Sunday, March 13, 2011

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል ፦ ፮

 


፩፦ የወደዱትን ማጣት፤
            የሰው ልጅ ፈርዶለትም ይሁን ፈርዶበት የሚወደውና የሚያፈቅረው አያጣም። የሚጀምረውም ገና በጧቱ በልጅነት በመሆኑ በዚህ ሕይወት ውስጥ ማለፍ የተፈጥሮ ግዴታ ነው። በአንድ ሰፈር አብሮ በማደግ፥ ወይም በአንድ ትምህርት ቤት አብሮ በመማር ፥ ወይም በአንድ ሰንበት ትምህርት ቤት አብሮ በማገልገል ፥ ወይም በአጋጣሚ በመተያየት የመፈላለግ ኹኔታ አለ።
፩፥፩፦ የልጅነት ፍቅር፤
            በልጅነት ዕድሜ ያዩትን ሁሉ የመውደድና የማፍቀር ስሜት ቢኖርም ልብ ወደ አንድ አቅጣጫ ማተኰሩ አይቀርም። እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ፦ የወደዱትን ሰው ጧትም ማታም የማየት ፍላጐት እየጠነከረ ይሄዳል። ይኸውም የዓይን ፍቅር የሚባለው ነው። እንዲህም ስል የልብ ፍቅር የለም ማለቴ አይደለም። ነገር ግን በዚያ ዕድሜ በአብዛኛው የልብን አውጥቶ የመናገር ባሕሉም ልምዱም ስለሌለ በአንደበት ሳይገለጥ ይቀራል። ማፈር መፈራራት የነገሠበት ሕይወት በመሆኑ ተዳፍኖ የሚቀረው ይበዛል። ትንሽ ደፈር ያሉት በአማላጅ ወይም በደብዳቤ አሳባቸውን ለመግለጥ ይሞክራሉ። ከዚህም ሌላ መልሱ መጥፎ ቢሆንስ ብለው በይሉኝታ ዝምታን የሚመርጡ እንዳሉ ሁሉ ሲግደረደሩ ያልሆነ መልስ የሚሰጡም አሉ። «አልህ ከማር ይጣፍጣል፤» እንዲሉ እልህ ውስጥ የሚገቡም ጥቂቶች አይደሉም።
            የአስተዳደጋችን ባሕል ብዙዎችን ቁጥብና ጥንቁቅ እንዳደረጋቸው በሁሉ ዘንድ ይታወቃል። ይህንን ባሕል የምንደግፍ እንዳለን ሁሉ የምንነቅፍም አለን። ምንአልባት ድጋፋችንም ሆነ ነቀፋችን በጭፍን ይሆናል። ነገር ግን፦ ጠቃሚውን ባሕል ከጐጂው ለይቶ መደገፍም መንቀፍም ይገባል። በሰከነ አእምሮ ላስተዋለው የአስተዳደጋችን ባሕል ከብዙ ጥፋት ጠብቆናል። ልዩነቱን የምናውቀው አሁን ያለንበትን ዘመን ስንመለከት ነው። ምክንያቱም ልጆች ሙሉ በሙሉ ከባሕላቸው አፈንግጠው ወጥተው እንደ ክረምት አግቢ በጥፋት ሲረግፉ እያየን ነውና። በሰለጠነው ዓለምም ቢሆን ራሳቸው ባመጡት ጣጣ በልጆቻቸው ምክንያት በጣም እየተቸገሩ ነው። ወደ ባሕላቸው እንዳይመለሱ ባሕላቸውን አጥፍተው ባሕል አልባ ሆነዋል። በዚያው እንዳይቀጥሉም ከጥፋት ወደ ጥፋት መረማመድ ሆኖባቸዋል። እኛ እንደምናወቀው በሀገራችን ትልቅ ድግስ የሚደገሰው ልጆች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲመረቁ ነው። በሰለጠነው ዓለም ግን ልጆች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠነቅቁ ትልቅ ደስታ ይደረጋል። ምክንያቱም በሐሺሽና በዝሙት የሚሰነካከለው ስለሚበዛ ነው።  
            የልጅነት አእምሮ ንጹሕ ወረቀት በመሆኑ በጎውም፥ ክፉውም ቶሎ ሊሣልበት ይችላል። ስለዚህ በቤተሰብ፥ በትምህርት ቤት ፥ በቤተክርስቲያንም በጎ በጎው ብቻ እንዲቀረጽበት ለማድረግ ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ከቤት እስከ አደባባይ የሚበዛው ክፉ ክፉው ነውና። ያለው ችግር ከአቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱም ሕብረተሰቡ ተስፋ ከቆረጠ ውሎ አድሯል። ልጆች እየተጓዙ ያሉት በራሳቸው መንገድ ብቻ ነውና። ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም በአዋጅ የተነገረ እስኪመስል ድረስ ያልተያያዘ ሰው አይገኝም። ከዚህ ያመለጠው ደግሞ በምኞት ይቸገራል።
            በልጅነት በስሜት የተጀመረ ፍቅር በአብዛኛው ቀጣይነት የለውም። ባለማስተዋል የጀመሩትን ባለማስተዋል ያቋርጡታል። ብስለቱ ስለሌለም ተስፋ ይቆርጣሉ። ያለወቅቱ ብዙ ነገር ውስጥ ስለሚገቡም ውስጣቸው ይጐዳል። ከዚህ በኋላ የሚያደርጉት ሁሉ አንዱ ሌላኛውን የማስቀናት ይሆናል። በዚህም ምክንያት ያልሆነ ነገር ውስጥ መውደቅ ይመጣል። ይሁን እንጂ በልጅነታቸው በበጎ ኅሊና የጀመሩት ነገር በአእምሮአቸው ውስጥ ተቀርጾ ስለለሚቀር ኋለኛውን እንደፊተኛው አድርገው ለመውደድ ይቸገራሉ። በትዝታ ወደ ኋላ እየተጓዙ ወደፊት መራመድ ያቅታቸዋል። በወጣትነትም፥ በጉልምስናም፥ በእርግናም ቢሆን የሚፈልጉት የጥንቱን የልጅነታቸውን ነው። የወደድኩት አንድ ጊዜ አምልጦኛል ብለው ስለሚያስቡም ሁልጊዜ ያውጠነጥኑታል።
            ጠቃሚው ነገር በልጅነት እንደ ልጅ ማሰብ ነው። መፍትሔውም በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ላይ ማተኰር ነው። የነገ ማንነት የሚገነባው በዛሬው ልጅነት ላይ በመሆኑ የሚቀድመውንና የሚከተለውን ለይቶ ጨክኖ መቅደም የሚገባውን ማስቀደም ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት፦ «ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች ፥ እያሳቱና እየሳቱ ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ። አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር ፥ ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፫፥፲፪። ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትምህርቴ ነው። ለዘለዓለም ለእኔ ነውና፥ ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ትእዛዝህ ትምህርቴ ነውና፥ ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና፥ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፥ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አንተ አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ስለዚህ የዐመፃን መንገድ ጠላሁ።» ብሏል። መዝ ፻፲፰፥፺፯-፻፬። በተጨማሪም፦ «ምስክርህ ድንቅ ነው፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገችው። የቃልህ ነገር ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል። አፌን ከፈትሁ፥ ልቡናዬንም አሰፋሁ፤ ትእዛዝህን ወድጃለሁና።» ብሏል። መዝ ፻፲፰፥፻፳፱።
፩፥፫፦ የወጣትነት ፍቅር፤
            በግዕዙ፦ ወርዘወ ብሎ፦ ጐለመሰ፥አደገ፥ ጐበዘ ፥ ሪዝ አወጣ፥ አቀመቀመ ፥ ጸና ፥ በረታ፤ ውርዝው ብሎ፦ ያደገ፥ የጎለመሰ ፥ ብርቱ፤ ወሬዛ ብሎ፦ ጐልማሳ፥ ጎበዝ፥ ለጋ፥ ወጣት ፥ ከአሥራ አምስት ዓመት በላይ የሆነ፥ ለዘር የበቃ ይላል። ቅዱስ ዳዊት፦ «ወርዘውኩሂ ወረሣዕኩ፤ ጐለመስሁ፥ አረጀሁም፤ (ከልጅነት እስከ እውቀት ፥ከኲተት እስከ ሸበት ደረስሁ)፤» ያለበት ጊዜ አለ። መዝ ፴፮፥፳፭። እንደትርጓሜው ይህ ዕድሜ፦ በከተማ ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገባበት ጊዜ ነው። በገጠሩ ደግሞ ጎጆ ለመውጣት የሚንደረደሩበት ዕድሜ ነው።
            በወጣትነት ዘመን አውቆ አጥፊ እስካልሆኑ ድረስ ከስሜታዊነት ወጥተው በማስተዋል የሚጓዙበት ዕድሜ ነው። በልጅነት ዕድሜ ማስተዋሉ ቢኖሩም፦ «የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ ፥ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ፤» እንደሚባለው አይነት ነው። «ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም፤» የሚባልም አለ። በወጣትነት ግን ቢያጠፉም አውቀው ነው የሚያጠፉት፥ ቢያለሙም አውቀው ነው የሚያለሙት። እንደ ሰው ስሕተት ቢኖርም፦ በአብዛኛው ክፉውንና በጎውን የሚለይበት ኅሊና እያለው ፥ በስሜት ፈረስ እየጋለበ አውቆ የሚሳሳት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «በጎ ነገርን ማድረግን የሚያውቅ ፥ የማይሠራትም ኃጢአት ትሆንበታለች።» ያለው እንደነዚህ ዓይነቶቹን ነው። ያዕ ፬፥፲፯። ከሁሉም በላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የጌታውን ፈቃድ አውቆ እንደ ፈቃዱ የማይሠራና የማያዘጋጅ የዚያ አገልጋይ ቅጣቱ ብዙ ነው።» በማለት በወንጌል ያስተማረውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ሉቃ ፲፪፦ ፵፯። ከዚህም ሌላ አይሁድን፦ «ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።» በማለት የወቀሳቸው የአዋቂ አጥፊዎች ሆነው በመገኘታቸው ነው። ዮሐ ፱፥፵፩። በተጨማሪም፦ «እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም።» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፭፥፳፪።
            የወጣትነት ዘመን ይነስም ይብዛም የዕውቀት ጊዜ ነው። ከዚህም አልፈው የሚራቀቁበት የሚፈላሰፉበት ዕድሜ ነው። እንደ ንብ ታታሪ በመሆን ከተለያዩ መምህራንና መጻሕፍት ዕውቀት የሚቀሰምበት ዘመን ነው። በመሆኑም ዛሬ የሚደከመው ለነገ ውጤት ነው። ነገ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ እና ጥሩ ኑሮ ለመኖር ነው። የተቃራኒ ጾታ ጓደኛ ሲታሰብም ልክ እንደዚሁ ወደፊት ስለሚመ ሠረተው ጥሩ ትዳር በማሰብ መሆን አለበት። በሕገ እግዚአብሔር ጸንቶ እስከ ጋብቻ ድረስ በመጠበቅም የሚገኘውን ጸጋ ማስተዋል ያስፈልጋል። ያዕቆብ ራሔልን እስኪያገኝ አሥራ አራት ዓመት ጠብቋል።
            ብዙ ወጣቶች በዚህ ዕድሜ ጭልጥ ያለ ፍጹም ሥጋዊ ፍቅር ውስጥ ይገቡና ኃጢአትን በመለማመድ ተማሪዎች ከሆኑ ከትምህርታቸው ፥ ሠራተኞች ከሆኑ ከሥራቸው የሚዘናጉበት ጊዜ አለ። ተማሪዎች መማር ፥ ሠራተኞች መሥራት ይሳናቸዋል። አልፎ አልፎም ከትምህርትም ሆነ ከሥራ ገበታ የሚሰናበቱበት ጊዜ አለ። በአብዛኛው ግን በትምህርታቸው ደካማ ውጤት ያስመዘግባሉ ፥ ወይም ደካማ የሥራ ወጤት ያሳያሉ። እንዲህም ሆኖ በተለያየ ምክንያት አብረው ላይዘልቁ ይችላሉ። በጠብ ወይም በመለወጥ፥ ወይም ከገቡበት የህልም ዓለም በመንቃት፥ ወይም ከእነርሱ አቅም በላይ በሆነ ችግር ፥ ወይም ለእነርሱም በማይገባቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከዚህ በኋላ «እንደ እርሱ ያለ ፥ እንደ እርሷ ያለ አላገኝም፤» በሚል ቀቢጸ ተስፋ ይያዛሉ። «እግዚአብሔር ባይፈቅድ ነው፤» የሚለውን ቢያውቁትም ለኅሊናቸው መልስ አልሆን ይላቸዋል።
            በሌላ በኲል ደግሞ የሚወዱትን የሚያጡት በሁለት መንገድ ሊሆን ይችላል። አንደኛው፦ ወንዶች ከሆኑ በፍርሃት ወይም በጥርጣሬ ሊሆን ይችላል። ጥርጣሬ የሚባለው፦ «ጠይቄ አይሆንም ብባልስ? እምቢ መባሌም ቢወራብኝስ?» የሚለው ነው። በሴቶቹ በኲል ያለው ችግር ግን ከባህል የተነሣ የወደዱትን መጠየቅ ስለማይችሉ ነው። ደፍረው እንዳይጠይቁም «ቢኮራብኝስ?» ብለው ይፈራሉ። ቢሆንም በተለያየ መንገድ ፍላጎታቸውን ለመግለጥ ይሞክራሉ። ሁለተኛው ደግሞ፦ ጠይቀው በማጣት ነው። እነዚህም ከላይ እንደገለጥነው፦ ይኽንን ብቻ በኅሊናቸው ሥለው ስለሚኖሩ ሌላ ሥዕል ለመሣል ይቸገራሉ። ወይም በቀደመው ሥዕል ላይ አዲስ ሥዕል ለመሣል ይሞክሩና ይዘበራረቅባቸዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው በመንፈሳዊ ሕይወት መድከምን ነው። ስለሆነም ለራስ ሲባል ወጣትነትን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ያስፈልጋል። ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤» ያለው ለዚህ ሁሉ ችግር መፍቻ መሁኑን ማመን ይገባል። መክ ፲፪፥፩። ቅዱስ ዳዊትም «ጐልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው፤» ብሏል። መዝ ፻፲፰፥፱።
            ወጣቶች፦ በተለይም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገቡበት ጊዜ፦ ከቤተሰብ ርቀው ስለሚሄዱ ነፃነት ይሰማቸዋል። በቅርብ ሆኖ የሚቆጣጠር ሰው ባለመኖሩ ለተለያየ ነገር ሲጋለጡ ይታያሉ። በግቢ ውስጥም ከግቢ ውጪም ከተማሪ እስከ አስተማሪ ድረስ ወጥመዱ ብዙ ነው። ጐትጓቹ ፥ አሳዳጁ ፥ የቀን ዕረፍት የሌሊት እንቅልፍ የሚሰጥ አይደለም። በተለይ በመጀመሪያው ዓመት ላይ አዳዲስ ተማሪዎችን የማዋከብና እንደ ቅርጫ የመቀራመት ዘመቻ አለ። አዲስ ገቢዎችም ሊያከብሩት የሚገባ የግቢው ሕግ እስኪመስላቸው ድረስ ይጨናነቃሉ። በየተቋማቱ ዙሪያ የሚከፈቱ ሻይ ቡና የሚባልባቸው ቤቶችም ለተለያዩ ነገሮች የሚያጋልጡ ናቸው። ከዚህም አያሌ ጠቢባን የሚወጡባቸው የትምህርት ተቋማት የተዘረጋባቸው የጥፋት መረብ ቀላል አለመሆኑን እንረዳለን። የትምህርቱ ክብደት ሳያንስ ይኽንን ሁሉ ፈተና ተቋቁሞ ለምርቃት መብቃት በራሱ ትልቅ ችሎታ ነው።
            በሌላ በኲል ደግሞ በየተቋማቱ የተመሠረቱት የግቢ ጉባኤዎች የስንቱን ሕይወት እንደጠበቁት ስናስብ ደስታችን ከመጠን ያለፈ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያኒቱም ፥ ለሀገሪቱም አንድ ትውልድ ያዳነ ታላቅ ማኅበር ነው። ወጣቶች በመናፍቃን እጅ እንዳይወድቁ ትምህርተ ሃይማኖትን ፥ በኃጢአት እንዳይወድቁ ሥነ ምግባርን በማስተማር ጠብቋቸዋል። የተቃራኒ ጾታ ግኑኝነታቸውም ጤናማ እንዲሆን፦ ቅድመ ጋብቻን ፥ ጊዜ ጋብቻን እና ድኅረ ጋብቻን በተከታታይ በማስተማር ጠባቂ እረኛ ሆኖላቸዋል። በዚህ ዙሪያ ችግር ሲያጋጥማቸውም በምክር አገልግሎት ክፍል በኲል በቂ ምክር በመስጠት የብዙ ወጣቶች ሕይወት ታክሟል። የጠፉትንም በመብራት ፈልጎ ለንስሐ በማብቃት ከስብራታቸው እንዲጠገኑ አድርጓል።
             በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ፈተናው እንዳለ ሆኖ ለበጎ የመተሳሰብና የመፈላለግ ኹኔታም አለ። እንዲያውም ከዚያ በፊት የነበረውን ሁሉ እንደ ህልም ዓለም በመቊጠር በአዲስ ተስፋ ከብስለት ጋር የሚጠገኑበት ጊዜ ነው። መመዘኛውም መንፈሳዊ ሕይወት ብቻ እየሆነ መጥቷል። በግቢ ጉባኤ አብረው  ይማራሉ ፥ አብረው ይዘምራሉ ፥ አብረው ያስቀድሳሉ ፥ አብረው ያገለግላሉ። በመደበኛው ትምህርት ድካም እንዳይኖርም አንዱ ሌላኛውን የመጠበቅም ሥራ ይሠራል። የሰነበቱት አዲስ ገቢውን በማስጠናት ፥ ከሥርዓተ ትምህርቱ ጋር እንዲተዋወቁ በማድረግ ፥ የጥናቱንም ዘዴ በማሳየት ይተባበራሉ።
            እነዚህም ወጣቶች እንደማንኛውም ሰው ተቀራርበው ሊራራቁ ይችላሉ፥ ወይም በመፍራትና በማፈር የውስጣቸውን አይናገሩ ይሆናል ፥ ወይም ተጠያይቀው አይሆንም ተባብለው ይሆናል። ይኸንን እውነታ መቀበል ግድ ነው። አንዳንዶች ግን ለመቀበል ይቸገራሉ። እንዲያውም ከመንፈሳዊ ነገር ጋር ያያይዙታል። «እንዴት መንፈሳዊ ሆኖ እንዲህ ያደርገኛል? እንዴት መንፈሳዊት ሆና እንዲህ ታደርገኛለች? ሁለተኛ ቤተክርስቲያን አልመጣም ፥ አላገለግልም፤» ይላሉ። ይህም ትልቅ ስህተት ነው። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያንን እያገለገልን ያለነው ገና በወጣኒነት እንጂ ከፍጹምነት ማዕረግ ደርሰን እንዳልሆነ ማወቅም ማመንም አለብን። የሥጋ ድካም በአንድ ጀንበር የሚጠፋ አይደለም። በዚህም የወደድኩትን አላገኘሁም በሚል መንፈስ ችግር ውስጥ የመውደቅ አዝማሚያ አለ።
            በየመሥሪያ ቤቱም ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው። ትዳር ያለውም የሌለውም መስመር ለቅቋል ማለት ይቻላል። እንዲያውም የኃጢአት ሳይሆን የዘመናዊነት ምልክት እየመሰለ መጥቷል። ሥራ ለመቀጠር ፥ ዕድገት ለማግኘት የወጣቶች ሕይወት ሁልጊዜ ፈተና ላይ ነው። የትምህርት ቤቱን ወጥመድ አመለጥን ሲሉ ሌላ ወጥመድ ተዘርግቶ ይጠብቃቸዋል። ለዚህም መድኃኒቱ ዓርብ ዓርብ በየቤተክርስቲያኑ የተዘረጋው የሠራተኛ ጉባኤ ነው። በተጨማሪም የሰንበት ትምህርት ቤቶችና የሠርክ ጉባኤዎች ታላቅ አስተዋጽዖ አላቸው።
            ወጣቶች በአንድ መሥሪያ ቤት አብሮ በመሥራት ይበልጥ ይቀራረባሉ። በመቀራረብ ብዛትም መፈቃቀድ ይመጣል። በዚህን ጊዜ ዋናው መመዘኛ መንፈሳዊ ሕይወት ሊሆን ይገባል። አንዳንዶች ሚዛናቸው ሥልጣን ወይም የደሞዝ ትልቅነት ወይም መልክ እየሆነ በነፍስም በሥጋም እየተጐዱ ነው። እዚህም የወደድነውን በተለያየ ምክንያት ልናጣ እንችላለን። ቢሆንም ተስፋ መቁረጥ አይገባም። «ዛሬ ወይም ነገ ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በዚያችም እንኖራለን፤ እንነግዳለንም፤ እናተርፋለንም ፥ የምትሉ እናንተ ተመልከቱ፤ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና፥ ሕይወታችሁ ምንድነው? እናንተማ ላንድ ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንደጢስ አይደላችሁምን? በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል። አሁን እናንተ በሥራችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚች ያለችው ትምክሕትም ኋላ ክፉ ናት።» የሚለውን ማሰብ ነው። ያዕ ፬፥፲፫።

15 comments:

 1. መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ቃለ ህይወትን ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን ያገልግሎት ዘመንዎን ያርዝምልን አሜን፡፡
  የሰጡን ትምህርት በአውነት በመልካም ልቦና ላነበበው ጥሩ ትምህርት ነው፡፡ የእመቤታችን አማላጅነት የፃድቃን ሰማዕታት ተራዳዒነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

  ReplyDelete
 2. አባታችን አጥንትን የሚያለመልመውን የመላእክትን ቃል ያሰማዎት!!!!!!!!!!!!!! እግዚአብሔር ይስጥልኝ የቅዱሳን አምላክ በረድኤት ይጠብቆት፡፡ ትልቅ የሕይወት ለውጥ ነው የማመጣበትን ምክር ነው የሰጡኝ፡፡

  ReplyDelete
 3. እግዚአብሔር ይስጥልን፤ቃለ ህይወት ያሰማልን፤መንግስተ ሰማያት ያዉርስልን።

  ReplyDelete
 4. kale hywet yasemaln

  ReplyDelete
 5. በሌላ በኲል ደግሞ በየተቋማቱ የተመሠረቱት የግቢ ጉባኤዎች የስንቱን ሕይወት እንደጠበቁት ስናስብ ደስታችን ከመጠን ያለፈ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተክርስቲያኒቱም ፥ ለሀገሪቱም አንድ ትውልድ ያዳነ ታላቅ ማኅበር ነው። ወጣቶች በመናፍቃን እጅ እንዳይወድቁ ትምህርተ ሃይማኖትን ፥ በኃጢአት እንዳይወድቁ ሥነ ምግባርን በማስተማር ጠብቋቸዋል። የተቃራኒ ጾታ ግኑኝነታቸውም ጤናማ እንዲሆን፦ ቅድመ ጋብቻን ፥ ጊዜ ጋብቻን እና ድኅረ ጋብቻን በተከታታይ በማስተማር ጠባቂ እረኛ ሆኖላቸዋል። በዚህ ዙሪያ ችግር ሲያጋጥማቸውም በምክር አገልግሎት ክፍል በኲል በቂ ምክር በመስጠት የብዙ ወጣቶች ሕይወት ታክሟል። የጠፉትንም በመብራት ፈልጎ ለንስሐ በማብቃት ከስብራታቸው እንዲጠገኑ አድርጓል።
  Abatachin Be'Ewnet Egziabher amlak Mahiberun yitebikilin lersom kale hiowot yasemalin. Kemitefut wist andua hon neber be'Egziabher Fikad be mahiberu amakagninet tetebke wetichalehu.

  ReplyDelete
 6. kalehiwot yasemalen yagelegelot gizewotn yebarekelen

  ReplyDelete
 7. Betam tilik timihirt new yemisetew betam tiru new kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 8. እግዚያብሄር ይስጥልን ቃለህይወት ያሰማልን!!!

  ReplyDelete
 9. KALEHIWET YASEMALIGN ABATACHIN.

  ReplyDelete
 10. Melake Selam Kale hiwot yasemalin. Ye gibi Hiwot biyansi kesiga tifat endadanegn hiyaw misikir mehon ichilalehu. Yagelgilot zemenwon yarzimilin

  ReplyDelete
 11. Bekoptoche sinodose benkename egizeabehre yemsegen MK. yemesel nolawi setonale bertu selase eske mechershawe bewnte yetebkachu

  ReplyDelete
 12. I really lost my solemate because of my problem & couldnot forgive myselfe for that. As you said "ኋለኛውን እንደፊተኛው አድርገው ለመውደድ ይቸገራሉ"that is who i am & it jopardize your r/s.Hope you will say some thing how to forget & move forward with what you have.
  Kale hiowt yasemalen Erjim edem yistlen

  ReplyDelete
 13. ቀሲስ ቃለ ሕይወት ያሰማልን
  የአምስተኛው አስተያየት ሰጭ አስተያየት ለማህበሩ አገልግሎት ህያው ማሰረጃ ነው እግዚአብሔር የእርሶንና የማህበሩን አገልግሎት ይቀበል

  ReplyDelete
 14. ከካዛንችስApril 4, 2011 at 12:34 AM

  ቃለ ህይወት ያሰማልን! . . . አንድ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ጥሬ ቃሉን ጉልህ ለማድረግ የሚተኩት ቃላቶች ጥሬ ቃሉ እንዳለ ሆኖ በቅንፍ ቢቀመጡ መልካም ነው እላለሁ፡፡

  ReplyDelete
 15. ቃለ ሕይወት ያሰማልን አባታችን!

  ይህን ጽሑፍዎን በማነብበት ወቅት እጄ ላይ የነበረው “የትዳር አንድምታው እንደቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ” የተሰኘ መጽሐፍ እንዲህ ሲል አገኘሁት፡- “ቤተሰብ ትንሽዋ ቤተክርስቲያን ናት፡፡” (ገጽ 25)

  እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ቤተክርስቲያን እንዲኖረን ይፈልጋል ወይም ሰጥቶናል ማለት ነው፡፡ እያንዳንዳችን የምናስተዳድረው ቤተክርስቲያን አለን ወይም ይኖረናል ማለትም ነው፡፡ በፈሊጥ የማስተዳደር ብቃት ደግሞ ጠንካራ የትምህርት መሠረት ይጠይቃል፡፡

  አሁን ልፋትዎን፣ ድካምዎን በአዲስ መንገድ አየሁት፡፡

  ReplyDelete