Sunday, January 30, 2011

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፱

፲፦ ቃል ሥጋ የሆነው በተዋሕዶ ነው፤
ካለፈው የቀጠለ፦

            አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ሰው የሆነው በተዋሕዶ ነው። ተዋሕዶውም እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ ነው። ነፍስ ረቂቅ ናት ፥ ሥጋ ደግሞ ግዙፍ ነው፤ ነፍስ ረቂቅነቷን ሳትለቅ ፥ ሥጋም ግዝፈቱን ሳይተው በተዋሕዶ ጸንተው ይኖራሉ። በመሆኑም አንድ ሰው እንጂ ሁለት አይባሉም።
          ቅዱስ ቄርሎስ፦ የተዋሕዶን ነገር በብረትና በእሳት እየመሰለ አስተምሯል። «በእግዚአብሔር ቃል፦ በረቂቅ ባሕርይ የሆነውን ተዋሕዶ አንካድ ፤ ብረት ከእሳት በተዋሐደ ጊዜ፦ ከእሳትም በመዋሐዱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ ያደርጋል፤ (ማቃጣል መፋጀት ይጀምራል)፤ ብረት በመዶሻ በሚመታበት ጊዜ፦ ከእሳቱ ጋር በአንድነት(በተዋሕዶ) ይመታል፤ ነገር ግን ከመዶሻው የተነሣ የእሳት ባሕርይ በምንም በምን አይጐዳም፤ ሰው የሆነ አምላክ ቃልም በመለኮቱ ሕማም ሳይኖርበት፦ በሥጋ እንደታመመ እናስተውል፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፫ ፥፲፪)።
          ቅዱስ አትናቴዎስ፦ የተዋሕዶን ምሥጢር ሲያስረዳ፦ «አሁንም በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ ሰምተህ ዕወቅ፤ አምላክ ብቻ ከሆነማ እንደምን በታመመ ነበር? ወይስ እንደምን በሰቀሉት ነበር? ወይስ እንደምን በሞተ ነበር? ይህ ሥራ፦ (ሕማምና ሞት) ከእግዚአብሔር የራቀ ነውና፤ ዘዳ ፴፪፥፵። ሰው ብቻ ከሆነ በታመመ በሞተ ጊዜ ሞትን እንደምን ድል ይነሣው ነበር? ይህ ከሰው ኃይል በላይ ነውና። ፩ኛ ቆሮ ፭ ፥፲፫ ፣ ዕብ ፭፥፩-፬።» ብሏል። ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገር ደግሞ፦ «ድንግል ወንድ ሳታወቅ ሊዋሐደው በፈጠረው ሥጋ የፀነሰችውን ወለደች፤ ያለ ኃጢአት ያለ ምጥ ወለደችው፤ የአራስነት ግብር አላገኛትም፤ ያለ ድካም ያለ መታከት አሳደገችው፤ ያለ ድካም አጠባችው፤ ለሥጋ በሚገባ ሕግ ምን አበላዋለሁ? ምን አጠጣዋለሁ? ምን አለብሰዋለሁ? ሳትል አሳደገችው፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፳፯ ፥፮ ፣ ፳፰፥፲፱)። በተጨማሪም፦ «ዳግመኛም በክህደታቸው አስበው፦ ማርያም የወለደችው፦ ገዥ ፥ ፈጣሪ እንዳይደለ የሚናገሩ የመናፍቃን ልጆች ፈጽመው ምላሽ ይጡ፤ እግዚአብሔር ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እንደምን አማኑኤል ተባለ? ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ፥ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬ ፣ ማቴ ፩፥፲፰-፳፭። እንኪያስ ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በእውነት ለዘለዓለሙ የከበረ አምላክ ከሁሉ በላይ የሚሆን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋ ታመመ ብሎ እንደምን ጻፈ? ሮሜ ፭፥፯-፲፪ ፣ ፱፥፩-፭፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፴፭፥፲፱)።
          የቅዱስ ባስልዮስ ወንድም ቅዱስ ጎርጎርዮስ፦ «ትስብእትን ከመለኮት ልዩ ነው ፥ አትበሉ፤ ከተዋሕዶ በኋላ አይለይምና፥ አይቀላቀልምና፤ መለኮትን ከተዋሐደው ከትስብእት ልዩ ነው ፥ አትበሉ፤ በርሱ ያለውን ተዋሕዶውን እመኑ እንጂ፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፴፭ ፥፲፱)። በተጨማሪም፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት በተርጐመበት አንቀጽ፦ «እግዚአብሔር አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበትን ሥራ በልቡናችሁ ዕወቁ፤ ሽቶ(ፈልጎ) ቀምቶ ከእግዚአብሔር ጋር የተካከለ አይደለም፤ ራሱን አዋርዶ ሰው ኹኖ የተገዥን ባሕርይ ተዋሕዶ ነው እንጂ። ፊል ፪፥፭-፰። ሥጋን ከመዋሐድ የበለጠ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ድህነት አለ? ነገር ግን እርሱ ነገሥታትን ፥ መኳንንትን ፥የሚገዛ ሲሆን፦ እኛን ወደ መምሰል በመጣ ጊዜ፥ የተገዥን ባሕርይ በተዋሐደ ጊዜ ፥ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም። ምድርን የፈጠረ እርሱን በትውልድ እንበልጣለን የሚሉ ሐና ቀያፋ ዘበቱበት፤ ፍጥረትን ሁሉ የሚገዛ እርሱ የሚያርፍበት ቦታ አላገኘም፤ በሥጋ በተወለደ ጊዜ ላሞች በሚያድሩበት በረት አስተኙት እንጂ። መዝ ፳፫፥፩፤፺፪፥፩፤፺፭፥፲፫፤ ማቴ ፰፥፳፣ ሉቃ ፪፥፩-፯። የማይለወጥ ንጹሕ ቃል የሚለወጥ የሰውን ባሕርይ ተዋሐደ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፭፥፳፱-፴፫)።
          ቅዱስ አብሊድስ፦ «ዳግመኛም ቃልን ከሥጋ አዋሕደን እንሰግድለታለን፤ . . . ፍጡር ሥጋን ፈጣሪ እንደተዋሐደው እናምናለን፤ ፈጣሪ ከፍጡር በተዋሐደ ጊዜ ፦ አንድ አካል በመሆን የጸና አንድ ባሕርይ ሆነ፤ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አይደለም፤ የመለኮትንና የትስብእትን ተዋሕዶ እናውቃለን፤ ባሕርያችን ሁለት (ነፍስና ሥጋ) ሲሆን አንድ ይሆናል፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ያድጋል፤ አንድ ሰውም ይባላል፤ ዘፍ ፩፥፳፮፣ ዕብ ፪፥፲፬።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፱፥፳፩-፳፬) ። በተጨማሪም፦ «ከአብ ጋር አንድ ነው፥ እንዳልነው ሁሉ ሥጋን በመዋሐድ ከሰው ጋር አንድ ነው፥ እንላለን፤ መለኮትም ለሰው የሚገባ ስምን ገንዘብ ያደርጋል፤ ሥጋን በመዋሐድ ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ ስለሆነ ከእርሱም ጋር አንድ ስለአደረገው። ኢሳ ፱፥፮ ፣ ማቴ ፩፥፳፪ ፣ ፊል ፪፥፭። ከተዋሐደው ከሥጋ ባሕርይ ምንም አልተለወጠም፤ አንድ መሆንም ሰውን ወድዶ ስለ መዋሓዱ የመለኮት ባሕርይ እንዳልተለወጠ መጠን ፥ ከእርሱ ጋር አንድ ከሚሆን ከእግዚአብሔር ጋር ገንዘቡ የሚሆን መተካከል ያለበት ስም ነው። ማቴ ፳፰፥፲፱ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪ ፣ ዮሐ ፩፥፩ ፤ ፲፥፴ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፥፲፮)።
          ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ፦ «በዘመኑ  ሁሉ የማይለያዩትን የአምላክነትን የሰውነትን ግብራት በተዋሕዶ አጸና፤ ክርስቶስ በመለኮቱ ያይደለ በሥጋ አንደታመመ ተናገረ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረ መለኮት ከትስብእት አልተለየም፤ መለኮትና ትስብእት አንድ ባሕርይ በመሆን ተዋሓዱ እንጂ። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰ ፣፬-፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ መለኮትንና ትስብእትን አንድ አድርጎ እርሱን የክብር ባለቤትን ባልሰቀሉትም ነበር ብሎ ተናገረ፤ ፩ኛ ቆሮ ፪፥፰።» ብሏል።  (ሃይ፡ አበው ፶፯ ፥ ፴፮)።
          ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፦ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን ሰዎች የጻፈውን መልእክት በተረጎመበት እንቀጽ፦ «የተዋሐደውን ሥጋ ከመላእክት ባሕርይ የነሣው አይደለም ፥ ከአብርሃም ባሕርይ ነሣው እንጂ። ዕብ ፪ ፥ ፲፯። ለዚህ ታላቅ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰው ወገን ለተደረገ ለማይመረመር ለዚህ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ ይህ ለመላእክት ያላደረገው ነው። የተደረገውን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ፤ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና ፥ የመላእክት ባሕርይ አልተዋሐደችውምና ፥ የተዋሐደችው የእኛ ባሕርይ ናት እንጂ። ባሕርያችንን ተዋሕዷል እንጂ። ከባሕርያችን ከፍሎ ተዋሐደ ለምን አላለም? ወዳጁ እንደኮበለለ እስኪያገኘውም ድረስ እንደሄደና እንዳገኘው ሰው የእኛ ባሕርይ እንደዚህ ከእግዚአብሔር ተለይታ ነበርና፤ ከእርሱም ፈጽማ ርቃ ነበርና፤ ሥጋ በመሆን ገንዘብ እስኪያደርጋት ድረስ ፈጥኖ ፈለጋት ፤ እርሷም ተዋሐደችው፤ ይህንንም ተዋሕዶ እኛን በመውደድ እንዳደረገው የታወቀ ነው። መኃ ፫፥፬ ፣ ማቴ ፲፰፥፲፪ -፲፬፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፫፥፪-፭)። በተጨማሪም፦ «ተዋሕዶንም አስረዳለሁ፤ እግዚአብሔር ቃል በአካሉ ፍጹም የሚሆን ነፍስ ፣ ዕውቀት ያለው ሥጋን ከእኛ ባሕርይ ነሥቷልና፤ እርሱንም ተዋሕዷልና፤ ስለዚህም ነፍስን ሥጋን ተዋሕዶ ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃል አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ እንናገራለን፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፯፥፴)።
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ጌታን፦ በድንግልና መውለዷ በራሱ ምሥጢረ ተዋሕዶን ያስተምረናል። ይኸውም፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር በድንግልና የጸነሰችውን አምላክ በድንግልና የወለደችው፦ መለኮት ከእርሷ የነሣውን ሥጋና ነፍስ በመዋሐዱ ነው። ምክንያቱም፦ በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለመለኮት ሆኗልና። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ እመቤታችንን ባበሠራት ጊዜ፦ «ከአንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ (የእግዚአብሔር አብ ልጅ፦ እግዚአብሔር ወልድ ነው፥ ከሦሥቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው) ፤ ማለቱም ለምሥጢረ ተዋሕዶ ምስክር ነው። ሉቃ ፩፥፴፭። ምክንያቱም መለኮት በማኅፀን ነፍስን እና ሥጋን ባይዋሐድ ኖሮ ከእመቤታችን የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከሦስቱ ቅዱስ(ከሥላሴ) አንዱ ቅዱስ ነው ፥ አይባልም ነበር።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ በመዋዕለ ሥጋዌው ያደረጋቸው ተአምራትም ምሥጢረ ተዋሕዶን የሚያሳዩ ናቸው። ለምሳሌ፦ ሁለት ማየት የተሳናቸውን ሰዎች በእጆቹ በዳሰሳቸው ጊዜ፦ ተፈውሰዋል። ይህም ሊሆን የቻለው መለኮት በተዋሐዶ ከሥጋ ጋር ስለነበረ ነው። ማቴ ፱፥፳፯-፴፩። ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ፦ ዓይነ ስውር የነበረውንም ብላቴና በምራቁ  አፈሩን ለውሶ በዚያ ፈውሶታል። ምራቅ የሥጋ ነው፤ ነገር ግን መለኮት ሥጋን ስለተዋሐደው ፥ ከተዋሕዶ በፊት የሥጋ ብቻ የነበረ ምራቅ የብላቴናውን ዓይን አብርቶለታል። ዮሐ ፱፥፩-፲፪።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፦ መግነዝ ሳይፈታለት ፥ መቃብር ሳይከፈትለት ነው። ሥጋ በራሱ መቃብር ሳይከፈትለት መውጣት አይችልም ። መለኮት ግን የሚያግደው የለም። በመሆኑም፦ መለኮታዊ አካልና ባሕርይ ፥ ከሥጋ አካልና ባሕርይ ጋር ተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆኑ፦ ልዩነት ሳይኖር መቃብሩ እንደታተመ ከመቃብር ወጥቷል። ከትንሣኤው በኋላም በሩ ሳይከፈት ደቀመዛሙርቱ ወደነበሩበት ቤት ገብቷል። ደቀመዛሙርቱ፦ ይህ ምሥጢር ረቅቆባቸው፦ በእርሱ አምሳል ምትሐት የሚያዩ መስሏቸው ነበር። እርሱ ግን፦ « ምን ያስደነግጣችኋል? በልባችሁስ እንዲህ ያለ ሐሳብ ለምን ይነሣሣል? እጄንና እግሬን እዩ፤ ዳስሱኝም፤ እኔ እንደሆንሁም ዕወቁ፤ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና፤» ብሎ ተዳሰሰላቸው። ይህ የዳሰሱት አካል ነው፥ መዝጊያው ሳይከፈት የገባው። ምክንያቱም መዝጊያና ግድግዳ የማያግደው መለኮት እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶታልና። ማቴ ፳፰፥፩-፲ ፣ ሉቃ ፳፬፥፲፮ ፣ ዮሐ ፳፥፲፱።
          ጌታችን፦ በዝግ ቤት ለደቀመዛሙርቱ በተገለጠላቸው ጊዜ ቶማስ አልነበረም። የሆነውን ሁሉ በነገሩት ጊዜ፦ «የችንካሩን ምልክት በእጁ ካላየሁ ፥ ጣቴንም ወደተቸነከረበት ካልጨመርሁ ፥ እጄንም ወደጎኑ ካላገባሁ አላምንም፤ አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላም በሩ እንደተዘጋ ፥ ቶማስ ባለበት ተገልጦላቸው፦ «ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ »አላቸው። ከዚህም በኋላ ቶማስን ፦ ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን፤» አለው። ቶማስም ፦ ከዳሰሰ በኋላ፦ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ መለሰ። የዳሰሰው አካል፦ እሳተ መለኮት የተዋሐደው በመሆኑ እጁን ፈጅቶታል። በመሆኑም ቢዳሰስለት፦ «ጌታዬ» ቢፈጀው፦ «አምላኬ» ብሏል። ዮሐ ፳፥፳፰።
          ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም፦ አይታይ አይዳሰስ የነበር መለኮት የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ተዋሕዶ በሰውነት ( ነፍስንም ጭምር በመዋሐድ) በመገለጡ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን ፥ በዓይኖቻችንም ያየነውን፥ የተመለከትነውንም ፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን። ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት ፥ ምስክርም ሆንን፤ ለእናንተም ከአብ ዘንድ ያለችውንና ለእኛ የተገለጠችውን የዘለዓለምን ሕይወት እንነግራችኋለን፤» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩።
፲፩፦ አካልና ባሕርይ፤
          አካልና ባሕርይ አይነጣጠሉም፤ አካል ባለበት ባሕርይ አለ፤ ምክንያቱም የባሕርይ መገለጫው አካል ነውና። (ባሕርይ አካልን አስገኝቶ በአካል ላይ ይገለጣል)። ለምሳሌ፦ እሳት አካልም ባሕርይም አለው፤ አካሉ፦ በእንጨት በከሰል ላይ ይገለጣል ፥ ባሕርዩ ደግሞ፦ መፋጀት ማቃጠል ነው። በመሆኑም፦ የሚፋጀውን ወይም የሚያቃጥለውን የእሳት ባሕርይ፦ ከአካሉ መነጠል ወይም መለየት አይቻልም። ውኃም፦ እንዲሁ፦ አካልም ባሕርይም አለው። አካሉ፦ በማድጋ ተቀድቶ ፥ በቀላያት ተዘርግቶ ቦታ በመያዙ ይታወቃል፤ ባሕርዩ ደግሞ ርጥበት ነው፤ ይህንንም ርጡብ የሆነ የውኃ ባሕርይ ከውኃ አካል መለየት አይቻልም። አካሉ ባለበት ቦታ ሁሉ ባሕርዩ አለ።
፲፩፥፩፦ ሥጋዊ አካልና ባሕርይ፤
          ከራስ ጠጉር እስከ እግር ጥፍር ፥ በአጥንት፥ በጅማት ፥ በሥጋ ፥ በቁርበት ተያይዞና ተሸፍኖ ያለው በአንድነት አካል ይባላል። ፍጹም ገጽ ፥ ፍጹም መለክ ያለው ነው፤ ራሱን የቻለ ፥ ለራሱ የበቃ እኔ የሚል ፥ የባሕርይ የግብር እና የስም ባለቤት ነው። የሥጋ አካል፦ ግዙፍ ፥ ውሱን፥ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ነው፤ የሥጋ ባሕርይ ደግሞ፦ መራብ ፥ መጠማት ፥ መድካም ፥ ማንቀላፋት ፥ መሞት ነው።
፲፩፥፪፦ መለኮታዊ አካል እና ባሕርይ፤
          መለኮታዊ አካል፦ ረቂቅ፥ የማይጨበጥ ፥ የማይዳሰስ፥ እሳታዊና ምሉዕ ነው።
-       «ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፤ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጉር እንደ ነጭ ሱፍ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፤» ዳን ፯፥፱።
-       «ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው ፥ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፤» መኃ ፭፥፲፩።
-       «የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃኑ ፥ ጆሮቹም ወደ ልመናቸው ናቸውና፤» መዝ ፴፫፥፲፭።
-       «ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራል፤» መዝ ፲፥፬።
-       «እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፤» መዝ ፻፲፰፥፸፫።
-       «እግዚአብሔር የኖኅን የመሥዋዕቱን መዓዛ አሸተተ፤» ዘፍ ፰፥፳፩።
-       «ንስር ጫጩቶቹን በክንፎቹ በታች እንደሚሰበስብ ፥ በጎኑም እንደሚያቅፍ፥ በክንፎቹ አዘላቸው፤ በደረቱም ተሸከማቸው።» ዘዳ ፴፪፥፲፩።
-       «ወገቡን በጽድቅ ይታጠቃል፤ እውነትንም በጎኑ ይጎናጸፋል።» ኢሳ ፲፩፥፭።
-       «የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ  እንሰግዳለን፤» ፻፴፩፥፯።
-       «ሰማይ የእግዚአብሔር መቀመጫ ነውና፤» ማቴ ፭፥፴፫።
-       «እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና ፥ ሰማይ ስማ ፤ ምድርም አድምጪ፤» ኢሳ ፩፥፪ ።
-       «በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤» መዝ ፴፪፥፮።
          መለኮታዊ ባሕርይ ደግሞ፦ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ፥ እስከ የሌለው ዘለዓለማዊ ነው። ፊተኛውና ኋለኛ፥ መጀመሪያና መጨረሻ ፥ እርሱ ነው ፤ ፈጣሪ ፥ ሁሉን ቻይ ነው፤ የሚሳነው ነገር የለም፤ ሕያው ነው፤ ምሉዕ በኲለሄ ነው፤ የማይለወጥ ፥ የማይታመም ፥ የማይራብ ፥ የማይጠማ ፥ የማይደክም ፥ የማይሞት ነው።
-       «አልፋና ዖሜጋ ፥ ቀዳማዊና ደኃራዊ ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ ፤» ራእ ፥፳፪፥፲፫።
-       «አትፍራ ፥ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ፤ ሞቼም ነበረሁ፤ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ነኝ፤» ራእ ፩፥፲፯።
-       «ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የለም፤» ዮሐ ፩፥፫።
-       «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና፤ » ሉቃ ፩፥፴፯።
-       «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤» ሚል ፫፥፮።
-       «አቤቱ ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነትና ኃይል ፥ ክብርም ፥ ድልና ጽንዕ የአንተ ነው፤. . አቤቱ ፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ የሥልጣን ሁሉ ጌታ ነህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ኃያል ነህ፤» ፩ኛ ዜና ፳፱፥፲፩።
-       «ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ ፥ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ጥልቁም ብወርድ ፥ አንተ በዚያ አለህ፤» መዝ ፻፴፰፥፯።
-       «ከዘላለም እስከ ዘለዓለም ድረስ መቼም መች አንተ ነህ» መዝ ፹፱፥፪።
፲፪፦ አንድ አካል ፥ አንድ ባሕርይ፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በተዋሕዶ ከሁለት አካል፦ አንድ አካል ፥ ከሁለት ባሕርይ፦ አንድ ባሕርይ ሆኗል። ይህም ማለት፦ የሥጋ አካል እና የመለኮት አካል ተዋሕደው አንድ ሲሆኑ ፥ የሥጋ ባሕርይና የመለኮት ባሕርይም ተዋሕደው አንድ ሆነዋል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ አንድ አካል እና አንድ ባሕርይ ነው። ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የለም።
          ቅዱስ አቡሊዲስ ወደ ቅዱስ ዲዮናስዮስ በላከው መልእክቱ፦ «ወንጌላዊ ዮሐንስም ቃል ሥጋ እንደሆነ በተናገረ ጊዜ፦ አንድ ገዥ ነው አለ፤ ዮሐ ፩፥፲፬፣፩ኛ ቆሮ ፰፥፮። ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ፥ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ ወልድ ተብሎ ከተጠራ ፥ ሁሉ የተፈጠረበት እርሱ አንደ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ ወደ ሁለትነት መከፈል የለበትም። ለሥጋውም ከመለኮቱ ወደ አንድ ወገን የተለየ ባሕርይ የለውም። ሰው፦ አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ ሁሉ፥ ሰው የሆነ የባሕርይ ገዥ ክርስቶስም፦ እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንጂ፤ ፊል ፪፥፭-፰። አንዱን ክርስቶስ አንድ እንደሆነ ካላወቁትስ፦ እነሆ ፥ ዳግመኛ አንዱን ሰው ወደ ብዙ ወገን ሊከፋፍሉት ይገባቸዋል፤ ብዙ ባሕርያትም እንዳሉት ሊናገሩ ይገባል። ምክንያቱም ከብዙ ወገን የተጠራቀመ ነውና፤ ከአጥንት ፥ ከጅማት ፥ ከአሥራው ፥ ከሥጋ ፥ ከቁርበት፥ከጥፍር ፥ ከጠጉር ፥ ከደም ፥ከነፍስ የተጠራቀመ ነውና፤ እነዚህም ሁሉ እርስ በርሳቸው ልዩ ልዩ ናቸው። ነገር ግን በእውነት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ እንዲሁም መለኮት ከትብስእት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ ወደ ሁለት አካል ፥ ወደ ሁለት ባሕርይ አይከፈልም። ዮሐ ፫፥፲፫ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪። . . . ያለዚያ ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል እንጂ የሰው ልጅ አይባልም፤ ከድንግል ማርያም የተወለደውም የሰው ልጅ ይባላል እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይባልም። . . . ለእኛ ግን ከሰማይ በወረደ ፥ ከድንግል በተወለደ፥ በአንድ እግዚአብሔር እናምን ዘንድ ፥ እግዚአብሔር ያጻፋቸው መጻሕፍት ያስተምሩናል። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ፣ ገላ ፬፥፬ ፣ ዮሐ ፭፥፳፯ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪። . . . ሁለት ባሕርይ ብለው የሚያምኑ ለአንዱ እንዲሰግዱ ፥ ለአንዱ እንዳይሰግዱ፤ በመለኮት ባሕርይ እንዲጠመቁ ፥ በሥጋ ባሕርይ እንዳይጠመቁ  ግድ ይሆንባቸዋል። እምነታችን በጌታችን ሞት እንደምንከብር ከሆነ፦ የሚታመም ትስብእትና የማይታመም መለኮት አንድ ባሕርይ ይሆናል። መክበራችን እንዲህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በጌታችን ሞትም ፍጹማን እንሆናለን፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፱፥፮-፲፯)።
          ከዚህም በተጨማሪ፦ «እንዲሁም ከእግዚአብሔር አብ ጋር በአምላክነት ክብር አንድ ነው እንላለን፤ ሥጋም ይህን አንድ ስምን (ክርስቶስን) ገንዘብ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር አብን፦ በመልክ ከሚመስለው ፥ በባሕርይ ከሚተካከለው ከቃል ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነውና። ዮሐ ፩፥፲፬ ፣ ፲፰፤ ከአብ ጋር አንድ ነው፥ እንዳልነው፦ ሥጋን በመዋሐድ ከሰው ጋር አንድ ነው፥ እንላለን፤ መለኮትም ለሰው የሚገባ ስምን ገንዘብ ያደርጋል፤ ሥጋን በመዋሐድ ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ ስለሆነ ከእርሱም ጋር አንድ ስለአደረገው፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፥፲፭-፲፮)። ቅዱስ ኤራቅሊስም፦ «እግዚአብሔር ያለመለወጥ እንደምን ሰው እንደሆነ ፥ቃል ከፈጠረው ሥጋ ጋር ያለ መቀላቀል እንደምን አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደ ሆነ ፥ እግዚአብሔር የሥጋን ባሕርይ፦ ያለዘር፥ ያለሩካቤ ፥ እንደምን እንደተዋሐደ መላልሰህ በልቡናህ ብትመርምር፦ ይህ ድንቅ ምሥጢር የጎላ የተረዳ ሆኖ ታገኘዋለህ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፱፥፳፭)።
          የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት የከበረ ሰማዕት አግናጥዮስም፦ ጌታ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የመሆኑን ነገር ሲናገር፦ «ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ተወለደ፤ በእውነት አደገ ፥ በእውነት በላ ፥ ጠጣ ፥ በእውነት ተሰቀለ፥ በእውነት ታመመ ፥ ሞተ ፥ ተቀበረ ፥ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ። አመክ. ፮፥፲፪፣ ማቴ ፩፥፲፰-፳፭ ፣፲፩፥፲፪-፳ ፣ ሉቃ ፪፥፵-፶፪፣፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፫። ይህንን እንዲህ ያመነ ብፁዕ ነው፤ ይህንን የካደ ግን እኛ ተስፋ ከምናደርጋት ከተመሰገነች ሕይወት የተለየ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፪፥፳፭። ወልድ ዋሕድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከፍሉት፣ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ከሆነ በኋላ፦ ሁሉት አካል ሁለት ባሕርይ የሚያደርጉት፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፥ ስለ ስድብ ፥ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው እንጂ ብለው በአመፃቸው ከሚናገሩ  አምላክን ከሰቀሉ ከአይሁድ ጋር ይቆጠራሉ። ዮሐ ፲፥፴፪ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮። በወልደ እግዚአብሔር፦ ድካም ሕፀፅ አለበት የሚሉ፥ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ የሚያደርጉትም ዕድል ፈንታቸው ከከሐድያን አይሁድ ጋር የተካከለ ነው።» ብሏል። ዮሐ ፫፥፴፮፣ (ሃይ፡ አበው ፲፪፥፪-፭)።
          ኢየሱስ ክርስቶስን ሁለት አካል ማለት ሦስት የሆኑትን የሥላሴ አካላት አራት ማድረግ ነው። ሁለት ባሕርይ ማለትም አንድ የሆነውን የሥላሴ ባሕርይ ሁለት ማድረግ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ሐዋርያዊ (እንደ ሐዋርያት የሆነ) ቅዱስ አትናቴዎስ፦ የሃይማኖትን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ፦ «ሰው ሆነ ፥ ስለ ማለት ፈንታም ራሳቸውን ለመጉዳት ልበ ወለድን ነገር ፈጥረው፦ እግዚአብሔር በሰው አደረ አሉ፤ መለኮትና ትስብእት እርስ በርሳቸው ተዋሐዱ ስለ ማለት ፈንታ ሰው ሠራሽን ነገር ፈጥረው ተናገሩ፤ የጌታችን የኢየሱስ አካል አንድ ነው ፥ ስለ ማለት ፈንታ ሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርያት፣ሁለት ገጽ ብለው አመኑ፤ በሦስት አካለት ስለማመን ፈንታም ሊያምኑበት ሊያስተምሩት በማይገባ ሥራ አራት ብለው አመኑ፤» ብሏል። (ሃይ፡አበው ፳፭፥፳)።
          ቅዱስ ባስልዮስ ደግሞ፦ «ይህን አንድ ወልድን፦ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አንለውም፤ መለኮት ፥ በገንዘቡ አካል ፥ በገንዘቡ ባሕርይ ፣ ትስብእትም፦ በገንዘቡ አካል ፥ በገንዘቡ ባሕርይ ልዩ እንደሆኑ አንናገርም፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው ፥ እንላለን እንጂ። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ፣ ፪ኛ ቆሮ ፭፥፲፬። ቅዱስ ጴጥሮስም ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ ብሎ አልተናገረም፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን አምኖ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋ ታመመ አለ እንጂ። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፩።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፪፥፲፱)። ቅዱስ ቴዎዶጦስም፦ «ክርስቶስን የሚለየው ማነው? የአንዱን ስም ምሥጢርስ የሚከፍል ማነው? አንዱን ስም ሁለት ሲሉት ቢገኙ ጥቅሙ ምንድር ነው? አምላክ ሰው ካልሆነ፦ ተራበ ፥ ተጠማ እንዴት ተባለ? ትስብእትን ከእግዚአብሔር ቃል የሚለዩ ፥ በባሕርይ ስም አንድ የሆነውንም የሚከፍሉ ፥ አንዱ ክርስቶስ ሁለት እንደሆነ የሚናገሩ ፥ በነገርም ብቻ አንድ ነው የሚሉ እነዚያ እስኪ ይንገሩን። ፩ኛ ቆሮ ፲፪፥፫፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፶፫፥፴፫)።
          በዚሁ መጽሐፍ በቃለ ግዝት ላይ፦ «አንዱ ከእግዚአብሔር አብ ፥ አንዱ ከድንግል ማርያም ብሎ ሁለት ወልድ የሚል፦ ከእግዚአብሔር የተወለደው ከድንግልም የተወለደው አንድ አይደለም የሚል ቢኖር እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ከነገራቸው ልጅነት ይለይ። እኛ ክርስቶሳውያን ግን በተዋሕዶ ሰው የኾነው አምላክ በእውነት ባሕርዩ አንድ ነው፤ አካሉ አንድ ነው፤ ገጹ አንድ ነው፤ ነፍስም ሥጋም አለው ልንል ይገባናል፤ ሁለት ባሕርያት ፥ ሁለት አካላት ፥ ነፍስና ሥጋም ያለው ስለሆነም፦ አንዱ ሰው ሁለት ነዋ? ለእኛስ ከዚህ ትምህርት አንድነት የለንም፤ በጎላ በተረዳ ልትናገሩት የሚገባውስ ይህ ነው፤ ከድንግል ማርያም ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው የሆነ የእግዚአብሔር አብ ልጅ መድኃኒታችን ክርስቶስ አንድ ነው ፥ ማለት ነው። ይህም በማይነገር በማይመረመር ድንቅ በሚሆን ተዋሕዶ ተደረገ፤ የማይታየው እርሱ ከሚታየው ጋር ፥ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ከሚቆጠርለት ጋር፥ አንድ የኾነው አንዱ ነው፤ ሁለት አይደለም፤ ሳይለወጥ ሰው የኾነ እግዚአብሔር ቃል አንድ ባሕርይ ፥ አንድ አካል ፥ አንድ ገጽ ነው እንጂ፤» ይላል። (ሃይ፡ አበው ፻፳፥፯)

9 comments:

 1. kesis,kale hiwot yasemaln.mestere tewahedo denk new.bemehonum likawent bekalem bemetsafm yastemarutn end neb kesmeh kememh yemar enjera tewahedon selemegebken mesganaye kef yale new.temhertu becha sayhon yequanqua atekakemh fitsum orthodoxawi new.behamer ena betsema tsedk lay yatanewn tsehufehn bezeh menged bemag-gnetachen tedesetenal.behulum besebketem betsehufem endetastemr yetesetehn tsega betekekel eyetetekemkebet new.mechem kene gemero yebezu tsewochen menfesawi hiwot yatsenah,bezuwochenem ketefat kemenafikenet yemelesk bemehoneh enekorabehalen.menfesawi hiwotehm astemari bemehonu bezuwochachen wede sebket yemetanew anten ayten new.selezeh ahunem behon gena bizu neger selemetebekebh berta.betechemarim demtsehn atseman.amlake kidusan yetebekh. yante becha esketmeslh deres yemetwedat emebet ateleyh.

  ReplyDelete
 2. kesis,kale hiwot yasemaln.yetewahedon mester bemegeba teredechalehu.sebket lay becha eyatekorn meseretawewun temehert eyersanew neber.

  ReplyDelete
 3. melake selam,egzeabeher yetebekeh.yebetekerstyanachen temehert rekeknet ena telkenet egek denkognal.lenegeru besenbet temhert bet korse tektateyalehu.neger gen endezeh bezerzer altemarkutem.beteleyem bewechew alem lalenew egeg tekmonal.bertalen.

  ReplyDelete
 4. kesis,kalehiwot yasemalen.bezu legoch des belon yetsafnewn asteyat ayawetam selu semechalehu.menew wedase kentu yehonebegnal beleh new?yeh eko ketselot behuala amen,kesebket behuala kale hiwot yasemalen yemalet yahel new.

  ReplyDelete
 5. kesis,be-ethiopia ena bemelaw alem tezewawreh endalastemark beande bota meweseneh asazagn new.bewere ande wede lela state semechalehu.neger gen beki aydelem.anten hulum selemefelegeh betasebebet teru new.balefew hager bet yalk geze hezbu men yahel endetedesete aytehal.selezeh asebebet.fetari edme ketena yesteh amen.

  ReplyDelete
 6. ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 7. http://freetyping.geezedi.com

  For more information please check out,

  http://appft.uspto.gov/netacgi/nph-Parser?Sect1=PTO2&Sect2=HITOFF&p=1&u=%2Fnetahtml%2FPTO%2Fsearch-bool.html&r=1&f=G&l=50&co1=AND&d=PG01&s1=Aberra&s2=Molla&OS=Aberra+AND+Molla&RS=Aberra+AND+Molla

  ኣመሰግናለሁ!

  ዶ/ር ኣበራ ሞላ

  ReplyDelete
 8. ንጋቱ ወልዴFebruary 16, 2011 at 6:16 AM

  እግዚአብሄር ይስጥልን እድሜ ከጤና ያድልልን ቃለ ኅይወት ያሰማልን አሜን!

  ReplyDelete
 9. እግዚአብሄር ይስጥልን እድሜ ከጤና ያድልልን ቃለ ኅይወት ያሰማልን አሜን!

  ReplyDelete