Tuesday, April 5, 2011

ነገረ ቅዱሳን ክፍል፦ ፲፩

                እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው፤ የሚታየውን እና የማይታየውን፥ የሚያልፈውን እና የማያልፈውን ፈጥሮ የሚገዛው፥ የሚያስተዳድረው፥ በሥርዓት የሚመራውና የሚመግበው ሁሉን ቻይ በመሆኑ ነው። ዘፍ ፩፥፩-፴፮። በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴ፦ በአብርሃም ድንኳን በእንግዳ አምሳል በተገኙ ጊዜ፦ «እንደ ዛሬ ጊዜ ተመልሼ በረድኤት ወደ አንተ በመጣሁ ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤» ብለውት ነበር። ሣራ በድንኳኑ ደጅ ከአብርሃም ኋላ ቆማ ሳለች ይኽንን ነገር ሰማች። አብርሃምና ሣራ የጐልማስነታቸው ወራት አልፎባቸው ፈጽመው አርጅተው ነበር። በሴቶች የሚሆነው ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም፦ «ሲያረጁ አምባ ይዋጁ፤» እንዲሉ፦ «እስከዛሬ ድረስ ገና ቆንጆ ነኝን?» ብላ፥ አንድም «ጌታዬ አርጅቷል እኔ ገና ነኝን?» ብላ፥ አንድም «ጌታዬ አላረጀምን? ብላ» ተጠራጥራ ሳቀች። ሥላሴም፦ አብርሃምን፥ «ሣራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት? እስከ ዛሬ ገና ነኝን?» ብላ፥ አንድም «ጌታዬ አርጅቷል እኔ ገና ነኝን? በእውነትስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅቷል። እነሆ ፥እኔም አርጅቻለሁ ብላለችና። በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?» ብለውታል። ዘፍ ፲፰፥፲። እግዚአብሔር ሣራን በቸርነት፥ በረድኤት ጐበኛት፤ «ልጅ ትወልጃለሽ፤» ብሎ እንደተናገረ አደረገላት። ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ እግዚአብሔር በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ወለደችለት። ዘፍ ፳፩፥፩።

          የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ ከእግዚአብሔር ተልኮ መጥቶ፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር አምላክን በድንግልና ፀንሳ፥ በድንግልና እንደምትወልድ ለእመቤታችን በነገራት ጊዜ፦ «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል። እነሆ ከዘመዶችሽ ወገን የምትሆን አልሳቤጥም  እርስዋ እንኳ በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ፀንሳለች፤ መካን ትባል የነበረችው ከፀነሰች እነሆ፥ ይህ ስድስተኛ ወር ነው። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።» ብሏታል። ሉቃ ፩፥፴፭።

          ነቢዩ ዳንኤል፦ የባቢሎኑን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ሕልም በፈታለት ጊዜ፦ «ልዑልም የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ ፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደበሬም ሣር ትበላለህ፤ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፤ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል። የዛፉንም ጉቶ ተዉት ማለቱ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደሆነ እስክታውቅ ድረስ መንግሥትህ ይቈይልሃል። ንጉሥ ሆይ! ስለዚህ  ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ በጽድቅና በምጽዋት ትድናለህ፤ በደልህንና ኃጢአትህንም ለድሆች በመራራት እግዚአብሔር ይቅር ይልሃል።» ብሎት ነበር። ዳን ፬፥፳፭-፳፯። ከዐሥራ ሁለት ወር በኋላም ንጉሡ፦ «የባቢሎን ቤተ መንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?» ብሎ በትዕቢት ተናገረ። ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ (ተናግሮ ሳይጨርስ) ድምፅ  ከሰማይ መጣ፦ ነቢዩ ዳንኤል ነግሮት የነበረውን መልሶ ነገረው። በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጉሩም እንደ አንበሳ፥ ጥፍሩም እንደ ንስር ፥እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።

          ከሰባት ዓመት በኋላ ነቢዩ ዳንኤል፦ የናቡከደነፆር ልቡ በጸጋ እንደተመለሰ አውቆ፦ «ሂዳችሁ አምጡት፤» ብሎ ሹማምንቱን ልኳቸዋል። እነርሱም ከዛፍ ሥር ቁሞ አግኝተውት አምጥተውታል። እርሱም፦ «ከእነዚያም ዘመናት በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፤ ለዘላለም የሚኖረውንም አመሰገንሁ፤ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘለዓለም ግዛት ነውና። በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚቃወማት ወይም ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።» በማለት፦ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ እንደሆነና የሚሳነውም ነገር እንደሌለ መስክሯል። ዳን ፬፥፳፰-፴፭።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱ፦ «እንግዲያስ ማን ሊድን ይችላል?» ብለው አድንቀው በጠየቁት ጊዜ፦ «በሰው ዘንድ ይህ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል፤» በማለት መልሶላቸዋል። ማቴ ፲፱፥፳፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር እንደሌለ ሲናገር፦ «እንደወደደም በእርሱ የወሰነውን፥ የፈቃዱን ምሥጢር ገለጠልን። የሚደርስበትንም ጊዜውን ወሰነ፤ በሰማይና በምድር ያለውም ሁሉ ይታደስ ዘንድ ክርስቶስን በሁሉ ላይ አላቀው። እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ አስቀድመን የተወሰን በእርሱ ርስትን ተቀበልን።» ብሏል። ኤፌ ፩፥፱-፲፩።

፪፦ «የሚሳናችሁ ነገር የለም፤» ማቴ ፲፯፥፳።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ለነቢያቱ ለሙሴ ለኤልያስ፥ ለሐዋርያቱ ለጴጥሮስ ፥ለዮሐንስና ለያዕቆብ ክበረ መንግስቱን ገልጦ ከደብረ ታቦር ሲወርድ ሕዝቡን ከእግረ ደብረ ሲጠብቁት አገኛቸው። ያ ሕዘብ፦ የተቀሩትን ደቀመዛሙርት፦ «መምህራችሁ ወዴት ሄደ?» እያሉ ሲያደክሟቸው፥ ሲያዋክቧቸው ቆይተዋል። አንድ ከነገር ያልገባ ሰው፥ ለብቻው ቆይቶ፥ ወደ ጌታ ቀረበና፦ «አቤቱ፥ ልጄን ማርልኝ፤ ክፉ ጋኔን ጨረቃ ስትወጣ (በየወሩ መጀመሪያ) ያሠቃየዋልና፥ ይዞ ይጥለዋልና፤ ብዙ ጊዜም ወደ እሳት ይጥለዋል፤ ወደ ውኃም የሚጥልበት ጊዜ አለ። ወደ ደቀመዛሙርትህም አመጣሁት፤ እነርሱም ማዳን ተሳናቸው።» እያለ ከምልጃ ጋር ሰገደ።

          ከዚህ በኋላ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱን፦ «የማታምን ጠማማ (እንቢተኛ፥ አሉተኛ) ትውልድ እስከመቼ ድረስ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከመቼስ እታገሣችኋለሁ? (ዝም እላችኋለሁ)? አላቸው። ደቀመዛሙርቱ፦ ንጉሥ በሌለበት ከንቲባ መቅጣት እንዲገባው ባለማወቃቸው፦ «አድኑልኝ፤» ቢላቸው፦ «መምህራችን በሌለበት ጊዜ አይቻለንም፤» ብለዋል። ጌታችን፦ «እስከ መቼ ድረስ በዚህ ምድር ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤» ያላቸው ለዚህ ነው። ምክንያቱም፦ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱ፥ ወደ ሰማይ ማረጉ አይቀርምና ነው። «እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ፤» ያለበት ምክንያት ደግሞ፦ «ንጉሥ ባለ ጊዜ ከንቲባ መሥራት መቅጣት እንደማይገባው ባለማወቃቸው፦ «መምህራችን ባለበት እንጂ እርሱ በሌለበት አይሆንልንም፤» በማለታቸው ነው። ይኸውም፦  «እኔ ካለሁማ እኔው እሠራዋለሁ፤» ሲላቸው ነው። እንዳለውም በሽተኛውን «ወደ እኔ አምጡልኝ፤» ብሎ ጋኔኑን ገሠጸውና (ፃዕ መንፈስ እርኲስ አለውና) ከእርሱ እንዲወጣ አደረገው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ዳነ።

          የጌታ ደቀመዛሙርት ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀረቡና፦ «ስለምን እኛ ማውጣት ተሳነን?» አሉት። ጌታችንም፦ «ስለ እምነታችሁ መጉደል ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍንጭ ቅንጣት የሚያህል  እምነት ቢኖራችሁ ይሀን ተራራ ከዚህ ወደዚያ ተነቅለህ ሂድ ብትሉት ይፈልሳል፤ የሚሳናችሁ ነገርም የለም። ይህ ዓይነት ግን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም፤» አላቸው። ማቴ ፲፯፥፲፬-፳፪።

          ሰናፍጭ፦ የፍጹምነት ምሳሌ ናት፤ ሰናፍጭ እንደሌላው የእህል ዘር ነቅ የለባትም፥ ወንጌልም ነቅዕ፣ ኑፋቄ የለባትም፤ ሰናፍጭ ላይዋ ቀይ ውስጧ ነጭ ነው፤ ወንጌልም በላይ ደማችሁን አፍስሱ ትላለች፥ በውስጥ ግን ብሩኅ ተስፋ ያለት ሕግ ናት። አንድም ሰናፍጭ ጣዕሟ ምረሯን (ምረቷን) ያስረሳል፥ ወንጌልም ተስፋዋ መከራዋን ያስረሳል፤ አንድም ሰናፍጭ ቊስለ ሥጋን ታደርቃለች፥ ወንጌልም ቊስለ ነፍስን ታደርቃለች፤ አንድም ሰናፍጭ ደም ትበትናለች፥ ወንጌልም አጋንንትን ፣ መናፍቃንን ትበትናለች፤ አንድም ሰናፍጭ ከምትደቈስበት ተሐዋስያን አይቀርቡም ፥ ወንጌልም ከምትነገርበት (ከምትተረጐምበት፣ ከምትመሠጠርበት) አጋንንት፣ መናፍቃን አይደርሱም ፥ ቢደርሱ ይረታሉ፤ አንድም ሰናፍጭ ከበታችዋ ያሉትን አትክልት ታመነምናለች፥ ወንጌልም በትርጓሜዋ፣ በሚሥጢሯ የመናፍቃንን ጉባዔ ታጠፋለች፥ ትምህርታቸውንም ከንቱ ታደርጋለች፤ ሰናፍጭ አንድ ጊዜ የዘሯት እንደሆነ በየዓመቱ ዝሩኝ አትልም፥ ተያይዛ ስትበቅል ትኖራለች፥ ወንጌልም በመቶ ሃያ ቤተሰብ ተጀምራ እስከ ምጽአት ድረስ ስትነገር ትኖራለች። ሰናፍጭ ስትዘራ ከአዝርዕት ሁሉ ታንሳለች፥ ባደገች ጊዜ ግን ከአዝርዕት ሁሉ ትበልጣለች። ከአዕዋፍ መጥተው ማረፊያ፥ መስፈሪያ እስኪያደርጓት ድረስ ደግ ዕፅ ትባላለች።  ወንጌልም ስትጀመር በትንሹ በመቶ ሃያ ቤተሰብ ነበር፥ በጉባዔ በተነገረች ጊዜ ግን ከሕግጋት ሁሉ ትበልጣለች። ሕዝብም አሕዛብም እስኪያምኑባት ድረስ ደግ ሕግ ሆናለች።

          አምላካችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱን፦ «የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ፤» ማለቱ፥ ጥርጥር የሌለው ፍጹም ሃይማኖት ቢኖራችሁ ሲላቸው ነበር። ተራራ፦ ያለው ደግሞ ስለ ትዕቢቱ ዲያቢሎስን ነው። «የሚሳናችሁ ነገር የለም፤» ማለቱም፦ «ቸግሯችሁ የሚቀር ነገር የለም፤» ሲላቸው ነው። አንድም ተራራውም ቢሆን በሚሰጣቸው ሥልጣን በተአምር የሚነሣላቸው ስለሆነ ነው። ይኸውም ሙሴ ባሕር እንደከፈለው፥ ኢያሱም ፀሐይ እንዳቆመው ዓይነት ማለት ነው።

          ታሪክ፦ በአብርሃም ሶሪያዊ ጊዜ፦ ለሊቀጳጳሱ አንድ አይሁዳዊ ወዳጅ ነበረው፤ ሁለቱም ለንጉሡ ባለሞሎች ነበሩና በየፊናቸው ንጉሡን ለመጠየቅ ሲሄዱ ከዚያ ይገናኛሉ። የሃይማኖት ነገር አንሥተው ሲከራከሩም ሁል ጊዜ ሊቀጳጳሱ አይሁዳዊውን ምላሽ ያሳጣዋል። ከዕለታት በአንድ ቀን አይሁዳዊው ለብቻው ገብቶ በሊቀ ጳጳሱ ላይ ነገር ሠራ። ወደ ንጉሡ ቀርቦ፦ «የእነዚህ የክርስቲያኖች ሃይማኖታቸው ደካማ ነው፤» አለው። ንጉሡ ግን፦ «እንግዲያስ እየተከራከሩ ለምን ምላሽ ያሳጧችኋል፤» አለው። በዚህን ጊዜ አይሁዳዊው፦ «ወንጌላቸው፦ የሰናፍንጭ ቅንጣት ያህል ሃይማኖት ቢኖራችሁ ተራራ ማንሣት ይቻላችኋል ትላለች፤ አድርጉ ቢሏቸው ግን አያደርጉትም፤» አለ። ንጉሡም፦ ሊቀ ጳጳሱን ሲያገኘው ነገሩ እየጠፋው፥ ነገሩን ሲያስታውሰው ደግሞ ሊቀጳጳሱን እያጣው ብዙ ቀናት አለፉ። በኋላ ላይ ግን ሊቀጳጳሱ ባለበት ነገሩ ትዝ አለውና ጠየቀው፥ ሊቀጳጳሱም፦ «እውነት ነው፥ በወንጌል ተጽፏል፤» አለው። ንጉሡም፦ «እንኪያስ የዚህ ሁሉ ክርሰቲያን እምነት ቢደመር ከተራራ ይበልጣልና ሠርተህ አሳየኝ፤» አለው። ሊቀጳጳሱም ንጉሡን፦ «ቀን ስጠኝ ሠርቼ አሳይሃለሁ፤» ቢለው ሦስት ቀን ሰጠው።

          ሊቀ ጳጳሱ ቀጥታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ፥ ከሥዕለ ማርያም ሥር ተንበርክኮ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም አመለከተ። እመቤታችንም፦ «ልጄ፥ እንዲህ ያለው ላንተ አይደረግልህም፥ የሚደረግለት አለ፥ እርሱም ስምዖን አንድ ዓይና ነው፥ ተርታ ሰው መስሎ ከገበያ እንጨት ሲሸጥ ታገኘዋለህ፥ ሂደህ እመቤታችን ነግራኝ ነው ብለህ ንገረው፥ አለበለዚያ በጀ አይልህም፤» አለችው። ቢሄድ እንደነገረችው ሆኖ አገኘው፥ እየፈራም ሂዶ፥ በስተኋላው ልብሱን ቢይዝ፥ «የተሰወረውን ጸጋዬን አወቀብኝ፤» ብሎ ተቆጣው። «በሀገርህ ድኃ አይኖርበትም፤» ብሎ ጮኸበት። በዚህን ጊዜ ሊቀጳጳሱ፦ «እመቤታችን ልካኝ ነው፤» ብሎ በግልጥ ነገረው።

          በዚህ ጊዜ ስምዖን አንድ ዓይና፦ ለሊቀ ጳጳሱ፦ «የእኔን ማንነት አትግለጥብኝ፤ ሂደህ ክርስቲያኖችን ከተራራው ፊት ለፊት፥ አሕዛብን ደግሞ ከተራራው ጀርባ እንዲሆኑ አድርገህ፥ ካህናቱን ልብሰ ተክህኖ አልብሰህ፥ መስቀል ጽንሐ አስይዘህ ቆየኝ፤ አንተ እኔ የምሠራውን ሥራ እያየህ ሥራ፥ ሕዝቡ ደግሞ አንተ የምትሠራውን እያዩ ይሥሩ፤» አለው። ሊቀጳጳሱም ቀድሞ ሂዶ የተባለውን ሁሉ አደረገ። በመጨረሻ፦ አርባ አንደ ኪርያላይሶን አድርሰው ሰግደው ሲነሡ ተራራው ብድግ አለ፥ በተራራው ሥርም በወዲያና በወዲህ ያሉት ተያዩ፥ በዚህ ዓይነት ተራራው እየሰገዱ ሲነሡ ሦስት ጊዜ ብድግ ብሏል። በዚህም፦ «የሚሳናችሁ ነገር የለም፤» የሚለው ቃለ ወንጌል ተፈጽሞላቸው አሕዛብን አሳፍረዋል። የእምነታቸውም ኃይል ጌታ እንደተናገረ ጾምና ጸሎት ነበር። እንግዲህ እኛም እንደተሰጠን ጸጋ መጠን በእምነት ከጸናን፥ እምነታችንን በሥራ ከገለጥን፥ ጾምን ጸሎትን ገንዘብ ካደረግን፥ በሥጋ ከባድ መስሎ የታየን ሁሉ ቀላል ነው።

፪፥፩፦ «አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ፤»

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ረሀብ የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ በመዋሐዱ በማለዳ ወደ ከተማ ሲወጣ ተራበ። በመንገድም አጠገብ የበለስን ዛፍ አይቶ ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም ፍሬ አለገኘባትም፤ «እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይኑርብሽ፤» አላት፤ ያንግዜውንም በለሲቱ ደረቀች። ደቀመዛሙርቱም አይተው፦ «ይህች በለስ እንዴት ወዲያውኑ ደረቀች?» ብለው አደነቁ። ጌታችንም መልሶ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ፥ ባትጠራጠሩም በበለሲቱ እንደተደረገው ብቻ የምታደርጉ አይደለም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይደረግላችኋል። አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።» ብሏቸዋል። ማቴ ፳፩፥፲፰-፳፪።

          ፍሬ አልባ በለስ የተባሉት፥ ሃይማኖት ከምግባር የታጣባቸው እስራኤል ዘሥጋ ናቸው፤ በለሷን እንደመቅረብ ከእነርሱ ተወልዷል፥ በመካከላቸው ተመላልሷል፥ የቃሉን ተምህርት አስተምሯቸዋል፥ የእጁን ተአምራት አሳይቷቸዋል። አንድም ፍሬ አልባ በለስ የተባለች ኦሪት ናት፥ ምክንያቱም ሕይወትን አፍርታ አልተገኘችምና ነው። በለሷ ወዲያው እንደደረቀች ኦሪትም ፈጥና አልፋለች፤ አንድም ፍሬ አልባ የተባለች ኃጢአት ናት፤ ጌታችን ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የበለስ ቅጠሉ ሰፊ እንደሆነ ሁሉ ኃጢአትን ሰፍታ ሰፍና አግኝቷታል። «በአንፃረ በለስ ረገማ ለኃጢአት፤ በበለስ አንፃር ኃጢአትን ረገማት፤» እንዲል፦ «በአንቺ ምክንያት በመጣ ፍዳ የሚያዝ አይኑር፤» አላት። በእርሱ በጌታችን የኃጢአት ሥሯ ደረቀ፥ ቅጠሏ ጠወለገ። በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፥ ቆይቶ ይቆመጥጣል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ያሰኛል፥ በኋላ ግን ይጸጽታል፥ አንድም እንደመምረር ምረረ ገሃነምን ያመጣል። እኛስ ብንጐበኝ የመንፈስን ፍሬ አፍርተን እንገኝ ይሆን? «የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር ፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ምጽዋት፥ ቸርነት፥እምነት፥ ገርነት፥ ንጽሕና ነው።» ገላ ፭፥፳፪።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረ፦ ቅዱሳን በዚህ ዓለም በሃይማኖት ሊሠሩት ያልቻሉት ምንም ነገር የለም። በጾም በጸሎት ተወስነው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተደርጎላቸዋል፥ «የሚሳናችሁ ነገር የለም፤ አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኙታላችሁ፤» የተባለው ተፈጽሞላቸዋል። እንግዲህ ነገረ ቅዱሳንን መጠራጠር በጌታ ተቃራኒ፦ «የሚሳናቸው ነገር አለ፤» ማለት እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል።

፪፥፪፦ «በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን እርሱም ይሠራል፤»

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀመዛሙርቱ አንዱ ፊልጶስ፦ «አብን አሳየንና ይበቃናል፤ (መስማቱ ይበቃናል፥ መስማቱ በማየት ይፈጸምልናል፥ ለናፍቆት፣ ለዕሤት ፣ ለደጅ ጥናት ይሆንልናል)፤» ብሎት ነበር። ጌታችን ግን፦ «ፊልጶስ፥ ይህን ይህል ዘመን አብሬአችሁ ስኖር አታውቀኝምን? (አላወቅኸኝምን)?  እኔን ያየ አብን አየ፤ እንግዲህ እንዴት አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ አንዳለ (ህልዋን እንደሆንን፥ በህልውና፣ በመለኰት፣ በስልጣን፣ በፈቃድ፣ በባህርይ፣ አንድ እንደሆንን) አታምንምን? እኔ የምነግራችሁ ይህ ቃልም ከራሴ (ከራሴ ብቻ አንቅቼ) የተናገርኩት አይደለም፤ በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ ። (በአብ ልብነት የታሰበ ነው)። እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑ። (ይህን ሥራ አምላክ ቢሠራው አንጂ ዕሩቅ ብእሲ አይሠራውም ብላችሁ እመኑ)።» አለው።

          ከዚህ በኋላ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱን፦ «እውነት እውነት እላችኋለ ሁ፤ በእኔ የሚያምን (ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ ሰው የሆነ የባሕርይ አምላክ ነው፥ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባህርይ፣ በህልውና፣ በሥልጣን በፈቃድ፣ በመለኰት አንድ ነው፥ ብሎ የሚያምን) እኔ የምሠራውን ሥራ (ያደረግኋቸውን ተአምራት) እርሱም ይሠራል፤» ብሏቸዋል። ዮሐ ፲፬፥፰-፲፪። ቅዱሳን ሐዋርያትን በመረጣቸውም ጊዜ፦ « ሄዳችሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች እያላችሁ አስተምሩ። ድውያንን ፈውሱ፤ ሙታንንም አንሡ፤ ለምጻሞችንም አንጹ፤ አጋንንትንም አውጡ፤ ያለ ዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ፤» ብሏቸው ነበር። ማቴ ፲፥፮-፰። ከትንሣኤው በኋላም፦ «ይህችም ምልክት በስሜ የሚያምኑትን ትከተላቸዋለች፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋም ( ባላደጉበት፥ ባልተማሩት፥ ተናጋሪም አድማጭም ሕዝብ ባለው ቋንቋ) ይናገራሉ። እባቦችንም በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚጎዳቸውም ነገር የለም፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡም የሚጎዳቸው የለም፤ በድውያን ላይም እጃቸውን ይጭናሉ፤ ድውያንም ይፈወሳሉ።» በማለት ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮፥፲፮-፲፰።

፪፥፫፦ «ከዚህም የሚበልጥ ይሠራል፤»

 ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤» ካለ በኋላ፦ «ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል፤» ብሏል። ይህም፦ ፍጡር ከፈጣሪው በላይ የሚሠራ ሆኖ አይደለም። እርሱ፦ ወንጌልን ያስተማረው፥ ተአምራትን ያደረገው ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ነው፥ እነርሱ ደግሞ ብዙ ዘመን ስለሚያስተምሩ ብዙ ተአምራትንም ስለሚያደርጉ ነው። ዕውራንን በማብራት፥ አንካሳዎችን በማርታት፥ ድውያንን በመፈወስ፥ ሙታንን በማስነሣት፦ በቊጥር የበዙ ተአምራትን ስለሚያደርጉ ነው። ወንጌልንም በማስተማር ረገድ፥ እርሱ መቶ ሃያውን ቤተሰብ አስተምሯል ፥ እነርሱ ደግሞ በቊጥር ከዚህ የበዙ ደቀመዛሙርትን ስለሚያስተምሩ ነው። «በሐዋርያት እጅም በሕዝብ ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፤ በቤተ መቅደስም በሰሎሞን መመላለሻ በአንድነት ነበሩ። ሕዝቡም እጅግ ያከብሩአቸው ነበረ። ከሌሎችም ይቀርባቸው ዘንድ አንድ ስንኳን የሚደፍር አልነበረም። በጌታችንም የሚያምኑ ብዙዎች ይጨመሩ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙዎች ነበሩ።» ይላል። የሐዋ ፭፥፲፪-፲፫።

፫፦ ጌታችን ያደረጋቸው ተአምራት፤

ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው አያሌ ተአምራትን አድርጓል። እነዚህንም በቃል ተናግረዋቸው፥ በፊደል ቀርጸዋቸው የሚወስኗቸው አይደሉም። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ሁሉ ባልበቃቸውም ይመስለኛል፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፩፥፳፭።

፫፥፩፦ ማየት የተሳናቸውን መፈወሱ፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በዓይነ ሥጋ ማየት የተሳናቸውን በተአምራት፥ ዓይነ ልቡና ቸው የታወረባቸውን ደግሞ በትምህርት አብርቶላቸዋል። ሁለት ዕውራን፥ «የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ራራልን፤» ብለው እየጮኹ ተከተሉት። ጌታችንም ለእነርሱ ርቆ መሄድ አይሆንላቸውም በማለት ከቤት ገብቶ ቆይቷቸዋል። ዓይነ ስዉራኑም፦ ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ፥ «ይህን ማድረግ እንዲቻለኝ ታምናላችሁን?» አላቸው፤ እነርሱም፦ «አዎን ጌታ ሆይ !» አሉት። «እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ፤» ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሳቸው። ያንጊዜም ዓይኖቻቸው ተገለጡ፤ ማቴ ፱፥፳፯-፴። ጌታችን፦ «አዎን እናምናለን፤» እንደሚሉት እያወቀ «ታምናላችሁን?» ብሎ የጠየቃቸው አላዋቂ የነበረን ሥጋ መልበሱን ለማጠየቅ ነው። አንድም በዓይነ ስዉራኑ ልብ ያለ እምነት በአንደበታቸው እንዲገለጥ ነው።

           ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ከኢያሪኮ በወጣ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ብዙ ሰውም ነበረ፤ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስም በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደሆነም ሰምቶ፥ «የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ፤» ብሎ ጮኸ ። ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን ድምፁን ከፍ አደረገና፥ «የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ» አለ። ጌታችን ኢየሱስም ቆመና፥ «ጥሩት» አለ፤ እነርሱም ዓይነ ስውሩን ጠሩት፤ «በርታና ተነሥ፥ መምህር ይጠራሃል፤» አሉት። እርሱም ተነሥቶ፥ አዳፋውን ልብሱን ትቶ፥ ደኅናውን ለብሶ ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጣ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ «ምን ላደርግልህ ትሻለህ?» አለው፤ ዕውሩም፥ «መምህር ሆይ፥ እንዳይ ነው፤» አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ «ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ» አለው፤ ወዲያውም አየ፤ በመንገድም ተከተለው። ማር ፲፥፵፮-፶፪።

           ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ አይሁድን፦ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ፤» ብሏቸው ስለነበር፥ ያንን ቃሉን በሥራው ለማስረዳት ከዚያ አልፎ ሲሄድ ዓይነ ስዉር ሆኖ የተወለደውን ሰው አየ። ደቀመዛሙርቱም፦ «ኃጥአን ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ ተለዩ፤» የሚለውን ይዘው፦ «መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዓይነ ስዉር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ነውን?» ብለው ጠየቁት። «ብዙ ሕፃናት በወላጆቻቸው በደል ይሞታሉ፤» የሚለውንም ይዘው፦ «ወይስ በወላጆቹ ኃጢአት ነውን?» በማለት ጣምራ ጥያቄ ጠይቀውታል። ጌታችን ኢየሱስም፦ «የእግዚአብሔር ሥራ (አምጻኤ ዓለማትነቱ፥ ከሃሊነቱ፥ ጌትነቱ፥ ተአምራቱ፥ መጋቢነቱ) እንዲገለጥበት ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፤ ወላጆቹም አልበደሉም። ነገር ግን ቀን ሳለ (ፀሐይ ዕድሜዬ በመስቀል ሞት ሳይጠልቅ) የላከኝን ሥራ፦ (የአባቴን የፈጣሪነት ሥራ ሠርቼ እናንተን ማሳመን ይገባኛል)፤ ማንም ሥራ ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት (የመስቀል ሞት) ትመጣለችና። በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን (የሰው ዕውቀቱ) እኔ ነኝ።» አላቸው። ይህንንም ብሎ በምድር ላይ ምራቁን እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ የዓይነ ስዉሩን ዓይኖች ቀባው። «ሂድና በሰሊሆም ጸበል ተጠመቅ፤» አለው። ትርጓሜውም የተላከ ማለት ነው፤ ሄዶም ተጠምቆ እያየ ተመለሰ። ዮሐ ፱፥፩-፯።

፫፥፪፦ ሕሙማንን መፈወሱ፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ሁለቱን ዓይነ ስዉራን፦ «እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ፤» ብሎ ከፈወሳቸው በኋላ፦ ጋኔን ያደረበትን ድዳ ወደ እርሱ አመጡ። መናገርም መስማትም አይችልም ነበር። አንድም ድዳ ደንቆሮም የሆነ ጋኔን አድሮበት ነበር። ጋኔኑ «ድዳ» የተባለው ጥንት አመስግን ሲባል ላለማመስገን ዝም በማለቱ ነው፥ «ደንቆሮ» የተባለው ደግሞ ትእዛዘ እግዚአብሔርን ባለመስማቱ ነው። ይህ ሰው ያደረበት ጋኔን በወጣ ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ ተናግሯል፥ ጆሮውም አድምጧል። ማቴ ፱፥፴፪ ፣ ፲፪፥፳፪። ጌታችን፦ አንካሶችንም ፈውሶ እንደ እንቦሳ እንዲዘሉ አድርጓል። ማቴ ፳፩፥፲፬። እጃቸው የሰለለባቸውንም ፈውሷል። ማቴ ፲፪፥፲። ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ አንካሶች ሲራመዱ፥ ዓይነ ስዉራን ሲያዩ አይተው፥ እስኪደነቁ ድረስ፥ የእስራኤልን አምላክ ያመሰግኑት ነበር።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የከነዓናዊቱን ሴት ልጅም ባለበት ሆኖ በቃሉ ብቻ ፈውሷታል። ይህች ሴት፦ «አቤቱ የዳዊት ልጅ እዘንልኝ፤ ልጄን ክፉ ጋኔን ይዞ ያሠቃያታልና፤» ብላ አብዝታ በጮኸች ጊዜ እምነቷ፥ ትዕግሥቷ ይገለጥ ዘንድ ዝም አላት። ጩኸቷን ባለማቋረጧም፦ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ «ይህችን ሴት አሰናብታት፤ እኛን እየተከተለች ትጮሃለችና፤» ብለው ማለዱት። መማለዳቸውም፦ ትምህርት ታስፈታለች፥ አንድም ወይ ተናግረው አያስፈጽሙ፤ ወይ አያሰናብቱ ትላለች ብለው፥ አንድም ብታሳዝናቸው ነው። እርሱም መልሶ፦ «ከእስራኤል ቤት ወደ ጠፉ በጎች (ትምህርት አብነት አጥተው ወደ ተጐዱት) ብቻ እንጂ አልተላክሁም፤» አላቸው። እንዲህም ያለው የተነገረውን ትንቢት፥ የተቈጠረውን ሱባዔ የሚያውቁት እነርሱ በመሆናቸው ነው። ሴቲቱም፦ ቀርባ፦ «አቤቱ ጌታዬ እርዳኝ፤» ብላ ሰገደችለት። እርሱም መልሶ፦ «የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መስጠት መልካም አይደለም፤» አላት። እንዲህም ማለቱ ይህች ሴት፦ «ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።» ከተባለው ወገን በመሆኗ ነው። ትርጉሙም የተመረቀው የሴም በረከት ለተረገመው ለከነዓን አይሰጥም ማለት ነው። ሴቲቱም በፍጹም እምነትና ትህትና፦ «አዎን ጌታዬ ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤ (ለእስራኤል ደጋጉን ተአምራት ብታደርግላቸው ጥቃቅኑን ተአምራት አታደርግልኝምን)? አለችው። ከዚህም በኋላ ጌታችን መልሶ፦ «አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ፤» አላት፤ ከዚህችም ሰዓት ጀምሮ ልጅዋ ዳነች። ማቴ ፲፭፥፳፩-፳፰። ጌታችን ይህችን ሴት ሦስት ነገር አግኝቶባታል። እነርሱም፦ እምነት፥ ትህትና እና ጥበብ ናቸው፤ ልጄን ያድንልኛል ብላ መምጣቷ እምነት ነው፥ በውሻ ሲመስላት «አዎን ውሻ ነኝ፤» ማለቷ ትሕትና ነው፥ «የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም፤» ብሎ በጥበብ ሲናገር፥ እርሷም፦ «ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤» ብላ በጥበብ ተናግራለች።
         
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ለሕዝቡ ቃሉን ነግሮ በፈጸመ ጊዜ ወደ ቅፍርናሆም ገባ።አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ አገልጋዩም ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር፤ እርሱም በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነበር። የጌታችን የኢየሱስንም ነገረ በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ አገልጋዩን እንዲያድንለት ይማልዱት ዘንደ የአይሁድን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ላከ። ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስም መጥተው ማለዱት፤ «ፈጥነህ ውረድ፣ ይህን ልታደርግለት ይገባዋልና። እርሱ ወገናችንን ይወዳልና፤ ምኲራባችንንም ሠርቶልናልና፤» ብለው አጥብቀው ለመኑት። ጌታችን ኢየሱስም ከእነርሱ (ከአማላጆቹ) ጋር ሄዶ ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ፥ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን፦ «አቤቱ አትድከም፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና። እኔም እኮ ገዢ ሰው ነኝ፤ ወታደሮችም አሉኝ፤ አንዱን ሂድ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ና ብለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም እንዲህ አድርግ ብለው ያደርጋል ብሏል፥ ብላችሁ ንገሩልኝ፤» ብሎ ወደ እርሱ ላካቸው። እነርሱም ይኽንን ወስደው ነገሩት። ጌታችን ኢየሱስም ይህን ከእርሱ በሰማ ጊዜ አደነቀው፤ ዘወር ብሎም ይከተሉት ለነበረው ሕዝብ፥ «እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው ሰው አላገኘሁም፤» አላቸው። የተላኩትም (አማላጆቹ) በተመለሱ ጊዜ ብላቴናውን ድኖ አገኙት።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ይህንንም ሰው ሦስት ነገሮች አግኝቶበታል። እነርሱም፦ እምነት፥ ትሕትና እና ጥበብ ናቸው። የእነርሱን ልመና ተቀብሎ አገልጋዬን ያድንልኛል፥ ብሎ አማላጆችን መላኩ እምነት ነው፥ «ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና፤ እኔም ወደ አንተ ልመጣ አይገባኝም፤» ማለቱ ትሕትና ነው፥ «እኔም እኮ ገዢ ሰው ነኝ፤ ወታደሮችም አሉኝ፤ አንዱን ሂድ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ና ብለው ይመጣል፤» ማለቱ ጥበብ ነው።

          ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ የመቶ አለቃውን ታሪክ የጻፈው «አቤቱ፥ ልጄ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተጨነቀ በቤት ተኝቶአል፤» ብሎ ራሱ ቀርቦ ተናገረ፥ ብሎ ነው። ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ የጻፈው አስቀድሞ የአይሁድ ረበናትን፥ በኋላም ወዳጆቹን አማላጅ አድርጎ ልኳል በማለት ነው። ንባቡ የሚጣላ ይመስላል፥ ነገር ግን ትርጓሜው ያስታርቃቸዋል። ቅዱስ ማቴዎስ እንደተናገረው ራሱ ሄዶ ቢናገር የከነዓናዊቱን ሴት ጩኸት ሰምቶ ዝም እንዳለ እርሱንም ዝም ብሎታል። በዚህን ጊዜ «እኔ የበቃሁ ባልሆን ነው፤» ብሎ ወደ ቤቱ ተመልሶ፥ የአይሁድ ሽማግሌዎችን አማላጅ አድርጎ ልኳል። ሁለቱም ታሪክ የተፈጸመ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ባወቀ ወንጌላውያኑ ተከፋፍለው ጽፈውታል። ማቴ ፰፥፩-፲፣ ሉቃ ፯፥፩-፲።

ይቀጥላል . . .

7 comments:

 1. እግዚሐብሔር ይስጥልን ይህን ጽሁፍ ለማያገኙት ሰዎች ፎቶ ኮፒ እያደረግን እያሰራጨን ነው ስለዚህ ትምህርትዎን አያቋርጡብን እንላለን። እግዚሀብሔር የአገልግሎት ጊዜዎን ይባርክልዎት
  ላሜዳ ከአ.አ

  ReplyDelete
 2. EGIZIABHER YISTILI !AMLAK YIBARKOT, YEEMBETACHI YEKIDUSA MILIJA AYILEYOUT.YAGELIGILOT ZEMEOU YIBARK.YIHI EDAEB YEFEQEDE EGIZIABHER KIBIR YIGBAWU,
  KEEP THE BLESSED WORK!!

  ReplyDelete
 3. kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 4. kesis degene egzer yirdawo yerson sbket s'sema adgeyalehu...bezih melku demo tshufon mag'gnet mechale yasdestal egzer yabertawo amen.......

  ReplyDelete
 5. Kale Hiwoten yasemalen yeagelgelot zemenon yarzemelen

  ReplyDelete
 6. kale hiwoten yasemalen, betena yetebekelen

  ReplyDelete
 7. Kale Hiwoten yasemalen yeagelgelot zemenon yarzemelen

  ReplyDelete