Friday, January 7, 2011

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል፦ ፬

፩፦ መገባበዝ፤
          በማንኛውም ኅብረተሰብ ዘንድ በየምክንያቱ መገባበዝ የተለመደ ግብር ነው። ግብዣው እንደየሰዉ ኹኔታ፦ ከአቅም በታች ፥ በአቅም ፥ ከአቅም በላይ ሊሆን ይችላል። የግብፅ ንጉሥ ፈርኦን የልደት በዓሉን በቤተመንግሥት በሚደረግ ታላቅ ግብዣ ያከብር ነበር። ዘፍ ፵፥፳። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም እንዲሁ ያደርግ ነበር። ማቴ ፲፬ ፥፮። ሠርግ ደግሶ ማብላት ማጠጣትም ከጥንት ጀምሮ የተለመደ ነው። ላባ ሴት ልጁን ልያን ለያዕቆብ በሰጠበት ዕለት ለአካባቢው ሕዝብ ታላቅ ግብዣ አድርጓል። ዘፍ ፳፱፥፳፪። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ፥ እመቤታችንና ደቀመዛሙርቱ በተገኙበት ሠርግ ተደርጓል። በዚህ ሠርግ ላይ የእመቤታችን አማላጅነት ፥የጌታችን ተአምራት ተገልጧል። ዮሐ ፪፥፩-፲፩። ገበሬዎች ደግሞ፦ በእርሻ ፥ በዘር ፥ በመከር ጊዜ እየተረዳዱ በጋራ ስለሚሠሩ እንደ አቅማቸው ይደግሳሉ። ምእመናንም በጌታ ፥ በእመቤታችንና በቅዱሳን መታሰቢያ ዕለት ጠበልና ጻድቅ በማዘጋጀት ያዘክራሉ። ይኸውም፦ «የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤. . . . ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀመዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።» ያለውን ይዘው አምነው ነው። ምሳ ፲ ፥ ፯ ፣ ማቴ ፲፥፵፪።
          በመግቢያዬ ለመግለጥ የሞከርኩት ግብዣ የሚደረገው ለደስታና ለበረከት መሆኑን ነው። ከዚህም ሌላ ዘመድ ከዘመዱ ፥ ጐረቤት ከጐረቤቱ ፥ ባልንጀራ ከባልንጀራው እየተጠራሩ መገባበዝ ሥር የሰደደ የአገራችን ባሕል ነው። በመሆኑም በዚህ ባሕል ውስጥ ተወልደን ያደግን ሰዎች ፦ በመጠናናትና በመተጫጨት ዘመን እንደ ጾምና ጸሎት የሥራ መጀመሪያ የምናደርገው እርስ በርስ መገባበዝን ነው። ግብዣውም፦ ከታናናሽ ኬክ ቤቶች እስከ ታላላቅ ሆቴሎች ይዘልቃል። ኬክ ቤቶችንም ቢሆን ለምዶብን ታናናሽ አልናቸው እንጂ ወጪያቸው ኪስ አስደንግጥ ነው። ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰብ ለእግዚአብሔርም የሰሰትነውን ገንዘብ ለዚህ ሲሆን ዓይናችንን አናሽም። በአብዛኛው አቅማችንን ያገናዘበ አይደለም።
          ግብዣው በሁለታችን ብቻ የሚቆም አይመስልም። «የወንድ ጓደኛዬን ፥ የሴት ጓደኛዬን ተዋወቁ፤» በሚል ወደ ባልንጀራም ፥ ወደ ቤተሰብም እየዘለቀ ስለሚሄድ ግብዣውን መለስተኛ የጽዋ ማኅበር ያደርገዋል። «ይህ እጮኛሽ አይደማውም ፥ ይህች እጮኛህ አይደማትም፤» እያሉ የሚገፋፉ ፦ «የእነ እንብላው የእነ እንብላት ፤» ቡድኖችም ቀላል አይደሉም፦ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሽሮ ልትጋብዟቸው ብትወስዷቸው ሥጋ ወጥ ያዛሉ ፥ ለሥጋ ወጥ ብትወስዷቸው ክትፎ  ያዛሉ፤ ለሻይ ቡና ብትወስዷቸው ቢራ ፥ለቢራ ብትወስዷቸው ውስኪ ያዛሉ። ይሉኝታ የሚባል ነገር የለም። በልጋብዝሽ ፥ በልጋብዛቸው ይጀመርና ፦ አትጋብዘኝም እንዴ? አትጋብዛቸውም እንዴ? በሚል ይደመደማል። መወደድ ፥ መፈቀር የምንፈልገው በግብዣው ጥራትና ትልቅነት በመሆኑ ችግር ውስጥ እንወድቃለን። ሲጀመር፦ በዓታ ለማርያም ፥ ግቢ ገብርኤል ፥ቅድስት ማርያም ፥ምስካየ ኅዙናን ሠርክ ጉባኤ ላይ እንገናኝ እንዳልነበር ፦ «የቤት ምግብ ሰልችቶኛልና፦ መገናኛ ክትፎ ቤት ፥ቦሌ ኬክ ቤት እንገናኝ ይባላል። በውጭው ዓለም ደግሞ አበሻ የማይበዛበት ወይም አበሻ ፈጽሞ ዝር የማይልበት ቦታ እንገናኝ እንላለን። በአንድ ጊዜ ከመንፈሳዊ ማዕድ ወደ ሥጋዊ ማዕድ ይወረዳል። «አቅሜ አይችልም፤» ማለት ሽንፈት ይመስለናል። ወይ ዕዳ ውስጥ እንገባለን ፥ ወይም በምክንያት ሽሽት እንጀምራለን። ይሁን እንጂ እዳውም ሆነ ሽሽቱ ችግሩን በአሸናፊነት መወጣት አይደለም።
          እንዲህ ዓይነቱ ልምድ ችግሩ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን  ለነገም ነው። ዛሬ በሰፊው ተለምዶ ነገ ጠበብ ካለ ፈተና ይሆናል። ምክንያቱም ልማድ ከሰይጣን ይከፋልና፤ ገቢያችንን እያወቅን ዓይናችን የለመደውን ይናፍቃል ፥ ሆዳችንም አምጡ አምጡ ይለናል። አቅሙ ኖሮ ከቤት ቢሠራም አይጣፍጠንም። ብዙ ሰዎች እንደ ወንደ ላጤና እንደ ሴተ ላጤ ውጪ ውጪውን የምንለው ለዚህ ነው። በየግልም ድብብቆሽ ይጀመራል። ወንዱም ቋጥሮ የሄደውን ምሳ ለዘበኛ ሰጥቶ ቄራ እንደለመደ ውሻ ይሆናል። ሴቷም በበኲሏ ከቤት ወጪ ቀነጣጥባ በፊናዋ ትጓዛለች። ከደሞዝም ቢሆን ቆረጥ ተደርጐ በመዋጮ ይሳበባል።ምክንያቱም በየመሥሪያ ቤቱ ፥ በየሠፈሩ የመዋጮው ዓይነት በየቀኑ እየጨመረ ነውና።
          የእኔ ዓላማ ግብዣን መቃወም አይደለም። ስለ አቅማችንም በግልፅ ተነጋግረን ፥ የምናደርገው ሁሉ አቅምን ያገናዘበ ይሁን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ልጁን ጢሞቴዎስን « ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤» እንዳለው፦ ነገራችንን ሁሉ በልክ ልናደርገው ይገባል ነው። ፪ኛ ጢሞ ፬፥፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመጠን እንድንኖር አስተምሮናል። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፫። ስለዚህ፦ «ብዙ ደስታ ከሞላበትና ከክርክር ጋር የዐመፃ ፍሪዳ ካለበት ቤት ይልቅ ከሰላም ጋር ደረቅ ቊራሽ ይሻላል።» ያለውን የጠቢቡን ቃል ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። ምሳ ፲፯፥፩። ተርፏቸው ከሚበትኑም ጋር መፎካከር የለብንም። ይኽንንም በተመለከተ ፦ «አንተም ደሀ ስትሆን ከባለጠጋ ጋር አትወዳደር፤ »ብሎናል። ምሳ ፳፫፥፬። ሀብታሙም ቢሆን እግዚአብሔር የሰጠውን በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባዋል እንጂ በግብዝነት እንዲበትነው አልተፈቀደለትም። ከዚህ ይልቅ የእግዚአብሔርን አሥራት ማውጣት ፥ የደሀን ምጽዋት መስጠት የሃይማኖት ሥራ ነው። እንዲህ ካልሆነ ግን ድሆች ይከሱናል። ሉቃ ፲፮፥፪። እግዚአብሔርም፦ «ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኲራት ነው። እናንተ ይህ ሕዝብ ሁሉ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። » ይለናል። ሚል ፫፥፰።
          እጅግም ስስታምና ንፉግም መሆን አይገባም። በመጽሐፈ ሲራክ፦  « ሦስት ዓይነት ሰዎችን ሰውነቴ ፈጽማ ጠላቻቸው፤ ኑሮአቸውም እጅግ አበሳጨኝ፤ እነዚህም ትዕቢተኛ ደሀ ፥ ንፉግ ባዕለጸጋና አእምሮ የሌለው ሴሰኛ ሽማግሌ ናቸው።» የሚል ተጽፏል። ሲራ ፳፭፥፪። ጠቢቡ ሰሎሞንም፦ «ከስስታም ሰው ጋር አትመገብ ፥ ምግቡንም አትመኝ፤ ሣርን እንደሚበላ ይበላል፥ ይጠጣልም፤ ወደ አንተም አታስገባው ፥ ከእርሱም ጋር እንጀራ አትብላ፤ ብላ ፥ ጠጣ ፥ ይልሃል፥ ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም። የበላኸውን ትተፋለህ ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋለህ።» ብሏል። ምሳ ፳፫፥፮። እንግዲህ፦ እንደ ትዕቢተኛ ደሀ ከመጠን በላይ ሳንሆን ፥ እንደ ስስታም ባዕለጸጋም እጅግ ከመጠን በታች ሳንወርድ ሁሉንም ነገር በመጠን ፥ በልክ ልናደርገው ይገባል። መገባበዛችንም በግብዣ ብዛት አሸንፈን ለመፈቀር ወይም በግብዣ ብዛት ተሸንፈን ለማፍቀር ሳይሆን መሠረታዊው ዓላማ ላይ ልናተኲር ያስፈልጋል። ያን አጋጣሚም በነፃነት የምንወያይበትና የምንመካከርበት መድረክ ብናደርገው ይመረጣል። ከሁሉ ይልቅ ሊፈቀር የሚገባው የሰው ልጅ ነው፤ አለበለዚያ ግብዣው ሲቀንስ የሚቀንስ ፥ ሲቀርም የሚቀር ፍቅር ይሆናል።
ስጦታ መለዋወጥ፤
          በዓላትንና የሥራ ጊዜያትን ተንተርሶ ስጦታ መለዋወጥ የተለመደ ነው። አይሁዳዊው መርዶክዮስ ፦ በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ ፥ በቅርብና በሩቅ ወዳሉት አይሁድ ሁሉ ፥ በጻፈው ደብዳቤ፦ በየዓመቱ አዳር (መጋቢት) በሚባለው ወር በአሥራ አራተኛውና በአሥራ አምስተኛው ቀን ፥ አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙበት ቀን ፥ ወሩም ከኀዘን ወደ ደስታ ፥ከልቅሶም ወደ መልካም ቀን የተለወጠበት ወር ሆኖ ይጠብቁት ዘንድ ፥ የግብዣና የደስታም ቀን ፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበትና ለድሆች ስጦታ የሚሰጡበት ቀን እንዲያደርጉት አዝዟቸዋል። አስ ፱፥፳-፳፪። በዚህ ብቻ ሳይሆን ከበጎ አገልግሎት ዋጋ ጋር እንደ ተጨማሪ አድርጐ የሚሰጥበትም ጊዜ አለ። ዳን ፪፥፮። እንደ እጅ መንሻ ሆኖም ይቀርባል። ምሳ ፲፰፥፲፮።
          በመንፈሳዊውም ረገድ ለመንፈሳዊ አገልግሎት አንዲውል ስጦታ ይሰጣል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጻፈው መልእክቱ፦ «በጌታችን እጅግ ደስ አለኝ ፤ ቢሳናችሁ እንኳን አሁንም እንደምታስቡልኝ ፥ ከድሮ ጀምሮ ለእኔ ችግር ታስቡ ፥ትተጉም ነበርና። ይህን የምለው ስለአጣሁ አይደለም፤ ያለኝ እንደሚበቃኝ አውቃለሁና። እኔ ችግሩንም ምቾቱንም እችላ ለሁ፤ ራቡንም ፥ ጥጋቡንም ፥ማዘኑንም ፥ደስታውንም ፥ሁሉን በሁሉ ለምጄዋለሁ፤ በሚያስችለኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላ ለሁ። ነገር ግን በመከራዬ ጊዜ ተባባሪዎች መሆናችሁ መልካም አደረጋችሁ። እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች፦ በመጀመሪያው ትምህርት ከመቄዶንያ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትም ቢሆን ፥ በመቀበል ከእኔ ጋር እንዳልተባበሩ ታውቃላችሁ። በተሰሎንቄም ሳለሁ ደግሞ ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ላካችሁልኝ። ይህንም የማነሣ ሣው ስጦታችሁን ፈልጌ አይደለም፤ በእናንተ ላይ የጽድቅ ፍሬ ይበዛ ዘንድ ፈልጌ ነው እንጂ።» ብሏል። ፊል ፬፥፲-፲፯።
          የስጦታ ዓላማ ከእነዚህ የወጣ አይደለም። በመጠናናትና በእጮኝነት ዘመንም ልክ እንደ ግብዣው ትልቁን ሥፍራ ይዞ የሚቆየው ስጦታ ነው። ከዓውደ ዓመት ካርድ ጀምሮ እስከ ወርቅ ድረስ ስጦታ ይዥጐደጐዳል። በልብስም በኲል፦ ከካልሲ ከከነቴራና ከሻሽ ጀምሮ የማይሰጥ የለም። የሚገዛውም ውድ የሆነ ተፈልጐ ነው። ይህም፦ ሌላኛውን አካል ከማስደሰት አንፃር እንጂ ከአቅም እንፃር አይመስልም። ተበድረንም ሆነ ተለቅተን እናደርገዋለን። ያላቸውማ ውድ ውድ የሆኑ ስጦታዎችን በገፍ ይለዋወጣሉ። ፍቅርን ቁሳዊ ያደርጉታል። «እድሜ ለገንዘቤ፤» እያሉ ሸቀጥ ያስመስሉታል። ብዙዎቹ በመጠናናት ጊዜ እንደማይኳኳኑ ልባቸው እያወቀ በዚያው የሚገፉበት የስጦታው ብዛት በይሉኝታ ስለሚያስራቸው፥ አፋቸውንም ሸብቦ ስለሚይዛቸው ነው። በኋላም «እንዲህ አድርጌልህ ፥ እንዲህ አድርጌልሽ ፥» እያሉ፦ ወይ መኲራሪያ ወይ መወቃቀሻ ያደርጉታል።
          አሁንም ዓላማዬ ስጦታን ለመቃወም አይደለም። ስጦታ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገባኛል። ነገር ግን መስመሩን የለቀቀ ወይም መንገዱን የጣሰ መሆን የለበትም ፥ የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ በግብዣው ጉዳይ ላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ በመጠን በልክ ልናደርገው ይገባል። ወደፊት፦ ሠርግና ጐጆ መቀለስ፥ ብዙ የትዳር ጣጣም እየጠበቀን ራሳችንን ልናደክም አይገባም፥ ደሀ ላለመምሰልም መፍጨርጨር የለብንም፥ ጌታ እንኳ በወንጌል ያደነቀው የደሀይቱን ስጦታ ነው። ማር ፲፪፥፵፬። ስለዚህ ክርስትና ማለት ክርስቶስን መምሰል ስለሆነ ቆም ብለን ራሳችንን ማየት አለብን። ባዕለጸጎችም ብንሆን በመንፈስ ራሳችንን ደሀ ማድረግ ይጠበቅብናል። ጌታ በወንጌል፦ «በመንፈስ ነዳያን የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና። » ብሏል። ማቴ ፭፥፫። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን ፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ደሀ ሆነ፤» ብሏልና። ፪ኛ ቆሮ ፰፥፱። ብዙ የዋሃንም በመጠናናትና በእጮኝነት ዘመን የለመድነው ሁሉ ከጋብቻ በኋላም እንዲጓድልብን ስለማንፈልግ ለነገም ችግር እያቆየን እንደሆነ አይገባንም።
          ከሁለት አንዳችን ፦ በአቅም ማነስ ወይም በመዘንጋት ወይም ለተሻለ ነገር በማሰብ ያስለመድነውን ስጦታ ብናስታጉል፦ ቅዳሴ የታጐለ፥ ጾም የተሻረ ያህል ይሰማናል። «ከእንግዲህ የትም አይሄድም ብለሽ ነው ፥ ከእንግዲህ የትም አትሄድም ብለህ ነው ፤ » መባባል እንጀምራለን። ኲርፊያው ከበድ ይላል። ይህ ነገር ከእኛ የሚጠበቅ አይደለም። ከእኛ የሚጠበቀው፦ «ምንም አይደለም፤ አንተ ደህና ፥ አንቺ ደህና ፤» መባባል ነው። ከዚህ ይልቅ የእግዚአብሔር ስጦታ አሥራቱ ፥ የነዳያን ስጦታ ምጽዋቱ እንዳይታጐል መጠንቀቅ ነው።

፫፦ አሳዝኖኝ ፥ አሳዝናኝ ነው፤
          ሐዘን ከርኅሩኅ ልቡና የሚመነጭ ነው። ርኅራኄ ለእግዚአብሔር የባህርይ ገንዘቡ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራላቸዋል፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፲፯፥፳፪። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «በመልእክተኛም አይደለም፤ በመልአክም አይደለም፤ እርሱ ራሱ ያድናቸዋል እንጂ። እርሱ ይወዳቸዋልና ፥ይራራላቸውማልና ተቤዣቸው፤» ብሏል። ኢሳ ፷፫፥፬። እግዚአብሔር ራሱ፦ ነቢዩ ዮናስን፦ «አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ፥ ላላሳደግሃትም ፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች ፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?» ብሎታል። ዮና ፬፥፲፩። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፦ ወንጌል እየሰበከ ፥ ደዌና ሕማምንም ሁሉ እየፈወሰ በከተሞችና በመንደሮች በሚዘዋወርበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ አየ። እረኛም እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው ፥ ይላል። ማቴ ፱፥፴፭-፴፮።
          ክርስትና ማለት በግብር ክርስቶስን መስሎ መገኘት በመሆኑ ፦ ክርስቲያኖችም ርኅሩኃን ልንሆን ይገባል። ጌታችን በወንጌል፦ «አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኁሩኆች ሁኑ፤» ያለው ለዚህ ነውና። ሉቃ ፮፥፴፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ በጌታ ትምህርት ላይ ተመሥርቶ፦ «እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤» ብሏል። ኤፌ ፬፥፴፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ፦ «የሁሉም ፍጻሜ የባልንጀራችሁን መከራ እየተቀበላችሁ አንድ ልብ ትሆኑ ዘንድ ነው፤ እንደ ወንድሞችም ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታንም ሁኑ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፰። ይልቁንም፦ «የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው ፥ መጽናናትን ያገኛሉና፤ » እንደተባለ፦ መከራ መስቀልን ፥ የግል ኃጢአትን ፥ የባልንጀራን ኃጢአት ፥ በደጋግ ሰዎች ላይ የተፈጸመውንና የሚፈጸመውን ግፍ እያሰቡ ማዘን ይገባል። ማቴ ፭፥፬።
          ስለ ሐዘን እና መተዛዘን ያነሣሁት ያለ ምክንያት አይደለም። በሐዘን ተፀንሰን በሐዘን የተወለድን ፥ በሐዘን አድገን በሐዘን የተማርን ሰዎች በመሆናችን ፥ ድራችንም ማጋችንም ሐዘን ነው። «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ።» እንዲል፦ ብዙ የደከምንበት ትምህርትም አልሳካ ብሎን የምናዝንም ሰዎች ቁጥራችን ከቁጥር በላይ ነው። ትምህርቱ ተሳክቶልን ሥራ አጥተን የምናዝን ወይም በያዝነው ሥራ መደሰት አቅቶን ሐዘን ድባቡን የጣለብን ሰዎችም ጥቂቶች አይደለንም። በትምህርት ቤት መምህራችን ፥ በመሥሪያ ቤት አለቃችን ጠምደውን የምናዝነውም ሐዘን ሚዛኑ ቀላል አይደለም። በኑሮው መወደድ የተነሣ ደመወዛችን አልበቃ ብሎን ቤተሰብ በሚጠብቀው መልክ ለመርዳት አለመቻልም ሐዘን ነው። ጨርሶም ሥራ የሚባል ነገር አጥቶ የቤተሰብ ሸክም መሆንም የሐዘን ሐዘን ነው። ያመኑት የወንድ ጓደኛ ወይም ያመኗት የሴት ጓደኛ ክዳትም ሐዘኑ የእድር ጥሩንባ የሚያስነፋ ፥ ድንኳንም አስተክሎ ፍራሽ ላይ የሚያስቀምጥ ነው። አባት ሞቶ በእናት እጅ ፥ ወይም እናት ሞታ በአባት እጅ ፥ወይም ሁለቱም ሞተው እንዲሁ ማደግም መቼም መች ከኅሊና የማይፋቅ ሐዘን ነው። እርግጥ ከእንጀራ አባት የማይሻሉ አባቶች ፥ ከእንጀራ እናትም የማይሻሉ እናቶች ፈጽመው የሉም አይባልም። ከወለደች እናት የሚበልጡ የእንጀራ እናቶች ከወለደ አባትም የሚበልጡ የእንጀራ አባቶች ፈጽሞ አልተፈጠሩም ሊባል አይችልም። የጹሑፉ ዓላማ በሚበዛው መናገር እንጂ የጅምላ ጭፍጨፋ አይደለም።
          በስደት የሚያጋጥመው ሐዘንም እድሜ ልክ ጥቁር የሚያስለብስ ነው። በሱዳን ፥በኬንያ ፥ በሶማልያ ፥ በግብፅ ፥ በጂቡቲ ፥ በዩጋንዳ ፥በደቡብ አፍሪካ ፥ በአረብ አገሮች ፥ በአውሮፓ ፥ በአሜሪካ ያልፍልናል ሲሉ ያለፈባቸው ፥ የሐዘናቸውን ልክ እነርሱ ያውቁታል። የየአንዳንዱ ሰው ታሪክ በራሱ መጽሐፍ ይወጣዋል። አውሬ የበላቸውን ፥ ወንዝ የወሰዳቸውን ፥ ቁጥራቸውን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። በየሀገራቱ ጠረፍ ጠባቂዎች ወይም በሌሎች የተደፈሩትን የተገደሉትን ኅሊና የሚሸከመው አይደለም። «እናቱ የሞተችበትም ፥ ውኃ ልትቀዳ ወንዝ የወረደችበትም ልጅ እኲል ያለቅሳሉ፤» አትበሉኝ እንጂ በቦሌ የመጣነውም ብንሆን ሙሉ በሙሉ ደስተኞች ነን ለማለት አይቻልም። ደግሞም በዚህ ዓለም ሙሉ ሐዘን እንጂ ሙሉ ደስታ የሚባል ነገር የለም።
          እንግዲህ ለጋብቻ በምንጠናናበት ወቅት፦ እነዚህን ከላይ በጥቂቱ የዘረዘርናቸውን ታሪኮች ሁሉ፦ ከእንባ ጋር በተቀላቀለ ድምፅ መስመታችን ግድ ነው። እንደ መጽሐፍ ትረካ ይተረከልናል፥እኛም አሳምረን እንተርካለን። አልቅሰው ያስለቅሱናል ፥ አልቅሰን እናስለቅሳለን። በሂደትም፦ ወንዶቹ ለሴቶቹ ፥ ሴቶቹም ለወንዶቹ እያዘንን እንሄዳለን። በነገርም ሁሉ «እንዴት የምታሳዝን ልጅ መሰለቻችሁ ፥ ምስኪን ናት፤ እንዴት የሚያሳዝን ልጅ መሰላችሁ ፥ ምስኪን ነው፤» ማለት እንጀምራለን። «ምኗን አይተህ ነው የወደድካት?» ስንባል፦ «አሳዝናኝ ነው፤» እንላለን። «ምኑን አይተሽ ነው የወደድሽው?» ሲባሉ፦ «አሳዝኖኝ ነው፤» ይላሉ። በመሠረታዊ ነገሮች ላይ ለመወያየት ስንሞክርም፦ «እባክህ ተወኝ ፥እኔ ለራሴ ያለፈውንም ሐዘን አልረሳሁትም ፥ እባክሽ ተዪኝ እኔ ለራሴ ያለፈውም ቁስል አልደረቀልኝም፤» እንባባላለን። አብዛኛውን ጊዜም በዚህ ተጋርደን ማንሣት የሚገባንን ጥያቄዎች ሳናነሣ እንቀርና ለትዳራችን ችግር እናቆያለን።
          ለመሆኑ አሳዛኝ ታሪክ የትዳር መለኪያ ነው? ይህ ጥያቄ በቅድሚያ መመለስ አለበት። ምክንያቱም ብዙ አሳዛኝ ታሪክ የነበረን ፥ነገር ግን በእጮኝነትም ሆነ በትዳር ዘመን በትዳር ጓደኞቻችን ላይ ፥ አሳዛኝ ታሪክ የፈጸምን ፥ እየፈጸምንም ያለነውን ሰዎች ቁጥራችንን ይኽን ያክላል ከማለት ይልቅ ፥ ቤት ይቁጠረው ማለቱ ይቀላልና። በሌላው የደረሰብንን በደል ፥ አጠገባችን ባለው ሰው ላይ የምንበቀል ሰዎች እንመስላለን። «ታሞ የተነሣ ፈጣሪውን ረሳ፤» ዓይነት ሰዎች ነን። ስንንገላታ የኖረን ሰዎች የምንረካው በማንገላታት ነው።
          በሌላ በኲል ደግሞ፦ «ተበደልን እንጂ በድለናልን፤» የማናውቅ ሰዎች መሆናችንንም መርሳት የለብንም። ምክንያቱም የሚነገረን አሳዛኝ ታሪክ ሐሰትም ሊሆን ይችላልና፤ ወይም ሐሰት ተቀላቅሎበት ሊሆን ይችላል። እንዲያውም፦ ከትናንት ወዲያ የተናገርነውን ረስተን ዛሬ ሌላ ነገር ስናወራ፦ «ምነው ካሁን ቀደም እንዲህ ብለኸኝ አልነበር? እንዲህ ብለሽኝ አልነበር? » የምንባባልበት አጋጣሚም አለ። ወይም፦ «መቻል ምን ይከፋል ፥ ሆድ ከሀገር ይሰፋል፤» ብለን ዝም እንላለን። ችግሩ በእፍ እፍ ዘመን የሰፋው ሆድ ከጋብቻ በኋላ የጠበበ እንደሆነ ነው። የኑሮ ውጣ ውረዱም ቢሆን የጋራ ነው። ስለዚህ፦ በተቻለን መጠን መጽናናት የሚገባውን ማጽናናት ፥ መረዳት በሚገባውም መንገድ መርዳት ፥ መጠናት የሚገባውንም ማጥናት ይኖርብናል። አለበለዚያ ልቅሶ ቤቱንና ሠርግ ቤቱን መቀላቀል ፥ ለሐዘንም ለደስታም ችግር ይሆናል። «ነገ ተነገ ወዲያ፥ እኔ ድሮውንም ያገባሁሽ አሳዝነሽኝ እንጂ መች ወድጄሽ ነው፤ እኔ ድሮውንም ያገባሁህ አሳዝነኸኝ እንጂ መች ወድጄህ ነው፤» ከማለት ፥ ዛሬውኑ ሐዘኑን እንደ ሐዘን ፥ ፍቅሩንም እንደ ፍቅር ልንይዘው ይገባል። እንዲህም መባሉ የሚያሳዝን ታሪክ ያላቸው ሰዎች «ለትዳር አይሆኑም፤» ማለት እንዳልሆነ ግልጽ መሆን አለበት። የሚያሳዝን ታሪክ የሌላቸውም ሆነው ችግር ያለባቸው ስላሉ ሚዛኑ ይህ አይደለም።

10 comments:

 1. kesis kale hiwotin yasemawot.be ejigu ginizabe agegnehu!!! lelam lelam techemari lemanbeb ayinoche ekefetu!ersom endemiyarekulign tesfaye new! ye ageliglot zemenon amlak yibarkilot!!!

  ReplyDelete
 2. ደግሞም በዚህ ዓለም ሙሉ ሐዘን እንጂ ሙሉ ደስታ የሚባል ነገር የለም
  እግዚሐብሔር ይስጥልን የአገልግሎት ዘመኖትን ይባርክሎት የአመለካከት አድማስዎን ያስፋልዎት እናመሰግናለን ቀጣዩን ፅሁፍ ለማንበብ የነገ ሰው ይበለን
  ላሜዳ …ከአ.አ

  ReplyDelete
 3. <> It is right. This is the word I was looking for to express the challenges of immigration. Thank you kesis, Pray for US.

  ReplyDelete
 4. abatachin kale hiwote yasemalen. ye ethiopia amelake lejochiwon yibarekelewot. Ewunetegna ye egzabiher begoch tebaki bemehonewot egna yeresewo lejoch betam koretenebetewal. ye EOTC mene yaleh endemetekorabewo yisemanal. ende eresewo yale abat leseten menem yemayalekebete egzabiher yikebere yimesegen. amen

  ReplyDelete
 5. ቃለ ህይወት ያሰማልን ያገልግሎቶን እድሜ ያብዛልን

  ReplyDelete
 6. ተበደልን እንጂ በድለናልን፤»የማናውቅ ሰዎች መሆናችንንም መርሳት የለብንም። kale hiwot yasemalin kesis.ketayu kifil eyetebekin new
  God bless ur work and ur life as well ur family

  ReplyDelete
 7. abatachen erjem edima yestlen

  ReplyDelete
 8. በጣም የሚያስደስት ትምህርት ነዉ ከዚህ አምድ እያገኘን ያለነዉ.ፈጣሪ ረጅም እድሜ ይስጥህ.

  ReplyDelete
 9. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ዕድሜና ጤና ይስጥልን

  ReplyDelete
 10. በስደት የሚያጋጥመው ሐዘንም እድሜ ልክ ጥቁር የሚያስለብስ ነው. Kale hiwot yasemaln ..

  ReplyDelete