Saturday, February 12, 2011

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል ፭፦

ልብ በቁሙ ሲተረጐም፦ የታወቀ ሕዋስ ፥ ከንዋያተ ውስጥ አንዱ፥ በሕያው ፍጥረት ውስጥ በየደረቱ የሚገኝ የደም መሰብሰቢያ ፥ ደም ከእርሱ እየመነጨ ወደ ገላ ሁሉ የሚናኝበት ፣ የሚሰራጭበት ፥ ውስጥ ውስጣዊ ገላ ፥ የሐሳብ፣ የፈቃድ፣ የዕውቀት ምንጭ ወይም ከልብ የሚወጣ ሐሳብ፣ ፈቃድ፣ ዕውቀት ማለት ነው። ዳን ፬፥፲፮ ፣ ፯፥፬፤ ማር ፫፥፭፣ በምሳሌ ሰሎሞን ላይ ፦ «ልብ እንተ ትወልድ ኅሊና እኩየ፤ ክፉ ዐሳብን የሚያበቅል ልብ፤» የሚል አለ። ምሳ ፮፥፲፰። በወንጌለ ማቴዎስ ፦ «ለምንት ትኄልዩ እኩየ በአልባቢክሙ፤ ስለምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? » የሚል ተጽፏል። ማቴ ፱፥፬። በሉቃስ ወንጌል ደግሞ፦ ለብዙ ዘመናት አጋንንት እንደ ንብ ሰፍረውበት በሰንሰለትና በእግር ብረት ታስሮ ሲጠበቅ የነበረውን ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደፈወሰው ከተናገረ በኋላ፦ «አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ፥ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ። ያዩትም ደግሞ አጋንንት የደሩበት ሰው እንዴት እንደዳነ አወሩላቸው፤» ይላል። ሉቃ ፰፥፴፭።
          መንታ ልብ ማለት፦ ሁለት ሐሳብ መሆንን ያመለክታል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «ሁለት ሐሳብ (መንታ ልብ) ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው፤» ብሏል። ያዕ ፩፥፰። ስለዚህ ሰው የሚፈልገውን ለማግኘት አንድ ልብ መሆን አለበት። የሰው ልጅ በአምልኮተ እግዚአብሔር ለመጽናት አንድ ልብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለሥጋዊ ኑሮውም አንድ ልብ ያስፈልገዋል።
          ትዳርን የምንመኘው ፥ ስለ ትዳር የምናስበው ፥ ስለ ትዳር የምናጠናው ፥ ለትዳር የምንተጫጨው ፥ ከዚያም አልፈን ወደ ትዳር ሕይወት የምንገባው በመንታ ልብ ነው። በጥርጥር ጀምረን በጥርጥር እንጨርሳለን፤ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።» ብሏል። ያዕ ፩፥፮። ሐዋርያው እንደተናገረው ማንኛውም ሰው መንታ ልብ የሚሆነው ልቡ በጥርጥር ማዕበል ሲመታ ነው። ጓደኝነትን፦ ልጀምር አልጀምር ፥ የጀመርኩትን ላቁመው ወይስ ልቀጥልበት ፥ ወደ ትዳር ዓለም ልግባ ወይስ አልግባ ፥ እንላለን። እኛነታችን በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦች ይወጠራል። አንዱን ለመምረጥ እንቸገራለን ፥ ወይም ሁለቱንም እንመርጣለን። ማቆምም ፥ መቀጠልም እንፈልጋለን። ብዙ ጊዜ የጀመርነውን ለማቆም እንወስንና ብዙ ጊዜ ደግሞ ያቆምነውን ለመቀጠል እንወስናለን። የማልነው ፥ የተገዘትነው ሁሉ ይረሳል። ምለን ተገዝተን የቀጠልነውንም እንደገና ለማቆም ብዙ አንቸገርም። በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ሐሳባችን ሃያ አራት ጊዜ ይለዋወጣል። ቅዱስ ዳዊት፦ «አቤቱ ደግ ሰው አልቋልና ፥ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሏልና። እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ።» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፲፩ ፥፩። ስለዚህ፦ እንዲህ እንዳይሆን ልባም፥ ልብ አድራጊ ፥ ተመልካች ፥አስተዋይ፥ ብልኅ ፥ዐዋቂ ፥ ጠንቃቂ መሆን ያስፈልጋል። በመጽሐፈ ሲራክ ፦ «እነዚያ ነገር አዋቂዎች በልቡናቸው ይራቀቃሉ ፥ የተረዳ ምሳሌንም ይናገራሉ፤» የሚል ተጽፏል። ሲራ ፲፰፥፳፰። እግዚአብሔርም፦ በገሃዱ ዓለም ያለውን ቀርቶ በራእይ የተገለጠውን የረቀቀውን እንኳን የሚያስተውሉበትን ጸጋ ይሰጣል። ዳን ፱፥፳፫።
          እንግዲህ መንታ ልብ ሆነን መወሰን ካቃተን ያለን ትልቁ ተስፋ ለእግዚአብሔር አሳልፈን መስጠት ብቻ ነው። የጌታ ደቀመዛሙርት፦ ይሁዳ ወደ ገዛ  ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት አገልግሎቱና ሐዋርያነት ስፍራ ከሁለቱ (ከዮሴፍና ከማትያስ) አንዱን ለመምረጥ ዕጣውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሰጥተዋል። የሐዋ ፩፥፳፬። የትኛውን ልተው ፥ የትኛውን ልያዝ ብሎ ከመጨነቅ እንዲህ ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «እርሱ ስለእናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ጴጥ ፭፥፯።
          ከሁሉም በላይ ልብን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ይገባል። ያን ጊዜ እግዚአብሔር በመንታ ልብ ላይ የተንጠለጠለውን ልባችንን በአንድ መንገድ ይመራዋል፤ እንደ ሰማይና እንደ ምድር የተራራቀውን የእርሱን መንገድና የእኛን መንገድ ፥ የእርሱን ሐሳብና የእኛን ሐሳብ አንድ ያደርገዋል። ኢሳ ፶፭፥፰። ይኽንን በተመለከተ፦ «ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ ፥ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ።» የሚል አለ። ምሳ ፳፫ ፥ ፳፮።
፪፦ የተሸራረፈ ልብ፤
          የሰው ልጅ የተቃራኒ ፆታን ጉዳይ ማሰብ የሚጀምረው ከሕፃንነት ነው ማለት ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ ሕፃናት ዕቃ ዕቃ የሚጫወቱት ፦ እንደ ባልና ሚስት ወይም እንደ ሌባና ፖሊስ ነው። ወጣቶችና ወላጆችም በልጆች ፊት የምናወራውን እና የምንሠራውን ስለማንለይ ተፅዕኖው ቀላል አይደለም። በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፈውም ከአሥራ ስምንት ዓመት በላይና በታች የሚለው አልሠራም። በኢንተርኔት የሚለቀቀውም ገሃድ የወጣ የዝሙት መርዝም የብዙ ሕፃናትንና ወጣቶችን ፥ የጎልማሶችንና የአዛውንቶችንም አእምሮ ያኮላሸ ነው። በመሆኑም የተቃራኒ ፆታ ጓደኝነት የሚጀምረው በአብዛኛው ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው።
          አንድ ሰው፦ ወንድም ሆነ ሴት ከልጅነት ጀምሮ ከብዙ ሰው ጋር የማሳለፍ ልምድ አለው። እንደ ሸሚዝ ይቀያይራል ፥ ትቀያይራለች የሚለው አባባል የመጣው በዚህ ምክንያት ነው። መቀያየራችንም በማይረቡ ወይም በሚረቡ ምክንያቶች ባለመስማማት ወይም ዓመል አድርጎብን ይሆናል። ወይም በአፋችን ሳንናገረው ፥ በተግባርም ሳናውለው በልባችን (በሐሳብ ደረጃ) ሠላሳውን የመቀያየር ሁኔታም አለ። ይህም የልብ አመንዝራነት ነው።
          ስንቀያይርም፦ ሙሉ በሙሉ ጠልተን ሳይሆን ፥ ከመቶ አምስትም ይሁን አሥር እጅ የምንወድላቸው ወይም የሚወዱልን ነገር ይኖራል። ያን ነገር ደግሞ ከሌላው ዘንድ ላናገኝ እንችላለን። ከሌላው ዘንድ የምናገኘው ከቀደመው ያጣነው ነገርም ይኖራል። ተለያይተንም ሆነ ሳንለያይ ፦ «ይህን ነገሩን እወድለታለሁ ፥ ይኽንን ነገሯን እወድላታለሁ ፤» የምንለው ነገር አለን። የምንጠላውንም እንደዚያው ነው፥ «ይኽንን ነገር እጠላባታለሁ ፥ እጠላበታለሁ ፤» እንላለን። እንዲያውም የሚበዛው የምንጠላው ነው። እርግጥ መውድድ የማይገባንን የምንወድበት ፥ መጥላት የማይገባንንም የምንጠላበት ጊዜ አለ።
          እንዲህ ፦ ከልጅነት እስከ እውቀት ድርስ በዚህ ዓይነት መንፈስ የምናሳልፍ ከሆነ ከእያንዳንዱ ሰው ዘንድ እየተሸረፈ የሚቀር ልብ አለን ማለት ነው። እዚህም እዚያም የቀረውን ልብ ስንደምረው ከመቶ ስድሳ እጅ (60%) ሊሆን ይችላል። በመሆኑም እንደገና እድላችንን የምንሞክረው ተሸራርፎ በቀረው በአርባው እጅ (በ40%) ነው። እርሱም ቢሆን የተረጋጋ አይደለም። መቶውንም እጅ አስረክቦ በባዶ መከራውን የሚያይ የባሰበትም አይጠፋም።
          ስለዚህ በተቻለ መጠን ከመጀመራችን በፊት እንደ ሰው ማድረግ የሚገባንን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ አለብን። ከጀመርንም በኋላ እኛም ዘንድ የማይገኘውን ፍጹም የሆነ ነገር ሳንጠብቅ በትዕግሥት መቀጠል ነው። ትዕግሥት መራራ ሊሆን ይችላል ፥ ፍሬው ግን ጣፋጭ ነው። በሌላ በኲል ደግሞ የእኛን ትዕግሥት ብቻ ሳይሆን እነርሱም ለሚታገሡን ነገር ሁሉ ከፍተኛ ዋጋ ልንሰጥ ይገባል። አልሆን ብሎን ማለትም ፦ ከአቅም በላይ ሆኖብን ወይም ትዕግሥት አጥተን የጀመርነውን ለማቋረጥ ከተገደድን  በደንብ አድርጐ ማቋረጥ ነው። እርግጥ ካቋረጡ በኋላ እንደገና ጀምረው ለቁም ነገር የደረሱ ይኖራሉ። በዚያው አንፃር ወደ ትዳር ዓለም ከገቡ በኋላ ያኔ እንዳቋረጥነው በቀረ ኖሮ ብለው የሚቆጩ አሉ። ከዚህ ሁሉ የምንረዳው የሰው ልጅ ምንም ቢማር ቢመራመር ፥ ምን ጥበበኛ ቢሆን ፥ ምን ባዕለጸጋ ቢሆን ፥ የእግዚአብሔር ቸርነት ፥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ፥ የቅዱሳን ሁሉ በረከት ፥ የአበው ጸሎት ካልረዳው በስተቀር ምን ያህል ደካም እንደሆነ ነው።
፫፦ የዓይን አዋጅ፦
          የዓይን አዋጅ ማለት፦ ያዩትን ሁሉ እየተመኙ ለመምረጥ መቸገር ነው። በሌላ አነጋገር ዝም ብሎ በምኞት ፈረስ መጋለብ ነው። ይህ መንፈስ በራሱ የዝሙት መንፈስ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «አታመንዝር እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ ፥ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል፤ » ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፭ ፥ ፳፯። እንዲህ ከሆነ ማን ይተርፋል? እንል ይሆናል። እንደ ሰው (ሰው ሰውኛውን) ማንም አይተርፍም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት መትረፍ ይቻላል። የእግዚአብሔር ቸርነት መገለጫውም የእኛ ትጋት ነው። በጾም፥ በጸሎት፥ በስግደት የምንተጋ ከሆነ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ሥራውን ይሠራል። ይህም ከወጣኒነት ወደ ማዕከላዊነት ፥ ከማዕከላዊነት ወደ ፍጹምነት  በምናደርገው መንፈሳዊ እድገት ቀስ በቀስ የምንደርስበት እንጂ በአንድ ጊዜ የሚደረስበት አይደለም። ይህን አንቀጽ በተመለከተ፦ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፦ የሰው ልጅ ከዝሙት እንዲርቅ አርቆ ሲያጥር ነው፤» ይላሉ። ይኸውም፦ «አይቶ መመኘቱ ዝሙት ከሆነ ፥ ግብሩን መፈጸምማ ምን ያህል ይከፋ፤» ብለው ፈጽመው እንዲሸሹ ለማድረግ ነው።
          የዓይን አዋጅ ያለብን ሰዎች የራሳችን የምንለውን መርጠንም ዓይናችንም ልባችንም አያርፍም። ከዚያም በላይ አግብተንም ከችግሩ ለመላቀቅ እንቸገራለን። ከመረጥናቸው ጋር አብረን እየሄድን ፥ አብረን ተቀምጠንም ዓይናችን ሌላውን ያማትራል። ዓይነ ልቡናችንም እንደዚያው ነው። ከዚህ የተነሣ በየመንገዱ ፥ በየግብዣው ቦታ ተጣልተን ተኳርፈን የምንለያይ ሰዎች አለን። «አፍጥጠህ የምታየው ፥ አፍጥጠሽ የምታዪው ማንን ነበር? ምን ግንኙነት አላችሁ? እየተባባልን እንዲሁ ስንቋሰል የምንኖር ወይም ተቋስለን የምንለያይ ፥ እየተፈላለግን ክፉ ዓመል ያራራቀን ጥቂቶች አይደለንም። «ክፉ ጠባይ ከሰይጣን ይከፋል፤» የሚሉት አባባል አለ።
          አጋነንክ አትበሉኝ እንጂ የሠርጋቸው ዕለት ከሚዜዎች ጋር በዓይን የሚነጋገሩ ሙሽሮች አሉ። በሂደትም፦ «ሚዜዬ፦ ባሌን ቀማችኝ ፥ ሚስቴን ቀማኝ፤» የሚል ዜና አልፎ አልፎ ሲነገር ይሰማል። አብዛኛው ግን በአበሻ ይሉኝታ ተሸፍኖ ይቀራል። ከጋብቻም በፊት፦ «ሳይቸግረኝ ከሴት ጓደኛዬ አስተዋውቄው ጉድ ሠራኝ ፥ ሳይቸግረኝ ከወንድ ጓደኛዬ አስተዋውቂያት በጎን ሌላ ነገር ጀመሩ፤» የሚለው ጸጸት ያንኳኳው ደጅ ብዙ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «አቤቱ ደግ ሰው አልቋልና ፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሏልና፤ » ያለው ይኽንን ነው። መዝ ፲፩ ፥፩። ሰውን ማፈር እግዚአብሔርን መፍራት ጠፍቷል።
          አልፎ አልፎም የሚያጋጥም ነገር አለ። ከታላቋ ጋር የጀመሩትን ግንኙነት አቁመው ከታናሿ ጋር የሚቀጥሉ አሉ። በሴቶችም በኲል ከታላቅየው ጋር የጀመሩትን አቁመው ከታናሹ ጋር የሚቀጥሉ አሉ። ወይም በዝሙት መንፈስ ሰክረው በስውር ከወንድማማቾች ጋር ወይም ከእኅታማማቾች ጋር ድብብቆሽ የሚጫወቱ አሉ። ይህም የሚያመለክተው የድፍረት ኃጢአት መብዛቱን ነው።
          ንጉሥ ዳዊት ብዙ ሚስቶችና እና ብዙ ቁባቶች እያሉት ፥ የባለሟሉን የኦርዮንን ሚስት ቤርሳቤህን አይቶ የተመኘው ፥ የተመኘውንም በተግባር የፈጸመው (ቤርሳቤህን ያስነወረው) ፥ ጽንስ ለማሳሳት መከራውን ያየው ፥ ከዚያም አልፎ ኦርዮንን በጦር ሜዳ ያስገደለው ፥ ተቸግሮ ሳይሆን የዓይን አዋጅ ሆኖበት ነው። ፪ኛ ሳሙ ፲፩፥፲፪። ይኽንን በተመለከተ፦ «ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት፤» የሚል አባባል አለ። ስለሆነም እንደዚህ ልንሆን አይገባም። እኛ የምናየው መልክን ነው ፥ ልብን አይደለም። ልብን ማየት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው ፥ እርሱ ልብ ያሰበውን ኲላሊት ያጤሰውን ያውቃል። ቅዱስ ዳዊት፦ «እግዚአብሔር ልቡናን እና ኲላሊትን ይመረምራል፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፯፥፱። ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር፦ «ሰው ፊትን ያያል ፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል፤» በማለት ለነቢዩ ለሳሙኤል ነግሮቷል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፯።
          እንግዲህ በክርስትና ሕይወት «እንዴት ይቻላል?» እንደማይባል ማወቅ ብቻ ሳይሆን አምነን፦ «ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ፤» ልንል ይገባል። ፊል ፬፥፲፫። ይህ ኃይል መንፈሳዊ እንዲያድርብንም በቤተ ክርስቲያን መቆየት፥ በጾም በጸሎት ደጅ መጥናት ያስፈልጋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን፦ «አባቴ የሰጠውን ተስፋ (ጸጋ መንፈስ ቅዱስን) እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤» ብሏቸው ነበር። እነርሱም ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ። ሉቃ ፳፬፥፵፱-፶፫። በደጅ ጥናት በመቆየታቸውም ፦ ጸጋው ተሰጥቷቸዋል። የሐዋ ፪፥፩። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ ፥ አይደክሙም፤» ብሏል። ኢሳ ፵፥፴፩።
፬፦ የዕድሜ ማነስ፦
          በእጮኝነት ዘመን የእድሜ ማነስ በራሱ ችግር ነው። በዕድሜ ያልበሰሉ አዳጊ ወጣቶች፦ ግራ ቀኙን ለማየት ፥ ነገሮችን ለማመዛዘን ፥የነገን ኪሳራና ትርፍ ለማየት ይቸገራሉ። ዛሬ ላይ ሆነው ነገን ለማየት ቀርቶ ዛሬ ላይ ሆነው ዛሬን ለማየት ይሳናቸዋል። ፍላጐታቸው ያለው ዓይናቸውና ጆሮአቸው ላይ ነው። ባዩት በሰሙት ነገር ሁሉ ቶሎ ይማረካሉ። «ለዓይን ቅንድብ አይታየውም፤» እንደሚባለው፦ እንኳን የሩቁ የቅርቡ ይሰወርባቸዋል። በአጠገባቸው በወንድሞቻቸውና በእኅቶቻቸው ላይ ከተፈጠረው ችግር አይማሩም። እንዲያውም እንደ ችግር አይቆጥሩትም።
          በልጅነት እንደ ልጅ ማሰብ ሲገባ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን እንደደረሱ ታላላቅ ወጣቶች የማሰብ ኹኔታ አለ። ይህም ከማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል። ምክንያቱም ያለጊዜው የሚዘንብ ዝናብ በማሳ ላይ ያለውን ሰብል ገና ሳይዘረዝር በቡቃያነቱ እንደሚያጠፋው ሁሉ፥ ያለ ዕድሜ የሚጀመር የተቃራኒ ፆታ ግንኙነትም ለብዙ አዳጊ ወጣቶች መቅሠፍት ነው። ሕይወታቸውን ያመሰቃቅለዋል ፥ ገና በጧቱ በዝሙት ይወድቃሉ፤ የልጅ ጠባይ ሁሉን ልያዘው ፥ ሁሉን ልሞክረው ስለሆነ ውጤት የማያመጣ ቤተ ሙከራ ይሆናሉ። ይህም ግላዊ ኑሮአቸውን ቤተሰባዊና ማኀበራዊ ግንኙነታቸውን ፥ ከሁሉም በላይ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ያናጋዋል።
          ልጆች በትንሽ ነገር ይደለላሉ። በመሆኑም ይኽንን የሚያውቁ ታላላቅ ወጣቶች በዕድሜ ያልበሰሉ የብዙ ወጣቶችን ሕይወት አጨልመዋል። ይህ ነገር በተለይም ባዕለጸጎችና ባለሥልጣኖች ወደ ሆኑ አባቶች አድጎ ከልጅ ልጆቻቸው ጋር በመቅበጥ በአበባነታቸው እያረገፏቸው ነው። አንዴ ከሆነ በኋላ በሚል ቀቢጸ ተስፋም የብዙ ልጆች ሕይወት ተሰነካክሎ ቀርቷል። ይህም ከዘመኑ በሽታ ጋር ተደምሮ እንደ ሰደድ እሳት በመቀጣጠሉ ዓይናችን እያየ አንድ ትውልድ እየጠፋ ነው። በዚህ ውስጥ ያለፉ ወጣቶች ለምንም ነገር ግድ የላቸውም። ምክንያቱም አንድ ሕንፃ ምን ታላቅ ቢሆን መሠረቱ ላይ ብልሽት ካለው ነገ ፈርሶ የድንጋይ ክምር መሆኑ አይቀርም።
          ስለዚህ መሠረቱ እንዳይበላሽ ልጆች በልጅነታቸው እንደ ልጅ እንዲያስቡ፥ ከወላጆችም ከቤተ ክርስቲያንም ብዙ ይጠበቃል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን፦ « ግልገሎቼን አሰማራ፤ . . .  ጠቦቶቼን ጠብቅ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፩፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ «እናንተም አባቶች ሆይ ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጓቸው እንጂ አታስቆጧቸው፤» ብሏል። ኤፌ ፮፥፬። በልጅነት እንደ ልጅ ማሰብ እንደሚገባም፦ «ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር ፥እንደ ልጅም አስብ ነበር ፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር ፤ ጐልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ፤» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፲፫፥፲፮። የእኛ ችግር ከክፉ ነገር አንፃር ልጅ ሆነን እንደ ጎልማሳ ማሰባችን ነው ፥ ጎልማሳ ሆነን ደግሞ ፦ «የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ ፥ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ፤ » እንሆናለን።
          እንግዲህ ከአዳጊ ወጣትነት ወደ ሙሉ ወጣትነት የምንደርሰው ጨርሶ የተበላሸ ሕይወት ወይም ባለማስተዋል የቆሰለ ሕይወት ይዘን ነው። ይህም የዛሬውንም ሆነ የነገውን ኑሮአችንን የሚያበላሽ ነው። በመሆኑም ይህ ቊስል እንዲሽር ፥ ጠባሳውም እንዲጠፋ ሕክምና ያስፈልገዋል። ሕክምናውም ምክር መንፈሳዊ ነው። ይኽንን በተመለከተ ቅዱስ ዳዊት፦ «ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር ፥ ምክር ሠናይት ለኲሉ ዘይገብራ ፥ ወስብሐቲሁኒ ይነብር ለዓለም፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ፥ ለሚሠራት (ለሚያደርጋት ፥ ለሚጠቀምባት) ሁሉ መልካም ምክር በጎ ትምህርት ናት፥ ጌትነቱ ለዘላለም ሲነገር ይኖራል፤ » ብሏል። መዝ ፻፲፥፲።
          የምክር አገልግሎት በአብዛኛው በንስሐ አባቶች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው፤ እርሱም፦ ለንስሐ ለቀረቡት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በሰንበት ት/ቤት ደረጃ ታስቦበት በዚህ በኲል ትልቅ ሥራ መሥራት ይገባል። የሕፃናት ክፍል መቋቋሙ፦ ለመዝሙር ጥናት ብቻ ሳይሆን ልጆች በልጅነታቸው ችግር ላይ እንዳይወድቁ በምክር መንፈሳዊ የሚጠበቁበት ሊሆን ይገባል። ምክሩም እርስ በርስ ሳይሆን በታላላቅ ወንድሞችና አባቶች ቢሆን ይመረጣል። ከዚህም ጋር አገልግሎቱ መፈጸም ያለበት በመላ ምት ሳይሆን በጥናት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። በዕድሜና ፥ በትምህርት ደረጃ እየከፋፈሉ ከታች እስከ ላይ ወጥ የሆነ ተከታታይ ት/ት መስጠት ያስፈልጋል።
፭፦ የዕድሜ መግፋት፦
          የዕድሜ መግፋት ያልኩት፦ ቅዱስ ዳዊት፦ «የዘመኖቻችንም እድሜ ሰባ ዓመት ፥ ቢበረታም ሰማንያ ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ » ያለውን አይደለም። መዝ ፹፱፥፲። የጋብቻ ዘመን መተላለፍን ነው ፥ «ቆሞ ቀረ ፥ ቆማ ቀረች፤» የሚባለውን ነው። ይህ ዘመን በተለይ ለእኅቶቻችን፦ የስጋትና የጭንቀት ጊዜ ነው። ባለፈው የሚቆጩበት ፥ ባሉበትም ሆነ በሚመጣው በአብዛኛው ተስፋ የሚቆርጡበት ፥ የሚበሳጩበት ፥ ከራሳቸውም ከሌላውም የማይግባቡበት ወቅት ነው።
          አንዳንዶቹ ከልጅነት ጀምሮ ትዳር እየፈለጉ አልሳካ ብሏቸው ፥ ታማኝ ሰው አጥተው ነው፤ የሚያጋጥማቸው ሁሉ ቁም ነገር ላይ ሲሆን ወገቤን የሚል ነው፤  ቀረብኩ የሚለው ሁሉ በኃጢአት መንገድ ለሥጋ ፍላጎቱ ብቻ ነው፤ ወይም እዚህም እዚያም የሚያምታታ፥ ሰውን የማያፍር እግዚአብሔርንም የማይፈራ ነው። አንዳንዱ ከቤተሰብ ተዋውቆ ቤተኛ ከሆነ በኋላ ያፈገፍጋል ፥ ሌላው ሽማግሌ ልኮ ቤተሰብን «እሺ፤» ካሰኘ በኋላ ቀኝ ኋላ ሳይሆን ግራ ኋላ ይዞራል ፥ የባሰበት ደግሞ ቀለበት ካሰረ በኋላ የውኃ ሽታ ሆኖ ይቀራል። ከዚህም የባሰበት አለ ፥ እርሱም፦ የሠርግ ቀን ተቀጥሮ ፥ ድግስ ተጀምሮ  ፥የጥሪ ካርድ ተዘጋጅቶ ፥ የአዳራሽ ኪራይ ተከፍሎ ፥ ለዘመድ አዝማድ ተነግሮ እንደ ዋዛ ትቼዋለሁ ይላል። በዚህ ዓይነት ሦስት እኅቶችን አውቃለሁ ፥ ሦስቱም የቤተክርስቲያን ልጆች ናቸው። ከወንዶችም እንዲህ ዓይነት መከራ የወረደባቸው ፥ የሠርጋቸውን ዕለት በናፍቆት ሲጠብቁ መርዶ የመጣላቸው ወንድሞች አሉ። ከዚህም ሌላ በእጮኝነት ዘመን ለምን ኃጢአት አንሠራም ብለው የብዙ ዘመን እጮኛቸውን ጥለው የሚሄዱም አልጠፉም። «ነገር ሁሉ ለበጎ ነው፤» የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ቃለ ትምህርት ያጽናናል እንጂ ነገሩስ ከባድ ነው።
          አንዳንዶቹ፦ ምርጫ ማስተካከል አቅቷቸው አቃቂር እያወጡ ፥ አንዱን ሲጥሉ አንዱን ሲያነሡ ፥ ያነሡትን መልሰው ሲጥሉ የትዳር ቀናቸው ይመሽባቸዋል። ከመሸ በኋላም የቀደመውን ቢናፍቁ አያገኙትም፥ በመጨረሻም፦ «መራጭ ከምራጭ ላይ ይወድቃል፤» እንደተባለው ይሆናሉ፥ አልፎ አልፎም ምራጩም የሚጠፋበት ጊዜ አለ። እንደነዚህ ዓይነቶቹ፦ ወይ በዘራቸው ፥ ወይ በትምህርታቸው ፥ በይ በመልካቸው የሚኮሩ ናቸው። ጨክነው ካገቡም፦ በዘራቸው ፥ በዕውቀታቸው ፥ በመልካቸው እየተመጻደቁ ፥ ለእኔ አትገባም ነበር ፥ ለእኔ አትገቢም ነበር ፥ አትመጥነኝም ፥ አትመጥኚኝም ፥ እነ እገሌ ጫማ ልሰው ለምነውኝ ነበር፤» እየተባባሉ ሲቋሰሉ ይኖራሉ፥ ወይ ይፋታሉ።
          እንዳንዶቹ ደግሞ ፦ እንዲሁ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ድንገት የመሸባቸው ፥ ሳያውቁት ቀኑ እንደ ዕለተ ሞት ፣ እንደ ዕለተ ምጽአት የደረሰባቸው ናቸው። ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ይደነግጣሉ ፥ መንፈሳቸው ይረበሻል፥ መረጋጋት ያቅታቸዋል። በዚህን ጊዜ ምንም ይሁን የተገኘውን ለማስተናገድ ይገደዳሉ ፥ ለመጋባትም ይጣደፋሉ ፥ ነገራቸው ሁሉ፦ «የነቶሎ ቶሎ ቤት ዳር ዳሩ ሰንበሌጥ ፣ የቸኮለ አፍሶ ለቀመ፤» ይሆናል። ከጋብቻው ዕለት ጀምሮም የልጅ ነገር ያሳስባቸዋል።
          አንዳንዶቹ በተለያየ ዓላማ ምክንያት ይዘገያሉ፤ በትምህርት ምክንያት ፥ ቤተሰብ ለመርዳት ፥ ወንድምን እኅትን ለማስተማር ሲሉ እያወቁትም ሳይታወቃቸውም ጊዜው ይገሰግሳል። ከዚህ በኋላ መነጫነጭ ይጀምራሉ፥ በተለይም ብዙ የተደከመላቸውና መሥዋዕት የተከፈለላቸው ሰዎች እንደተደከመላቸው ካልሆኑ ፥ «እስከዚህ ድረስ ምን አድርገህልኝ ፥ ምን አድርገሽልኝ ነው?» እያሉ፦ እጃቸውን አመድ አፋሽ ካደረጉባቸው ቅስማቸው ይሰበራል ፥ ሐሞታቸው ይፈስሳል። በጨዋነት ቢኖሩም በዓላማ የሚቀርባቸው ይጠፋል። በዚህም ላይ « አታገባም እንዴ? አታገቢም እንዴ?» የሚለው የዘመድም የባዕድም ጭቅጭቅ ቀላል አይደለም። በሀገር ቤት «የወንድ ደሞዝ እና የሴት ዕድሜ አይጠየቅም፤» ይባላል ፥ በውጪው ዓለም ግን አይሠራም ፥ ከመታወቂያ ጀምሮ እያንዳንዱ ነገር አሳባቂ ነው።
          በሰከነ አእምሮ ስንመለከተው የዕድሜ መግፋት ጋብቻ ከልክል አይደለም፤ የሰው ልጅ በዕድሜው እየገፋ በሄደ ቁጥር የማስተዋል አድማሱ እየሰፋ ይሄዳል። የተረጋጋ መንፈስ ይኖረዋል ፥ ነገሮችን በቁጣ ሳይሆን በትዕግሥት ፥ በጭቅጭቅ ሳይሆን በውይይት ለመፍታት ይሞክራል። የልጅም ነገር ቢሆን እምነቱ እስካለ ድረስ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ፤ እንኳን በአርባዎቹ ያሉት ቀርቶ አሮጊቷ ሣራም በተአምር ይስሐቅን ወልዳለች ፥ አብርሃምም የመቶ ዓመት ሰው ነበር። ዘፍ ፳፩፥፪። ቅድስት ኤልሳቤጥም በስተ እርጅና መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ወልዳለች ፥ ካህኑ ዘካርያስም ዕድሜ የተጫነው ሽማግሌ ነበር። ሉቃ ፩፥፲፰።
          እንግዲህ ሁሉ ነገር ካለፈ በኋላ ከመጸጸት ጊዜውን ጠብቆ በጊዜው ማድረጉ ይመረጣል። ይኽንን በተመለከተ፦ ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «ለሁሉ ዘመን አለው ፥ ከፀሐይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው ፥  ለመፅነስ ጊዜ አለው ፥ ለመውለድም ጊዜ አለው ፤ ለመኖር ጊዜ አለው ፥ ለመሞትም ጊዜ አለው ፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው ፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው ፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው ፥ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው ፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ ድንጋይን ለመወርወር ጊዜ አለው ፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው ፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው ፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው ፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው ፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው ፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው ፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው ፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው ፥ ለሰላምም ጊዜ አለው፤» ብሏል። መክ ፫፥፩-፰።

7 comments:

 1. Kale Hiwoten Yasemalen!!!

  ReplyDelete
 2. እግዚአብሔር ይስጥልን አሜን፡፡

  ReplyDelete
 3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 4. kale howot yasemalin.
  Silegabicha siriatim endiker entebkalen.(silekurbani na Teklil)

  ReplyDelete
 5. kalehiwot yasemalin kesis የዓይን አዋጅ endet yiwegedal,

  ReplyDelete
 6. ቃልከ ግርምት (ለእለ ያኀሥሙ ፍኖቶሙ)
  ወትምህርትከ ጥዕምት (ለእለ ያጸምዑከ በትሕትና)
  ወምክር ይእቲ ሠናይት፡፡ (ለኵሉ ዘይገብራ)

  ReplyDelete
 7. Kale hiwot Yasemalin!!!

  ReplyDelete