Sunday, December 19, 2010

ነገረ ቅዱሳን ክፍል፦ ፯

፩፦ የባህርይ ጌታ
          ጌታ የግብር፣ የክብር፣ የማዕረግ ስም ነው። ትርጓሜውም፦ ገዥ፥ ሹም፥ ባለቤት፥ መምህር፥ ታላቅ ማለት ነው። በመሆኑም፦ የፍጥረት ገዥና አዛዥ የሆነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ጌታ ነው። (ጌነት የባ ህይ ገንዘቡ ነው)። ቅዱስ ዳዊት፦ «የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል።» እንዳለ ቅዱሳን መላእክት ለጌትነቱ ተንበርክከዋል። መዝ ፺፮፥፯፤ ዕብ ፩፥፮። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊም፦ «እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱ ለት፤» እንዳለ የሰው ልጆችም ለጌትነቱ ተንበርክከዋል። ማቴ ፳፰፥፱። ነሳት ባሕርና ማዕበላትም ለጌትነቱ ተገዝተዋል። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው፦ «ባሕርና ነሳትስ እንኳ የሚታዘዙለት ይህ ማነው?» እያሉ አድንቀዋል። ማቴ ፲፥፳፮። አጋንንትም፦ «የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? (አንተን የምንቃወምበት ምን ኃይል፥ ምን ሥልጣን አለን?) ጊዜው (ዕለተ ዓርብ፥ ዕለተ ምጽአት) ሳይደርስ ልታሠቃየን (ልትፈርድብን) ወደዚህ መጣህን? . . . ከሰው ልቡና ካወጣኸንስ በእሪያዎቹ መንጋ እንድናድር ወደዚያ ስደደን።» እያሉ፥ እየለመኑት ለጌትነቱ ተገዝተዋል። ማቴ ፰፥፳፱። በተሰቀለበት ዕለት ደግሞ ምድር በመነዋወጥ፥ መቃብራት በመከፈት፥ ታላላቅ ዐለቶች በመሰነጣጠቅ ፀሐይ በመጨለም፥ ጨረቃ ደም በመምሰል፥ ከዋክብት በመርገፍ ለጌትነቱ ተገዝተዋል። ማቴ ፳፯፥፵፭፣ ማር ፲፭፥፴፫፣ ሉቃ ፳፫፥፵፬፣
          ጌታችንን፦ ለምጻሙ ሰው፦ «ጌታ ሆ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤» እያለ ቀርቦ ሰግዶለታል። ማቴ ፲፥፪ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በታንኳ በባሕር ላይ በሚጓዝበት ጊዜም ብርቱ ማዕበል በመነሣቱ፦ «ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን፤» ብለውታል። ማቴ ፲፥፳፱። ከነዓናዊቷም ሴት ስለ ልጇ በማለደችው ጊዜ «ጌታ ሆይ እርዳኝ፤» እያለች ሰግዳለታለች። ማቴ ፲፭፥፳፭። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌትነቱን ክብር በደብረ ታቦር በገለጠ ጊዜ፦ ፊቱ እን ፀሐይ በርቷል፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጸብራቅ ሆኗል። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን አይቶ፦ «ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው።» ብሏል። ማቴ ፲፯፥፬። ከተራራው በወረደ ጊዜም፦ አንድ ሰው በጉልበቱ ተንበርክኮ እየሰገደ፦ «ጌታ ሆይ ልጄን ማርልኝ» ብሎታል። ማቴ ፲፯፥፲፭።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈሪሳውያንን እና ሰዱቃውያንን፦ «ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው?» ብሎ ጠይቋቸው ነበር። እነርሱም፦ «የዳዊት ልጅ ነው፤» አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ ዳዊት፦ «ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፦ አለው፤ ሲል እንዴት በመንፈስ (በትንቢት) ታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል?» አላቸው። እንዲህ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ አንዳችም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም። ከዚያ ቀንም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። «ጌታ፥ ጌታዬን፤»የሚለው ትርጉሙ፦ «ጌታዬ እግዚአብሔር አብ፥ጌታዬ እግዚአብሔር ወልድን፤» ማለት ነው። መዝ ፻፱፥፩፣ ማቴ ፳፪፥፵፩። ቅድስት ኤልሳቤጥ፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎበኘቻት ጊዜ፦ «የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆናልኛል?» ያለችው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ጌታ በመሆኑ ነው። ሉቃ ፩፥፵፫። ቅዱስ ቶማስም በእጆቹ ከዳሰሰው በኋላ፦ «ጌታዬ አምላኬም፤» ብሎታል። ዮሐ ፳፥፳፰። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ «የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ለሚጠሩት ሁሉ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።»  ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፪ በተጨማሪም «ሁሉ በእርሱ የሆነ፥ እኛም በእርሱ የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ፤» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ከዚህም ሌላ አንድ ጌታ ሲሆን፥ ልዩ ልዩ አገልግሎት እንዳለ ተናግሯል። ፩ኛ ቆሮ ፲፪፥፭። ይህ ሐዋርያ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱም፦ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የጌቶች ጌታ፣» ብሎታል። ፩ኛ ጢሞ ፮፥፲፭። ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ «የጌቶች ጌታ የሚል ስም አለው፤» ብሎናል። ራእ ፲፱፥፲፩። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የጌቶች ጌታ፤» የተባለው፦ ቅዱሳን በጸጋ ጌቶች በመሆናቸው ነው።
፪፦ የጸጋ ጌቶች (አጋዕዝት ዘጸጋ)፤
          ቅዱሳን ስለተሰጣቸው ጸጋ ከፍ ያለ ክብርና ማዕረግ ስላላቸው ጌቶች ናቸው፥ ጌቶችም ተብለው ይጠራሉ። ይህ ጸጋ፥ ክብርና ማዕረግ ከእግዚአብሔር ነው። ይኸንን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «ሰውነቴ በእግዚአብሔር ትከብራለች፤» ብሏል። መዝ ፴፫፥፪። ሐርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «ያጸደቃቸውንም እነዚህን አከበራቸው፤» ብሏል። ሮሜ ፰፥፴። በመሆኑም ቅዱስ የሚለው ለቅዱሳን እንደሚቀጸልላቸው ሁሉ፦ ጌታ፦ የሚለውም ይቀጸልላቸዋል። ጌታዬ አብርሃም ፥ ጌታዬ ሙሴ ፥ ጌታዬ ዮሴፍ ፥ ጌታዬ ጳውሎስ ፥ እንላቸዋለን። ጌታ፦ ያሰኛቸውም የማይሰፈረው ፥ የማይቆጠረው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው።
                                  ፪፥፩፦ ጌታ አብርሃም፤
          እግዚአብሔር፦ አብርሃምን መርጦ እንዳከበረው የምታውቅ ሣራ፦ «ጌታዬ» ኢያለች ትጠራው፥ ትታዘዘውም ነበር። ወደ ድንኳናቸው በእንግድነት የገቡ ቅድስት ሥላሴ፦ «የዛሬ ዓመት እንደሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስት ሣራም ልጅን ታገኛለች፤» ብለው ለአብርሃም ቃል ሲገቡለት ሰምታ፦ «እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ጽሞ ሸምግሏል፤» ብላለች ዘፍ ፲፰፥፲፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ላይ ተመሥርቶ፦ «ቀድሞም እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ የተቀደሱ ሴቶች እንዲሁ ለባሎቻቸው በመገዛት ራሳቸውን ያስጌጡ ነበር። እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ትታዘዘው ነበር፤ ጌታዬም ትለው ነበር፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር ምንም ሳትፈሩ በበጎ ሥራ ልጆችዋ ሁኑ።» በማለት አስተምሮበታል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፭።
          አብርሃም በከነዓን ሲኖር ጢያውያንም በሰሜኑ ክፍል በዚያ ይኖሩ ነበር። እነዚህም ከከነዓን የተገኙ ወገኖች ናቸው። ዘፍ ፲፥፲፭። ከነዓን የካም ልጅ፥ የኖኅ የልጅ ልጅ ነው የአብርሃም ሚስት ሣራ አንድ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ሲሆናት፦ በቈላ አውራጃ ባለች አርባቅ በምትባል ሀገር ሞተች። ይህችውም በከነዓን ውስጥ ያለች ኬብሮን ናት። አብርሃምም፦ ለሚስቱ ለሣራ ፈጽሞ ሲያለቅስላት ከቆየ በኋላ የጢን ልጆች፦ «እኔ ከእናንተ ጋር ይህን ያህል ዘመን ስኖር መጻተኛ ነኝ፤ እንደ እናንተ እናንተን መስዬ እኖር ዘንድ የመቃብር ቦታ በጋ ሽጡልኝ፤» አላቸው። እነርሱም፦ «ጌታችን ሆይ፥ የምንነግርህን ነገር ስማ፤ ከእግዚአብሔር ታዝዘህ የመጣህ ንጉሣችን አንተ ነህና፤ እኛ ከምንቀበርበት ከወደድኸው ቦታ ሬሣህን ቅበር፤ ይህን እንዳታደርግ ከእኛ ወገን የሚከለክልህ የለም፤» አሉት። አብርሃምም የኬጢን ልጆች እጅ ከነሣ በኋላ፦ «ሬሣዬን ከፊቴ አርቄ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፤ ለዓር ልጅ ለኤፍሮንም ስለ እኔ ንገሩት፤ በእርሻው ዳርቻ ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን ይስጠኝ፤ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን በሚገባ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፤ ከእርሱም እገዛለሁ፤» አላቸው ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ስለነበር፦ «አይደለም፥ ጌታዬ ቀርበህ ስማኝ፤ እርሻውን በውስጡም ያለውን ዋሻውን ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሣህን ቅበር።» አለው። ኤፍሮን ለጊዜው አልቀበልም ብሎ ቢያስቸግረውም፥ አብርሃም፦ አራት መቶ ምዝምዝ ብር መዝኖ ሰጥቶታል ርስት ሆኖ ስለጸለትም ሣራን በዚያ ቀብሯል። (ይህች ስፍራ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት)። ዘፍ ፳፪፥፩-፳።

፪፥፪፦ ጌታ ዮሴፍ፤
          ዮሴፍ፦ የያዕቆብ አሥራ አንደኛ ልጅ የራሔል የበኲር ልጅ ነው። ዘፍ ፴፥፳፪። ከጠባዩ መልካምነትና ከዝናው፥ ከፈጸመውም ትልቅ ሥራ የተነሣ ከያዕቆብ ልጆች ሁሉ የተከበረ ሆነ ያዕቆብም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወድደው ነበር እርሱ በሽምግልናው የወለደው ስለሆነ፥ በብዙ ኅብር ያጌጠች ቀሚስ አለበሰው። በዚህም ምክንያት ወንድሞቹ ጠሉት። በሰላም ይናገሩት ዘንድ አልቻሉም። ዮሴፍ ህልም የማየት ጸጋም ስለነበረው፦ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክ ብትም ሲሰግዱለት ማየቱን በወንድሞቹ ፊት በመናገሩ አባቱ ገሠጸው። ቀጥሎም፦ «ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድን ነው? በኑ እኔና እናህ፥ ወንድሞችህም ጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?» አለው። ወንድሞቹም ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ ይጠብቀው ነበር። በመጨረሻም ዮሴፍን ወንድሞቹ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች ሸጡት። የዮሴፍንም ልብ ስ በደም ነክረው ከሜዳ እንዳገኙት አድርገው ክፉ አውሬም እንደበላው አስመስለው ለአባታቸው ሰጡት። ያዕቆብም፦ «ይህ የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍን ቦጫጭቆታል፤» እያለ ብዙ ቀን አለቀሰ። «ወደ ልጄ ወደ መቃብር እያዘንሁ እወርዳለሁ፤» ብሎ ሐዘንን እንቢ አለ። ዘፍ ፴፮፥፩
፪፤፪፥፩፦ ዮሴፍና በረከቱ፤
          ዮሴፍ ወደ ግብፅ እንደወረደ፦ በፈርዖን ቤተ መንግሥት፥ በመጋቢዎች ላይ አለቃ የሆነ ጲጥፋራ የተባለ ሰው ገዛው። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ስለነበር ሥራው ሁሉ ተከናወነለት። ጌታውም እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንዳለ፥ ሥራውንም ሁሉ አይቶ በቤቱ ላይ ሾመው። ዮሴፍ በሁሉ በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ። እግዚአብሔርም ስለ ዮሴፍ ቤቱን ባረከው። በረከት በቤትም በውጪም ተትረፈረፈ። ከዚህ የተነሣ ጌታው ሀብቱን ሁሉ እንዲያስተዳድር ለዮሴፍ አስረከበው።
፪፤፪፥፪፦ ዮሴፍና ፈተናው፤
          ዮሴፍ መልኩ ያማረ፥ ፊቱም እጅግ የተዋበ ነበር። ከዚህ በኋላ የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት። ባለቤቷ በሌለበት ጠብቃ፦ «ከእኔ ጋር ተኛ፤» አለችው፥ እርሱ ግን ለጌታውም ለእግዚአብሔርም ታማኝ ሆኖ እን አለ። «እንዴት ይህን ክፉ ነር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃአት እሠራለሁ?» አለ። በየዕለቱም ትነንዘው ነበር። ይባስ ብላ ልብሱን ይዛ፦ «ከእኔ ጋር ተኛ፤» አለችው። እርሱም ልብሱን ትቶላት ሸሸ። እርሷም በብስጭት፦ «ሰው አለመኖሩን አይቶ ሊደፍረኝ ነበር፥ ነገር ግን ድምፄን ከፍ አድርጌ ስለጮኽኩኝ ልብሱን ትቶብኝ ሸሸ፤» ብላ ለባለቤቷ ከሰሰችው። በዚህም ምክንያት ወደ እስር ቤት ተወረወረ። እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ። ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው። የሚያደርገውንም ሁሉ በእጁ ያቀናለት ነበር። ዘፍ ፴፱፥፩-፳፫።
፪፤፪፥፫፦ ዮሴፍና ጥበቡ፤
          ዮሴፍ የእስረኞችን ህልም ይፈታላቸው ነበር። ዮሴፍ እንደተረጐመላቸው፦ የፈርዖን ቤተ መንግሥት የጠጅ አሳላፊች አለቃ፥ በሦስት ቀን ውስጥ ወደ ሹመቱ ተመለሰ። የእንጀራ አሳላፊዎች አለቃ ግን በሦስት ቀን ውስ ሰቅለው ገደሉት። ዮሴፍ፦ ወደ ሹመቱ የሚመለሰውን ሰው። «ነገር ግን በጎ በተደረገልህ ጊዜ አበኝ፥ በግፍ ታስሬያለሁና ለፈርዖን ነግረህ አስፈታኝ፤» ብሎት ነበር እርሱ ግን ረሳው። ዘፍ ፵፥፩-፳፫። ሁለት ዓመት ሉ አላስታወሰውም ነበር።
          ከሁለት ዓመት በኋላ ፈርዖን ህልም አይቶ መንፈሱ ታወከችበት። የግብፅ ጠቢባንም ሊተረጉሙለት አልቻሉም። በዚህን ጊዜ የጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍ አስቦ ለፈርዖን ነገረው። ፈርዖንም ዮሴፍን ከግዞት ቤት አውጥቶ፦ «ሕልሜን ተርጉምልኝ፤» አለው። ዮሴፍም፦ «እግዚአብሔር ከገለጸለት ሰው በቀር መተርጐም የሚችል የለም፤» ካለው በኋላ ተረጐመለት። በመጨረሻም፦ ፈርዖን፦ « እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና ከአንተ ይልቅ ብልህና አዋቂ ሰው የለም። አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፤ ህዝቡም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔም ከዙፋኔ በቀር ከአንተ የምበልጥበት የለም።» ብሎ በሁሉ ላይ ሾመው። የዮሴፍ ዕድሜ ገና ሠላሳ ነበር። በእናት በአባቱ ቤት አሥራ ሰባት ዓመት ፥ በጲጥፋራ ቤት አሥር ዓመት ፥ በእሥር ቤት እንደ መጽሐፈ ኲፋሌ ሦስት ዓመት በጠቅላላው ሠላሳ ይሆናል። ዘፍ ፵፩፥፩-፵፮።
፪፡፪፥፬፦ ዮሴፍ ግብፃውያንን እንደታደጋቸው፤
          ዮሴፍ የፈርዖንን ህልም በፈታለት መሠረት ፥ የሰባቱ ዓመት የጥጋብ ዘመን ሲጀምር ፦ የግብፅ አገር ያስገኘችውን እህል ሁሉ ነዶውን እያስከመረ ፥ የሚነቅዘውን እያስፈጨ ፥ ጡብ እያስጣለ ፥ የማይነቅዘውን በሪቅ ፥በጎተራ አኖረ። የግብፅ ሰዎች መስፈር መቊጠር እስኪሳናቸው ድረስ እህሉን እንደ ባሕር አሸዋ ብዙ አድርጎ ሰበሰበ። በዚህን ጊዜ ሁለት ልጆች ተወለዱለት። የበኲር ልጁን ምናሴ አለው። መርስኤ ሐዘን ማለት ነው። ሁለተኛውንም ኤፍሬም አለው። ዕበይ (ክብር) ፍሬ ማለት ነው።
          የጥጋቡ ዘመን ሲያልፍ ሰባቱ የረሃብ ዘመን ጀመረ። በግብፅ ሀገር ሁሉ ረሃቡ ታዘዘ። ሕዝቡም እህል እንዲሰጣቸው ንጉሣቸውን ቢጠይቁት ወደ ዮሴፍ አሰናበታቸው። ዮሴፍም እየሰፈረ ይሸጥላቸው ነበር። የግብፅ ሀገር ሰዎች ሁሉ እህል ሊሸምቱ ዮሴፍ ወደአለበት ይመጡ ነበር። ዘፍ ፵፮፥፵፯-፶፯።
፪፡፪፥፭፦ ዮሴፍና ይቅርታው፤
          ሽማግሌ ከመንደር ዳር ፥ ከድንበር መቀመጥ ልማድ ነውና ፥ ያዕቆብ ከዚያ ተቀምጦ ሳለ፦ ነጋድያን ከግብፅ እህል ሸምተው ሲመለሱ  ጠይቆ ስለተረዳ ልጆቹን ወደዚያ ሰደዳቸው። እነርሱም በከነዓን ረሃብ ጸንቶ ነበርና ፥ ነገ ፥ ተነገ ወዲያ ሳይሉ ወዲያው ተነሡ። ከዚያም ሲደርሱ የሸጡት ወንድማቸው መሆኑን ሳያውቁ ለዮሴፍ ሰገዱለት። በዚህም የዮሴፍ ሕልም ተፈታ ፥ የእግዚአብሔርም ዓላማ ተፈጸመ። ዮሴፍም እንደማያውቃቸው ሆኖ ፦ « ሰላዮች ናችሁ፤» አላቸው። እነርሱም እውነቱን ነገሩት። አውቆ በአስተርጓሚ ያናግራቸው ነበር። ነገራችሁ እውነት የሚሆነው « ቢኒያም» ያላችሁትን ወንድማችሁን ስታመጡት ነው ፥ እስከዚያው ብሎ ስምዖንን አቆይቶ ፥ ለእነርሱ እህል በየስልቻቸው ሞልቶ የከፈሉትንም ገንዘብ በምሥጢር በውስጥ አድርጐ ሰደዳቸው። የሆነውንም ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት። ቢኒያምን ይዘው በተመለሱ ጊዜ፦ ዮሴፍ የእናቱን ልጅ በማየቱ ወደ እልፍኙ ገብቶ አለቀሰ። ተመልሶም፦ መልካም ግብዣ አደረገላቸው። በመጨረሻም ራሱን ገለጠላቸው። «አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ ፥ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። . . . እግዚአብሔርም  በምድር ላይ እንድትድኑና እንድትተርፉ እመግባችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ፤ » አላቸው። ሁሉንም ሳማቸው አንገታቸውንም አቅፎ አለቀሰ። ዘፍ ፵፫፤፵፬፤፵፭። ከዚህ ሁሉ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ፥ የዮሴፍን መገኘት ነግረው ፥ አባታቸውን ያዕቆብንና ቤተሰቡን ይዘው ወደ ግብፅ ተመለሱ። የልጆቹ ሚስቶች ሳይቆጠሩ ወደ ሰባ ነበሩ ። ኑሮአቸውንም በዚያ አደረጉ። ዘፍ ፵፮ ፥ ፩-፴፬።
፪፡፪፥፮፦ የያዕቆብ ሞት፤
          ያዕቆብ፦ ልጆቹን ሁሉ ጠርቶ መረቃቸው ፥ በኋለኛውም ዘመን ስለሚገጥማቸው ነገር ሁሉ ነገራቸው። ከዚያ በፊት ሁለቱን የዮሴፍን ልጆች እጁን አመሳቅሎ ባርኳቸው ነበር። ይህም በአዲስ ኪዳን ዘመን በመስቀል ለመባረካችን ምሳሌ ነው። ዘፍ ፵፰፥፵፬። አብርሃምና ሣራ ፥ ይስሐቅና ርብቃ በተቀበሩበት ስፍራም እንዲቀብሩት ካዘዛቸው በኋላ ሞተ። የልቅሶውም ወራት  ከተፈጸመ በኋላ እንዳዘዛቸው አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖንን አስፈቅዶ ከወንድሞቹ ጋር አባቱን ቀብሮ ተመለሰ። ይህም ሰው ሲሞትብን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደን ለመቅበራችን ምሳሌ ነው። ዘፍ ፵፱ ፤፶።
፪፡፪፥፯፦ ዮሴፍ ወንድሞቹን ማረጋጋቱ፤
          ከቀብር በኋላ ፥ የዮሴፍ ወንድሞች ፦ « ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል ፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራትን ይመልስብን ይሆናል ፤» አሉ ። መልእክተኛም ልከው ፦ «አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞናል፦ ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ እባክህን የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል ፥ እነርሱ ከፍተውብሃልና ፤ አሁንም እባክህን የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።» አሉት። ዮሴፍ ይህን ሰምቶ አለቀሰ። ወንድሞቹም፦ እግዚአብሔር በጌትነት ጸጋ እንዳከበረው አምነው ፦ በፊቱ ከሰገዱለት በኋላ ፦ «እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን፤» አሉት። ዮሴፍም ፦ «እኔ በእግዚአብሔር ፈንታ ነኝን? እናንተ ክፉ ነገር አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። አሁንም አትፍሩ። እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ። » አላቸው። አጽናናቸውም ፥ ደሰ አሰኛቸውም። እነርሱም፦ የግብፅን ምድር ከረገጡበት ጊዜ ጀምሮ የሚያነጋግሩት «ጌታችን ሆይ፤» እያሉ ነበር። ዘፍ ፵፪ ፥፲ ። ይሁዳ፦ ወደ እርሱ ቀርቦ ፦ «ጌታዬ ሆይ ፥ እኔ ባሪያህ በጌታዬ ጆሮ አንዲት ቃልን እንድናገር  እለምንሃለሁ፤ እኔንም ባሪያህን አትቆጣኝ ፤ አንተ እንደ ፈርዖን ነህና።» እያለ የተማጸነበት ጊዜ ነበር። ዘፍ ፵፬ ፥፲፰። (የዮሴፍን ታሪክ በመጠኑ ዘርዘር ያደረግነው ፥ ለወጣቶችም ሆነ ለሌሎችም አርአያና ምሳሌ ስለሆነ ነው።)

5 comments:

 1. ቃለ ሕይዎት ያሰማልን በውነት ዐገልገሎተዎን ይባክለዎ

  ReplyDelete
 2. KHY Egziabhere Yageliglot zemenown yabzalot Teninetin, Edmen selamin fekeirin yesetewo
  Cher yaseman

  ReplyDelete
 3. I have never seen it before.we found 2 blogs "+1" now.
  Kesis bewunet nefisen alemlemewatal.I was copying every thing on my notebook.
  YIBEL KESIS!!

  ReplyDelete
 4. እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና
  እግዚአብሔር ለሁላችንም እንዲህ ዓይነት የይቅርታ ልብ ይስጠን
  ለዚህኮ ነው ጊዮርጊስን
  ኦ ፍጡነ ረድኤት ለጽኑዕ ወለድኩም ወለነፍሰ ኩሉ ቃውም
  ጊዮርጊስ የዋህ እንበለ መስፈርት ወዓቅም ከመ እግዝእትከ ቡርክት ማርያም
  እስመ ርህሩሃ ልብ አንተ እምበቀል ወቂም፣ የምንለው፣
  ቅዱሳን ከበቀል ከቂም የራቁ ናቸውና፣
  አምላከ ቅዱሳን ይዕቀብከ

  ReplyDelete
 5. ቃለ ሕይዎት ያሰማልን በውነት ዐገልገሎተዎን ይባክለዎ

  ReplyDelete