Saturday, December 11, 2010

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፭

                 
፩፦ «ሰው እናታችን ጽዮን ይላል»

«እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፥ ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ፤ ወውእቱ ልዑል ሣረራ። ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጧም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።» ይላል። መዝ ፹፮፥፭። ቅዱስ ዳዊት ጽዮንን እናት ብሏታል። እናት፦ ወላጅ፥ መገኛ፥የአባት ሁለተኛ ናት። እግዚአብሔር በአሠርቱ ትእዛዛት፦ «አክብር አባከ ወእመከ፤ ከመ ይኩንከ ጽድቀ፥ ወይኑኅ መዋዕሊከ በውስተ ምድር ዘይሁበከ እግዚአብሔር አምላክከ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ (ቸርነቱ ረድኤቱ ይደረግልህ ዘንድ) ፥ እግዚአብሔር አምላክህ በሚስጥህ ምድርም ዕድሜህ እንዲረዝም፤ » እንዳለ፦ እናት ከአባት እኲል ክብር ይገባታል። ዘጸ ፳ ፥፲፪።  ጽዮን ማለት ደግሞ አምባ መጠጊያ ማለት ነው።

፩፥፩፦ የጽዮን ተራራ፤
                               
          ጽዮን ኢየሩሳሌም ከተሠራችባቸው ተራራዎች አንዷ ናት። በመጀመሪያ ኢያቡሳውያን መሸገውባት ይኖሩ ነበር። እነዚህም ከከነዓን የተገኙ ወገኖች ናቸው። ከነዓን የካም ልጅ ፥የኖኅ የልጅ ልጅ ነው። ዘፍ ፲፥፮ ንጉሣቸውን የገደለው ኢያሱ ወልደ ነዌ ነበር። ኢያ ፲፥፳፫። ነገር ግን፥ ንጉሥ ዳዊት፦ እስኪያስለቅቃቸው ድረስ ጽዮን የተባለች አምባቸው በእጃቸው ነበረች። ኢያ ፲፭፥፷፫። በጽዮን ላይ ኢያቡስ የሚባል አምባም ነበራቸው።  መሳ ፲፱፥፲።

ንጉሥ ዳዊት በኬብሮን ለሰባት ዓመታት ከነገሠ በኋላ ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። እነርሱም ዳዊት ወደዚህ ሊገባ አይችልም ብለው አስበው ነበር። ነገር ግን፥ ዳዊት፦ አምባይቱን ጽዮንን ይዞ በዚያ ተቀመጠ። የዳዊት ከተማ ብሎ የሰየማትን ይህቺን አምባም ዙሪያዋን፦ ከሚሎ ጀምሮ ወደ ውስጥ በግንብ አጠራት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለነበረ እየበረታ ሄደ። ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገ አወቀ። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፩-፲፪።

ጽዮን የሚለው ስም በኋላ ላይ ለሞሪያ ተራራ ተሰጥቷል። ይኸውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በዚያ ስለተሠራ ነው። ሞሪያ፦ አብርሃም ይስሐቅን ለመሠዋት የሄደበት ተራራ ነው። በዚያ መሠዊያ ሠርቶ ልጁን ለእግዚአብሔር አቅርቧል። እግዚአብሔር ከላይ ከሰማይ ጠርቶ፦ «እምነትህ ታይቷልና፥ በብላቴናው ላይ እጅህን አንዳትዘረጋ፤» ባይለው ኖሮ፥ ስለቱን በአንገቱ ላይ አሳርፎ ነበር። ሊቃውንቱ በኅሊናው ሠውቶታል፦ ይላሉ። በመጨረሻም እግዚአብሔር ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ ነጭ በግ አሳይቶት ስለ ይስሐቅ ፈንታ ሰውቶታል። ዘፍ ፳፪፥፩። ይህም ለነገረ ድኅነት ምሳሌ ነው። ዕፀ ሳቤቅ የእመቤታችን፥ በግ የክርስቶስ፥ ይስሐቅ ደግሞ የአዳም ምሳሌዎች ናቸው። ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሠራው በዚህ ቦታ ላይ ነው። ይኸንን በተመለከተ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ላይ፦ «ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ላይ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።» የሚል ተጽፏል። ፪ኛ ዜና ፫፥፩።

ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚ አብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።» ብሏል ኢሳ ፲፥፲፰። ምልክት የተባለው የሰናክሬም ጥፋት፦ የብልጣሶር ሞት ነው። ሰናክ ሬም ከ705-681 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነገሠ የአሦር ንጉሥ ነው። በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት፥ ቤተ መቅደስን ለማፍረስ ብዙ ሺህ ሠራዊት አሰልፎ ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ስለቀሠፋቸው፦ በአንድ ሌሊት አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ሠራዊት በድኖች ሆነው አድረዋል። እርሱም ወደ ነነዌ ተመልሶ ለጣዖት ሲሰግድ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ ገድለውታል። የገደሉትም፦ «ሕዝቡን አስጨርሰህ መጥተህ ፥ እኛ በማን ላይ ልንነግሥ ነው፤ » ብለው ነው። የሥልጣን ነገ ር እንዲህ ነው። ፪ኛ ነገ ፲፰፥፴፭፣ ኢሳ ፴፮፥፴፯ ብልጣሶር ደግሞ የናቡከደነፆር የልጅ ልጅ የናቦኒዶስ ልጅ ነው። ይህ ሰው በሺህ ለሚቆጠሩ መኳንንቱ በቤተ መንግሥት ታላቅ ግብዣ አደረገ። በፊታቸውም የወይንጠጅ ይጠጣ ነበር። በሰከረም ጊዜ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ዘርፎ ያመጣቸውን፥ እግዚአብሔር ብቻ የሚገለገልባቸውን ቅዱሳት ንዋያት፥ (የወርቅ የብር ጽዋውን፥ ጻሕሉን)፥ መኳንንቱ፥ ሚስቶቹና ቁባቶቹ እንዲበሉበት እንዲጠጡበት አደረገ። እነርሱም እየበሉ እየጠጡ አማልክቶቻቸውን (ጣዖቶቻቸውን) አመሰገኑ። በዚያም ሰዓት በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ በመቅረዙ አንጻር የሰው እጅ ጣቶች ሲጽፉ፥ ንጉሡ በገሀድ አይቶ፦ ወገቡ እስኪላቀቅ፥ ጉልበቱን እስኪብረከረክ ድረስ ደነገጠ። የተጻፈው ጽሑፍ ምን እንደሆነ እስከነትርጉሙ እንዲነግሩትም ወደ አስማተኞቹ ጮኸ። ነገር ግን፥ ነገሩ የመጣው ከእግዚአብሔር በመሆኑ፥ ንባቡንም ትርጉሙንም ሊነግሩት አልቻሉም በዚህን ጊዜ ነቢዩ ዳንኤል ተጠርቶ መጣ። ንጉሡንም ከናቡከደነፆር ጥፋት ሊማር ባለመቻሉ ገሠጸው። በመጨረሻም፦ «የተጻፈው ጽሕፈት ማኔ፥ ቴቄል ፋሬስ ይላል። ማኔ ማለት፦ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፦ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፦ መንግሥትህ ተከፈለ፤ ለሜዶንና ላፋርስ ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው።» በማለት ተርጉሞታል። በዚያም ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገድሏል። ዳን ፭፥፩-፴  ደብረ ጽዮንን የደፈሩ ሁሉ እንዲህ መጨረሻቸው አላማረም።

በሌላ በኲል ደግሞ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ በደብረ ጽዮን ለእግዚአብሔር ክብር የሚደረገውን ሲናገር፦ «በዚያ ዘመን ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር፥ ከተዋረደና ከደከመ ሕዝብ፥ ከዛሬ እስከ ዘለዓለም ታላቅ ከሆነ ወገን፥ ተስፋ ከሚያደርግና ከሚረገጥ፥ በሀገሩ ወንዝ ዳር ከሚኖር ሕዝብ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም በተጠራበት በደብረ ጽዮን እጅ መንሻ ይቀርባል፤» ብሏል። ኢሳ ፲፰ ፥፯። ከዚህም በተጨማሪ፦ «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣ ልና፥ በሸማግሌዎቹም ፊት ይከብራል። (በሊቃውንቱ ይመሰገናል)።» ብሏል ኢሳ ፳፩፥፳፫

ደብረ ጽዮን እግዚአብሔር ኃይሉን በረድኤት የሚገልጥባት፥ በረከቱን የሚሰጥባት፥ ቸርነቱን የሚያሳይባት፥ ጸሎትና ምልጃ ምስጋናም የሚቀበልባት፥ መሥዋዕት የሚያርግባት፥ ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙባት የሚታረቁባት ስፍራ ናት። ያከበሯትን የምታስከብር፥ የደፈሯትን የምታሥቀስፍ የእግዚአብሔር ስፍራ ናት። እነ ናቡከደነፆር ወደ አውሬነት ተለውጠው፥ ከአራዊት ጋር ተቀላቅለው፥ ለሰባት ዓመታት እንደ ከብት ሣር እየነጩ ኖረዋል። ዳን ፬፥፴፫። በዚህም፦

፩፡፪፦ ታቦተ ጽዮን፤

የነቢያት አለቃ ሙሴ፦ እግዚአብሔር፦ «አስቀድመህ እንዳየሃቸው ዓይነት አድርገህ ጽላት አዘጋጅ፥ ቃሎቹን እኔ እቀርጽባቸዋለሁ።» ባለው መሠረት ሁለት ጽላት አዘጋጅቷል። ያንንም ይዞ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሟል። እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም። በጽላቱም ላይ አሥሩን የኪዳን ቃሎች እግዚአብሔር ፈቅዶለት ቀረጸ። ጽላቱንም ይዞ ከደብረ ሲና በወረደ ጊዜ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ተናጋግሮ ነበርና ፊቱ አንጸባረቀ። ዘጸ ፴፬፥፩፥፳፱። ከዚያ በፊት ለጽላቱ ማኖሪያ ታቦት እንዲያዘጋጅ እግዚአብሔር ነግሮት ነበር። ታቦቱም በውስጥም በአፍአም በወርቅ ተለብጦ ነበር። መክደኛውም በወርቅ የተሠራ ነበር። በላዩም ሁለት የኪሩቤል ሥዕል ተቀርጾ በወርቅ ተለብጦ ነበር። እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት ስለ ታቦቱ ክብር በታቦቱ ዙሪያ የወርቅ አክሊል አድርጐለት ነበር። በመጨረሻም፦ «በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እናገርሃለሁ። » ሲል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሰጥቶታል። ዘጸ ፳፭፥፩-፳፪

የነቢያት አለቃ ሙሴ ታቦቱን ወደ ማደሪያው ካስገባ በኋላ በመጋረጃ ሸፍኖታል። በእግዚአብሔር ማደሪያ፥ በመገናኛው ድንኳን ሊሠራው የሚገባውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ከደነው። የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላው። ደመናው በላዩ ስለነበረ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለሞላው ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም ነበር። ዘጸ ፵፥፳-፴፰

፩፡፪፥፩፦ ታቦቱና ኢያሱ፤

እሥራኤል ዘሥጋ በጉዟቸው ሁሉ ታቦቱን ይከተሉ ነበር። በእነርሱና በታቦቱ መካከል ያለውም ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ነበር። በኢያሱ መሪነት ከዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ታቦቱን ያከበሩት ካህናት እግሮቻቸው ከወንዙ መጥለቅ ሲጀምር ውኃው ተቋረጠ። ሕዝቡም በደረቅ ተሻገሩ። የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር። ሕዝቡ በጠቅላላ ከተሻገረ በኋላም ከዮርዳኖስ ሲወጡ ውኃው እንደቀድሞው ተመለሰ። እግዚአብሔር ኃይሉን የገለጠው በታቦቱ ላይ ነው። ኢያ ፫፥፩-፲፯፤፬፥፩-፳፬። ታላቁ የኢያሪኮ ግንብም የፈረሰላቸው ሰባት ቀን ታቦቱን አክብረው በግንቡ ዙሪያ በመዞራቸው ነው። እንዲህ እንዲያደርጉ ያዘዘቸውም እግዚአብሔር ነበር። «እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን፥ ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። ሰልፈኞቻችሁ ሁሉ ከተማይቱን አንድ ጊዜ ይዙሯት፤ እንዲህም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከት ይንፉ። ቀንደ መለከቱን ባለማቋረጥ ሲነፉ ፥ የመለከቱንም ድምጽ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ አለው፤» ይላል። ኢያ ፮፥፪-፮። ኢያሱ በነገር ሁሉ ከጧት እስከ ማታ በታቦቱ ፊት እየሰገደ እግዚአብሔርን ይማጸን ነበር። እግዚአብሔርም ቃል በቃል ያነጋግረው፥ ማድረግ የሚገባውንም ይነግረው ነበር። ኢያ ፯፥፮-፱።

፩፡፪፥፪፦ የታቦተ ጽዮን መማረክ፤

ታቦቱ፦ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅርብ በሆኑ ሰዎች፥ በአፍኒን እና በፊንሐስ የድፍረት ኃጢአት የተነሣ በፍልስጥኤማውያን የተማረከበት ጊዜ ነበር። አፍኒን እና ፊንሐስ የሊቀ ካህናቱ የዔሊ ልጆች ናቸው። እግዚአብሔርን የማያውቁ ምናምንቴዎች ነበሩ። በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ያመነዝሩ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲፪፣፳፪። በዚህ ምክንያት ለፈተና ጦርነት መጣ። በጦርነቱም ላይ አፍኒን እና ፊንሐስ ተቀሰፉ። ታቦቷም ተማረከች። ዔሊም ይህን መርዶ ሰምቶ፥ ከተቀመጠበት ወንበር ወድቆ፥ አንገቱ ተቆልምሞ ሞተ። ፩ኛ ሳሙ ፬፥፩-፲፰

ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጐን ቤት (ወደ ቤተ ጣዖት) አገቡት። በዳጎንም አጠገብ አኖሩ ት። በማግሥቱ ዳጎን የሰው እጅ ሳይነካው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ ወድቆ (ሰግዶ) ተገኘ። አንሥተውም ወደ ሥፍ ራው መለሱት። አሁንም ዳጐን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ አገኙት። ራሱና እጆቹም ተቈራርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር። በመጨረሻም፦ አዛጦን፥ ጌት፥ አስቀሎና፥ በሚባሉ የፍልስጥኤም ከተሞች ላይ የእግዚአብሔር እጅ ከበደችባቸው። እግዚአብሔር በእባጭ ቊስል መታቸው። ሕዝቡም፦ «እኛንና ሕዝባችንን ሊገድሉ የእስራኤልን አምላክ ታቦት አመ ጡብን፤» ብለው ጮኹ። በከተሞቹ ሁሉ የሞት ድንጋጤ ነበር። ብዙ ሰዎችም እየተቀሠፉ ሞተው ነበር። በዚህን ጊዜ ልከው የፍል ስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው፦ «የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱ፥ እኛንና ሕዝባችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመ ለስ፤» አሉ። ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ፤ ፪ኛ ሳሙ ፭፥፩፥፲፪

፩፡፪፥፫ ፦ ታቦቱና የቤትሳሚስ ሰዎች፤

ከሰባት ወር በኋላ፥ ታቦቱን አክብረው፥ ከወርቅ እጅ መንሻ ጋር፥ በሰረገላ ላይ ጭነው መለሱ። ሰረገላውን ይስቡ የነበሩት ሰዎች ታቦቱን እስከ ቤትሳሚስ ድረስ ሸኙ። የቤትሳሚስ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር። የታቦቱንም መምጣት አይተው ደስ አላቸው። የሰረገላውንም እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውንም የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሣጥን አወረዱ። በታላቁም ድንጋይ ላይ አኖሩት። በዚህ አጋጣሚ፦ የቤትሳሚስ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ታቦት ውስጥ ተመልክተው ስለነበረ እግዚአብሔር ከአምስት ሽህ ሰዎች መካከል ሰበዓውን መታቸው። እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግድያ ስለመታ ሕዝቡ አለቀሰ። የቤትሳሚስም ሰዎች፦ «በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል?» አሉ። ምክንያቱም በታቦቱ ፊት መቆም በእግዚአብሔር ፊት መቆም ነውና።  ፩ኛ ሳሙ ፮፥፩፥፳፩

፩፡፪፥፬፦ ታቦቱና ዖዛ፤

የእግዚአብሔር ታቦት ከፍልስጥኤም ምድር ከተመለሰ በኋላ በአሚናዳብ ቤት ለሃያ ዓመታት ተቀምጧል። የእግዚአብሔርን ታቦት ለመጠበቅ የተቀደሰው የአሚናዳብ ልጅ አልዓዛር ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፯፥፩-፪። በኋላ ግን ንጉሡ ዳዊት ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ያህል ሰዎች ሰብስቦ ታቦቱን ለመቀበል ተዘጋጀ። እነርሱም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ወደ አሚናዳብ ቤት ሄዱ። በአዲስ ሰረገላም ጫኑት። የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር። ንጉሡ ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና፥ በመስንቆም በከበሮም፥ በነጋሪትና በጸናጽል፥ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይዘምሩ ነበር። አሁንም በእግዚአብሔር ፊት የተባለው በታቦቱ ፊት የፈጸሙት አገልግሎት ነው።

ወደ ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና (እምቧ እያሉ እየዘለሉ ያመሰግኑ ነበርና) ታቦቱ ተነቃነቀ። በዚ ህን ጊዜ ዖዛ ሳይገባው እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦተ ያዘ፤ ሳይገባው፥ ሥልጣን ሳይኖረው ነክቷልና የእግዚአብሔር ቊጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ ስለ ድፍረቱም በዚያው ቀሠፈው። በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፩-፲

፩፡፪-፭፦ ታቦቱና አቢዳራ፤

ንጉሡ ዳዊት ደፋሩ ዖዛ እንደተቀሠፈ አይቶ እግዚአብሔርን ፈራ። «የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል?» አለ። በዚህ የተነሣ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማው ይወስድ ዘንድ አልወደደም። አለመውደዱም እግዚአብሔርን ከመፍራት የተነሣ፥ በነዖዛ የደረሰ በእኔም ይደርስብኛል ከማለት እንጂ በሌላ አይደለም። ወደ አቢዳራ ቤትም አገባው። አቢዳራም ልክ እንደ አሚናዳብ ቤቱን ለእግዚአብሔር ታቦት ለቀቀ። ታቦቱም በዚያ ለሦስት ወራት ያህል ተቀመጠ። እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። በረከት በግቢም በውጪም ተትረፈረፈ። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፲፩።

፩፡፪፥፮፦ ዳዊትና ታቦቱ፤

ከሦስት ወር በኋላ ንጉሥ ዳዊት፦ እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት እንደ ባረከ ሰማ። በዚህን ጊዜ በዖዛ መቀሠፍ የደነገጠው ኅሊናው ፥ የፈራው ልቡናው ፥ የተብረከረከው ጉልበቱ መለስ አለ። ሄዶም የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው በደስታ አመጣው። ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ሰባት መሰንቆ የሚመቱ ክፍሎች ነበሩ። የእንስሳት መሥዋዕትን ይሠዉ ነበር። ዳዊትም ለዓይን የሚያንጸባርቅ ቀሚስ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት በገና ይደረድር ነበር። በእግዚአብሔር ፊት የተባለው በታቦቱ ፊት የተፈጸመው አገልግሎት ነው። የእሥራኤል ቤት ሁሉ በእልልታ ቀንደ መለከት እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ።

፩፡፪፥፯፦ የሜልኮል ንቀትና የዳዊት አገልግሎት፤

ሜልኮል፦ ከሳኦል ሴቶች ልጆች ታናሽቱና የዳዊት ሚስት ናት። ታቦቱን ለመቀበል ከቤት አልወጣችም። በመስኮት ሆና ስትመለከት፦ ንጉሡ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘምር አይታ በልቧ ናቀችው። የእግዚአብሔርንም ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት። ንጉሡ ዳዊትም የሚቃጠልና የሰላም መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት ካሳረገ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቃቻው። ቤተሰቡንም ለመመረቅ በተመለሰ ጊዜ ሜልኮል ልትቀበለው ወጣችና ፦ « ከተርታ ዘፋኞች እንዳንዱ ፦ የእስራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ ሚስቶች ፊት በመገለጡ ምንኛ የተከበረ ነው ። » በማለት አላገጠችበት። ንጉሡ ዳዊት ግን ፦ «በእግዚአብሔር ፊት እዘምራለሁ ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ፤ እዘ ምራለሁም ፤ አሁንም እገለጣለሁ ፤ በዓይንሽ ፊትና እንዴት? ከበርህ ባልሽባቸው ሴቶች ልጆች ፊት የተናቅሁ እሆናለሁ።» አላት። ሜልኮል፦ ለታቦቱም፥ ለአገልግሎቱም ፥ ለዳዊትም ክብር ባለመስጠቷ እግዚአብሔር ማኅፀኗን ዘጋው ፥ እስከሞተችበት ቀን ድረ ስም ልጅ አልወለደችም። እግዚአብሔር አልጋ ወራሽ የሆነ ልጅ እንዳትወልድ አደረጋት።

ንጉሡ ዳዊት ታቦቱን ወደ ጽዮን በማምጣቱ በዚህ ምክንያት ታቦተ ጽዮን ሊባል ችሏል። በዚህም ደብረ ጽዮን እንዲል፦ ታቦተ ጽዮን ተብሎ ይጠራል ማለት ነው።

፩፥፫ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን፤

 ቤተ ክርስቲያንም ጽዮን ትባላለች። ደብረ ጽዮን የሚሠዋበት መሥዋዕተ ኦሪት ነበር። በደብረ ጽዮን ዘሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ግን የሚሠዋው መሥዋዕተ ሐዲስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። « በጽዮን መለከት ንፉ፤ በቅዱሱም ተራራ ላይ ዓዋጅ ንገሩ፤» እንደተባለ፦ ሐዲስ ሕግ ወንጌል ይታወጅባታል። ኢዩ ፪፥፩። በተጨማሪም፦ «በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ምሕላንም ዓውጁ፤» የሚል አለ። ኢዩ ፪ ፥፲፭። በመሆኑም ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት ይታወጅባታል። ጸሎተ ምሕላ ይያዝባታል። ጡት ከሚጠ ቡት ሕፃናት ጀምሮ እስከ ሽማግሌዎቹ ድረስ ሕዝቡን ሰብስቡ፤ እንደተባለ፦ ሁሉም ለቅዳሴ፥ለማኅሌት፥ ለሰዓታት ፥ ለመዝሙር ይሰ በሰቡባታል። ሕፃናት በአርባ በሰማኒያ ቀን እየተጠመቁ አባል ይሆኑባታል። ጌታችን በወንጌል፦ «ሕፃናትን ተዉአቸው፤ ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፲፱ ፥፲፬። ለሐዋርያው ለቅዱስ ጴጥሮስም፦ ሕፃናቱን ፥ ወጣቶቹን እና አ ረጋውያኑን፦ በግልገሎች ፥ በጠቦቶችና በበጎች መስሎ ጠብቃቸው ብሎታል። ዮሐ ፳፩፥፲፭።
፩፥፬፦ ጽዮን ማርያም ፤

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «ጽዮን» ተብላ ትጠራለች። ምክንያቱም ጽዮን ማለት አምባ መጠጊያ ማለት እንደ ሆነ ሁሉ እመቤታችንም፦ ለነፍስና ለሥጋ ፥ለኃጥአንና ለጻድቃን፥ አምባ መጠጊያ ናትና። ቅዱስ ዳዊት፦ «እስመ ኀረያ እግዚ አብሔር ለጽዮን ፥ ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ ፥ ዛቲ ይእቲ ምእራፍየ ለዓለም፤ ዝየ አኅደር እስመ ኅረይክዋ። እግዚአብሔር ጽዮን መርጧታልና ፥ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።» ያለው እመቤታችንን ነው። መዝ ፩፻፴፮ ፥ ፲፫። ምክንያቱም ፦ ለእናትነት መርጦ ያደረው በእርሷ ማኅፀን ነውና። «ለ ዘላለም መረፊያዬ ናት፤» ማለቱም፦ እርሱ የዘለዓለም አምላክ እንደሆነ ፥ እርሷም ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ ተብላ እንደምትኖር የሚያመለክት ነው። በሌላ ምዕራፍም፦ « ደብረ ጽዮን ዘአፍቀረ ፥ ሐነፀ መቅደሶ በአርያም ፥ወሳረረ ውስተ ምድር ዘለዓለም። የወደ ደውን የጽዮንን ተራራ ፥ መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ። ለዘለዓለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።» ብሏል። መዝ ፸፯፥፷፰።

ጽርሐ አርያም ከሰባቱ ሰማያት አንዱ ነው። በዚያ፦ ኪሩቤል የሚሸክሙት ፥ ሱራፌል የሚያጥኑት የእግዚአብሔር የእሳት ዙፋን አለ። ዙፋኑም በሰባት የእሳት መጋረጃዎች የተጋረደ ነው። ኢሳ ፮፥፩ ፣፪ኛ ሳሙ ፬፥፬ ፣ ሕዝ ፩፥፭-፲፰ ፣ ራእ ፬፥፮-፱። ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ፦ እመቤታችንን፦ «በሰማይ ባለ ጽርሐ አርያም ፈንታ በምድር ላይ አርያምን ሆንሽ፤» ብሏታል። ከ ዚህም፦ ቅዱስ ዳዊት «የወደደውን የጽዮንን ተራራ፥ መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፤» ያለው ለእመቤታችን እንደሆነ እንረዳለን።

ድንግልናዋን በተመለከተም፦ «ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ፥ ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጸዮን ፥ እስመ አጽንዐ መናግሥተ ኆኃትኪ ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ ፥ ጽዮንም ሆይ አምላክሽን አመስግኚ ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፤» ብሏል። መዝ ፩፻፵፯፥፩። ይህም ፦ ለጊዜው ለከተማይቱ ሲሆን ለፍጸሜው ለእመቤታችን ነው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ኢየሩሳሌም ፥ ጽዮን ፥ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር አምላክን በድንግልና በፀነ ሰች ጊዜ፦ «ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች። ልቡናዬም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች።» በማለት አመስግናለች። ሉቃ ፩፥፵፮። የእርሷ ሰውነት፦ የሥጋን ንጽሕና ፥ የልብን ንጽሕና ፥ የነፍስን ንጽሕና ፥ አስተባብራ አንድ አድርጋ ይዛ የተገኘች ናት። «የዶጆችሽን መወርወሪያ አጽንቷልና፤» የተባለውም ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን ነው። እመቤታችን፦ ቅድመ ወሊድ ፥ ጊዜ ወሊድ ፥ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና። ይኽንንም ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ፤ ወንድ ልጅም (ወልድን) ትወልዳለች ፤ ስሙ ንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።» በማለት ተናግሯል። ኢሳ ፯፥፲፬። ነቢዩ ሕዝቅኤልም፦ «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስ ተውጭ ወዳለው በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ (ድንግል ማር ያም ለዘለዓለም በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)። ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘ ግታ ትኖራለች። (አምላክ በማኅፀኗ ተፀንሶ፥ ከእርሷ ተወልዷልና በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)።» ብሏል። ሕዝ ፵፬፥፩-፪።

ደብረ ጽዮንና ታቦተ ጽዮን ምሳሌዋ የሆኑላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረላት፦ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላታል። ይህም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፥ ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ በፈጸመ ጊዜ ፥ ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስን፦ «እነኋት እናትህ፤» ብሎታል። ዮሐ ፲፱፥፳፭።

፩፥፭፦ ጽዮን መንግሥተ ሰማያት፤
                  
የምእመናን ሁሉ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትም ጽዮን ተብላለች። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እናንተ ግን የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ፥ በሰማያት ወዳለችው ኢየሩሳሌም ፥ ደስ ብሏቸው ወደሚኖሩ አእላፍ መላእክት ደርሳችኋል። ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈ ወደ ማኅበረ በኲርም፥ ሁሉን ወደሚገዛም ወደ እግዚአብሔር ፥ ወደ ፍጹማን ጻድቃን ነፍሳት ፥ የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደ ሚሆን ኢየሱስ ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ ተረጨው ደም ደርሳችኋል። » ብሏል። ዕብ ፲፪፥፳፪-፳፬። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ፦ በራእይ መጽሐፉ ላይ ፦«እነሆ ፥ በጉን (ኢየሱስ ክርስቶስን) በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ አየሁ፤ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግንባራቸው የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ ፥ ደርዳሪዎችም እንደሚደረድሩት በገና ድምፅ ያለውን ሰማሁ። በዙፋኑም ፊት በአራቱ እንስሶችና (በኪሩቤልና) በአለቆቹ ፊት (በሱ ራፌል ፊት) አዲስ ምስጋናን አመሰገኑ። ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺህ በቀር ፦ (ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሰማዕታተ ሕፃ ናት በቀር) ያን ምስጋና ሊያውቅ ለማንም አልተቻለውም። ከሴቶችም ያልረከሱ እነዚህ ናቸው ፤ ደናግል ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበ ት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኲራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአንደበታቸውም ሐሰት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውምና፤ » ብሏል። ራእ ፲፬፥፩-፭። እግዚአብሔር በቅዱስ ዳዊት አንደበት፦ «እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ ፥ በተቀደሰ ተራራው በጽዮን ላይ።» ማለቱ ፦ ለጊዜው በዳዊት ከተማ በደብረ ጽዮን በረድ ኤት እንደሚገለጥ ሲሆ ን ፦ ለፍጻሜው ግን ማኅፀነ ድንግል ማርያምን መናገሻ ከተማ እንደሚያደርግ የሚያመለክት ነበር። በኋላም በምጽአት የጽዮን ተራራ በተባለች በመንግሥተ ሰማያት እንደ ባህርይ ንጉሥነቱ በእሳት ዙፋን እንደሚገለጥ ያመለክታል። መዝ ፪፥፮። በመሆኑም የሕይወት አክሊል(የክብር መጨረሻ፥ የክብር መደምደሚያ) የሆነች መንግሥተ ሰማያትም እናታችን ትባላለች። እናት ልጆቿን ችግር ላይ እንዳይወድቁባት ሰብስባ እንደምትይዛቸው፥ መንግሥተ ሰማያትም፦ ልጆቿ ወደገሃነመ እሳት እንዳይወድቁባት እንደ እናት ሰብስባ ትይዛቸዋለች።

3 comments:

 1. kale hiwot yasemalen abatachin

  ReplyDelete
 2. Kidus wwek Mahibere SelamDecember 12, 2010 at 9:14 PM

  ቀሲስ እድሜ ይስጥልን፡፡

  ለመጀመሪያ ጊዜ http://www.betedejene.org/ በሚለው ተጠቅሜ የብሎግዎት ተጠቃሚ ለመሆን በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡

  እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

  ReplyDelete
 3. Live long life for us!

  ReplyDelete