዲህ እንዳሸበረቀ አይቀርም፥ ይፈርሳል)፤» በማለት አድንቀው ለነገሩት ለደቀመዛሙርቱ ነግሯቸዋል። ማቴ ፳፬፥፪። እንደተናገረውም የሮም ንጉሥ ጥጦስ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ በ70 ዓም ፈርሷል። እመቤታችን ግን ቅዱስ ኤፍሬም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፥ በቅዳሜው ክፍል እንደተናገረው፥ «የማትፈርስ ቤተ መቅደስ» ናት።
ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ፥ አይሁድ፦ «እነሆ አሥራ አምስት ዓመት ሆኗታል፥ መጠነ አንስትም አድርሳለች፥ ቤተ መቅደስ ታሳድፍብናለችና ትውጣልን፤» እያሉ አላስቆም አላስቀምጥ አሉት። እርሷ ግን፦ ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ምንም ነውር የለብሽም።» እንዳለ፥ እድፍ ጉድፍ የሌለባት፥ ንጽሕተ ንጹሐን፥ ቅዱስተ ቅዱሳን ናት። የረከሰውን የምትቀድስ ናት። መኃ  ፬፥፯። ዘካርያስም ወደ እርስዋ ገብቶ «ምን ይበጅሻል? እንዴት ትሆኚ?» ቢላት «ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ፤» ብላዋለች። ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት፦ «ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን አስቈጥረህ፥ በትራቸውን ከቤተ መቅደስ አግብተህ ስትጸልይበት እደርና አውጣው፤» ብሎታል። እንደተባለው ቢያደርግ ከበትረ ዮሴፍ ላይ፦ «ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት፥ ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ፤ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ እጮኛህን ማርያም ለመውሰድ አትፍራ፤» የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበት ተገኝቷል። ይኸውም፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ፥ እግዚአብሔር እንዳዘዘው፥ በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ፥ አሥራ ሁለት በትሮችን ሰብስቦ፥ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ ቢጸልይበት፥ በትረ አሮን ለምልማ፣ አብባና አፍርታ እንደተገኘችው ማለት ነው። ዘኁ ፲፯፥፩-፰። ሁለተኛም፦ ነጭ ርግብ ወርዳ ከዮሴፍ ራስ ላይ አርፋበታለች፤ ሦስተኛም፦ ዕጣ ቢጣጣሉ ዕጣው ለዮሴፍ ወጥቶለታል። ከዚህ በኋላ ለማኅደረ መለኰትነት የተመረጠች ድንግል ማርያምን ይጠብቃት፥ ይንከባከባትም ዘንድ ወደ ቤቱ ይዟት ሄዷል።
፬፦ እግዚአብሔር እሥራኤልን ማጨቱ፤
እግዚአብሔር እስራኤልን በማጨቱ የእስራኤል እጮኛ ተብላለች፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር፥ በነቢዩ በሆሴዕ አድሮ ሲናገር፥ «ስለዚህ እነሆ አቅበዘብዛታለሁ፤ ወደ ምድረ በዳም አወጣታለሁ፤ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የተገኘውን ገንዘብዋን እሰጣታለሁ። ምክርዋንም በአኮር ሸለቆ እገልጣለሁ፤ እንደ ሕፃንነትዋ ወራት፥ ከግብፅም እንደወጣችበት ቀን ትዘምራለች። በዚያን ቀን ባሌ (እግዚአብሔር ፈጣሪዬ ነህ)፤ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ በዓሊም (ጣዖቱ እንደማያድን እርሱም አያድንም)፤ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የበዓሊምን (የጣዖታቱን) ስሞች ከአፍዋ አስወግዳቸዋለሁና፥ (ጣዖታቱን እንዳታመሰግን አደርጋታለሁ)፥ ስማቸውም ከእንግዲህ ወዲህ አይታሰብም። (ቤል፣ ዳጎን እያለች ስማቸውን አታነሣም)። በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች (ከአሕዛብና ከኃያላን) ጋር ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ። (በጠላትነት ተነሥተው እንዳያጠፏት አደርጋለሁ)። ቀስትንና ሰይፍን፥ ጦርንም ከምድሩ እሰብራለሁ፤ (በቀስትና በሰይፍ፥ በጦርም ሊያጠፉ የሚችሉትን ሁሉ አጠፋቸዋለሁ)፤ ተዘልለሽም ትቀመጫለሽ። (ጠላት ጠፍቶልሽ በሰላም ትኖሪያለሽ)፤» ካለ በኋላ፥ «ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ እጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በይቅርታ አጭሻለሁ። (በሃይማኖት ጸንተሽ፥ ጽድቅን፣ ርትዕን፣ ጸሎትን፣ ገንዘብ አድርገሽ ብትገኚ፥ እውነትን፣ ፍርድን፣ ምሕረትንና ይቅርታን ማጫ አድርጌ ለዘለዓለም ማደሪያዬ ልትሆኚ አጭሻለሁ)። ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ። (ይቅርታን ቸርነትን አድርጌልሽ ፈጣሪሽ እኔ እንደሆንኩ ታውቂኛለሽ)።» ብሏል። ሆሴ ፪፥፲፬-፳።
እስራኤል ዘሥጋ፥ ከግብፅ ምድር በወጡ በሦስተኛው ወር፥  እግዚአብሔር ሙሴን፦ «በግብፃውያን ላይ ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ (ንስር ፈጣን እንደሆነ ፈጥኜ እንዳወጣኋችሁ)፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ (በባለሟልነት እንዳቀርብኳችሁ) አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ፥ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ (የታጨ) ርስት (ወገን) ትሆኑኛላችሁ፤ እናንተም የክህነት መንግሥት፥ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። (ካህናቱ ነገሥታቱ ከእናንተ ይወለዳሉ፥ ምግባር ሃይማኖት የሚጠብቁ ከእናንተ ይወለዱልኛል፥ በእኔ በእግዚአብሔር ላይ የጣዖት ውሽማ የማያበጁ ከእናንተ ይገኙልኛል)፤ ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።» ብሎታል። ዘፀ ፲፱፥፫-፮። በኦሪት ዘዳግም ላይ ደግሞ፦ «ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዘብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦሃልና። እግዚአብሔር የወደዳችሁና የመረጣችሁ፥ ከአሕዛብ ሁሉ ስለበዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አባቶቻችሁን መረጣቸው፤ ወደዳቸውም፤ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መረጠ።» የሚል ተጽፏል። ዘዳ ፲፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እኒህም፦ ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥ ተስፋም የተሰጣቸው፥ እስራኤላውያን ናቸው። እነርሱም አባቶቻችን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን።» ብሏል። ሮሜ ፱፥፬-፭።
፭፦ ምእመናን ለክርስቶስ መታጨታቸው፤
የአዲስ ኪዳን እስራኤል፦ በሥላሴ ስም የተጠመቁ፥ በሜሮን የከበሩ፥ በሥጋ ወደሙ የታተሙ ምዕመናን ናቸው። እነርሱም እስራኤል ዘነፍስ ይባላሉ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ፥ «እውነት እላችኋለሁ፤ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ።» ብሎታል። ማቴ ፲፱፥፳፯-፳፰። «በእስራኤል ትፈርዳላችሁ፤» ማለቱም በእስራኤል ዘሥጋ በአይሁድ ብቻ ሳይሆን እስራኤል ዘነፍስ በሚባሉ በምዕመናንም ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤል ዘሥጋ ለእግዚአብሔር እንደታጩ፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ ምዕመናን ለክርስቶስ መታጨታቸውን ሲናገር፦ «በስንፍናዬ እናገር ዘንድ (በመመካት መናገሬን) ጥቂት ልትታገሡኝ ይገባ ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ፤ (መመካት ሥርዓት እንደሆነ አድርጋችሁ አትያዙብኝ)፤ ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና፤ (መንፈሳዊ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና)፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ (አዋህዳችሁ) ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁና።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፩-፪።

3 comments:

 1. kale hiwot yasemalin kessis

  ReplyDelete
 2. መልአከ ሰላም፤
  ቃለ ሕይወት ያሰማልን። እንዲህ አብራርቶ የሚያስተምር አባት አያሳጣን

  ReplyDelete
 3. Kesis Dejene kale hiwotin yasemalin, Yageliglot zemenuwon yarzimilin betam betam bezu timihirt yagegnenibet new bertulin Abatachin alemachin yetefaw endih yale timihirt selemayak new, tenawon yestiwo betesebwon yetebkilowot.

  ReplyDelete