Saturday, February 19, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል ፲፦

የሰው ልጅ ባሕርይ በአዳም ኃጢአት ምክንያት አድፎ ቆሽሾ ይኖር ነበር። በዚህም ምክንያት ጽድቁ ሁሉ የመርገም ጨርቅ ሆኖበት ፥ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ ተጨምሮበት ወደ ሲኦል ሲጋዝ ኖሯል። ይህንንም ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ፦ «ሁላችን እንደ ርኲስ ሰው ሆነናል ፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል ፦ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል፤ » በማለት ገልጦታል። ኢሳ ፷፬፥፮ ። እንዲህም ማለቱ፦ ነቢያት እና ካህናት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት የጸለዩት ጸሎት ፥ የሰዉት መሥዋዕት ፥ በዕደ እግዚአብሔር ለመያዝ አበቃቸው እንጂ፦ ለክብር ፣ ለልጅነት ፣ ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት እንዳላበቃቸው ለመናገር ነው። እንደ «ቅጠል ረግፈናል፤» ያለውም፦ ለጊዜው በመዓት፣ በመቅሠፍት መርገፍን ሲሆን ፥ ለፍጻሜው በአካለ ነፍስ በሲኦል መርገፍን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ስለዚህም በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባች፤ ስለዚችም ኃጢአት ሞት ገባ፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስለ አደረጉ በሰው ሁሉ ላይ ሞት መጣ። . . . ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው፤ ሁሉ በአዳም አምሳል ተፈጥሮአልና ፥ አዳምም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳል ነውና፤» ብሏል። ሮሜ ፭፥፲፪-፲፬።
          ከሰው ወገን ባሕርይዋ ያላደፈባት ፥ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልወደቀባት ፥ ጥንተ አብሶ (የአዳም የጥንት በደል) ያልነካት ፥ በሥጋም በነፍስም ፍጽምት ሆና የተፈጠረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። በዚህም ምክንያት የአዳም ኃጢአት እንደ ቅጠል ላረገፈው የሰው ዘር በጠቅላላ የባሕርዩ መመኪያ ሆናለታለች። ነቢዩ ኢሳይያስ፦ « የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን ፥ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር፤» ያለው ለፍጻሜው ስለ እርሷ ነው። ኢሳ ፩፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ የነሣውን (ነፍስንና ሥጋን ነሥቶ የተዋሐደው) ከአብርሃም ዘር እንጂ ከመላእክት የነሣው አይደለምና። (የመላእክትን ባሕርይ ባሕርይ አላደረገም)።» ያለው እመቤታችንን ነው። ዕብ ፪ ፥ ፲፮።  ይህንን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በዕለተ ሰንበት የውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ «ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልን ዘንድ ለአንቺ ይገባል፤ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ፤ ከነቢያትም ከመምህራንም ትበልጫለሽ፤ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፤» ካላት በኋላ፦ «በእውነቱ የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፤» ብሏታል።
          አምላካችን በሁሉ ባዕለጸጋ ነው፥ ሁሉ የእርሱ ነው ፥ የእርሱ ብልጽግና የማይጎድል ብልጽግና ነው፤ ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!» ብሏል። ሮሜ ፲፩፥፴፫። እግዚአብሔርም ከዚህ ጥልቅ ከሆነ ብልፅግናው ለሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ አድርጎ በልግስና ሰጥቷል፥ በየጊዜውም በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምራል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «እኛም ሁላችን ከሙላቱ በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን። ኦሪት በሙሴ ተስጥታ ነበርና፤ ጸጋና እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን፤»ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፲፮።
          የባዕለጸጎች ባዕለጸጋ የሆነ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእኛን ባሕርይ በመንሣቱ፦ «ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ ፥ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። እንደ ሰው ራሱን አዋረደ፤» ተብሏል። ፊል ፪፥፯። በቆሮንቶስ መልእክትም ላይ ፦ «የጌታችን የኢየሱስ ክርሰቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለእናንተ ራሱን ድሃ አደረገ፤» የሚል ተጽፏል። ፪ኛ ቆሮ ፰፥፱። ከሁሉም በላይ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ሁሉ የእርሱ ሲሆን ፦ «ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መስፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም፤» ብሏል። ማቴ ፰፥፳።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ እንጂ፦ ከባሕርዩ ምንም አልተለወጠም። የእኛን ባሕርይ በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኗል። እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው፥ የክብር አምላክ ሲሆን በተዋሕዶ ከበረ፥ ተባለ፤ ሕይወት ሲሆን ነፍስን ነሣ፥ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «ሕይወት በእርሱ ነበረ፥ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤» ብሏል። ዮሐ ፩፥፬። በመልእክቱም፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን ፥ በዓይናችንም የተመለከትነውንም ፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን። ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት፤ ምስክርም ሆንን፤ ለእናንተም ከአብ ዘንድ ያለችውንና ለእኛ የተገለጠችውን የዘለዓለምን ሕይወት እንነግራችኋለን፤» በማለት ነግሮናል። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት ፤ » በማለት አይሁድን የወቀሳቸው እርሱ ሕይወት ስለሆነ ነው። የሐዋ ፫፥፲፭። ጌታችንም ፦ «እኔ ሕይወት ነኝ፤» በማለት ለደቀመዛሙርቱ ነግሮአቸዋል። ዮሐ ፲፬፥፮።
          አንድ ክርስቶስ (ወልድ ዋሕድ) የሕይወት እንጀራ ሲሆን ባሕርያችንን በመንሣቱ ማለትም ረሀብ የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ በመዋሐዱ ተራበ፥ ዮሐ ፮፥፴፭፤ ማቴ ፳፩፥፲፰፤ የሕይወት ውኃ ሲሆን ተጠማ፥ ዮሐ ፬፥፲፤ ፲፱፥፳፰፤ ተንገላታ፥ « ለሞት እስከመድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው።» እንዲል፦ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ፤ ፊል ፪፥፰። ጌታችን ከባሕርይ አባቱ ከአብ፥ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በፈቃድ አንድ ሲሆን፦ «አባቴ ሆይ ፥ የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይደለም፤ » ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፳፮፥፴፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ልጅም ቢሆን መከራን ስለተቀበለ መታዘዝን አወቀ፥ ከተፈጸመም በኋላ ለሚታዘዝለት ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ የዘላለም መድኅን ሆነ፤» ብሏል። ዕብ ፭፥፰።
          እርሱ በባሕርዩ ሞት የለበትም፥ ሕያወ ባሕርይ ነው፤ ጌታችን ፦ ቅዱስ ዮሐንስን፦« አትፍራ፥ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበረሁ፤ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእኔ ዘንድ አለ፤» ያለው ለዚህ ነው። ራዕ ፮፥፲፯። ጌታችን ሞት የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ በመዋሐዱ ሞተ፥ሞተ የተባለውም ነፍስ ከሥጋ በመለየቷ ነው። «ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፤» እንዲል፦ ከሥጋ የተለየች ያቺ ነፍስ የእርሱ ናት። ዮሐ ፲፱፥፴። በሉቃስ ወንጌል ደግሞ ፦ «አባት ሆይ ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤» የሚል አለ። ሉቃ ፳፫፥፵፮። ጌታችን «ነፍሴ» ማለቱ በተዋሕዶ የራሱ ገንዘብ ስላደረጋት ነው። «እነሆ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ፥ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስ ከምትባል ከይሁዳ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። » እንዲል፦ ነፍስ የተለየችው ሥጋም በተዋሕዶ የእርሱ ገንዘብ ነው። ዮሐ ፲፱፥፴፰።
          መለኮት የእኛን ባሕርይ ተዋሐደ፥ ስንል ፦ የተዋሕዶው ምሥጢር የሰው አእምሮ ሊረዳው ከሚችለው በላይ ነው፥ ይህም፦ በሥጋ እውቀት የሚረዱት አይደለም ማለት ነው። ለመሆኑ የነፍስን እና የሥጋን ተዋሕዶ ልንረዳ የምንችለው በምን መልክ ነው? ነፍስ በባሕርይዋ የሥጋን ፈቃድና ምቾት ባትካፈልም፦ ፈቃዷን የምትፈጽመው በሥጋ ላይ ነው። ሥጋ የእርሱን ፈቃድ ትቶ ለእርሷ ፈቃድ እንዲገዛ ሁልጊዜ ትፈልጋለች። ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እላችኋለሁ፤ በመንፈስ (በፈቃደ ነፍስ) ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ። ሥጋ፦ መንፈስ (ነፍስ) የማይሻውን ይሻልና፥ መንፈስም (ነፍስም) ሥጋ የማይሻውን ይሻልና፥ የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፤» ያለው ለዚህ ነው፤ ገላ ፭፥፲፮። ክርስቶስም ፦ በመለኮቱ ሕማም (መከራ) የማይስማማው ሲሆን ሕማም የሚስማማትና ሁሉን አዋቂ የሆነች ነፍስ ያለውን ሥጋ ተዋሕዷል።
          ጌታ በሥጋው መከራ ሲቀበል፦ በተዋሐደው ሥጋ መከራ ተቀበለ፥ በዚህም አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ገንዘብ አደረገ። በመሆኑም ከተዋሕዶ በኋላ ጌታን ለሁለት ከፍሎ በመለኮቱ መከራ አልተቀበለም፥ በሥጋው ብቻ መከራ ተቀበለ አይባልም። አንድ ሰው ሥጋም ነፍስም ስላለው አንድ ሰው እንጂ ሁለት አይባልም፤ ነፍሱ ከሥጋው ጋር በተዋሕዶ አንድ ስለሆነች አንድ ሰው መባሉ ግድ ነው። ክርስቶስም በተዋሕዶ የከበረ አምላክ ስለሆነ አንድ እንጂ ሁለት አይባልም። ከዚህ በመቀጠል ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
የጽላት ፥ የታቦት ምሳሌነት፦
          የጽላት የታቦት ምንጭ እግዚአብሔር ነው ፥ ልበ-ወለድ አይደለም። «እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ ሁለቱን የምስክር ጽላት ፤ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ( በግብር አምላካዊ ተጽፈው የተገኙትን) የድንጋይ ጽላት ለሙሴ ሰጠው።» እንዲል፦ ጽላትን ቀርጾ አክብሮ ለሙሴ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፩፥፲፰። «ጽላቱም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቱ ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ፤» ይላል። ዘጸ ፴፪፥፲፭።
          ጽላቱ በተሰበሩ ጊዜም፦ እንደገና የቀደሙትን አስመስሎ እንዲቀርጽ እግዚአብሔር ለሙሴ ፈቅዶለታል። እግዚአብሔር ሙሴን፦ «የቀደሙትን ጽላት አስመስለህ ሁለት ጽላት ቀርጸህ እኔ ወደምገለጽበት ተራራ ውጣ ፥ ቀድሞ በሰበርካቸው ጽላቶች ተጽፈው የነበሩ አሥሩ ቃላትም በእነዚህ ጽላቶች ጽፌ እሰጥሃለሁ፤ ማለዳ ወደ ደብረ ሲና ትወጣለህና ተዘጋጅተህ ንጹህ ሁነህ እደር ፥ ማልደህም ወደ ደብረ ሲና ወጥተህ ቁም፤ ሌላ ሰው ግን ካንተ ጋር ወጥቶ ከተራራው ላይ አብሮህ የሚቆም አይኑር፥ ላሞችም በጎችም ቢሆኑ በተራራው አቅራቢያ ሊሠማሩ አይገባም፤» አለው። ሙሴም የቀደሙትን ጽላቶች አስመስሎ ሁለት የእብነበረድ ጽላት ቀርጾ ይዞ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ማልዶ ገሥግሦ ወደ ደብረ ሲና ወጣ።
          እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ፥ በደብረ ሲና ራስ ላይ ቁሞ ፥ እኔ፦ «መሓሪ ወመስተሣህል ነኝ፤ » ብሎ ተናገረ። በሙሴም ፊት በብርሃን ሠረገላ ሁኖ የጌትነቱን ስም እየጠራ አለፈ፤ «ስሜም፦ ይቅር ባይ ፥ ከመዓት የራቀ ፥ ቸርነቱ የበዛ ፈጥሮ የሚገዛ መባል ነው፤ የአብርሃምን መሓላ አጽንቼ ፥ ለአእላፈ እሥራኤል ቸርነትን የማደርግ ፥ አመጽን፣ በደልን ፣ ኃጢአትን የማርቅ ፥ ይቅር የምል እኔ ነኝ፤ በድሎ የማይመለሰውን ግን ከኃጢአት አላነጻውም፤ (ይቅር አልለውም) ፤» አለ። አመጻ የድፍረት ፥ በደል የስህተት ፥ ኃጢአት የድካም ነው።
          ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል በሰማ ጊዜ፦ ደንግጦ ፥ አንገቱን ሰበር አድርጎ ለእግዚአብሔር የፍርሃት ስግደት ሰገደ፤ እግዚአብሔርንም፦ «በአንተ ዘንድ ሞገስን (ባለሟልነትን) ካገኘሁ ፥ አንተ ጌታዬ ከእኔ ጋር በረድኤት አብረኸኝ ሂድ ፥ እሥራኤል ክሣዳ ልቡናቸው በኃጢአት የጸና ነውና የወገኖችህን ፍጹም ኃጢአት ይቅር በል፥ ይህን ያደረግህልን እንደሆነ ለአንተ ስንገዛ እንኖራለን፤» አለው። እግዚአብሐርም ሙሴን፦ «በወገኖችህ ዘንድ የኪዳን ምልክት ይሆን ዘንድ ብርሃን በፊትህ እሥልብሃለሁ፥ በአራቱም መዓዝን ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ሁሉ ተደርጎ የማያውቅ ጭጋግ ተአምራት አደርግልሃለሁ፤ እኔም የማደርግልህ ነገር ድንቅ ነውና አንተ በመካከሉ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል፤ » አለው። ከዚህም አያይዞ አያሌ ትእዛዛትን አዝዞታል።
          በመጨረሻም እግዚአብሔር ሙሴን፦ «በእነዚህ ቃሎች ከአንተ ከእሥራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና (ሕጌን ቢጠብቁ እጠብቃቸዋለሁና) እነዚህን ቃሎች (የነገርኩህን ሁሉ) ጻፍ፤» አለው። በዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ነበረ፤ እንጀራም አልበላም ፤ ውኃም አልጠጣም፤ በጽላቱም አሠሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። ዘጸ ፴፬፥፩-፳፰።
          የቀደመው ጽላት የአዳም ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ እምኀበ አልቦ እንደተገኘ ፥ አዳም እንበለ ዘርእ ለመገኘቱ ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ ሁለት ወገን መሆኑ ለነፍሱና ለሥጋው ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ በጣዖት ምክንያት መሰበሩ ደግሞ አዳም በኃጢአት ምክንያት ለመጎዳቱ ምሳሌ ነው፤ የመጀመሪያው ጽላት በእግዚአብሔር እጅ መሠራቱ አዳም በእግዚአብሔር እጅ ለመፈጠሩ ምሳሌ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «እጆችህ ሠሩኝ ፥ አበጃጁኝም፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፻፲፰፥፸፫። የኋለኛው ጽላት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። ሁለት መሆኑ የነፍሷና የሥጋዋ ምሳሌ ነው። በጽላቱ ላይ ቃለ እግዚአብሔር መቀረጹ፥ ከሦሥቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል (ቃለ አብ ፥ ቃለ መንፈስ ቅዱስ) ከሰማይ ወርዶ፥ በመንፈስ ቅዱስ ግብር በማኅፀኗ ሰው ሁኖ ለመቀረጹ ምሳሌ ነው። የኋለኛው ጽላት ከሰው ወገን በሙሴ እጅ መቀረጹ ፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሰው ወገን በሕግ በሆነ ሩካቤ ፥ ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና ለመወለዷ ምሳሌ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ ፦ «ድንግል ሆይ ፥ በኃጢአት ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም ፥ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፤» ብሏል። (ቅዳ፡ ማር፡ ቁጥር ፴፰)
          እግዚአብሔር ጽላቱን ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት የጽላቱን ማደሪያ ታቦቱን እንዲያዘጋጅ ነግሮታል። ከምንና እንዴት መሥራት እንዳለበትም አስተምሮታል። ይኽንንም ፦ «ከማይነቅዝ (ሽምሸርሰጢን ከሚባል) ዕፅ ቆርጠህ የምስክሩን ታቦት ሥራ፤ . . .  በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፤ » በማለት ነግሮታል። ዘጸ ፳፭፥፲-፲፪። ታቦት የትስብእት ፥ ወርቅ ደግሞ የመለኮት ምሳሌዎች ናቸው፤ ታቦቱ በውስጥም በውጭም በወርቅ እንደተለበጠ፥ በወርቅ የተመሰለ መለኮትም፦ በውጭ የሚታይ ሥጋን እና በውስጥ ያለች የማትታይ ነፍስንም ተዋሕዶ ሰው ሆኗል። ታቦቱ ከማይነቅዝ ዕፅ መሠራቱም፦ የጌታችን ሥጋው በመቃብር፦ የማይፈርስ የማይበሰብስ ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ይኽንን በተመለከተ ባለቤቱ ራሱ በነቢዩ በዳዊት አድሮ፦ «ነፍሴን (ሰውነቴን) በሲኦል አትተዋትምና ፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውምና፤» ብሏል። መዝ ፲፭ ፥፲። ታቦቱ የተለበጠበት ወርቅ ንጹህ መሆኑ፦ እግዚአብሔር በባሕርዩ ንጹሕ ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ጌታ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ወርቅ መገበራቸው እርሱ ባወቀ «ንጹሐ ባሕርይ ነህ፤ » ሲሉት ነበር ፥ አንድም ወርቅ መለኮትህ ትስብእትን ተዋሕዷል ማለትም ነው። ማቴ ፪፥፲፩። ቅዱስ ኤፍሬምም በእሑዱ የውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ፦ «ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ፥ ያለመለየትና ያለመለወጥ ሰው የሆነ ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ይመስልልናል። ይኽውም መለወጥ የሌለበት ንጹሕ መለኮት ነው፥ ከአብ ጋር የተካከለ ነው።» ብሏል።
የሁለቱ አዕዋፍ ምሳሌነት፤
          በኦሪቱ ለምጽ የርኲሰት ምልክት ስለነበረ፥ እግዚአብሔር በልሙጻን ላይ ከመንጻታቸውና ከነጹም በኋላም ሕግ ሠርቶባቸው ነበር። ይኽንንም፦ «ለምጽ የያዘው ሰው ሕጉ ይህ ነው፤ ከለምጽ በነጻበት ቀን ወደ ካህኑ ይወስዱታል ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም ፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው ፥ የዝግባም እንጨት ፥ቀይ ግምጃም ፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንደኛዋን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ያዝዛል። ያልታረደችውን ወፍ ፥ የዝግባውንም እንጨት ፥ ቀዩንም ግምጃ ፥ ሂሶጱንም ወስዶ በታረደችው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። ከለምጹም በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ይሆናል፤ ያልታረደችውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቃታል።» በማለት ነግሮታል።ዘሌ ፲፬፥፩-፯።
          ሁለቱ ወፎች ንጹሐን መሆናቸው፦ መለኮትም  ፥ የተዋሐደው ሥጋም ንጹሐን ለመሆናቸው ምሳሌዎች ናቸው። አንዷ ወፍ ታርዳ በፈሰሰው ደም ሁለተኛዋ ወፍ ተነክራ በሕይወት መኖሯ ፦ ጌታ በተዋሐደው ሥጋ፦ ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ቢሞትም፦ በመለኮቱ ሕያው ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ስለ እኛ ፥ ስለ ኃጢአታችን በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ (በመለኮት) ግን ሕያው ነው፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰። የምንጩ ውኃ ደግሞ ለጥምቀት ውኃ ምሳሌ ነው። ይኸውም፦ «ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤»ተብሎ የተነገረለት ነው። ዮሐ ፫፥፭። እርሱም ራሱ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ፦ በጥምቀቱ የባረከው የቀደሰው ነው። ማቴ ፫፥፲፫።
          የእኛን ባሕርይ በመንሣት በተዋሕዶ ሰው የሆነ ጌታ፦ በሚበሩ አዕዋፍ የተመሰለው ከሰማይ ሰማያዊ መሆኑን ለመግለጥ ነው። ይኽንንም፦ «ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም ፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) ነው።» በማለት ጌታችን ነግሮናል። ዮሐ ፫፥፲፫። እንግዲህ ለምጻሙ ሰው በወፉ ደም ተረጭቶ ከለምጹ ፈጽሞ እንደሚነጻ ፥ የአዳም ልጆችም በመስቀል ላይ በፈሰሰ በክርስቶስ ደም፦ ከኃጢአት ፈጽመን ነጽተናል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «የኢየሱስ ክርሰቶስም ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፤»  ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። ነውርና እድፍ እንደሌለው በግ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያንን ጠብቁ፤» ብሏል። የሐዋ ፳፥፳፰።
          እግዚአብሔር ባሕርያችንን ነሥቶ ሰው ሆነ ፥ እኛን መሰለን ፥ የሥጋ ዘመድ ሆነን ፥ የምንለው የባሕርያችን መመኪያ በሆነች እመቤት ፥ በቅድስት ድንግል ማርያም ተመክተን ነው። እርሷን ምክንያተ ድኂን አድርጎ በደሙ ፈሳሽነት ስላዳነን እንመካባታለን ፥ ለድኅነተ ዓለም፦ በመልዕልተ መስቀል የተቆረሰ ሥጋ ፥ የፈሰሰ ደም ፥ አሳልፎ የሰጣት ነፍስ ፥ የባሕርያችን መመኪያ ከሆነች ከእርሷ የነሣው ነውና። ለዚህም ነው፥ የጌታን አዳኝነት ስንናገር እመቤታችንን መተው የማንችለው፤ ለሚያስተውል ሰው ነገረ ማርያም ነገረ ክርስቶስ ነውና።      

8 comments:

 1. "መለኮት የእኛን ባሕርይ ተዋሐደ፥ ስንል ፦ የተዋሐዶው ምሥጢር የሰው አእምሮ ሊረዳው ከሚችለው በላይ ነው፥ ይህም፦ በሥጋ እውቀት የሚረዱት አይደለም ማለት ነው።" መልዓከ ሰላም እግዚአብሔር ቃለ ሕይወት ያሰማዎ!

  ReplyDelete
 2. kindu the JohannsburgFebruary 20, 2011 at 11:58 AM

  i really love the commentery {andimta} part of it Kesis Burakewe yidresen

  ReplyDelete
 3. Amlak rejim edmen ketena gar yistilin kale hiwoten yasemalin.

  ReplyDelete
 4. Kale hiowten yasemalen.

  ReplyDelete
 5. ቀሲስ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ ከሰሞኑን የእመቤታችን ባላት ስናከብር ግር ያለኝ ነገር ነበረ ይህም የካቲት16 የምናከብረዉ የእመቤታችን የቃልኪዳን ቀን ብለን እና እመቤታችን በሰኔ21 በጎለጎታ እደጸለየችና ጌታችንም ተገልጾ ከባለሟሎቹ ጋረ ወደርሷ ቀርቦ ብዙ ቃልኪዳኖችን እንደሰጣት በሰኔ ጎለጎታ ሁሌ እናነባለን፡፡ ታዲያ ይህ ከሆነ የካቲት16 ቀን የምህረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ቀን ብለን ለምን እናከብራለን?
  ምናልባት ይህ ጥያቄ የኔ ብቻ ሊሆን ይችላልና mercysn@gmail.com ላይ በአጭሩ ቢያሳዉቁኝ ደስ ይለኛል፡፡
  ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 6. ቀሲስ በእዉነት በአሁኑ ሰዓት እዲህ አይነት የቁርጥ ቀን ለጆች ያሰፈልጋሉ ለእናት ቤተክርስቲያን፡፡ ቀሲስ አሁን አሁን ምን እደናፈቀኝ ያዉቃሉ? በአዉደምህረቶች የሚሰጡ ስብከቶች ሁሉ ከመጽሕፍ ቅዱስ አንድ ጥቅስ በመምዘዝ ሁልጊዜ ያለፉ ታሪኮችን መተረክ ብቻ በመሆኑ የቤተክርስቲያን ስርዓት ዶግማ ቀኖና ምስጢራተ-ቤተክርስቲያን የሚባሉት እነማን ናቸዉ እንዴትስ ይፈጸማሉ ከተፈጸሙ በኃላስ ምነ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል እና መሰል ትምህርቶችን ምዕመኑ መስማት ያቆመበትና በልማድ ብቻ በትላልቅ ድምጽ ማጉያ ድምጻቸዉ ከፍ ብሎ የሚሰሙ ሰወች እየተለመዱ ቀስ ብለዉ በሰከነ መንፈስ ቃለእግዚአብሔርን ለሰዉነት የሚያሰርጹ መምህራን ናአባቶቸ የተተዉበት ሁኔታ በየአዉደምህረቱ በስፋት የሚስተዋልበትና በጣሙን አሰጊ ሁኔታ ላይ የደረሰበት ጊዜ ነዉ፡፡
  ይህ ክርስቶስን አስኳል አድርገህ ስበክ የሚለዉ የተሃድሶ ስልት ምዕመኑ በአዉደምህረት ስለቅዱሳን ክብር አማላጅነት ስለገዳማት ጾም ጸሎት ምጽዋትና ስግደት ጨርሶ የተረሳ የሚመስልበት ጊዜ አናን በጣም ነዉ እያስጨነቀኘ ያለዉ፡፡እናም እባካችሁ እናተ ካህናት አባቶች በጸሎታችሁ አስቡን ነገሩልን ለእግዚአብሔር በየአዉደምህረቱ ያለዉን ነገርም ለማስተካከል የበኩላችሁን ድርሻ ተወጡ፡፡
  እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን ሃገራችንን ይባርክ፡

  ReplyDelete
 7. ስለአገልግሎትዎ እግዚአብሔር ጸጋ በረከቱን ይስጥልን፡፡በመቀጠል አንድ ጥያቄ እዲያብራሩልኝ የምፈልገዉ አንድ ሰዉ ከባለቤቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ያለበት ከሰኞ -እሁድ መቸ መቸ ነዉ? ከሚስቱ ጋር አድሮሰ /አድራ ቤተክርስቲያን ለጸሎት ሲሄዱ መከልከል የሚገባችዉ ነገር ከምንድን ነዉ?ወዴትስ ከመግባት መታቀብ ሊኖርባቸዉ ይችላል?
  ማብራሪያዉን ለሁሉም የማይለቁት ከሆነ Emailaddres, mercysn@gmail.com ቢያሳዉቁኝ ከታላቅ ደስታ ጋር ነዉ፡፡

  ReplyDelete