Monday, March 28, 2011

፩ «ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም፤» ማቴ ፬፥፬

           ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕደ ዮሐንስ፥ በፈለገ ዮርዳኖስ እንደተጠመቀ፥ ልዋል ልደር ሳይል፥ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዷል። በዚያም ከቆመ ሳያርፍ፥ ከዘረጋ ሳያጥፍ፥ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾመ። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፦ «መንፈስ ጌታችን ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፤» ብሏል። ይህም፦ መንፈስ ቅዱስ ሰማዕታትን አነሣሥቶ ወደ ደም፥ ጻድቃንን አነሣሥቶ ወደ ገዳም እንደሚወስዳቸው አይደለም። ወንጌላዊው፦ መንፈስ፦ ያለው ፈቃዱን ነው። ምክንያቱም ከአብ ጋር በፈቃድ አንድ እንደሆኑ ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር በፈቃድ አንድ ናቸውና ነው።
          ጌታችን፦ ወደ ገዳም (ወደ በረሀ) የሄደው ለወጣንያንም ለፍጹማንም አብነት ለመሆን ነው። በገዳም፦ ለወጣንያን ፆር ይቀልላቸዋል ፥ ለፍጹማን ደግሞ ይከብድባቸዋልና ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ተክልና ውኃ ከማይገኝበት በረሀ ሆኖ የጾመው፦ መብል ለኃጣውእ መሠረት እንደሆነ ፥ ጾም ለምግባር ለትሩፋት መሠረት፥ ዲያቢሎስንም ድል ለመንሣት ኃይል እንደሆነ ለማሳየት ነው። ቅዱስ ያሬድ፦ ጾምን፦ «እማ ለጸሎት፥ ወእኅታ ለአርምሞ፥ ወነቅዓ ለአንብዕ፥ ወጥንተ ኲሉ ገድል ሠናይት፤ ለጸሎት እናቷ፥ ለዝምታ እኅቷ፥ ለዕንባ ምንጯ፥ ለመልካም ገድል ሁሉ ጥንቷ (መሠረቷ) ናት፤» ብሏል።
          ጌታችን፦ ከጾሙ በላ ተርቧል፤ መራቡም፦ የፈቃድ ረሀብ እንጂ እንደ እኛ የግድ ረሀብ አይደለም፤ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነ አምላክ፥ ረሀብ የሚስማማውን የሥጋ ባሕርይ እንደተዋሐደ ለማጠየቅ ተረበ። ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት ስለሌለም አምላካችን ተራበ እንላለን።
፩፥፩ «ፈታኝ ቀረበ፤»
          ፈታኝ የተባለው ዲያቢሎስ ነው፥ ለመቅረብም ምክንያት ይፈልጋል፤ ጌታችንን ተራብኩ ሲል ሰምቶት፥ አንድም ፍሬ ያለው ተክል ሲፈልግ አይቶት፥ አንድም መልኩን አጠውልጎ ታይቶት፥ ይህን ምክንያት አድርጎ ሊፈትነው ቀርቧል። አመጣጡም፦ በቀዳዳ ስልቻ ሁለት ትኲስ ዳቦ የያዘ ገበሬ መስሎ፥ በሌላ በኲል ደግሞ ሁለት ድንጋዮችን ይዞ ነው። ዓላማውም፦ «እነዚህን ሁለት ድንጋዮች ዳቦ አድርጋቸውና አንዱ ለእኔ፥ አንዱ ለአንተ ይሆናል፥ እለዋለሁ፤ እርሱም ድንጋዩን ዳቦ ከማድረግ በስልቻህ የያዝከውን ትኲስ ዳቦ ለምን አንበላም ይለኛል፤ በዚህን ጊዜ፦ አዳምን በመብል ምክንያት ድል እንደነሣሁት እርሱንም በመብል ምክንያት ድል እነሣዋለሁ፤» ብሎ ነው።
          ዲያብሎስ፦ በዮርዳኖስ፥ አብ ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤» ሲለው ሰምቷል። ይኽንንም ይዞ፦ «እመሰ ወልደ እግዚአብሔር አንተ፥ በል ፥ ከመ እላ አዕባን ኅብስተ ይኩና፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ፤» ብሎታል። እንዲህ ማለቱ፦ «ቢያደርገው የሰይጣን ታዛዥ ብዬ ዕዳ አደርግበታለሁ፥ ባያደርገው ደካማ አሰኘዋለሁ፤ አንድም፦ ቢያደርገው ሌላ ፈተና እፈልግለታለሁ፥ ባያደርገው ድካሙን አይቼ እቀርባለሁ፤» ብሎ ነው።
          ዲያቢሎስ፦ ጌታን፦ «ድንጋዩን ዳቦ አድርግ፤» ያለው በዮሴፍ ልማድ ነው። የዮሴፍ ወንድሞች፦ የአባታቸውን የያዕቆብን በጎች ይዘው ወደ ሴኬም ጎዳና ሄደው ነበር። ያዕቆብም አብልጦ የሚወደውን ልጁን ዮሴፍን ስንቅ እንዲያደርስላቸው ወደ ወንድሞቹ ላከው። «ወንድሞችህ ፥ በጎቻቸውም ደኅና እንደሆኑ ሂደህ አይተህ ንገረኝ፤» ብሎ የስንቊን አቅማዳ (ስልቻ) አስይዞ ከኬብሮን ቈላ ላከው፤ ዮሴፍም ከኬብሮን ቈላ ተነሥቶ ወንድሞቹ ከአሉበት ደረሰ። በዚያም ወደ ወንድሞቹ የሚሄድበት ጎዳና ጠፍቶት ሲዞር፥ ሲባክን፥ በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ፥ መልአከ እግዚአብሔር በአምሳለ ብእሲ (በሰው አምሳል) ታይቶ ተነጋግሮታል። «ወንድሜ ማንን ትፈልጋለህ?» ብሎም ጠይቆታል፤ እርሱም፦ «ወንድሞቼ በጎች አሰማርተው የሚጠብቁበት ቦታ የት ነው? ወንድሜ እስኪ ንገረኝ?» አለው።
          ዮሴፍ ወንድሞቹን ለማግኘት በምድረ በዳ በሚቅበዘበዝበት ወቅት የያዘው ስንቅ አልቆበት እጅግ ተቸግሮ ነበር። ከወንድሞቹ ስንቅ እንዳይበላ፥ አባቱ አድርስ አለው እንጂ ከቸገረህ ብላ ብሎ አላዘዘውም። ረሀብ ጸንቶበት ሳለም፦ መልአከ እግዚአብሔር፦ «የአባትህን ፈጣሪ ድንጋዩን ዳቦ አድርግልኝ አትለውምን?» ብሎታል። ዮሴፍም መልአኩ እንደነገረው ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት ድንጋዩ ዳቦ ሆኖለት ተመግቧል። ዘፍ ፴፯፥፲፪-፲፯። እንግዲህ ዲያቢሎስ፦ «ድንጋዩን ዳቦ አድርግ፤» ያለው «ጥንት ለዮሴፍ የተገለጥኩለት የእግዚአብሔር መልአክ ነኝ፤» ለማለት ነው። ጌታ ግን፦ «ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፎአል፤» በማለት ከመጽሐፍ ጠቅሶ አሳፍሮታል። ጌታ እንደተናገረው፦ በኦሪት ዘዳግም ላይ፦ «አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ። ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፤ አንተም ያላወቅኸውን፥ አባቶችህም ያላወቁትን መና መገበህ። የለበስኸው ልብስ አላረጀም፤ እግርህም አልነቃም፤ እነሆ አርባ ዓመት ሆነ፤ ሰውም ልጁን እንደሚገሥጽ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን እንዲገሥጽ በልብህ ዕወቅ።» የሚል ተጽፏል። ዘዳ ፰፥፪-፭።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኦሪት ያናገረውን ቃል ደግሞ የተናገረው፥ ቃለ እግዚአብሔር (ሕጉን ማክበር፥ ትእዛዙን መጠበቅ) ምግበ ሕይወት መሆኑን ለመግለጥ ነው። ረሀብ ማለት ይኸንን ማጣት ነውና፤ ይኸንንም በተመለከተ፦ ነቢዩ አሞጽ፦ «እነሆ በምድር ላይ ራብን የምሰድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፤ አያገኙትምም። » በማለት ተናግሯል። አሞ ፰፥፲፮-፲፪።
          «ይህን ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን አዘዝ፤» የሚለው ኃይለ ቃል ምሥጢራዊ የሆነ መልእክትም አለው። ይኸውም፦ ዲያብሎስን፦ «በጾም ብዛት እንደ ድንጋይ ፈዞ ያለውን ይህን ሰውነትህን፦ ኅብስተ ሕይወት፥ ኅብስተ መድኃኒት ይሁን ብለህ እዘዝ፤» ሲያሰኘው ነው። ጌታም፦ «ሰው የሚድነው በእሩቅ ብእሲ (ሰው በቻ በሆነ) ሥጋ እንዳይደለ ተጽፏል፥ አካላዊ ቃል በተዋሐደው ሥጋ ነው እንጂ፤» ብሎታል።
፩፥፪፦ ለምን አርባ ቀን ጾመ? (አርባ ቊጥር ለምን ተመረጠ?)
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት የጾመው የአበውን ሥርዓተ ጾም ሲጠብቅ ነው። አባቶቹ ነቢያት አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾመዋል። በዚያ ልክ እንዲጾሙ ያደረጋቸውም እርሱ ነው። ጌታችን ከዚያ አትርፎ ቢጾም፦ «አተረፈ፤» ብለው፥ ቢያጎድል ደግሞ፦ «አጎደለ፤» ብለው አይሁድ ደገኛይቱን ሕግ ወንጌልን ከመቀበል በተከለከሉ ነበር።
          ፩ኛ፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ በአርባ ዘመኑ ለዕብራዊው ረድቶ ግብጻዊውን ገድሎ በአሸዋ ቀብሮታል። ሙሴ የኢየሱስ ክርስቶስ፥ ዕብራዊው የአዳም፥ ግብጻዊው የዲያቢሎስ፥ አሸዋ ደግሞ የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ዘጸ ፪ ፲፪፤ ጌታም አርባ ቀን ጾሞ ዲያቢሎስን ድል ነሥቶታል፤ አንድም በመስቀል፦ ተሰቅሎ ፈጽሞ አሸንፎታል። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ፤ . . . ጥልን በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር (ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር ፥ ከአብ የባሕርይ ልጅ ከራሱ ጋር፥ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር) ያስታርቅ ዘንድ ነው፤» ብሏል። ኤፌ ፪፥፲፬። ሐዋርያው ጥል ያለው፦ በግብሩ ዲያብሎስን ነው። ምክንያቱም ሰውን እና እግዚአብሔርን ያጣላ እርሱ ነውና።
          ፪ኛ፦ ዳግመኛም የነቢያት አለቃ ሙሴ፦ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጹሞ ሕገ ኦሪትን ሠርቷል፤  «እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ፤» ይላል። ዘጸ ፴፬፥፳፯። ጌታም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ ሕገ ወንጌልን ሠርቷል።
          ፫ኛ፦ ሦስተኛም የነቢያት አለቃ ሙሴ፦ በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ አሥራ ሁለት ሰዎችን መርጦ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ወደ ከነዓን ልኳቸዋል። እነርሱም በዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በስለላ ከቆዩ በ ከምድሪቱ በረከት የስንዴዋን ዛላ የወይኗን ዘለላ ይዘው ተመልሰዋል። ጌታም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት የጾመ አካሉን (ስንዴ ሥጋውንና ወይን ደሙን) ምግበ ነፍስ አድርጎ ሰጥቶናል። ዘኁ፲፫፥፳፭።
          ፦ እስራኤል ዘሥጋ በገዳም አርባ ዘመን ኑረው ምድረ ርስት ገብተዋል፤ እናንተም ጾመ አርባን ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ሲለን ነው። ዘኁ ፲፬፥፴፫።
          ፦ ነቢዩ ኤልያስ፦ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ እስከ እግዚአብሔር ተራራ ደርሷል፤ በኋላም በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ አርጓል። «የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፦ የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው። ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ  እግዚአብሔር ተራራ  እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ፤» ይላል። ፩ኛ ነገ ፲፱፥፯። ፪ኛ ነገ ፪፥፲፩። እናንተ፦ ጾመ አርባን ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ሲለን ነው።
          ፮ኛ፦ ነቢዩ ሕዝቅኤል፦ በግራ ጎኑ አርባ ቀን ተኝቶ ስድስት መቶ ሙታን አስነሥቷል። ይኽንንም ያደረገው እግዚአብሔር ፦ «አንተም በግራ ጎንህ ተኛ፤ በምትተኛበት ቀን ቊጥር የእሥራኤልን  ቤት ኃጢአት አኑርባት፤ ኃጢአታ ቸውንም ትሸከማለህ። እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቊጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ የእሥራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፤ እነዚህንም በፈጸም ጊዜ በቀኝ ጎንህ ትተኛለህ፤ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት አርባ ቀን ትሸከማለህ፤ አንዱን ቀን አንድ ዓመት አደረግሁልህ።» ስላለው ነው። ሕዝ ፬፥፬-፭። እናንተም ጾመ አርባን ብትጾሙ ትንሣኤ ዘለክብር ትነሣላችሁ ሲለን ነው።
          ፯ኛ፦ ካህኑ  ዕዝራ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ከምግብ ተከልክሎ መጻሕፍትን አጽፏል። እነዚያ ቀን ሲጽፉ እየዋሉ ማታ ይመገባሉ፤ እርሱ ግን ቀን ሲያጽፈው የሚውለውን ሌሊት ሲያስበው ያድር ነበር። እናንተም ጾመ አርባን ብትጾሙ ምሥጢረ መጻሕፍት ይገለጥላችኋል ሲለን ነው።
          ፰ኛ፦ ዕባብ አካሉ ያረጀበት እንደሆነ አርባ ቀን ከምግብ ተከልክሎ ይሰነብታል። ከዚህ በኋላ በተበሳ እንጨት ወይም በድንጋይና ድንጋይ መካከል አልፎ ሲሄድ ተገፎ ይወድቅለትና ይታደሳል። እናንተም ጾመ አርባን ብትጾሙ ነፍሳችሁ ትታደሳለች ሲለን ነው።
          ፱ኛ፦ አዳም የጸጋ ልጅነትን አግኝቶ ወደ ገነት የገባው በአርባ ቀኑ ነው። «በተፈጠረበትም ምድር ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ያበጃትና ይጠብቃት ዘንድ ወደ ኤዶም ገነት አስገባው። ሚስቱም በሰማንያኛው ቀን አስገባናት።» ይላል። ኲፋሌ ፬፥፱። እንግዲህ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀን አርባ ሌሊት የጾመው፦ የዕፀ በለስን ፍሬ አልጾም ብሎ በአርባ ቀኑ የተሰጠውን ልጅነት ላስወሰደው ለአዳም እርሱ በበደለ ሊክስለት ነው።
          እኛ ብንጾም፦ ክብረ ሥጋ፥ ክብረ ነፍስ፥ ጽድቅ ይሆንልናል ብለን ነው። እርሱ ግን እከብር አይል ክቡር ፥ እጸድቅ አይል ድቅ ሲሆን አብነት ሊሆነን ጾሞ አሳየን። ምሳሌነቱም ሥጋ ለባሽ ደካማ ብትሆኑም በጾምና በጸሎት ብዛት ባላጋራችሁን ታሸንፉታላችሁ፥ እንደ ትቢያ ትበትኑታላችሁ ሲለን ነው። ከምሳሌነቱም ሌላ ሠርቶ በማሳየት ጾማችንን ሁሉ ባርኮልናል፣ ቀድሶልናል። በመሆኑም የአዲስ ኪዳን ጾም በኢየሱስ ክርስቶስ የተባረከና የተቀደሰ ነው። ሰይጣን፦ «የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ ለምን ትራባለህ? ይህን ድንጋይ ዳቦ  አድርገህ ብላ፤» ብሎ ጌታን እንደፈተነው፥ «የጌታ ልጆች ከሆናችሁ ብሉ፤» እያለ ዓለምን ከጾም እየለየው ነው። በዚህም የሚሸነፍበትን መሣሪያ እያስጣላቸው ነው። እኛ ግን፦  «ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም፤» ብለን እንቃወመው። «ዲያቢሎስ ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸል።» ያዕ ፬፥፯።
፪፦ «መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያደርሰንም»
          የሃይማኖት ዓላማው ወደ እግዚአብሔር ቅረብ ፥ ከእርሱ ዘንድ መድረስ ነው። ለዚህም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ያስፈልጋል። ያን ጊዜ ተግባረ ሥጋን ይሆን ተግባረ ነፍስን ማስቀደም እንችላለን። እነዚህም፦ አሥራት በኲራት ፥ ጾም ጸሎት ፥ ስግደት ምጽዋት ናቸው። ጠቅለል ባለ አነጋገርም፦ ሕጉን ማክበር ፥ ትእዛዙን መጠበቅ ነው። ነገር ግን ለፈቃደ ሥጋ ተገዝተን፦ «ሆዴ ይላ ፥ ደረቴ ይቅላ፤» የምን ከሆነ፥ ኃጢአት ይሰለጥንብናል። ኃጢአት ደግሞ የእግዚአብሔር ፊቱን ይሰውርብናል፥ በደልም ከእግዚአብሔር አንድነት ይለየናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያደርሰንም፤ (በእግዚአብሔር ንድ ግዳጅን አያስፈጽምልንም፤» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፰። ስለዚህ፦ መብል መጠጥ ወደ እግዚአብሔር የማያቀርብ ከሆነ፥ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ጾምና ጸሎት መሆኑን ማመን ያስፈጋል።
፫፦ «ብንበላም አይረባንም፤ ባንበላም አይጎዳንም፤»
          ብዙ ሰዎች፦ ጾምን ሽረው በመብላታቸው ብዙ ያተረፉ ይመስላቸዋል። ዓላማ ብለው ጾምን ሳይሆን መብል መጠጥን ይሰብካሉ። «ለምን አትጾሙም?» ተብለው መጠየቅ ሲገባቸው፥ «ለምን ትጾማላችሁ?» ብለው ይጠይቃሉ። ይኽንንም ነገራቸውን በነጠላ ጥቅስ መንፈሳዊ ካባ ለማልበስ ስለሚጥሩም ለራሳቸውም  ሆነ ለሌላው እንቅፋት ይሆናሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግን፦ «ብንበላ አይረባንም ፥ አይጠቅመንም፤» በማለት በግልጥ ተናግሯል። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፰ ። በመሆኑም የማይረባውን የማይጠቅመውን መተው ነው።
          በሌላ በኲል ደግሞ፦ ባለመብላታችን (በመጾማችን) የቀረብን፥ የጎደለብን፥ የተጎዳን የሚመስለን ሰዎች ብዙዎች ነን። ምክንያቱም ሥጋ ለባሾች በመሆናችን የለበስናት ሥጋ ለፈቃደ ነፍስ ላለመገዛት እስከመጨረሻው ትታገለናለች። ቀረብኝ፥ ጎደለብኝ፥ ተጐዳሁ፥ ታመምኩ፥ ተራብኩ፥ ከሳሁ፥ ጠቆርኩ፦ እያለች የማያቋርጥ አቤቱታ ታቀርባለች፥ ተስፋ አትቆርጥም። እንዲያውም በፍስክ ጊዜ እስከ አኲለ ቀን የማይርበን ሰዎች ጾም ወቅት ሲሆን ከአልጋ ሳንነሣ በጧቱ ይርበናል። አንዳንዶች ደግሞ የሚታያቸው የኃጢአታቸው መብዛት ሳይሆን፥ እንደ ጉዳት ስለሚቆጥሩት «የጾሙ መብዛት» ነው። በመሆኑም በህልማቸውም በውናቸውም የሚታያቸው «የበዛው ጾም» ሲቀነስ ነው፥ የመጨረሻ ግባቸውም ጾምን ማጥፋት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግን፦ «ባንበላም (ብንጾም) አይጎዳንም፤» በማለት መንገድ ዘግቶባቸዋል። በመሆኑም ጾም የማይጎዳ ከሆነ እርሱን ገንዘብ ማድረግ ይገባል።
፬፦ «መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤» ፩ኛ ቆሮ ፮፥፲፪።
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ በተፈጥሮ የተሰጠውን ነፃ ፈቃድ፦ «ብየ ሥልጣን ላዕለ ኲሉ ዘኮነ፤ በሆነው ሁሉ ላይ ሥልጣን አለኝ፤» በማለት ከገለጠ በኋላ፦ «ወአኮ ኲሉ ዘይበቊዐኒ፤ ነገር ግን ኹሉ የሚረባኝ፥ የሚጠቅመኝ አይደለም፤» ብሏል። አባታችን አዳም የዕፀ በለስን ፍሬ የመብላትም ያለመብላትም ነፃ ፈቃድ (ሥልጣን) ነበረው። ነገር ግን በሰይጣን አሳሳነት የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን መለየት ተሳነው፥ ዓይነ ልቡናው ታወረ፥ ዕዝነ ልቡናው ደነቆረ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «አይረባኝም አይጠቅመኝም፤» ያለው፦ አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን በመለየቱ ነው። ይህንንም እምነቱ አጠንክሮ ሲናገር፦ «ወኲሉ ይትከሃለኒ፥ ወአልቦ ዘእሬሲ ይሰለጥ በላዕሌየ፤ ሁሉም ይቻለኛል፥ ነገር ግን በእኔ ላይ እንዲሠለጥን የማደርገው ምንም የለም፤» ብሏል። ከዚህም አያይዞ፦ «መብልዕ ለከርሥ፥ ወከርሥኒ ለመብልዕ፤ እግዚአብሔር ይሥእሮሙ ለክልኤሆ፤ መብል ለሆድ ነው፥ (ኃይሉ ነው ያጸናዋል)፥ ሆድም ለመብል ነው፤ (ጎታው ፥ ጎተራው ነው ይሸመዋል)፣ እግዚአብሔር ሁለቱንም ያሳልፋቸዋል፤» ብሏል። መቼም ማግባት ከታዘዘ ተብሎ ከሁሉ አይደረስም፥ አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት ፥ አንዲትም ሴት ለአንድ ወንድ ነው። አንድም፦ አንድ ወንድ ለአንድ ሴት፥ አንዲት ሴትም ለአንድ ወንድ ከተፈቀደ ተብሎ ኹልጊዜ ግብሩን መፈጸም አይገባም። በዓላትን፥ አጽዋማትን፥ ኅርስን(የአራስነት ጊዜን)፥ ትክትን (የወር አበባ ጊዜን) ምክንያት አድርጎ ከግብሩ መከልከል ያስፈልጋል። ስለዚህ፦ መብል ለሆድ ፥ ሆድም ለመብል ከኾነ ብሎ ኹሉ አይበላም፥ ኹልግዜም አይበላም።
፭፦ «የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥ አይደለችም፤» ሮሜ ፲፬፥፲፯
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሚያስተምርበት ጊዜ ሁለት ክፍሎች ነበሩ፦ አንደኛዎቹ፦ ጥንቱንም በአምልኮተ እግዚአብሔር የነበሩ ቤተ አይሁድ ናቸው። እነርሱም፦ ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ተስፋም የተሰጣቸው፥ ተስፋውንም ሲጠባበቁ የኖሩ ናቸው። በሥርዓትም በኲል እንዲበሉ በእግዚአብሔር የታዘዙትን እንስሳት ብቻ የሚበሉ፥ የተከለከሉትን ግን ፈጽመው የማይበሉ ናቸው። ዘሌ ፲፩፥፩-፵፮። ሁለተኛዎቹ ደግሞ፦ ከአምልኮተ  እግዚአብሔር ውጭ የኖሩ፥ ያገኙትን ሁሉ የሚበሉ አሕዛብ ናቸው። ነርሱም ጣዖት ሲያመልኩ፥ ለጣዖት ሲሠዉ በመኖራቸው፥ አይሁድ እንዳይረክሱ ከእነርሱ ጋር አይተባበሩም ነበር።
          የድኅነት ወንጌል በተሰበከ ጊዜ፦ ሁለቱም ክፍሎች ወደ ክርስትና ሃይማኖት መጡ። አመጣጣቸውም የጥንቱን ሥርዓታቸውን ይዘው ነበር። ይልቁንም አሕዛብ ለአምልኮተ እግዚአብሔርና ለሥርዓቱም አዲሶች ናቸው። እስራኤል ግን የተነገረው ትንቢት፥ የተቆጠረውን ሱባዔ፥ የተሰጠውን ተስፋ ያውቃሉ። ችግራቸው አፈጻጸሙ ላይ ነው፥ ምክንያቱም፦ ክርስቶስ እነርሱ በጠበቁት መንገድ አልመጣምና ነው። በመሆኑም በመጀመሪያ ክርስቶስን በኋላም ክርስትናን ተቃወሙ። ወደ ክርስትናው ከመጡ በኋላ ደግሞ ለአምልኮተ እግዚአብሔር እንግዳ የሆኑትን አሕዛብን በሚበሉትና በሚጠጡት ይንቋቸው ይነቅፏቸው ጀመር። ከላይ እንደገለጥነው እነዚያ ያገኙትን ሁሉ ይበሉ ነበር። እነርሱም በመብል የማይመ ስሏቸውን እስራኤልን ይነቅፏቸው ጀመር። ይህም፦ ወደ ክርስትናው የመጡትን ሕዝቦች ቀንዷን እደተመታች ላም ወደ ኋላቸው ሊመልሳቸው ሆነ።
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽንን ችግር አይቶ ዝም አላለም። የሁለቱንም ኅሊና ጠብቆ (ለኅሊናቸው መልስ እንዲሆን አድርጎ) አስተምሮአቸዋል። ትምህርቱም፦ የሚያስማማ፥ የሚያስታርቅ፥ አንድ የሚያደርግ ነበር። ይኸውም፦ እስራኤል፦ በክርስትና መድ፥ ወገን፥ የሆኑአቸውን አሕዛብን በፍቅር እንዲቀበሉአቸው ነው። በመሆኑም፦ «እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ እርስ በርሳችን አንነቃቀፍ፤ ይልቁንም ለወንድም እንቅፋት ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖር ይህን ዐስቡ። በሱ ርኲስ የሆነ ነገር እንደሌለ በጌታችን በኢየሱስ ሆኜ ዐውቄአለሁ፤ ተረድቼአለሁም፤ ነገር ግን ማናቸውም ነገር ርኲስ እንደሚሆን ለሚያስብ ያ ለእርሱ ርኲስ ነው። በመብል ምክንያት ባልንጀራህን የምታሳዝን ከሆንህ ፍቅር የለህም፤ (ለምን? በላ፥ ብለህ አረማዊውን የምትነቅፈው ከሆ ፍቅር የለህም፤ አንተም አረማዊው መብሉን አልተው ብለህ አይሁዳዊውን የምትነቅፍ ከሆንክ ፍቅር የለህም)፤ በውኑ ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለት ያ ሰው በመብል ምክንያት ሊጎዳ ይገባልን? እንግዲህ ጌታችን የሰጠንን መልካሙን ነገር አታሰድቡ። (ጌታችን እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ ብሎ የሰጠንን ሕገ ወንጌልን አታፍርሱ)። የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ነው እንጂ መብልና መጠጥ አይደለምና። እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ ግን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና በሰውም ዘንድ የተመረጠ ነው፤» ብሎአቸዋል። ሮሜ ፲፬፥፲፫-፲፰። እንዲያውም በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ፦ «እምነቱ ደካማ የሆነውን ሰው (አረማዊውን) ታገሡት፤ በዐሳቡም አትፍረዱ። ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደተፈቀደለት የሚያምን ሁሉን ይብላ፤» ብሏል። ሮሜ ፲፬፥፩። በዚህም መብል ላይ ማተኰር የእምነት ድካም መሆኑን ተናግሯል። በእምነት እየበረታ ሲሄድ ግን ማንኛውም ሰው መብል መጠጥ አይገዛውም።
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ያላት ወንጌልን ነው። ምክንያቱም ጸንተው ቢኖሩባት ለመንግሥተ እግዚአብሔር የምታበቃ ናትና ነው። ትርጉሙም፦ ፩ኛ፦ መንግሥተ እግዚአብሔር ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሃይማኖትን፥ ፍቅርን እና ተስፋን ትሰብካለች እንጂ መብልን እና መጠጥን አትሰብክም። ፪ኛ፦ መንግሥተ እግዚአብሔር ወንጌል ልብላ ልጠጣ ለምትል ሰውነት አትነገርም፤ ብትነገርም አታድርም፥ አትዋሃድም። ፫ኛ፦ መንግሥተ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሃይማኖትን፥ ፍቅርን፥ ተስፋን ገንዘብ ባደረገች ሰውነት እንጂ ጾምን ትታ መብል መጠጥን ገንዘብ ባደረገች ሰውነት አትወረስም፥ ማለት ነው። ሃይማኖትን፥ ተስፋን፥ ፍቅርን፥ በያዘ ሰውነት ለክርስቶስ የሚገዛ በእግአብሔርም ዘንድ ያማረ የተወደደ ነው።
፮ኛ፦ «ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤» ዕብ ፲፫፥፱።
          ጸጋ፦ በቁሙ ሲተረጐም፦ ሀብት፥ መልካም ስጦታ፥ ዕድል ፈንታ፥ ትምርት፥ ስርየት፥ ይቅርታ፥ ብዕል፥ ክብር፥ ሕዋስ፥ ሞገስ፥ የቸርነት ሥራ፥ አለዋጋ የሚሰጥና የሚደረግ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ በዚህ አንቀጽ ላይ ጸጋ ያለው ወንጌልን ነው። በቲቶ መልእክቱም ላይ፦ «የሚያድነው የእግዚአብሔር ጸጋ (ጸጋው ወንጌል) በሰው ሁሉ ታውቆአልና። እርስዋም፦ ከኃጢአትና ከዓለም ፍትወት እንለይ ዘንድ፥ በዚህ ዓለምም በጽድቅ፥ በንጽሕናና በፍቅር እንኖር ዘንድ ታስምረናለች፤» ብሏል። ቲቶ ፪፥፲፩። በመሆኑም፦ «የሰው ልጅ፥ በሕገ ወንጌል ጸንቶ ቢኖር መልካም ነው እንጂ በመ ብል አይደለም፤» በማለት መክሮናል። ምክንያቱንም ሲነግረን፦ «በዚያ ይሄ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና፤» ብሏል። እንግዲህ የሚረባውን የሚጠቅመውን ገንዘብ ማድረግ የማይረባውን የማይጠቅመውን ደግሞ መተው ይገባል።
፯ኛ፦ «እነርሱ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያይደለ ለሆዳቸው ይገዛሉና፤» ሮሜ ፲፮፥፲፰።
               ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ ሰውነታቸውን ለመከራ አሳልፈው እስከ መስጠት ድረስ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት   የተባበሩትን ሁሉ ስም እየጠራ ሰላምታ እንዲያቀርቡለት ከተናገረ በኋላ፦ «ወንድሞቻችን ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፥ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን (በሐሰተኞች መምህራን ላይ) እንድታውቁባቸው እማልዳችኋለሁ፤ ከእነርሱም ተለዩ፤ እነርሱ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያይደለ ለሆዳቸው ይገዛሉና፤» ብሏል። እነዚህ ሰዎች በአንደበታቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ቢጠሩም ሰውነታቸው ለመብል ለመጠጥ ያደረ ነው። ፈቃደ ሥጋቸው ያሸነፋቸው፥ የገዛቸው፥ የሰለጠነባቸው ሰዎች ናቸው። ሐዋርያው እንዳለው ለኢየሱስ ክርስቶስ የማይገዙ ሰዎች ቢሆኑም ማስመሰል (መንፈሳዊ ትያትር መሥራት) ይችሉበታል። ይኽንንም፦ «በነገር ማታለልና በማለዛ ዘብም (በለስ ላሳና ሚያቈላምጥ ንግግር) የብዙዎች የዋሃንን ልብ ያስታሉ፤»በማለት ተናግሯል። ሮሜ ፲፮፥፲፯። በፊልጵስዩስ መልእክቱም ላይ፦ «ዘወትር እንደምነግራችሁ፥ ልዩ አካሄድ የሚሄዱ (በመንፈሳዊነት ስም ተሸፍነው ሥጋዊ ኑሮ የሚኖሩ) ብዙዎች አሉና፤ አሁንም እነርሱ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች እንደሆኑ (የክርስቶስ ቤዛነት እንደሚያቃልሉ፥ በመስቀል ላይ የተቈረሰውን ቅዱስ ሥጋውን እና የፈሰሰውን ክቡር ደሙን እንደሚንቁ) በግልጥ እያለቀስሁ እነግራችኋለሁ። እነዚህም፦ ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸውም ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊውንም የሚያስቡ ናቸው።» በማለት ተመሳይ መልእክት አስተላልፏል። ፊል ፫፥፲፰-፲፱። እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ሆዳቸው አምላካቸው የሆነባቸው ሰዎች ክርስቶስን ማምለክ አይችሉም።

3 comments:

  1. እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ግልጽ የሆነ ምግብ ነው ስለዚህ የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልን ወላዲተ አምላክ በአማላዻነት አትለይብን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንንም ይጠብቀን አሜን፡፡

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete